Wednesday, November 20, 2013

ምናልባት ሰሚ ከተገኘ( ቢንያም ክፍሌ/ ከሪያድ)

Foreign workers wait for a taxi as they leave the Manfuhah neighbourhood of the Saudi capital Riyadh on November 10, 2013, after two people have been killed in clashes between Saudi and other foreign residents the previous day, according to the Saudi police. On November 4, the authorities began rounding up thousands of illegal foreign workers following the expiry of a final amnesty for them to formalise their status. AFP PHOTO/FAYEZ NURELDINE (Photo credit should read FAYEZ NURELDINE/AFP/Getty Images)
በተለይ በዚህ አስከፊ ጊዜ ምን በጎ ዜና አገኝ ይሆን እያለ የሚያውቃቸውን የዜና ምንጮች ሁሉየማይጎረጉር በውጪ ሃገራት በተለይም በሳዑዲ የሚኖር ኢትይጵያዊ አለ ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ። እኔም ከነዚህ
ህዝቦች አንዱ ነኝ። ያውም ሪያድ የምኖር። ባለፈው ሳምንት በሪያድ መንፉሃ ከተከሰተው ሁከት በኋላ የሳዑዲ የዜና አውታሮች በሙሉ ኢትዮጵያውያኑን በመኮነን ዘመቻቸው ላይ ሃይላቸውን ሲያስተባብሩ ስመለከትና
በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተዘራው የጥላቻ ዘር መብቀል መጀመሩን እኔና ሌላ ኢትዮጵያዊ ባልደረባዬ ባለቅነት በምናሰራቸው ግለሰቦች ሳይቀር ጥላቻውና ግፊቱ ቢበዛብን “ምን እየተደረገ ነው?” ብለን ለማጣራት በምሳ ሰዓት እረፍታችን ወደ “ኢትዮጵያ ኤምባሲ” አመራን፤ ሚዛናዊ ዜና ፍለጋ።
ስንደርስ ያስተዋልነው ነገር ለማመን የሚያስቸግር ሆኖ አገኘነው። ከሁሉ የከፋው ግን የ”ኤምባሲው” የስራ አፈጻጸም ብቃት ማነስ ነበር። በሁለቱም መንግስታት ዘንድ ምንም እንኳን “ህገወጦቹን” ወደሃገራቸው
መመለስ የታሰበበትና “በቂ ጊዜ” የተሰጠው ቢሆንም፤ በሁለቱም መንግስታት ዘንድ ይህን አይነቱ የጅምላ ዘጸኣት ይሆናል ተብሎ ግን በጭራሽ እንዳልታሰበበት ለመታዘብ የስራ አፈጻጸም እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ሆኖ አላገኘነውም። ምንም አይነት የ”አደጋ ጊዜ” ዕቅድም ሆነ ዝግጅት በቦታው አልነበረም። ነገር ግን በሁለቱ መንግስታት ዘንድ አንዱ ሌላኛውን መኮነኑን አጧጡፈውታል። ከሳዑዲ ወገን “የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለዜጎቹ የጉዞ ሰነድ ሊያቀርብልን አልቻለም” የሚል አቤቱታ በተገኘው የመገናኛ ብዙሃን ሁሉ ሲዛመት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደግሞ “የሳዑዲ መንግስት በጣት አሻራ በማሳበብ ነገሮችን እያጓተተ ነው” የሚል ምላሽ ባንድ ወገን ሲሰጥ በሌላ ወገን ደግሞ “እነዚህ ሁሉ ህገወጦች ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለን ስለማናምን የያንዳንዱን ግለሰብ ማንነት ማጣራት የጉዞ ሰነዱን ከማደል በፊት ልንሰራው የሚገባን ሃገራዊ ጊዴታችን ነው” በማለት ለነገሩ መጓተት ሌላ መልስ ይሰጣል።
