እውነት ከሕሊና ፍርድም በላይ እንደሆነች እረዳለሁ፡፡ ብዙዎች በህሊናቸው ትክክል ሆነው እውነትን ግን
ስተዋታልና፡፡ በትክክል አባባሌን ይገልጽ እንደሆነ አላውቅም ግን የሳዖል ኋላም ቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ
ያንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ እሱ አስቀድሞ ስላወቀው/ስለተማረው ነገር ብቻ የክርስቲያኖች አሳዳጅ
ነበርና፡፡ ሳዖል ግን ስለህሊናው ትክክል ነበር ምንም እውነትን ባያገኛትም፡፡ በአንጻሩ ሌሎችን ጨምሮ
ራሱ አስተማረኝ የሚለው ገማልያ ሳይቀር እውነትን ቢያውቋትም ሊመሰክሩላት አልፈለጉም ወይም
ፈርተው ክደዋታል፡፡ ከህሊና ፍርድ ወጥተዋል፡፡ እኔን እንደሚገባኝ ሕሊናችንን ካልካድን እግዚአብሔር
እውነትን ለማወቅ ከፈለግን ይገልጥልናል፡፡ ለቅዱስ ጳውሎስ የተደረገለት ይሄው ይመስለኛል፡፡ የእኛ
አቅም ስለሕሊናችን መኖር ነው፡፡ እውነትን ለማወቅ የእግዚአብሔር እገዛ ያስፈልጋል፡፡ እውነትን ግን
መናፈቅ ያስፈልገናል፡፡ እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ደግሞ አብዝተን መፈለግን
ይጠበቅብናል፡፡ ማለትም ለሕሊናችን ማደርን፤ ፍጹማን አለመሆናችንን አወቀን ያላወቅንውን ለማወቅ
መትጋትን፡፡ በተቃራኒው እግዚአበሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ
አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ይላልና፡፡ አንዴ ለማይረባ አእምሮ ከተሰጠን ምን ዋጋ አለን?! የማይረባ
አእምሮ/ሕሊና ያጣ/ ከባድ ነው!
የሕሊና ፍረድና የእውነትን መፈለግ/መናፈቅ ለሰው ሁሉ የሚያሰፈልግ ሲሆን በመሪነት ያሉ ሰዎች፣ዳኞች፣
በተለይም ደግሞ የኀይማኖት አባቶች እጅግ የሚጠበቅባቸው ነው፡፡ እነሱ ስለብዙዎች ይኖራሉና፡፡ በአንዱ
የሐማኖት አባት መውደቅ ምክንያት ብዙዎች ሊወድቁ ይችላሉና፡፡ ሥለትሷ የሕሊና ፍርድ ማጓደል
ከመኖር በስጋ ቢሞቱ ይሻላቸዋል፤ ስለብዙዎች ሕያዋን ናቸውና፡፡ ይህንን ብዙ የሀይማኖት አባቶች
አደርገውት አልፈው ዛሬ ደርሰናል፡፡ አሁን አሁን በሀይማኖት መሪዎች የሚታየው ግን እኛ ተራዎቹ
እንኳን የማንደፍረው ከሕሊና የራቀ ድርጊት (ድፍረት ብለው ይመቸኝ ነበር) ነው፡፡ እርሶ በሚመሯት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሕሊናን የሚያከሱ፣ ምዕመናንን የሚገፉና፣ እንዲህስ ከሆነ ቢቀር
ይሻላል በሚል ሕዝቡን ከአምልኮተ እግዚአብሔር እያራቁ የሚገኙ በቤተክርስቲያኗ በመሪነት ቦታ ያሉ
ሰዎች የሚፈጽሟቸው ብዙ ድርጊቶች አሉ፡፡ አባ ይህንን ሁሉ የምነግርዎት እርሶን ለማስረዳት
አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ ያቁታልና፡፡ ጽሑፌ ለተነሳበት ሀሳብ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ እንጂ፡፡
ቀደም ብለው ሰዎች ብዙ ስላሉባቸው በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጸሙ ግደፈቶች ብዙም ስለማላውቅ
እኔ አስተያየት ሰጥቼም አላውቅም፡፡ አንዳንዶቹም ሰዎች ስለተሳሳቱ የሚያወሯቻ እንጂ እውነት ሆነዋል
ብዬ ለማመን እቸገርባቸው ስለነበርም፡፡ ሰሞኑን ግን እኔው የማውቀው እኛ ተራዎቹ የማናደርገው
የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችና ደብር አስተዳዳሪ ሆነው በተሾሙ ሰው በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን
አንድ ድርጊት ተፈጽሞ ይሄው ሕዝቡን እያነጋገረ ይጋኛል፡፡ እንደውም ይሕንንው ድርጊት በመደገፍ
ከእርሶ ጽ/ቤት ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤም አለ፡፡ ደግነቱ እርሶ አይደሉም የፈረሙት! ይመስለኛ ጉዳዩን
ሰምተውታል፡፡ ይሄውም በደብሩ (ቅ. እስጢፋኖስ) ቅጥር ግቢ ውስጥ ወንጌል ያስተምሩና በተሰጣቸውም
ፀጋ ሰዎችን በርኩሳን መናፍስት ከሚመጡ ልዩልዩ ደዌያትና ሌሎች ውስብስብ የኑሮ ችግሮች ይታደጉ
ስለነበሩት መምህር (መልአከ መንክራት) ግርማ ወንድሙ ጉዳይ ነው፡፡ አባ ፤ መምህር ግርማ በደብሩ
ቅጥር ግቢ እየሰጡ የነበሩትን አገልግሎት ማገድ ሥልጣንና ጉልበት እስካለ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡
ለቤተክርስቲያንም እውን ከመቅናት የተነሳ ድርጊት ከሆነም ሕሊና ስላሰበው ተደርጓልና ከክፋት
አይቆጠርም የቱንም ያህል እውነትን ካለመረዳት ስህተት አንኳን ቢሆን፡፡ የሆነው ነገር ሁሉ ግን ሕሊናንም
እውነትንም በመካድ ስለሚመስል አደገኛ ድፍረት ነው በዬ አምናለሁ፡፡ ሒደቱ ሁሉ ውስብስብ
ተንኮለኝነት የተቀመሙበት ይመስላልና፡፡ መምህር ግርማን ይሁን እግዚአብሔርን እየተዳፈሩ ያሉት ማንን
እንደሆነ ሁላችንንም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነበርና፡፡ መምህር ግርማን ስለነኩ ማለቴ አይደለም፡፡
የወንጌል ማስተማሪያ መድረክ አፈረሱ፣ ቅዱሳን ስዕላት ቀደዱ፣ ሌሎችንም ሥጋዊ ኃይልና ሥልጣን
የሚችሏቸውን ድርጊቶች ፈፀሙ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የሆነው በሰሞነ ሕማማት፣ የክርስቶስ ሕማም
በሚታሰብበት ሳምንት መሆኑ ያሳዝናል/ያስገርማልም፡፡ እንዲህ ያለውን ድርጊት ለእኛ ስታስተምሩን
ሐጥያት ነው በተለይ ደግሞ በሰሞነ ሕማማት፡፡ የቤተክርስቲያን ሰዎች ነን የሚሉት ግን ሲያደርጉትስ?
እውን ስህተትስ ቢኖር እንዲህ ባለ ከመንፈሳዊ ባህሪ በወጣና በጀብደኝነት በሚደረግ ግርግር ለሕዝብ
ማስተዋልን በማይሰጥ ሁኔታ ስህተትን ማረም ይቻላል? ደግሞስ ካልጠፋ ጊዜ ያ ጊዜ ለምን ተመረጠ?
መምህር ግርማ የነበሩት በቅድስት አገር እየሩሳሌም ስለነበር ነው የተመረጠው? የሕሊና ጉዳይ ከሆነ
እሳቸው ባሉበትስ አይቻልም ነበር? በዚያውም ስህትቱን ተናግሮ ሕዝብንም አሳምኖ? እንኳንስ ለዘመናት
ያስተማሩትን መምህር ግርማን ይቅርና በአንድ ጉባዔ የተከሰተ ሕዝብን የሚያሳስት ነገር ከሆነ በተቻለ
መጠን ስህተት በፈመው ፊት ስህተቱን ተናግሮ ማረም ይጠበቃል፡፡ አባ ሁሉንም ነገር አርሶ ያዎቁታል
ማለቴ ሥርዓቱን ሁሉ፡፡ መምህር ግርማ እየተከሰሱበት ያለውን ሁሉ፡፡
የተፃፉትን ደብዳቤዎች ስናነብ ግን ማን በምን አስተሳሰብ ደረጃ እንዳለ ስለነገሩን በሕዝብ ዘንድ የፈጠሩት
ትዝብትን እንጂ የመምህሩን ስህተት አይደለም፡፡ የደብዳቤዎቹ ቅደም ተከተል፣ይዘትና የቃላት አጠቃቀም
ከመውረዱ ጋር ተዳምሮ፡፡ በተለይ ደግሞ ከእርሶ ጽ/ቤት የወጣው ደብዳቤ ሲጀምር ደብዳቤው
ላልተጠየቀበት ጉዳይ ነው የተፃፈው፤ ከተጻፈም ሥርዓትና አግባብ ባላቸው ቃላቶች ቢሆን መልካም
ነበር፡፡ ደብዳቤው ጉዳዩችን በስርዓቱ ከማበራራት ይልቅ በስደብ የታጨቀ ነበር፡፡ ሕገ-ወጥ፣ ሥርዐተ-
አልበኛና የመሳሰሉት ቃላቶች እውን ከእገዳው ጋር በተያያዘ ሊያውም ከቤተክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው?
ኋላ በሕግም እኮ ሊያስጠይቁ ይችላሉ፡፡ ግን ሲጀመር በ28/08/2005 በደብሩ አስተዳዳሪ የተጻፈው
ደብዳቤ የመምህር ግርማን ማገድ ወስኖ ለእርሶ ጽ/ቤት በግልባጭ አሳወቀ እንጂ እገዳውን እንዲያጸናለት
አልጠየቀም፡፡ እና ላልተጠየቀበት ጽ/ቤቱ አፅድቄአለሁ ማለት አለበት? በዚህ አይነት ግልባጭ
የተደረገላቸው ሁሉ አጽድቀናል እያሉ መጻፍ አለባቸው? በግልባጭም ቢደርሰው የእርሶ ጽ/ቤት ደብዳቤ
ለደብሩ የሚፅፍበት ሁኔታ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ኃላፊነት ስላለበት ግልባጭ የተደረገለት ጉዳይ ስህተት
ሆኖ ቢገኝ ለማረም፡፡ ይባስ ብሎ ስንት አመት ሲያስተምሩ ምንም ሳይባሉ ይሄው የእርሶ ጽ/ቤት ደብዳቤ
በአሰቸኳይ ከሚል ልዩ ማሳሰቢያ ጋር ነው የተጻፈው፡፡ አባ እንዲህ አይነቱ ነገር ውስጥ የተሸረበ ሴራን
ለሕዝብ እያሳበቀ እንደሆነ ጸሐፊዎቹ ቢረዱት እንዴት ጥሩ ነበር፡፡
ደብዳቤዎቹ በየኢነተርኔቱ ስለተበተኑ ሕዝብ እያያቸው ስለሆነ ሌሎች ጉዳዮቹን አላነሳም፡፡ ከደብዳቤዎቹ
በተጭማሪም የደብሩ ሰንበት ት/ቤት አጥንቼ አግኝቼዋለሁ የሚለውንም የመምህር ግርማን ክስ
በየኢነተርኔቱ አስነብቦናል፡፡ የሚያሳዝነው ግን አሁንም ጥናት ብለው ባቀረቡት ጽሑፍ የተጠቀሟቸው
ቃላቶች በጣም ከግበረ-ገብነት የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ጥናት የመረጃ አቀራረቡ እንዴት እንደሆነ
ቢጠይቁ እንሱንም ከትዝብት ያድናቸው ነበር፡፡ አንድ የጥናት ሰነድ ሲቀርብ መጠቀም ያለበት መደበኛ
ቃላቶችን እንጂ አንባቢን በሚያስደንቡሩ ስድቦችና አስነዋሪ ቃላቶች ታጅቦ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ
አጠኚው ሲጽፍ እራሱን ገለልተኛ አድርጎ በአገኘው ውጤት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንጂ የራሱን ስሜት
አጠናሁት በሚለው ጉዳይ ቢያስነብብ ልብወለድ እንኳን ለመሆን አይበቃም ምንአልባት አሉባልታ ከሆነ
እንጂ፡፡ ልብወለድም የብዙ ማሕበራዊና ነባራዊ ጉዳዮችን ጥልቅ ግንዛቤ ይጠይቃልና፡፡ በዚህ አጋጣሚ
እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ለሕዝብ ማንነታቸውን ማሳወቅን እንጂ የጥናታቸውን ማረጋገጫ በመተንተን
ጭብጥን ማሳወቅ አይደለም፡፡ ከጥላቻ፣ ከቅናት፣ ከአደመኝነት፣ ከበቀልና ከመሳሰሉት የክፋት በሕሪያት
በተወረሱ ቃላቶች የጥናትን ውጤት መዘገብ ከንቱ ነው፡፡ ድርጊቱ አንኳን እነሱ እንደሚሉት ቢሆን
እውነታንም ያጨልማልና፡፡
አጥኚ ነን ያሉት ግን ሁከት በሆኑ ቃላቶች እውነት ነው ብለው ሊያሳምኑን የሞከሯቸው ጉዳዮች
አንዳቸውም እውነት አለመሆናቸው ነው፡፡ አሁንም ሙሉ ጥናት የተባለው ከኢነትረኔት ሊነበብ ይችላል
ግን አለፍ አለፍ እያልኩ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ መምህር ግርማ ቢያንስ ካህን ናቸው
ከዚህም በላይ ቤተክርስቲያኗ በሰጠቻቸው ማዕረግ በተለምዶ መምህር ግርማ ብንላቸውም መላከ
መንክራት ተብለው ተሰየመዋል፡፡ በዚህም ላይ በእድሜያቸው ብቻ እንኳን አንቱ መባል አያንስባቸውም፡፡
ትልቅን ሰው አንተ እያለኩ ባቀል ራሴን ማቅለሌን ማወቅ አለብኝ፡፡ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ደግሞ
ከዚህም በላይ በሆኑ አክብሮቶች ሰዎችን ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ ጉዳያቸውንም በትክክሉ ለማስተላለፍ
ይረዳ ነበርና፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ አጥማቂ ነኝ ፈዋሽ ነኝ ባይ ይላል፡፡ እሳቸው ስላሉ ነው
ወይስ ሕዝብ ራሱ ስላየ? መምህር ግርማ አጥማቂም ፈዋሽም ነኝ ብለው አይደለም ሰው የአገልግሎቱ
ተጠቀሚ የሆነው፡፡ መምህር ግርማ ከብዙዎች በተሻለ የአምላካቸውን ክብር ያውቁታል፡፡ የሚያድነው
የእግዚአበሔር የስሙ ኃይል ነው! እኔ አገልጋዩ ነኝ (ሁሌም የሚሉት ነው)! ከማለት በቀር እኔ ፈዋሽ ነኝ
ሲሉ ሰምተናቸው አናውቅም፡፡
ለመምህር ግርማ በትክክልም የማዳን ፀጋ እንደተሰጣቸው ሕዝብ በትክክል በተግባር አየ እንጂ በወሬ
እንኳን የሰማው ብቻ አይደለም፡፡ ለምን ሕሊናችንን እንደምንክድ አልገባኝም፡፡ አይነስውር
አላየም?ሽባዎችና አንካሶች አልሮጡም? ሌሎች በሕክምና ተስፋ የተቆረጠባቸው በሽተኞች አልዳኑም? ይህ
እውነት አይደለም? ብዙዎቻችንን ለዘመናት የእግዚአብሔርን ሀልዎት እንኳን ረስተን የነበርነውን ኃይሉን
በገሃድ አሳይተውን ሳንወድ በግዳችንም ቢሆን እንድናምን አድርግዋል፡፡ ከሌላ እምነት ሳይቀር! ይህ
እውነት አይደለም? አኛ አኮ ለዘመናት የተደናገርን ሰዎች ነን፡፡ ይህ በእሳቸው እየተካሄደ ያለው ሐዋሪያዊ
አይደለም? አባ እርሶ ራስዎ እንዲነግሩን እንፈልጋለን፡፡ እውን አሳቸው የሚሰሩት የጥንቆላ ሥራ ነው?
ለነገሩ እንደኔ ላለነው የትኛውም ኃይል ይሁን እንዲህ ያለ ነገር እንዳለ ማወቁ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምንም
አናውቅም ነበርና! የእግዚአብሔርን መኖር እንኳን በአፋችን እንጂ በልባችን ወደ ክህደት የተጠጋው
ጥርጣሬው ነበረብንና፡፡ ሰይጣን የሚባለው በእኔና መሰሎቼ ዘንድ ከነጭርሱም የሌለ ነገር እንደሆነ
ልባችንን ሞልተን የምንናገረው ነበር፡፡ እግዚአብሔርንም እኮ እንደው ስለፈራን (ምን አለባት ካለ በሚል)
እንጂ እንዳለ ስላመነው አልነበረም፡፡ ይሄንን ሁሉ በመምህር ግርማ ምክንያት በገሃድ አይተን እንድናምን
ተገደናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምርጫችንን ማስተካከል የየራሳችን ነው፡፡
አባ እውን ልንቃወመው የሚችል አንድ ስህተት እንኳን ተሰርቷል? ሰዎችንስ እያዳኑ ያሉት
በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ስም አይደለም? መቁጠሪያውስ አርሶ ሳይቀሩ አባቶቻችን የምትይዙት
አይደለም? በዲቁናስ ማዕረግ ሆነው ያጠምቁ የነበረው እውን ስሕተት ነው? እግዚአበሔር ከፈቀደ ደግሞ
ከልካዩ ማን ነው?! እንኳንስ የዲቁና ስልጣን የነበራቸውን መምህር ግርማን ይቅርና የእግዚአበሔር ፈቃድ
በሌላ ክህነት ከነጭርሱ በሌለው ሰውስ ቢሆን ማን ሊያግደው ይችላል? ረጋሚው በለዓም እኮ ነው
የክርስቶስን መምጣት ከዘመናት በፊት ያስተዋለው! ክርስቶስን አሳዳጁ ሳኦል እኮ ነው የክርስቶስ ድንቅ
ሐዋሪያ የሆነው! ሽፍታው አኮ ነው ገነት በመግባት ቀዳሚ የሆነው! በተቃራኒው ስርዐት አለን የሚሉት
ካህናት እኮ ናቸው ክርስቶስን የሰቀሉት፣ ደቀመዘሙሩ የነበረ ይሁዳ እኮ ነው ጌታን አሳልፎ የሰጠ፡፡ ሰዎች
ስርዐትንና ቀኖናን እነሱ በሚመቻቸው እየተረጎሙ መጠቀሚያ ካደረጉትስ? እንደምረዳው መምህሩ
ከጅምሩ በዲቁናቸው ዘምን ያጠምቁ የነበሩት የተሰጣቸውን ጸጋ (ካልተጠቀሙበት ዕዳ ነውና)
ተጠቅመው ወገናቸውን ለመርዳት እንጂ እኔ አጥማቂ ልሁን ብለው እንዳልሆነ ያለፉባቸው ታሪኮች
ምስክሮች ይሆኗቸዋል፡፡ ደግሞስ የቅስናውን ማዕረግ ሰጥቶ አገልግሎታቸውን ማጽናት የቤተክርስቲያኗስ
ኃላፊነት አይደለም? ይህስ ከባድ ጉዳይ ነበር ዲቁናው እስካላቸው ድረስ? ነው ማውገዝ ተቀዳሚውና
ቀላሉ ስለሆነ? አንዳች ከበጎ የወጣ ሥራ እንኳን ሰርተው ቢሆን እሺ ግን አኮ ለዘመናት ስቃይ ውስጥ
የነበሩ በሽተኞችን፣ ችግረኞችን ለመታደግ ነው ፀጋቻን የተጠቀሙበት! አባ ለእንደኔ ያለው ብዙ
የማይገቡኝ ነገሮች በቤተክርስትያን ቢኖሩም በጎ ነገርን የሚቃወም ሁሉ ግን ከእግዚአበሔር እንዳልሆነ
አውቃሉሁ፡፡ እኔ ብቻም ሳልሆን ጤነኛ አእምሮ ያለው ሁሉ ያውቃል፡፡
የመምህር ግርማ በዲቁና ማጥመቅ አንድ የሰማሁትን ታሪክ ትዝ አስባለኝ፡፡ አባ እርሶ ታርኩን በትክክል
ያውቁታል፡፡ ታሪኩን በትክክል አላስታወስኩት እንሆን ያርሙኛል፡፡ መሠረታዊ ነገሩ ግን እንደዚሁ ነው፡፡
የሆነው በታላቁ የቤተክርስቲያን ሰው በአትናቲዎስ ዘመን ነው ተብዬ የተነገርኩት፡፡ ታላቁ አባት
አትናቲዎስ ሕፃኑ ራሱ ይሁን በወቅቱ የሕጻኑን ጥምቀት ያፀደቀው ካህን ይሁን በትክክል አላስታውስም፡፡
ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ ከክርስቲያን ወገን የሆነ ሕጻን ውሎው ከአሕዛብ ልጆች ጋር ነበርና ለአህዛቦቹ
ልጆች ስለክርስቶስ፣ ጥምቀትና ክርስትና እየነገራቸው ሕጻናቱ አምነው ያንን ሕጻን አጥምቀን አምነናል
ይሉታል፡፡ እሱም በንጹኅ ሕሊናው ልጆቹን ያጠምቃቸውና ወደ ካህኑ ወስዶ ስለሆነው ነገር ሁሉ ለካህኑ
ይነግረዋል፡፡ ያ ካህን ሁለተኛ እነዚያን የአህዛብ ልጆች አላጠመቃቸውም ሕጻኑ በአጠመቃቸው ጥምቀት
የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን አጸደቀ እንጂ፡፡ ከሌላውም ጥምቀት በላይ ይህ የእግዚአበሔርን ልጅነት
የሚያሰጥ ጥምቀት ነው፡፡ ግን እግዘአበሔር ካለ ማን ሊያግድ ይችላል?! ይህ ነው የታላላቆቹ አባቶች
እምነት! ዝም ብሎ ተነስቶ ወግና ባሕልን እየደባለቁ ለራስ በሚመች አይነት የእግዚአብሔርን ሥራ
መንቀፍ ለሕሊና ዕዳ ከመሆን በቀር ትክክል አይደለም፡፡
ብዙ ሌሎች የተባሉ ነገሮች ጥናት በተባለው ላይ የቀረቡ አሉ፡፡ የሚኖሩበት ቤት ዘመናዊነት ተነስቷል፡፡
እውን መምህሩ ከሕዝብ በሰበሰቡት ገነዘብ ነው ይህን ቤት የገዙት? ለብዙ ዘመናትስ ብዙ ሺ ሕዝብ
እያገለገሉ በዚሁ አገልግሎታቸው ከቤተክርስቲያን ሰዎችና ከአንዳንድ ግፍ ተናጋሪዎች ጠንቋይ ናቸው
ተብለው የሚያከራያቸው እንኳን አጥተው ሲንከራተቱ የነበሩ ሰው አልነበሩም? በተሰጣቸው ፀጋ
ለሚሰጡት አገልግሎት ሳንቲብ ሰጠሁ የሚል አለ? በሚሊዮን ቢያወጣ የመዳን ተስፋ የሌለው በሽተኛና
ልዩ ልዩ የኑሮ ውስብስቦች ያሉበት አይደለም እያዳነ ያለው? ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በራሱ ተነሳሽነት
ችግራቸውን አስተውሎ ደስ ስላለው ብቻ ሚሊዮን አውጥቶ ቤት ቢገዛላቸው ምን ይገርማል? የእሳቸውስ
በዘመናዊ ቤት መኖር ሐጥያት ነው? ደግሞ እግዚአበሔር ፈቀደ! ትዕግስታቸውን ተመለከተ! በደሳሳም ኖሩ
በዘመናዊ ቤት እንደማይለወጡ ያውቃልና! መቁጠሪያ ይሸጣሉ? አዎ ግን አኝህ ሰው መኖር የለባቸውም?
ቤተክርስቲያኒቷ ደሞዝ ትከፍላቸዋለች? እንደሰማነው የቤተሰብ አስተዳደሪ ናቸው፡፡ ደግሞስ
መቁጠሪያውን በነጻ ነው የሚሰሩት? በቅጥረ ቤተክርስቲያን መሸጥ መለወጥ አይቻልም? አዎ ትክክል
ነው! ግን ምን ዓይነት ዕቃ? መንፈሳዊ መጻሕፍት? መንፈሳዊ መዘሙሮችና ትመህርቶች? ሌሎች
መንፈሳዊነት ያላቸው መገልገያዎች? አዎ ሁሉንም ከተባለ ደግሞ እንደዛው መሆን አለበት፡፡ መምህር
ግርማ ጋር ብቻ ሲመጣ አይደለም ጥፋት የሚሆነው፡፡ ለሌሎቹም ስህተት ሀኖ ዝም ስለተባሉ መምህር
ግርማም ዝም ይባሉ እያልኩ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የንግድ ሳይይሆን የአገልግሎት ነው ብዬ ስለተረዳሁት
እንጂ፡፡ ስህተት ከሆንም የመምህር ግርማ አግባብ ባለው እርምት በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል
ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም ለማስተካከል በሚያስቸግሩ ሁኔታዎች በዚያው ደብርና በሌሎችም እየተካሄዱ
ያሉ ንግዶችን እንዴት ማየት አልቻሉም አጥኚዎቹ? የወይራ ዘይት ግን ሲሸጥ አላየሁም፡፡ ሰዎች ገዝተው
ያመጡትን ሲባርኩ እንጂ፡፡ ከፋብሪካ የወጣ ዘይት? ታዲያ ከሰማይ የወረደ መሆን አለበት? የወይራ ዘይት
በዘይትነቱ ዘይት ነው! ከፋብሪካ መውጣቱ የወይራ ዘይትነቱን ይቀይረዋል? እንደውም ጥራቱን የጠበቀ
ያደርገዋል እነጂ፡፡ ቅባ ቅዱስ የሚሆነው በጸሎት ስለሚባረክ ነው፡፡ መቁጠሪያ ከውጭ አትግዙ ከእኔ ብቻ
ግዙ አላሉም ገዝተው ሲያመጡ ባርከው ሲሰጧቸው ግን እናያለን፡፡ ግን ለምን የምናውቃትን እውነት
እንክዳለን? ባለማወቅ ከሆነ በጥርጣሬም ቢሆን ገማልያ ክርስቶሳውያንን ይከሱ የነበሩትን የመከራቸውን
አንኳን ምክር ለማደመጥ እንሞክር፡፡
ከሕዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ገብቷል? እኮ ካለም በማስረጃ ቢሆን አይሻልም? በተቃራኒው
ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለቤተክርስቲያን አስገብተዋል! በተረጋገጠ ሰነድ! ይልቁንም እሳቸው
የሚያስገቡትን ገቢ ለመቀራመት ብዙዎች ሲሞክሩ የእሳቸው ለእግዚአብሔር ቤት የተሰበሰበ የሕዝብ
ገንዘብ በምንም ዓይነት በግለሰቦች እጅ አይወድቅም የሚለው ፅንፈኛ አቋማቸው ብዙ የቤተክርስቲያን
ሰዎች ነን በሚሉ ሰውች ጥርስ ውስጥ እንዳስገባቸው እንታዘባለን፡፡ ሌሎችንም ደብራት ትተው ሁሉንም
የሳምንት ጉባዔያቸውን እስጥፋኖስ ያደረጉበት ምክነያቶች አንዱ እሳቸው ለቤተክርስቲያን የሚያሰገቡትን
ገንዘብ አለአግባብ ሲጠቀሙ ስለሚበሳጩ ነው፡፡ እስጥፋኖስ ግን በተለይ ከቀድሞው አስተዳዳሪ ከነበሩት
ጋር በነበራቸው የፍቅርና የመተሳሰብ ግንኙነት ጉባዔውም በአግባቡ እየተካሄደ የሚገኘውም ገቢ በትክክል
መግባቱን በሰነድ/ካርኒ እየተሰጣቸው ነበር፡፡ እስካሁንም የገንዘብ አሰባሰቡ ሂደት ቀድሞ በነበረው አሰራር
ስለቀጠለ የእስጥፋኖስ ጉባዔ ገንዘብ እዛው ተቆጥሮ ካርኒ ይቆረጥባታል፡፡ ይህ ግን በአሁኑ አስተዳደር
የተወደደ አይመስልም፡፡ የአሁኑ አስተዳደር ሰሞኑን ያደረገው ድርጊትም ብዙዎቻችን እንደምንረዳው
ዋነኛው መንሰዔ ከዚሁ የገንዘብ ጉዳይ ጋር ይመስለናል፡፡ ሌላ ሌላውን ሳይጨምር የቀድሞው አስተዳዳሪ
በነበሩት ጊዜ መምህር ግርማ የሚያስተምሩበት ጉባዔ ለቤተክርስትያኗ ሕንጻ ማሳደሻ ብቻ ከአንድ
ሚሊየን ሁለት መቶ ሺ ብር በላይ በተረጋገጠ ሰነድ አበርክቷል፡፡ በእንዲህ ያለ ሕብረት የተሰራን በጎ
ሥራን ለማጥላላት አጥኚ ነኝ ያለው በዛሬው የደብሩ አስተዳዳሪ የሚመራው የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ግን
የቀድሞው አሰተዳዳሪ የነበሩትንም በጽኑ ይኮንናል፡፡ ግን ለምን? ሕሊና እያወቀ የሚሸረብ ሴራ ለንስሐ
እንኳን ይመቻል? አባ አኛ ተራዎቹ ይሄንን አንደፍረውም! ነው ወይስ ወደ ቤተክርስትያን ጠጋ ብለን
ሚስጥሩን ብንረዳ ድፍረትን እናገኝ ይሆን? ነው ወይስ በጎ የሚባለው ነገር እኛ ከምናውቀው ውጭ
ነው?አባ ግን አኮ እግዚአበሔር ለእኛም ማስተዋሉን ሰጥቶናል! ሕሊና ከሳሽም ፈራጅም ነው! ሌሎችም
ለክስ የቀረቡ ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ አባ እውነትን አለመረዳት ይኖራል ከአወቅናት በኋላ ግን ብንክዳት
ከሳሽም መስካሪም ፈራጅም የሆነው ሕሊናችንን እንደበቀው ዘንድ አይቻለንም!
እንደሰው ስህተት እንኳን ቢኖር ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ ያለ አለ? አባ እኔ በበኩሌ ይሁዳ ክርስቶስን
አሳልፎ ሰጠ ብዬ ለመክሰስ አቅም የለኝም፡፡ እኔም በዘመኑ ብኖር ከይሁዳ ወይም ሌሎች በክርስቶስ ላይ
አጃቸውን ከሰነዘሩት እንደ አንዱ አለመሆኔን ማረጋገጥ አልችልምና፡፡ እውነትን ካለመረዳትስ ቢሆን
ምህረት አለኝ፡፡ ግን ከሕሊና ክፋት ከሆነ ለመጸጸትም (ለንስሀም) ይከብዳል፡፡ ይሁዳም ሞክሮ ነበር፡፡
ከሕሊናው ክፉ የሆነ ሰይጣንን የሚወክል ባሕሪ እንዳለው አስባለሁና፡፡ ወደ አእምሮ አንዴ የገባች
እውቀት በሁለት መንገድ ልትካድ ትችል ይሆናል፡፡ አንድ ከሕሊና ክፋት፣ ሁለት ከስጋ መሰሰት (ለጥቅም
ወይም በፈርሀት)፡፡ ከስጋ መሰሰት የምተመጣዋ ክደት የጴጥሮስን አይነት ልትሆን ትችላለች፣ ከሕሊና
ክፋት ግን የምትመጣዋ የይሁዳ አይነት ትሆናለች፡፡ በሕሊና ያልበደለ ግን ሁሌም ተስፋ ያለው
ይመስለኛል፡፡ እውነትን አንኳን ቢሳሳት ያወቀ ዕለት ሕሊናው የእውነት ምስክር ለመሆን ብቁ ናትና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ እረዳዋለሁ! አባ አባክዎን እውቀቱ ሁሉ እርሶ ጋር አለ ግን እንዲሁ እንዳወቁት
ስለሕሊና ፍርድ የዚህንም ሌሎችንም የበቤተክርስቲያንና የሚመሩትን ሕዝብ ነገር ይዳኙ፡፡ ሥለ ሕሊናና
ዕውነት ብዙዎች ከእርሶ ጋር እንቆማለን!
እግዚአብሔር የምናስተውልበትን አእምሮ ይስጠን! ለማይረባ አእምሮም ከመዳረግ ይሰውረን! የሠላም
አመላክ ከሁላችን ጋር ይሁን! አሜን!
ከሕሊና ፍርድ ናፋቂው አንዱ
No comments:
Post a Comment