Monday, April 21, 2014

ኢትዮጵያን ለዘመናት የተቆራኛት ልክፍት፡ ከዓላማ ይልቅ ጥላቻን መሪ ያደረገ ፖለቲካ!




እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳዔ በዓል አደረሳሁ!
ይህ የእኔ ብቻ አመለካከት ነው ብዬ አላምንም፡፡ እንደ እኔ አረዳድ ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ዘመናት ለትውልድና አገር በማያስቡ መሪዎች የተመራች እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ማመን ብቻም ሳይሆን ምንአልባትም ማንም ምሁር ነኝ የሚል ሳይቀር አደለም ብሎ ማሳመኛ ማቅረብ በማይችልበት መልኩ የታሪክ እውነታዎቹ ለእምነቴ ዋቢ ሆነው ይቆሙልኛል፡፡ ዛሬ የምናያት ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ታላቁ ሰው ምኒሊክ ከመመስረታቸውም በፊት በሌላ ሥምም ቢሆን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አካል የሆነው ታሪክ በዓለማችን ካሉ ጥንታዊ ከሚባሉ አገራት አንዷ ያደርጋታል፡፡አክሱማውያንና በአገዋውያን (ዛግዌያውያን) የነበሩ የታሪክ ምስክሮቿ ብልህና አስተዋይ መሪዎች እንደነበሯት የሚያሳየውን ያህል ከዚያ በኋላ የመጡ መሪዎቿ በጣም የወረደና አሳፋሪ አስተሳሰብ እንደነበራቸው እንገነዘባለን፡፡ እርግጥ በቀደሙት የአክሱማውያን ወይም ዛግዌያውያንም ዘመን ምን ያህሉ ዘመናት በአስተዋይ መሪዎች ምንያህሉ ደግም በወራዳ መሪዎች እንዳለፈ አላውቅም፡፡ ሆኖም ተደምሮና ተቀንሶ ውጤቱ የአስተዋይ መሪዎቹ ዘመናትና ሥራዎች እንደሚመዝን እረዳለሁ፡፡

ከአገዋውያኑ በኋላ ግን በግልጽ የሚታይ ከመንደር ያለፈ አስተሳሰብ ባልነበራቸው የዱርዬነት ባሕሪ በነበራቸው አለሌ መሪ ተብዬዎች ታላቁ ባለራዕይ ምኒልክ አንድ አስከሚያደርጓት ድረስ አገሪቱ ተበታትና እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የታላቁ ባለራዕይ ምኒልክ ምኞትና ቁርጠኝነት አገሪቱን ወደ ትልቅነት መስመር ላይ ሊያመጣ ቢችልም ባለራዕዩ በዘመናቸው ከነበረባቸው የማየሕይብ ከሰፈርና ከራሳቸው ሆድ በላይ ማሰብ ከማችሉ ሰዎች ጫና በተጨማሪ ለሕይወታቸው ሕልፈት ሳይቀር የክፉ ሰዎች መሠሪ እጅ እንደነበረበት ይነገራል፡፡  የምንሊክ የሥልጣን ሂደት ሁሉ ግን በተቀናቃኞቻቸው ላይ መሠሪ በመሆን አልነበረም፡፡ ይህ በአለፈው ከአነሳሁት አገርን አንድ የማድረግ ጦርነቶች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ምኒልክ ከእሳቸው በፊት ለነበሩት ለዮሐንስም ሆነ ለአሳዳጊያቸው ግን ሊያጠፏቸው ለሚፈልጓቸው ቴዎድሮስ መጥፋት ምክነያት አይደሉም፡፡ እንደውም የቴዎድሮስን ሞት ሌሎች አንደምስራች ሲነግሯቸው እሳቸው የመረረ ሐዘን ውስጥ እንደገቡ ይነገራል፡፡ በቴዎድሮስም ላይ እንዲያምጹ እንግሊዞቹ ሲጎተጉቷቸው የቱንም ያህል ሊያጠፋኝ የሚፈልገኝ ጠላቴ ቢሆንም እጄን በእሱ ላይ አነሳ ዘንድ ከጠላቶቹ ጋር በጠላትነት በአሳዳጊዬ ላይ ለመተባበር አይቻለኝም ያሉ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ለቴዎድሮስ መጥፋት ዮሐንስ ከእንግሊዞቹ  ጋር እንደተባበሩ ይነገራል፡፡ ሆኖም ዮሐንስ በመታልል ነበር እንጂ በአገር ላይ በነበራቸው አመለካከት እንዳለነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ምኒልክ ከዮሐንስ ጋር በነበራቸው ሥልጣን ሽኩቻ አቅሙና የተመቻቹ ሆኔታዎች ቢኖራቸውም ዮሐንስን በማጥፋት ሥልጣን መያዝን አልፈለጉም፡፡  በዚህ ሁሉ ትግስታቸውና በጎ አመለካከታቸው እግዚአብሔር ለእኚህ ሰው ይችን አገር ይገነቧት ዘንድ  ሥልጣንን አሳልፎ እንደሰጣቸው እረዳለሁ፡፡
   
