Showing posts with label ግጥም. Show all posts
Showing posts with label ግጥም. Show all posts

Thursday, September 18, 2014

“ክልክል ነው”

“ክልክል ነው”

(በእውቀቱ ስዩም)
not allowed
ማጨስ ክልክል ነው
ማፍዋጨት ክልክል ነው
መሽናት ክልክል ነው
ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ኃይል ባደለኝ
“መከልከል ክልክል ነው”፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡
(በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000)

Tuesday, December 10, 2013

ለካ የማዶዎቹ ጭራቆች ነበሩ!!!

ለካ የማዶዎቹ ጭራቆች ነበሩ!!!

ከትበው እንዳኖሩት ጥንታዊ ልጆችሽ፣
ለሌሎች ስትሰጭ ተርፎት ቤተሰብሽ፣
ዘር አትይ ሀይማኖት ሁሉን በአንድ አይተሽ፣
የስላሴን ፍጡር ሰውን ያከበርሽ፣
ጦር ላሳደዳቸው  ከለላቸው ሆነሽ ፣
ከማዶ ለመጡት መጠጊያ እንደነበርሽ፣
በማህደር ሆኖ ያትታል ታሪክሽ፣
ዛሬ እጅሽ ቢያጥር በረከትሽ ቢነጥፍ፣
ወለላሽ ተመጦ ዘለላሽ ቢረግፍ፣
የትውልድሽ  ዕድል ሆነና መሰደድ፣
ከማዶዎቹ አገር ዳቦ ሽቶ ቢሄድ፣
ልጅሽን አረዱት አጋድመው  በካራ ሥጋውን መተሩ ፣
ለካ  የማዶዎቹ ሰውን የሚበሉ ጭራቆች ነበሩ!!
መታሰቢያነቷ በሳውዲ እየታረዱ ላሉ ወገኖቻችን
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 6ኛው 2006 ዓ.ም (Son of the Great day Nov. 15th 2013)

የእኛ ሰቆቃ መቼ ያብቃ?? ለኢትዮጵያ

የእኛ ሰቆቃ መቼ ያብቃ?? ለኢትዮጵያ
ችግር ቤትሽ ገብቶ ሲጫውት ዕቃዕቃ፣
ያሻውን ሲረግጥ ቀላቅሎ ከጭቃ፣
ያሻውንም ሲያርድ ያሻውን ሲወቃ፣
ሁሌ የሲቃ ድምፅ ሁል ጊዜ ሰቆቃ፣
ትናንትና ዛሬም ነገም ላያበቃ፣
በአዘቦት በሰንበት በፀሐይ በጨረቃ፣
ዘላለም ዕድልሽ እንዲህ ሆነ በቃ???!
የታላቋ ቀን ልጅ 1994 (Son of the great day 2002) 

Monday, December 2, 2013

የሽፍታው፣ከተሜዎቹና፣አራዊት ቃል ኪዳን


የሽፍታው፣ከተሜዎቹና፣አራዊት ቃል ኪዳን
የአራዊት ሁካታ በጣም የሰለቸው፣
ብቸኝነት ጎድቶት ኑሮ የመረረው፣
አንድ ልዩ ሽፍታ ከተማ የማያውቅ፣
ጥቅትቅ ባለ ደን የሚኖር በድብቅ፤
ከዕለታት በአንድ ቀን ከሩቅ የሚመጡ የሰዎች ድምፅ ሰምቶ፣
ሲጠባበቀቸው አሳቻ መንገድ ላይ ለዝርፍያ አድብቶ፣
ወደእሱ ሲቀርቡ ሲጠራ ድምጻቸው፣
የጫካውን ሰላም ሲያደንቁ ሰማቸው፡፡

ለመዝረፍ የአደባው ይሕ አደገኛ ሰው፣
ለመማረክ ወጥቶ እሱ ተማረከ በውይይታቸው፡፡
ስለደኑ ውበት ስለጫካው ሠላም፣
ገነት የገቡ ያህል ተደስተው በጣም፣
እያወዳደሩ ከከተማው ኑሮ ሠላም ከጠፋበት፣
ጩኸት ከበዛበት ኹከት ከሞላበት፣
ሲያደንቁ ሰማቸው የጫካውን ሠላም የጫካውን ውበት፡፡
የእኚህ ከተሜዎች እጅግ የተዋቡ፣
በከተማው ኑሮ ምሬታቸው ገርሞት ተመስጦ ቀልቡ፣
ከአደባበት ወጣ ሊቀላቀላቸው፣
ሊካፈል አስቦ በውይይታቸው፡፡
ግን ከተሜዎቹ ሰው ሽሽትን መጥተው፣
እዚህ ሠላም ቦታ ሰው በማየታቸው፣
ፊታቸው ደመነ እጅግ ቅር አላቸው፡፡
ሰላምታውን ሲሰጥ ሽፍታው ቀረበና፣
የድመፁ አወፋፈር የቅላጼው ቃና፣
ጆሯቸው ሲገባ ፊታቸውን ሞላው ፈገግታ እንደገና፡፡
ሁሉም በአንድ ቃል አጸፋ መልሰው ለሰጠው ሰላምታ፣
ሰው በማይኖርበት በዚህ ልዩ ቦታ፣

ምን እንደሚሰራ በአንድነት ጠየቁት፣
ተክለ ቁመናውን በአግራሞት እያዩት፡፡
ፈገግታ ተላብሶ ያ ሪዛም ገጹ፣
ሽፍታውም መለሰ በነጎድጓድ ድመፁ፡፡
በብቸኝነቴ ከሰው ሳላወራ፣
ከዛፍ፣ከወፎቹ ከአራዊቱ ጋራ፣
ብዙ ዓመት ኖሪያለሁ እኔ በዚህ ሥፍራ፡፡
ፍጹም ተማርሬ  በብቸኝነቴ፣
ከተማ ለመግባት ነበረ ምኞቴ፡፡
አሁን ግን ስሰማ የእናንተን ውይይት፣
ልቤ አመነታ ከጫካው ለመውጣት፣
የከተማው ኑሮ የሚብስ ይመስላል፣
እንኳን እኔንና የጫካውን ልዑል፣
ያደጋችሁበት እናንተን አማሯል፡፡
አዎ በትክክል ከዚያ ሰላም ጠፍቷል፣
ጩኸትና ምሬት ሁከት በዝቶበታል፡፡
አንተም አትታለል አተናፍቅ ከተማውን፣
ከደኑ አትውጣ ኑር የምትኖረውን፣
ፍቃድህ ቢሆንስ ለእኛም አለማምደን፣
የዚህን የአንተ አገር ጥቅጥቅ ያለውን ደን፣
ይህን ንፁህ አየር በነፃ  እየማግን፣
በወፎች ዝማሬ በአራዊት ቡረቃ እየተደሰትን፣
በዚህ ሰላም ቦታ ልንኖር መጥተናል፣
የአንትም ብቸኝነት ከእንግዲህ አብቅቷል፡፡
ቃል እንገባባ ፍፁም ላንካካድ፣
ነበሳችን ከደኑ ከአራዊት ትዛመድ፣
ተነስተን እንጓዝ እረጅሙን መንገድ፣
ሀረናን ሰንጥቅን አማዞን እንሂድ፡፡





 


ታሪኩ በትክክል ከግጥሙ ጋር ባይገናኝም አንድ የተነገረኝ አባ ኤበሉ (የእንትና አባት) የሚባል እውን ይኖር የነበረ ሽፍታ ታሪክ ለሀሳቡ መሻዬ ነው፡፡
ኤበሉ ማለት በአማርኛ እንትና እንደሚባለው ነው፡ ሥሙን በትክክል ያልገለጽኩት ይህን ግጥም ከምታነቡት የተወሰናችሁት የዚህ ሥም መጠሪያ ሊኖራችሁ ስለሚችል ደግሞ የእኔ አባት ሽፍታ የነበረው መቼ ነው እንዳትሉ ነው፡፡  ይህ ሽፍታ የሚዘርፈው ከሚስቱ ጋር ሲሆን ሚስቱ ጠበመንጃ እሱ ደግሞ ቦምብ ይዘው ነው የሚዘረፉት፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቂም የያዘበት የባለአባት ሰርግ ላይ ይገኝና ያ ሁሉ ሰው ባለበት ሁሉንም በቦመብ እያስፈራራ የባለአባቱን ሚስት (ሙሽራይቱን) ይዞ ወደ ሚኖርበት ጫካ (ደን) ሲሄድ የምትከተለው ስንኝ በሰርገኞቹ ተቋጥራለታለች (ኦሮምኛ ለምታውቁት ብቻ በመሆኑ አዝናለሁ)፡፡
አባ ኤበሉ ኤሳ መኒ ኢሳ፣
ቦምቢን ነማ ቦቤሳ፡፡
ሀረናን ለማታውቁ ባሌ ውስጥ ያለ የታወቀ ደን ነው (ጉግልም ብታደርጉ ታገኙታላችሁ)፡፡

የታላቋ ቀን ልጅ -2005 (መነሸው 1994) ዓ.ም (Son of the great day-2012 (mini-draft 2002)




Friday, November 29, 2013

አራምባና ቆቦ ወይስ ወላፈንዳ (ቦጋለ ዳኜ)



ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ
ሥጋ ሜዳ፤ ሽሮ ሜዳ፤
እሚቀመስ የለም ጓዳ።

ሳይኖር አውራ፤ ዶሮ ሲካካ፤
እንቁላል ፋብሪካ።

እንቁላል ሾላ፤ ፋብሪካ ጉለሌ፤
እንጀራ አዲሳባ መሶብ መቀሌ።
(ገበያ መርካቶ፤ ሲሚንቶ መቀሌ።)

ስንቅ አቀባይ ባሌ፤ እስረኛ ሰንቀሌ፤
"ዘይገርም ሻሸመኔ፤ ትብስ ኮፈሌ።"

ታዳሚ አገር ፍቅር፤ ብሔራዊ ቲያትር፤
ድራማ ሰቱድዮ፤ ማስታወቂያ ሚኒስቴር።

ባለ ጉዳይ ይፋት፤ የዳኛ ቀጠሮ፤
ጉዳይ ባሕር ዳር ባዲሳባ ዞሮ።

አስለቃሽ ደኅንነት፤ ቀብር ቀራንዮ፤
ሟች ራሱ አልቃሽ፤ ደረት ጥሎ ወዮ።

በጸጥታ ጩኸት፤ በደኅንነት ችግር
አልገናኝ አለ፤ መጠርያና ተግባር።

ይካፈል በልማት፤ ያገባዋል ሕዝብ፤
ልማቱን ለኛ ተው ብር ብቻ ሰብስብ።

ሥልጣን በምርጫ ነው፤ ዐዋጅ ተመዝገቡ፤
የምርጫ ካርዱን ግን፤ ሁሉን ለኔ አግቡ።

ሁሉ በእኩል ይታይ፤ መልካም አስተዳደር፤
ብሔር ብሔረ ሰብ፤ ባዶ መፈክር።

ደኑ አይጨፍጨፍ፤ ትውልድ እንዳይወቅስ፤
እየሰሙ ዝም፤ጆሮ ዳባልበስ።

ወደ ክልልህ ሒድ፤ ውጣ ከመሬቴ፤
ባዕዳን ሕንድ ቻይና፤ ኑ ግቡ በሞቴ።

ለሳውዲ ሲሰጥ የተንጣለለ እርሻ፤
ተጠራርጎይውጣ ከሳውዲ አበሻ።

ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ

eth iopiazare

Thursday, November 28, 2013

ሕገ ወጥ ስደተኛ (illegal immigrant)

ሕገ ወጥ ስደተኛ (illegal immigrant)

