Tuesday, April 29, 2014

የጌታን እናት ማርያምን ነገር ማን ያውቀዋል?!




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ በሥጋ ትዛመደን ዘንደ ከእኛ ወገን በመረጥካት ቅድስት እናትህ ማርያም ሥም እንዲሁ እንደተዛመድከን መከራችንን ሁሉ ትቀበል ዘንድ በወደድክበት ፍቅርህ ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
በቅርቡ አንድ "ነገረ ማርያም የተባለው መተጽሐፍ ልዩ ወንጌል (ከወንጌል ያፈነገጠ) ነው" በማለት ስለ ነገረ ማሪያም የሚተች ጽኁፍ ከአንድ አባ ሰላማ ከሚል ደረ-ገጽ (www.abaselama.org/2014/03/blog-post_27.html‎) ማንበቤን ተከትሎ ይህንን አስተያየተን ለመሰንዘር ወደድኩ፡፡  በዚህ ዘመን ሀይማኖታዊ የሚመስሉ ነገሮችን በጥንቄ ማስተዋል እንዳለብን ስለአሳሰበኝ ይህችን ላካፍላችሁ በሚል፡፡ አነበብኩት ያለኳችሁን ነገረ ማርያምን የሚተቸው ጽሁፍ ብዙዎቻችሁ አንብባችሁታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ትችቱን በደፈናው ለቃወም አይደለም፡፡ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት የቅንነት ሳይሆን አንድ ነገርን መዞ ብዙ ሕዝብን ለማደናገር የታሰበ ስለመሰለኝ እንጂ፡፡ እርግጥ ይህ ጽሑፍ መነሻ ሆነኝ እንጂ ብዙ ሌሎች ተቃርኖአዊ የሆኑ መልዕክቶችን ስለሀይማኖት የሚያስተላልፉ በተለይም ደግሞ የጌታ እናት ነገር ከነዚያ አይሁዳውያን ቀናተኞች ባልተናነሰ የሚያናድዳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ግን ምን ማድረግ ይቻላል ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናት ነች! ይሄንን ማን ሊሽረው ይችላል! ነገረ ማርያምም በሉት ሌላ ታሪክ ከዚህ እውነታ በላይ ስለጌታ እናት ማንነት ሊመሰክርልን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምንአልባት የአምላክ እናት የሆነችበትን ሆኔታዎች በሰውኛው ሊተነትኑልን ይሞክሩ ይሆናል እንጂ፡፡ የአምላክ እናት ለመሆን የበቃችበት ማንነቷ ግን ፈጣሪዋም ልጇም በነው እግዚአብሔር የሚታሰብ እንጂ በእኛ አእምሮ ሊታሰብ የሚችል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህ ሚስጢር ነብያትንም በጨረፍታ እየመጣ ሲያስጨንቃቸው የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ እሷ ራሷ እንኳን መልአኩ ነገራት እንጂ በፈጣሪዋ ዘንድ የዚህን ያህል የተከበረች እንደሆነች የተረዳችው አይመስልም፡፡ መልዐኩም ቢሆን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በማለት የተነገረውን ከሴቶች ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ብሎ ምስራቹን ነገራት እንጂ ሂደቱን ምን እንደነበር አልገጸውም፡፡ ኤልሳቤጥ የጌታን እናት ማንነት ለማየት የቻለቸው በመንፈስቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ኤልሳቤጥም የቱንም  ያህል የጌታ እናት ዘመዷና በእድሜም ልጇ ልትሆን ብትችልም ልተጎበኛት ወደቤቷ በመምጣቷ እጅግ የተደሰተችም ቢሆን ከራሷ ክብር ጋር አነጻጽራ የጌታዬ እናት ሆይ ወደእኔ ትመጭ ዘንድ እኔ ምንድነኝ ስትል ነበር የደነገጠችው፡፡ ኤልሳቤጥ ግን ከነበይም በላይ የሆነው የዮሐንስ እናት ነች፡፡  ዮሐንስ ስለጌታ ሲናገር የእግሩን ጫማ እንኳን ልፈታ የማይገባኝ እንዳለው ነበር እናቱ ኤልሳቤጥ የጌታን እናት በአየች ጌዜ የተናገረችው፡፡ ይህ እውነታ በሥጋ የሚታይ አይለም፡፡
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመልሳችሁና ይህ አነበብኩት ያልኳችሁ ነገረማርያምን የሚተቸው ጽሑፍ መሠረታዊ ነገሩ ለመቃወም ብቻ ይመስላል፡፡ እንደዘመኑም ሀይማኖታዊ ነገር ላይ ትችት ለመሰንዘር ምንም የማይከብዳቸው አይነት ሰው የጻፈው የሚስላል፡፡ ሲጀምር ነገረ ማርያም የሚባለውን መጽሐፍ ተችው አንብበውት የሚያውቁ አይመስልም፡፡ ከአነበቡት ደግሞ ሆን ብለው ደብቀውታል፡፡ እንደእውነቱ አኔም ይህ ነገረ ማርያም የሚባለውን መጽሐፍ አንብቤው አላውቅም፡፡ እኔ በብዙ ፀሎት መፅሐፍት ላይ የተካተተው ነገረ ማርያም የሚለው የነገረ ማርያም ዋናው መጽሐፍ መሆኑንም አላውቅም፡፡ ይልቁንም ይህ በጸሎት መጽሐፍ የተካተተው ነገረ ማርያም እንዳለ በነገረ ማርያም በማለት ብዙ ዋቢዎችን ከነገረ-ማርያም፣ ከሌሎችም መጻሕፈት እያጣቀሰ የሚናገር እንደሆነ አንብቤያለሁ፡፡ ይህን በጸሎት መጽሐፍ የተካተተውን ነገረ-ማርያም ልብ ብላችሁ እንደሆነ የእመቤታችንን ታሪክ እስከ ወደ ቤተመቅደስ የገባችበትን ጊዜ ሊተርክ ይሞክርና ከዚያ ፍጹም ከዚህ ታሪክ ጋር የተቋረጠ ሌላ ትንተና/ሐተታ ጀምሮ እንደገና ወደ ታሪኩ ሲመለስ እናያለን፡፡ እንግዲህ ይህ በመሀል የገባ ሐተታ ነው ለተችው ክፍተት ፈጥሮ ነገረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ ልዩ ወንጌል ነው ሲሉ በሰፊው የነገረ-ማርያም መጽሐፍ ሊነቅፉ ለጸሐፊው እድል የሰጣቸው፡፡ በትክክልም ይህ በመሀከል የገባው ሐተታ በልዩ ሚስጢራዊ ትርጓሜ ካልሆነ ለጌታ እናት ይነገራል ብዬ እኔም አልቀበለውም፡፡ ግን ይህ የነገረ ማርያም አካል ለመሆኑም ምንም ማሳያ የለም፡፡ እዛ ሐተታ ውስጥ በሌሎቹ የጽኸሑፉ ክፍሎች እንደምናነበው ነገረ ማርያም እንዳለ የሚል ወይም ሌላ መጽሐፍ አንድም ዋቢ ሲጠቀስበት አይታይም፡፡ ጸሐፊው ይህንን ሐተታ መተቸት ወይም ጥያቄ ማቅረብ ቢሞክሩ ሐሳባቸው ከቅንነት የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የተችው አካሄድ ለመቃረንና በድፍረት በአላወቁትም ነገር ወይም ሌሎችን ሆን ብሎ ለማሳሳት እንዳይሆን አሰጋለሁ፡፡ ይህ መሀል የገባ ሀተታ ግን በቤተክርስቲያን ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው በዬ አምናለሁ፡፡
አንድ አንድ ጊዜ መጽሐፍትን የሚበርዙ ነገሮች ልዩ ፍላጎት ባለቸው ተርጓሚዎችና አሳታሚዎች በቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚካተቱ እናውቃለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ዋናው መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን መሠረታዊ ትርጉምን የሚያፋልሱ ብዙ የሚበርዙ ዓረፍተ ነገራት ተካተውበት እናያለን፡፡ ዛሬ ዛሬ እንደውም ይህ መጽሐፍ እየታተመ ያለው እንደየ እምነቱ ፍላጎት ሆኗል፡፡ ይህ የመጽሐፍት በልዩ ታሪክ መበረዝ ደግሞ በሌሎች መጻሕፍትም እንደሚከሰት እራዳለሁ፡፡ ስለ እመቤታችን ዛሬም ድረስ ብዙዎች ሊተነትኑት የሚሞክሩበት አካሄድ መሠረታዊ እውነታዎችን እንዳያፋልስ እሰጋለሁ፡፡ ብዙዎች በሥጋ ዕውቀትና ፍልስፍና እንዲሁም በተራ ስሜት እንጂ በልዑል አምላክ ሀይል ሥር በመንበርከክ በምትመጣ ጥበብ/ፍልስፍናና ማስተዋል ላይጽፉ ይችላሉና፡፡ የሀይማኖትን ነገር ደግሞ ብዙ ሕዝብ የሚቀበለው በየዋሕነት እንጂ ተረድቶና አውቆ አይደለም፡፡ ለክርስትናው ግን የተነገረው መልዕክት እንደ አባብ ብልህ እንደ እርግብ የዋሕ እንጂ የዋህነት ብቻ አይደለም፡፡ ይሄው የዋሕነት በትላልቅ አባቶች ሳይቀር ስለሚያይል ጥፋት እየጠፋ እያዩ እነኳን ተው ብሎ ለመገሰፅ የማይቻለቸው ጊዜ ብዙ ነው፡፡
የጌታ እናት ሩሕሩሕነት በሰው አእምሮ እንኳን ሊታሰብ የማይችል እንደሆን አምናለሁ፡፡ ባሕሪዋ የልጇ በሕሪ ነውና፡፡ ሞትንም የምትፈራው ነች ብዬ አላምንም፡፡ ወዴት እንደምትሄድም ታዋቃለችና፡፡ ይልቁንም ምድራዊ ሕይወቷ ሁሉ የመከራና የሐዘን እንደነበር እናያለን፡፡ ስለብዙዎች እሷ ማዘን ነበረባትና! እንግዲህ በጸሎት መጽሐፍ ነገረ-ማርያም በሚለው ምዕራፍ ውስጥ የገባው ይህ ልዩ ሐተታ እንዴት እንደሆነ አባቶች ቢያብራሩት መልካም ነው፡፡ እንደተባለውም ስሕተት ከሆነ በትክክል በይፋ ተነግሮ መሰረዝ አለበት  ብዬ አምናለሁ፡፡ ስህተት ሆኖ እያለ ቢዘነጋ ግን ራሱ ኑፋቄ ከመሆኑም በላይ ለሌላ ኑፋቄ መዳረጉ ግልጽ ነው፡፡ ነገረ-ማርያምን በድፍኑ ለመንቀፍ ምክነያት እንደሆነ ሁሉ ሌላ የሀይማኖት ጉድፍ እንዳይሆን አስባለሁ፡፡ ብዙዎቻችን በማንበብ እንጂ በማስተዋል የምንሄድ አይደለንምና፡፡ ለፈላስፎቹ ግን አለም አለማትን (the entire universe) በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ አምላክ እናት ከመሆን ያለፈ ታርክ አያስፈልጋቸውም፡፡ ለዛም ይመስላል አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰው ሆኖ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ/ሚስጢር የሚያስደንቃቸው፡፡ የጌታ እናት ማንነት ታሪክ ደግሞ ያለው አዚህ ልዩ ሚስጢር ውስጥ ነው! 
ቅዱስ አባት ሆይ በማስተዋል አንኖር ዘንድ ከአነት የምትገኝ ዕውቀትን ስጠን!
አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሚያዝያ 21፣ 2006 ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment