የህወሓት የልዩነት አፈታት ታሪክ ምን ይመስላል?
-----------------------------------
Abraha Desta ·
"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህውሃት ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የዕርቅ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይሰማል፡፡ በፓርቲው
ውስጥ ከረዥም ጊዜ በፊት የነበረው የልዩነት አፈታት ምን ይመስል ነበር?... አሁን የተጀመረው የዕርቅ ሂደት
አፈታተሽ ምን ይመስላል? አቦይ ስብሃት ነጋ በቅርቡ ከዘ-ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ‹‹በህወሃት ውስጥ
ጥፋት ያጠፉ ከመባረራቸው በስተቀር ልዩነት ተፈጥሮ አያውቅም፤ አንጃ የሚባል እንቅስቃሴ ኖሮ-አያውቅም›› ብለዋል፡፡
ይህን ጉዳይ እንዴት ትመለከተዋለህ? በእነ ስዬ አብርሃ ላይ ትግራይ ውስጥ ተጀምሯል የተባለው የስም ማጥፋት
(የጦርነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው የሚባለው) መንስኤው ምንድነው?....በአጠቃላይ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረው
የልዩነት አፈታትም ሆነ የዕርቅ መንገድ አሉታዊና አዎንታዊ መልኩ ምን ይመስላል? ምን ትላለህ?"
መልስ:
በህወሓቶች ልዩነት መፈጠር የጀመረው ገና ከጅምሩ ነበር። የሐሳብ ልዩነት መኖር በራሱ ችግር አይደለም። የሐሳብ
ልዩነት ችግር የሚሆነው የልዩነቱ አፈታት ጤናማ ካልሆነ ብቻ ነው። ህወሓቶች ልዩነታቸው የሚፈቱት ተንኮል በተሞላበት
የሃይል እርምጃ ነበር።
ከድሮ ጀምሮ የህወሓት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በተወሰኑ የደም ትስስር ባላቸው
ግለሰቦች ነው። ሌላኛው አብዛኛው ታጋይ በጦር ግንባር እየተፋለመ የሚውል ነበር። በህወሓት ዉስጥ ችግር ሲፈጠር
የፖለቲካ መሪነቱ የተቆጣጠሩ ግለሰቦች በሁለት መንገዶች ችግሩን ለመፍታት ይሞክራሉ። (አንድ) የሐሳብ ልዩነት
የፈጠሩ (ከመሪዎቹ ያልተግባቡ) ግለሰቦች ወይ ቡድኖች ባብዛኛው ታጋዮች የሚታወቁና ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ
መጀመርያ ካድሬዎች ሰብስበው ስለነሱ መጥፎ ነገር ለታጋዮቹ እንዲወራ ይደረጋል። ለተወሰነ ግዜ ስም የማጥፋት ዘመቻ
ከተካሄደባቸው በኋላ በድምፅ እንዲሸነፉ ወይ ሀገር ለቀው እንዲወጡ ይደረጋል። ይህ ካልተሳካ በክህደት (ወደ ደርግ
