Saturday, November 9, 2013

“የዓለም ተፈጥሮአዊ እሴት ነፃነት ነው”

            የጀርመኑ ፈላስፋ አማኑኤል ካንት ስራዎች በአብዛኛው የሥነ ምግባር ጥያቄዎችን የሚዳስሱ ክፍሎች አሏቸው። በCritique of practical reason ውስጥ መሰረታዊ የሥነ ምግባር ሐሳቦችን በሰፊው ዘርዘር አድርጎ ጠቃቅሷቸዋል፡፡ ዋናው እና መሰረታዊው የሥነ ምግባር አስተምህሮዎችን ያስቀመጠበት ሥራው ግን Groundwork of the metaphysics of morals(ኅላዌያዊ የግብረ ገብ መሰረት) ብሎ በሰየመው ድርሳኑ ውስጥ ነው። ለጽሑፎቹ ከሚሰጠው ርዕስ ጀምሮ ካንት የጠገነኑ ሐሳቦችን ይወዳል። ከእርሱ በፊት የነበሩትን የሥነ ምግባር አስተምህሮዎች በሰላ ትችት እየከተከተ “የአስተሳሰብ አዲስ ዓለም” ለመፍጠር ይሞግታል። ጥቅም/ፌሽታ የሚያስገኝ ነገር ሁሉ መልካም ምግባር ነው፤ጥበብን የምናተርፍበት ተግባር ሁሉ መልካም ምግባር ነው፤የምንሰራው ሥራ ለአብዛኛው ሰው ትሩፋት የሚያስከትል ከሆነ መልካም ሥነ ምግባር ነው የሚሉ ፍልስፍናዎች ከካንት በፊት ሲዘመርላቸው ነበር። ካንት በጣም ጥብቅ የሆነ የራሱ የሕይወት መመሪያ ስለሚከተል ከመጽሐፍት ቤት ወደ ቤቱ የሚንቀሳቀስበትን ሰዓት እንኳን ስለማያዛንፍ የአካባቢው ሰዎች ስንት ሰዓት መሆኑን የካንትን መምጣት አይተው በቀላሉ ያውቁ ነበር።
ከሚኖርበት አካባቢ ወጥቶ እንደማያውቅ ይነገራል፤ እዚያችው ቁጭ ብሎ እራሱን ከዩኒቨርስ ጋር እያነጻጸረ ይፈላሰፋል። የዲበ አካል/ኅላዌ ጥያቄዎችን ያነሳል ይጥላል፤ ንጽሓ (Pure) አመክንዮ/እውቀት እንዴት ይገኛል፤ንጽሓ ተግባራዊ አመክንዮ፤የመጭው ኅላዌ ፍልስፍና ወዘተ… የመሳሰሉ የፍልስፍና ድርሳኖችን ያስኮመኮመን ከሠፈሩ ሳይወጣ ነው። ለምንሰራቸው ሥራዎቻችን የምናቀርባቸው አመክንዮዎች ለራሳችን ፈቃድ መልካም ሆነው እንደታዩን ሁሉ ለሰው ልጅ በሙሉ/ለዓለማቀፋዊ ፈቃድ መልካም እንደሚሆኑ ካወቅን፤ ይህ ተግባር ሥነ ምግባራዊ ነው ይለናል። ሌሎች የሥነ ምግባር ፈላስፎች’ሥነ ምግባርን ከሚለኩበት የተግባር ውጤትና ውጤቱን ካስመዘገብንበት መንገድ ባሻገር እንድናስብ ይጋብዘናል። ኮፐርኒከስ የተባለው የፊዚክስ ምሁር የዩኒቨርሳችን ማዕከል ፀሐይ መሆኗን አስተዋውቋል፤ ከእርሱ ዘመን በፊት የነበረውን “ምድር ናት ማዕከሏ” የሚለውን የአርስጣጣሊስ አስተሳሰብ ንዶ።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ የካንትም ፍልስፍና የተግባራችንን ውጤትና ውጤቱን ካስመዘገብንበት መንገድ ባሻገር የሁሉም ነገር ማዕከል ሰው ነው ወደሚል ድምዳሜ በማምጣቱ “የካንት ኮፐርኒከሳዊ አብዮት” እየተባለ ይጠራል። አንድን ተግባር ሥነ−ምግባራዊ ነው ወይስ ኢ−ሥነ ምግባራዊ ነው የሚለው ብያኔ ላይ ለመድረስ አንዳንድ ፈላስፎች የስራችንን ፍጻሜ/ውጤት በማየት’ አንዳንዶቹ ደግሞ ፍጻሜውን ሳይሆን ሥራውን የሠራንበትን መንገድ በመገምገም ይበይናሉ። ለምሳሌ ለአንዳንድ የሥነ ምግባር ፈላስፎች፤ ለተቸገረ ሰው ገንዘብ መስጠት መልካም ምግባር ነው፤ምክንያቱም ውጤቱ ችግርን ያቃልላልና። ነገር ግን በሌሎች ፈላስፎች አመለካከት የምለግሰውን ገንዘብ ያገኘሁበት መንገድ መታወቅ አለበት፤ (ይህ ተግባር ሥነ ምግባራዊ ነው ወይስ ኢ−ሥነ ምግባራዊ ነው) የሚለውን ለመበየን፤ ይላሉ። ካንት ከዚህ አስተሳሰብ ወጣ ይልና ሰውን ዩኒቨርስ ላይ ይሰቅለዋል። ከጥቅም አንጻር የሚመነጩ ተግባራት ነጻነት ይጎድላቸዋል፤ ይልቁንስ ነጻነት የሚገኘው በአመክንዮ በሚመራ ተግባር ነው።
በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ ፍላጎት ለማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር የሚስማማ ፍላጎት ነው፤ ስለዚህም አመክንዮን መሰረት ያደረገ ተግባር በግለሰብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አይችልም። ይልቁንስ ይህ ተግባር ዩኒቨርሳል ህግ ቢሆን ምን ይከሰታል? የሚለውን እያሰብን የምናከናውነው ንተገብረው ድርጊት ሥነ−ምግባራዊ ነው፤ ይለናል ካንት። በጠራ አመክንዮ ላይ የተመሰረቱ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ለመቅረጽ እንድንችል ሰዎች በዘልማድ ከተስማሙበት፣ የግለሰብ አመለካከት ከሚያደላበት እና በመንደርተኛው ሰው ፍላጎት ከሚመራ የሥነ ምግባር መመሪያ ነጥሎ ማሰብ ይጠይቃል። የዩኒቨርሳል ህግ ቀመር የተባለው የካንት የሥነ ምግባር መመሪያ እንደሚለው ከሆነ፤ “ማድረግ የምፈቅደው ነገር ሌሎችም ቢያደርጉትና ዩኒቨርሳል ህግ መሆን የሚችል ካልሆነ በስተቀር ፈቃዴን መፈጸም የለብኝም።” ይህ የካንት መመሪያ እንደሚለን@አንድን ተግባር ኢ−ሥነ ምግባራዊ የሚያደርገው ሌሎችም ሰዎች ልክ እንደኔው ቢተገብሩት ችግር የሚያመጣ ከሆነ ነው። ባለጉዳይን ማጉላላት ኢ−ሥነ ምግባራዊ የሚያደርገው ዋናው ነገር፣ ይህንን ተግባር አጠቃላይ በአለማችን/ዩኒቨርስ ላይ ብንፈጽመው ሥራ መከወን ስለማይቻል ነው፤ እንደ ካንት አስተሳሰብ። የድርጅት አባል የሆነን ሰው ብቻ ተጠቃሚ ማድረግና ሌላውን ዜጋ ከተጠቃሚነት ማግለል ኢ−ሥነ ምግባር የሚያደርገው ይህንኑ መመሪያ ሁላችንም ወስደን ብንተገብረው የድርጅት አባል የሆኑትን እኛም በተራችን ልንጎዳቸው ስለምንችል ነው።
