Friday, November 22, 2013

ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ አፍሪካዊ መሆን አይቻልም! /Getachew shiferaw/


pm haile
ጠቅላይ ሚንስትርነት በስምም ቢሆን የአገሪቱ ስልጣን ሁሉ የበላይ ነው፡፡ በማይተገበረው ህገ መንግስት መሰረት ከ16 በላይ ስልጣኖችን ያጠቃልላል፡፡ ጤና ባለው ፖለቲካ ቢሆን ኖሮ እዚህ ስልጣን ላይ የወጣ አካል መሸም ነጋም ለአገሩ ብሄራዊ ጥቅም፣ ለዜጎች መብትና ክብር መጨነቁ የግድ ነበር፡፡ዜጎቻችን ከአረቡ አናት ከሆነችው ሳውዲ አረቢያ ጎዳናዎች እየታረዱ የአረቡንና የአፍሪካን ግንኙነት ሲያወድሱ ሰንብተዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ሞት፣ ቁስለትና ክብር መዋረድ አንድም ነገር ያልተነፈሱት ስለ አፍሪካውያን ዜጎች የወደፊት እጣ ፈንታ ደስኩረው ተመልሰዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ሳይጨነቁ ይህን ያህል ስደትና መከራ ስለማይነካቸው የደቡብ አፍሪካ፣ የሞሪሺየስ፣ የሲሸልስ፣ የግብጽ…ዜጎች ከአፍሪካና የአረቡ ዓለም መልካም ግንኙነት የሚጠቀሙትን ለመተንተን፣ ለማስረዳት ሲቃጣቸው አላፈሩም፡፡
ከኩየት ወደ ፖላንድ ያቀኑት ‹‹ፎርጅዱ›› ጠቅላይ ሚኒስትር የእኛዎቹ ህዝቦች ሳውዲ ጎዳና ላይ በስለት እየሞቱ፣ እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተደፈሩ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት በአፍሪካውያን ላይ ስለሚያመጣው ችግር በመናገር ‹‹ጀግና›› ሆነው ተመልሰዋል፡፡የአየር ንብረት ችግር አይሆንም እያልኩ አይደለም፡፡ ግን ሙቀት ለወደጊት ከሚያዛባውና በአሁኑ ወቅት ስለትና ጥይት ከሚገድለው ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር›› በተባለው ሰው የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበር?
እናም ስልጣኑ ሳይሰጣቸው ባለስልጣን የመሰሉት አቶ ሀይለማሪያም ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ፣ ለኢትዮጵያውያን ሳይጨነቁ፣ ለኢትዮጵያውያን ሳይሰሩ ለአፍሪካውያን ለመቆም መሞከራቸው አስቂኝም፣አሳዛኝም፣ አስተዛዛቢም ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ሳያስቡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር መሆን አይቻልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊ በደልና ሰቆቃ ሳይናገሩ አፍሪካዊ መሆን አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ አፍሪካዊ መሆን አይቻልም!

No comments:

Post a Comment