እንዳይገባና ምስጢር እንዳያባክን በሚል) አሳበው እንዲረሸን ያደርጋሉ።
(ሁለት) ችግር የፈጠሩ
(ማለት ለስልጣን ስጋት የሆኑ) ታጋዮች ብዙ የማይታወቁ ወይ ያልተማሩ የገበሬ ልጆች ከሆኑ ግን በቀጥታ በድብቅ
ይረሸናሉ። ከዛ ‘በጦርነት ተሰውተዋል’ ወይም ‘ወደ ዉጭ ሀገር ተልከዋል’ ተብሎ ይወራላቸዋል። በዚህ መንገድ
የዉስጥ ጠላቶች (የሐሳብ ልዩነት ያላቸው) ታጋዮች እየተወገዱ በአንድ ቡድናዊ አስተሳሰብ ለሚያምኑ ታጋዮች ብቻ
ስልጣን በመስጠት ህወሓት እነሆ የአንድ ቡድን ንብረት ሆነች።
ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በነበራቸው
ግንኙነት በሚመለከት ደግሞ ህወሓት ከሌላ ድርጅት ጋር ጤነኛ ዕርቅ ወይ ስምምነት ፈፅሞ አያውቅም። ሌሎች ድርጅቶች
ከህወሓት ጋር አብረው ለመታገል ጥያቄ ያቀረቡ የነበሩ ቢሆኑም ህወሓት ግን የዉሸት ስምምነት እየተፈራረመ የሌሎች
ድርጅቶች ታጋዮች በሌሊት (ጨለማ ተገን በማድረግ) ይረሽን ነበር። ድርጅቶቹ ካልተምበረከኩ ደግሞ መጀመርያ ስለ
ድርጅቶቹ መጥፎነት የሚመለከት ወሬ እንዲበተን ይደረጋል። ከዛ ሌሎቹ ድርጅቶች በህወሓት ላይ ጦርነት እንዲያውጁ
ምክንያት ይሆናል። ህወሓትም እነሱ ለመምታት ከህዝብ ፍቃድ ያገኛል ማለት ነው። ስለዚህ አንዱና ዋነኛው የህወሓት
ልዩነትን የመፍታት መንገድ በሃይል እርምጃ ማጥፋት መቻል ነው። ልዩነት የሚፈጥሩ አካላት በማጥፋት ልዩነቱ የጠፋ
ይመስላቸዋል።
በዉስጣቸው የሚፈጠር ችግር በቀላሉ ማሸነፍ እንደማይችሉ ሲረዱስ (ለራሳቸው ህልውና
አስጊ መሆኑ ሲረዱስ)? የተፈጠረው የዉስጥ ችግር ለህወሓት ራሷ አደጋ ላይ የሚጥል ዓይነት ልዩነት ከሆነ ደግሞ
የዉጭ ጠላት ሆን ብለው ይፈጥራሉ። ለምሳሌ በህወሓት ታጋዮች መካከል ዓመፅ የሚነሳበት ሁኔታ ከተፈጠረ የህወሓት
መሪዎች የስለላ መረጃዎችን በማዘጋጀት ወደ ደርግ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንዲደርስና ደርጎች በህወሓቶች ላይ ጦርነት
እንዲከፍቱ ይደረጋል። በዚህ ግዜ ለህወሓቶች የ’ጋራ ጠላት’ መጣ ማለት ነው። ህወሓቶች ለራሳቸው ህልውና ሲሉ
ልዩነታቸው ወደ ጎን ትተው በጋራ ደርግን ይወጋሉ። ስለዚህ ሌላኛው ልዩነት መፍቻ መንገዳቸው የዉጭ ጠላት በመጥራት
ነው።
የህወሓት መሪዎች ልዩነት የሚፈጥሩ እያስወገዱ፣ ሌሎች አዳዲስ ታጋዮች የሚያፈሩበት መንገድ
ነበራቸው። ህወሓቶች በተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ይንቀሳቀሱና ይጠፋሉ። መንቀሳቀሳቸው የደርግ ወታደሮች እንዲያውቁ