ሌላው የካንት የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎችንም ሆነ የራሰህን ሰብእና በፍጹም መጠቀሚያ አታድርግ@የሚጠቀሙበትንም ነገር በማቅረብ አስተናግዳቸው እንጂ።” ይህ የካንት መመሪያ የሚያስተምረን ደግሞ ሁሉም ሰው ምክንያት/አመክንዮ የሚገዛው ነው@ስለሆነም በራሱ ላይ ቢደረግበት የማይፈቅደውን ነገር አታድርግበት ነው የሚለን። ይህንን ህግ (formula of the end in itself) በራሱ ሙሉ የመሆን ቀመር ይሉታል፤ የሥነ ምግባር ፈላስፎች። ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት የራሳችንን ጥቅም ብቻ ለማግበስበስ ሰዎችን መጠቀሚያ ማድረግ እንደሌለብን ይመክረናል ካንት። ችግር ሲደርስብን’ ጠላት ሲወርረን እና አንዳንድ የድርጅት ፈተናዎች ሲያጣብቁን ብቻ “የመንግስት ሥልጣን የህዝብ ነው፤ ከህዝብ በአደራ በምርጫ አማካኝነት የተቀበለው ነው” እያሉ የህዝቡን ድጋፍ ማሰባሰብ ሳይሆን፤ ችግር ባፈጠጠበት ወቅትም፣ በጥጋቡም ዘመን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት አክብሮ በተግባር ማስመስከር ነው ሥነ ምግባራዊ የሚያስብለን።
ባላገሮች ዛሬ ጥዋ ተርታው ደርሶን፣ ሥልጣን ላይ ስንሆን፤ ስንቅ እያቀበሉ የታገሉለትን ዓላማ ካልፈጸምንላቸው… ሌላ አማራጭ መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፤ የራሳቸው የትግል አመክንዮ አላቸውና እንደ ማለት ነው። የካንት ወሳኝ የሥነ ምግባር ፍልስፍና አስተዋጽኦ ተብሎ ከሚጠቀስለት አንዱ “ድርጊቶች የግብረ ገብ ዋጋ የሚኖራቸው አንድ ሰው ድርጊቱን የምፈጽመው የውዴታ ግዴታዬ /duty for its own sake/ ነው ብሎ አምኖበት ከሆነ ብቻ ነው” የሚለው አስተምህሮው ነው። የውዴታ ግዴታ የምንለው ምንም ቀጥተኛ ጥቅም የማናገኝበት፣ ነገር ግን ስራው መሰራት ስላለበት የምንሰራውን ስራ ያጠቃልላል። ለምሳሌ መኪና ስናሽከረክር የመንገድ ምልክቶችን እና መብራቶችን ማክበር ያለብን… ትራፊክ ፖሊስ ስላለ ብቻ ሳይሆን… መኪና ስናሽከረክር ምልክቶችን አክብረን በህግ መገዛት ስላለብን መሆን አለበት እንደ ማለት ነው። እንዲህ ያለ ጥቅም እንዳገኝ ይህንን መልካም ስራ ልስራ ብለን የምንሰራው ሁሉ ለካንት ሥነ−ምግባር… ከንቱ ነገር ነው።
ይህንን ስራ መስራት ይገባኛል፣ ግዴታዬ ነው፤ ሰው እስኪያዝዘኝ ድረስ መጠበቅ የለብኝም፤ ወይም አንዳች ጥቅም እስካላገኘሁበት ድረስ ምን አገባኝ! ብለን መተው የለብንም ይለናል ካንት። ለማንኛውም፤ ተራ የግብረገብ አስተሳሰብ የሚስማማ ሐሳብ ነው፤ ብሎ መጀመሪያ ቢያስተዋውቀውም፤ ሰነባብቶ ግን በአመክንዮ ለሚመሩ የግብረገብ ሐሳቦች መሰረታዊ ክፍል አድርጎታል። ማንኛውም ጭንቅላት/አመክንዮ ያለው ሰው የሚፈጽመውን ድርጊት ሥነ ምግባራዊ ነው ወይስ ኢ−ሥነ ምግባራዊ ነው ብሎ ለመበየን እርሱ የሚሰራውን ድርጊት ሌሎች ሰዎች እንዲፈጽሙት ቢፈቅድላቸው በዩኒቨርሳችን ላይ ምን ዓይነት ምስቅልቅል ወይም ውበት ይከሰታል ብሎ በመወሰን መሆን አለበት፤ ይለናል። ለካንት፤ የተፈጥሮ ህግና የግብረገብ ህጎች ዋናው መሰረታቸው የሰው ልጅ አመክንዮ ነው። እነዚህ፤ ሁለት ህጎች/የተፈጥሮ ህግና የስነ ምግባር ህግ/ በአንድ መለኪያ መስፈር የማንችላቸው የሁለት ዓለም “ሰዎች” ናቸው፤ ተፈጥሮና ነጻነት። አንዱ/ተፈጥሮ/ የሆነ ነው@ ሌላኛው/ነጻነት/ ሲሆን እንደ ምን መሆን ይገባናል? የሚል ብያኔ በውስጡ ያዘለ ነው። ካንት፤ እነዚህን የተለያዩ የሚመስሉንን ዓለማት አንዳች ድልድይ ሰርተን ማገናኘት ይገባናል ይላል።
ምክንያቱ ደግሞ፤ ሁለቱ በአእምሯችን የፈጠርናቸውና በኃይል እላያችን ላይ የጫንናቸው ጉዳዮች በመሆናቸው ምክኒያት ነው። ይህንን ጉዳይ የበለጠ ሲያብራራም እንደሚከተለው ይላል፡- ሁለት ጉዳዮች አእምሮዬን በአዲስና በላቀ አድናቆት ይሞሉታል@ እነዚህም በከዋክብት የተዋጠው ከላዬ ላይ ያለው ሰማይና ከውስጤ ያለው የግብረገብ ህግጋት ናቸው። ሁለቱንም ከፊት ለፊቴ አምጥቼ አያቸዋለሁ@ ወዲያውም ከራሴው ኅልውና ጋር ይጣበቃሉ። በአንድ መለኪያ ለመለካት ከባድ የሚመስሉትን ነገሮች በዚህ አስተያየቱ ሊያስታርቃቸው ይሞክራል። የውጫዊውን (የዩኒቨርሱን) ህግጋት እና የውስጡን በሰው ልጅ ፍላጐት ምርጫ የሚመጡ ህግጋትን እያነጻጸረ የሕይወት መመሪያዎችን ይቀርጻል። የዓለም ተፈጥሯዊ እሴት ነጻነት ነው፤ ፈቃድ ላይ የተመሰረት ነጻነት፤ ምንም አስገዳጅ ነገር የማይጫንበት ነጻነት። የሰው ልጆች በራሳቸው ፍጻሜ/ምልዑ ናቸው፤ ስንል አመክንዮ/ምክንያት ስላላቸው ሳይሆን፤ ይልቁንም የነጻነት ባለቤት ስለሆኑ ነው ይለናል ካንት። አመክንዮ ዝም ብሎ አንድ ሃሳብ ላይ ለመድረስ የምንጠቀምበት መንገዳችን ነው፤ ከነጻነታችን ሊበልጥብን አይችልም። የሰው ልጆች ክብርን ለድርድር ማቅረብ የሌለብን፡- ክብራቸው ከነጻነታቸው ስለሚመነጭ ነው፤ ከተፈጥሮ ህግጋት ጋር እያነጻጸርነውም ቢሆን፣ የሰው ልጆች መገዛት ያለባቸው እራሳቸው በፈቃዳቸው ላወጧቸው ህጎች ነው።