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
An Ethiopian worker argues with Saudi security forces while waiting for repatriation in Manfouha
ምን ማለት ነው እሱ ወዳጀ፤ ይሄ ሕገ ወጥ ስደተኛ
ወዶ የሚሰደድ ከሌለ፤ ከሀገሩ የሚርቅ መከረኛ
ነፍሱን ለማትረፍ የሻ ሰው፤ ይሸሻል እንጅ ባመራው
እንግዳ አይደለ ወይ ጎብኚ፤ ፈቃድ ጠይቆ የሚገባው
እስኪ ንገረኝ እባክህ፤ ለእናንተው መሐመድ ሰዎች
ተቸግረው ለተሰደዱት፤ ከሀገራቸው ላለመሆን ሟች
ቪዛ ተመቶላቸው ነበረ? ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ?
   አሳልፋቹህ ስጡን ብለው፤ በጠላት ለሰይፍ ሲታሰቡ
   ውሰዷቸው ተብለው ነበር? ወይስ ቤዛ ሆነ እርግቡ?
   ውጡልን ተብለውስ ነበር? ፊቱን ነስቷቸው ሕዝቡ?
   አንተ ግን ውለታ ቢሱ፤ አምላክ የማታውቅ የማትፈራ
   የነፍስ ብለው የተጠጉትን፤ ለማምለጥ ከአጋንንት ጭፍራ
   እያረድክ ፈነገልካቸው፤ ደፍረህ አርክሰህ በጠራራ
   ይሄ ነው ላንተ ጽድቅ ማለት፤ ደም ጠጥቶ መስከር ግፍ ሥራ
ከሰይፍህ የተረፉትን፤ ደክሞህ ሰልችቶህ መተራ
እያነክ አስረከብካቸው፤ ለግዞት ሞት ለመከራ
አምላክን የፈራ ማለት፤ ለሰብአዊነትም ያደረ
ምርጫ ያጣን መርዳት እንጅ፤ ድጋፍን መስጠት ለተቸገረ
ያለውን መቀበል አይደለም፤ ለሥጋዊ ጥቅም እየመከረ
በሥጋ ገበያው ገብቶ፤ ካዝና የሚሞላን እየጨመረ

goolgule

Wednesday, November 27, 2013

ኧረ እነማን ናቸው? (ጌታቸው ቃሉ)

ኧረ እነማን ናቸው? (ጌታቸው ቃሉ)


ጌታቸው ቃሉ
ከየት ነው የመጡ ከነጥላቻቸው?
የሀገር መሪ ሆነው ሕዝብን መጥላታቸው
ምንድነው ዓላማው? ወንበር መያዛቸው
እንቅልፍ ሳይተኙ እንዲ መኖራቸው
ሀገር አይበድልም ምን አስቀይሟቸው?

ሕዝብን ከሕዝብጋ ሊያጣሉ ሴራቸው
ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ናቸው?!
ሠራዊቱስ ምነው እንዲ አከበራቸው?
ከእናት ካባቱ እውን በልጦባቸው
እህቶቹን ሁሉ ገረድ ላረጋቸው
ወንድሞቹን አስሮ ጭራሽ ደፍረዋቸው
ሀገሩን ቆራርሰው ለባዳ ሸጧቸው
ኧረ በምን ሂሳብ ዘብ የቆመላቸው?!
ሰምተን የማናቀው ጉድ ተፈፀመብን
መራዝ፣ መራባችን መጠማቱን ትተን
እንዴት ባገራችን ክብር እናጣለን?!
ምን ሆኗል ትውልዱ? በቁም የሞተበት
ለክብሩም ለሆዱ እንዲ ያላወቀበት
እነሱ ሲበሉ ዐይቶ ያፋሸከበት
ዕንፃ ሲገነቡ ድንጋይ ያቀበለበት
ምን ዓይነት ምታት ነው ለሱስ ያረጉበት
ፍፁም አይመስለኝም ሀገሬ የቆመች
በሰመመን ዕንቅልፍ እንጂ የወደቀች
ማን ፈቅዶ ይገፋል ከመብቱ
አደለም ለመብላት ለወሬም ከመቱ
የዓላማ ሳይሆን ጥላቻ መሆኑን
የሚያስጨንቃቸው ባንዳነታቸውን
አውቀን ካልተነሳን አይ ካላልናቸው
እነዚህ ጭራቆች ያወቁ መስሏቸው
ሀገሩን ለማጥፋት የቆረጡ ናቸው።
ጌታቸው ቃሉ

ethiopiazare

የሞተው ሀገር ነው (አንዱዓለም በቀለ)

የሞተው ሀገር ነው (አንዱዓለም በቀለ)


አንዱዓለም በቀለ 
ምነው ህልሜ ከፋ ... መተኛት አቃተኝ፣
እሚታየው ሁሉ ... ድንግርግር አለብኝ፣
እሚሰማው ሁሉ ... ተአምር ሆነብኝ፣
እውን ነው? ቅዠት ነው? ... አልጨበጥ አለኝ፣
ኡ ኡ ያገር ያለህ ... ልጩህ ቢወጣልኝ፤
አትጩህ አትበሉኝ ... እጮሀለው በጣም፣