ይደረጋል። ደርጎችም ህወሓቶች በተንቀሳቀሱበት አከባቢ እየተዘዋወሩ ህዝብን (አርሶአደሮቹን) ያስፈራራሉ፣
ይገድላሉ። የድርግን ግፍ የሚያስቆጣቸው ወጣቶችም ለመበቀል ጫካ ይገባሉ። ከህወሓቶች ጋር ይቀላቀላሉ። የአብዛኞቹ
ታጋዮች ዓላማ ደርግን ከትግራይ ማባረር ነበር ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ታጋዮቹ በብዛት ጫካ የሚገቡበት ምክንያት
የድርግ ወታደሮች ወደ እርሻ ማሳ እየገቡ ስለሚረቡሿቸው ይመስለኛል። የህወሓት መሪዎች ዓላማ ግን ስልጣን እንደነበር
መገመት ይቻላል።
ስለዚህ የህወሓት የዕርቅ መንገድ የሃይል እርምጃ ነበር። በሃይል የተደገፈ ዕርቅ
ደግሞ የለም። ስለዚህ ህወሓት ልዩነትን በሃይል እስካስወገደ ድረስ የዕርቅ ታሪክ የለውም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም
በህወሓት መንደር የሐሳብ ልዩነት የሚፈታው በሃይል እንጂ በሐሳብ ክርክርና ስምምነት አይደለም። ህወሓት
ተፎካካሪዎቹን በሃይል ያጠፋቸዋል።
ህወሓቶች በሁለት ይከፈላሉ፤ የህወሓት መሪዎችና የህወሓት ታጋዮች።
የህወሓት መሪዎች ዓላማ ስልጣን መያዝ ሲሆን የህወሓት ታጋዮች ዓላማ ግን የደርግን ወታደር በማባረር በነፃነት
ለመኖር ነበር። ለዚህም ነበር ብዙ የህወሓት ታጋዮች (ገበሬዎች ናቸው) ደርጎችን ከትግራይ መሬት ካባረሩ በኋላ ወደ
እርሻ ስራቸው ለመመለስ የወሰኑት። በዚህ ግዜ የህወሓት መሪዎች አዲስ አበባ እንዲያስገቧቸው ገበሬ ታጋዮችን
ለማሳመን ብዙ ጥረት ያደረጉ።
የህወሓት መሪዎች ታጋዮቹን ለምነው ለማምነው አዲስ አበባ
እንዲስገባቸው ተደረገ። መሪዎቹ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ሁኔታዎች ተቀያየሩ። መሪዎቹ የመንግስት ስልጣናቸው ጨበጡ።
የታጋዮቹ የነፃነትና የዴሞክራሲ ዓላማ ተዘነጋ። ታጋዮቹ ጥያቄ አነሱ። ጥያቄ ያነሱ ታጋዮች “ጓሓፍ ፅረጉለይ”
(ቆሻሾቹ አስወግዷቸው) በሚል የመሪዎቹ ትእዛዝ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ያስገቧቸውን 32, 000 የህወሓት ታጋዮች
ባንዴ ተባረሩ። ተቃውሞ ያስነሱ ታጋዮች ታሰሩ፣ ተገረፉ። ስለዚህ ህወሓት ልዩነት ለመፍታት የሚጠቀመው መንገድ
ያልሰለጠነና በሃይል የተሞላ ነው።
ስብሃት ነጋ ተናገረው ለተባለው ነገር ያው የተለመደ የህወሓቶች
ፕሮፓጋንዳ ነው። ህወሓቶች በሐሳብ ልዩነት አያምኑም። የሐሳብ ልዩነት ያለው ሰው እንደጠላት ነው የሚታየው። የተለየ
