Saturday, November 23, 2013

አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ክፍል 6




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን  በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ማይክሮ ችፕስ 3፡ ውጤታማ አስተዳደር ማሳጣት፡፡ ዛሬ ሁሉም መልካም አስተዳደር እያለ የሚደሰኩረው አይነት ልፍስፍስና በአለፉ ውድቀቶችና ውርደቶች ላይ ቁጭትና እልህ የሌለበት አስተዳደር አይደለም እንደ እኛ አይነቱ ገና በልተን ለማደር ዋስትና የሌለንን የምጣኔ ሀብት ጣሪያውን የነኩትን እንኳን አይዋጥላቸውም፡፡ እኛ ይርበናል እነሱ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት፣ ምናምን እያሉ ያልፈሰፍሱናል፡፡ በእኔ እምነት ለረሀብና ለድህነት የተገዛና የተዋረደ ሕዝብ አለም የሚዘፍንለት "ዲሞክራሲ" አያስፈልገውም፡፡  ይህ ማለት ግን ስብዕናን መጣስ ማለት አይደለም፡፡ የሄንን ከባሕላችንና በአኗኗራችን ከጥንት ጀምሮ እኛ እናውቀዋለን፡፡ ዛሬ ድህነት አዋርዶን ውሉ ጠፍቶብንና የሌሎች ባሪያዎች ሆነን ሌሎች ከሌሎች የራሳችንን ልንሰማው ተገደድን እንጂ፡፡ ዲሞክራሲ ሲጀምር በሪ አልባ የሞሆን ፍልስፍና እንጂ የፍትህ አመራርን የሚጋብዝ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ ማለት የሕዝብ አመራር መለት ነው፡፡ ሕዝብ የፈለገውን የሚወስንበት እንደ ማለት ነው፡፡ በየተኛውም መስፈርት ግን አንድ አገር በሕዝብ ውሳኔ እየተመራች ውጤታማ የመሆን እድል የላትም፡፡ ይህ እውነት ነው! አገራት ሁሉ ውጤታማ የሆኑትና እየሆኑ ያሉት ልዩ ተሰጥዖ ለአገራቸው ከውስጥ የሆነ ራዕያ ባላቸው ዜጎቻቸው ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች ግን በብዙ አፍሪካና ሌሎች ደሀ አገራት እንደሚነሱ በጡንቻ ብቻ ከራሳቸው ሆድ ያለፈ ራዕይ የሌላቸው አይነት አይደሉም፡፡ ይልቁንም በሌላኛው ጽንፍ ያሉ የአገርና የዜጎች ክብር ከምንም በላይ የሆነባቸው፣ የቀደመ የውድቀት ታሪኮቻቸው እጅግ የሚቆጯቸው፣ የጎደፈ ታሪክን ለመቀየር ቁርጠኛና አልህን የተላበሱ፣ ስለአገራቸውና ሕዝባቸው ክብር ራሳቸውን መስዋዕት የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ዛሬ አኛን ዲሞክራሲ እያሉ የሚዘፍኑብን የሕዝብ መብት አክባሪ መሳይ አገራት እኛ ከድህነ ውርደትና ባርነት ነጻ አይደግፉንም፡፡ የአስተሳሰብ ነጻነት ሊኖር ይገባል እያሉ ያጃጅሉናል፡፡ በዚህ በአስተሳሰብ ነጻነት ሽፋን ደግሞ የሙታን አስተሳሰቦች በእኛ ላይ ነግሰው ይባስ ወደዘቀጠ የውርደት ውርደት የምንገባበትን ስልት ያዘጋጁልናል፡፡ ተሳስቶ ለአገሩ ጠንካራ አስተሳሰብ ያለው መሪ ቢመጣ የአስተሳሰብ ነጻነት ነፋጊ ነህ ብለው ይጥሉታል፡፡ የሚገርመው ዘሬ የእኛውም አገር ምሁራንና ሌሎች የተሸሉ ናቸው የተባሉት የጠላቶቻቸው ሴራ እንደሆን እንኳን ሳያውቁ የአስተሳሰብን ነጻነት ከምንም በላይ አድርገው ብዙ ቁምነገር የሚሰሩበትን ጊዜ የአስተሳሰብ ነጻነት ለማስከበር ያባክናሉ፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል! ውድ ወገኖቼ በዚህ ጉዳይ ግልጽ አይደለሁ እንደሆነ ሊጠይቀኝ የሚፈልገውን ሊጠይቀኝ ይችላል፡፡ እኔ ግን በራሴ በጣም ትክክል ስለሆንኩበት ነገር አናገራለሁ! ስብዕናን አከብራለሁ! የአስተሳሰብ ነጻነት የሚል ቀልድ ግን በአገር እድል ሊኖረው አይገባም እላለሁ፡፡  ስለ አስተሳሰብ ነጻነት ሰዎች አብዝተን እንጨነቃለን በድህነት ባርነት ስለተያዝንበት ነጻነጸት ግን ምንም አንልም ወይም ብንልም ትንሽ ለወሬ ማሞቂያ ብለናል፡፡
