Monday, July 7, 2014

ስለምንደግፈው ወይም ስለምንቃወመው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት የራሳችን አእምሮ ምን ያህል ፍትሀዊ ነው? የሐሳብ ልዩነት እርስ በእርስ ለመተናነፅ እንጂ ለቂመኝነትና በቀለኝነት አይዳርገን!



ብዙ ጊዜ የምንደግፋቸውና የምንቃወማቸው ነገሮች ምክነያታዊና ከማስተዋል ሳይሆን በደረቅ ስሜተኝነት ሲሆን ለምንደግፈው ከስኬት ይልቅ ውድቀት ለምንቃወመው ደግሞ ከምክነት ይልቅ ብርታት ይሆናል፡፡ የሰው ልጆች በስሜተኝነት መደገፍና መቃወም በሁሉም ማህበረሰብ የሚታይ ሲሆን በአንዳንድ ማህበረሰብ ግን ገዝፎ ይታያል፡፡ በስሜተኝነት የመደገፍና የመቃወም ባሕሪ ግን በዘር የሚተላለፍ ተፈጥሮአዊ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይልቁንም ለዚህ ባሕሪያችን ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብዬ የምገምተው ከተወለድን በኋላ የሚገጥሙን የሕይወት ልምዶቻችንና ከባቢያዊ ተፅእኖዎች ናቸው፡፡ ያደግንበት ማሕበረሰብ አስተሳሰብ፣ በግላችን የገጠሙን የሕይወት ተሞክሮዎች፣ የኑሮ አለመረጋጋትና አልፎም ተስፋ የቆረጠ አኗኗርና የመሳሰሉት ይመስለኛል፡፡ እንዚህ ስሜታዊ የሆኑ አመለካከቶቻችን ከሚንጸባረቁባቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የፖለቲካ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት ነው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት ስመጣ ከብዙ አገሮች እምብዛም የተለየ ነው ብዬ ባላምንም በውጭ በሚኖሩ (ዲያስፖራ) ኢትዮጵያውያንና ተማርን በሚሉ ዜጎች ያለው ምክነያታዊ ያልሆነው ደጋፊነት ወይም ተቃዋሚነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ብዙ ሕዝብ የከፋ ነው፡፡ ይህ ልዩነት በተለይ አሁን አሁን በአገር አመለካከትም ላይ በውጭ በሚኖሩትና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩት መካከል ክፍተት እየፈጠረ መጥቷል፡፡  በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ስሜታዊነት ከፖለትካ አመለካከት ብቻም ሳይሆን ፍጹም የሕሊና መታመንን በሚጠይቀው ሀይማኖታዊ ጉዳዮችም ላይ በአገሩ ከሚኖረው የከፋ ሳይሆን አልቀረም፡፡  በዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ የአገርና ሕዝብን ትክክለኛ ጥቅሞችንና ደህንነቶችን ሳይቀር ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ለራሳቸው ስሜታዊ ተቃዋሚነት ወይም ደጋፊነት መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ይታያል፡፡ ቀጥሎ ተማርን በሚሉ ብዙ ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኛ ነን በሚሉ ሰዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ ኃላፊነትን የዘነጋ አገርንና ሕዝብን ያላማከለ ስሜት ወለደ አልፎም ሴራዊ የሆኑ አካሂዶች ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም የፖልቲካ ፓርት መሪዎችና ጋዜጠኞች ብዙ ሕዝብም ለማሳተፍ ከሚያስችላቸው ስሜታቸውን የማጋራት ዕድል ጋር በተያያዘ የሚያደርሱት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

ይሄው ተጽኗቸው በሚያመጣው ስጋት ታዲያ በስልጣን ላይ ያለ አካል የእንዚህን አካላት አመለካከትና አካሄድ የሚመለከተው በአትኩሮት ነው፡፡ ሥጋቱ ሲጨምርም እንዚህን አካላት እንቅስቃሴያቸውን ያስጠነቅቃል ሰበብ ፈጥሮም ያስራል ይቀጣል፡፡ ይህ የሁሉም አገራት ሂደት ነው፡፡ ሴሜታዊ እርምጃው ግን ስልጣን ላይ ያለው አካልም ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እርምጃዎች ሌሎች በስሜት እየተነዱ አልፎ አልፎም በልዩ ሴራዊ በሆነ አካሄድ የሚያጠፉን የፖለቲካ መሪዎችንም ሆነ ጋዜጠኞችን  ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ከማድረግ ይልቅ የቅጣትና የበቀለኝነት እርምጃ ሲወሰድ ይታያል፡፡ እንዲህ ያለው እርምጃ ደግሞ በስሜትና በልዩ ሴራ የተጠነሰሱ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ልዩ ግዝፈት እየሰጣቸው ተራ የሆኑ ሰዎችን ሳይቀር ወደ ትልቅ ታዋቂነት፣ ጥቃቅን አለመገባባቶች ወደ ትልቅ አገራዊና አህጉራዊ ብሎም አለም ዓቀፋዊ ጠቦች ያደርሳቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችንና አንዳንደ የፖለቲካ አመለካከት የላቸውን ሰዎች አስሯል በሚል  በሰፊው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳይቀር ይወቀሳል፡፡ የታሰሩት ጋዜጠኞችም ሆኑ ፖለቲከኞች ግን ለእስር ያበቃቸውን ነገር በውል የሚያውቁት አሳሪዎቹና ታሳሪዎቹ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግስት በሕዝብና በአገር ደህንነት ላይ ችግር ፈጥረዋል ባይ ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ደግሞ አሁን ያለው መንግስት የፕሬስ ነጻነትና ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካን ስለማይቀበል በነጻ አስተሳሰብ አራማጆች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው ባዮች ናቸው፡፡ ችግሩ ግን ሁለቱም አካላት (አሳሪውም ታሳሪውም) ጋር ከስሜተኝነት የመጣ ድርጊቶች ይነበባሉ ባይ ነኝ፡፡ በመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ባለስልጣኖች በእልህና በቀጭነት መንፈስ የሚወስዱት እርምጃ ብዙ የችግሩ ግዝፈት ምክነያት እንደሆነም ይሰማኛል፡፡ ዜጎችን በአስተማሪነትና በአስተዋይነት ዘለቄታ ያለውን ኃላፊነት በመስጠት በስሜት ብቻ ተቃዋሚ የነበሩትን ለሕዝብና አገር ጠቀሜታ ያለውን