ሐሳብ የሚያራምድ ሰው በጠላትነት ከተፈረጀ እንዴት የሐሳብ ልዩነት በዕርቅ ወይ ስምምነት መፍታት ይቻላል? ስለዚህ
ህወሓቶች የሐሳብ ልዩነት አልተፈጠረም ብለው ቢሉ አይደንቅም። የሐሳብ ልዩነት ብህወሓት ዉስጥ አይፈቀድማ።
በህወሓት የሐሳብ ልዩነት ስለማይፈቀድ ብዙ የራሳቸው ሐሳብ ሊያራምዱ የሚችሉ ወጣቶች በህወሓት መሪዎች ዘንድ
ተቀባይነት የላቸውም። ማንኛውም አባል አንድና ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ ባሁኑ ግዜ የህወሓቶች
መመዘኛ መስፈርት “የመለስ ራእይ” የሚል ነው። ማንኛውም ወጣት በህወሓት ቦታ እንዲኖረው ከፈለገ “የመለስ ራእይ
ለማሳካት” ቆርጦ የተነሳ መሆን አለበት። ይሄ በራሱ ችግር ነው። አንደኛ “የመለስ ራእይ” የሚባል ትርጉም
ያለው ተልእኮ የለም። የመለስ መንገድ ግልፅ አይደለም። ስለዚህ የመለስ መንገድ የሚከተል ወጣት ገደል ነው
የሚገባው።
ሁለተኛ በዚህ መንገድ ህወሓት ወጣት መሪዎች ሊኖሩት አይችሉም። ምክንያቱም አንድ ወጣት
መሪ ለመሆን የራሱ ወይ የግሉ የሆነ “ራእይ” ሊኖረው ይገባል። የራሱ ራእይ የሌለው ሰው ሌሎችን ሊመራ አይችልም።
የራሱ የሆነ ራእይ ካለው ደግሞ በህወሓቶች ተቀባይነት አይኖረውም። ምክንያቱም በህወሓት ለመመረጥ የራስህ ራእይ
ሊኖርህ አይገባም። ምክንያቱም የራስህ ራእይ ካለህ እንዴት ስለ ሌላ ሰው ራእይ (የመለስ ራእይ) ትጨነቃለህ?
የሌላ ሰው ራእይ ለማሳካት የራስህ ራእይ ሊኖርህ አይገባም። አንድ የራሱ ራእይ ያለው ወጣት ስለ “መለስ ራእይ”
ሊዘምር አይችልም። ምክንያቱም ያ ወጣት “ራእይ” ካለው ጎበዝ መሆን አለበት። ጎበዝ ከሆነ ደግሞ መለስ ራእይ
እንዳልነበረው ማወቁ አይቀርም። ስለዚህ የራሱ ራእይ ያለው ጎበዝ ወጣት “የመለስ ራእይ” ስለሚባለው ተረት ለማሳካት
ብሎ አይደክምም። ለዚህም ነው ጎበዝ ወጣቶች በህወሓት ጥሩ ቦታ የማይሰጣቸው።
በህወሓት ጥሩ ቦታ
ለማግኘት ጎበዝና ባለ ራእይ መሆን አይጠበቅብህም። ጥሩ ቦታ ለማግኘት ከፈለክ ለነሱ ጥሩ ታማኝ አገልጋይ መሆን
አለብህ። በሌላ አባባል የነሱ ‘ባርያ’ መሆን አለብህ። ለነፃነት ከቆምክና ዓቅም እንዳለህ ከታወቀ ግን እንደጠላት
ተቆጥረህ፣ ስም የማጥፋት ዘመቻ ይከፈትብሃል፣ ትገለላለህ፣ ትገመገማለህ፣ ባጠቃላይ ተስፋ የምትቆርጥበት መንገድ
ይመቻቻል። በህወሓት ጎበዝ መሆን ወንጀል ነው።
ህወሓቶች አባላቶቻቸውን ታማኝ ባርያ የሚያደርጉበት
መንገድ አላቸው። አባላቶቻቸው ወንጀል ሲሰሩ ዝም ብለው ይመለከታቸዋል። ሙስና እንዲሰሩ ያበራታቷቸዋል። ጥፋቶቹን
ይመዘግባሉ። አንድ አባል የህወሓት መሪዎች የሚያውቁትን ተራ ወንጀል ወይ የሙስና ተግባር ካለው ታማኝ አገልጋይ
