Friday, November 15, 2013

ናይጄሪያ Vs ከኢትዮጵያ፡ ከዋሊያዎቹ ምን እንጠብቃለን? ከአጎናፍር ገዛኸኝ


ጊዜው እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር 1950ዎቹ ነው። የሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ጦርነት የተፋፋመበት። በጦርነቱም የድል ጮራ ወደ ሰሜናዊያኑ ወገን መውጣት በመጀመሯ ደቡቦቹ የሽንፈት ጽዋን ሊጎነጩ ተገደዱ። ዓለምም ትኩረቱን ወደ ተሸናፊዋ ሀገር አዞረና የእርዳታ እጁን ሊዘረጋላት ተነሳሳ። በዚህ ጊዜ አንድ ትልቅ ዜና ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ለሩቅ ምሥራቋ ደቡበ ኮሪያ ደረሳት «ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለእናንተ ሊወግኑ ልባቸው ተነሳስቷል» የሚል። እናም ኢትዮጵያውያኑ ለደቡብ ኮሪያውያን ሲሉ በተፋፋመው ጦርነት ገቡ።
ኮሪያውያኑም ቀድመው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የኢትዮጵያውያንን እርዳታ ስላገኙ በደስታ ጮቤ ረገጡ። እነርሱ እንደገመቱትም የጠላቶቻቸው ጡንቻ በኢትዮጵያውያን እርዳታ ተመክቶ የድል ጀምበር አቅጣጫዋን ቀይራ ከደቡባውያኑ ጎን ወጣች። ይህ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ድል ኮሪያውያን ሲያስታውሱት ይኖራሉ። ለልጅ ልጆቻቸውም በቃልና በጽሑፍ እየተረኩላቸው እዚህ ደርሰዋል።
Ethiopia national team
ወደ ኮሪያ የዘመተው ቃኘው በመባል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ጦርም ሀገሩ የሰጠችውን አደራ በድል ተወጣ። ሀገሩን አክብሮና አስከብሮ በድል አድራጊነት ተመለሰ።
በጦር ሜዳ እንደሚታወቀው መሞት፣ መግደልና መማረክ የተለመደና የታወቀ ነው።ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ የሚያስፈራውና የተሸናፊውን አንገት የሚያስደፋው ግን በጠላት እጅ መማረክ ነው። መማረክ የተለመደ ቢሆንም በዓለም ላይ ከተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ በጦር ግንባር ተሰልፎ ያልተማረከ የጦር ሠራዊት (አርበኛ) ወደ ኮሪያ የዘመተው የቃኘው ጦር ብቻ ነው።
እነሆ ይህ ትልቅ ገድል ከተፈጸመ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ሌላ ሰላማዊ ዘማች ጦር ሀገራችን ወደ ናይጀሪያ ካላባር ልካለች። ዋልያዎቹ ለሌላ ገድል በናይጄሪያ ተገኝተዋል። ከንስሮቹ ጋር የሚገጥመውን ይህን ዘማች አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመሩታል።
የእዚህ ሰላማዊ ጦርነት የመጀመሪያ ክፍልም ከአንድ ወር በፊት አንድ ለእናቱ ሆኖ በኖረው አዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል። በጦርነቱም የድል አድራጊነት ዘውዱን መድፋት የቻለው እንግዳው ቡድን መሆኑ አይዘነጋም። ይህንን ሽንፈት ለመቀልበስና ብሎም ወደ ላቲን አሜሪካዊቷ የቡና እና የእግር ኳስ አገር ወደ ሆነችው ብራዚል ለማቅናት ነው የአቶ ሰውነት ቢሻው ጦር የሕዝብ አደራ ተቀብሎ የተጓዘው።