ከዚህ ዘመን ሀኋላ ስናይ የኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግር እንትና እንትናን ገደለ፣ እንትና እንትናት ከስልጣን አወረደ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምኒልክ ወንድ ልጅ ስላልነበራቸው የልጅ ልጃቸው ኢያሱን እንደመረጡ ይነገራል፡፡ ልብ እንበል ኢያሱ ብዙዎች ለመካድ የማይችሉት የምኒልክ አይነት ራዕይ እንደነበራቸው ታሪክ ይናገራል፡፡ ምኒልክ የኢያሱ የጭቅላነት እድሜ እንኳን ሳይከልላቸው ሊተካቸው የሚችለውን ሰው ለመምረጥ ችለው ነበር፡፡  ሆኖም የኢያሱን ልጅነታቸውንና ከልጅነት ጋር የተያያዙ ባሕሪያቸውን እንደምክነያት አድርገው መሠሪዎቹ ኢያሱንና የምኒልክን ራዕይ ለማጥፋት መሴራቸውን ቀጠሉ፡፡ ኢያሱንም በእንጭጩ አስቀሯቸው፡፡ በምትካቸው የምኒልክ ልጅ የሆኑት ዘውዲቱ መጡ፡፡ ዘውዲቱ በአገር የመምራት አቅምና አስተዎሎታቸው ምን ያህል እንደነበር ባላውቅም እሳቸውም ቢሆኑ በሴረኞቹ ጠፉ፡፡ አገሪቷን ለብዙ ዘመን ለመምራት እድል የገጠማቸው ኃ/ሥላሴ ተተኩ፣ እሳቸውም ያው ዕጣ ገጠማቸው፣ በደርግና በንጉሱ መካከል ብዙ ጥሎ ማለፎች ተካሄዱ ደርግ መጣ ሁሉንም ይውደም እያለ አወደመው፡፡ የደርግ መሪ የነበሩት መንግስቱ የሞት ዕጣ ባይገጥማቸውም ሌሎች ብዙ ባለስልጣናት የዛሬውን መንግስት በመሠረቱ ቡድኖች በነው ጠፉ፡፡ አሁንም ይህ ሂደት አላባራም እንደ ቀጠለ ነው፡፡

ከምኒልክና ከልጅ ልጃቸው ኢያሱ በቀር ከዚያ በኋላ በመጡት መሪዎች ሁሉ መሠሪነትና አልፎም በእጃቸው ደም እንዳለ እረዳለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋ አደገኛ ትውልድ ግን የሚባለው ያ የንጉሳውያኑን ስልጣን አስወገድኩ የሚለው ትውልድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እስካሁንም ያ ትውልድ ለዚች አገር የጥፋት ማሕደር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ያ ትውልድ የሕዝብ ሕመም የማይሰማው ጥላቻ የለከፈው ውጤታማነትን ሁልጊዜ ሌላውን ተቀናቃኝ ብሎ የሚያምነውን በማጥፋት ብቻ ጋር የሚያቆራኝ፣ ሐይማኖትና ማንነትን የሚገልጽ ባሕል የሌለው የነወረ ትውልድ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ያ ትውልድ ግን ራሱን የለውጥ ሐዋሪያ እንደሆነ አድርጎ ዛሬም ድረስ ይነግረናል፡፡ አሁንም ብዙ በመርዝ የተለወሱ አስተሳሰቦችን ይመግበናል፡፡ እንግዲህ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት መሪዎችም ሆኑ ተቃዋሚ ነን የሚሉ በተለያዩ አገራትና አገር ቤትም ያሉ ቡድኖች መሪዎች በዋነኝነት የዚያ ትውልድ "በረከቶች" እንደሆኑ እናስተውል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሥልጣንና የግል ፍላጎት ጥማት እንጂ የአገራዊ አላማና ራዕይ ተቀናቃኞች እንዳልሆኑም እንረዳለን፡፡ ስለሆነም የእነሱ ሥልጣናቸውንና የግል ጥማታቸውን የሚያሳካላቸው ከሆነ የቱንም ያህል የሕዝብንና የአገርን ጥፋት የሚያስከትል አካሄድ ትክክል እንደሆነ ያምናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ከላይ በመግቢያነት ያነሳኋቸው ጉዳዮች በዝርዝር ለማስተዋል እንዲረዳን ያቀረብኩበት ምክነያት የግንቦት 7 የሚባለው ቡድን ሰሞኑን ያስነበን "ይድረስ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት" በሚል ያወጣው ጽሑፍ ነው፡፡ ሲጀምር ጽሑፉ ያው እንደተለመደው ኃላፊነት የጎደለውን የጥፋት ዜማ ሊያስነበበን ተፍጨረጨረ እንጂ በበሳል አቀራረብ እንኳን የቀረበ አይደለም፡፡ እርግጥ ጉልበትኝነትና ቂመኝነት እንጂ ማስተዋልና በሳልነት ያ ትውልድ በምለው ብዙም ባሕሪው አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ባለስልጣን ስላቀረበው ሪፖርት ማግዘፍና አቅራቢውን ግለሰብ ባለስልጣን ተራ ስድብ በመሳደብ አገራዊ ራዕይና አላማ ያለው ድርጅት ነኝ የሚል ሕዝብን ለመማረክ መሞከር አለመብሰል ነው፡፡ የከፋው ግን ከራስ ፍላጎትና ጥቅም ባለፈ የአገርና የሕዝብ ጥፋት ጉዳዩ እንዳልሆነ የሚያሳየው የሐገርን መከላከያ ሰራዊት መሳሪያህን በባለስልጣናት ላይ አዙር የሚለው ጥሪው ነው፡፡

በእኔ ግንዛቤ የአገር መከላከያ ሠራዊት የጠበቀ ሥርዓታዊ አወቃቀር፣ የአዛዥና ታዛዥ አስተዳደር በጽኑ የሚከበርበት ተቋም ነው፡፡ ይህ ደግም ለኢትዮጵያ የተለየ ሳይሆን በሁሉም ሀገራት ያለ የተቋሙ መዋቅራዊ ባሕሪ ነው፡፡ የዚያንው ያሕል የዚህ አደረጃጀት ማላላትና አንዱ በአንዱ ላይ ማመጽን የሚፈጥር ክፍተት ከፍተኛ ጥፋትንና ለአገር ውድመት ሳይቀር አደጋን የሚያስከትል ነው፡፡ ይህ ተቋም እጁ ያለው አውዳሚ ግን ጠላትን ለመከላከል ታስበው የተዘጋጁ የጦር መሳሪያዎችን እንጂ ዳቦና ኬክ አይደሉም፡፡ እንጊዲህ እንዲህ ያለው ተቋም አባላት መካከል አለመግባባትና ወደጦርነት የሚያመራ ግጭት ቢፈጠር ውጤቱ ምን እንደሆነ እናስተውል፡፡ ይበልጠውንም ተቋሙን በሚመሩት ላይ ሠራዊቱ ቢያምፅ ማን እየመራው ሊቀሳቀስ እንደሚችል አስቡት! አነሰም በዛም፣ ወደድናቸውም ጠላናቸውም ዛሬ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የሚመሩት ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ አነሰም በዛም፣ ወደድናቸውም ጠላናቸውም አገሪቱንም አየመሩ ያሉት እነዚሁ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ የእነዚህ ባለሥልጣኖች በመልዕክቱ እንደተላለፈው በሠራዊቱ አባላት መጥፋት አገሪቷን ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል ማሰብን አንዴት አለተቻለውም ግንቦት 7 የሚባለው ቡድን ወይም በግልም ከሆን የጽሑፉ አቀራቢ፡፡ መልዕክቱስ እውን ሠራዊቱ እየደረሰበት ስላለው አድልዖና በደል በመቆርቆር ነው ወይስ ዛሬ ባሉት የአገሪቱ ባለስልጣናት ላይ ስላለው ጥላቻና የእራስንም ፍላጎት ለማሳካት በሚል እሳቤ ብቻ  አገርና ሕዝብ ምኔ ነው በሚል ለጥፋት መዘጋጀት፡፡

በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ቀረበ የተባለው ሪፖርት ታይተዋል በተባሉት የቤሕረሰብን ስብጥር የሚያሳዩ የሠራዊት ብዛት በዛው ልክ የሠራዊቱን አመራር ሥብጥር ያሳያል ማለት እንደሆነ ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ እንደ አዲስ ነገር የዚህን ሪፖርት መልዕክትና ግድፈት ማሳየትም አያስፈልገንም፡፡ የሪፖርቱን ግድፈትና ደካማነትስ እንደ ልዩ የገዥው ፓርቲ ማሳያ አድርጎ ማቅረቡ ምን ያህል የበሰለ ነው?  በብዙ ተቋማት የቤሕር ተዋፅዖ አለመመጣጠን እንዳለ እናውቃለን፡፡ መፍትሔ ግን ግደለው ፍለጠው ነው? ወይንስ ሰዎችንም ይሁን ቡድኖችን ወደትክክለኛ አመለካከት ማምጣት? ደግሞስ ማንን ነው የምንገድለው? የማን ወገን ሟች የማን ወገን ገዳይ ነው የሚሆነው?! ሲጀምር እኔ በብሔረሰብ ማንነት አላምንም፡፡ ብዙው ራሱ በፈጠረው ማንነት ሊያምን ይችላል፡፡ እኔ ግን ማንንም የሚወክል ብሔረሰብ የለኝም፡፡ ኢትዮጵያዊነቴ አላነሰኝም፡፡  ወደድኩም ጠላሁም ግን የዚሁ የዘር ማንነት ችግሮች ሰለባ በሆኔ አልቀረም፡፡ መቼም ቢሆን ግን በሌላው ላይ ጥላቻን ለማስተናገድ አእምሮዬ ፍቃደኛ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ለራሳቸው የኑሮ መደላደልና ጥቅም የፈጠሩት የማንነት መመንዘር ሴራ ብዙዎቻችን ተገዥ መሆናችን ሳያንስ እኛው እየረገምን እኛው የዚሁ ሴራ ዋና አዛማች ስንሆን አዝናለሁ፡፡ ትክክለኛው አመለካከት ግን ብዙም የዚያን ያህል የማደንቀው ሰውም ባይሆን ብዙዎች ባሕሪው ነው ሰዎችን ከጥላቻ ይልቅ በፍቅር ለማሸነፍ አቅም ነበረው የተባለው የደቡብ አፍሪካዊው ማንዴላን ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ እኔ የሚገባኝ ምኒልክ ከማንም በላይ የዚህ ባሕሪ ባለቤት ቢሆንም ብዙዎቻችሁ ዘንድ የማታምኑበት ስለሆነ ነው ማንዴላን ማንሳቴ፡፡

እንግዲህ የግንቦት ሰባትም ይሁን ሌላ ቡድን ወይ አባል ጥላቻን እየሰበከ እሱ በተራው ሥልጣን ቢይዝ ለዚያ ዛሬ ጠላቻውን በሚነገረን ሕዝብም ይሁን ግለሰብ ላይ በቀሉ ምን ሊሆን ነው?! የብሔረሰብ ሥም መጥራት ስላልፈለግሁ ነው ግን እርግማን ሆኖብን ፌደራላዊ አወቃቀራችንም፣ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የቡድን ስብስብ (ፓርቲዎች)ም በዘር መሠረት ላይ የተደራጁ ናቸው፡፡ ብዙ ተቃዋሚዎችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በግልጽ ሥማቸውን የዘር ከአደረጉት በተጨማሪ ብሔራዊ ነን የሚሉ የአገሪቱን ሥም በሥማቸው ያስገቡትን ጨምሮ ሌሎች ሥሞችን የመረጡ ቡድኖች ሁሉ ከዚህ ከዘር ልክፍት የጸዱ ለመሆናቸው ምንም ማሳያ የለም፡፡ እናስተውል ብዙዎቹ መሪዎቻቸው የዚያ የብሔር(ዘር) ጥያቄ እመልሳለሁ በሚል ዘረኝነትን የወለደው ትውልድ መሆናቸውንም አንዘንጋ፡፡ ከዚህ ቢተርፉም የዚያው ትውልድ ልዩ መገለጫው በሆነው ውጤታማነትን ለማሳካት ተቀናቃኝህን አጥፋ (Eliminate your competitor) የሚል ፍልስፍና ልክፍት የተጠናወታቸው እንደሆኑ እናስተውል፡፡ እድል ሆኖ የዛሬውም ትውልድ ከእነሱ በቀልን የተማረ እንጂ ምህረትንና ሰብዐዊ ክብርን የተላበሰ ሊሆን አልቻለም፡፡ የጥላቻ በአመረቀዘው አእምሮ ራስወዳድነት በተጠናወተው ሕሊና አገርንና ሕዝብን የሚወክል መሪ ማግኘት አይቻልም፡፡ማንም አገር መምራትን የሚፈልግ ቡድን ወይም ግለሰብ ለሁሉም እኩል የሆን ንጉሳዊ (Royal) ልብ ሊኖረው ይገባል፡፡ በሳልና ከጥላቻ የነጹ አእምሮዎች አሸናፊነታቸው የሰፋ ነው፡፡ ግደለው ፍለጠው አብቅቶ የአንዱ ውድቀት ለሌላው እንደ ስኬት የሚታሰብበት ዘመን አብቅቶ መሠረታዊ የሰብዓዊ ማንነት ተምሳሌት እንሆን ዘንድ አመኛለሁ፡፡ ጥንታዊያኖቹ ክርስቲያን የነበሩት መሪዎች ከሌላ አገር የመጡ በሐይማኖትም የመልክም የማይመሳሰሏቸውን አረብ ሙስሊሞች ሲቀበሉ መሠረታዊ ፍልስፍናቸው ሰው መሆናቸው እንጂ የዘር ወይም የሐይማኖት ማንነታቸው እንደልሆነ እንረዳለን፡፡  ዛሬ በብዙ አለፍንባቸው ዘመናት የተነሱ ወራዳ መሪ ተብዬ ምክነያት በመጣብን ድህነት ምክነያት የሚያደምጠን አጥተን ሌሎች ስለ ስብዕናና መልካም አስተዳደር ሊያስተምሩን ቢሞክሩም አሁንም ቢሆን ከማንም በተሻለ ሰበዓዊነትና መልካም አስተዳደርን ለመፍጠር በሕሎቻችንና የማሕበራዊ ፍልስፊናዎቻችን ጥሩ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ግን እየዘገየን በሄድን ቁጥር ሁሉም ደብዛው ጠፍቶ ማንነቱን ያለወቀ ሌላ ትውልድ እየመጣብን እንደሆነ እሰጋለሁ፡፡ ያ አብዮት አምጥቻለሁ የሚለው ጥላቻን ከብቃት ያልለየው ትውልድ ግን ዝም ይበል እሱ ደም የተለወሰ እጅ አለውና፡፡   

እግዚአብሔር ሆይ የቅርታን የሚያደርግ ለሕዝብና አገር አሳቢ መሪ ስጠን! አሜን!

የታላቋ ቀን ልጅ ሚያዝያ13 2006 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment