Tuesday, November 19, 2013

ይድረስ ለንጉስ አብደላ እንዴት ከረሙ ንጉስ ሆይ!?

ንጉስ ሆይ የስደት ህይወት ምን ያህል የስቃይ ህይወት እንደሆነ ያውቃሉ ብዬ አልጠይቆትም፤ እንዲያ ባለው የህይወት ዝቅታ ውስጥ እንዳላለፉ አውቃለሁና። ነገር ግን እንደው ተሳስተው የእስልምና ወይም የታሪክ መፅሃፍትን አንብበው ካወቁ ከዛሬ 1400 አመት በፊት በነብዩ መሃመድ አመላካችነት የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው እንደነበር ይገነዘባሉ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንኮራባቸው ባህሎቻችን አንዱ እንግዳ ተቀባይነታችን ነው። ለእኛ ለሃበሾች እንግዳ ክቡርነው ስንል እንዲያው ለማለት ብቻ አይደልም። እንግዳን የምናክብረው ጎንበስ ብለን እግሩን አጥበን፣ አልጋችንን ለእንግዳለቀን መሬት ተኝተን ነው። ያ ብቻ እንዳይመስሎት ጌታው! ከጠቦቶቻችን መሀል የሰባውን መርጠን አርደን በማቅረብ ነው። እንደዚያ አድርገን ነበር ቤተሰቦችዎን ከዘመናት በፊት የተቀበልን።
ንጉስ ሆይ!
የእኛ ያልናቸው መከራችንን ቢያበዙት ወደ አገርዎ ተሰደድን። ተሰደን ከደጅዎ ስንመጣ ክፉ ቀናችንን በመንደርዎ ለማሳለፍ ነበር። አያቶቻችን ለአያቶችዎ ያደረጉትን መልካም ነገር አስበን እግራችንን እንዲያጥቡን አልጠየቅንም። ክፉ ቀንንና ቅዝምዝምን ብቻም ሳይሆን የስደት ህይወትንም ጎንበስ ብሎ ማሳለፍን ህይወት አስተምሮናልና ይልቅስ ዝቅ ብለን እያገለገልናችሁ መኖር ጀመርን። ነገር ግን በመንደርዎ አጎንብሰን ብናድርም በሰላም መኖር አልቻልንም።
እንኳን የምንከራከረው የአገርዎን ባንዲራ በአደባባይ ማቃጠል የለብንም እያልን ነው። እስቲ ስለ እውነት ብለው ይፍረዱ ንጉስ ሆይ! ወንድሙ የታረደበትና እህቱ ታፍና ተወስዳ የተደፈረችበት ሰው በባንዲራዎ ላይ የነብዩ መሀመድ ስም ስላለ ማቃጠል የለብንም ሲል ቢሰሙ ምን ይሰማዎታል!? እውነት እውነት እሎታለው እንዲህ ያለን ጨዋነት ከአበሻ ምድር ውጪ የትም አያገኙ። እርሶ ግን ባንዲራውን ግንባሩ ላይ ያሰረ ወንድማችንን ሲገሉ ለባንዲራችን ያሎትን ንቀት ነው ያሳዩን። እየነገርኮት ያለሁት የሀበሻ ምድር የሚያበቅለው የሀገርዎን ህዝብ ሆድ የሚሞላውን ሩዝ ብቻ ሳይሆን ጨዋነትንና አስተዋይነትንም እንደሆነ ነው።
ንጉስ ሆይ ወንድም እህቶቻችንን በምድርዎ ሊያይዋቸው ባይፈልጉ እንኳን ከመግደል የተሻለ አማራጮች ነበሩዎት። ስደተኛ ማለት ህፃን ማለት ነው። ልክ ያቀፈውን አምኖ ያለስጋት እንደሚያንቀላፋ ጨቅላ። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ እንደ ህፃን አምኖዎት በጓዳዎ የተኛች ስደተኛን አስገድዶ መድፈር ጀግናም አያስብል። እውነት እውነት እሎታለው ጀግንነትም አይደል ስደተኛን መግደል።
ንጉስ ሆይ ታሪካችንን የማንበብ እድሉን ካገኙ በአለም አቀፍ መድረክ ከበሬታ የነበራቸው ንጉሶች ነበሩን። የወደዱትን በክብር በእንግድነት ተቀብለው የሚያስተናግዱ። ያልወደዱት ቢሆን እንኳን መግደል ሳይሆን ከጫማው ላይ የሚወዷት አገራቸውን አፈር እንዲያራግፍ አድርገው በሰላም የሚሸኙ።
ንጉስ ሆይ እኛ ኢትዮጵያውያን በበርካታ የመከራ ዘመኖች ውስጥ አልፈናል። የትኛውም መከራ ግን ጥሎ አስቀርቶን አያውቅም። ወደቁ ሲሉን ተነስተናል። ተበታተኑ ሲሉን ተቃቅፈናል። እንዲህ የእኛ የምንለው መንግስት በሌለን ሰሃት እንኳን ተደጋግፈን መቆም ችለናል። እንዴት ብለው ከጠየቁኝ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ከማለት ውጪ መልስ የለኝም። ምናልባት ዛሬ ሲሰነዝሩብን መልሶ መሰንዘር ቀርቶ መመከት እንኳን በማንችልበት የመጠቃት ህይወት ውስጥ ሆነን ቀን ጨልሞብን አግኝታችሁን ይሆናል። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውምና ነገ ሲሰነዘርብን የምንመክት ብቻ ሳይሆን ሰንዝረን ደም የምንመልስ እንሆናለን።
ልድገምሎት ንጉስ ሆይ! የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም! እንዲያማ ባይሆን የአፄ ቴዎድሮስ፣ የዮሃንስና የሚኒሊክ አገርን ልጅ እንደጠቦት በግ አጋድመው አያርዱትም ነበር። ቀን ጨልሞብን ባያገኙን ኖሮ የጣይቱን አምሳያ ሰርቶ አዳሪ ጀግና እህታችንን እንደ እንስሳ አስገድዳችሁ ደፍራችሁ አትገድሏትም ነበር። እመኑኝ ንጉስ ሆይ! የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም። እንዲያማ ባይሆን የአሉላን፣ የባልቻ አባ ነፍሶ ዘርን ገድለው ሬሳውን በአደባባይ አትጎትቱትም ነበር። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ ክፉ ቀን ሰብሮ አግኝተውን ነው የጎዱን።
እውነቴን ነው የምሎት ንጉስ ሆይ! አገራችን ኢትዮጵያ የሀገር ፍቅር በሌላቸው ባንዳዎች እጅ ባትሆን ኖሮ እመኑኝ ለእርሶ ቤት ግርድና አንሰደድም ነበር።
እመኑኝ ንጉስ ሆይ! ቀን ጨልሞብን የእኔ ባይ መንግስት አጥተን አግኝተውን እንጂ ሺዎችን ሲነዳ የኖረን ሀበሻ እንደ ለማዳ ከብት እየነዱ ማጎሪያ ጉረኖ ውስጥ አያስሩትም ነበር። ወደ ኋላ ሄደው ታሪካችንን ከጠየቁ እንኳንስ ለእኛ የእኛ ላልሆነውም የተበደለ የሰው ዘር ጦር ሰብቀን የምንደርስ ነበርን። እርሶ ምን ያድርጉ ቀን ጥሎን አገኙን። እውነት ምስክሬ ናት ንጉስ ሆይ ቀን ከፍቶባት ባያገኙዋት የበላይን ዘር ከስራችሁ ጥላችሁ አትደፍሯትም ነበር። ልቤ በሀዘን እየደማ ይሄንን ሀቅ ልንገሮት፣ በህብረት መቆም አቅቶን እርስ በርስ ስንወነጃጀል የቀን ሚዛን አጋድሎብን ባየገኙን ኖሮ “እንኳን ባንድ አካሉ ያውን በሚስቲቱ ይቆጣ ነበረ በታሰበች እህቱ”ን እየንጎራጎረ ያደገን የሀበሻን ልጅ ሚስቱንና እህቱን እፊቱ አትደፍሩም ነበር። ቀን ጨልሞበት አገኛችሁትና በቁሙ ገደላችሁት።
ንጉስ ሆይ እንደባቢሎናውያን በቋንቋ ካብ ተለያይተን የአንድ እናት ልጆች መደማመጥ አቅቶን አግኝተውን በአደባባይ አዋረዱን እንጂ ጥርኝ አፈራችን ተነካ ብለን ዘራፍ የምንል ነበርን። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ “የምስራቁን እብሪተኛ አስተንፍሰንዋል! የምእራቡ ነው የቀረን እሱንም…” እያልን የምንፈክርበት ዘመን እንኳን ብዙ አልራቀንም። ንጉስ ሆይ የቀን ሚዛን ለእርስዎ አድልቶ ልናድናቸው ያልቻልናቸው የወገኖቻችን የጣር ጩኸት ሰላም ቢነሳን በአደባባይ አለቀስን ። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ” ብለን ቅኔ የምንቀኝና የወንድን በአደባባይ ማልቀስ የምናነውር ኩሩዎች ነበርን። ምን ያደርጋል ዘመን ጀርባውን ቢሰጠን ወንድማማቾች ተሰባስበን በአደባባይ እንደ ሀገር አለቀስን።
ንጉስ ሆይ ሌላ የምሎት የለኝም። ብቻ የእኛ የምንለው መንግስት ኖሮን በክብር ቆመን ያገናኘን። ይመኑኝ ንጉስ ሆይ ያ ቀን እሩቅ አይደለም!
ጋዜጠኛና ደራሲ ኃይለገብርኤል ይመር


 http://revolutionfordemocracy.com/2013/11/18/56-92/

No comments:

Post a Comment