Thursday, November 21, 2013

መድረክ በሳዑዲ መንግስት ላይ ስልፍ እንዳይወጣ በከለከለው ኢሕአዴግ ላይ ሰልፍ ሊወጣ ነው


- ሰላማዊ ሰልፉ ለህዳር 29 ተጠርቷል

በዘሪሁን ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ጉዳት በመቃወም በሳዑዲ አረቢያ መንግስት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢጠራም መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ይካሄዳል፤ በቂ የፖሊስ ኃይል የለኝም የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ መድረክ ተቃውሞውን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንደሚያደርግ ገለፀ።
የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው መድረክ የተቃውሞ ሰልፉን በተመለከተ በመንግስት የተሰጠው ምላሽ የማያሳምንና የሕዝብን ብሦት በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያፍን ተግባር በመሆኑ የሳዑዲ አረቢያ መንግስትን ለመቃወም ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የተቃውሞ ሰልፉ ሕዝብን እያፈነ ባለው መንግስት ላይ ማነጣጠሩን የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል።
merara gudina
ሰልፉ በመጪው ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም መነሻውን ስድስት ኪሎ የመድረክ ጽ/ቤት አድርጎ መድረሻውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እንደሚሆን ዶ/ር መረራ ጨምረው ገልፀዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት የሳዑዲ አረቢያን መንግስት እንዳንቃወም አድርጎናል።” ያሉት ዶ/ር መረራ የኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሕዝቡን ብሦት በተቃውሞ እንዳይገልፅ አድርጓል። የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ባለው ፍቅር ይሁን በሌላ ምክንያት ለጊዜው ግልፅ ባልሆነልን ምክንያት ተቃውሞአችንን በመከልከሉ የአሁን ሰላማዊ ሰልፍ በመንግስት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ዶ/ር መረራ ተናግረዋል።
እስከአሁን ባለው ሂደት መንግስት ሕገ-መንግስታዊና ሰብአዊ መብት የሆነውን ተቃውሞን በሰልፍ የመግለፅ መሠረታዊ መብት አሳማኝ ባልሆነ መንገድ በመጣስ እየተረባረበ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መረራ ሕዝቡም ይህንኑ እንዲገነዘብልን ሲሉ ጠይቀዋል። “በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ መንግስታት ኢትዮጵያዊያን የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲዎች በሚገኙባቸው ከተሞች ሁሉ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ እየፈቀዱ የሀገራችን መንግስት ግን ከራሱ አልፎ ሌሎችን ባዕዳን መንግስታትን እንዳንቃወም መከልከሉ አስገራሚም አሳዛኝም ነው” ሲሉ አያይዘው ገልፀዋል።
ባለፈው እሁድ ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም መድረክ ጠርቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማዋ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንዲሁም በቀጣይ የሚደረጉ ስብሰባዎች ስለሚኖሩ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ማስታወቁ አይዘነጋም። ባለፈው ቅዳሜ የክፍሉ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ይህንኑ የሚገልፅ ደብዳቤ ለመድረክ መላካቸው ታውቋል። በተመሳሳይ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው አርብ በሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ አካባቢ የጠራው ሰልፍ እውቅና እንደሌለው በመንግስት በኩል ተገልጾ ለሰልፉ የወጡ ከሳዑዲ አረቢያ የመጡ ተሳታፊዎች ጭምር በፖሊስ መደብደባቸውና የፓርቲው አመራሮችና ጋዜጠኞች ጭምር ታስረው መፈታታቸው አይዘነጋም። (ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ)
በዶ/ር መረራ ጉዲና መፅሐፍ ላይ
ሊደረግ የነበረው ውይይት ተሰረዘ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
በቅርቡ ለሕትመት የበቃው “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ እና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚል ርዕስ ለሕትመት በበቃው መፅሐፍ ባለፈው አርብ ሕዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ሊካሄድ የነበረው ውይይት ተሰዘረ።
ውይይቱ ተዘጋጅቶ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የጀርመን ተቋም የሆነው የፍሬዲሪክ ኤቨርት ፋውንዴሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ነው። ተቋሙ ከዚህ በፊት የንባብ ባህልን በማበረታታት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ምሁራን በታተሙ መፅሐፎች ላይ ሕዝባዊና ምሁራዊ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል። በህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ፕሮግራምም ላይ የመፅሐፉ ደራሲ ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ ምሁራን አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢም የፕሮግራሙ ማስታወቂያ ተለጥፎ ሲያበቃ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጎ የዕለቱ ዝግጅት ተሰርዟል።
የመፅሐፉ ደራሲ ዶ/ር መረራ ጉዳዩን በማስመልከት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መፅሐፉ ኢህአዴግን ሳያስጨንቀው የቀረ አይመስለኝም ብለዋል። በተለይ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እየመራ ያለበት “ቀልድ” ሀገሪቱን የትም አያደርሳትም የሚለው የመፅሐፉ መደምደሚያ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ ቅሬታ መፍጠሩን አፍቃሪ መንግስት ከሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ታትመው ከሚወጡ ፅሁፎች እየተረዳሁ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ስለጉዳዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አዳራሹን እንደሚፈልገው በመግለፁ ዝግጅቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋግጠዋል። የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ የጀርመን ተቋም የሆነው ፍሬድሪክ ኤቨርት ፋውንዴሽን መሆኑን ጠቅሰዋል። የዚህን ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ያሬድ ፈቃደን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምስቅልቅል ጉዞ እና የህይወቴ ትዝታዎች” የሚለው የዶ/ር መረራ መፅሐፍ በቅርቡ በሀገሪቱ ከወጡ የፖለቲካ መፅሐፎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።¾

zehabesha

No comments:

Post a Comment