ነገ ኅዳር ሰባት ቀን በናይጄሪያዋ ካላባር ከተማ በሚካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡድኗን የምትልከው አደራዎችን ሰጥታ ነው።
አደራ አምስት
እናንት ኩሩና ታሪክ ሰሪ ልጆቼ ሆይ እነርሱም እንደ እናንተው 11 ሆነው ነው ሜዳ የሚገቡት። ግጥሚያችሁ መሳ ለመሳ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም። ስለዚህ በዚህ ሰላማዊ ትግል ሀገራችሁ በተደጋጋሚ ጊዜ ያስመዘገበችውን የጦር ሜዳ ውሎ እያስታወሳችሁ ላለመሸነፍ ታገሉ፤ያኔ ድሉ የእናንተ ይሆናል። ናይጄሪያን አሸንፋችሁ ወደ ብራዚል ብታቀኑ ሀገራችሁ ብቻ ሳትሆን የክፍለ አህጉሩም (ምሥራቅ አፍሪካ) የኩራት ምንጭ ትሆናላችሁ። ለእዚህ ድል ታገሉ !!!
አደራ አራት
ናይጄሪያን አሸንፋችሁ ወደ ብራዚል ማቅናት ባትችሉ እንኳ በሜዳውና በደጋፊው ፊት የሚጫወተውን የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊውን ቡድን አሸንፉት። ከሰው ሜዳ ባገባ በሚለው የፊፋ ሕግ ከዓለም ዋንጫ ብትቀሩም ናይጄሪያን በማሸነፋችሁ ደማቅ ታሪክ ትፅፋላችሁ፤ ሀገራችሁም ይህንን ታሪካችሁን በወርቅ ሙዳይ ታስቀምጥላችኋለች። ለእዚህም ታገሉ!!!
አደራ ሦስት
በተደጋጋሚ ጊዜ በዓለምና አፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች የተሳተፈውን ቡድን ለማሸነፍ ቢሳናችሁ ደግሞ በሜዳችሁ ያጣችሁትን አንድ ነጥብ ከካላባር ይዛችሁ ተመለሱ። በዚህም እናታችሁ ደስታዋ ልክ የለውም። የእናንተን እግር ተክተው ነገ ለሀገራቸው የሚጫወቱ ታዳጊዎችም እናንተን በማየት መነሳሳት ይጀምራሉ። ይህ ገድላችሁም ቢሆን ታሪካችሁን በወርቅ ሙዳይ ከማስቀመጥ አያግደውም፤ምክንያቱም እናንተ ማለት ይህንን ቀን እንድናይ ያደረጋችሁን ታሪክ ሰሪ ልጆቻችን ናችሁና። ስለዚህ ይህንን ዕድል ላለማጣት ታገሉ!!!
አደራ ሁለት
የመጀመሪያውን ጨዋታ በሰው ሜዳ ተጫውቶ በለስ የቀናው ቡድን የመልሱን ጨዋታ በሜዳው ሲያካሂድ መረቡን ላለማስደፈር ይጫወታል። እናንተም ከናይጄሪያ አቻችሁ ይህ ሊጠብቃችሁ ይችላል። እናንተ የሰው ምሽግ ልትደፍሩ በሙሉ ኃይላችሁ ስታጠቁ በመልሶ ማጥቃት በእናንተ መረብ ላይ ተባራሪ ኳስ ሊያርፍ ወይም ልትሸነፉ ትችላለችሁ። ግድ የለም ተሸነፉ። ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት በመጀመሪያው ጨዋታ የዳኛና የእናንተው ጥቃቅን ስህተቶች እንድትሸነፉ አድርጓችኋል። አሁንም የመልሱን ጨዋታ በሰው ሜዳ ስለምታደርጉ ባለሜዳው ቡድን የሜዳ ተጠቃሚነቱን ሊገለገልበት እንደሚችል አያጠራጥርም። ወታደሮቹም (ተጫዋቾቹም) ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው፤የወቅቱ የአህጉሪቱ የበላይ ቡድን ነው።
ደጋፊዎቻቸውም ቢሆኑ የዋዛ አይደሉም። አዲስ አበባ ላይ እንዳየናቸው ቁጥራቸው የአንድ እድር አባላት እንኳ ሳይሞላ (ሁለት መቶ ብቻ ነበሩ) ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በከበሯቸው ታጅበው እንዴት ቡድናቸውን ሲያበረታቱ እንደነበር አይተናል። ይህ ደጋፊ በሀገሩ ላይ ሲሆን ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።
እስከ አሁን እንደተስተዋለው ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞችም ቢሆኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳርፉት አሉታዊ ተጽዕኖ ሲታሰብ የነገው ጨዋታም ፍርደ ገምድልነት የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እነዚህና የራሳችሁ ድክመት እንዳሉ ሆነው የተጋጣሚዎቻችሁም ጥንካሬ ተጨምሮበት ልትሸነፉ ትችላላችሁ። ምንም አይደል ተሸነፉ ፤መሸነፍ ራሱ የእግር ኳስ አንዱ አካል ነውና ለነገው አስቡ። ለእዚህም ቢሆን ታገሉ!!!
አደራ አንድ
ይህንን ስናገር ምናልባት ጨለምተኛ ልትሉኝ ትችላላችሁ፤ጨለምተኝነት ሳይሆን ቅድመ ዝግጅት መሆኑን ተረዱልኝ። ይህ አደራ ከባዱና ዋናው ነው። ከላይ የተገለጹት ውጤቶች ቢመዘገቡም ሀገራችሁ ከመደሰት ውጪ አትከፋም። ምክንያቱም የተጓዛችሁበት መንገድ በራሱ በቂ እንደሆነ ትረዳላችኋለች፤የሚቀጥለውን አደራ ግን አብዝታ ታሳስባችኋለች።
ይህ አደራ ምን መሰላችሁ? ኢትዮጵያውያን የጦር ሜዳ ውሎ አልሸነፍ ባይነታቸውን ወደ እግር ኳሱም ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ለእዚህም ነው እንድታሸንፉ የምንመክራችሁ። ነገር ግን ይህ የቆየ ደካማ ውጤታችንን በአንድ ጀምበር ለመቀየር እናንተ ላይ አላስፈላጊ ጫና መጣል አትፈልግም። እስካሁን ለደረሳችሁበት መንገድም ደስተኛ ነች። ነገም እኮ ሌላ የዓለምና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ይጠብቁናል። ሥራችንም ቢሆን ቀጣይነት ያለው እንጂ፣ለአንድ ቀን ወይም ለአንድ ተልዕኮ ብቻ የታሰበ አይደለም።
ስለዚህ ሀገራችሁ የምትፈልገው ውጤት ግን መረባችሁ በብዙ ኳሶች እንዳይጎበኝ ነው።ይህንን አደራ ነው ሀገራችሁ አጥብቃ የምትሰጣችሁ። በሰፊ የግብ ልዩነት መሸነፍ በጦር ሜዳ ከመማረክ በምንም ተለይቶ አይታወቅም፤ ምክንያቱም ሁለቱም የተሸናፊውን ወይም የተማራኪውን ወገን አንገት ያስደፋሉና።
አውቃለሁ እናንተ በሜዳችሁ ሁለት ለአንድ ስትሸነፉ ታሪካዊ ተቀናቃኛችን ግብጽ ኩማሲ ላይ ለስድስት ጊዜያት ያህል መረቧን በጋናውያን አጥቂዎች አስጎብኝታለች። ይህ ውጤት የግብጻውያንን ሞራል ይነካ አይነካ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን አናውቅም፤ እኛ ላይ ተመዝግቦ ቢሆን እንደሚያሸማቅቀን ሳይታለም የተፈታ ነው። ለእዚህ ማሳያው ባለፈው ጥር ወር በአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ጨዋታችሁን ከቡርኪናፋሶ ጋር አድርጋችሁ እነርሱ አስር እናንተ አስራ አንድ ሆናችሁ ብትጫወቱም እነርሱ የእናንተን መረብ ለአራት ጊዜያት የተመላለሱበት ሁኔታ ነው።ይህ ያሳደረብን ትካዜ የሚዘነጋ አይደለም። በቡርኪናፋሶው ዓይነትም ይሁን ከዚህ በትንሹ ባነሰ የግብ ልዩነት ብንሸነፍ ውጤቱ ያስተክዘን እንደሆነ እንጂ እስካሁን በተጓዛችሁበት ርቀት እንድንጽናና አያደርገንም።
ስለዚህ ይህ ውጤት እንዳይመዘገብ አደራ።ትግላችሁ ለእዚህ የጠነከረ ይሁን።ታገሉ!!!
መልካም ዕድል ለታሪክ ሰሪ ልጆቻችን!!!


zehabesha

No comments:

Post a Comment