አታልቅስ አትበሉኝ ... አለቅሳለሁ በጣም፣
ከዚህ የበለጠ ... አሥር ሞት አይመጣም፣
ከዚህስ የከፋ ... መዋረድ አይመጣም፤
እጮሃለሁ እንጂ ... እላለሁኝ ዋይ ዋይ፣
ላሥር ስትደፈር ... እህት ሥትሰቃይ፣
ወገኔ ሲታረድ ... በጠራራ ፀሀይ፣
ደራሽ ወገን ጠፍቶ ... ዘራፍ የሚል ከልካይ፣
እንዴት አያስጮህም ... አያሰኝም ዋይ ዋይ?!
ከየትኛው ዘመን ... የትኛው ለይ ደረስን!
ከየተኛው ውርደት ... የትኛው ተሻለን?
ሁሉን የሚሸከም ... ምን ትከሻ ሰጠን!
የምን ልክፍት ነው ... እንዲህ ያደረገን?
እህት ስትደፈር ... እንደ ፊልም እያየን፣
እንደ በግ ሲቀላ ... ወገንን እያየን፣
ሶፋ ላይ ተቀምጠን ... ከንፈር ብቻ መጠን፣
ኦ አምላኬ ባክህ ... ከዚህስ ሰውረን፣
በሩቁ ያዝልን ... ብለን እንዳላየን፣
ወደ አልጋ ስንሮጥ ... እንቅልፍ የሚወስደን፣
አቤት ያንተ ያለህ ... እንደምን ቢያስችለን!
ፊልም እኮ አደለም ... ባይናችን ያየነው፣
ተውኔት አይደለም ... ደራሲ የጻፈው፣
እንደ ሬት ቢመርም ... የምንቀበለው፣
የሁላችን ዕዳ ... ሸሽተን የማንሸሸው፣
በገሃድ የታየ ... መራር እውነታ ነው።
ክብሩን ግንባሩ ላይ ... አሥሮ የወደቀው፣
አረብ በረሃ ላይ ... ውሻ የተባለው፣
እውነት ... አንድ ሰው ነው??
እውነት ሀገር ያጣ ... ውዳቂ ውሻ ነው?
ካልሳትነው በስተቀር ...
የዛች ኩሩ ሀገር ... መጠሪያ ዜጋ ነው፣
እንደኔ እንደናንተ ...
ህይወት የሚያባርር ... ንፁህ ኢትዮጵያዊ ነው፤
መቼ ይህ ብቻ ነው ...!
የሦስት ሺህ ዘመን ... አኩሪ ታሪክ ያለው፣
የጥቁሮች ኩራት ... መመኪያ የሆነው፣
ያልበገሬነት ... ማህተም የሆነው፣
ከአፍሪቃ አልፎ ... በዓለም ከፍ ያለው፣
ዛሬ ሁላችንም ... አርገን የምንኮራው፣
የማንነታችን ... መለያ የሆነው፣
ዛሬ አረብ ምድር ... እንዲህ የተናቀው፣
ሰንደቅ ዓላማችን ... ክብራችን እኮ ነው፤
ውሻ የተባለው ... ኢትዮጵያዊነት ነው፤
እንዲህ የረከሠው ... ማንነታችን ነው፤
አንድ ሰው አደለም ... ወድቆ የምናየው፣
ደጋግሞ ደጋግሞ ... የሞተው ሀገር ነው፤
ሀገር ነው የሞተው ... አብረን ነው የሞትነው።
እና ለምን አልጮህ ... ተወው አትበሉኝ፣
ይልቅ የኔን ጩኸት ... አንድ ላይ ካልጮህን፣
እንዲህ ስንዋረድ ... በጋራ ካልቆምን፣
ከኛ በላይ ለኛ ... ታዲያ ማን ይምጣልን?
የሰው ልጅ መገኛ ... መሠረት የሆነች፣
ዘርፈ ብዙ ታሪክ ... ገድል የፈፀመች፣
ዛሬ ለሚገሉን ... ገነት የነበረች፣
ዛሬ ውሻ ላሉን ... ምፅዋት የሰጠች፣
እስላም ክርስቲያኑን ... በፍቅር ያኖረች፣
የሐበሻ ምድር ... ቅዱስ የተባለች፣
እቺ ኩሩ ሀገር ... ምነው እንዲህ ሆነች?!
ከምን ላይ ተነስታ ... እምን ላይ ደረሰች?
ከሁሉም ከሁሉም ... እጅጉን የሚያመው፣
ሳያንስ የተገፋው ... ሳያንስ የተደፋው፣
ለሞተው ወገኔ ... ልጩኽለት ላለው፣
አብሬው ባለሞትም ... ላልቅስለት ላለው፣
የወገንን ጩኸት ... ዳግም እሚያፍነው፣
የሟቾችን እናት ... መልሶ ሚገርፈው፣
መታደጉ ቢቀር ... ለቅሶ የነፈገው፣
ይህ ነው መንግሥታችን ... ከገዳይ ያበረው፤
ይህ ነው መንግሥታችን ... ለሀገር የቆመው፤
እርግጥ ነው ... እውነት ነው፣
እነሱ ምን ያርጉ ... ተመችተናቸው፣
ጫንቃችን ደንድኖ ... ተሸክመናቸው!
እስቲ በቃ እንበል ... በቃችሁ እንዲለን፣
መጠላለፍ ይቅር ... አንድ ላይ ያቁመን፣
ከወሬ ባለፈ ... ተግባር ይፈትሸን፣
እንዲህ በሚጮኹት ... በወገኖቻችን፣
መሬት በወደቀው ... ሰንደቅ ዓላማችን፣
እስቲ እንማማል ... ይያያዝ እጃችን፣
ይብቃ ስደታችን ... ይብቃ ውርደታችን፣
ብሔራዊ ክብር ... ይታደስ ስማችን፣

