Friday, November 22, 2013

የሳምንቱ የአብርሃ ደስታ በፌስቡክ ላይ የተለቀቁ ምርጥ ጽህፎች


የነቀዘው የሙስና ትግል!
————————-
Abrham Destaስለ “የነቀዙ ህሊናዎች” አንድ የነቀዘ ፅሑፍ አዘጋጅቼ ስጨርስ መብራት ሃይል ነቀዘብኝና መብራት ሲጠፋ ፅሑፌን አብሮ ጠፋ። የፅሑፉ መሰረተ ሐሳብ ባጭሩ እነሆ።
የኢህአዴግ መንግስት የነቀዘውን ዘጋቢ ድራማ (ዘጋቢ ፊልም አላልኩም) በማቀናበር “ሙስናን ከልቤ እየታገልኩ ነው። እየታሰሩ ያሉ ባለስልጣናት በስርቅ እንጂ በፖለቲካ አለመሆኑ ይታወቅልኝ፣ ሰው ግን አያምነኝም” አለን። መንግስት ለሚናገረውና ለሚያደርገው ነገር ህዝብ እንደማያምነው ማመኑ አንድ ትልቅ ነገር ነው። ችግሩ ግን አሁንም በድራማው ማመን አለመቻለ ነው።
እኔ “የነቀዙ ህሊናዎች”ን ድራማ መንግስት በፈለገው መጠን አልተቀበልኩትም። በኔ እምነት በሙስና ሰበብ የታሰሩ ሰዎች በትክክል በስርቅ (ሙስና) የተያዙ አይመስለኝም። የታሰሩት በፖለቲካ ሊሆን ይችላል። ይህን የምልበት ምክንያት የታሰሩት (ወይ የተያዙት) ባለስልጣናት ሙስና አለመስራታቸው (አለመስረቃቸው) ወይ አለመስራታቸው (አለመስረቃቸው) ማስረጃ ስላለኝ ወይ ስለሌለኝ አይደለም። የኔ መከራከርያ ሐሳብ ‘በኢህአዴግ መንደር ሙስና የሰራ (የሰረቀ) ይታሰራል ወይ?’ የሚል ነው። ሙስና የሰራ የሚታሰር ቢሆን ኑሮ አብዛኞቹ ባለስልጣናት ይታሰሩ ነበር። አሳሪዎቹም ጭምር ይታሰሩ ነበር። የኢህአዴግ ሙሰኞች የታሰሩት ሰዎች ብቻ ናቸው? ከነሱ በባሰ ሁኔታ በሙስና የተዘፈቁ ግን ያልታሰሩ የሉም?
ኢህአዴግ ልናምነው ከፈለገ ሙስና የሰሩ ባለስልጣናት ሁሉንም መታሰር አለባቸው። የተወሰኑ እያሰረ ሙስና መስራታቸው ቢነግረን የታሰሩት በሙስና ነው ብለን ለማመን ይከብደናል። ምክንያቱም የሰረቀ ሁሉ እንደማይታሰር እያየን ነው። ብዙ ግዜ ኢህአዴግ የራሱ ልጆች የሚያስረው የፖለቲካ ልዩነት ሲፈጥሩ ነው። ለምሳሌ አቶ ስየ አብርሃ በሙስና ሰበብ የታሰረው ከመለስ ጋር አለመግባባት ከፈጠረ በኃላ ነበር። ስየ በትክክል ሙስና ሰርቶ ከሆነ የሰረቀው ከክፍፍሉ በኋላ ነው? ሊሆን አይችልም። ስየ ሰርቆ ከሆነ ከክፍፍሉ በፊት ነው መሆን ያለበት። ከክፍፍሉ በፊት ግን አልታሰረም። ስለዚህ ስየ ከመለስ ዜናዊ ጋር ባይጣላ ኑሮ ያለመታሰር ዕድል ነበረው ማለት ነው። ባይታሰር ኑሮ ሙስና መስራቱ አንሰማም ነበር።
ስለዚህ በኢህአዴግ የሚታሰር ሁሉ ሙስና የሰራ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እናም ኢቲቪን አላመንኩትም። ለመታመን ከፈለገ የሰረቁት ሁሉ ይታሰሩ።

“ከህወሓት የባስክ ትሆናለህ” አሉኝ
——————————
—–
“ጨቋኝ ስርዓት አልፈልግም” ብዬ በፃፍኩት ላይ አንድ የፌስቡክ ወዳጄ “አንተ ራስህ ስልጣን ብትይዝ ከህወሓት የባስክ አምባገነን ትሆናለህ” አለኝ።
እኔም እላለሁ፣
ከህወሓት የተሻልኩ እንደምሆን እርግጠኛ አይደለሁም (ራሴ ለግዜው እንደ ፓርቲ ልቁጠር)። ስለ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ። እኔ ሰለማዊ ታጋይ ነኝ። ስልጣን የምይዘው በህዝባዊ ምርጫ እንጂ በጠመንጃ አይደለም። የምወዳደረው በሐሳብ እንጂ በሃይል አይደለም።
ስለዚህ ስልጣን ስይዝ የራሴ ወታደር፣ ፖሊስ፣ ዳኛ ወዘተ ይዤ አልመጣም። ስልጣን የምይዘው በሕገመንግስት መሰረት እስከሆነ ድረስ በኔና በወታደሮቹ ያለ ግንኙት ሕገመንግስታዊ ይሆናል። ስለዚህ ወታደሮቹ እንደፈለኩ የግሌ የስልጣን ጥም ለማርካት አላዝዛቸውም። ዳኞችም ነፃ ይሆናሉ።
ስለዚህ እኔ ስልጣን ከያዝኩ በኃላ ከህወሓት ካልተሻልኩ በህዝብ ምርጫ እንደወጣሁ ሁሉ በሚቀጥለው በህዝብ ምርጫ ከስልጣን እወርዳለሁ። ከስልጣን ላለመውረድ ምንም ዓቅም የለኝም፤ ምክንያቱም በምርጫ ስልጣን የያዘ አካል የግሉ ወታደርና ፖሊስ የለውም። የስልጣን መሰረቴ የህዝብ ድምፅ ከሆነ በስልጣን ለመቆየት ስል ህዝብን አልጨቁንም። ከጨቆንኩ ደግሞ ህዝቡ ያወርደኛል።
የኢህአዴግ መንግስት ሰለማዊ ትግልን አጨልሞብኝ በትጥቅ ትግል ስልጣን ከያዝኩ ግን አምባገነን የመሆን ዕድል አለኝ። ምክንያቱም የስልጣን ምንጬ ጠመንጃ እንጂ ህዝብ አይደለም። ለህዝብ ታማኝና አገልጋይ የምሆንበት ዕድል ይጠባል። ስለዚህ በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት ቢያበላሽ እንኳ በምርጫ ይወርዳል። አሁን የቸገረን በጠመንጃ የመጣ መንግስት ነው።
ዓላማችን ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ስልጣን በጠመንጃ ከመያዝ በምርጫ የምያዝበት ስርዓት መገንባት ጭምር ነው።
(ስልጣን የመያዝ ዕቅድም ፍላጎትም የለኝም። የኔ ፍላጎት በነፃነት የፈለኩትን ማድረግ ነው። እኔ የሌሎችን መብት ሳልዳፈር የፈለኩትን የማድረግ ነፃነት እንዲኖረኝ የህዝብ መንግስት ወይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አለበት። ስልጣን መያዝ ነፃነትን ይገድባል)።

‘ኢትዮዽያዊነት’ ምንድነው?
——————————
የህወሓት በስልጣን የመቆየት ስትራተጂ መከፋፈል ነው። ለመከፋፈል ወዳጆችና ጠላቶች መለየት ነው። ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት “ሸዋ አማራ” ጠላቱ እንደሆነ ይሰብካል (‘ዓረና ከጠላቶቻችን ጋር እያበረ ነው’ የሚል ፕሮፓጋንዳ መሰረት እናድርግ)።
እንዴት ነው አንድ ህዝብ ለሌላ ህዝብ ጠላት የሚሆነው? የህዝብ ጠላት ሊሆን የሚችለው ገዢ መደብ ነው። ህዝብን የሚጨቁን ገዢ የህዝብ ጠላት ነው። ስለዚህ መወገድ ይኖርበታል። ህዝብ ግን የሌላ ህዝብ ጠላት ሊሆን አይችልም።
‘የሸዋ አማራ’ የትግራይ ጠላት መሆኑ የሚነግሩን ደርግ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍ በማጣቀስ ነው። ደርግ ጨካኝ የነበረው ለትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም፤ አማራውም፣ ኦሮሞውም ሌላውም ተጨቁኗል። የአማራ ህዝብም “ደርግ አማራ ነው፣ የኛ ነው” ብሎ ከሌሎች ህዝቦች የተለየ ድጋፍ ለደርግ አልሰጠም። ደርግም “ለአማራ ህዝብ የቆምኩ ነኝ” አላለም። ደርግ “ለኢትዮዽያ የቆምኩ ነኝ” እያለ ሁሉም ኢትዮዽያውያንን በደለ።
ህወሓት ከስልጣን የሚወርድ ከሆነ ትግራይ ኢትዮዽያ እንዲሆን የሚፈልግ አይመስልም። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በተመሳሳይ ዕድሜ መመዘን ግን ስህተት ነው። ምክንያቱም የህወሓት የስልጣን ዕድሜ አጭር ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ለዘላለም ይኖራል። በሌላ ስርዓት ሌላ ታሪክ ያስመዘግባል። ህወሓት ግን በምርጫ ወይ በጠመንጃ በቅርብ ግዜ መውደቁ አይቀርም፤ የተፈጥሮ ሕግ ነውና።
“ኢትዮዽያዊ ነኝ” ካልክ “የሸዋ ልሂቃን ደጋፊ ነህ” ይሉሃል። ኢትዮዽያ የሸዋ ፖለቲከኞች ብቻ የግል ንብረት ነች እንዴ? ኢትዮዽያኮ የሁላችን ነች። የትግራዮች፣ የአማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ ቤኑሻንጉሎች፣ ጋምቤላዎች፣ ዓፋሮች፣ ደቡቦች … የሁሉም ናት።
ኢትዮዽያዊ ማንነት ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሰጠነው ተሳስተናል። የፖለቲካ ተፎካካሪዎቻችን “ኢትዮዽያውያን ነን” ስላሉ እነሱን ለመቃወም “ኢትዮዽያውያን አይደለንም” ካልን ችግሩ የኛ ነው። ምክንያቱም ኢትዮዽያዊነታችን በራሳችን ፍቃድ ለሌሎች አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው። ኢትዮዽያዊነት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ማን ሰጠው? ኢትዮዽያውነት’ኮ የጋራ ማንነታችን ነው።
እያንዳንዱ ሰው የራሱ (የግሉ) የሆነ ማንነት አለው። በወረዳ፣ ዞን፣ ብሄር ወዘተም ቡድናዊ የግል ማንነት አለው። በኢትዮዽያ ደረጃ ደግሞ የሁላችን የጋራ የሆነ ኢትዮዽያዊ ማንነት አለን።
ፖለቲከኞች “እነዚህ ሰዎች ኢትዮዽያዊ ስሜት የላቸውም፣ በዘር ያስባሉ፣ ትክክለኛ ኢትዮዽያውያን እኛ ነን ወዘተ …” ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል። ምክንያቱም ኢትዮዽያ የየተወሰኑ ግለሰቦች አይደለችም። ኢትዮዽያ የሁሉም ነች። ኢትዮዽያዊነት የተወሰነ ብሄር ወይ ክልል ወይ አውራጃ የሚወክል አይደለም። ሁሉም የኢትዮዽያ ህዝቦች የሚወክል ነው።
የኢትዮዽያ ህዝቦች እንደ አንድ ሰው አንድ ዓይነት ሃይማኖት፣ ባህልና ማንነት ሊኖራቸው አይችልም። በአንድ ሀገር የተለያዩ ሰዎች እስካሉ ድረስ የተለያየ ማንነት አለ (በብሄር፣ ወረዳ ወዘተም የተለያየ ማንነት ነው ያለው)። ስለዚህ ኢትዮዽያዊነት የአንድ ሰው ማንነት ሳይሆን የብዙ ሰዎች ማንነት ድምር ዉጤት ነው።
ስለዚህ ኢትዮዽያዊነት የጋራ ማንነት ነው። ኢትዮዽያዊነት አብሮነት ነው። እናም አንድ ግለሰብ ወይ የፖለቲካ ድርጅት “እኔ ነኝ ትክክለኛ ኢትዮድያዊ” ካለ ኢትዮዽያዊነት ወደ አንድ አከባቢ (ብሄር ወይ ክልል ወይ መንደር) አውርዷታል ማለት ነው። ይህም ስህተት ነው።
ኢትዮዽያዊ መሆን ከደበረን ችግር አለ ማለት ነው። ችግሩ ጭቆና ሊሆን ይችላል። ጭቆና (ለምሳሌ የብሄር ጭቆና) ካለ ጭቆናውን ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮዽያውን ህዝቦች ተባብረው መፍታት ይኖርባቸዋል። ሁላችን ከተባበርን ችግሮችን (ብሄራዊ ጭቆናን) ማስወገድ እንችላለን።
ጭቆና ስለበዛብን ከኢትዮዽያ መገንጠል (አብሮነትን መቃወም) መፍትሔ ሊሆን አይችልም። እንበልና በትግራይ ህዝብ ወይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ብሄራዊ ጭቆና ተፈፅሟል። አሁን መታገል ያለብን በነዚህ ህዝቦች ላይ የነበረውን ብሄራዊ ጭቆና በማስወገድ ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ጉዳይ ሁሉም ዜጎች መተባበር ይኖርባቸዋል።
“ብሄራዊ ጭቆና ስለነበረ (ስላለ) መገንጠል እንፈልጋለን” የሚለው ሐሳብ አይመቸኝም። ምክንያቱም ጭቆናው ከነበረ አሁንስ ቢሆን እንዴት በመለየት መቅረፍ ይቻላል? ትግራዮችና ኦሮሞዎች ጭቆና የደረሰባቸው ባለፉ ስርዓቶች ከሆነ ላለፈው በደል አሁን በመገንጠል እንዴት መቅረፍ ይቻላል? ብሄራዊ ጭቆናው ያለው አሁን ድረስ ከሆነም ለመለየት ከመምረጥ አብሮ ታግሎ ጨቋኝ ስርዓቱ በመጣል እኩልነትን ማስፈን እየተቻለ ለመገንጠል ማሰብ ምን አመጣው?
ጨቋኝ ስርዓቱ ለማስወገድ አቅሙ ከሌለን ለመገንጠልም አቅሙ አይኖረንም። ምክንያቱም ከመገንጠል ስርዓቱን መቀየር ይቀላል። ምክንያቱም ለመገንጠል ብቻህን ነው የምትታገለው፤ ስርዓት ለመቀየር ግን ከኢትዮዽያውያን ወገኖችህ ጋር ነው የምትታገለው። ደግሞ በመገንጠል ጭቆና አይወገድም። ለእኩልነት ጠንክረው በመታገል እንጂ በመገንጠል ጭቆናን ያስወገዱ ህዝቦች የሉም።
ኢትዮዽያዊነቴ ለማንም አሳልፌ አልሰጥም። ኢትዮዽያዊነት ለ”ሸዋ አማራ” ብቻ የተሰጠ ማንነት አይደለም። ኢትዮዽያዊነት የሁላችን ነው።

ስም የማጥፋት ዘመቻ!???
—————————–
ህወሓቶች በኔ መጨነቅ የጀመሩ መሰለኝ (ስም የማጥፋት ዘመቻ መጀመራቸው ሳስብ ነው)። እርግጥ ነው የኔ ስም ማጥፋት / ማፍረስ አይችሉም። ምክንያቱም የኔ ስም አልተገነባም። ያልተገነባ አይፈርስም። እኔን አጀንዳ ማድረጋቸው (በዚህ ሳምንት በተለይ) ግን ለምን ይሆን?
መልሱ ቀላል ነው። ያሁን የህወሓት መሪዎችና የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች መለየት በመቻሌና ለይቼ በመምታቴ ይመስለኛል። ህወሓቶች ከትግራይ ህዝብ ተለይተው እንዲታዩ አይፈልጉም። ምክንያቱም ተቃዋሚዎች የትግራይን ህዝብ ከህወሓት ጋር ደርበው ዒላማ ሲያደርጉት ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ድጋፍ ያገኛል።
ስም ለማጥፋት አንዴ “አብርሃ የሚፅፈው ዉሸት ነው” ይላሉ፤ ሌላ ግዜ “የትግራይን ማንነት ትቶ ኢትዮዽያዊ ለመሆን ጥረት ያደርጋል” ይላሉ። የምፅፈው “ዉሸት” ከሆነ ለምን ት ሸበራላቹ? ዉሸት ከሚፅፍ ሰው በዉሸት የሚሸበር ሰው የባሰ ከንቱ ነው (እኔ የምፅፈው ዉሸት ነው ብላቹ ካመናቹ)። አዎ! አሁንም ኢትዮዽያዊ ነኝ። ምክንያቱም ትግራይ ነኝ። ትግራይ ደግሞ ኢትዮዽያ ነው።
ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ነጠልነው። አሁንም ከቀድሞ ታጋዮች ስንነጥለው ተሸበረ። አዎ! ለይተን አነጣጥረን መምታት አለብን።
ስም የማጥፋት ስትራተጂ የውድቀት መንገድ ነው።

No comments:

Post a Comment