Showing posts with label ሐይማኖታዊ መረጃዎች. Show all posts
Showing posts with label ሐይማኖታዊ መረጃዎች. Show all posts

Tuesday, April 29, 2014

የጌታን እናት ማርያምን ነገር ማን ያውቀዋል?!




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ በሥጋ ትዛመደን ዘንደ ከእኛ ወገን በመረጥካት ቅድስት እናትህ ማርያም ሥም እንዲሁ እንደተዛመድከን መከራችንን ሁሉ ትቀበል ዘንድ በወደድክበት ፍቅርህ ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
በቅርቡ አንድ "ነገረ ማርያም የተባለው መተጽሐፍ ልዩ ወንጌል (ከወንጌል ያፈነገጠ) ነው" በማለት ስለ ነገረ ማሪያም የሚተች ጽኁፍ ከአንድ አባ ሰላማ ከሚል ደረ-ገጽ (www.abaselama.org/2014/03/blog-post_27.html‎) ማንበቤን ተከትሎ ይህንን አስተያየተን ለመሰንዘር ወደድኩ፡፡  በዚህ ዘመን ሀይማኖታዊ የሚመስሉ ነገሮችን በጥንቄ ማስተዋል እንዳለብን ስለአሳሰበኝ ይህችን ላካፍላችሁ በሚል፡፡ አነበብኩት ያለኳችሁን ነገረ ማርያምን የሚተቸው ጽሁፍ ብዙዎቻችሁ አንብባችሁታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ትችቱን በደፈናው ለቃወም አይደለም፡፡ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት የቅንነት ሳይሆን አንድ ነገርን መዞ ብዙ ሕዝብን ለማደናገር የታሰበ ስለመሰለኝ እንጂ፡፡ እርግጥ ይህ ጽሑፍ መነሻ ሆነኝ እንጂ ብዙ ሌሎች ተቃርኖአዊ የሆኑ መልዕክቶችን ስለሀይማኖት የሚያስተላልፉ በተለይም ደግሞ የጌታ እናት ነገር ከነዚያ አይሁዳውያን ቀናተኞች ባልተናነሰ የሚያናድዳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ግን ምን ማድረግ ይቻላል ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናት ነች! ይሄንን ማን ሊሽረው ይችላል! ነገረ ማርያምም በሉት ሌላ ታሪክ ከዚህ እውነታ በላይ ስለጌታ እናት ማንነት ሊመሰክርልን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምንአልባት የአምላክ እናት የሆነችበትን ሆኔታዎች በሰውኛው ሊተነትኑልን ይሞክሩ ይሆናል እንጂ፡፡ የአምላክ እናት ለመሆን የበቃችበት ማንነቷ ግን ፈጣሪዋም ልጇም በነው እግዚአብሔር የሚታሰብ እንጂ በእኛ አእምሮ ሊታሰብ የሚችል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህ ሚስጢር ነብያትንም በጨረፍታ እየመጣ ሲያስጨንቃቸው የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ እሷ ራሷ እንኳን መልአኩ ነገራት እንጂ በፈጣሪዋ ዘንድ የዚህን ያህል የተከበረች እንደሆነች የተረዳችው አይመስልም፡፡ መልዐኩም ቢሆን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በማለት የተነገረውን ከሴቶች ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ብሎ ምስራቹን ነገራት እንጂ ሂደቱን ምን እንደነበር አልገጸውም፡፡ ኤልሳቤጥ የጌታን እናት ማንነት ለማየት የቻለቸው በመንፈስቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ኤልሳቤጥም የቱንም  ያህል የጌታ እናት ዘመዷና በእድሜም ልጇ ልትሆን ብትችልም ልተጎበኛት ወደቤቷ በመምጣቷ እጅግ የተደሰተችም ቢሆን ከራሷ ክብር ጋር አነጻጽራ የጌታዬ እናት ሆይ ወደእኔ ትመጭ ዘንድ እኔ ምንድነኝ ስትል ነበር የደነገጠችው፡፡ ኤልሳቤጥ ግን ከነበይም በላይ የሆነው የዮሐንስ እናት ነች፡፡  ዮሐንስ ስለጌታ ሲናገር የእግሩን ጫማ እንኳን ልፈታ የማይገባኝ እንዳለው ነበር እናቱ ኤልሳቤጥ የጌታን እናት በአየች ጌዜ የተናገረችው፡፡ ይህ እውነታ በሥጋ የሚታይ አይለም፡፡
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመልሳችሁና ይህ አነበብኩት ያልኳችሁ ነገረማርያምን የሚተቸው ጽሑፍ መሠረታዊ ነገሩ ለመቃወም ብቻ ይመስላል፡፡ እንደዘመኑም ሀይማኖታዊ ነገር ላይ ትችት ለመሰንዘር ምንም የማይከብዳቸው አይነት ሰው የጻፈው የሚስላል፡፡ ሲጀምር ነገረ ማርያም የሚባለውን መጽሐፍ ተችው አንብበውት የሚያውቁ አይመስልም፡፡ ከአነበቡት ደግሞ ሆን ብለው ደብቀውታል፡፡ እንደእውነቱ አኔም ይህ ነገረ ማርያም የሚባለውን መጽሐፍ አንብቤው አላውቅም፡፡ እኔ በብዙ ፀሎት መፅሐፍት ላይ የተካተተው ነገረ ማርያም የሚለው የነገረ ማርያም ዋናው መጽሐፍ መሆኑንም አላውቅም፡፡ ይልቁንም ይህ በጸሎት መጽሐፍ የተካተተው ነገረ ማርያም እንዳለ በነገረ ማርያም በማለት ብዙ ዋቢዎችን ከነገረ-ማርያም፣ ከሌሎችም መጻሕፈት እያጣቀሰ የሚናገር እንደሆነ አንብቤያለሁ፡፡ ይህን በጸሎት መጽሐፍ የተካተተውን ነገረ-ማርያም ልብ ብላችሁ እንደሆነ የእመቤታችንን ታሪክ እስከ ወደ ቤተመቅደስ የገባችበትን ጊዜ ሊተርክ ይሞክርና ከዚያ ፍጹም ከዚህ ታሪክ ጋር የተቋረጠ ሌላ ትንተና/ሐተታ ጀምሮ እንደገና ወደ ታሪኩ ሲመለስ እናያለን፡፡ እንግዲህ ይህ በመሀል የገባ ሐተታ ነው ለተችው ክፍተት ፈጥሮ ነገረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ ልዩ ወንጌል ነው ሲሉ በሰፊው የነገረ-ማርያም መጽሐፍ ሊነቅፉ ለጸሐፊው እድል የሰጣቸው፡፡ በትክክልም ይህ በመሀከል የገባው ሐተታ በልዩ ሚስጢራዊ ትርጓሜ ካልሆነ ለጌታ እናት ይነገራል ብዬ እኔም አልቀበለውም፡፡ ግን ይህ የነገረ ማርያም አካል ለመሆኑም ምንም ማሳያ የለም፡፡ እዛ ሐተታ ውስጥ በሌሎቹ የጽኸሑፉ ክፍሎች እንደምናነበው ነገረ ማርያም እንዳለ የሚል ወይም ሌላ መጽሐፍ አንድም ዋቢ ሲጠቀስበት አይታይም፡፡ ጸሐፊው ይህንን ሐተታ መተቸት ወይም ጥያቄ ማቅረብ ቢሞክሩ ሐሳባቸው ከቅንነት የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የተችው አካሄድ ለመቃረንና በድፍረት በአላወቁትም ነገር ወይም ሌሎችን ሆን ብሎ ለማሳሳት እንዳይሆን አሰጋለሁ፡፡ ይህ መሀል የገባ ሀተታ ግን በቤተክርስቲያን ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው በዬ አምናለሁ፡፡
አንድ አንድ ጊዜ መጽሐፍትን የሚበርዙ ነገሮች ልዩ ፍላጎት ባለቸው ተርጓሚዎችና አሳታሚዎች በቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚካተቱ እናውቃለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ዋናው መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን መሠረታዊ ትርጉምን የሚያፋልሱ ብዙ የሚበርዙ ዓረፍተ ነገራት ተካተውበት እናያለን፡፡ ዛሬ ዛሬ እንደውም ይህ መጽሐፍ እየታተመ ያለው እንደየ እምነቱ ፍላጎት ሆኗል፡፡ ይህ የመጽሐፍት በልዩ ታሪክ መበረዝ ደግሞ በሌሎች መጻሕፍትም እንደሚከሰት እራዳለሁ፡፡ ስለ እመቤታችን ዛሬም ድረስ ብዙዎች ሊተነትኑት የሚሞክሩበት አካሄድ መሠረታዊ እውነታዎችን እንዳያፋልስ እሰጋለሁ፡፡ ብዙዎች በሥጋ ዕውቀትና ፍልስፍና እንዲሁም በተራ ስሜት እንጂ በልዑል አምላክ ሀይል ሥር በመንበርከክ በምትመጣ ጥበብ/ፍልስፍናና ማስተዋል ላይጽፉ ይችላሉና፡፡ የሀይማኖትን ነገር ደግሞ ብዙ ሕዝብ የሚቀበለው በየዋሕነት እንጂ ተረድቶና አውቆ አይደለም፡፡ ለክርስትናው ግን የተነገረው መልዕክት እንደ አባብ ብልህ እንደ እርግብ የዋሕ እንጂ የዋህነት ብቻ አይደለም፡፡ ይሄው የዋሕነት በትላልቅ አባቶች ሳይቀር ስለሚያይል ጥፋት እየጠፋ እያዩ እነኳን ተው ብሎ ለመገሰፅ የማይቻለቸው ጊዜ ብዙ ነው፡፡
የጌታ እናት ሩሕሩሕነት በሰው አእምሮ እንኳን ሊታሰብ የማይችል እንደሆን አምናለሁ፡፡ ባሕሪዋ የልጇ በሕሪ ነውና፡፡ ሞትንም የምትፈራው ነች ብዬ አላምንም፡፡ ወዴት እንደምትሄድም ታዋቃለችና፡፡ ይልቁንም ምድራዊ ሕይወቷ ሁሉ የመከራና የሐዘን እንደነበር እናያለን፡፡ ስለብዙዎች እሷ ማዘን ነበረባትና! እንግዲህ በጸሎት መጽሐፍ ነገረ-ማርያም በሚለው ምዕራፍ ውስጥ የገባው ይህ ልዩ ሐተታ እንዴት እንደሆነ አባቶች ቢያብራሩት መልካም ነው፡፡ እንደተባለውም ስሕተት ከሆነ በትክክል በይፋ ተነግሮ መሰረዝ አለበት  ብዬ አምናለሁ፡፡ ስህተት ሆኖ እያለ ቢዘነጋ ግን ራሱ ኑፋቄ ከመሆኑም በላይ ለሌላ ኑፋቄ መዳረጉ ግልጽ ነው፡፡ ነገረ-ማርያምን በድፍኑ ለመንቀፍ ምክነያት እንደሆነ ሁሉ ሌላ የሀይማኖት ጉድፍ እንዳይሆን አስባለሁ፡፡ ብዙዎቻችን በማንበብ እንጂ በማስተዋል የምንሄድ አይደለንምና፡፡ ለፈላስፎቹ ግን አለም አለማትን (the entire universe) በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ አምላክ እናት ከመሆን ያለፈ ታርክ አያስፈልጋቸውም፡፡ ለዛም ይመስላል አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰው ሆኖ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ/ሚስጢር የሚያስደንቃቸው፡፡ የጌታ እናት ማንነት ታሪክ ደግሞ ያለው አዚህ ልዩ ሚስጢር ውስጥ ነው! 