ለምን ጣልከኝ? (ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ)

ለምን ጣልከኝ? (ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ)


ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ልሞግትህ ፍቀድልኝ!
አንድ ግዜ ብቻ ልናገር ለባሪያህ እሺ በለኝ
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ደስታዬን ወሰድክብኝ አሳዘንከኝ
እስቲ ንገረኝ ለምን ጣልከኝ?

እንዳለህ በመንበርህ አምናለሁ
በሦስትነት ባንድናትህም አውቅሀለሁ
ደብረ ደብሬ ታቦት ቀርጬ
ድረሳን ጽፌ ማህሌት ቆሜ
ኤሉሄ ኤሉሄ እልሀለሁ
ዕድሜ ዘመኔን ጽናጽል አጮሀለሁ
ሀሌ ሉያ ህያው ነህ ብዬ እላለሁ
ደግሞም ስምህ ቢቀየር በሬቻ
አላህም ቢልህ ቃልቻ
አንተ አንድ ነህ አመልክሀለሁ
ጠዋትም ማታ አቤቱ እልሀለሁ።
ከኦሪት በፊት በልቦናዬ አሀዱ ብዬ
በኦሪትም ቢሆን አመሳጥሬ ብዬ አንድዬ
በሀዲስማ እንዳስተማርከኝ አንድነትህን ተከትዬ
ስምህን ጠርቼ አልጠግበውም
እልሀለሁ አምላኬ መድኃኒዓለም
ታዲያ ለምን ጣልከኝ?
ልሞግትህ እሺ በለኝ
አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር ለባሪያህ ፍቀድልኝ
ለምን ጣልከኝ?
ትላንት ከማዕዴ የቆረሰ
እራፊ ጨርቁን ከዕኔ የተዋሰ
ዛሬ እንዴት በረታብኝ?
እስቲ ንገረኝ
እንደ ዳዊት ቅድስና ባይኖረኝም
የያዕቆብን ታላቅነት ባላገኝም
ሳትነግረኝ አለቅህም
እጮሀለሁ ደግሜ ደግሜ እጮሀለሁ አልተውህም
እናም ደግሜ እልሀለሁ
ለምን ጣልከኝ ብዬ እጠይቃለሁ?
ብወድቅም የምታነሳኝ አንተ ነህና እማጸናለሁ።
ለምን ጣልከኝ?
ያንንም ስም ገናናነትን አንተ ነበርክ የሰጠኸኝ
በዓለም ፊት ያከበርከኝ ያገነንከኝ
ታዲያ ዛሬ ለምን ጣልከኝ
ጥቁሩ ወንድሜ የሚመካብኝ ታላቅ ህዝብ ነው የሚለኝ
ነጩ የሚያፍረኝ በሙሉ አይኑ የማያየኝ
ክንዴ እሳት የጠላውን የሚፋጅ የሚጎስም
ለወዳጁ ፈጥኖ ደራሽ የሚደጉም
ይህ ሁሉ ግን ዛሬ የለም