የበኩላቸውን ድርሻ ከሚቃወሙት መንግስት ጎን ሳይቀር በመሰለፍ ሊያበረክቱ በቻሉ ነበር፡፡  በእኔ እምነት ብልህ መሪ ለሚቃወመው አካል ኃላፊነት ሰጥቶ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ተቃውሞን ወደ ደጋፊነት ሊዘውር የሚችል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እርግጥ ይህ የሚሆንበት ደረጃ አለው፡፡ በተቃዋሚነት ወንጀል ጭምር የሰሩ ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆኑና ነጻ ይሁኑ ማለት ፍትሀዊ አይደለምና፡፡ ገና ለገና ግን ይሄ ችግር ይፈጥርብኛል በሚል ስጋት የሚቃወመንን ስልጣንና ጉልበት ስላለን ብቻ ማሰርና ማስወገድ ስህተት ነው፡፡ ይልቁንም ሌላ ግዙፍ ጫጫታ መፍጠር ነው፡፡ ሌላ አገርንና ሕዝብንም የሚያውክ ግዙፍ አለመገባባት ሲብስም ወደ እርስበርስ ጦርነት የሚያመራ ነው፡፡

ወደ ታሰሩ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጉዳይ አትኩሮቴን ላድርግና፤ በእኔ እምነት መንግስት አሰራቸው የተባሉት ጋዜጠኞችም ሆኑ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደተባለው ልዩ ወንጀል እውንም ሰርተው ካልሆነ ለሌላ የበለጠ ራሱ መንግስት ሊጠቀምበት የሚችልበት ሚና ተሳታፊ ሊያደርጋቸው የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነበር፡፡ ልዩ ወንጀልም ሠርተዋል ከተባለ የሠሩት ወንጀል ካለማወቅና፣ አንዳንዴም ከስሜተኝነት የተነሳ ከሆነ አሁንም ስሜተኝነታቸውን እንዲያስተውሉትና አስተማሪ በሆነ እርምት ሀላፊነትን በማሸከም ምህረት ቢያደርግ የመልካም አስተዳደር ልዩ መገለጫ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም ከስሜተኝነትና ከአለማወቅ በዘለለ በልዩ ሴራ ወንጀል ለፈጸሙ አካላት ይህ ምህረት ተገቢ ነው ብዬ አላንም፡፡ ምክነያቱም በልዩ ሴራ የተሰማራ አካል መቼም ቢሆን የተለከፈበትን ሴራውን ለመቀጠል ይችላልና ነው፡፡ ከነዚህ ልዩ ሴራ ከሚያራምዱት ውጭ ግን በአለማወቅና በስሜተኝነት የመጡ ጥፋቶችን ይቅር ማለት ለአጥፊዎቹ አስተማሪ በመሆን ለሌላ በቀል አዘል እልኸኝነት እንዳይነሳሱ ከማድረጉም በላይ ፍትሀዊነትንም ለሕዝብ በማሳየት ሌላ ጊዜ አጥፊዎች ሲታሰሩና ሲቀጡ በጭፍኑ ከሕዝብና ከሌሎች ያገባናል ከሚሉ ሰዎች ወቀሳን ጫጫታን ለማስወገድ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ካልሆነ ግን ይቅርታ የማይገባውን የተረጋገጠውንም ወንጀለኛ መንግስት ሲቀጣ ይህ የሆነው ወንጀለኛ ሆኖ ሳይሆን መንግስት ኢ-ፍትሃዊ ስለሆነ ነው የሚሉ ጫጫታ ፈጣሪዎችን ማብዛት ይመስለኛል፡፡

በእንዲህ ያለ ግርግር ወንጀለኞች ከሌሎች አካላት እንደ ልዩ የፍትህ ወይም የነጻነት ታጋይ ተቆጥረው ሊሸለሙ ሊወደሱ ይችላሉ፡፡ ሸላሚዎቹ ደግሞ ወይ በውል ውስጡን የማይረዱ ስሜትን ብቻ ተከትለው የሚበይኑ ናቸው ወይ ደግሞ ውስጡን በውል የሚያውቁ ግን የወንጀሉ ሁነኛ ደጋፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ የአገርንና ሕዝብን የጠራ ደህንነት ሊጋፋ ይችላል፡፡ ታሳሪዎች ወንጀለኛ ባይሆኑምና እውንም ለሕዝብና ፍትህ በመታገላቸው ታስረው እንኳን ቢሆን እስር ቤት እያሉ መሸለም ጥሩ አካሄድ እንዳልሆነ አስባለሁ፡፡ እንዲህ ያለው ሽልማት ከበጎ ጎኑ ጥፋቱ የበለጠ ይሆናልና፡፡ ሂደቶችንም በእልኸኝነትና ጥላቻ ከፍትሀዊ አመለካከት አስወጥቶ አሳሪዎችን ለበለጠ መጨከን ታሳሪዎችን ለበለጠ እንግልት ሊዳርግ ይችላልና፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን አሳሪንም ታሳሪንም በተግሳጽም ሆነ በማግባባት አሳሪዎች ፍትሀዊ አመለካከታቸው የሚዳብርበትን ታሳሪዎችም ፍትሀዊ በሆነ መልክ ከእስር የሚፈቱበትን ተጽዕኖ መፍጠር ታላቅነት ነው፡፡ በተመሳሳይ በውጭ ኃይሎች የሚደረግ ግፊትና ውግዘት አዘል መግለጫዎችም ብዙ መዘዞች አሏቸው፡፡ በወዳጀነት ከሚሆን ተግሳጽና በማገባባት የሚመጡ መፍትሔዎች ግን ዘላቂም አስተማማኝም ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ብዙ አገራትም ይሁኑ ሌሎች አለም አቀፍ ይመለከተናል የሚሉ አካሎች ደግሞ በአብዛኛው ጉልበተኝነታቸውን የሚያሳዩባቸውን የውግዘትና የማስፈራራት ቃላቶችን አሳሪ ወይም እነሱ አጥፊ ብለው በሚያቧቸው መወርወር በተቃራኒው ታሳሪዎችን ወይም እነሱ መበታቸው ነው ብለው ለሚያሰቧቸው ውዳሴንና አዞህ ባይ ቃላቶችን ባዶ ተሰፋ ይሰጣሉ

ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር በተያያዘ ብዙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ወሕኒ እንዲገቡ መደረጉን ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው በዚህ ወቅት ከወትሮው ለየት ያለና ኢትዮጵያዊነትንና የሕዝቦቿን ባህላዊ እሴት የሚያንጸባርቅ መንግስትንና ታሳሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ለማደራደርና በመጨረሻም የታሰሩ ወገኖችን ከእስር እንዲፈቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ የሽምግልና ቡድን ታይቶ ነበር፡፡ ይህ ቡድን በቀጣይነትም መሰል ችግሮቻችንን በማስወገድ ሁሉም ወገን በመግባባትና ኃላፊነት በተሞላው ሁኔታ ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ በሚሆኑ ጉዳዮች ለመሥራት ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ የዚህ ቡድን ዋነኛው ተዋናይና የትልልቅ ራዕዮች አመንጪ የነበሩትም ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅ ቃል ገብተውልን የነበረውም እንደዛው ነበር፡፡ ሆኖም ይህ በብዙዎቻችን በጥሩ እይታ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አገር በቀል የሽምግልና ቡድን ብዙም በዘላቂነት ልናየው አልቻልንም፡፡ ምክነያቶቹ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከምክነያቶቹ አንዱ ይሆናል ብዬ የማስበው ግን ቡድኑን ከመንግስት ጋር የሚወግን፣ ለግል ጥቅም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ደግሞ በእውንም በቅንነትና በበጎ አሳቢነት ለአገርና ለሕዝብ በአለን ተጽኖ ፈጣሪነታችን እናገልግል ብው የተነሱ ግለሰቦችን ከማሳዘኑና ጥረታቸውንም ዋጋ ቢስ እንደሆነ ከማሳሰቡም በላይ እናቀራርባቸዋለን የሚሉትን ተቃራኒ ቡድኖችን ለማግባባት ትልቅ ዕንቅፋት ነው፡፡

በእኔ አስተሳሰብ የእነፕሮፌሰር ኤፍሬም አገርኛው የሽምግልና ቡድን ከየትኛውም ዲፕሎማሳዊና ሌላ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካል የተሻለ ለዘለቄታውም ተቃራኒ የነበሩ ቡድኖች ወደ አንድ መጥተው በወንድማማችና እህትማማች መንፈስ የሀሳብ ልዩነታቸውን የበለጠ የአገርና የሕዝብ ጉልበት እንዲሆን ለማድረግ ትልቅ አቅም ሊኖረው የሚችል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደነበር እረዳለሁ፡፡ እኔ ፕሮፌሰር ኤፍፌምንና አጋሮቻቸውን ተረድቻቸው የነበረው ፍጹም በሆነ የእኔነት መንፈስ ነው፡፡ በእርግጥም የፕሮፌሰሩ ፍልስፍና እኔ ከማስበው ጋር በጣም የተጣጣመ ነበር፡፡ በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ እንዳደረጉት እሳቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ሌሎች ጣልቃ እንዲገቡ አይፈልጉም፡፡ ከብዙዎቻችን በተሻለ እናደራድር በሚል የሚያመጡትን መዘዝ ጠንቅቀው ያውቁታልና፡፡  በእርግጥም ከእኛ በላይ ለእኛ ሊያስብልን የሚችል የለም፡፡ እኛ ደግሞ ከሌሎች የአለም አገራት በተለየ ሁኔታ ብዙ ጊዜ በዲፕሎማሳዊ ድርድር ሰበብ የተካድንና ለልዩ ሴረኞች ሰለባ የሆንን ሕዝብ ነን፡፡ በተለይ አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያኑ በምንም መልኩ አመኔታ ሊሰጣቸው የሚችሉ አደራዳሪዎች አይደሉም፡፡ ለሌላው ሕዝብ ቅንጣት ደንታ የሌላቸው በዲሞክራሲና ፍትሕ ሥም የአገራትን ሕዝቦች እርስ በእርስ በማፋጀት ኑሮአቸውን በሰው ልጆች ደም የሚገነቡ ናቸውና፡፡ እናስተውል ዛሬ በአረቡ ምድር እያደረጉ ያሉትን፡፡ በተለይም ደግሞ የሰሜን አፍሪካ አገራትን ልብ እንበል፡፡ ሊቢያ ዛሬ ካላት ሠላምና ፍትህ ምዕራባዊያኑ አምባ ገነን ባሏቸው ጋዳፊ ዘመን ፍትሕና ሰላም ነበራት፡፡ ግብፅም፣ ቱኒዚያም እንደዚያው፡፡ ሳዳም ሁሴን ለኢራቅ ዛሬ ካሉት በብዙ እጥፍ በተሻለ ጥሩ መሪ እንደነበሩ እናስተውል፡፡  የሶሪያው አልአሳድ ለሶርያውያን አምባገነን ሆነው አይደለም እስካሁንም አገራቸው ጦርነት ውስጥ ያለችው፡፡ ሌላ ልዩ ማስተዋል በአሁኑ ወቅት የአልአሳድ መንግስት ጉልበት እያገኘና ተቃዋሚዎቹንም እያሸነፈ ለሕዝብም መረጋጋትና ሠላም እያመጣበት ባለበት ሁኔታ የአሜሪካው መሪ ኦባማ ተቃዋሚዎችን ለማጠናከር የ500ሚሊዮን ዶላር ፍቃድ ኮነግረሳቸውን