ለምን ጣልከኝ? (ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ)
ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ልሞግትህ ፍቀድልኝ!
አንድ ግዜ ብቻ ልናገር ለባሪያህ እሺ በለኝ
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ደስታዬን ወሰድክብኝ አሳዘንከኝ
እስቲ ንገረኝ ለምን ጣልከኝ?
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ልሞግትህ ፍቀድልኝ!
አንድ ግዜ ብቻ ልናገር ለባሪያህ እሺ በለኝ
ለምን ጣልከኝ? አሳፈርከኝ!
ደስታዬን ወሰድክብኝ አሳዘንከኝ
እስቲ ንገረኝ ለምን ጣልከኝ?
እንዳለህ በመንበርህ አምናለሁ
በሦስትነት ባንድናትህም አውቅሀለሁ
ደብረ ደብሬ ታቦት ቀርጬ
ድረሳን ጽፌ ማህሌት ቆሜ
ኤሉሄ ኤሉሄ እልሀለሁ
ዕድሜ ዘመኔን ጽናጽል አጮሀለሁ
ሀሌ ሉያ ህያው ነህ ብዬ እላለሁ
ደግሞም ስምህ ቢቀየር በሬቻ
አላህም ቢልህ ቃልቻ
አንተ አንድ ነህ አመልክሀለሁ
ጠዋትም ማታ አቤቱ እልሀለሁ።
ከኦሪት በፊት በልቦናዬ አሀዱ ብዬ
በኦሪትም ቢሆን አመሳጥሬ ብዬ አንድዬ
በሀዲስማ እንዳስተማርከኝ አንድነትህን ተከትዬ
ስምህን ጠርቼ አልጠግበውም
እልሀለሁ አምላኬ መድኃኒዓለም
ታዲያ ለምን ጣልከኝ?
ልሞግትህ እሺ በለኝ
አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር ለባሪያህ ፍቀድልኝ
ለምን ጣልከኝ?
ትላንት ከማዕዴ የቆረሰ
እራፊ ጨርቁን ከዕኔ የተዋሰ
ዛሬ እንዴት በረታብኝ?
እስቲ ንገረኝ
እንደ ዳዊት ቅድስና ባይኖረኝም
የያዕቆብን ታላቅነት ባላገኝም
ሳትነግረኝ አለቅህም
እጮሀለሁ ደግሜ ደግሜ እጮሀለሁ አልተውህም
እናም ደግሜ እልሀለሁ
ለምን ጣልከኝ ብዬ እጠይቃለሁ?
ብወድቅም የምታነሳኝ አንተ ነህና እማጸናለሁ።
ለምን ጣልከኝ?
ያንንም ስም ገናናነትን አንተ ነበርክ የሰጠኸኝ
በዓለም ፊት ያከበርከኝ ያገነንከኝ
ታዲያ ዛሬ ለምን ጣልከኝ
ጥቁሩ ወንድሜ የሚመካብኝ ታላቅ ህዝብ ነው የሚለኝ
ነጩ የሚያፍረኝ በሙሉ አይኑ የማያየኝ
ክንዴ እሳት የጠላውን የሚፋጅ የሚጎስም
ለወዳጁ ፈጥኖ ደራሽ የሚደጉም
ይህ ሁሉ ግን ዛሬ የለም
ስለጣልከኝ፣
የሚያዝንልኝ አልተገኘም!
ሐበሽ ብሎ እንዳልጠራኝ
እጄን ስቦ እንዳልሳመኝ
ደስታዬ ነው ቤቴ መጣህ ብሎ እንዳላለኝ
ዛሬ ግን ጥላት ሆኖ ተነሳብኝ
ስለጣልከኝ!
ሳዱላዎቼን ለቤቱ ግርድና ወሰዳቸው
ሳተናዎቼን ግመል በፊቱ አስጎተታቸው
በጊንጠ ጅራፍ ገረፋቸው
ሀሞት ከርቤ ጋታቸው
የሞት ጥዋ አጠጣቸው።
ማን አየልኝ የእኔን ስቃይ
ማን ሰማልኝ የእኔን ጉዳይ
እስኪ ንገረኝ!
ለምን ጣልከኝ?
መገፋትን መገረፍን
መበደልን ፍትህ ማጣትን
ታውቀዋለህ ለዚህ ሁሉ ምሳሌ ነህ።
እውነትን በማያውቁ
በሌሎች ሀዘን በሚስቁ
በጨካኞች በክፉዎች መንገላታት
ታውቀዋለህ በደቦ ሕግ መገፋት
እስኪ የሆነብኝን ዕይልኝ
በቃሽ በለኝ ፍረድልኝ
ወድቂያለሁ ደቅቄያለሁ እባክህ ትችላለህና አንሳኝ
ለምን ጣልከኝ?
ማን አጠፋ?
የመረጥህ የሾምካቸው?
መከራህን (መስቀልህን) ያስያዝካቸው?
በነሱ አልፈርድ እነሱም እንደኔ ፍጡር ናቸው
ድንጋይ መካብ ግንብ መስራት ካማራቸው
ጣፋጭ ወይን ከጣላቸው
የሺ ዓመቱን በዕለት ጉርስ ከቀየሩ
ከያዕቆብ ሳይሆን ከኤሳው ስጋ ከተሰሩ
ባለም ነዋይ ከዓለም ጋር ከተዳሩ
አንተን ትተው ለምድር ጌቶች ካደሩ
ለኔም ተርፎ ጥፋታቸው ክፋታቸው
በረሀቡም በበሽታ በስደቱም ዕቀጣለሁ
የእንባ ዘለላዬን አፈሳለሁ።
በእነሱ ግፍ ከቀጣሀኝ
እልሀለሁ ስላለፉት ስትል ማረኝ
ይህ ካልሆነ፣ በምን ምክንያት አሳጣኸኝ?
ፍቅር በሌላቸው እጅ ተውከኝ ጣልከኝ!
እናም ፍቅሬ ውዴ
አንተው ነህ የሩቅ የቅርብ ዘመዴ
የፍልስፍና የኃይማኖት አምዴ
መቀመጫ መሽከርከሪያ አውዴ
ኤሉሄ ኤሉሄ ማለቴን
የምታነሳኝ አንተ ነህና ተመልከትልኝ ስቃዬን
ለምን ጣልከኝ?
ሀምሳ መቶ አብርሀሞች ባይገኙ
ባዶም ቢሆን አደባባይ ዕልፍኙ
የሰበርከውን ስትጠግን አውቃለሁና
ክፉ ዘመኔን አሳልፍልኝ ቃልህን ብቻ ተናገርና።
አምርሬም እጮሀለሁ!
ለምን ጣልከኝ? እልሀለሁ(2)
ፀጋዬ ኃይለማርያም ግርማ
ህዳር፣ 2006፣
መታሰቢያነቱ በሳውዲ ዐረቢያ በከንቱ ደማቸው ለፈሰሰ ወገኞቼ!!
ህዳር፣ 2006፣
መታሰቢያነቱ በሳውዲ ዐረቢያ በከንቱ ደማቸው ለፈሰሰ ወገኞቼ!!
No comments:
Post a Comment