ስለጣልከኝ፣
የሚያዝንልኝ አልተገኘም!
ሐበሽ ብሎ እንዳልጠራኝ
እጄን ስቦ እንዳልሳመኝ
ደስታዬ ነው ቤቴ መጣህ ብሎ እንዳላለኝ
ዛሬ ግን ጥላት ሆኖ ተነሳብኝ
ስለጣልከኝ!
ሳዱላዎቼን ለቤቱ ግርድና ወሰዳቸው
ሳተናዎቼን ግመል በፊቱ አስጎተታቸው
በጊንጠ ጅራፍ ገረፋቸው
ሀሞት ከርቤ ጋታቸው
የሞት ጥዋ አጠጣቸው።
ማን አየልኝ የእኔን ስቃይ
ማን ሰማልኝ የእኔን ጉዳይ
እስኪ ንገረኝ!
ለምን ጣልከኝ?
መገፋትን መገረፍን
መበደልን ፍትህ ማጣትን
ታውቀዋለህ ለዚህ ሁሉ ምሳሌ ነህ።
እውነትን በማያውቁ
በሌሎች ሀዘን በሚስቁ
በጨካኞች በክፉዎች መንገላታት
ታውቀዋለህ በደቦ ሕግ መገፋት
እስኪ የሆነብኝን ዕይልኝ
በቃሽ በለኝ ፍረድልኝ
ወድቂያለሁ ደቅቄያለሁ እባክህ ትችላለህና አንሳኝ
ለምን ጣልከኝ?
ማን አጠፋ?
የመረጥህ የሾምካቸው?
መከራህን (መስቀልህን) ያስያዝካቸው?
በነሱ አልፈርድ እነሱም እንደኔ ፍጡር ናቸው
ድንጋይ መካብ ግንብ መስራት ካማራቸው
ጣፋጭ ወይን ከጣላቸው
የሺ ዓመቱን በዕለት ጉርስ ከቀየሩ
ከያዕቆብ ሳይሆን ከኤሳው ስጋ ከተሰሩ
ባለም ነዋይ ከዓለም ጋር ከተዳሩ
አንተን ትተው ለምድር ጌቶች ካደሩ
ለኔም ተርፎ ጥፋታቸው ክፋታቸው
በረሀቡም በበሽታ በስደቱም ዕቀጣለሁ
የእንባ ዘለላዬን አፈሳለሁ።
በእነሱ ግፍ ከቀጣሀኝ
እልሀለሁ ስላለፉት ስትል ማረኝ
ይህ ካልሆነ፣ በምን ምክንያት አሳጣኸኝ?
ፍቅር በሌላቸው እጅ ተውከኝ ጣልከኝ!
እናም ፍቅሬ ውዴ
አንተው ነህ የሩቅ የቅርብ ዘመዴ
የፍልስፍና የኃይማኖት አምዴ
መቀመጫ መሽከርከሪያ አውዴ
ኤሉሄ ኤሉሄ ማለቴን
የምታነሳኝ አንተ ነህና ተመልከትልኝ ስቃዬን
ለምን ጣልከኝ?
ሀምሳ መቶ አብርሀሞች ባይገኙ
ባዶም ቢሆን አደባባይ ዕልፍኙ
የሰበርከውን ስትጠግን አውቃለሁና
ክፉ ዘመኔን አሳልፍልኝ ቃልህን ብቻ ተናገርና።
አምርሬም እጮሀለሁ!
ለምን ጣልከኝ? እልሀለሁ(2)

ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ
ህዳር፣ 2006፣
መታሰቢያነቱ በሳውዲ ዐረቢያ በከንቱ ደማቸው ለፈሰሰ ወገኞቼ!!