Friday, November 22, 2013

የመጠላለፉ ፖለቲካ ለማን ይጠቅማል? #Miniliksalsawi #Ethiopia

በዚህ 20 አመት ውስጥ ለኢትዮጵያውያን የማይወጣ ዳገት የሆነው የኢህአዴግ ስርዓት ብቻ አይደለም፡፡ የተቃዋሚዎች መጠላለፍም ህዝብን ተስፋ ሲያስቆርጥ ኖሯል፡፡ እንዲያውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥውን ለመቃወም ከሚያደርጉት በላይ እርስ በእርስ ለመጠላለፍ በርካታ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ሆነዋል፡፡
ሰሞኑን ፌስ ቡክ ላይም የምናነበው ይህን መጠላለፍ ነው፡፡ ሳውዲ ውስጥ ዜጎቻችን ሰቆቃ እየደረሰባቸው ባለው ወቅት ሳይቀር ተቃዋሚዎች እርስ በእርሳቸው ይናቆራሉ፡፡ ምንም እንኳ ጭቅጭቁ ፌስ ቡክ ላይ ቢሆንም የፓርቲዎቹን አቋም ግን የሚያንጸባርቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የሚያስገርመው ደግሞ የሚናቆሩት ይህ ነው የሚባል የፖሊሲም ሆነ ሌላ የሚያጨቃጭቅ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች አለመሆናቸው ነው፡፡
ተጨቃጫቂዎቹ የዚህ ትውልድ ወጣቶች መሆናቸው ደግሞ ይበልጡን ያስገርማል፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሁለቱ ፓርቲዎች የተቀራመቷቸው የባለ ራዕይ ወጣቶች አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ በእድሜ ከገፉት ፖለቲከኞች ይልቅ ወጣቶች ከመግባባትም አልፎ ሁለቱን ፓርቲዎች ማቀራረብ ነበረባቸው፡፡ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲ ያደረገውን ሰልፍ ሲነቅፉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ደግሞ አንድነት መንግስትን ገፍቶ መሄድ እንዳልቻለ ይተቹታል፡፡ መተቻቸት አንድ ነገር ነበር፡፡ ሆኖም በሁለቱ አባላት መካከል የሚደረገው እሰጣ ገባ ከምክንያታዊነት ይልቅ በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጭራሹን ጥላቻም ይታከልበታል፡፡ ከአሁኑ ካድሬያዊ ባህሪም ይታይበታል፡፡
እንደ እውነት ከሆነ ሁለቱ ፓርቲዎች አብረው ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ነበረባቸው፡፡ ሆኖም በመካከላቸው ባለው የመጠላለፍና የመጠላላት ችግር ለየብቻቸው አድርገውታል፡፡ አንድነት ደግሞ ጭራሹን አልቻለም፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ አንድነትና ሰማያዊ ክፍተቶች ታይቶባቸው ይሆናል፡፡ ግን እነዚህ ክፍተቶች ኢህአዴግ የፈጸመውን በደል እያለ ሁለቱን መነታረክ አልነበረባቸውም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የመጨረሻው አይደለም፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች (ወጣቶቻቸውም) ሌሎች በርካታ ትግሎች ይጠብቃቸዋል፡፡ ባለፈው የታየውን ስህተት በሚቀጥሉት ማረም ይችሉ ነበር፡፡ አሁን የሚታየው ግን አንዱ የሌላውን ስህተት ሲያገን፣ አንዱ ውድቀቱን በሌላው ላይ ሲያላክክ፣ አሊያም በማይተቸው ሲተች ነው፡፡
በበኩሌ ‹‹ተባበሩ አሊያም ተሰባበሩ›› የሚለው መርህ አይመቸኝም፡፡ ቢያንስ ለገዥው ባለመተባበር ላይ ግን መተባበር የግድ ይላቸዋል፡፡ እርስ በእርሳቸው ሲናቆሩ ተስፋ የሚያስቆርጡት፣ የሚያስገዙት ህዝብን ነው፡፡ ከ97 በኋላ የተፈጠረው መከፋፈል፣ መናቆርና መጠራጠር በርካታ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ የፓርቲዎቹ አባላት ደግሞ ቀዳሚ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ እናም መጠላለፉ ለገዥው ካልሆነ በስተቀር ለማንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሀሳብን በነጻነት መናገር አንድ ነገር ነው፡፡ የሀሳቡን ጥቅምና ጉዳት ሳይመዝኑ መዘላለፍ፣ መናቆር ግን ፖለቲካችን በብስለት ላይ ያልተመሰረተ ለመሆኑ አመላካች ነው፡፡
በሚያስማማቸው መተባበር ቢችሉ መልካም ነገር ነው፡፡ መተባበር ባይችሉ እንኳን አንዱ ሌላውን ባለመጥለፍ ቢተባበር መልካም ይመስለኛል፡፡ አይደለም በአሁኑ ዘመን ፖለቲካ በ1970ዎቹ ታጣቂዎች ለገዥዎች ክፍተት ላለመፍጠር ልዩነታቸውን በሰላም ፈትተዋል፡፡ ሳይግባቡ ሲቀሩ እርስ በእስር ላለመጠላለፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ እንዴት በዚህ ዘመን ያቅታል?
የፓርቲዎች ድክመት ለፖለቲካ ትግሉ እንቅፋት እየሆነ ነው ከተባለ እንኳ ችግሩ መፈታት ያለበት በመጠላለፍ አይደለም፡፡ በሰከነ መንገድ ተወያይቶ መፍታት፣ ተነጋግሮ መግባባት ካልተቻ የየራሱን ትግል አጠናክሮ ትክክለኝነቱን በማሳየት የሌላው መንገድ ስህተት መሆኑን ማሳየት ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት እነዚህ ሁለቱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግን መቃወም ብቻ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ህዝብ ተቃዋሚዎች የትግሉ ዳገት ላይ ሲደርሱ እርስ በእስር ተጓትተው እንደገና ተስፋ እንደማያስቆርጡት፣ ዋጋ እንደማያስከፍሉት፣ እንደገና ተከፋፍለው እንደማያስገዙት ካወቀ ብቻ ነው ሊከተላቸው የሚችለው፡፡ እንዲያው ቢከተላቸው እንኳ እነዚህን ስህተቶች ላለመድገም መዘጋጀት ይሆርባቸዋል፡፡ ከሁለቱም ፓርቲዎች አባል ባልሆንም ለመጠጋት ስሞክር ይች መጠላለፋቸው እምነት አሳጥጣ እንደገና ትገፈትረኛለች፡፡ ይህ ለሌሎችም ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡ ህዝብ ትግሉን በሙሉ ልብ ለመቃለቀል የሚፈራውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በቅርብ ጊዜያት እንደምናየው መጠላለፍ ከሆነ አሁን የሚጠላለፉት ፓርቲዎች መካከል አንዱ ስልጣን ቢይዝ ከኢህአዴግ ባልተነሰነሰ ሌላኛውን ለማፈን ወደኋላ እንደማይል ነው፡፡ መሳሪያ ቢኖራቸው ደግሞ ተጨፋጭፈዋል፡፡ ህዝብ ተቃዋሚን የሚደግፈው ገዥውን ስለሚቃወም ብቻ ሳይሆን ገዥው የፈጠሩትን ስህተት የማይደግሙ ከሆኑ ብቻ ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ ‹‹ብሄራዊ እርቅ›› ሲወራ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ስላለው አለመግባባት ነው የሚወራው፡፡ ኢህአዴግ ለብሄራዊ መግባባትም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች እጁን ያልሰጠው ተቃዋሚዎች መካከል ባለው መጠላለፍ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ የተቃዋሚዎች መጠላለፍ ኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች ከሚሰሩለት በላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶለታል፡፡ ስለሆነም ከገዥው ጋር ከሚደረገው ትግል ቀድሞ ተቃዋሚዎች እርቅ፣ መግባባት…ብቻ ትግሉን ወደኋላ ከመጎተት የሚታደግ አንዳች መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን እንደተለመደው በትኩሳትና ሰሞነኛ ፖለቲካ ዳገቱ ላይ ደርሶ እርስ በእርስ ተከፋፍሎ፣ ህዝብን ተስፋ አስቆርጦ፣ ገዥዎችን አጠናክሮ ከመመለስ ያለፈ ውጤት ጠብ ሊል አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ ትውልዱን ለማይወጣው ተገዥነት አሳልፎ ይሰጠዋል፡፡
 
 

No comments:

Post a Comment