ይህ በንዲህ እያለ ከመንፉሃው ሁከት በኋላ በመላው ሪያድ ያለ ራሱን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚቆጥር ህዝብ ሁሉ በየመንገዱ ወቶ ወደ ሃገሩ የሚወስደውን ወገን በመጠባበቅ ላይ ነው። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ዋናው ጉዳይ እነዚህ በየጎዳናው የፈሰሱት ወገኖች በሁለቱ መንግስታት መካከል ያለው ህጋዊም ሆነ ከንዝህላልነት የመነጨው ዜጎችን ካንድ አገር ወደሌላ ሃገር የማንቀሳቀስ ቢሮክራሲ የተረዱ አይደሉም። ሁሉም እጃቸውን ለፖሊስ ባስረከቡበት በዚያው ቀን ከዘገየ ደግሞ በማግስቱ ወደ ሃገራቸው እንደሚገቡ ብቻ ነበር የሚያውቁት። እዚህ ላይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ሌላው እውነት ደምሞ (መራራም ቢሆን) እነዚህን ዜጎች ማሳፈሩ የሚጠይቀው ቅድመሁኔታ ነው።
የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ መንግስታት ላንድ ሰው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የሚከሉት ናቸው፡
የስራው ክፍፍል ባለድርሻ
1, ከየመንገዱና ከየቤቱ ኢትዮፕያውያኑም እየሰበሰቡ ከፍተት በተገኘበት ቦት ሁሉ ማጎር - ሳዑዲ
2. ለታጎሩት ሰዎች ምግብና ውሃ ማቅረብ -ሳዑዲ
3. በቀን ለተወሰኑ ደቂቃዎች የህክምና ባለሙያዎች ማቅረብ- ሳዑዲ
4. ሴቶች የከፋ ችግራ በሳዑዲ ወጣቶች እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ማድረግ- ሳዑዲ
5. የኢትዮጵያ ኤምባሲ የምዝገባ ግብረሃይል እስኪመጣ መጠበቅ- ሳዑዲ
6. ስም ምዝገባ (እናቶች፣ ህጻናት፣ ነፍሰጡሮች፣ ሴቶችና ምናልባት በስተመጨረሻ ወንዶች) -ኢትዮጵያ
7.በየምድባቸው መሰለፍ- ኢትዮጵያ
8. ከሰላሳ መጠይቆች በላይ ያለው መጠይቅ መሙላት- ኢትዮጵያ
9. ፎቶ መነሳት- ኢትዮጵያ
10. አሻራ መስጠት- ኢትዮጵያ
11. ከላይ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከመጠይቁ ጋር አባሪ አድርጎ ወደኤምባሲ ወስዶ የተጻፈውን መረጃ ሁሉ ወደጉዞ ሰነዱ እየገለበጡ ፎቶ ግራፍና የሰነድ ቁጥር እየሰጡ ለፊርማና  ለማህተም ማዘጋጀት (ባንድ ግለሰብ ብቻ ነው የሚሰራው)- ኢትዮጵያ
12. የተዘጋጁትን የጉዞ ሰነዶች ፎቶኮፒ እያደረጉ ፋይል ማድረግ- ኢትዮጵያ
13, የተዘጋጁትን የጉዞ ሰነዶች ለሳዑዲ ፓስፖርት ቢሮ ማስረከብ- ኢትዮጵያ
14, ሰነዳቸው የደረሰላቸውን ሰዎች ወደማሳፈሩያ እስር ቤቶች ማንቀሳቀስ- ሳዑዲ
15. የያንዳንዱን ገለሰብ የጣትና ያይን አሻራ መውሰድ- ሳዑዲ
16. የበረራ ቲኬት ማዘጋጀት- ሳዑዲ
17. የበረራ ወረፋ ማስጠበቅ- ሳዑዲ
18. ማሳፈር-ሳዑዲ
እዚህ ላይ መስተዋል ያለባቸው ሌሎች አንኳር ጉዳዮችም አሉ። አንደኛ ከነዚህ ታጓሪዎች መካከል ከግማሽ የማያንሱት ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም በርካታ የደረሱም ሆነ ያልደረሱ ነፍሰጡሮች መሆናቸው ሲሆን
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከላይ በተለይ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የተደረደሩት ጉዳዮች በእንዲህ አይነትም ያደጋ ጊዜ መከተል ምን ያህል ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። ከነዚህ በማይተናነስ መልኩ ደግሞ እነዚህ ሁሉ ዜጎች የታጎሩባቸው ማጎሪያ ቦታዎች ያሉት ጣራ ያላቸው ክፍሎች በምንም ሁኔታ ከታጓሪዎቹ 20% እንኳን ስለማይስተናግዱ አብላጫው ዜጋ ሰማይን ጣራው አድርጎ ብቻ ነው ያለው። ምናልባት ይህ መረጃ ለብዙዎች ላይገርም ይችላል። አንድምታውን የሚረዱት የሪያድን ያየር ጸባይ የሚያውቁት ብቻ ናቸው። በዚህ ወቅት ሪያድ በመጀመሪያ ባቧራ አስከትሎም በዝናብ ከዚያም በቁር የምትመታበት ወቅት ነው። ምናልባት እንዲህ ያለ ያየር ጸባይ ባገራችን የሚከሰትው በቀናት ወይም በሳምንታት ልዩነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እዚህ ሁሉም ባንድ ቀን የሚከሰቱ እውነቶች ናቸው።
እንግዲህ በዚህ አይነት መከራ ውስጥ ያሉት ወገኖች ህጻናት፣ ነፍሰጡሮች፣ እናቶች፣ ሴቶች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን መሆናቸው መዘንጋት የሌለበት ሃቅ ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚደርስላቸው አንዳች አካል ይጠብቃሉ። ሁሉም ወደወገኖቻቸው ባገኙት የመገናኛ ዘዴ ያሉበትን ሁኔታ ለማስታወቅ ይጥራሉ። የጥሪዎቻቸው ተቀባዮች ግን አንዳች የሚያደርጉበት ስልጣንም ሆነ ጉልበት የላቸውም። ፖለቲካዊ ስልጣኑን ወደጨበጠው ኤምባሲም እሪታቸውን ያሰማሉ። ኤምባሲውም ካለበት ያቅም ውሱንነትና ካስቀመጠው የተውሰበሰበ ቢሮክራሲ የተነሳ የነሱን ጩኽት የሚያዳምጥበት ጆሮ አቷል። እኒሁ ወገኖች ከታጎሩበት ቦታ ሆነው ዙሪያቸውን ለሚጠብቋቸው የሳዑዲ ፖሊሶች እሮሯቸውን ማሰማታቸውን አላቆሙም። ነገር ግን ማጎሪያዎቹን እንዲጠብቁ የተመደቡት ፖሊሶች ከልምዳልባነታቸው በተጨማሪ ለነሱም ከመንግስታቸው የተሰጣቸው ምንም አይነት መረጃ ባለመኖሩ ዝምታን መርጠዋል። ትኩረታቸውን ተደጋግሞ በሚከሰተው የታጓሪዎች ግጭት ላይ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። መናገር የሚችሉትም አንድ ነገር ብቻ ነው። “የኛ መንግስት ምግብና ውሃ ከመጠለያ ጋር እያቀረበላችሁ ነው። መንግስታችሁ ግን የጉዞ ሰነዳችሁን አላዘጋጀላችሁም።” ብች ይሏቸዋል። የሚያውቁትም ይህንኑ ብቻ ነው። እንግዲይ የቀራቸውን ያላቋረጡት ነገር ቢኖር ሁሉም በየምነታቸው ለፈጣሪያቸው የ”ድረስልን” ጥያቄ ማቅረብ ብቻ ነው። እስካሁን ግን ከዚያም አቅጣጫ የመጣ ምላሽ አላዩም። ይልቁንም ዝናቡና ብርዱ በረታባቸው እንጂ።
አንድ ነገር መካድ አይቻልም። በሚኖሩበት ሃገር ህግ መሰረት ህገወጦች ናቸው። ይሁንና ህገወጥም ሰውነው። ይህ መዘንጋት የለበትም። እናትና ልጅ የተለያዩበት አጋጣሚ አለ። እናት ሪያድ ልጅ ኡምዘሃሚያ
(90ኪሜ)። አባት አስር አመት ያልሞላ ልጁን ይዞ እናትየዋ የት እንዳለች እንኳን ማወቅ ያልቻለበት ሁኔታ ትንሽ አይደለም። በተለያየ ቦታ በደረሱት ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ምንም አይነት የህክምና እርዳታ ያላገኙት ብዙ ናቸው። ህጻናት ልጆቻቸው በበሽታ የሚሰቃዩባቸው፣ ባሎቻቸው በግርግሩ የሞቱባቸውመበለቶች፣ አባቶቻቸው የሞቱባቸው ደሃደጎች፣ ለወራትን ላመታት ጉልበታቸውን የገበሩበትን ምንዳ ያልተከፈላቸው ሴቶችና ወንዶችን፣ ከሞቱት ጋር አብረው እንዳይቆጠሩ ትንፋሻቸው ጉሮሯቸውን አላልፍ ብላቸው በጣር ያሉትን ወገኖች፣ ራሳቸውን እየሳቱ ቢወድቁም ወደህክምና የሚያደርሳቸው ያጡትን ብዛት የታጎሩበት ማጎሪያዎች ይቁጠሯቸው።(በነገራችን ላይ ማጎሪያዎቹን የሚጠብቁት ፖሊሶች የመጀመሪያ ህክምና እንዲቀርብ ከማድረግ ወጪ በሽተኞችን ከታጎሩበት ቦታ ወደተሻለ የህክምና ቦታ ለመውሰድም ሆነ አምቡላንስ ለመጥራት ስልጣን የላቸውም። ይህ ወገኖችን ለማንኛውም ምክንያት ወደ ማንኛውም ቦታ የማዛወር መብትም ሆነ ስልጣን ያለው ኤምባሲው ብቻ ነው) በየማጎሪያ ጣቢያው የሚወልዱት፣ መውለጃቸውን ደቂቃ የሚጠባበቁም ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። አስት ቀን ያልሞላቸው ህጻናት፣ ወር ያልሞላቸው ህጻናት፣ አመት ያልሞላችው….. ስንቱ ተዘርዝሮ እንደሚያልቅ ለኔ ከመረዳትና ከመግለጽ ችሎታዬ በላይ ሆኖ አጊኝቸዋለሁ።
መከራቸው የከበደባቸው፣ ሃዘናቸው ያየለባቸው፣ ጩኸታቸው ያልተሰማላቸው፣ የተስፋ ጭላንጭል የማይታያቸውና አለም፣ መንስታቸው፣ በጠቅላላው ሰብዓዊ ፍጡርም ሆነ ፈጣሪ ጆሮ የከለከላቸው፤ መከራና ተስፋ
ካገራቸው ያሰደዳቸው፣ ስደት ያንገላታቸውና ያረብ አገር ስራና አሰሪ ያንሰፈሰፋቸው 35000 በላይ ወገኖቻችን በየማጎሪያውና በይጎዳናው ወድቅው ቀጣዩን ሰቆቃቸውን ብቻ እንደተስፋ የሚጠባበቁትን ወገኖቼን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል በየማጎሪያው በተዟዟርኩበት ያለፉት ሰባት ቀናት ያስመለከቱኝ ነገር ከመከራቸው ውቅያኖስ በማንኪያ ጨልፌ ለማቅረብ ፈለኩ እንጂ ጸሃፊነት ሞያዬም ፍላጎቴም አልነበረም። እናም እባካችሁ ይህንን የምታነቡ ሁሉ ሌላ እኔ ያልጠቀስኩት ነገር ግን የመከረኛን ጩኸት ሊሰማና እንባውንም ሊይብስ የሚችል ጆሮ ያለው አካል የምታውቁ ከሆነ፣ የነዚህን መከረኞች ጩኸት አስተጋቡለኝ።
(በትናንትናው ዕለት በራሳቸው ተነሳሽነት በየማጎሪያው ቦታዎች እየተዘዋወሩ የጉዞ ሰነድ ቅድመፎርም ሲያስሞሉ የዋሉ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለኤምባሲው ቋሚ ሰራተኛ ምንም አይነት ስራ እንዳይሰሩ
ታግደው “ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጠይቅን ስራ በራሳቸው ብቻ በመስራታቸው እንደሚጠየቁበት ሁሉ ተነግሯቸዋል።)
ቢንያም ክፍሌ (ከሪያድ)

 http://revolutionfordemocracy.com/2013/11/20/79-25/

No comments:

Post a Comment