በአስተሳሰብ ነጻነትና የሕዝብ አስተዳደር (ሕዝበ ውሳኔ) በሚል ሽፋን እጅግ የከፉ አዘቅት ውስጥ ገብተናል፡፡ ዛሬ በአገራችን ያለው አስተዳደር ወደዳችሁም ጠላችሁም በዚህ ወዥንብር የተፈጠረ ነው እንጂ የአገር ማንነት ክብር ያቃጠለው ዜጋ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ በሰው ልጆች የአስተሳሰብ ብቃት ደረጃዎች የወረደው ኢድ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ልቅ አስተሳሰብ ማለት ነው፡፡ የሰውን ልጅ ደግሞ ብቃት እንዲኖረው የሚያደርገው በልቅ አስተሳሰብ መመራት አይደለም፡፡ ጥብቅና ጥልቅ በሆኑ አስተሳሰቦች መመራትን እንጂ፡፡ ምንአልባት ኢትዮጵያ ውስጥ የማሰብ ነጻነት ተገድቧል ሊባል ይችላል፡፡ ግን የተኞቹ አስተሳሰቦች ናቸው የተገደቡት? በማንስ ተገደቡ? አስተውሉት! እንደ አስተሳሰብ ነጻነትና ጠንካራ አስተሳሰብ ከወረደው አስተሳሰብ እኩል ሊመዘን እኮ ነው! በሕዝብ ውሳኔ እየተባሉ የሚጸድቁ ጉዳዮችም ክፉንና ደጉን ጠንቅቆ በማያስተውል ሁሉ ተደምሮ በኮታ የአገር ጉዳይ ሊወሰን እኮ ነው! ይሄ እኮ ነው እየሆነ ያለው! የሚገርም አይነት የፍርድቤት ዳኝነት እንኳን ሳይቀር እኮ ነው ሕዝብ በሆያ ሆዬ (ሰላማዊ ሰሎፍ) ወሰነ ተብሎ ፍርድ የሚሰጠው፡፡ የሕዝቤ ውሳኔና የአስተሳሰብ ነጻነት ቅቦች እኮ ናቸው ጥሩ አስተሳሰብና ውጤታማ አስተዳደር አንዳይበቅሉ የተደረጉት፡፡ እናንተ በየአገራቶ ትላልቅ ከተሞች ያለችሁ ፖለቲከኛ ነን የምትሉ ሁሉ እኛ ችግራችን አስተሳሰቦችን አንገዋሎ ጥራት ያላቸውን አስተሳሰቦች በመጠቀም አገርን ከድህነት ውርደት የሚያወጣ አስተዳደር እንጂ የአስተሳሰብ ነጻነት በሚል ለዘቀጡ አስተሳሰቦች ባርነት የሚዳርገንን አይደለም፡፡ ከውርደታችን ስነወጣ ያኔ ሁላችንም ባይሆን ብዙዎቻችን ጥራት ያለው አስተሳሰብ ስለሚኖረን ያኔ የአስተሳሰብ ነጻነት ብለን ብናውጅም  ጥሩ አስተሳሰብ ስለሚያይል ሊያዋጣን ይችላል፡፡ አሁን ላይ ግን የአስተሳሰብ ነጻነትና የሕዝብ ውሳኔ የሚሉ ዲስኩሮች አይገቡኝም፡፡ እነዚህ ያተረፉልን አደገኛ የሆኑ ውድቀቶችን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አምባገነናዊነት ይመስላል ግን የሚከተለውን በደምብ ያጢኑት፡፡
ሁሉም አገራት ወሳኝ የሆኑ ታሪኮቻቸውን ያለፉት በአስተሳሰብ ነጻነትና የሕዝብ ውሳኔ ሳይሆን ወሳኝ በሆኑ ዜጎቻቸው ነው፡፡ ዛሬ አለምን በምጣኔ ሀብቱም ይሁን በፖለቲካው አለምን እየተገዳደረች ያለቸው አገር ቻይና በብዙዎች አረመኔ የሚያሰኛቸውን ውሳኔ በወሰኑት እንደነ ማኦ የመሰሉ መሪዎቿ ነው የእድገት መሠረቷ የተጣለው፡፡ የቻይና መሬዎች ግን ዛሬም ድረስ ያሉት ከአገራቸው ክብር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ልጁ ቢሆን አገርን የሚያጎድፍ ሥራ ሲሰራ ቢያየው የቻይና መሪ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡ ጃፓን ኮሪያ በአጠቃላይ የሩቅ ምስራቅ አገራት የዛሬው ብልፅግናቸው የሀገርን ክብር ከሁሉ በሚያስቀድሙ መሪዎች እንደሆነ እናስተውል፡፡ ኮሪያውያን የዛሬ 50 ዓመት ገደማ እንደኛው በሚባል ሁኔታ በገጠር ተዝረክርከው የሚኖሩ ድሆች ነበሩ ዛሬ ከዓለም 8ኛውን የምጣኔ ሀብት ቆንጮ ይዘውታል፡፡ አኗኗራቸውም እጅግ ዘመናዊ የሆነ፤ እድገታቸውም ገና ወጣት የሚመስል፡፡ ኮርያን ዛሬ ለማየት እድሉ የገጠማችሁ የዛሬ 50 ዓመት ብለው የሚተርኩት የድህነት ታሪክ በፍጹም የእነሱ ሊሆን ይችላል ብላችሁ ለመገመት ያስቸግራችኋል፡፡ በዚህ ፍጥነት እንዴት ሊሳካላቸው ቻለ ብለን ስናስብ የሌሎች አገራት እገዛ እንዳለ ሆኖ ዋነኛው ምክነያቶቹ ግን ራሳቸው ኮርያውያን ናቸው፡፡ የአስተሳሰብ ጥራት እንጂ ማንም እነደፈለገው የሚዘባርቅበት አስተሳሰብ በዚህች አገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ የደቡብ ኮርያውያን ታሪክ ሲሆን ሰሜን ኮርያውያንም ቢሆኑ በሳይንሱ መጥቀውበታል በምጣኔ ሀብታቸው ከደቡቦቹ ወደኋላ ቢቀሩም፡፡ የሰሜኖቹ እድገት በእኛ አይነት አገር እንደለመዱት ሴረኞቹ አገራት እንደሚያወሩት አይምሰላችሁ፡፡ ሰሜኖቹን ሥም የሚያጠፉት አገራት እድገታቸው ስላሰደነገጣቸው ወደፊት እንደ አደጋ ስለፈሩት ነው፡፡ ደቡቦቹ ከእነሱ ጋር ወዳጅ ስለሆኑ ጉዳት አይኖረውም ብለው በማሰብም ነው፡፡ እውነታው ግን ሰሜኖቹም የሚያስደንቅ የሳይንስ ምጥቀትን ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ሳይንሱና ቴክኖሎጂው ከአደገ ደግሞ ኢኮኖሚው በአጭር ጊዜ ሊያድግ ይችላል፡፡ አሁንም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአጣቃላይ ሲታይ ግን የሩቅ ምስራቃውያኑ የጥበብ ታሪክ እንደ አፍሪካውያኑ አይደለም፡፡ ሩቅ ምስራቃውያኑ በሆነ ወቅት ተሸውደው የምዕራባውያኑ የበላይነት ታየ እንጂ የሩቅ ምስራቃውያኑ የጥበብ ታሪክ እጅገ ጥንታዊ ነው፡፡ ዛሬ ቤጂንግ የምትባለው የቻይና ከተማ ከ5000ዓመት በላይ ያስመዘገቡ የጥበብ አሻራዎችን ምስክር አድርጋ ነው የምትመካው፡፡ የፎርቢድን በሎክን ጨምሮ ብዙ ሌሎች ስነ-ሕንዎች የሩቅ ምስራቃውያኑ የጥንት ጥበብ ምስክሮች ናቸው፡፡
ሌላው አሁን ድረስ የምናየው ምሳሌ የሩስያው ቁርጠኛ መሪ የፑቲንን አስተዳደር ነው፡፡ ሩስያ የምዕራባውያኑን የበላይነት ለመግታት ከድሮም ጀምሮ የተሻለ አቅም ያላት አገር ናት፡፡ ይህች አገር ከየትኛውም አገር በላይ ጥልቅ የሳይንስ ችሎታ ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም በአስተዳደር ብክነት ምክነያት አገሪቱ የሚቻላትን ያህለ አልተራመደችም፡፡ ቀድሞ  በኮሚኒስት አስተሳሰብ ብዙ ዘመን አባክና ይህ አስተሳሰብ አባርቶ ነጻ የሚባለው አስተሳሰብና አስተዳደር በዚያች አገር ሲሰፍን የአገሪቱ መሠረት ሁሉ ተናጋ፣ ሥርዓት ጠፋ፣ ሌብነት (ሙስና) በአስከፊ ሁኔታ አየለ በአጠቃላይ አገሪቱ የውርደቱን መንገድ ተከተለች፡፡ ደግነቱ የዜግነትና የአገር ክብር የሚያቃጥላቸው ዜጎቿ ከመጥፋታቸው በፊት የአሁኑ መሪዋ ፑቲንና ሌሎች የቁርጥ ቀን ልጆቿ አገሪቱን ተረከቧት፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያችን አገር ከወደቀችበት አነሷት! እነዚህ ልጆቿ የሚያስጨንቃቸው ዜጎችን ከሌሎች ባዕዳን የምጣኔ ሀብትና የወረዱ አስተሳሰቦች ባርነት ነጻ ማድረግ፣ የአገርንና የዜጎችን ክብር መመለስ እንጂ የአስተሳሰብ ነጻነቶች አይደሉም፡፡ ከፑቲን አስተዳደር በኋላ ምዕራባውያን የሚዘፍኑት የአስተሳሰብ ነጻነት በዚያች አገር የለም፡፡ የዜጎችና የአገር ክብርና የበላይነት ግን በሚያስደነቅ ሁኔታ ተገንብቷል፡፡ በአንድ ወቅት ፑቲን ፓወር ኤንድ ፖሊቲክስ በሚል ርዕስ ወደ ሩሲያ ሄደው የነበሩ የሲኤንኤን ጋዜጠኞች በፑቲን አስተዳደር ምክነያት የዚያች አገር ዜጎች ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑና በልበሙሉነት ስለአገራቸው የምጣኔ ሀብትና የክብር እድገት ሲነግሯቸው ጋዜጠኞቹ ያልጠበቁት በመሆኑ እጅግ ተደንቀዋል፡፡ ትዝ የሚለኝ አንድ ቤኪ አንደርሰን የተባለች ጋዜጠኛ ለአንድ የተቃዋሚ ፓርት ተወካይ "የሩሲያ ሕዝብ ቢያንስ 60 በመቶው የፑቲን ደጋፊ ነው እናንተ ምን ትላላችሁ?" ብላ ላቀረበችለት ትያቄ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ የሰጠው ምላሽ የሚገርም ነበር፡፡ የመለሰላት መልስ "እውነታው ከዚህም በላይ ነው በእኛ ግምት ከ72 በመቶ ያላነሰ ሩሲያዊ የፑቲን አስተዳደር ደጋፊ እንደሆነ እናውቃለን" ነበር ያላት፡፡ ታዲያ የዜጎችንና የአገርን ክብር የሚያስጠብቅ፣ ዜጎች የሚደሰቱበት አስተዳደር ካለ የአስተሳሰብ ነጻነት ቦታው የት ነው?! የፑቲን አስተዳደር የባዕዳን አስተሳሰብ የአገሩን ሕዝብ እንዲበክል አይፈቅድም፡፡ ዜጎችንም ከተለያዩ የባዕድ አስተሳሰቦችና ርካሽ መጤ ባህሎች እንዳይተባበሩ ይከለክላል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ግብረሶዶማዊነትን ለመግታት ያወጣው ሕግ፣ እነደ ሀሎይን የመሳሰሉ የሩሲያ ሕዝብ ያልሆኑ ባዕድ ባህሎችን በውገዝ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ሀላፊነት የማየሰማቸው፣ መንነት የማይገባቸው ተራ አስተሳሰቦች የሚመሯቸው እንደ እኛ ያሉ ደሀ አገራት (በተለይ አፍሪካ) ግን በአስተሳሰብ ነጻነት ሽፋን የምዕራባውያኑ ርካሽ አስተሳሰቦችና ነውሮች መሞከሪያና መጣያ ይሆናሉ፡፡ የምዕራባውያኑ ቁልፍ አላማ በእነሱ ነውሮች አውረው እኛን ከአረከሱ ማንነታችንን ከሳጡን በኋላ እነሱ እንደልባቸው የሚዘውሩት ማህበረሰብ ማፍራት ነው፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋበሻል!