ቅዱስ አባት ሆይ በማስተዋል አንኖር ዘንድ ከአነት የምትገኝ ዕውቀትን ስጠን!
አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሚያዝያ 21፣ 2006 ዓ.ም.

Sunday, March 30, 2014

ይድረስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፓትሪአርክ)


እውነት ከሕሊና ፍርድም በላይ እንደሆነች እረዳለሁ፡፡ ብዙዎች በህሊናቸው ትክክል ሆነው እውነትን ግን
ስተዋታልና፡፡ በትክክል አባባሌን ይገልጽ እንደሆነ አላውቅም ግን የሳዖል ኋላም ቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ
ያንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ እሱ አስቀድሞ ስላወቀው/ስለተማረው ነገር ብቻ የክርስቲያኖች አሳዳጅ
ነበርና፡፡ ሳዖል ግን ስለህሊናው ትክክል ነበር ምንም እውነትን ባያገኛትም፡፡ በአንጻሩ ሌሎችን ጨምሮ
ራሱ አስተማረኝ የሚለው ገማልያ ሳይቀር እውነትን ቢያውቋትም ሊመሰክሩላት አልፈለጉም ወይም
ፈርተው ክደዋታል፡፡ ከህሊና ፍርድ ወጥተዋል፡፡ እኔን እንደሚገባኝ ሕሊናችንን ካልካድን እግዚአብሔር
እውነትን ለማወቅ ከፈለግን ይገልጥልናል፡፡ ለቅዱስ ጳውሎስ የተደረገለት ይሄው ይመስለኛል፡፡ የእኛ
አቅም ስለሕሊናችን መኖር ነው፡፡ እውነትን ለማወቅ የእግዚአብሔር እገዛ ያስፈልጋል፡፡ እውነትን ግን
መናፈቅ ያስፈልገናል፡፡ እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ደግሞ አብዝተን መፈለግን
ይጠበቅብናል፡፡ ማለትም ለሕሊናችን ማደርን፤ ፍጹማን አለመሆናችንን አወቀን ያላወቅንውን ለማወቅ
መትጋትን፡፡ በተቃራኒው እግዚአበሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ
አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ይላልና፡፡ አንዴ ለማይረባ አእምሮ ከተሰጠን ምን ዋጋ አለን?! የማይረባ
አእምሮ/ሕሊና ያጣ/ ከባድ ነው!
የሕሊና ፍረድና የእውነትን መፈለግ/መናፈቅ ለሰው ሁሉ የሚያሰፈልግ ሲሆን በመሪነት ያሉ ሰዎች፣ዳኞች፣
በተለይም ደግሞ የኀይማኖት አባቶች እጅግ የሚጠበቅባቸው ነው፡፡ እነሱ ስለብዙዎች ይኖራሉና፡፡ በአንዱ
የሐማኖት አባት መውደቅ ምክንያት ብዙዎች ሊወድቁ ይችላሉና፡፡ ሥለትሷ የሕሊና ፍርድ ማጓደል
ከመኖር በስጋ ቢሞቱ ይሻላቸዋል፤ ስለብዙዎች ሕያዋን ናቸውና፡፡ ይህንን ብዙ የሀይማኖት አባቶች
አደርገውት አልፈው ዛሬ ደርሰናል፡፡ አሁን አሁን በሀይማኖት መሪዎች የሚታየው ግን እኛ ተራዎቹ
እንኳን የማንደፍረው ከሕሊና የራቀ ድርጊት (ድፍረት ብለው ይመቸኝ ነበር) ነው፡፡ እርሶ በሚመሯት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሕሊናን የሚያከሱ፣ ምዕመናንን የሚገፉና፣ እንዲህስ ከሆነ ቢቀር
ይሻላል በሚል ሕዝቡን ከአምልኮተ እግዚአብሔር እያራቁ የሚገኙ በቤተክርስቲያኗ በመሪነት ቦታ ያሉ
ሰዎች የሚፈጽሟቸው ብዙ ድርጊቶች አሉ፡፡ አባ ይህንን ሁሉ የምነግርዎት እርሶን ለማስረዳት
አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ ያቁታልና፡፡ ጽሑፌ ለተነሳበት ሀሳብ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ እንጂ፡፡
ቀደም ብለው ሰዎች ብዙ ስላሉባቸው በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጸሙ ግደፈቶች ብዙም ስለማላውቅ
እኔ አስተያየት ሰጥቼም አላውቅም፡፡ አንዳንዶቹም ሰዎች ስለተሳሳቱ የሚያወሯቻ እንጂ እውነት ሆነዋል
ብዬ ለማመን እቸገርባቸው ስለነበርም፡፡ ሰሞኑን ግን እኔው የማውቀው እኛ ተራዎቹ የማናደርገው
የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችና ደብር አስተዳዳሪ ሆነው በተሾሙ ሰው በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን
አንድ ድርጊት ተፈጽሞ ይሄው ሕዝቡን እያነጋገረ ይጋኛል፡፡ እንደውም ይሕንንው ድርጊት በመደገፍ
ከእርሶ ጽ/ቤት ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤም አለ፡፡ ደግነቱ እርሶ አይደሉም የፈረሙት! ይመስለኛ ጉዳዩን
ሰምተውታል፡፡ ይሄውም በደብሩ (ቅ. እስጢፋኖስ) ቅጥር ግቢ ውስጥ ወንጌል ያስተምሩና በተሰጣቸውም
ፀጋ ሰዎችን በርኩሳን መናፍስት ከሚመጡ ልዩልዩ ደዌያትና ሌሎች ውስብስብ የኑሮ ችግሮች ይታደጉ
ስለነበሩት መምህር (መልአከ መንክራት) ግርማ ወንድሙ ጉዳይ ነው፡፡ አባ ፤ መምህር ግርማ በደብሩ
ቅጥር ግቢ እየሰጡ የነበሩትን አገልግሎት ማገድ ሥልጣንና ጉልበት እስካለ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡
ለቤተክርስቲያንም እውን ከመቅናት የተነሳ ድርጊት ከሆነም ሕሊና ስላሰበው ተደርጓልና ከክፋት
አይቆጠርም የቱንም ያህል እውነትን ካለመረዳት ስህተት አንኳን ቢሆን፡፡ የሆነው ነገር ሁሉ ግን ሕሊናንም
እውነትንም በመካድ ስለሚመስል አደገኛ ድፍረት ነው በዬ አምናለሁ፡፡ ሒደቱ ሁሉ ውስብስብ
ተንኮለኝነት የተቀመሙበት ይመስላልና፡፡ መምህር ግርማን ይሁን እግዚአብሔርን እየተዳፈሩ ያሉት ማንን
እንደሆነ ሁላችንንም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነበርና፡፡ መምህር ግርማን ስለነኩ ማለቴ አይደለም፡፡
የወንጌል ማስተማሪያ መድረክ አፈረሱ፣ ቅዱሳን ስዕላት ቀደዱ፣ ሌሎችንም ሥጋዊ ኃይልና ሥልጣን
የሚችሏቸውን ድርጊቶች ፈፀሙ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የሆነው በሰሞነ ሕማማት፣ የክርስቶስ ሕማም
በሚታሰብበት ሳምንት መሆኑ ያሳዝናል/ያስገርማልም፡፡ እንዲህ ያለውን ድርጊት ለእኛ ስታስተምሩን
ሐጥያት ነው በተለይ ደግሞ በሰሞነ ሕማማት፡፡ የቤተክርስቲያን ሰዎች ነን የሚሉት ግን ሲያደርጉትስ?
እውን ስህተትስ ቢኖር እንዲህ ባለ ከመንፈሳዊ ባህሪ በወጣና በጀብደኝነት በሚደረግ ግርግር ለሕዝብ
ማስተዋልን በማይሰጥ ሁኔታ ስህተትን ማረም ይቻላል? ደግሞስ ካልጠፋ ጊዜ ያ ጊዜ ለምን ተመረጠ?
መምህር ግርማ የነበሩት በቅድስት አገር እየሩሳሌም ስለነበር ነው የተመረጠው? የሕሊና ጉዳይ ከሆነ
እሳቸው ባሉበትስ አይቻልም ነበር? በዚያውም ስህትቱን ተናግሮ ሕዝብንም አሳምኖ? እንኳንስ ለዘመናት
ያስተማሩትን መምህር ግርማን ይቅርና በአንድ ጉባዔ የተከሰተ ሕዝብን የሚያሳስት ነገር ከሆነ በተቻለ
መጠን ስህተት በፈመው ፊት ስህተቱን ተናግሮ ማረም ይጠበቃል፡፡ አባ ሁሉንም ነገር አርሶ ያዎቁታል
ማለቴ ሥርዓቱን ሁሉ፡፡ መምህር ግርማ እየተከሰሱበት ያለውን ሁሉ፡፡
የተፃፉትን ደብዳቤዎች ስናነብ ግን ማን በምን አስተሳሰብ ደረጃ እንዳለ ስለነገሩን በሕዝብ ዘንድ የፈጠሩት
ትዝብትን እንጂ የመምህሩን ስህተት አይደለም፡፡ የደብዳቤዎቹ ቅደም ተከተል፣ይዘትና የቃላት አጠቃቀም
ከመውረዱ ጋር ተዳምሮ፡፡ በተለይ ደግሞ ከእርሶ ጽ/ቤት የወጣው ደብዳቤ ሲጀምር ደብዳቤው
ላልተጠየቀበት ጉዳይ ነው የተፃፈው፤ ከተጻፈም ሥርዓትና አግባብ ባላቸው ቃላቶች ቢሆን መልካም
ነበር፡፡ ደብዳቤው ጉዳዩችን በስርዓቱ ከማበራራት ይልቅ በስደብ የታጨቀ ነበር፡፡ ሕገ-ወጥ፣ ሥርዐተ-
አልበኛና የመሳሰሉት ቃላቶች እውን ከእገዳው ጋር በተያያዘ ሊያውም ከቤተክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው?
ኋላ በሕግም እኮ ሊያስጠይቁ ይችላሉ፡፡ ግን ሲጀመር በ28/08/2005 በደብሩ አስተዳዳሪ የተጻፈው
ደብዳቤ የመምህር ግርማን ማገድ ወስኖ ለእርሶ ጽ/ቤት በግልባጭ አሳወቀ እንጂ እገዳውን እንዲያጸናለት
አልጠየቀም፡፡ እና ላልተጠየቀበት ጽ/ቤቱ አፅድቄአለሁ ማለት አለበት? በዚህ አይነት ግልባጭ
የተደረገላቸው ሁሉ አጽድቀናል እያሉ መጻፍ አለባቸው? በግልባጭም ቢደርሰው የእርሶ ጽ/ቤት ደብዳቤ
ለደብሩ የሚፅፍበት ሁኔታ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ኃላፊነት ስላለበት ግልባጭ የተደረገለት ጉዳይ ስህተት
ሆኖ ቢገኝ ለማረም፡፡ ይባስ ብሎ ስንት አመት ሲያስተምሩ ምንም ሳይባሉ ይሄው የእርሶ ጽ/ቤት ደብዳቤ
በአሰቸኳይ ከሚል ልዩ ማሳሰቢያ ጋር ነው የተጻፈው፡፡ አባ እንዲህ አይነቱ ነገር ውስጥ የተሸረበ ሴራን
ለሕዝብ እያሳበቀ እንደሆነ ጸሐፊዎቹ ቢረዱት እንዴት ጥሩ ነበር፡፡
ደብዳቤዎቹ በየኢነተርኔቱ ስለተበተኑ ሕዝብ እያያቸው ስለሆነ ሌሎች ጉዳዮቹን አላነሳም፡፡ ከደብዳቤዎቹ
በተጭማሪም የደብሩ ሰንበት ት/ቤት አጥንቼ አግኝቼዋለሁ የሚለውንም የመምህር ግርማን ክስ
በየኢነተርኔቱ አስነብቦናል፡፡ የሚያሳዝነው ግን አሁንም ጥናት ብለው ባቀረቡት ጽሑፍ የተጠቀሟቸው
ቃላቶች በጣም ከግበረ-ገብነት የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ጥናት የመረጃ አቀራረቡ እንዴት እንደሆነ
ቢጠይቁ እንሱንም ከትዝብት ያድናቸው ነበር፡፡ አንድ የጥናት ሰነድ ሲቀርብ መጠቀም ያለበት መደበኛ
ቃላቶችን እንጂ አንባቢን በሚያስደንቡሩ ስድቦችና አስነዋሪ ቃላቶች ታጅቦ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ
አጠኚው ሲጽፍ እራሱን ገለልተኛ አድርጎ በአገኘው ውጤት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንጂ የራሱን ስሜት
አጠናሁት በሚለው ጉዳይ ቢያስነብብ ልብወለድ እንኳን ለመሆን አይበቃም ምንአልባት አሉባልታ ከሆነ
እንጂ፡፡ ልብወለድም የብዙ ማሕበራዊና ነባራዊ ጉዳዮችን ጥልቅ ግንዛቤ ይጠይቃልና፡፡ በዚህ አጋጣሚ
እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ለሕዝብ ማንነታቸውን ማሳወቅን እንጂ የጥናታቸውን ማረጋገጫ በመተንተን
ጭብጥን ማሳወቅ አይደለም፡፡ ከጥላቻ፣ ከቅናት፣ ከአደመኝነት፣ ከበቀልና ከመሳሰሉት የክፋት በሕሪያት
በተወረሱ ቃላቶች የጥናትን ውጤት መዘገብ ከንቱ ነው፡፡ ድርጊቱ አንኳን እነሱ እንደሚሉት ቢሆን
እውነታንም ያጨልማልና፡፡
አጥኚ ነን ያሉት ግን ሁከት በሆኑ ቃላቶች እውነት ነው ብለው ሊያሳምኑን የሞከሯቸው ጉዳዮች
አንዳቸውም እውነት አለመሆናቸው ነው፡፡ አሁንም ሙሉ ጥናት የተባለው ከኢነትረኔት ሊነበብ ይችላል
ግን አለፍ አለፍ እያልኩ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ መምህር ግርማ ቢያንስ ካህን ናቸው
ከዚህም በላይ ቤተክርስቲያኗ በሰጠቻቸው ማዕረግ በተለምዶ መምህር ግርማ ብንላቸውም መላከ
መንክራት ተብለው ተሰየመዋል፡፡ በዚህም ላይ በእድሜያቸው ብቻ እንኳን አንቱ መባል አያንስባቸውም፡፡
ትልቅን ሰው አንተ እያለኩ ባቀል ራሴን ማቅለሌን ማወቅ አለብኝ፡፡ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ደግሞ
ከዚህም በላይ በሆኑ አክብሮቶች ሰዎችን ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ ጉዳያቸውንም በትክክሉ ለማስተላለፍ
ይረዳ ነበርና፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ አጥማቂ ነኝ ፈዋሽ ነኝ ባይ ይላል፡፡ እሳቸው ስላሉ ነው
ወይስ ሕዝብ ራሱ ስላየ? መምህር ግርማ አጥማቂም ፈዋሽም ነኝ ብለው አይደለም ሰው የአገልግሎቱ
ተጠቀሚ የሆነው፡፡ መምህር ግርማ ከብዙዎች በተሻለ የአምላካቸውን ክብር ያውቁታል፡፡ የሚያድነው
የእግዚአበሔር የስሙ ኃይል ነው! እኔ አገልጋዩ ነኝ (ሁሌም የሚሉት ነው)! ከማለት በቀር እኔ ፈዋሽ ነኝ
ሲሉ ሰምተናቸው አናውቅም፡፡
ለመምህር ግርማ በትክክልም የማዳን ፀጋ እንደተሰጣቸው ሕዝብ በትክክል በተግባር አየ እንጂ በወሬ
እንኳን የሰማው ብቻ አይደለም፡፡ ለምን ሕሊናችንን እንደምንክድ አልገባኝም፡፡ አይነስውር
አላየም?ሽባዎችና አንካሶች አልሮጡም? ሌሎች በሕክምና ተስፋ የተቆረጠባቸው በሽተኞች አልዳኑም? ይህ
እውነት አይደለም? ብዙዎቻችንን ለዘመናት የእግዚአብሔርን ሀልዎት እንኳን ረስተን የነበርነውን ኃይሉን
በገሃድ አሳይተውን ሳንወድ በግዳችንም ቢሆን እንድናምን አድርግዋል፡፡ ከሌላ እምነት ሳይቀር! ይህ
እውነት አይደለም? አኛ አኮ ለዘመናት የተደናገርን ሰዎች ነን፡፡ ይህ በእሳቸው እየተካሄደ ያለው ሐዋሪያዊ
አይደለም? አባ እርሶ ራስዎ እንዲነግሩን እንፈልጋለን፡፡ እውን አሳቸው የሚሰሩት የጥንቆላ ሥራ ነው?
ለነገሩ እንደኔ ላለነው የትኛውም ኃይል ይሁን እንዲህ ያለ ነገር እንዳለ ማወቁ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምንም
አናውቅም ነበርና! የእግዚአብሔርን መኖር እንኳን በአፋችን እንጂ በልባችን ወደ ክህደት የተጠጋው
ጥርጣሬው ነበረብንና፡፡ ሰይጣን የሚባለው በእኔና መሰሎቼ ዘንድ ከነጭርሱም የሌለ ነገር እንደሆነ
ልባችንን ሞልተን የምንናገረው ነበር፡፡ እግዚአብሔርንም እኮ እንደው ስለፈራን (ምን አለባት ካለ በሚል)
እንጂ እንዳለ ስላመነው አልነበረም፡፡ ይሄንን ሁሉ በመምህር ግርማ ምክንያት በገሃድ አይተን እንድናምን
ተገደናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምርጫችንን ማስተካከል የየራሳችን ነው፡፡
አባ እውን ልንቃወመው የሚችል አንድ ስህተት እንኳን ተሰርቷል? ሰዎችንስ እያዳኑ ያሉት
በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ስም አይደለም? መቁጠሪያውስ አርሶ ሳይቀሩ አባቶቻችን የምትይዙት
አይደለም? በዲቁናስ ማዕረግ ሆነው ያጠምቁ የነበረው እውን ስሕተት ነው? እግዚአበሔር ከፈቀደ ደግሞ
ከልካዩ ማን ነው?! እንኳንስ የዲቁና ስልጣን የነበራቸውን መምህር ግርማን ይቅርና የእግዚአበሔር ፈቃድ
በሌላ ክህነት ከነጭርሱ በሌለው ሰውስ ቢሆን ማን ሊያግደው ይችላል? ረጋሚው በለዓም እኮ ነው
የክርስቶስን መምጣት ከዘመናት በፊት ያስተዋለው! ክርስቶስን አሳዳጁ ሳኦል እኮ ነው የክርስቶስ ድንቅ
ሐዋሪያ የሆነው! ሽፍታው አኮ ነው ገነት በመግባት ቀዳሚ የሆነው! በተቃራኒው ስርዐት አለን የሚሉት
ካህናት እኮ ናቸው ክርስቶስን የሰቀሉት፣ ደቀመዘሙሩ የነበረ ይሁዳ እኮ ነው ጌታን አሳልፎ የሰጠ፡፡ ሰዎች
ስርዐትንና ቀኖናን እነሱ በሚመቻቸው እየተረጎሙ መጠቀሚያ ካደረጉትስ? እንደምረዳው መምህሩ
ከጅምሩ በዲቁናቸው ዘምን ያጠምቁ የነበሩት የተሰጣቸውን ጸጋ (ካልተጠቀሙበት ዕዳ ነውና)
ተጠቅመው ወገናቸውን ለመርዳት እንጂ እኔ አጥማቂ ልሁን ብለው እንዳልሆነ ያለፉባቸው ታሪኮች
ምስክሮች ይሆኗቸዋል፡፡ ደግሞስ የቅስናውን ማዕረግ ሰጥቶ አገልግሎታቸውን ማጽናት የቤተክርስቲያኗስ
ኃላፊነት አይደለም? ይህስ ከባድ ጉዳይ ነበር ዲቁናው እስካላቸው ድረስ? ነው ማውገዝ ተቀዳሚውና
ቀላሉ ስለሆነ? አንዳች ከበጎ የወጣ ሥራ እንኳን ሰርተው ቢሆን እሺ ግን አኮ ለዘመናት ስቃይ ውስጥ
የነበሩ በሽተኞችን፣ ችግረኞችን ለመታደግ ነው ፀጋቻን የተጠቀሙበት! አባ ለእንደኔ ያለው ብዙ
የማይገቡኝ ነገሮች በቤተክርስትያን ቢኖሩም በጎ ነገርን የሚቃወም ሁሉ ግን ከእግዚአበሔር እንዳልሆነ
አውቃሉሁ፡፡ እኔ ብቻም ሳልሆን ጤነኛ አእምሮ ያለው ሁሉ ያውቃል፡፡
የመምህር ግርማ በዲቁና ማጥመቅ አንድ የሰማሁትን ታሪክ ትዝ አስባለኝ፡፡ አባ እርሶ ታርኩን በትክክል
ያውቁታል፡፡ ታሪኩን በትክክል አላስታወስኩት እንሆን ያርሙኛል፡፡ መሠረታዊ ነገሩ ግን እንደዚሁ ነው፡፡
የሆነው በታላቁ የቤተክርስቲያን ሰው በአትናቲዎስ ዘመን ነው ተብዬ የተነገርኩት፡፡ ታላቁ አባት
አትናቲዎስ ሕፃኑ ራሱ ይሁን በወቅቱ የሕጻኑን ጥምቀት ያፀደቀው ካህን ይሁን በትክክል አላስታውስም፡፡
ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ ከክርስቲያን ወገን የሆነ ሕጻን ውሎው ከአሕዛብ ልጆች ጋር ነበርና ለአህዛቦቹ
ልጆች ስለክርስቶስ፣ ጥምቀትና ክርስትና እየነገራቸው ሕጻናቱ አምነው ያንን ሕጻን አጥምቀን አምነናል
ይሉታል፡፡ እሱም በንጹኅ ሕሊናው ልጆቹን ያጠምቃቸውና ወደ ካህኑ ወስዶ ስለሆነው ነገር ሁሉ ለካህኑ
ይነግረዋል፡፡ ያ ካህን ሁለተኛ እነዚያን የአህዛብ ልጆች አላጠመቃቸውም ሕጻኑ በአጠመቃቸው ጥምቀት
የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን አጸደቀ እንጂ፡፡ ከሌላውም ጥምቀት በላይ ይህ የእግዚአበሔርን ልጅነት
የሚያሰጥ ጥምቀት ነው፡፡ ግን እግዘአበሔር ካለ ማን ሊያግድ ይችላል?! ይህ ነው የታላላቆቹ አባቶች
እምነት! ዝም ብሎ ተነስቶ ወግና ባሕልን እየደባለቁ ለራስ በሚመች አይነት የእግዚአብሔርን ሥራ
መንቀፍ ለሕሊና ዕዳ ከመሆን በቀር ትክክል አይደለም፡፡
ብዙ ሌሎች የተባሉ ነገሮች ጥናት በተባለው ላይ የቀረቡ አሉ፡፡ የሚኖሩበት ቤት ዘመናዊነት ተነስቷል፡፡
እውን መምህሩ ከሕዝብ በሰበሰቡት ገነዘብ ነው ይህን ቤት የገዙት? ለብዙ ዘመናትስ ብዙ ሺ ሕዝብ
እያገለገሉ በዚሁ አገልግሎታቸው ከቤተክርስቲያን ሰዎችና ከአንዳንድ ግፍ ተናጋሪዎች ጠንቋይ ናቸው
ተብለው የሚያከራያቸው እንኳን አጥተው ሲንከራተቱ የነበሩ ሰው አልነበሩም? በተሰጣቸው ፀጋ
ለሚሰጡት አገልግሎት ሳንቲብ ሰጠሁ የሚል አለ? በሚሊዮን ቢያወጣ የመዳን ተስፋ የሌለው በሽተኛና
ልዩ ልዩ የኑሮ ውስብስቦች ያሉበት አይደለም እያዳነ ያለው? ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በራሱ ተነሳሽነት
ችግራቸውን አስተውሎ ደስ ስላለው ብቻ ሚሊዮን አውጥቶ ቤት ቢገዛላቸው ምን ይገርማል? የእሳቸውስ
በዘመናዊ ቤት መኖር ሐጥያት ነው? ደግሞ እግዚአበሔር ፈቀደ! ትዕግስታቸውን ተመለከተ! በደሳሳም ኖሩ
በዘመናዊ ቤት እንደማይለወጡ ያውቃልና! መቁጠሪያ ይሸጣሉ? አዎ ግን አኝህ ሰው መኖር የለባቸውም?
ቤተክርስቲያኒቷ ደሞዝ ትከፍላቸዋለች? እንደሰማነው የቤተሰብ አስተዳደሪ ናቸው፡፡ ደግሞስ
መቁጠሪያውን በነጻ ነው የሚሰሩት? በቅጥረ ቤተክርስቲያን መሸጥ መለወጥ አይቻልም? አዎ ትክክል
ነው! ግን ምን ዓይነት ዕቃ? መንፈሳዊ መጻሕፍት? መንፈሳዊ መዘሙሮችና ትመህርቶች? ሌሎች
መንፈሳዊነት ያላቸው መገልገያዎች? አዎ ሁሉንም ከተባለ ደግሞ እንደዛው መሆን አለበት፡፡ መምህር
ግርማ ጋር ብቻ ሲመጣ አይደለም ጥፋት የሚሆነው፡፡ ለሌሎቹም ስህተት ሀኖ ዝም ስለተባሉ መምህር
ግርማም ዝም ይባሉ እያልኩ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የንግድ ሳይይሆን የአገልግሎት ነው ብዬ ስለተረዳሁት
እንጂ፡፡ ስህተት ከሆንም የመምህር ግርማ አግባብ ባለው እርምት በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል
ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም ለማስተካከል በሚያስቸግሩ ሁኔታዎች በዚያው ደብርና በሌሎችም እየተካሄዱ
ያሉ ንግዶችን እንዴት ማየት አልቻሉም አጥኚዎቹ? የወይራ ዘይት ግን ሲሸጥ አላየሁም፡፡ ሰዎች ገዝተው
ያመጡትን ሲባርኩ እንጂ፡፡ ከፋብሪካ የወጣ ዘይት? ታዲያ ከሰማይ የወረደ መሆን አለበት? የወይራ ዘይት
በዘይትነቱ ዘይት ነው! ከፋብሪካ መውጣቱ የወይራ ዘይትነቱን ይቀይረዋል? እንደውም ጥራቱን የጠበቀ
ያደርገዋል እነጂ፡፡ ቅባ ቅዱስ የሚሆነው በጸሎት ስለሚባረክ ነው፡፡ መቁጠሪያ ከውጭ አትግዙ ከእኔ ብቻ
ግዙ አላሉም ገዝተው ሲያመጡ ባርከው ሲሰጧቸው ግን እናያለን፡፡ ግን ለምን የምናውቃትን እውነት
እንክዳለን? ባለማወቅ ከሆነ በጥርጣሬም ቢሆን ገማልያ ክርስቶሳውያንን ይከሱ የነበሩትን የመከራቸውን
አንኳን ምክር ለማደመጥ እንሞክር፡፡
ከሕዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ገብቷል? እኮ ካለም በማስረጃ ቢሆን አይሻልም? በተቃራኒው
ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለቤተክርስቲያን አስገብተዋል! በተረጋገጠ ሰነድ! ይልቁንም እሳቸው
የሚያስገቡትን ገቢ ለመቀራመት ብዙዎች ሲሞክሩ የእሳቸው ለእግዚአብሔር ቤት የተሰበሰበ የሕዝብ
ገንዘብ በምንም ዓይነት በግለሰቦች እጅ አይወድቅም የሚለው ፅንፈኛ አቋማቸው ብዙ የቤተክርስቲያን
ሰዎች ነን በሚሉ ሰውች ጥርስ ውስጥ እንዳስገባቸው እንታዘባለን፡፡ ሌሎችንም ደብራት ትተው ሁሉንም
የሳምንት ጉባዔያቸውን እስጥፋኖስ ያደረጉበት ምክነያቶች አንዱ እሳቸው ለቤተክርስቲያን የሚያሰገቡትን
ገንዘብ አለአግባብ ሲጠቀሙ ስለሚበሳጩ ነው፡፡ እስጥፋኖስ ግን በተለይ ከቀድሞው አስተዳዳሪ ከነበሩት
ጋር በነበራቸው የፍቅርና የመተሳሰብ ግንኙነት ጉባዔውም በአግባቡ እየተካሄደ የሚገኘውም ገቢ በትክክል
መግባቱን በሰነድ/ካርኒ እየተሰጣቸው ነበር፡፡ እስካሁንም የገንዘብ አሰባሰቡ ሂደት ቀድሞ በነበረው አሰራር
ስለቀጠለ የእስጥፋኖስ ጉባዔ ገንዘብ እዛው ተቆጥሮ ካርኒ ይቆረጥባታል፡፡ ይህ ግን በአሁኑ አስተዳደር
የተወደደ አይመስልም፡፡ የአሁኑ አስተዳደር ሰሞኑን ያደረገው ድርጊትም ብዙዎቻችን እንደምንረዳው
ዋነኛው መንሰዔ ከዚሁ የገንዘብ ጉዳይ ጋር ይመስለናል፡፡ ሌላ ሌላውን ሳይጨምር የቀድሞው አስተዳዳሪ
በነበሩት ጊዜ መምህር ግርማ የሚያስተምሩበት ጉባዔ ለቤተክርስትያኗ ሕንጻ ማሳደሻ ብቻ ከአንድ
ሚሊየን ሁለት መቶ ሺ ብር በላይ በተረጋገጠ ሰነድ አበርክቷል፡፡ በእንዲህ ያለ ሕብረት የተሰራን በጎ
ሥራን ለማጥላላት አጥኚ ነኝ ያለው በዛሬው የደብሩ አስተዳዳሪ የሚመራው የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ግን
የቀድሞው አሰተዳዳሪ የነበሩትንም በጽኑ ይኮንናል፡፡ ግን ለምን? ሕሊና እያወቀ የሚሸረብ ሴራ ለንስሐ
እንኳን ይመቻል? አባ አኛ ተራዎቹ ይሄንን አንደፍረውም! ነው ወይስ ወደ ቤተክርስትያን ጠጋ ብለን
ሚስጥሩን ብንረዳ ድፍረትን እናገኝ ይሆን? ነው ወይስ በጎ የሚባለው ነገር እኛ ከምናውቀው ውጭ
ነው?አባ ግን አኮ እግዚአበሔር ለእኛም ማስተዋሉን ሰጥቶናል! ሕሊና ከሳሽም ፈራጅም ነው! ሌሎችም
ለክስ የቀረቡ ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ አባ እውነትን አለመረዳት ይኖራል ከአወቅናት በኋላ ግን ብንክዳት
ከሳሽም መስካሪም ፈራጅም የሆነው ሕሊናችንን እንደበቀው ዘንድ አይቻለንም!
እንደሰው ስህተት እንኳን ቢኖር ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ ያለ አለ? አባ እኔ በበኩሌ ይሁዳ ክርስቶስን
አሳልፎ ሰጠ ብዬ ለመክሰስ አቅም የለኝም፡፡ እኔም በዘመኑ ብኖር ከይሁዳ ወይም ሌሎች በክርስቶስ ላይ
አጃቸውን ከሰነዘሩት እንደ አንዱ አለመሆኔን ማረጋገጥ አልችልምና፡፡ እውነትን ካለመረዳትስ ቢሆን
ምህረት አለኝ፡፡ ግን ከሕሊና ክፋት ከሆነ ለመጸጸትም (ለንስሀም) ይከብዳል፡፡ ይሁዳም ሞክሮ ነበር፡፡
ከሕሊናው ክፉ የሆነ ሰይጣንን የሚወክል ባሕሪ እንዳለው አስባለሁና፡፡ ወደ አእምሮ አንዴ የገባች
እውቀት በሁለት መንገድ ልትካድ ትችል ይሆናል፡፡ አንድ ከሕሊና ክፋት፣ ሁለት ከስጋ መሰሰት (ለጥቅም
ወይም በፈርሀት)፡፡ ከስጋ መሰሰት የምተመጣዋ ክደት የጴጥሮስን አይነት ልትሆን ትችላለች፣ ከሕሊና
ክፋት ግን የምትመጣዋ የይሁዳ አይነት ትሆናለች፡፡ በሕሊና ያልበደለ ግን ሁሌም ተስፋ ያለው
ይመስለኛል፡፡ እውነትን አንኳን ቢሳሳት ያወቀ ዕለት ሕሊናው የእውነት ምስክር ለመሆን ብቁ ናትና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ እረዳዋለሁ! አባ አባክዎን እውቀቱ ሁሉ እርሶ ጋር አለ ግን እንዲሁ እንዳወቁት
ስለሕሊና ፍርድ የዚህንም ሌሎችንም የበቤተክርስቲያንና የሚመሩትን ሕዝብ ነገር ይዳኙ፡፡ ሥለ ሕሊናና
ዕውነት ብዙዎች ከእርሶ ጋር እንቆማለን!
እግዚአብሔር የምናስተውልበትን አእምሮ ይስጠን! ለማይረባ አእምሮም ከመዳረግ ይሰውረን! የሠላም
አመላክ ከሁላችን ጋር ይሁን! አሜን!
ከሕሊና ፍርድ ናፋቂው አንዱ

ይድረስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተናግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ብፁዕ አባታችን፡ ከዚህ በፊት የጻፍኩልዎት ደብዳቤ ይደረስዎት አይድረስዎት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን እንደደረሰዎት እገምታለሁ እኔ ለአንባብያን በማህበራዊ ድህረገፆች እንዲነበብ ባደርገውም በደብዳቤው መልዕክት የተሳቡ አንዳንድ ሰዎች የእኔን ፍቃድ ጠይቀው በቀጥታ በፋክስ እንላኩልዎት ነግረውኛል፡፡ ጉዳዩ ዛሬ ደግሜ ከማነሳው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የበፊቱንም ደብዳቤ በድጋሜ አንባብያንም ይሁኑ እርሶም ማመሳከር ትችሉ ዘንድ ከዚሁ መልዕክት ጋር አያየዛለሁ፡፡ ከጉዳዩ መመሳሰል ባሻገር የወራቶቹም መመሳሰል ነገሩን በውል ላስተዋለው አስገራሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ወራት በመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የጾምና ጸሎት እንዲሁም የንስሃ መቀበያ ወቅት እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ ልክ የዛሬ ዓመት በዚሁ የጾም ወቅት ተከስቶ የነበረ (እንደውም የዛሬ ዓመት በጌታ ሕማም መታሰቢያ ሳምንት በነበረው የጾሙ ጊዜ ነበር) ጉዳይ ዛሬም ተከስቶ ሳየው ተገረምኩ እናም ተመሳሳይነት ያለው መልዕክት በድጋሜ ለእርሶና ለቤተክርስቲያኒቱ የውጭ ግንኙነጽ ኃላፊ እንዲሁም ለትዝብት ለሕዝብ ማስተላለፍ ፈለግሁ፡፡ ይህ ጉዳይ የመልአከ መንክራት (መምህር)ግርማ ወንድሙን አገልግሎት ይመለከታል፡፡
ሰሞኑን በአቡነ ገሪማ መምህሩን አስመልክቶ እንደተጻፉ የሚያሳዩ ሁለት ተቃራኒ መልዕክት ያለቸው ደብዳቤዎች ለሕዝብ በማሕበራዊ ገጾች በመድረሳቸው የዛሬ ዓመት ተከስቶ የነበረው አይነት ወዥምበር በሕዝብ ዘንድ ፈጥረው ታላቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆነው ሰንብተዋል፡፡  የመጀመሪያው ደብዳቤ ከሰባት ወር በፊት እንደተጻፈ የሚያመለክት ሲሆን ደብዳቤው ለመምህሩ ዕውቅና የሰጠና አገልግሎታቸውንም ዓለም ዓቀፍ እንዲሆን የፈቀደ ሲሆን በቅርቡ በተመሳሳይ ፊርማና ማህተብ የወጣው ሌላ ደብዳቤ ደግሞ የበፊቱን በማጭበርበር የወጣ ብሎ የሚከስና የሚያወግዝ ነው፡፡
አሁን ጥያቄው የመምህሩ ችግር ወይንስ የእርሶና የፀሀፊው ሊቀ ጳጳስ ጽ/ቤት ችግር ነው የሚል ነው፡፡  መምህሩ በተጭበረበረ ማህተብና ፊርማ ሌላ ቦታ ያሰሩት ደብዳቤ ከሆነ በእርግጥም መምህሩ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ግን ከእርሶ ጽ/ቤት የወጡ ደብዳቤዎች ከሁኑ መምህሩን የሚያስጠይቃቸው አንዳች ጉዳይ አይታየኝም፡፡  ደብዳቤዎቹ ግን በተጭበረበረ ማህተብ የተጻፉ አይመስሉም፡፡ ፊርማውምና ቲተሩም  ቢሆን የሊቀ ጳጳሱ የራሳቸው እንደሆነ አናያለን፡፡ እነዚህ ተቃራኒ መልዕክት ያላቸው ደብዳቤዎች እንዴት በአንድ ሰው ፊርማ ወጡ ለሚለው የብዞዎች ግምት የጸ/ቤቱ እንደሆነ እንጂ የመምህሩ እንደሆነ አያሳይም፡፡ በተመሳሳይ የዛሬ ዓመት ከዚሁ ከእርሶ ጽ/ቤት የመምህሩን አገልግሎት ያወገዘውና ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ያገደው ደብዳቤ ከፍተኛ የሆነ ግድፈትና  የጽ/ቤቱን ደረጃ የማይመጥን በልዩ ሴራ የደብዳቤን ይዘት፣ ሥርዓትና ቅደም ተከተል እንኳን በማያውቁ ግለሰቦች እንደተጻፈ አንበበናል፡፡ የአሁኖቹም ቢሆኑ ከቤተክርስቲያን መሠረታዊ መርሆ ወጣ ባሉ የጎደፉ ሕሊናዎች ሊሆኑ እንሚችሉ አንዳንድ ቃላቶችንና የሁኔታዎችን ሂደት እናያለን፡፡  
የመጀመሪያው ደብዳቤ ስሕተት ነው ከተባለና ሁለተኛው እውነተኛ ሆኖ የመምህሩ አገልግሎት እውንም የሚወገዝ አይነት ከሆነ መምህሩ በይፋ የሚሰጡትን አገልግሎት በፖስታ በሚታሸግ ደብዳቤ ብቻ  ሊያውም ለማይመለከተው ሁሉ (አገልግሎትዎ ስህተት ነው ከተባለ የሚመለከተው በመጀመሪያ መምህሩን ነው) የጅምላ ደብዳቤ መጻፍ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው በፊት ለተፈው ስህተት ለተባለው ምላሽ ብቻ ከሆነም የበፊቱ ለሚመለከተው ሁሉ ይላልና ይሄም ለሚመለከተው ሁሉ ቢባል ችግር የለውም ካልንና የመምህሩ አገልግሎት ግን ስህተት የለውም ተብሎ ከታመነ ሁለተኛው ደብዳቤ ከመጻፉ በፊት ቢያንስ የበፊቱ በምን አግባብ እንደሆነ ተጠንቶ መምህሩም ተጠይቀው ስህተቱ ይት ጋር እንዳለ ከተረጋገጠ በኋላ ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ ማንም ይጻፈው ማንም የመምህሩ አገልግሎት ግን እስከታመነበት ድረስ እንደተባለው የበፊቱ ከጽ/ቤቱ ያልወጣ ወይም አግባብ ባልሆነ ሁኔታ የወጣ ከሆነ ደብዳቤውን ማውገዝ ተገቢ ነው በምትኩ ግን የመምህሩን አገልግሎት የሚደግፍ ሌላ ትክክለኛ ደብዳቤ መስጠት የበጎ ሕሊና አሰራር ከመሆኑም ባሻገር አጋጣሚዎችን ለራሳቸው ፍላጎት ሊጠቀሙ የሚያስቡትን በር መዝጋት ነበር፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ይዘት የመምህሩን አገልግሎት አንቀበልምና ፍቃድ አለኝ ቢሏችኁ አተቀበሏቸው ጭምር ይመስላል፡፡ በዚህ የይዘት ትርጉም ደግሞ መምህሩ አሁን በይፋ  ተጻፈላቸውም አልተጻፈላቸውም በአለም አቀፍ ደረጃ እየሰጡት ያለው አስተምህሮትና  የፈውስ አገልግሎት በቤተክርስቲያኒቱ ሥምና በእርግጥም በቤተክርስቲያኒቱ አብያት ቅጥር ውስጥ እንደሆነ ስናስብ አገልግሎታቸውን በይፋ መንቀፍ ድፍረት በልታጣ ነበር፡፡ በይዘትና ደረጀ ሚዛን ሲመዘኑ ግን ሁለቱም ደብዳቤዎች የተንገዳገዱና ነገር እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ መምህሩ ግን የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም፡፡
እኔ የመምህሩን አስተምህሮትም ሆነ የፈውስ አገልግሎት በአትኩሮትና በመገረም በአካልም በጉባዔያቸው በመገኘት  ጭምር የምከታተል ሰው ነኝ፡፡ የመምህሩ አስተምህሮት ዛሬ እንደ አሸን የፈሉት ተራ ሰባክያን አስተምህሮት ከጩኸት የዘለለ ሕይወትን ለመለወጥ አቅም የሌለው ሳይሆን በትኩረት ለአዳመጠው ጥልቅ የሆነ ከልዑል አምላክ ዘንድ በምትፈስ ጥበብ/ፍልስፍና የተዋበ አእምሮና ሕሊና እውነትን እንዲጋፈጧት የሚያስገድድ ነው፡፡ በተግባር የሚያደርጉት የልዑል እግዚአብሔርን ኃይል በገሀድ ማሳየትና የጠላታችንን ሴራ ማጋለጥ የአገልግሎታቸው ምስክሮች ናቸው፡፡  ይህ ነበርና ጥንታዊው የሐዋርያት ክርስትና፡፡ ዛሬ ግን ጰውሎስ እንህ አለ፣ እንዲህ አደረገ፤ ዮሐንስ እንዲህ አለ እንዲህ አደረገ ከሚለን በቀር እነዚያ ታላላቅ ተአምራትን በጌታ ሥም የሚያደርጉትን የሚያደርግ ለመኖሩ ማረጋገጫ እንኳን አጥተናል፡፡ በአንጻሩ ቀሚሳቸውን አስረዝመው እጅጌያቸውን አስፍተው በከተማ በመንገማለል በአለባበሳቸውና በአነጋገራቸው ሊከብዱብን የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእንዲህም አይነት ሳይገደቡ በቤተክርስቲያንና በሕዝብ ገንዘብ የራሳቸውን ዓለም የሚቀጩት ይሄ ለቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደርና ሥርዓት አደገኛ ኪሳራ ሆነዋል፡፡   ይህን እውነት ሕሊናችን ሊክደው አይችልም፡፡ በጎ ነገርንና ለልዑለአማላክ መገዛትን በቀጥታ የሚናገሩት ግን መምህሩን ጨምሮ በበጎ አይን አይታዩም፡፡ መምህሩ በልዑል አማላክና በቅዱሳኑ ሥም ከክፉ መናፍስት በመናፍስቱ ከሚመጡ ደዌያትንና የኑሮ ምስቅልቅሎች የተጨነቁትን መታደጋቸው አደገኛ ጠንቋይ አስማተኛ አሰኝቷቸዋል፡፡ እርግጥ አስማተኛ መባላቸውን እኔም ብሆን ቅር የምሰኝበት አይደለም፡፡  የመምህሩ አስማት ግን ሌሎች ክፉዎቹ የሚጠሩት ሳይሆን፣ ኃያሉና ጉልበትን ሁሉ የሚያንበረክከው የክርስቶስና ስሙ በስማቸው የታተመው የቅዱሳኑ ግን ሥም እንደሆነ በአየናችን አይተናል እኛም እንድንሞክረው አድርገው ብዙዎች በሥሙ ክፉውን መንፈስና ጠንቆቹን እተዋጉት ይገኛሉ፡፡ ይህ አስማተ መለኮት መተተኞቹ የሚቋቋሙት አይደለም፡፡ መምህሩ  ጠንቋይና መተተኛ ላለመሆናቸው እኛ ምስክሮች ነን፡፡ ችግሩ ቤተክርስቲያንን የወረሯት መተተኛ ደብተራዎችና ጠንቋዮች ሥራቸው እየከሸፈባቸው ስለሆነ የመምህሩን ከምድረገጽ መጥፋት አጥብቀው ይፈልጉታል፡፡ መጻሕፍ ይጠቅሳሉ፣ ሴራ ይሸርባሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ይሞክራሉ፡፡ ግን የልዑል አማላክን ክንድ ሊያጥፍ የሚችል ማን ነው! ሌሎች የተደነባበሩትን ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ አልቀረባቸውም ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል በማለት የመምህሩን የማዳን ፀጋ ሊያጣጥሉ ይሞክራሉ፡፡ ጌታም ሆነ ሐዋሪያቱ ምልክትን እንድንመረምር አስጠነቀቁን እንጂ አይተን እንዳናምን አልተናገሩም፡፡ ጌታንም ሆነ ሐዋሪያትን የተቀበሏቸው ብዙዎች በአዩት ተዓምር እንጂ በትምህርታቸው እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ደግሞ በተግባር የማይገለጥ እምነት የለመድንው ተረት አይነት እንጂ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ በሥሙ ለሚያምኑት ሁሉን ያደርጉ ዘንድ ሥልጣንን እንደሰጣቸው ሲታወስ ምንም ማድረግ የማንችል የመተተኞችታ የክፉ መናፍስት መጫወቻ የሆንን ግን ክርስቲያነ ነን ብለን የሚናምን እስኪ ለክርስትናችን ምልክቱ ምንድነው?
እውነት እንደ መምህር ግረማ ብዙዎችን ከዘመናት ጭንቅ የገላገለ ማን ነው? ብዙዎችንስ እምነታቸውን እንዲያውቁ ያደረገ ማን ነው? ብዙዎቻችን እኮ ክርስትናው ከተረት ያለፈ ትርጉም አልሰጠን ብሎ ነበር! የየትኛው ሰባኪ አስተምሮት ነው ብዙዎችን ከሌላ እምነት ወደክርስትናው የመለሰ? ሰብከት ተብዬዎች ብዙዎች ጦርነትን መለያየትን የሚያውጁ አይደሉም እንዴ! ማነው እንደ እኚህ መምህር ዘር ሳይል ሀይማኖት የተሰጠውን ፀጋ ለሁሉም በእኩል ሊያበረክት የወደደ፡፡ ዘረኝነትና ጎጠኝነትን የሚያስፋፉ አይደሉም እንዴ ዛሬ ቤተክርስቲያኒቱን የወረሯት፡፡ ማን ነው እን እኚህ መምህር ለቤተክርስቲያን ልማት ተሳታፊ የሆነ፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለቤተክርስቲያን ዛሬ እያስገባ ያለው በእሳቸው ትምህርት አይደለም እንዴ? ማንው ይህንን ሁሉ ገቢ ለቤተክርስቲያን እያስገባ በነጻ አንዳች ደሞዝ እንኳን ሳይቀበል የሚያገለግል፡፡ በየክብረ በዓል በአሰልቺ ሁኔታ የሚሰበሰብን ገነዘብ  ካላካፈላችሁን፣ አበል ካልከፈላችሁን የሚሉ ሰባክያንና መዘምራን አይደሉም እንዴ ዛሬ የሞሉን፡፡ የጌታን ትዕዛዝ በለመጠበቃቸው ግን መካኖች እንደሆኑ አይረዱም፡፡ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ ይላልና፡፡ እንደመምህሩ ያለ ጸጋ ሊኖረው የሚፈልግ ገዘብን ወዶ ሊሆንለት አይችልም፡፡
አባ በእናንተስ መካከል (በጳጳሳቱ ማለቴ ነው) ስለመምህሩ ለምን ይሄን ያህል መለያየት ተፈጠረ? ጥሩና አስተዋይ መሆናቸውና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ብዙዎቹ ጳጳሳት መምህሩን በትክክልም ሲደግፉ በጉባዔያቸውም እየተገኙ ሕዝቡን ሲባርኩ አይተናል፡፡ ደብዳቤዎቹ ማን እንደጻፋቸውም ስለማናውቅ ተጭበረበሩ እንበል፡፡ ግን እኮ አይናችን እያየ ጆሮአችንም እየሰማ ከእናነተ እኮ የመምህሩን አገልግሎት አለም አቀፋዊነት በአንደበታቸው ነው የተናገሩት፡፡ ይሄም ፊልም ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ እኛ ግን በአካል ተገኝተን የያየንና የሰማን ምስክሮች ነን፡፡ ደግሞ እግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት የማንንም ፍቃድና እውቅና ማግኘት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ጥንታዊው የሐዋሪያትም ጉዞ በካህናትና በነገስታት ፍቃድ ሳይሆን ከአምላካቸው የተሰጠውን ትዕዛዝ ብቻ ከመፈጸም ነበርና፡፡
አባ አሁንም አላለሁ ሕሊና የልዑል አምላክ እንደራሴ ነው፡፡ እውነት ግን ከሕሊናም በላይ ስለሆነች በልዑል አምላክ የምትመሰል ናት፡፡ እግዚአብሔር እውነት ነውና፡፡ በሕሊናችን ካልበደልን እውነትን ብንስታት እንኳን የእውነት ባለቤት እግዚአብሔር እውነትን እንድናውቃት ያደርጋል፡፡ ሁሌም አነሳዋለሁ በሕሊናው ምንም በደል የሌለበት ግን እውነትን ባለማወቁ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረውን ሳውል (ቅዱስ ጳውሎስን)፡፡ በተቃራኒው እውነትን አውቆ ግን ሕሊናውን በሰላሳ ብር የሸጠውን ይሁዳንም እናስተውል፡፡ እውነትን ለመቀበል እያወቁ እምቢ ያሉትን የአይሁድ ካህናትንም፡፡ ጳውሎስ ስለሕሊናው ምርጥ የክርስቶስ ምርጥ ሊሆን ተመረጠ እውነት በተገለጠችለት ጊዜ ሕሊናው እውነትን ሊክድ የሚችል አልነበረምና፡፡    
አባ አሁንም አላለሁ ሁላችሁም የሕሊናችሁን ንፅሕና እንድትመረምሩ፡፡ በስልጣንና በከፍተኛ ማዕረግ መቀመጥ እንደ አይሁድ ካህናት ክርስቶስን የሚያስክዳችሁ ምቾት አይሁንባችሁ፡፡ ስለ ሕዝብና ስለትውልድ መጨነቅን ልመዱ፡፡ የድህነትን መንገድ ለማሳየት መነገድ የጠፋበትን ታች ወርዳችሁ ምሩት፡፡ ክርስትናው ወግና ልማድ ብቻ ሆኖ ሕዝብ በክፉ ኃይል እንደወደቀ አስተውሉ፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር ክብር ሕዝብ ለክፉ መንፈስ እንደተገዛም እዩ፡፡ ጠንቋዮችና ደብተሮች ከፍተኛ ክብር አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱም ከፍተኛ ስልጣን ላይ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሲያስፈራሩን ቆይተዋል! ዛሬ ግን ሊቋቋሙት የማችሉትን እኛም ታጥቀናል፡፡ የዛሬ ዓማት በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የነበረው የመምህሩ የማስተማሪያና የፈውስ አገልገሎት መስጫ መድረክ ከነቅዱሳን ሥዕላቶቹ ድምጥማጡ ሲጠፋ ከጠንቋዩች፣ ቃሊቻዎች፣ ሌሎችም ጣዖት አማላኪዎች እየተሰበሰቡ የሚመጡ የጣዖት ማመለኪያ እቃዎች የሚጣሉባት አንዲት ትንሽ ክፍል ግን አንዳች አልተነካችም፡፡ ሰይጣን ነብረቱን ምን ያህል እንደሚጠብቅ ብዙዎቻችን አየን፡፡ ዛሬም ድረስ በዚያው ጊቢ ያቺ ክፍል ብቻዋን አለች፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው  ያለው ፈላስፋው እውነት ነው፡፡ አስደንጋጭም ነው! አንዴ ለማይረባ አእምሮ ከተጣልን በምን ማሰብ እንችላለን፡፡ ጌታን በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ባሉት ጊዜ የተናገረው አሳዛኝ መልዕክትም በአእምሮዬ መጣ፡፡ "እኔ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን የማወጣ ከሆነ ልጆቻችሁ በምን ያወጧቸዋል" አለ፡፡ አዎ በጌታ ሥም ማመን ካልቻልን በምን ክፉውን ልንቋቋመው እንችላለ፡፡
ብዙ ጉዳዩች በአእምሮዬ አሉ እዚሁ ላይ ላቁም ግን ለሁለተኛ ጊዜ እለምንዎታለሁ፡፡ ሥለ ሕሊና ፍርድ ራስዎ በይፋ ይናገሩ፡፡ ስለመምህሩም ስለሌላውም የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ፡፡ እኛም ስለሕሊናችን አገልጋዮች እንሆናለን፡፡ አምላክም እውነትን እንከተላት ዘንድ እንደ ቅዱስ ጰውሎስ የአይናችንን ቅርፊት ያስወገድልናል! በእውነትም ተጉዘን መንግስቱን እንወርሳለን፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር አእምሮአችንን ይክፈት!
አሜን
የታላቋ ቀን ልጅ መጋቢት 21 2006 ዓ. ም
 

Saturday, December 28, 2013

በከፊቾ ዞን የጽላት ዝርፊያና ቀበኞቹ


"ባለሃብቶች በእድሳት ስም ቤተ መቅደስ ዘልቀው ጽላት ይቀይራሉ"
tabot
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በከፊቾ ዞን በጥንታዊ አድባራት ጽላት መዘረፉን እናውቃለን ያሉ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ገለጹ። የዜናው ምንጮች የዞኑ አገረ ስብከት በዞኑ በሚገኙ አድባራት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል። ዝርፊያውን የሚያካሂዱት “ባለሃብቶች” መቀመጫቸውን አዲስ አበባና ጅማ ከተማ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ነዋሪነታቸው ቦንጋና ጊምቦ እንደሆነ የሚገልጹት የዜናው ምንጮች “ቀበኞች” በማለት የሚጠሯቸውን የጽላት ዘራፊዎች የዝርፊያ ስልት ተናግረዋል። በመጀመሪያ እድሜ ጠገብ የሆኑትን አድባራት ይለያሉ። በቃፊሮቻቸው አማካይነት መረባቸውን ዘርግተው ሰዎችን ያጠምዳሉ። ህዝበ ክርስቲያን በሚሰበሰብበት ወቅትና ዓመታዊ የበዓላትን ቀን መርጠው በርዳታና በእድሳት ስም ውዳሴ ይቀበላሉ።
በዞኑ የሚገኙት አቢያተ ክርስቲያናት እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በርካታ ጥንታዊ ቅርስም እንዳላቸው የሚጠቁሙት ክፍሎች “ያረጁትን አድባራት እናድሳለን በማለት ጥቁር ለምዳቸውን ለብሰው መቅደስ ውስጥ ይዘልቃሉ” በማለት የዝርፊያው ድራማ እንዴት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
ለሃይማኖታቸው የቀኑና የታመኑ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ሲያጋጥሟቸው መቅደስ ውስጥ ተመላልሰው በሚሰበስቡት መረጃ መሰረት አብረቅራቂ ሃሰተኛ ጽላት በመተካት ዝርፊያ እንደሚካሂዱ፣ ለዝርፊያ የሚመችና ስብናው የወደቀ አገልጋይ ሲያገኙም በግልጽ ያሻቸውን አድርገው ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ።
ድርጊቱ የቆየና ሰዎቹም የሚታወቁ እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ “ቀበኞቹ” ካላቸው የገንዘብ አቅም አንጻር እጃቸው ከወቅቱ ጉልበተኞችና የቤተ ክህነት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት በላይ አመላክተዋል። በዚህ ተነሳ “እንፈራለን፤ ፊት ለፊት ለመግጠምም እንቸገራለን” በማለት ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምስጢራቸው እንዲጠበቅ አስጠንቅቀው መረጃውን ለመስጠት ችለዋል።
“ይህንን ዜና ጥቅማቸው የሚነካና ችግር ያለባቸው አካላት ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞች ሊያስተባብሉት ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ዜናው የሚያስደነግጣቸው ክፍሎች የሚወስዱትን የመጀመሪያ ርምጃ ያመላከቱት ተቆርቋሪዎች፣ “የእኛ ጥያቄ ግን ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እውነታው እንዲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የዞኑ አገረ ስብከት ዛሬ ነገ ሳይል በተቀደሱ የማምለኪያ አድባራት ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት ያሳሰቡት ክፍሎች፣ ቀበኞቹ በርዳታ ስም እድሳት ባካሄዱባቸው አድባራት ላይ የሙከራ ምርመራ ቢደረግ ጥቆማው ምላሽ እንደሚያገኝም በርግጠኛነት ተናግረዋል።
በእድሳትና በርዳታ ስም መቅደስ በመዝለቅ ከሚከናወነው ዝርፊያ በተለየ በድርድር የሚካሄዱም ዝርፊያዎች ስለመኖራቸው ያመለከቱት ክፍሎች “ጉዳዩ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ስምና ቦታን ለይተን ለመጠቆም እንቸገራለን” ብለዋል። “መልዕክቱ ለቀበኞቹ፣ ለተባባሪዎቻቸውና የሚሰማ ተቆጣጣሪ አካል ካለ ለነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል። በዞኑ ያሉ የህዝብ ወኪል እንደራሴዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ወስደው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
“የቃል ኪዳን ጽላት ዘርፎ ከማነከስና ሰልሎ ከመሞት ውጪ ሌላ ዕድል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ተቆርቋሪ አዛውንቶች በ2005 መገባደጃ ላይ ዋሻ ውስጥ ተገኘ የተባለ ጽላት የት እንደገባ እንደማይታወቅ አመልክተዋል። ዜናው የመገናኛ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ደርሶ እንደነበር፣ ነገር ግን በማይታወቅ ሁኔታ ተዳፍኖ መቅረቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላትን እስካሁን እንደሚከነክናቸው አመልክተዋል።
ከዝግጅት ክፍሉ
ይህ ዜና ከመታተሙ በፊት ከጥቆማው በተጨማሪ ሰዎችን ለማነጋገር ተሞክሯል። የዞኑን አገረ ስብከት ለማግኘትም ተሞክሯል። ከዜናው ባህሪ በመነሳት ጉዳዩ ሳይጣራ ግለሰቦችን የሚያመላክቱ መገለጫዎችን ከመጠቀም ተቆጥበናል። በተጠቀሰው ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ በርካታ ቦታዎች ነዋያትና ጥንታዊ ቅርሶች እንደሚዘረፉና ለዝርፊያው ተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉት የድንበር ጠባቂዎች መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማ እውነት በመሆኑ ተጨማሪ ጥቆማ ለምታቀርቡልን መድረኩ ክፍት ነው። ከቦንጋና አካባቢው፣ እንዲሁም ከጅማ ነዋሪዎች ለደረሰን ጥቆማ እናመሰግናለን። በዜናው ላይ ቅሬታም ሆነ ተቃውሞ ካለ እናስተናግዳለን።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Friday, November 15, 2013

ወላዲተ አምላክ ድንግል እመብርሃን



ወላዲተ አምላክ ድንግል እመብርሃን
የሊባኖስ ዝግባ የሳባውያን ፅድ፣
የሰሎሞን ጥበብ የቤተመቅደሱ አምድ፣
የማኑሄ ልጅ ኃይል የፀጉሩ ጎንጉን፣
የኤልሳዕ ማሰሮ የኤልያስ ሰበን፣
የዳንኤል ሕልሙ የኢሳያስ ትንቢት፣
የመስቀል ስጦታ የዮሐንስ እናት፣
የያቆብ መሰላል የሕይወት አሳንሳር፣
የመላዕክት ንግስት የሰው ልጆች ክብር፣
የወልድ ማህደር የአብ ጥበብ ውጤት፣
ንጺሕተ ንፁሀን የመንፈስ ቅዱስ ቤት፣
የአርያም እህት የስላሴ ዙፈን፣
ትርሲተ መለኮት የኪሩቤል ዘባን፣
ከገነት ለወጣው የአዳም ቃል ኪዳን፣
የተወገደባት የጨለማው ዘመን፣
ወላዲተ አምላክ ድንግል እመብርሃን፡፡
የታላቋ ቀን ልጅ ነሀሴ 19 2005