አመክንዮ ዋጋ የሚኖረው በራሱ ሳይሆን ነጻነት እንድንጎናጸፍ ወይም እራሳችንን እንድንሆን የሚያደርገን ከሆነ ነው። ስለዚህም፤ ነጻነት እንዲኖረኝና እራስን የመሆን ክብርም እንድጎናጸፍ እያንዳንዱን የምሰራውን ስራ የመስራት የውዴታ ግዴታዬ መሆን አለበት። ዛሬ የደለበ ሥልጣን ሊኖረኝ ይችላል፤ ምናልባትም ከአፌ ትዕዛዝ እስኪወጣ የሚጠባበቁ ወጠምሻ ወታደሮች በዙሪያዬ ሊኖሩም ይችላሉ። ነገር ግን፤ ይህንን ጉልበቴን እየተመካሁ የምሰራቸው ስራዎች ሌሎችም ይህንን እድል ቢያገኙትና እኔ ላይ ቢፈጽሙት’ክብሬንና ነጻነቴን የሚያስከብርልኝ መሆን አለበት። ስለሆነም፤ እያንዳንዱ የምከውነው ስራ የውዴታ ግዴታዬ የሚሆነው የራሴኑ ክብርና ነጻነት ለማስጠበቅ ነው ማለት ነው። ዛሬ ብዙ ሰዎችን በደልኩ ማለት፤ ነገ የነሱ ተራ ሲሆን ደግሞ ብዙ የማወራርደው የበቀል እርምጃ ይጠብቀኛል ማለት ነው። ዛሬ አመክንዮዬን ሳላንጋድድ፣ በአግባቡ እየተጠቀምኩ የምከውናቸው ስራዎች ግን ማንኛውንም በአመክንዮ የሚመራን ሰው የሚያስማሙ ስለሚሆኑ ያልተወራረደ ውዝፍ ሒሳብ አይኖርብኝም ማለት ነው፤ በእራሴ ነጻና ምልዑ እሆናለሁና። ከዚሁ ጋር የሚያያዝ አንድ ታሪክ ላንሳ። ኢየሱስ ክርስቶስና መጥምቁ ዮሐንስ በስድስት ወር ነው አሉ የሚበላለጡት።
እናም ልጅ ሆነው እንደ ልጆች ወግ ትግል ጥሎሽ ጨዋታ እየተጫወቱ ሳለ፤ዮሐንስ ትልቅነት ይሰማውና ክርስቶስን ይጥለዋል። ሁለተኛም ሲታገሉ ዮሐንስ ድል አድራጊነቱን ለማሳወቅ ጠበቅ አድርጎ ክርስቶስን ጣለው (አሉ) በሦስተኛው ሲታገሉ ክርስቶስ ዮሐንስን አናቱ እስኪ ዞርበት ድረስ ከመሬት ቀላቀለው። ዮሐንስ ሰማይና ምድር ተደበላለቀበት፤ ቀስ ብሎ እራሱን አረጋጋና ክርስቶስን ጠየቀ “እስካሁን ለምን ዝም አልከኝ፤ለምን ቀድመህ አልጣልከኝም” ሲል ጠየቀው፤ ክርስቶስም ሲመልስ “ሳይጥሉኝ አልጥልም ብዬ ነው” አለ፤ አሉ። የሰው ልጅ የውስጥ የግብረገብ ህግጋትና የሰማዩ ከዋክብት ሳይጥሉት የማይጥል ተፈጥሯዊ ህግ አላቸው። የሰው ልጅ ሲያከብሩት መከበርን ማወቅ አለበት። ለመከበርም ማክበርን መማር አለብን። ነጻነትንና እራስን መሆንንም በዚህ መልኩ መጎናጸፍ እንችላለንና።

addisaddmas

No comments:

Post a Comment