Tuesday, November 26, 2013

የሳምንቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዜናዎች





ገነት ያለው የኦቡዱ ኢንተርናሽናል የተራራ ላይ ሩጫ አሸናፊ ሆነች አምስተኛው የአፍሪካ የተራራ ላይ ሩጫ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ከናይጄሪያው ኦቡዱ ኢንተርናሽናል የተራራ ላይ ሩጫ ጋር በጥምረት የተከናወነ ሲሆን በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ገነት ያለው በወንዶች ኬንያዊው ፊሊሞን ሮኖ አሸናፊ ለመሆን ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተከታታይ በመግባት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ በተቆጣጠሩብት የሴቶቹ ምድብ ፉክክር ገነት ያለው በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ 9 ኪሎ ሜትሩን ለመሸፈን የወሰደባት ግዜም 58 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ነበር፡፡ ገነትን ተከትለው የሀገሯ ልጆች የሆኑት ሰላም አበረ (59:46) 2ኛ፣ አፈራ ጎድፌ (1፡00:00) 3ኛ እንዲሁም እቴነሽ ዲሮ (1፡02.36) 4ኛ በመሆን ጨርሰዋል፡፡ ምንም እንኳ የሀገራችን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በቀዳሚነት ቢያጠናቅቁም ኢትዮጵያ በይፋ የወከለችው ቡድን ባለመኖሩ ምክንያት የአፍሪካ ሻምፒዮንነቱ ክብር በ1:04.29 አምስተኛ ሆና ላጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ኦልታሩኤሽ ፔሪኔ ኔንካምፒ ተሰጥቷል፡፡ ኔንካምፒን ተከትለው የገቡትም አንጄሊና ሙቴኡ እና ሚልድሬድ ቼቦሲም ኬንያዊ መሆናቸው ኬንያ በቡድን የሴቶቹን አሸናፊነት በሙሉ ስድስት ነጥብ እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ ኬንያዊው ሮኖ 13 ኪሎ ሜትሩን 1:00:43 በሆነ ሰዓት በመጨረስ ማሸነፉ በወንዶቹ ምድብ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላለፉት ስድስት ዓመታት ይዘውት የነበረውን ያለመሸነፍ ጉዞ ያቋረጠ ሆኗል፡፡ ኬንያዊው ለአሸናፊነት የበቃው አስቀድሞ የመሪነቱን ስፍራ በመቆጣጠር ሲሆን በ2010 እና 2012 የዚህ ውድድር ሻምፒዮን የነበረው አበበ ድንቄሳም ብርቱ ተፎካካሪው ሆኖ ተስተውሏል፡፡ በ10000 ሜ. የመም ውድድር የዓለማችን አምስተኛው ፈጣን እና የግሉ ምርጥ 26:30.74 የሆነ ሰዓት ያለው አበበ ውድድሩን በሁለተኝነት ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን የጨረሰበት ሰዓትም ከሮኖ በ14 ሰከንድ የዘገየ ነበር፡፡ በወንዶቹ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ሮኖ እና አበበ በግላቸው የተወዳደሩ መሆናቸውም የአፍሪካ ሻምፒዮንነቱ ክብር ሶስተኛ ለወጣው ኡጋንዳዊ ጆፍሬይ ኩሱሮ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ሶፊያ አሰፋ የ32ኛው ክሮስ ኢንተርናሽናል ደ ላ ኮንስቲቱሲዮን ውድድርን በበላይነት አጠናቀቀች ባለፈው ዕሁድ በማድሪድ ከተማ ዳርቻ አልኮቤንዳስ በተደረገው 32ኛው ክሮስ ኢንተርናሽናል ደ ላ ኮንስቲቱሲዮን ውድድር ሶፊያ አሰፋ የሴቶቹ 7.6 ኪሎ ሜትር አሸናፊ ሆናለች፡፡ የለንደን ኦሊምፒክ እና የሞስኮ ዓለም ሻምዮና የ3000ሜ. መሰናክል የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት የሆነችው የ26 ዓመቷ ሶፊያ ያለተቀናቃኝ በበላይነት የጨረሰችበትን የአልኮቤንዳሱን ውድድር 25 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ድል ስታደርግ እርሷን ተከትላ በሁለተኝነት የጨረሰችው ሞሮኳዊቷ ማሊካ አሳህሳህን ከአንድ ደቂቃ በላይ በሆነ ግዜ ቀድማት ነበር፡፡ የወንዶቹን 9.5 ኪ. ሜ. ኬንያዊው ኤማኑኤል ቤት በቀዳሚነት ጨርሷል፡፡
  
አፀዱ ፀጋዬ እና ነፃነት ጉደታ የ2013 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊዎች ሆኑ ዕሁድ ዕለት በአዲስ አበባ በተከናወነው የ2013 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ሁለተኛ ተሳትፎውን ያደረገው የመከላከያው አፀዱ ፀጋዬ የወንዶቹ የበላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የሴቶቹን ምድብ ለመጀመሪያ ግዜ የውድድሩ ተካፋይ የሆነችው የኦሮሚያ ውሀ ስራዋ ነፃነት ጉደታ አሸንፋለች፡፡ በባቡር መስመር ግንባታ ምክንያት በ13 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ሙሉ በሙሉ የመወዳደሪያ መስመሩን የቀየረው የዘንድሮው ውድድር መነሻ እና መድረሻው ጃን ሜዳ ነበር፡፡ ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊዎች ሀጎስ ገብረሕይወት እና አበሩ ከበደ አሸናፊነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ ባይሮጡም የ2013 የቦስተን ማራቶን አሸናፊው እና የሞስኮ ዓለም ሻምፒዮና የማራቶን የብር ሜዳልያ ባለቤቱ ሌሊሳ ደሲሳ እንዲሁም የ2012 የቺካጎ ማራቶን አሸናፊዋ አፀደ ባይሳን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ አትሌቶች የውድድሩ አድማቂ ነበሩ፡፡ መጠባበቅ የበዛበት የወንዶቹ ምድብ ፉክክር እስከሰባተኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ወደፊት ቀድሞ የወጣ አትሌት አልታየበትም፡፡ ከሰባተኛው ኪሎ ሜትር በኋላ በተጀመረው ጠንከር ያለ ፉክክር ሌሊሳ ደሲሳ ወደኋላ ሲቀር የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች ተለይተው በመውጣት ያደረጉትን ፉክክርም የመጨረሻውን መስመር 29 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ያለፈው አፀዱ ፀጋዬ በበላይነት ጨርሷል፡፡ የኦሮሚ ፖሊሱ አዱኛ ታከለ (29:25) እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ሁነኛው መስፍን (29:28) ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የብር እና ነሐስ ሜዳልያ አግኝተዋል፡፡ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው አፀዱ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹በታላቁ ሩጫ ላይ ስካፈል ዘንድሮ ሁለተኛዬ ሲሆን በከዚህ በፊቱ ሙከራዬ ውጤታማ አልነበርኩም፡፡ ለዘንድሮው ውድድር ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ አዲሱ የመወዳደሪያ ስፍራ ዳገት የበዛበት የነበረ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹም ጠንካራ ነበሩ፡፡ ማሸነፌ የዝግጅቴ ውጤት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስላሸነፍኩም በጣም ደስ ብሎኛል›› ብሏል፡፡ አፀዱ በቀጣይነት በዘንድሮው የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉትን አትሌቶች ለመምረጥ በጥር ወር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የማጣሪያ ውድድር ላይ እንደሚካፈልም ጨምሮ ጠቅሷል፡፡
የሴቶቹ ምድብ ፉክክር ከወንዶቹ በተለየ መልኩ ገና ከሶስተኛው ኪሎ ሜትር አንስቶ አትሌቶች መበታተን የጀመሩበት ሲሆን የ2012 የቺካጎ ማራቶን ሻምፒዮኗ አፀደ ባይሳም አብዛኛውን የውድድሩ ርቀት ፊት መሪ ነበረች፡፡ ከአምስተኛው ኪሎ ሜትር በኋላ መሪነቷን አጠናክራ የቀጠለችው አፀደ ከተከታዮቿ ጋር የነበራትን ርቀት ማስፋቷ የውድድሩ አሸናፊ ትሆናለች ተብሎ እንዲገመት ቢያደርግም ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀረው ነገሮች በፍጥነት መልካቸውን ቀይረው የመሪነቱን ስፍራ በቅርብ ርቀት ስትከተላት ለነበረችው ታደለች በቀለ ለማስረከብ ተገዳለች፡፡ የታደለች መሪነትም ብዙም ሳይቆይ ከኋላ በመጣችው ያልተጠበቀችው የውድድሩ አሸናፊ ነፃነት ጉደታ የተወሰደ ሲሆን ነፃነት የመጨረሻውን 1.5 ኪሎ ሜትር ወደፊት ቀድማ በመውጣት 33 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ በሆነ ግዜ አሸናፊ ልትሆን ችላለች፡፡ ‹‹ታክቲካል የሆነ ሩጫን የተገበርኩ ሲሆን በመወዳደሪያ ስፍራው የመጨረሻ አቀበታማ ቦታ ላይ የተፎካካሪዎቼን አተነፋፈስ በመመልከት ለመውጣት ስሞክር የተከተለኝ ሰው ያለመኖሩም ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜትን ፈጥሮልኛል›› ያለችው ነፃነት በታላቁ ሩጫ አዘጋጅነት የተከናወነው የዘንድሮው የኮካ ኮላ ተከታታይ የ7 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የሴቶቹ ምድብ የአጠቃላይ አሸናፊ ነበረች፡፡

 http://www.ethiotube.net

No comments:

Post a Comment