ጠይቀዋል፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ አሜሪካ ራሷ አሸባሪ ባለችውና ዛሬ የኢራቅ ራስምታት የሆነውን አይሲስን ቡድን የአላሳድ መንግስት በሶሪያና ኢራቅ ድንበር በአየር ማጥቃቱን ተከትሎ ነው ኦባማ ኮነግረንሳቸውን ተቃዋሚዎችን ለማጠናከር በሚል የገንዘብ ድጋፍ የጠየቁት፡፡ ጉዳዩ ሶርያ ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ ለማስፈን ሳይሆን በዘላቂ ብጥብጥ ሕዝብን ለእልቂት መዳረግ ነው፡፡ ምዕራባውያኑ የሰው ደም የሚገብሩለት ሰይጣን ግብሩን ቢያቆሙበት ሊያጠፋን ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ አገራቱን የሚመሩት የልዩ ሚስጢራዊ ማሕበረሰብ እምነት ነው፡፡

እንግዲህ እንዲህ ያሉትን ሴረኞች እያመንን ነው ዲፖሎማሲ ዲሞክራሲ ምናምን እያልን ለዘመናት የተጃጃልነው፡፡ የእኛዎቹና አገሪኛዎቹ አደራዳሪዎች ግን ቢያንስ የሕሊና ክስ ስለሚገጠማቸው በአገርና ሕዝብ ላይ አንዳች ሴራ ለመወጠን እድላቸው የጠበበ ነው፡፡ በእርግጥም በወቅቱ በአገርበቀሉ የሽምግልና ቡድን የነበሩት ግለሰቦች ስብስብ ጥሩ ሥምና ስብዕና የነበራቸው እንደነበር እናስታውሳልን፡፡ የቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ከአርባ ዓመት በላይ ኑሯቸው በአሜሪካ ቢሆንም ብዙዎች ኢትዮጵያዊነትን ክደው አሜሪካዊ ለመሆን አለ የተባለ ድንጋይ ሲፈነቅሉ እሳቸው ለዚህ ሁሉ ዘመን ዜግነታቸውን ጠብቀው ከዚያም በላይ በባዕድ አገር ማንነታቸውን በጉልህ ለማሳየት በኢትዮጵያዊ የባህል ልብሳቸው ደምቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊነታቸውን ከምንም በላይ የሚኮሩበት ዜጋ ናቸው፡፡ ሌሎቹም የቡድኑ ስብስቦች እንደዚያው፡፡     

ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለታሰሩ ብቻ እንደ ልዩ የነጻነት ታጋይ ተቆጥረው ሊወደሱ አይገባቸውም፡፡ አሳሪዎችም ተራ በሆነ በግል ቂመኝነት ወይም ሕዝብንና አገርን ታሳቢ ባላደረገ መሠሪነት ዜጎችን ማሰር የለባቸውም፡፡ ብዙ እውነትም መታሰር የነበረባቸውና ፍትሀዊ ፍርድ ሊበየንባቸው የሚገባ ታሳሪዎች በግርግር ሲወደሱና እንደ ነጻነት አርበኛ ተደርገው ሲሸለሙ ጭምር እናያለን፡፡ አሳሪዎችም ብዙ ጊዜ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ዜጎችን እንደሚያስሩ እናያለን፡፡ ከዚህም በላይ አሳሪዎች እንደመሪ ጥፋት እንኳን ቢኖር በትዕግስትና በማስተዋል ጥፋተኞችን ወደ መልካም ስነምግባር በሚላበሱበት ሁኔታ ለማረም ብዙ እድል እያላቸው በተራ ስሜተኝነትና አልፎም በቂመኝነት ታሳሪዎችን በቀለኛ በሚሆኑበት ሁኔታ ሲያስሩና ሲቀጡ እናያለን፡፡ ይህም እንደ ልዩ ባሕል በትውልድ መካከል እየቀጠለ ለዘመናት የአንድ አገር ልጆች ለዘመናት በባላንጣነት እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡  የገዛ ወንድሙን ለመበቀል ከጠላቶቹ ሳይቀር ይወግናል፡፡  ዛሬ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ባለአንጣ ከሆኑ ቡድኖች  በመተባበር በኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ላይ እያሴሩ ናቸው የሚባለው በስልጣን ላይ ባሉት መሪዎችና ተቃዋሚ በሚባሉት መካከል ያለውን አለመግባባት በማርገብ ፋንታ ወደ ከረረ የመበቃቀል እልኸኝነት መንፈስ እንዲያመሩ ባደረጉ ስሜታዊ እርምጃዎች ነው እንጂ ከመጀመሪያው አሁን ያሉ ባለአንጣነትና በቀለኝነት በሁለቱም ወገን ኖሮ አይመስለኝም፡፡   

መንግስት እንደመንግስት ቻይነቱ ይብዛ ኃላፊነትም ስላለበት አጥፊዎችን (ከልዩ ወንጀለኞች በስተቀር) ወደ ጥሩ እርምት በማምጣት መልካም ዜጎች እንዲሆኑ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ አጥፊዎችም ጥፋታቸውን ማመን መቻል አለባቸው፡፡ ጥፋታቸውን ማመን እስካልቻሉ ድረስ ለወደፊትም አይታረሙምና፡፡ ዛሬ ብዙዎች እንደሚያናፍሱት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁን ነጸ አስተሳሰብ በሚል በሚጽፉ የመንግስትም ሆን የግል ጋዜጦችና ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን ያን ያህል ትኩረት ሊሰጥ አይፈልግም፡፡ ምክነያቱ ደግሞ ብዙ ጊዜ ተዋሽቷል ብዙ ጊዜም ተክዷል፡፡ በቃ በሠላም መኖርንና ብልፅግናን ብቻ ይፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ ምናምን እየተባለ ራሳቸው ፍትህና ዲሞክራሲ ባልገባቸው ስሜተኞችና አልፎም ሴረኞች መወናበድ አይፈልግም፡፡ ዲሞክራሲም ከሆነ የአሜሪካና የአውሮፓ የተባለው አይነት በአፍንጫችን ይውጣ፡፡ ዜጎቿን እስከዛሬም በቀለም ለይታ ፍትሕን በዜጎች መካከል ያላሟላች አሜሪካ በምን መስፈርት ለእኛ እንደ ምሳሌ ትጠቀሳለች፡፡ አለማስተዋላችን እንጂ ይቺ አገር (ኢትየጵያ) ብዙ ለሌሎች ሳይቀር ምሳሌ የሚሆን ታሪካውና ባህላዊ ፍትሀዊ አስተሳሰቦች ያሏት አገር ናት፡፡ አስተውሉ ይህች አገር በኋላ በመጣንው ትውልዶች የተበከለ ሥምና ታሪክ እንዲኖራት ሆነ እንጂ ከመሠረቱ እጅግ አስደናቂ በሆኑ የጥበብ ፈላስፎች ትመራ እንደነበር እናያለን፡፡ በዚች አገር ሀይማኖት፣ ቀለም፣ ዘር ሳይሆኑ ስብዕና ብቻ ፍትህን የሚያሰጥባት አገር ነበረች፡፡ የነብዩ መሀመድ ተከታዮች ወደ ክርስቲያኑ መሪ ለመጠለል ሲመጡ ሀይማኖታቸው ሌላ መሆኑ ሰብዓዊ የመኖር መብታቸውን አልከለከለውም፡፡ ይልቁንም በእንግድነት በክብር አቀባበል ተደረገላቸው እንጂ፡፡ ዛሬ ግን ለብዙዎቻችን ስብዕና ሳይሆን በሀይማኖት፣በዘር፣ በቀዬ፣ ወዘተ መመሳሰላችን ነው ትልቅ ድርሻ ያለው፡፡ በዙ ሙስሊም ዜጎቻችን ከአገራቸው ይልቅ የአረቡ አለምን የሚያስቀድሙ ናቸው፡፡ ከአውሮፓ በመጡ እምነቶች ጥላ ሥር ያሉም ብዙዎች  ከአገራቸው ይልቅ የምዕራቡ አለም ናፋቂዎች ናቸው፡፡  የግብፅና ኢትዮጵያ እግር ኳስ ሲካሄድ ለግብፅ ከስሜት የደገፉ ዜጎቻችን በአባይ ጉዳይ ግብጽና ኢትዮጵያ ቢጣሉ የግብጽ ባንዳ ላለመኆናቸው ዋስትና የለንም፡፡ እንኳንስ ይህን ያህል አረብን ናፋቂነት ስሜቱ እያለ ቀድሞም ብዙም ፈረንጅ ናፋቂ ባልሆኑት ዜጎቻችን ዘመን በጥቅም ታውረው ለጣሊያን ባንዳ የነበሩ ዜጎቻችን ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ከራሱ አገር ይልቅ ሌሎችን የሚናፍቅ ትውልድ ደግሞ ይህ የእኛው ዘመን ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ በራሱን ማንነት የሚያፍር የባሪያ አመለካከት ስላለው የራሱ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ በጎ እሴቶቹ አይታዩትም፡፡ ሴቶችን እንደ ዕቃ ይቆጥሩ የነበሩት የምዕራባውያንና የአረቡ (ዛሬም ያው ነው) አገራት ዛሬ ለእኛ ለሴቶች ልዩ ክብር ከጥንት ጀምሮ ይሰጥ የነበረው ባህል ባለቤቶች ስለሴቶች መብት ሊያስተምሩን ይሞክራሉ፡፡ እኛም የራሳችንን ትተን ልክ አዲስ እንደነገሩን እነሱን ሰማን፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ ሕዝቦች ባህል ሴት ንጉስም፣ ጀግናም ትወልዳለች እየተባለ ልዩ ክብር ይሰጣት እንደነበር ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡ ክፉኛ በተጣሉ ሁለት የሚደባደቡ ሰዎች መካከል ሴት ለግልግል ብትገባ በመሀል ስለገባችው ሴት የቱንም ያህል የከረረ ጥል ቢሆን ጠበኞቹ ሰይፋቸውን ወደሰገባው የሚመልሱበት ማሕበረሰብ እንደነበረን ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡  እነዚህ ሁሉ እውነቶች ግን በኋላ በመጣው ትውልድ ነቀዘው የሌላ ናፋቂዎች ሆንን፡፡

አሁንም እላለሁ እኛ አገርንና ሕዝብን ካስቀደምን ጠባችን ቢሆን ለአገሬና ሕዝቤ በዚህ መልኩ እንጂ ይሄኛው አይጠቅምም የሚል የሐሳብ ልዩነት ካልሆነ የበቀለኝነት አይሆንም፡፡ ጠባችን ግን እኔ ልብላ እኔ ልብላ ከሆነ አገርና ሕዝብ እዚህ ጋር ወደጎን ተገፍትረዋልና እርግማኑ በራሱ መጥፊያችን ይሆናል፡፡  አገርንና ሕዝብን ካልን ደግሞ የራሳችንን ገመና ለሌሎች አውጥተን አንሰጥም፡፡ ከጠላት ጋርም አንወግንም፡፡ ሞት ቢኖር ወንድሜ ይግደለኝ እንጂ አገሬን አልከዳምና፡፡ ለአንድ አገርና ዜጎቿ ከሆነ ጭንቀታችን የሁላችንንም ልብ የሚረዱት የእኛው ወገንና አካል የሆኑ አገር ወዳድ ሽማግሌዎቻችን እንዲዳኙን ፍቃደኞች ነን፡፡ ተግሳጻቸውንም ለመቀበል ለባችን በቂም አይመረዝም፡፡ አእምሮአችን በአወቀ ቁጥር በማስተዋል ፈንታ በስሜት የሚነዳም ከሆነ እወቀታችን መካን ነው፡፡ ጥበባኛና ለአገርና ሕዝብ አሳቢ ከመሆን ፈንታ በቀለኛ ከሆንም ሰይጣንን እንወክላለን፡፡ የአገሬ ልጆች ወደ ራሳችን እንመለስ፡፡ የአገሬ ሽማግሌዎች በተኳረፉ ልጆቻችሁ መሀከል ቁም፡፡ አንተም ተው አንም ተው በሉ! ባዕድ በመካከላችን አይግባ! ጓዳችንን ለጠላት አናሳይ! ስሜታችንን  እንግታ አካሂዳችን ሁሉ በማስተዋል ይሁን! እኛ እርስ በእርስ ጠላቶች አይደለንም! ካልተግባባን ሽማግሌርዎቻችን ይዳኙን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንን ይባርክ! አሜን!

የታላቋ ቀን ልጅ ሰኔ 30 2006ዓ.ም