ብዙ ምሁር ተብዬ ፖለቲከኞቻችን ስላረረብን ዳቦና ስለዜግነት ውርደታችን አይነግሩንም፡፡ ግን ስለመናገር ነጻነት አብዝተው ይደሰኩሩብናል፡፡ ስለ ምጣኔ ሀብት ነጻነትም፡፡ በእነዚህ ፖለቲከኞች አስተሳሰብ እንደልብ ማውራት መቻል ነጻነት ነው! ማንም ነጋዴ እንደፈለገው የሚዘውረው፣ አንዳችም የመንግስት ቁጥጥር የሌለበት ምጣኔ ሀብት ጤነኛ ነው! የዜጎች ክብር ግን ቦታ የለውም! ከመጽሐፍ ያነበቡትን፣ ምዕራባውያኑ የነገሯቸውን አስተሳሰብ በዚህች አገር ከማስፈን ሌላ ሕልም የላቸውም! ኢትዮጵያዊ የሆነ አስተሳሰብ አይታያቸውም! ቢታያቸውም አገራዊ አስተሳሰቡ ሁሉ በእነሱ ዘንድ ኋላ ቀር ነው፡፡ ዛሬ የብዙ ዲያስፖራውያን አስተሳሰብ በአስደንጋጭ ሁኔታ የተምታታበት እንደሆነ እናያለን፡፡ ምን አልባትም የስደት ኑሮ የፈጠረው ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል ግን የብዙዎቹ ጤነኛ ከሚባለው አስተሳሰብ አፈንግጧል፡፡ እነዚህ ናቸው ደግሞ አገር ውስጥ ያለውን የአስተዳደር ችግር እንፈታለን በማለት የሚዳክሩት፡፡ አስተሳሰባቸው አስደንጋጭና ተስፋ የቆረጡ አይነት ሰዎች ስለሚመስል አትምጡብን እዛው የሚያሰኝ ነው፡፡ የእኛ አገር በአሜሪካዊ ወይም በሌላ ምዕራባዊ አስተሳሰብና ፍልስፍና ልትመራ አትችልም፡፡ የሁሉም አገራት የስኬት ታሪክ የሚያሳየው ከውስጥ በሆነ ፍልስፍና እንጂ በመጤ ፍልስፍናዎች አይደለም፡፡ ድህነት ቀደመንነ ጥሩ የሆኑ አስተሳሰቦቻችንና ፍልስፍናዎቻችን ሁሉ ከኋላቀርነት ተቆጠሩ እንጂ ለምዕራባውያኑም የሚተርፉ አስተሳሰቦች እንዳሉን ባለፈው ጽሑፌ ጠቁሜ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ትልቁ ችግራችን ቁጭት፣ የዜጎችና የአገር ክብር የሚያቃጥለው ከምዕራባውያን የአስተሳሰብ ባርነት ነጻ የወጣ መሪና አስታዳደር ማጣታችን ነው፡፡ ምን አልባት በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር የአገርና የሕዝብ ጉዳይ አስጨንቆት ወደሥልጣን የሚመጣ የለም፡፡ የብዙዎቹ (95 በመቶ በላይ የሚሆኑት) የገዥውም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቻችን እውነተኛ ሕልማቸው ከራሳቸው የተደላደለ ኑሮ በላይ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የዜጎችና የአገር ክብር ጉዳይ አይገባቸውም፡፡  ቁጭት የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡ የአገሪቱ እድገት የሚለካው በእነሱ የኑሮ መደላደል ደረጃ እንጂ በዜጎች የኑሮ ለውጥ አይደለም፡፡ ለአንድ ራሳቸው እድሜ ልክ ቢረጩት የማያልቅ ነብረት በልቶ ለማደር ከተሳነው ሕዝብ ነጥቀው ሰብስበው ይኖራሉ፡፡ መቼ ሊበሉት እንደሆን አናውቅም ግን አሁንም እየሰበሰቡት ነው፡፡ ግን ይሞታሉ ሊያውም ከደሀው በአነሰ እድሜ! የመጽሐፉ ቃል እውነት ነው፡፡ አንዴ ለማይረባ አእምሮ ተላልፈው ተሰጥተዋልና ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ ለመምጣት አይችሉም!
ቆራጥና የዜጎች፣ የአገር ክብር ያገበራቸው መሪዎች ቁጭታቸው ኃያል ነው! ድህነትንም ለመበቀል ብርቱ ክንድ አላቸው! ዜጎቻቸውም ችግርን እንዲላመዱ እድል አይሰጡም! ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ  ያለው አሳቃቂ ግፍ ለዘመናት የደነዘዝንበት ችግርን አምቢ ለማለት አቅም ያጣንበት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ብዙዎች በአንድ ወቅት ተቸግረው ችግራቸውን በእልህ አሽቀንጥረው ጥለውት ዛሬ በችግር በራሱ ላይ እየተሳለቁበት ይገኛሉ፡፡ የዛሬ 50 ዓመት አካባቢ በቻይና ረሀብ ሆኖ ከ30 ሚሊየን በላይ ዜጎቿን እንዳጣች ይነገርላታል፡፡ የመንግስቷ እርምጃ ግን ወዲያው በሚቀጥለው ዐመት ሁለተኛ ረሀብን ላለማስተናገድ ቁርጠኛ ነበር፡፡ ተሳካ ይሄው ዛሬ ያለችበት ደርሳለች! በሕንድም እንዲሁ ነበር እንደኛውም በመዝገበ ቃላት ሳይቀር የችጋር ምሳሌ የተደረገችበት ወቅት ነበር፡፡ ወዲያው በአረንጓዴው ዘመቻ (Green revolution) ረሀብን በአምስት ዓመት ውስጥ አስወግዳ ለውጭ ተረፈ ምርት ማቅረብ በመቻሏ ከመዝገበ ቃላቱ ተሰርዛ ለቋሚ ምሳሌነት የተመረጠችው ኢትዮጵያ ብቻ ቀረች፡፡ ችጋር በአውሮፓም ነበር፡፡ ኧረ እንደውም እኛም እዳቂሚቲ የረዳንበት ታሪክ አለ! እንደኛ ግን አመታዊ የችጋር መጠን ሪፖርት በቋሚነት የሚቀርብበት አገር የለም፡፡
ይህ የሚቆጨው ትውልድ እንዳይበቅልባት የእኛዋ አገር ሳትረገም አይቀርም፡፡ በቀደምት ጠቢባኖቿ ያሾፈ ትውልድ ነበርና! ብዙዎቻችን በቃ የማሰብ ችሎታችን የራሳችን ሆድ እስኪሞላ ብቻ ሆነ ከዚያ ያለፈውን ለማሰብ አእምሮአችን ነጠፈብን፡፡ የሕዝብ ሰቆቃ እንዴት ይግባን! ሕዝብ መሪ እንዳሌለው የንብ መንጋ ይርመሰመሳል፡፡ ሁሉም የየራሱን ይሞክራል እንጂ መንግስት እንደሚመራው ሕዝብ አንድም ስርዓት የያዘ ነገር የለም! በየመስሪያቤቱ ብትሄዱ አስቂኝ ድራማዎችን ትመለከታላችሁ፡፡ ቴክኖሎጂ ነክ ልማቶቻችን ግንባታዎችን ጨምሮ የሌሎች አገር ዜጎች ናቸው የሚሰሩልን፡፡ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የመከላከያን ተቋም በቴክኖሎጂ ነክ ልማቶች ማሳተፍ መቻሉን እኔ እንደ ትልቅ ነገር አየዋለሁ! በዚያው ልክ ግን ሌሎች ቦታች ድሮ ከሚሰራውም የወረዱ ጥገኝነትን የሚያስፋፈ አሰራርን አያለሁ፡፡ ድሩ ደረጃውን የጠበቀ ሕንጻና መንገድ ይገነቡ የነበሩ ተቋሞች ዛሬ ጠንከር ያለ ሥራ ሲያገኙ በቻይናውያን ሰብ ኮነትራክት ነው የሚያሰሩት፡፡ እያደግን ነው? ውል በጠፋበት የምጣኔ ሀብት ደህንነት (economic security) እንዴት ነው እድገት የሚታሰበው? ባለስልጣኖቻችን እነሱ ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ ሚሊየነር ስለሆኑ በቃ አደገች ማለት ነው እቺ አገር? ወይስ የእድገት መስፈርቱ ምን ሆኖ ነው እያደገች ነው የሚባለው? በአለም የደረጃ ሰንጠረዥ ስንታይ ከፍ ስንል አይታይም! የ30ና 40ዓመት ታሪክ በፊት የነገረንን ሁኔታ በማወዳደሪያነት እያነሳን በዚህን ያህል ጨምሯል የምንለው የጊዜን ዋጋ እንዴት ነው የምናየው? ካደግን ለምን ኑሯችን ከሌሎች አገራት በንጽጽር አይሻሻልም፡፡ ከ50 ዓመት በፊት ያልነበረን የኢንተርኔት አገልግሎት ከ50 ዓመት ከነበረው ታሪክ ጋር ዛሬ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሆነናል ብሎ ማውራት ምን ይሉታል፡፡ ይልቁንስ ከሌሎች አገራት አንጻር የእኛ የዛሬው የኢንተርኔት አገልግሎት የት ነው ያለው? በባለራዕዩ መሪ በሚኒሊክ ዘመን የገባው የስልክ አጠቃቀማችንስ? ሚኒሊክ ስልክን ያስገቡት እኮ እነ ገርሀም ቤል ስልክን ከፈጠሩ ብዙም ቆየ በማይባል ታሪክ ውስጥ ነው! በዘመኑም አፍሪካ ይቅርና ብዙዎቹ አውሮፓዎችም ሳያውቁት! ኮሪያ በ50 ዓመት ፍጹም ሀበታም ከሚባሉት ጎራ ተሰለፈች ሲባል እኮ ስንቱ በምጣኔ ሀብት ይበልጧት የነበሩትን ወደ ኋላ ትታ ነው፡፡ ሁሉም ልማቶች በዜጎቿ ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡  
አኛን ዛሬ ችግር ከቤታችን እያበረረ በወራዶች እጅ ጣለን! ድህነትን ማሸነፍ ፉከራ እንችልበታለን! ደፋርና ቆራጥ ልብ ግን የለንም! እንደ እድል ሆኖ በአገራችን ታሪክ ድህነት ለማሸነፍ ተምሳሌት የነበሩ የቀደምት መሪዎቻችንን እንረግማለን፡፡ ግን የረገምንበት አንደበታችን ተመልሶ እኛንው ይረግመናል፡፡ ሚኒሊክ 1884 በተከሰተ ረሀብ ምክነያት እንደ ሌሎች ከላይ ድህነትን በመበቀል እንደጠቀስኳቸው መሪዎች ሕዝብን ለማስተባበር ራሳቸው ንጉሱ ዶማ ይዘው  በቀዳሚነት ወጡ ሲባል እንሰማለን፡፡   ሌላውን ሁሉ የአገርን ድህነት ለማስወገድ በዘመናቸው አንድ መሪ በእድሜው ሊሰራው ከሚችለው በላይ ሰርተ አለፉ፡፡ ምንአልባትም በጣም ከጣት ቁጥር የማይበልጡ እንደ ሚኒሊክ ያሉ መሪዎች በአለም ላይ ተነስተው ይሆናል፡፡ ሚኒሊክ ከእነዚህ ጥቂት በዓለም ላይ ከተነሱ መሪዎች ደግሞ ቀዳሚ የሚያደርጋቸው ሥራን ለዚህች አገር አበርክተዋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር አንድ ያደረጉ፣ ዛሬም ድረስ የምንጠቀምባቸውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሁሉ ወደ አገር ያስገቡ፣ ትውልድ በዘመናዊ ጥበብ እንዲታነጽ መሰረት የጣሉ፣ የቅኝ ገዥዎችን የአይገቴ ቅዠትን ያጨለሙ  በመሆናቸው በሕይወት ዘመኑ ይህን ሁሉ ያደረገ በዓለም ላይ የነበረ መሪ   ለእኛ የእኝህ ሰው ራዕይና ቁጭት ሊገባን አልቻለም፡፡ ይልቁንም ታሪካቸውን ጥላሸት ቀባነው፡፡ ለማይረባ አእምሮ ተላልፈን ተሰጥተናልና መልካም ነገር አይታየንም፡፡ ታሪካችን ሁሉ የማውደም ነበርና ሁሌም የቀደሙት የመሠረቱት ላይ መጨመር ሳይሆን አውድመን ስለምንነሳ ያው ባለህበት እርገጥ ወይም የምናውድመውን ያህል መገንባት ስለሚያቅተን የኋሊት እንጓዛለን፡፡ 
ምዕራባዊያኑ የሚኒሊክን ታሪክ ሊበቀሉት የሚፈልጉት ናቸው፡፡ እንደ ሚኒሊክ ያለ ባለራዕያ በአፍርካ ይቅርና በየትኛውም ዓለም እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ችግሩ በሁለት እግሩ የቆመ አስተዳዳር ያላት አገር ለእነሱ የሚያጎበደድላቸው አይደለም፡፡ ከሚኒሊክ በኋላ የእኛ አገር ታሪክ በአንድም ሆነ በሌላ በምዕራባውያኑ የሚደለሉ መሪዎች ሰለባ ሆነ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘመናዊነት ማደግ የነበረበት የአገር አስተዳደርም ከሀገርና ከዜጎች ክብር በላይ ራሳቸውን በአገዘፍ መሪዎች ቀጨጨ፡፡ ሚኒሊክ የጣሊያነን ወራሪ እንዲያ ከል አልብሰው እንዳልመለሱት በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በቂም ለበቀል መጥቶ ዳግም በዜጎቿ እንዲያፍር ሲሆን ንጉሱ የሀገርን ክብር ያስጠበቁ ጀግኖች እንደ ጀግና ለማየት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይልቁንም ትንሽ ዝናን ያተረፉትን ነገ ከእኔ በላይ የእሱ ሥም ሊነሳ ነው በሚል ወይ አጥፍተውታል ወይ አዋርደውት ሥሙ አንዳይነሳ አድርገውታል፡፡ ለምሳሌ ጠላት የነበረችውን ጣሊያንን በራሷ በጠላት አገር በተዓምረኛ ጀግንነቱ ሲያተራምሳት የነበረውንና የአገርን ሥም ከፍ እንዲል ያደረገውን ጀግና  የነጆውን አብድስ አጋን ኢንግሊዞቹ በጀግንነቱ  የጀነራልነት ማዕረግ ቢሰጡትም ንጉሱ ጀነራልነቱን ለመቀበል ደስተኛ ባለመሆናቸው አውርደው መቶ እልቅናን ብቻ ሰጥተውታል፡፡ ሌሎችም ብዙ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ጀግንነት የፈጸሙ የአገር ልጆችም ተመሳሳይ ዕድል እንደገጠማቸው ይነገራል፡፡ በተቃራኒው የመንደር አውደልዳዮችና ከነጭርሱም ከጠላት ጎን ሆነው በባንዳነት ሲያገለግሉ የነበሩ ኋላ ግን ለንጉሱ ጎንበስ ቀና ያሉ ብዙዎች የሹመት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡  እስከዛሬ ድረስም በአርበኝነት ስም ፀጉራቸውን አጎፍረው በየአመቱ በአርበኞች በዓል የሚገኙ ባንዳዎቹ ላለመሆናቸው ማረጋገጫ የለም፡፡ ጀግኖቹማ (አርበኞቹማ) ወይ በጦርነቱ ሞተዋል ወይ ደግሞ በጦርነቱ በደረሰባቸው ጉዳት እስከዛሬ መኖር አልቻሉም፡፡ ያ ሁሉ የዜጎች ደም የተከፈለበት የጣሊያን ወረራም ከጦርነቱ በኋላ ንጉሱና ባለስልጣኖቻቸው ከጣሊያን መንግስት የገንዘብ ድጎማ የሚቀበሉበት ሊላ አጋጣሚ እንደተፈጠረ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ የወገንን ሥጋ የመበላት ያህል እርም ነው፡፡ አንድ ይሄንኑ የሚያረጋግጥ Ethiopian in the hands of Mosoloni የሚል ሚስጥራዊ መጽሀፍ እንዳለ በአንድ ወቅት ከአንድ ሰው ሰምቼ ነበር፡፡ በጽሐፉን ግን አግኝቼ ለማንበብ ዕድሉን አላገኘሁም፡፡ ምዕራባውያኑ ሁሉ በዚያ ክፉ ቀን ለኢጣልያ መቆማቸውን ልብ እንበል! ኢትዮጵያን ለመበቀል አውሮፓ በሙሉ ነበር አንድ የሆነው ኋላ የአምላክ ሥራ ሆነና በራሳቸው የውስጥ የጥቅም ግጭት ለሁለት ሲከፈሉና ሲታሉ አገራችንም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ በማለት ከኢታሊያ ጋር ከተጣሉት አንደ ኢንግሊዝ ያሉ አገራት ጎን በመሆን የነጻነት ትግሏን ቀጠለች፡፡ ኢንግሊዞቹም የኢትዮጵያን ጀግኖች በኢጣሊያን የተነጠቁትን የቅኝ ግዛቶቻቸውን ለማስመለስ ተጠቀሙባቸው፡፡ ኢንግሊዝ ግን ለኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የማትበጅ አገር እንደሆነች የሚያረጋግጥልንን መርዟን በሞግዚትነት ለ10 ዓመታት በአስተዳደረቻት ኤርትራ ቀብራ ሄደች፡፡ በተሸለ የኢጣሊያ ወራሪ መንግስት የልማት ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ኢነግሊዞቹ ከኤርትራ ሲለቁ ጣሊያን ትቶት የሄደ የምግብ ቆርቆሮ አልቀራቸውም ለቃቅመው ሲወጡ፡፡  በንጉሱ ዘመን የነበረ ወዳጅነታችን ግን ከሁሉም የአውሮፓ አገር በተሻለ ከመርዘኛዋ ኢንግሊዝ ጋር ነበር፡፡ አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል!
ደርግ ከሩሲያ በመጣ የሶሻሊዝም ልክፍት ግራ እጅ እያነሱ ይውደም እያለ ሁሉንም እያወደመ ቆይቶ ተራውን ለሌላ በይውደም ፍልስፍና የተለከፈ ትውልድ አስረክቦ ሄደ፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ ልዩ መገለጫው በሀሳብ ተፎካካሪውን ማጥፋት (eliminate your competitor) የሚል ነው! ብዙም ጊዜ ይህ ትውልድ በሀሳብ የመፎካከር አቅም ስለሚያንሰው ማጥፋት ዋነኛ እራስን የማቆያ ኃይል ነው፡፡ ልብ በሉ በአስተሳሰባቸው የበሰሉት ለሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ ስለሚሰጡ ሕወትን ላለማጥፋት በሚያደርጉት ጥንቃቄ ለሕይወት ርህራሄ በሌላቸው እየተቀደሙ ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በሌሎች አገራትም ተቃዋሚ የሚሆንን ማጥፋት ይተገበራል፡፡ ልዩነቱ የበላይነቱን የያዙት ከአገርና ዜጎች ክብር ጋር በተያያዘ የትኞቹ ናቸው የሚል ነው፡፡ ከላይ በጠቀስኳቸው የጥሩ ምሳሌ አገራት የበላይነቱን የያዙት ለአገርና ዜጎቻቸው ክብር ቁርጠኝነት ያላቸው የቁርጥ ቀን ልጆቻቸው ስለሆነ ጥፋቱም ቢኖር የሚጠፉት ለአገርና ዜጎች አደጋ የሆኑት ናቸው፡፡ የእኛው አገር ግን የተገላበጠ ነገር ነው፡፡ የበላይነቱን የያዙት አብዛኞቹ የአገርና ዜጎች ክብር የማይሰማቸው ናቸው፡፡ ዛሬ ራሱን የ60ዎቹ ትውልድ እያለ የሚጠራው በብዛት የዚህ አይነት ነው፡፡ ይህ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉትን ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎቹንም የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዛሬ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ክብር እታመናለሁ የሚለው ስብስብ (ፓርት) ሁሉ ነገ ስልጣን ላይ ሲወጣ ሌላ የከፋ አደጋ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም፡፡ ሲጀምር መሠረታዊ አስተሳሰብ ላይ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች የሚመሯቸው ፓርቲዎች ይበዛሉ፡፡ አጀንዳዎቻቸውም ከመቃወም ወጭ ግልጽ አይደሉም፡፡ በ1997 አብዛኛው ሕዝብ ለተቃዋሚዎች ድጋፉን የሰጠው ገዥውን ፓርቲ ከመሰልቸት እንጂ የተቃዋሚው ፓርቲ ራዕይና አጀንዳ አማልሎት አልነበረም፡፡ ብዙዎችም ለመቃወም ብርቱዎች ናቸው እንጂ አገር ለመምራት ብቃቱና ዝግጅቱ የላቸው አይመስልም፡፡ ሕዝብም የጠገበውን ጅብ አስወጥቶ የራበውን ጅብ ማስገባት ካልሆነ ፋይዳ የለውም በሚል አሁን አሁን ብዙም ለፖለቲካ ጉዳይ ጆሮ የሚሰጥ አይደለም፡፡  ብዙዎቹ ተቃዋሚ ነን የሚሉት ደግሞ ሕዝብን ማግደው እነሱ በደህንነት በሚኖሩባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች ነዋሪ ናቸው፡፡ ምዕራባውያኑ የሚፈልጉት በትክክልም እንደዚህ ማለቂያ የሌለውን የአስተዳደር ውዥንብር ነው፡፡ እውን ለእኛ ቢያስቡ ግን በአንድ ሌሊት ለአገርና ዜጎች ክብር የሚኖር አስተዳደር ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ የሌሎች አገራት ዕድገትና ብልፅግና ለእነሱ አደጋ ስለሚሆን መቼውንም የአገርና የዜጎች ክብር የሚሰማው መሪ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ከአለም አቅሙ ከአላቸው ይጥሉታል፡፡ ይሄው በገሀድ የተረጋጋ አስተዳደርና የተሻለ ብልፅግና ሂደት ላይ የነበሩትን የአረብ አገራት ምን እያደረጓቸው እንደሆን በገሀድ እያየን ነው! ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያና ሌሎችም፡፡ እጅግ ኋላቀር አስተዳደርና ስብዕና የማይገባቸው እነደ ሳውዲ አረቢያ የመሰሉት አገራት ግን ሠላም ናቸው፡፡
የምዕራባውያኑ የቀን ከሌሊት እንቅልፍ አጥተው የሚወጥኑት ሁልጊዜ ሥለሰብዓዊ መብት ሳይሆን በሰብዓዊ መብት ሽፋን የአንድን በእድገት ላይ ያለች ለእነሱ ሥጋት የመሰለቻቸውን አገር ዕድገት መጨናገፍ ነው፡፡ ጉልበት ያላቸው እንደ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኮሪያ (ሰሜን) የመሳሰሉት ስለሚቋቋሟቸው የምዕራባውያኑን ልፍለፋ እንደምናምን ቆጥረው የራሳቸውን ብልጽግና ቀጥለዋል፡፡ ደከም ያሉትን ግን ከልፍለፋ ዘለው አገራቱን ያወድማሉ፡፡ ልብ በሉ በምዕራባውያኑ ድጋፍ የሌላቸው መሪዎች በአገራቸው ግን ከፍተኛ የሕዝብ ክብርና ፍቅር ያላቸው መሆኑን፡፡ የሩሲያውን ፑቲን ከላይ ጠቅሼዋለሁ፡፡ የሰሜን ኮሪያው መሪ ሲሞቱ በአገሪቱ ሕዝብ የነበረውን ሐዘን ልብ እንበል፡፡ የሊቢያው መሪ የነበሩት ጋዳፊ ሳይቀሩ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው እንደነበር ለገመት አይከብድም፡፡ ያ ሁሉ የአውሮፕላን ድብደባ ባይኖር ተቃዋሚ ተብዬዎቹ የትም መድረስ ባልቻሉ፡፡ ለጠቃዋሚዎቹ የበለጠ የጦር መሣሪያ ቢያስታጥቋቸው እንኳን  የጋዳፊን የሕዝብ ከለላ ሊቋቋሙት ባልቻሉ፡፡ ልብ በሉ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሀን (በምዕራባውያኑ የተገዛውን አልጀዚራን ጨምሮ) የአለምን ሕዝብ ምልከታ ለማዛባት የላቸውን ሴራ፡፡
ወደእኛው አገር ስንመጣ የዚያን ያህል ስጋት ባለመሆናችን በአካል አልመጡብንም ግን ውስጥ ለውስጥ በደንብ እያሰሩን ነው፡፡ አንድ በጣም የገረመኝ ነገር ሁለነገራችንን ራሱ እነሱ በሚሉት እየነዱን እንደሆነ የታዘብኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን በሚኒስቴርነት ደረጃ ያሉት ሚኒስቴሮች በተሾሙበት አስቀድሞ በአንድ ኤምባሲ ውስጥ ይሠራ የነበረ የውጭ ዜጋ ማን ማን በሚኒስቴርነት እንደሚሾም ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ ይህ ሰው ስለሚኒስትሮች የግል አኗኗር ሳይቀር የሚያውቅ ነው፡፡ በሌላ ጊዜ በኢትዮጵ የአውሮፓ ዩኒየን ከፍተኛ ስልጣን ያለው ሰውዬ በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን ሲያወራኝ ብዙ የገረሙኝን ነገሮች ተናግሮኝ ስለሙስና ስጠይቀው አይ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው የሚባል የለም አለኝ፡፡ እውነታው ግን እሱ እንዲሆን ስለፈለገው እንጂ ሙስናው የከፋ እንደሆነ አጥቶት አይደለም፡፡ ብቻ ብዙ ጉዶች አሉብን፡፡
የታላቋ ቀን ልጅ የአገርንና የዜጎችን ክብር ከምንም በላይ ያደርጋቸዋል፡፡ የፈለግከውን የመናገር፣ የፈለግከውን የማሰብ፣ የፈለግከውን የማመን የሚል ፍልስፍና አይገባውም፡፡ ግለሰቦች እንደግለሰብነታቸው የፈለጉትን ማሰብ፣ ማመን ይችላሉ ግን የእነሱ አስተሳሰብ አደገኛ እስከሆነ ድረስ ለሌሎች እንዲያሰራጩ እድል መስጠትን አይቀበልም፡፡ ምክነያቱም ብዙ የማየረቡ አእምሮዎች የሚያፈልቋቸው ለአገርና ለዜጎች አደገኛ የሆኑ አስተሳሰቦችና እምነቶች አሉ፡፡ ለሁሉም ገደብና መስፈርት/ደረጃ ያስፈልገዋል ብሎ ያምናል የታላቋ ቀን ልጅ፡፡  ስለ አገራቸውና ዜጎቻቸው የሚቆጫቸው መሪዎች ኢትዮጵያ ያስፈልጓታል ብሎ ያምናል፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ አስተሳሰብ ግን (በየትኛውም ፓርቲ ያለ ቢሆን) ለአገር አደጋ እንደሆነ ያምናል፡፡ አብዮተኝነት ሳይሆን ለዜጎች አሳቢነትንና በተሰላ አካሄድ የሚመራ የአገር ብልፅግናን ይናፍቃል፡፡ ለታላቋ ቀን ልጅ ማርቲን ሉተር ኪንግ ቼጉቬራና ማንዴላ ጥሩ ምሳሌዎቹ አይደሉም! ኢትዮጵያ የእንደነሱን አይነት መሪ አያስፈልጋትምና፡፡ ምስሌዎቹ የአገሩን ሚኒሊክን በማስቀደም እንደነፑቲን የመሳሰሉ መሪዎች ናቸው፡፡ የታላቋ ቀን ልጅ እንደልብ ማውራትንም አይፈቅድም ብዙ ለአገር ሚስጢር መሆን ያለባቸው ጉዳዮች አሉና፡፡ ስለ መናገር መብት አይገደውም ይልቁንም ያልታረሙ ንግግሮች አደጋ አንደሆኑ ያምናል፡፡ ሥለ ሆንም በመናገር መብት ሽፋን ማንም እየተነሳ የፈለገውን መጻፍ፣ የፈለገውን መናገር የሚባል ነገር አይመቸውም፡፡ አሁንም ሁሉም ሥርዓትና ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ ሆኖም ሥለ ሕዝብና አገር በማስተዋል የሚሆን ንግግርንም ይሁን ጽሑፍ አይቃወምም፡፡ ነገሮች ሁሉ ግን በተቃዋሚነት ሳይሆን በምክርና በማነጽ ላይ ቢሆኑ ይመርጣል፡፡ ሆን ተብሎ ለሚባክኑ የደህንነት ሚስጢራት ግን ይቅር ላይል ይችላል፡፡ በታላቋ ቀን ልጅ መስፈርት የሚከተሉት ደህንነቶች አሉ፡- 1፡ የብሔራዊ ደህንነት (የዳር ድንበርና አጠቃላይ የውስጥ መረጋጋት)፣ 2፡ የዜጎች ደህንነት (ዜጎች በየትኛውም ጊዜና ቦታ በሠላም ወጥተው  ሠርተው፣ በሠላም የሚኖሩበት)፡፡ ዜጎች ሁሉ ጤናቸውን ጨምሮ የኑሮ ደህንነት ዋስትና ሊኖራቸው ይገባል ይላል፡፡ ሥልጣን፣ ወይ ሌላ ጎልበት በዜጎች ላይ አቅም ሊኖረው አይገባም፡፡ 3፡ የምጣኔ ሀብት ደህንነት (የአገር ምጣኔ ሀብት የማየመዘበርበት፣ ዜጎችም በኢኮኖሚ የማይበዘበዙበትን የግብይት ሁኔታን ጭምሮ)፡፡ ይህ የአገርን የወደፊት የምጣኔ ሀብት ዕደገት መገመት የሚቻልበት፣ ትርፋማነትን መስላት የሚቻልበት (በአገር ወይም በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ) ይጨምራል፡፡ 4፡ የፖለቲካ ደህንነት (የነጠሩ ሀሳቦች የሚወጡበት) 5፡ የመሪዎች ደህንነት (ይህ እስከ ተወሰነ ጊዜ የሚያስፈልግ ነው)፡፡ የአገርና የዜጎች ክብርን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ባለስልጣናት  ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ሥልጣናቸውም በራስ ወዳዶች እንዳይነተቅ (ከፖለቲካ ደህንነቱ ጋርም ይያያዛል)፡፡   
ልዑል አባት ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የምናስተውልበትን አእምሮ ስጠን! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 12ኛው ቀን 2006 ዓ.ም (Son of the great day 21st  of November 2013)

   
       

No comments:

Post a Comment