የመሆን ዕድሉ ይሰፋል። ምክንያቱም የሆነ ወንጀል ከሰራ በነሱ እጅ ገባ ማለት ነው። እነሱን ከተቃወመ ወይ እነሱ
የሚያዙትን ካልተገበረ የሰራውን ወንጀል እየጠቀሱ ያስፈራሩታል፤ ያስሩታል፣ ያባርሩታል። ስለዚህ ላለመባረር ወይ
ላለመታሰር ሲል የነሱ ባርያ ሆኖ ያገለግላል። ስለዚህ የሙስና ወይ ሌላ ወንጀል መያዝም አንድ የሐሳብ ልዩነት
ለማጥፋት የሚጠቀሙት መንገድ ነው። ምክንያቱም ወንጀል ካለው ደፍሮ አይናገርም። ደፍሮ ካልተናገረ ልዩነት
አይፈጥርም።
አሁን ህወሓት ብቁና ሐሳብ ሊያመነጩ የሚችሉ አባላት የሏትም። ጎበዞቹ ተገፍትረዋል።
አገልጋዮችና አደርባዮች ብቻ የተሰበሰቡበት ድርጅት ህዝብና ሀገር መምራት አይችልም። ምክንያቱም ህዝብ ለመምራት
የፖለቲካ አቅጣጫ መቀየስ የሚችል መሪ መኖር አለበት። ህወሓት በሙስና፣ በቤተሰባዊነትና በሐሳብ እጥረት ምክንያት
በስብሷል። የበሰበሰ ስርዓት ደግሞ የመበታተን አደጋ አለው። በዚህ ምክንያት ህወሓት የመበታተን አደጋ ተደቅኖበታል።
በርግጥ ባሁኑ ግዜ በህወሓቶች መካከል የተፈጠረው ችግር የሐሳብ ልዩነት የፈጠረው አይመስለኝም።
ብዙ የተለያየ ሐሳብ ማመንጨት የሚችሉ አባላት የሉምና። ያሁኑ ችግር መሪነት የለም። አዛዥና ታዛኝ አይታወቅም።
መመርያ ሰጪና ተቀባይ የለም። እርስበርስ መከባበር የለም። መደማመጥ የለም። በዚህ ምክንያት የመበታተን አደጋ አለ።
የመበታተን አደጋው አስፈርቷቸዋል። ባሁኑ ግዜ አንድን ቡድን ሌላኛውን ቡድን አሸንፎ ጠንካራ ሁኖ የመውጣት ዕድሉ
የመነመነ ነው። ስለዚህ ህወሓቶች እንደ አማራጭ የያዙት መንገድ የዉጭ ጠላትን በመፍጠር እርስበርሳቸው የሚግባቡበት
መንገድ ማመቻቸት ነው። እንደዉጤቱም ህወሓቶች “ስየ አብርሃ ተቃዋሚዎችን አሰባስቦ የኢህአዴግ መንግስትን ለመጣል
እየተዘጋጀ ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ ጀመሩ። አንድምታው “እርስበርሳችን ካልተስማማን የጋራ ጠላት መጥቶ ሁላችንን
ሊያጠፋን ነው” የሚል ነው። ልብ በሉ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ካድሬዎች እነ ስየ አብርሃ ከህወሓት ከወጡ በኋላ
የመጡ ናቸው። ስለዚህ ስየ እንደ ጠላት ያየናል ብለው ማሰባቸው አይቀርምና ፈርተው አብረው ሊሰሩ ይችላሉ ከሚል
ነው።
ይህን የ“ስየ አብርሃ መጣ” ስትራተጂ ግን ብዙ የሚሰራላቸው አይመስልም። ምክንያቱም አንድ
ወድያው ተንኮሉ ተጋልጧል። ሁለት ስትራተጂው ከትግራይ ህዝብ እያጣላቸው ይመስላል። ስለዚህ አሁን የስየ አብርሃ ስም
የማጥፋት ዘመቻ አቁመውታል። የዓረና ፓርቲ “ጠላትነት፣ ከሃዲነት” ወዘተ እየተሰበከ ነው። “ዓረና ከትግራይ
ህዝብ ጠላቶች አንድነት ፈጥሮ የትግራይን ህዝብ ለመጨፍጨፍ እየተዘጋጀ ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ ጀምረው ነበር። ይህ
ስትራተጂም እያከሰራቸው ይገኛል። ምክንያቱም ብዙዎቹ የድሮ የህወሓት ታጋዮች ተቃውሞ እያስነሱ ይገኛሉ።
ከዚህ አልፈው ህወሓቶች በዓረና አባላት ላይ የሃይል እርምጃ በመውሰድ የትግራይ ህዝብ ፈርቶ እንዲገዛ ለማድረግ
ቆርጠው ተነስተዋል። የፖለቲካ ልዩነትን በሃይል ለመፍታት ማለት ነው። በመልካም አስተዳደር ዙርያ ጥያቄና ተቃውሞ
የሚያነሳ ሁሉ ለህወሓቶች “ዓረና” ነው። ዜጎች ዓረና እየተባሉ (የህወሓት አባላት ጭምር ማለት ነው) ይታሰራሉ፣
ይገረፋሉ፣ የደርግን ዓይነት ግፍ ይፈፀምባቸዋል። ይህ ስትራተጂም ለህወሓቶች ኪሳራ ነው። ግፍ የተፈፀመባቸው
የትግራይ ወጣቶች ትጥቅ ትግል ለመጀመር በረሃ እየወጡ ያሉ ይመስላል።
ከዚህ በኋላ ህወሓት
እየተከተለው ያለ ስትራተጂ ህዝብን ማሸበር ነው። ካድሬዎች የሽብር ተግባር በሻዕብያ አማካኝነት ሊፈፀም እንደሚችል
ይናገራሉ። የሻዕቢያ ሰላዮች መያዛቸው፣ ግድያ ሊፈፅሙ ዓልመው እንደነበር ወዘተ የሚሉ የፈጠራ ወሬዎች ይነዛሉ።
ህዝብን ለማሽበር የተዘጋጀ ሴራ ነው። ህዝብ ከተሸበረ አማራጭ ሐሳቦች የሚሰማበት ዕድል አይኖርም። ህዝብ ሰላምና
መረጋጋት ፈልጎ ለህወሓት ጎን እንዲሰለፍ ለማድረግ ነው።
አሁን ጠንከር ያለ ተቃውሞ እያነሱ ያሉ
ዜጎች የተረሱ የድሮ የህወሓት ታጋዮች በመሆናቸው የህወሓት መሪዎች መስጋታቸው አልቀረም። ምክንያቱም እነኚህ የድሮ
ታጋዮች በማስፈራራት መግዛት አይቻልም፣ እንደሌላ ተራ ሰው አይፈሩማ። እነሱ ተቃውሟቸው ከቀጠሉ ችግር ሊፈጠር
ይችላል። እናም በ1985 ዓም ጓሓፍ (ቆሻሻ) ተብለው ንክፅረጉ (እንዲወገዱ) የተወሰነባቸውና አሁን ባስከፊ የኑሮ
ሁኔታ የሚገኙ ታጋዮች ለማግባባት ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም “የታገላችሁበት ዓላማ ጠላቶች ሊነጥቁን ነው።
ተባበሩን” እየተባሉ ነው። ይህ ስትራተጂ የ2007 ዓም ሀገራዊ ምርጫ እስኪያልፍ ድረስ ይጠቀሙታል።
የሚሳካ ግን አይሆንም። ምክንያቱም ታጋዮቹ ተከድተዋል፣ ተበድለዋል። እነሱ ባመጡት መረጋጋት የተጠቀሙት ግን ጥቂት
ተላላኪ ካድሬዎች ናቸው። አሁን ብዙ የሚባሉ የድሮ የህወሓት ታጋዮች የሙሰኛ ሃብታሞች የቤት ዘበኞች ናቸው።
አሁን ቢታረቁ እንኳ ህወሓቶች ሊያስጠጓቸው አይችሉም። ምክንያቱም የትእምት ሃብት ለራሳቸው እንኳ አልበቃ ብሏቸው
እርስበርሳቸው እየተፋጁ ይገኛሉ። የድሮ ታጋዮችም በቀላሉ በጥቅም የሚደለሉ አይደሉም፤ የተታገሉለት ዓላማ ያውቃሉና።
ከድሮ ታጋዮች ጋር ዕርቅ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ያለው በትክክል ታጋዮቹን ለማቅረብና አብሮ ለመስራት ተፈልጎ
ሳይሆን የድሮ ታጋዮቹ ከዓረና ወይ ሌላ ተቃዋሚ ድርጅት ጎን ተሰልፈው የህወሓት መሪዎችን እንዳይዋጉ ለማድረግ ነው፤
ህወሓትን ባይደግፉ እንኳ ቢያንስ እንዳይቃወሙ ለማግባባት። ስለዚህ ዓላማው ዕርቅ ለመፈፀም አይደለም።
ከህወሓት የተገነጠሉ የድሮ የህወሓት አመራር አባላትም ቢሆኑ እንደምንም አግባብተው ህወሓትን እንዳይቃወሙ ማድረግ
ቢችሉ ነው እንጂ ወደ ህወሓት አመራር አባልነት መመለስ የሚችሉ አይመስለኝም። ለፕሮፓጋንዳ የሚረዱ አንድ ሁለት
ተመልሰው ቢገቡ እንኳ ምንም ህወሓትን ሊያድኑ አይችሉም። ህወሓት አሁን ሊድን በሚችልበት ደረጃ አይገኝም። እነሱም
ወደ በሰበሰ ድርጅት ተመልሰው የሚገቡ አይመስለኝም። ቢመለሱም አሁን ካሉ የህወሓት መሪዎች ጋር የስልጣን ሽኩቻ
ስለሚፈጠር ህወሓት ወደ ባሰ ዓዘቅት ነው የሚከታት።
ህወሓትን የማዳን ዘመቻ ቢጀመርም ህወሓትን
የማዳን ተግባር ሊሳካ አይችልም። ምክንያቱም ህወሓቶች ያሰባሰባቸው እህል ዉሃ እንጂ ፖሊሲ፣ ሐሳብ ወይ ርእዮተ
ዓለም አይደለም። የህወሓት አባላት የተሰፈሰፉት ለገንዘብ (ሃብት) ነው። ትልቁ የህወሓት የሃብት ምንጭ የሆነ
ትእምት ደግሞ አሁን ደርቋል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የህወሓት መሪዎች ያለ አግባብ ሲመዘብሩት ነበር። ዜጎች
ይሰራሉ፣ ያፈራሉ። መሪዎቹ ደግሞ የተገኘውን ትርፍ ይከፋፈሉታል። በዚህ መንገድ ትእምት ክፉኛ ከስሯል። ስለዚህ
ካሁን በኋላ የትእምት ሃብት ለመካፈል የሚገባ አባል አይኖርም።
ትእምት በግብር መልክ ከዜጎች
ከተሰበሰበው የመንግስት ካዝና ካልተደጎመ በቀር አንዳንድ ኩባኒያዎች ሊዘጉ ይችላሉ፣ ሰራተኞችም ሊቀነሱ ይችላሉ።
ስለዚህ ህወሓት ባሁኑ ግዜ በእህል ዉሃ እየተጣሉና እየተደባደቡ ባሉበት በጥቅም የሚሰባሰቡበት ዕድል አነስተኛ ነው።
ስለዚህ ህወሓት የማዳን ዕድሉ ትንሽ ነው።
ስለዚህ ህወሓት ልዩነትን አይፈታም፤ ልዩነትን ያጠፋል እንጂ። ህወሓት ልዩነትን የሚያጠፋበት መንገድ በሃይልና በስም ማጥፋት ዘመቻ ነው። የጥፋት ዉጤት ደግሞ ጥፋት ነው።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment