Tuesday, November 19, 2013

ተማጽኖ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም - ሳውዲን በተመለከተ

e
ግርማ ጌታቸው ካሳ
አይኖቼ በደም ቀሉ። ልቤ ተሰበረ። ከሳውዲ አረቢያ፣ ከባህር ማዶ፣ የወገኖቼ ጩኸትና ሮሮ፣ ከጣራዬ በታች የመነጨ ይመስል፣ በጆሮዬ በቅርበት ያቃጭላል። በርግጥ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ መዋረዳችንን አየሁ። በተለይም ደግሞ በአሁኗ ሰዓት፣ እንደ ወገን ምንም ማድረግ ባለመቻሌ ውስጤ ደበነ። የማድርገውን ሳጣ መሬት ተንበረከኩ። አይኖቼን ወደ ላይ አንስቼ፣ እጆቼን ዘረጋሁ።

"ሄሮድስ ሊገድልህ ፈልጎ በነበረ ጊዜ፣ በልጅነትህ ከእናትህና እናታችን ቅድስት ማሪያም እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ጋር ተሰደሃል። የስደትን ኑሮና መከራ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ። አንተ መድሃኔአለም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እባክህ እነዚህ ስደተኞች ወገኖቼን አስባቸው። አንተ ድረስላቸው" እያሉ ጮኽኩኝ።
ትላንትና በአገራቸው መከራ ሲያጋጥማቸው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበር በክብርና በሰላም፣ ኢትዮጵያ መጠለያ እንድትሆናቸው ያደረገው። ዛሬ፣ እነርሱ በእውቀታቸውና ጭንቅላታቸው ሳይሆን፣ ከመሬት በታች ፈረንጆች ባገኙላቸው፣ ዘይት "ሃብታም" ሆኑና፣ አሸዋ ላይ ከመተኛት ዳኑና፣ ይኸው ኢትዮጵያውያንን እንደ እንስሳ እያሰሩ ሲገርፉ እያየናቸው ነው። በርግጥ ይህ እንደ ኢትዮጵያዊ አንገት የሚያስደፋ ነው። የኢሕአዴግ ደጋፊ እንሁን፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁላችንም ተዋርደናል።
ይህ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት፣ በርግጥ፣ ያለ ምንም ማጋነን፣ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከማወጅ ያነሰ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ሳውዲ አረቢያ ለፈጸመችው ግፍ፣ ኦፌሴላዊ ይቅርታ እስክትጠይቅና ግፍ ለፈጸመችባቸው ወገኖች ሙሉ ካሳ እስክትከፍል ድረስ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርበታል። የሳውዲ አምባሳደር፣ ዲፕሎማቶች በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ መባረር ይኖርባቸዋል።
ያ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ቀለማቸው ጠቆር ያሉ አፍሪካውያን ተመሳሳይ እድል ገጥሟቸዋል። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝብ በሙሉ፣ ያላትን ንቀት ነው ሳውዲ አረቢያ ያሳየችው። ሌሎች የአፍሪካ አገራትን በማስተባበር፣ በአፍሪካ ሕብረት ዘንድም፣ ጠንካራ አቋም እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ፣ መንግስት የራሱ በሆኑ ምክንያቶች ማቅማማት ካሳየ፣ ከሁሉም ማእዘናት ኢትዮጵያውያን በመንግስት ላይ ግፊትና ጫና እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ።
ወደ ሁለተኛው ነጥቤ ልመለስ። ሳውዲ አረቢያን ማውገዝ በራሱ በቂ አይደለም። ከማዘን፣ ከመናደድ፣ ከማውገዘና ሰልፍ ከመውጣት ያለፉ እርምጃዎችን፣ እንደ ሕዝብ መውሰድ ያለብን ይመስለኛል።
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው ሊሰለፍ ይገባል። አረቦቹ እንደዚያ ቢያዋርዷቸውም፣ ወገንና ሕዝብ ያላቸው መሆናቸውን ማሳየት ይኖርብናል። አገራቸው መመለሳቸው የተሻለ ነእንጂ የባሰ እንደማይሆን የሚያመላክት ተስፋ፣ በትንሹም ቢሆን ጭል ጭል ማለት ይኖርበታል።
በዚህ አጋጣሚ ለተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝና ጓዶቻቸው፣ ኢትዮጵያዊ፣ ወንድማዊና አክብሮት የተሞላበት ተማጽኖ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። በአገራዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን ማሰባሰብ ያስፈልጋል። ለአባይ ትኩረት እንደተሰጠው፣ በሳውዲ የተጎሳቆሉ ወገኖቻችንን ለማቋቋም ከፍተኛ ገንዘብና ርብርብ ይጠይቃል። በውጭ አገር የሚገኘው፣ የገንዘብ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ፣ አገር ቤት ያሉ ባለሃብቶች፣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። አገር ቤት ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር በጋራ በመነጋገር አንድ ጠንካራ፣ ገለልተኛ፣ የሳውዲ ስደተኞች ኮሚሽን እንዲቋቋም እመክራለሁ። ይህ ኮሚሽን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ፣ በሕግ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሲሻል ዎርክ ባለሞያዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች በተወከሉ ኢትዮጵያውያን በመሳሰሉት ተዋቅሮ፣ በቅርበት ከመንግስት ጋር እየሰራ፣ በስፋት የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎች በማድረግ፣ ስደተኞችንም የማቋቋም የሚሰራ ይሆናል። በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ስደተኞችን ወክሎ በሳውዲ አረቢያ ላይ ክስ የሚመሰረትበትንም ሁኔታ ሊያመቻችም ይችላል።
ኢትዮጵያውያን መጀመሪያውኑ ከአገር ለመሰደድ የሚሞክሩት እንዲሁ በባዶ አይደለም። የኑሮ ውድነት፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት የመሳሰሉ ናቸው ለስደት ሰውን የዳረጉት። መንግስት በዚህ ረገድ አዎንታዊና ስር ነቀል ለውጦች ቢያደርግ፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኞች ቢፈታ፣ ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር፣ ቅንነት ያለበት ውይይት፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ አገር ቤት ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ቢያደርግ፣ የሕግ ስርዓቱ የመጨቆኛ ዱላ ሳይሆን ፍትህ የሚገኝበት ስርዓት ቢሆን፣ የአገራችን አየር የራቁትን የሚስብ እንጂ በቅርብ ያሉትን የሚያርቅ አይሆንም ነበር።
በዚህ አጋጣሚ፣ አገር ቤት ላሉ ተቃዋሚዎች፣ የሳውዲን ኢሰብዓዊ እርምጃዎች በማውገዝ፣ ለጠሩት ሰላማዊ ሰልፎች ያለኝን ታላቅ ድጋፍ እየገለጽኩ፣ አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮዎች ዙሪያ፣ ከኢሕአዴግ ጋር ለመነጋገር ፍቃደኝነቱን እንዲያሳዩም እጠይቃለሁ። መቃወም መልካም ነው። ግን ከመቃወም አልፍው በአገር ጉዳይ ከገዢው ፓርቲ ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል።
እስከምቼ ነው አገር እያለን የምንሰደደው? እስከመቼ ነው ምግብ እያለን የምንራበው? እስከመቼ ነው ክብር እያለን የምንዋረደው? እስከመቼ ነው ወገን እያለን ብቸኞች የምንሆነው? ሳውዲዎች ዘይት አላቸው። እኛም እኮ ፍቅር አጥተን ነው እንጂ፣ ማንም የሚመኘው የተፈጥሮ ሃብት አለን። እንደ ምሳሌ ያሉንን በርካታ ወንዞች መጥቀስ ይበቃል። ደግሞም ማን ያወቃል? ዛሬ ሳውዲዎች የተመጻደቁበት ዘይትም እኮ አገራችን ሊገኝ ይችላል። መቼ በስፋት ተፈልጎ?
በሕዝብ ብዛት ከሳውዲዎች ሶስት አራት እጥፍ ነን። እጅግ በጣም በርካታ ምሁራን፣ ጠበብት፣ ሳይንቲስቶች አሉን። ሳውዲዎቹ ሁሉንም ነገር የሚያሰሩት በነጮች ነው። እኛ ግን ለእኛው እንበቃለን። የጎደልን ፍቅር ብቻ ነው!!!!!
በነገራችን ላይ ፍቅር ሲኖረን፣ ይቅር ስንባባል፣ ፊታችንን ወደ ኢግዚአብሄር ስናዞር፣ ምድራችንንም አምላክ ይባርካታል። እንኳን ለኛ ለሌሎችም የምንተርፍ እንሆናለን። እንግዲህ እግዚአብሄር ፍቅሩን ይስጠን ! ጮሮ ያለው ይሰማ ፤ ልብ ያለው ያስተውል።
(ይሄን ጽሁፍ ለአንባቢያ ከመበተኔ በፊት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እግር ኳስ ጨዋታን ተመለከትኩ። እርግጥ ነው ለአለም ዋንጫ አልበቃንም። ነገር ግን ለተጨዋቾቻችን፣ ለአስለጣኙ ያለኝን ትልቅ አክብሮትና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ። እዚህ መድረሳቸው በራሱ ትልቅ ውጤት ነው። ኮርቼባቸዋለሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ)

No comments:

Post a Comment