Thursday, October 31, 2013

አንድነት ፓርቲ ስለ ብሄርተኝነት ያለውን አቋም ያውቃሉን?


የፓርተው የአምስት አመት ዕቅድና የስትራቴጂ መፅሀፍ የምከተለውን ይላል፡-
በብሄርተኝነት ዙርያ ያለ የተሳሳተ ግንዛቤና እንደምታዎቹ
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆንዋ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር በአገራችን ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ እንደያዘ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ የብሄር ብሄረ ሰብ መብት መከበር በቋንቋ የመናገር መብት ብቻ አይደለም’ በፖለቲካ የመወከልና የመደመጥ፤ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፍ አድልዎን የማጥፋትና ፍትሕንና እኩልነትን የማንገስ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ስስ ጉዳይ በሚገባ ሊያዝ ይገባዋል፡፡
የብሄር ጉዳይ አያያዝን በሚመለከት በአገራችን ሁለት ጫፍ የረገጡ አዝማምያዎች ይታያሉ፡፡ አንዱ ጫፍ ለኢትዮጵያ አንድነት እንጨነቃለን ከሚሉ ግን የብሔር መብትን ለመቀበል ከሚቸገሩ ወገኖች የሚመጣ ሆኖ ጉዳዩን የማሳነስና የማጣጣል ብሎም የብሔር መብት ጥያቄ የሕዝብ መብት ጥያቄ መሆኑን የመካድ ዝንባሌን የሚያጠቃልል ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች የሕዝብና የአገራችን አንኳር ጉዳይ መሆኑን በመቀበል ፈንታ የየብሄሩ ልሂቃን የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ብለው የፈጠሩት ችግር አድርገው ያነብቡታል፡፡ ልሂቃኑ አይለጥጡትም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን የጉዳዩን ክብደትና በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ስፍራ ለማሳነስ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡
ሁለተኛው ጽንፍ የረገጠው አመለካከት የብሔር ብሔረ ሰብ መብትን ለማስጠበቅ እንታገላለን ከሚሉ ወገኖች የሚመጣና የብሄር መብት መከበርን ከአገር አንድነትና አብሮነት ነጥሎ የሚመለከት ዝንባሌ ነው፡፡ ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ ጉዳዩን በማክረር ውጤቱ መገንጠል እንዲሆን የሚፈልጉ አሉ፤ በግልጽ መገንጠልን እንደ ዓላማ ያነገቡም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እኛ ያልነው ካልሆነ በማለት አንድነትን በመያዣነት ያግቱታል (ሆስቴጅ ያደርጉታል)፡፡ ሁሉም የየራሱን መብት እያጠበቀና እያከረረ ከሄደ እያንዳንዱ ብሄረሰብ ከአጠገቡ ካለው ሌላ ብሄረሰብ እየተናከሰ እንደሚኖርና ከአንድነቱ መፍረስ ጋራ ሰላምም እንደሚደፈርስ ያለመገንዘብ ችግር አለባቸው፡፡
ሁለቱም አመለካከቶች በሃሳብ ብቻ ሳይሆን ልዩነታቸው በአደረጃጀትም መልክ ይታያል፡፡ የመጀመርያው ሕብረ ብሄራዊ አደረጃጀት የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሄራዊ ወይም ክልላዊ የአደረጃጀት መልክ ያያዘ ሆኖ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ መስራትና መኖርን የማይቀበሉ ናቸው፡፡
በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በብሄር/ብሔረሰብ መብት ማስከበር ዙርያ ያለውን ልዩነት ማጥፋት አይቻል ይሆናል፡፡ ጫፍ ከረገጡት ሁለቱ አመለካከቶች ወጣ ያለና የአገር አንድነትን እና የብሔርብሄረሰቦች እኩልነትን የሚያረጋግጥ አማካይ መስተጋብር መቅረጽና አብዛኛው ሕዝብ ወደዚህ አስተሳሰብ እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በአደረጃጀትም እንደዚሁ ሕብረ ብሄራዊውና ክልላዊ አደረጃጀቶችን (ያቀናጀ) ያስተሳሰረ አንድ አገር አቀፍ መዋቅር ለመፍጠር መስራት ይገባል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በአንድ ድምጽ የኢህአዴግን አገዛዝ እንዳያስወግድ እንቅፋት እየሆነና ለቀጣይነቱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።
ክልላዊና አካባብያዊውን ገጽታ እንዲሁም አገራዊ ገጽታዎችን ያጣመረ አንድ አገራዊ ስብስብ ወይም ፓርቲ እንዴት ይፈጠራል? ይህንን የሚያንጸባርቅ አደረጃጀትስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥቄዎች መመለስ አንድነት ፓርቲ እንደ አንድ ትልቅ ፖለቲካዊ ተግዳሮት ይመለከተዋል፡፡
ከላይ የተዳሰሱት ሃሳቦች የያንዳንዱን የማህበረሰብ ክፍል የልብ ትርታ የማዳመጥን አስፈላጊነት አጉልተው ያሳያሉ፡፡ እንደዚሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄርብሄርሰቦች የአስተሳሰብ አስኳል ጋር ተቀናጅቶ እንዲሄድ የሚያደርግ ስትራቴጂ የመቀየስ አስፈላጊነትን ያሳያሉ፡፡ ስትራቴጂው የእያንዳንዱን ብሄረሰብ ልዩ ሁኔታ/ስፍራ/ችግር መሰረት ያደረገ ይዘት እንዲኖረው የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

zehabesha

ኢትዮጲያኖች እንደንስር! የንስር አሞራ ዳግም ልደት



gn
ንስር አሞራ ከአዋፋት ዘር ለ70 ዓመት የህወት ዘመን መቆየት የሚችል ነዉ። ንስር አሞራ70 አመት እድሜዉን ለመኖር ወይም ለመጠበቅ በ40ኛ አመቱ ላይ ከፍተኘ መስዋትነት የሚጠይቅ ዉሳኔ ይወስናል። የንስር አሞራ የእግር ጥፍር በአግባቡ መስራት የሚችለዉ ለ40 አመት ብቻ ነዉ።
ንስር አሞራ ከተፈለፈለ ጀምሮ 40 ዓመት ከኖረ በዃላ በሰዉነት ክፍሉ ላይ በሚታየዉ ለዉጥ የተነሳ ፤ የአፍ መንቁሩ፤የእግሩ ጥፍር ና ላባዉ እንደበፊቱ ሊያገለግሉት አይችሉም። የእግሩ ጥፍሩ ደካማ በመሆን አደኑን አይዝለትም ፤ረጅምና ስል መንቁሩ ይታጠፋል ፤ ላባዉ በሰዉነቱ ይለጠፍና ክብደት ስለሚፈጥር ፤እንደልቡ አይበርም ። በዚህ ወቅት ንስር አሞራ ፡ በሁለት ዉሳኔዎች ላይ ይወድቃል ፤ ዝምብሎ በመቀመጥ ሞቱን መጠበቅ ወይም 5 ወር የሚፈጅ ስቃይና መከራ ያለበት መሰዋትነትን በመክፈል ቀሪ 30 አመቱን እንደ ወጣት ንስር መኖር።
ሰላሳ ተጨማሪ ዓመት ለመኖር የአምስት ወር መሰዋትነት መክፈል፤
ንስር አሞራ ቀሪ 30 ዓመቱን ለመቀጠል ከፍተኛ ተራራላይ በመዉጣት ጎጆ ይቀልሳል።ንስር በተራራዉ ላይ ጎጆ ከቀለሰ በዃላ የመጀመርያ ስራዉ የአፉን መንቁር ከአለት ጋር በመፋቅ ነቅሎ መጣል ነዉ ይህም ከፍተኛ ህመምና ስቃይ አለዉ ይሁን እንጂ አዲስ መንቁር ለማዉጣት ይህንን ማድረግ የግድ ነዉ ፤ ከዚያም አዲስ መንቁር ከወጣላት ወይም ከበቀለለት በዃላ በአዲሱ መንቁር የእግሩን አሮጌ ጥፍር ነቅሎ ይጥለዋል ። አዲሱ የእግር ጥፍር ከበቀለለት በዃላ ይህንን አዲስ ጥፍር እንደመሳርያ በመጠቀም በሰዉነቱ የተጣበቀዉን ጥቅጥቅ ያለዉን ላባ ነቃቅሎ ጥሎ አዲስ ላባ እንዲበቅል ያደርጋል። ይህ ህመምና መከራ ያለዉ ድርጊት ነዉ ። ከዚያም የ 5 ወር የማገገሚያ ጊዜ ካጠነቃቀቀ በዃላ እንደገና ራስን የመዉለድ የትግል ሂደት ይጠናቀቅና ፡ተጨማሪ 30 ዓመቱን በሰማይ ላይ እየበረረ ና እያደነ በደስታ ይኖራል።
እኛ ኢትዮጲያኖች እንደንስሩ መሆን ያቅተን ይሆን?
በህወታችን ዉስጥ የምንፈልጋቸዉ ለዉጦች አንዳንድ ግዜ በአስቸጋሪና መራራ ሁኔታዎች ዉስጥ እንድናልፍ ግድ ይሉናል የሰዉ ልጅ በህይወቱ መከራ ሲገጥመዉ ከዚህ አስቸጋሪ ህወት ለመዉጣትና ለመለወጥ ፤ ብሎም ደስተኛ ለመሆን የህይወት ልምዱን መለወጥ ፤አሮጌ ልምዱን ፤ትዝታዎቹን፤ የእለት ተእለት ኑሮዉን አሽቀንጥሮ መጣል ግድ ይለዋል ፤ እነዚህ አሽቀንጥረን የምንጥላቸዉ ነገሮች ግን ለማስወገድ ከፍተኛ መሰዋትነት ይጠበቅብናል ፤ ይህንን መስዋትነት ከከፈልን ልክ እንደንስር አሞራዉ ቀሪህወታችንን በደስታ ልንኖር እንችላለን።
እኛ ኢትዮጲያኖች በአሁን ጊዜ ከመቸዉም ጊዜና ዘመን በከፋ መልኩ በሀገራችንም ሆነ በስደት ተሰቃይተን ተዋርደን የምንኖርበት ዘመን ሆኖ ሳለ ረዥሙን ዘመናችንን ለመኖር ትንሽ መሰዋትነት በመክፈል አሮጌ ልምዳችንንና ትዝታዎቻችንን፤አሽቀንጥሮ መጣል ተቸግረን ፤ የራሳችንን ቀሪ ህወት ብቻ ሳይሆን የዚችህን ለዘመናት በደም መሰዋትነት የኖረች ሀገር እድሜ ለማስቀጠል ፤ተስማምቶና ተባብሮ መስራት አቅቶን ፤ሀገራችን እላይዋላይ በተጣበቁ መዥገሮች ወዳለመኖር እየወረደች እያየን ፤ዝምብለን እንገኛለን አልያም ባላስፈላጊ ነገሮች ላይ አተካሮ ይዘን በአሮጌ ልምዶቻችን ተተብትበን እንገኛለን።
በኢትዮጲያ ታሪክ ዉስጥ በየዘመኑ የነበሩ ገዢዎች ጊዜያቸዉን ጨርሰዉ ሲወገዱ/ሲሄዱ/ አንጻራዊ ጠንካራ ወይም ደካማ ኢትዮጲያን ትተዉ ነዉ የሚሄዱት፤ወይም ኢትዮጲያ የምትባል ሀገር አትጠፋም።አሁን ኢትዮጲያ ባለችበት ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ይህ ይኖራል ወይስ ይቀጥላል? በፍጹም። የወያኔ አገዛዝ በዚህ ከቀጠለ ወይም ጊዜ በጨመረ ቁጥር ተገዶም ሆነ በራሱ ጊዜም ቢሄድ ኢትዮጲያ የምትባል ሀገር ልናገኛት አንችልም ወይም አሁን ያለዉን የኢትዮጲያ ግዛት ማግኘት ዘበት ነዉ የሚሆነዉ።ምክንያቱም የገዥዉ አካል ኢትዮጲያን የማጥፋትና የማፍረስ እቅድ ይዞ የተነሳና ለዚሁም ሀያአራት ሰአት የሚሰራ ሲሆን በአንጻሩ ያለንዉ ደግሞ ፤ኢትዮጲያ ኢትዮጲያ ከማለት ዉጭ መሬት የወረደ ስራ መስራት አቅቶን ሃያሁለት አመት አስቆጥረን በተቃራኒዉ ለጥፋቱ ሃይል ምቹ ሆነናል።
እንደሀገር ካሰብን ጊዜዉ አሁንም አልረፈደም እንደ ንስሩ ከፍ ያለ ተራራላይ እንዉጣ ዝቅ አንበል ከፍባልን ቁጥር ጥሩ እይታ ይኖረናል ጥሩ እይታ ታጋሽ፣አስተዋይ ፣ቻይ ያደርገናል፤ከዛ በዃላ አሮጌ አስተሳሰባችንን ፣የማያስማሙንን፣ እኔ ብቻ የሚለዉን ስሜታችንን ፣የሚያለያዩንን፣ መንቁራችንን ፣ጥፍራችንን ወደዚያ ነቅለን ጥለን ፤ በሚያስማሙንን ፣በሚያቻችሉን ፣እንተካቸዉ። ይህንን ስናደርግ ወያኔን ታሪክ አድርገን ኢትዬጲያን እንታደጋታለን።
ሞት ለወያኔ !
ትንሳኤ ለኢትዮጲያ !
Amha Alemu
Norway
ይገባናል – we deserve !

zehabesha

የተበተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች

ዳኛቸው ቢያድግልኝ
አገር ማለት ሕዝብ ነው ሕዝብም የሰዎች ስብስብ፡፡ መልክዐምድሩና የተፈጥሮ ሀብት ደግሞ የሰዎችን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚቀርጽና ማንነትንም የሚያላብስ ነው። በየመንደሩና አካባቢው ያለው የተለያየ የአኗኗር ሁኔታ የቋንቋና የባህል መስተጋብር ደግሞ ትብብርንና አንድነትን የሚያወርስ እኔነትንና የእኔነትን የሚሰጥ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትም እንደዚያ ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግን በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ያቺ የሰውን ዘር ትልቅ የመሆን ተስፋን የሰነቀች ምንጭ ትደርቅ ዘንድ የራስዋ ልጆች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ በፉክክር ሊያጠፏት ይሽቀዳደማሉ። የቀጨጨ ትውልድና የጫጨ አእምሮ ያለው ዘር ይጠፋ ዘንድ እውነት ነውና ኩራታችንን ተቀምተን አናሳና ሁዋላ ቀርነታችንን ተቀብለን እንድንጠፋ ተፈርዶብን መጥፋትንም ተለማምደን በዚህም ዳር እንቁም በዚያኛው እግር በእግር እየተጠላለፍን እንዘጭ እንዘጭ የምንልም በርካቶች ሆነናል። ከትናነንት በመማር ፈንታ በትናንቱ እያማረርን ቂም አርግዘን ሞት የምናምጥ በየጎጡ የሰፈርንም ብዙ ነን። “ለመጥፋት መጋፋታችን መቆም አለበት! መኖር ይገባናል! እኛ እኮ ምንጮች፤ የሰው ዘር፣ የእህል ዘርና የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች ነን!” ብለን በነበረን ላይ ያለችንን አክለን “የነገን ተስፋ ብሩህ አድርገን ማለፍ የሚገባንና ጮክ ብለን የማሰብ ሃላፊነት ያለብን የኢትዮጵያ ልጆች ነን” የሚል መነሳሳት ያስፈልገናል። ኮሎኒያሊስቶች ባሻቸው ቀጣጥፈው የሰሯቸው አገሮች እንኳን አገር ነን ብለው በሚኮሩበት በዚህ ዘመን የፈረንጅ የእውቀት ቃርሚያ የቀመሱቱ የኛው ልጆች  ኢትዮጵያ የምትባል አገር እኮ አልነበረቺም እያሉን መቃብራችንን ሊያስቆፍሩን ይውተረተራሉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ይሆን? ኢትዮጵያዊነት ለኔ እንዲህ ይገለፃል ወይም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል የሚሰማኝ ስሜት እንዲህ ነው።
“ከኢትዮጵያ አፈር ውሀና አየር የተሰራሁ፣ ማለትም የበላሁት የጠጣሁት፣ የተነፈስኩት አየርና የሞቅሁት ፀሀይ ያለኝን ተክለ ሰውነት እውነት ያደረገ፤ አስተሳሰቤን፣ ወግና ልማዴን ስነልቦናዬን ጭምር ያወረሰኝ፣ ሀሳቤን እግለጽበት ዘንድም አፍ የፈታሁበትን ቋንቋ የሰጠኝ የምንነቴ መገለጫ ነው”
ግን በዚህም አላበቃም ከዚህ በላይ የማንነቴ መገለጫ ትልቅ እውነትም አለና። ኢትዮጵያዊ ነኝ እንድል የሚያደርገኝ ሌላው እውነት ከውልደቴ በሁዋላ የተማርኩት ብቻ ሳይሆን በውርስ የተቀበልኩትምእኔነት ነው እላለሁ። ይህም ውርስ….
ከእናቴና አባቴ እኩል በእኩል በተቀበልኩት ክሮሞዞም ይት ድርና ማግ የተሸመንኩ ‘ጂን’ በሚሉት ዝንጉርጉር የዘርማንዘሮቼ አሻራ  ጥበብ የደመቅሁ አንድም ብዙም ሰው መሆኔም ጭምር ነው። አያቶቼን፣ ቅም አያቶቼን ከዚያም በፊት የነበሩትና የመጀመርያው ለተከታዩ ሲያወርሱት የቆዩት አሻራቸውን ሁሉ መረከቤና የዚያም ነጸብራቅ መሆኔ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።  ከኔ ጋር በአካል ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው ሳላያቸው ሳያዩኝ ግን እነሱን እንድመስል የሚያደርጉኝን መሰረታዊ የሆኑ ባህርያት የተረከብኩበት መገለጫዬ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።”
ስለዚህ እያንዳንዳችን የተሸከምነው ጓዝ ብዛቱ የትየለሌ በመሆኑ ግለሰብም ሕዝብን (ያሉትንና የነበሩትን) ይወክል ዘንድ እውነት ነው።  ዘር ከልጓም ሲሉ፣ የእናት ሆድ ዥጉርጉር ሲሉም ያንን ትልቅ እውነት በሀገራዊ ብሂል የሚገልጹበትና ሳይንሱም ይህንን እውነት የሚመሰክርበት ነው። ለዚህም ነው በሌላ ሀገር ተወልደው፣ የሌላ አገር ማንነትን ይዘው ነገር ግን ምንነታቸውን በሰጣቸው የጂን አሻራ ምክንያት ኢትዮጵያዊ የሚያስብሉ ባህርያትን የሚያንጸባርቁ ወገኖችን የምንመለከተው።
እንዲያም ሆኖ ግን እኔ የተሰራሁበት አፈር፣ ወሀና አየር የኢትዮጵያው ስለሆነ ዛሬ በዐለም ዙርያ በመዞሬ ያካበትኩት እውቀትና ልምድም ተጨምሮበት እንኳን ኢትዮጵያ ከውስጤ ከወጣች ባዶዬን የምቀር ነኝ። መሰረቴ ሀገሬ በመሆንዋ ያለሀገሬ ባዶ ነኝ። ብዙዎች ላይ የሚነበበውና ምትሀታዊ ሀይል የሚመስለው እውነትም ይኸው ነው። ስለዚህ ሀገራችን ከሌለች ሀገርም ከሌለን የኛ መኖር ካለመኖራችን ጋር አንድ ነው። ጎዶሎ ስሜት ያልተሟላ ማንነት ይዞ መንገታገት! በስደት አካላዊ ምቾት እንኳን ቢኖር የተሰበረ ቅስም የመያዛችን ትልቁ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። ለዚህ ነው አገር አልፈረሰችም ሲሉኝ ስብርባሪዎችዋን ተበታትነው እያየሁ እንደምን አልተነካችም ልበል? አገር ሕዝብ ከሆነ ሕዝብ ሲበተን አገር እየፈረሰ ነው ማለት ምን ውሸት አለው? የሚያሰኘኝ።
የኢትዮጵያ ጠላት ኢትዮጵያን ካስተዳደረ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ለሕዝባቸውና ለወገናቸው ማገልገል ተስኗቸው በስደት ለአፍሪካ ሀገሮች፣ አውሮፓና አሜሪካ እውቀታቸውን የሚሰጡ ከሆነ፣ የነገ ሀገር ተረካቢዎች የሆኑ ወጣቶች በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ “በሀገር ተዋርዶ ከመኖር እየሄዱ መሞት” ብለው የሚሰደዱ ከሆነ፤ ወይዛዝርቶች  ወደ አረብ ሀገር ለባርነትና፣ ለግርድና ሲያቀኑ ባዕድ ሀገራት ለም መሬታችን እየተሰጣቸው ሕዝባቸውን ሲመግቡ እንደሞኝ እየተመለከትን እድሜ የምንገፋ ከሆነ አገር ምንም አልሆነች ማለት እንደምን ይቻለናል? እንደ መለስ ዜናዊ “መሬቱ እኮ እዚያው ነው ሱዳኖች መጥተው አረሱት እንጂ” አይነት አባባል እኛም “ኢትዮጵያ እኮ አለች ሕዝብዋ እየተሰደደና እየተፈናቀለ ነው እንጂ …” ብለን በራሳችን ካልቀለድን በቀር እየፈረሰች ያለች አገር ናት።
ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስንደረደር የካፒቴን ተሾመ ተንኮሉን ቃለመጠይቅ ኢሳት ላይ እየተመለከትኩ ነበር። የደረሰበት በደል በጫካ ሕግ ላይ የተመሰረተ የጠላትነትና የማንአለብኝነት ተግባር ነበር። ለማመንም ለመቀበልም እጅግ የሚያዳግት ነው። እስከዛሬው ቀን ድረስ ለተቀበለው ስቃይ ምክንያት ምን እንደሆነ አልተነገረውም። ሀገሩን ማፍቀሩና ማገልገሉ በወያኔ ዘንድ እንደ ከባድ ጥፋት ከመቆጠሩ በስተቀር። ከዚያ በደል ሁሉ በሁዋላ ደግሞ አገርህ ትፈልግሀለች መባሉ ይበልጥ የሚያቆስል ነው። እንደ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ አይነት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ ያስተማረቻቸውና የሀገር መከታ የሆኑት ሁሉ ተሰደው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የተገኘውን ስራ እየሰሩ ተበትነው ይኖራሉ። በሙያቸው እየሰሩ ያሉትም ቢሆኑ ለመኖር እንጂ ሀሴትን ለማግኘት እንዳልታደሉ ይታወቃል። በ42 ፕሮፌሰሮች መባረር የተጀመረው ዘመቻ ዛሬ ከየተቋማቱ አገር ጥለው የሚኮበልሉ ምሁራን ቁጥር ከግምትም በላይ ነው። የመውጫ ቀዳዳ አበጅተው አገሬን የሚለውን በርካታ ወገን ከሀገሩ አስጨንቀው አስወጥተውታል እያስወጡም ነው የምንል ከሆነ በዚያች አገር መኖር የሚችለው መከራን ለመቀበልና ለመጋፈጥም ዝግጁ የሆነና ባርነትን በግዱና ምርጫ በማጣት የተቀበለው ነው ማለት ነው። ባለሀገር ነን ባዮቹና የሀገሪቱን ጸጋ እየተቀራመቱ ያሉት ጥቂት የወያኔ አባላትና ተላላኪዎቻቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም የቆቅ እንቅልፍ የሚተኙና ሀብት የሚያሸሹቱ ይበዙባቸዋል።
ትውልድን የሚያንጽና የሚቀርጽ አካል ከሌለ የሚጠብቀን ለባርነትና ለውርደት የተመቸ ዜጋን መተካት ግድ ይሆናል።ሀገረገዢዎቹ ደግሞ ከነርሱ የተሻለ የሚያስብ እንዲኖር አይሹም እንዲሁ እየተንገታገቱ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘመኑ የሚመጥን እውቀትና ሀብት ይዘው የሚፈነጩበትን አገር እየሰሩ ነው። በቁም መፍረስና መሞት ማለትም ይኸው ነው። በተለያየ የሙያ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ወገኖች በውጭው አለም ከእውቀታቸውና ከልምዳቸው ጋር የማይመጣጠን ስራ ሲሰሩ ማየት ትልቅ የሀገር ሀብት ከንቱ መቅረቱን መመስከር ስለሆነ ያማል። በሙያቸው የሚሰሩትም ቢሆኑ ለሀገርና ለወገን የሚገባውን ማድረግ ካልቻሉ በደሉ ያው ነው። በጥቂት የወያኔ ባለስልጣኖች ባለንብረትነት የሚገነባው ሕንጻ ሽቅብ ሲወጣና ወደ ጎን ሲሰፋ ኢትዮጵያዊነት ግን ቁልቁል ሲሄድና የሃገሪቱም ጠረፍ ወደጎን ሲጠብ ማየትስ ምንኛ አሳዛኝ ነው?
ያለው መንግስት ባመነው መሰረት ብቻ እንኳን በሁለት አመት ውስጥ አራት መቶ ሺህ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ተሰደዋል የሚል ዜና ሰምተናል። ምናልባትም ተመሳሳይ ቁጥር በህጋዊ መንገድ ከሀገር ለቀው ወጥተዋል ይህ ከቶ ምንን ያመለክታል? የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም የሰሃራ በረሃን እያጠጣው ነው፣ የውቅያኖስ አሳዎችን እየቀለበ ነው። በየመን ሞት ነው፣ በሊቢያም ሞት ነው። በኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ ወጣቶች እስርቤቶችን አጨናንቀውታል። የአለም ደቻሳ የጣር ድምጽ ዛሬን ድረስ ይሰማል። በፈላ ውሃ የተቃጠለችው ሸዋዬ ሞላ ምስል አሁንም አለ፤ የሚደርስላት ጠፍቶ አስፋልት ላይ ደሟ የተነዠቀዠቀው ወጣት ምስል በሃሳባችን ወስጥ ትኩስ ሀዘን አስፍሯል። ኤምባሲዎቻችን ሱቅ በደረቴዎችና ሰላዮችን እንጂ ኢትዮጵያን ጉዳዬ የሚሉ ሰዎችን አልያዘም። ወደ ሞታቸው እየተጋፉ መርከብ ወይም ጀልባ የተሳፈሩ ወጣቶች በላምባዱዛ መርገፋቸው አንገት ያስደፋል። በአንድ ዘመን አረቦች በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰደው እየኖሩ የእለት ጉርሳቸውን ያገኙ እንዳልነበር ዛሬ አረቦች በጋጠወጥ ድርጊት ልጆቻቸንን እህቶቻቸንን ሚስቶችንም ጨምሮ እንደ አሻንጉሊት እየተጫወቱባቸው ነው። ቀኑን በስራና በችጋር ለሊቱን በመደፈር እያሳለፉት መጨረሻቸው እብደትና ሞት ሆኗል። በዚህ አይነት መከራ የሚመጣ ገንዘብን የሚጠብቁ ተጧሪዎች ደግሞ ልጆቻቸውንህቶቻቸውን ወንደሞቻቸውን እና ሚስቶቻቸውን ለዚህ መከራ አሳልፈው ከሰጡ በርህራሄና በመተሳሰብ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት አብቅቶለታል።  መከታነት አጋርነትም በችጋር ምክንያት ተሟጥጦ ሄዷል፣ ክብርም እንዲሁ። ወጣቶቻችን እንደ ባርያ እየተሸጡ ነው፣ የኛው ጉዶችም ባርያ ፈንጋይና ደላሎች ሆነው ወገኖቻቸውን  ያሻሽጣሉ። እንዲህ ከዘቀጥን እውነት ኢተዮጵያ የምንላት ሀገር አልፈረሰችምን? በትክክል እየፈረሰች ነው የሚያሰኘኝ የተበታተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች በመላው አለም መበተናቸውን መመስከሬና አንዱም እኔው መሆኔ ነው።
ወድቀናል መነሳት ግን ይቻለናል። ፈርሰናል መልሰን የመጠገን አቅም ግን አለን። ስለዚህ በዚህች በምንወዳት አገራችን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ከየተበተንበት ጉድባ ከየወዳደቅንበት ቀዬ ደልቶን ከምንኖርበት የሰው አገርም ቢሆን ቀና ብለን ተስፋችንን ልናለመልም ቃልኪዳናችን ልናድስ ይገባል። ሀገር የሌለው፣ መሸሻ፣ ማኩረፊያና ማረፊያ የሌለው ሰው ያበቃለት ነው። የተቀበልነው ፓስፖርትና የያዝነው ዜግነት አገሮች በመልካም ፈቃድ የሰጡንን ባልፈቀዱ ጊዜም የሚነጥቁን መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ባይነጥቁንም ሁለተኛ ዜጎች ጥገኞችም ነን።
በኢትዮጵያ ተስፋ እንዳንቆርጥ ማንነታችንን አሽቀንጥረን እንዳንጥል የሚያደርጉ ክስተቶች ስንመለከት ደግሞ ታላቅ  ብርሃን ይሆንልናል። ኢትዮጵያችንን በዚያም በዚህም ቢቀጠቅጧትና እያንዳንዱ ሰው ሀገሩን እንዲጠላ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በቀን በቀን ቢገጥሙት፣ ምርር ብሎት በሰሃራ በረሃም ቢያቋርጥ፣ በኬንያ ቢፈተለክ በሱዳን ቢያቀጥን በቦሌም ቢከንፍ ሃሳቡ አረፍ ሲልለት ኢትዮጵያዊነቱ ይነግስበታል፤ በረሃውን ሲያቋርጥ ድህነት ቢያሸማቅቀውም እንኳን ኢትዮጵያዊ ኩራቱን ይዞ ቀን እስኪያልፍ እያለ የጭለማውን ጊዜ ይገፋዋል። ሰው እንጂ ሀገር አይሞትም የሚል የተስፋ ደወል አድማስ እየሰነጠቀ ግም ድው ኳ ሲል ይሰማዋል። ሰለዚህም ነው ባንዲራውን ሲያሳንሱበት ለብሶት፣ ቆብ አድርጎት፣ የአንገት ልብስ አሰርቶት ጉንጭና ሌላም የሰውነት ክፍሉን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀብቶት አደባባዩን የሚያደምቀው። ሀውልቱን ሲያፈርሱበት ታሪኩን አስውቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ መጽሃፍ አድርጎ ያወጣዋል። በሃይማኖቱ ሊያናክሱት ሲፈልጉ ተቃቅፎ ይሳሳማል። ይህን ስሜት እንደ ምርኩዝ ይዞ ኢትዮጵያን ማዳን ይቻለናል። መንደርደርያና ማኮብኮብያውን ግብ አድርገው ነገር የሚወናጨፉቱ ይህንን ታላቅ ነገርም ሊገነዘቡ ይገባል። የምቾት ፖለቲካ ለማሻመድ ጊዜው የለንም፣ አገር የማዳን ጥድፊያ እንጂ የምርጫና የድምጽ ብልጫ ጊዜ ላይ አይደለንምና ቀዳሚውን ቀዳማይ ዓላማ አድርገን እንጀግን። ወደ ድል ለሚወስደው ጎዳና መንገድ ጠራጊ እንሁን ያም ቢያቅተን እንቅፋት መሆናችን ይብቃ በማለት ኢትዮጵያችን በነጻነት ለዘለዐለም ትኖርልን ዘንድ ጀግነው የተነሱትን እናበረታታ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን!

ecadef

ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ


(ገለታዉ ዘለቀ)
reinventing
መግቢያ
የዛሬው የመወያያ ሃሳብ ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ መዋቅር በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ መዋቅር ኢትዮጵያን ወደ ኣዲስ ኪዳን የሚጋብዝ ነው። ኢትዮጵያ የገጠማት የከፋ ችግር በኣብዛኛው ከታችኛው የማህበራዊ ፖለቲካ (socio politics) መዋቅር ጋር የተገናኘ በመሆኑ በዚህ ላይ ኣማራጭ ሃሳብ ማምጣት በተለይ ይህ የኣሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ይመስላል። ያለፉትን ችግሮች ኣስር ጊዜ እያወጣን ብናወርዳቸው ድካም ብቻ ይሆንብናልና።
በተለምዶ ያ ትውልድ እያልን የምንጠራው ቀዳሚው ትውልድ ኣንድ የሆነ ሼል ሰብሮ የወጣ ነበር። ያ ትውልድ ለዘመናት የነበረውን ዘውዳዊ ኣገዛዝ ደፍሮ የጠየቀ፣ የፍትህና የእኩልነትን ጥያቄዎች ኣንግቦ ግንባሩን ለጥይት የሰጠ በመሆኑ ታሪክ ሁልጊዜም ያ ትውልድ….እያለ ሲያስታውሰው እንዲሁ ይኖራል።
ያ ትውልድ የሆነ ሼል ሰብሮ ሲወጣ ፍትህና እኩልነት እንደ እንጀራና ውሃ ለሰው ልጅ ያስፈልጋሉ ብሎ ያመነ እንደነበር መረዳት እንችላለን። ያ ትውልድ ለበሩለት ለነዚህ ቁልፍ ጉዳዩች ታላቅ ንቅናቄን ኣድርጓል። ይሁን እንጂ ፍትህና እኩልነት የሚበየኑበት ወይም መሬት ላይ ወርደው የሚከፋፈሉበት ሜካኒዝም በሚገባ ማጤን ተገቢ ነበረና ያ ትውልድ  ይህን ሃላፊነትም ተሸክሞ ነበር። የዘውዳዊው ኣገዛዝ ማክተሙ ብቻ ሳይሆን ፍትህ እንዴት በኢትዮጵያ ሁኔታ ይበየናል? የሚለው ጉዳይ ታላቅ የቤት ስራ ነበር።
የታሪክ ኣጋጣሚ ሆነና በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ ኢትዮጵያን ተጭኖ ስለነበር ፍትህና እኩልነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩበትን ወይም የሚተረጎሙበትን መነጽር በወጣቶች ላይ ኣደረገ። ንጹህ ኣይምሮ ይዘው ፍትህና  እኩልነትን ያነሱ ወጣቶች የፍትህና የእኩልነትን ትርጓሜ ሶሻሊዝም ባጠለቀላቸው መነጽር ማየት ጀመሩ። ሳይንሳዊ መሆኑ ብዙ ልባቸውን የማረካቸው ወጣቶች ፍትህን እና አኩልነትን በወል የማየትና የመተርጎም ኣስተሳሰብ ሰረጻቸው። ከፍ ሲል እንዳልነው ኣማራጭ የኣስተሳሰብ ዘየ ባለማየሉ እነዚህን ጥያቄዎቻቸውን በነሲብ እንዲያዩ ስላደረጋቸው ይህ ዝንባሌ በተፈጥሮ በቋንቋና ባህል ተቦድኖ ባለው ቡድን ላይ የፖለቲካ ኣይናቸው እንዲያርፍ ኣቀብሎ ሰጣቸው። ችግሩን የስርዓት ኣድርጎ ከማየት በላይ የብሄር ጥያቄ በማንሳት ፍትህ በኢትዮጵያ የሚበየንልን ብሄሮች እኩል ሲሆኑ ነው የሚል ኣስተሳሰብ በሃይል ሰረጸ።
ዋላልኝ መኮንን በኖቬምበር  17, 1969  የሁሉን ስሜት የነካ “On the Question of Nationalities in Ethiopia” የተሰኘ ኣርቲክል ጽፎ በ ስትራግል መጽሄት ላይ  ኣሳተመ። ዋለልኝ ለውይይት ብሎ ያነሳው የመወያያ ሃሳብ በሁለት ዋና ዋና ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን ኣንደኛው ኢትዮጵያ ከማህበራዊ (Sociological) ቅርጿ ኣንጻር እውነተኛ መልኳን ኣናይም የሚል የባህልና የቋንቋ ተዋጽኦን የሚመለከት ሲሆን ይህንን መልኳን ዋለልኝ “ፌክ” ነው ብሏል። በዚህ ረገድ ያነሳው የውይይት ሃሳብ እውነት ያለው ሲሆን እንዴት ግን  ሚዛናዊ የሆነ የባህል ዝውውር ሊፈጠር ይችላል? ለሚለው ተግባራዊ ጥያቄ በዚያን ጊዜም ውይይት የተደረገበት ኣይመስልም እስካሁንም የጠራ ዘዴ ኣልተፈጠርም።
ዛሬ በምንሰጠው ኣሳብ ዋለልኝ የናፈቀውን የኢትዮጵያን እውነተኛ መልክ ሊያሳይ የሚችል ቅርጽ ለውይይት ለማቅረብ እንሞክራለን። ከዚያ በፊት ግን ሁለተኛውን የዋለልኝን የመወያያ ሃሳብ እንመልከት። ሁሉተኛውና በጣም ከባድ ሆኖ የመጣው ጥያቄ የብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ተሳትፎ ይኑራቸው የሚለው የፖለቲካ ጥያቄ ነበር። ከፍ ሲል እንዳልነው የጸዳውን ኣይምሮ ገና ብቅ ሲል የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ ቀልሞ ይዞት ነበርና የኢትዮጵያ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ በቡድን እኩልነት ጥያቄ ላይ ነው ቤቱን የሰራው።ፍትህና እኩልነት የሚሰፈሩትም በዚሁ በቡድን ቁና እንደነበር መረዳት ይቻላል። በመሰረቱ ግን ቡድኖች ኣልነበሩም የተጎዳዱት። የሆነ ስርዓት ነው የሃገሪቱን ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ኢፍትሃዊ እንዲሆን ያደረገው።
ዋለልኝ በጻፈው ኣርቲክል ላይ ኢትዮጵያዊ ለመባል ኣማርኛ መናገር፣ በኣማራ ስም መጠራት፣  ያስፈልጋል… ብሎ ኣጥብቆ ይኮንናል። የሚገርመው ግን ራሱ ዋለልኝ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበረው የወሎ ዘየ መሳቂያ ሆኖ በግቢው ውስጥ ኣማርኛ መናገር ኣቁሞ በእንግሊዝኛ መናገር ጀምሮ ነበር። በቀየው ኣማርኛ ይሸማቀቅ ያፍርና መግቢያ ያጣ ነበር ማለት ነው። ዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ኦሮሞዎች ወይም ወላይታዎች የራሳቸውን ቋንቋ ሲነጋገሩ ከሚሰማቸው በላይ እሱ በወሎው ዘየ ተጠቅቶ ስለነበር ኣማርኛ መናገር ኣቁሞ እንደነበር ኣብረውት የነበሩ ሲመሰክሩ ስምተናል። ራሱ ከኣማርኛ ተናጋሪም ሆኖ ነጻነት ያስፈልገው ነበር ማለት ነው። ከጎጃም ከመንዝ የመጡ በስሞቻቸው ኣዲስ ኣበባ ላይ ይሸማቀቁ ነበር። ኣሁንም ይህ ነገር ኣለ። በርግጥ ይህ ችግር የመጣው የፖለቲካው ችግር ብቻ ሳይሆን በገጠሩና በከተማው መካከል እያደር እየሰፋ የመጣው ምጣኔ ሃብታዊ ልዩነት የፈጠረው ልዩነትና በኋላቀርነትና በሞደርናይዜሽን መካከል ያለ ሽሙጥም ሊሆን ይችላል።
ከቡድን እይታ ወጥተን ፍትህና እኩልነት በግለሰቦች ደረጃ የሚበየንበትን ስርዓት በመፍጠር ላይ ነበር ውይይት የሚያስፈልገው።ያ ማለት የቡድን ጥያቄ ዳዋ ይብላው ማለት ኣይደለም። እሱም ቅርጹን ጠብቆ ሊፈታ ይገባዋል።እንደ ኣጠቃላይ እንደ ሃገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውና ያለው ችግር የቡድኖች መጎዳዳት ሳይሆን የስርዓት ነው። ኢትዮጵያ የኣንድ ብሄር ኣገር ማለትም የኣማራው ብቻ ብትሆን ኖሮም ያን የዘውድ ኣገዛዝ ተቃውሞ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ኣይቀርም ነበር እኮ።መሬት ላይ ያለውን ነገር ብናይ ኣንድን ሃጎስ ኪሮስ የሚባል የትግራይ ገበሬ፣ ኣንድን በርሶማ ገለታ የተባለ የኦሮሞ ገበሬ፣ ኣንድን ኣበበ ስንሻው የተባለ የኣማራ ገበሬና ሌሎችም ገሬዎች ብናይ የሚኖሩበት ቤት፣ ለስልጣኔ ያላቸው መጋለጥ፣ የኢኮኖሚ ህይወታቸው ሁሉ እጅግ ተቀራራቢ ነው። ስለ ገበሬው  የምናወራው ኢትዮጵያ ስንል ሰማኒያ ፐርሰንት በላይ ገበሬ በመሆኑ ኣጠቃላይ ቁመናዋን ስለሚያሳይ ነው። ይህን ያመጣነው ኢፍትሃዊነቱ ያለው በተወሰኑ የስርዓቱ ኣራማጆች ኣካባቢ በመሆኑ የፍትሁ ጥያቄ በግለሰቦች ዘንድ እንዲበየን ሆኖ በሌላ በኩል የባህል ፍስሰት ሚዛናዊ የሚያደርግ ስርዓት መቀርጽ ያሻል ያ ነው መፍትሄው ለማለት ነው።።  በርግጥ ያ ትውልድ የቻለውን ሰርቷል። ከዚህ በሁዋላ ተተኪው ትውልድ ደግሞ ኣይምሮው ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን ፈጥሮ ሊመራ ይገባዋል። ምን ኣይነት ኢትዮጵያን ነው የምፈልገው?  ብሎ በኣይምሮው መሳል ኣለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ድቡልቡል የሆኑ የዴሞክራሲና የእኩልነት ኣንቀጾችን ብቻ ሳይሆን ካለፉት የውህደትና የልዩነት ማህበራዊ ቅርጾች የተለየ ኣዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ ስርዓት ነድፈው ሊታገሉ ይገባል።
ከፍ ሲል እንዳልነው ዋለልኝ ብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ተሳትፎ ያሻቸዋል ብሎ ነበር። ግን እንዴት ነው ብሄሮች እኩል ተሳትፎ የሚያደርጉት?  በተግባር መሬት ላይ ኣሳዩን ቢባል ኣስቸጋሪ ሁኔት ይመጣል። በመጀመሪያ ደረጃ እኩል ማለት እኩል ቁመት በሌላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች ሁኔታ (context) ምን ማለት እንደሆነ መተርጎም ኣለበት።እኩል የሚለው ነገር በቡድን ታጅሎ ስለመጣ ነው ለማስተናገድ የሚያስቸግረው። ብሄሮች ሁሉ እኩል ይሳተፉ የሚለው ኣረፍተ ነገር ጠቅላላ እውነት ያለው ስለሚመስል ልብ ያማልላል። ነገር ግን በኢትዮጵያ የብሄሮች ተፈጥሮ ኣንጻር እኩል በስቴት ዙሪያ እንዴት ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል የሚለውን በጥልቀት መወያያት ያስፈልጋል። የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ መጀመሪያ የተጫነው ወገን እኩልነትን ለመበየን ቀመር (formula) ሲያወጣ በብሄሮች ቁጥር ሊያደርገው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ይሳተፉ የሚለው ጠቅላላ እውነት እንደተድቦለቦለ ጥሩ ቢመስለንም ይህንን ለመበየን ከሚያስቸግርበት ኣንዱ ነገር ብሄሮች በቁጥር ቁመታቸው እጅግ ስለሚለያዩ ነው። ከሺህ እስከ ሚሊዩን ይለያያሉ። ሶሻሊስታዊ በሆነ እይታ ምን ኣልባት በቁጥራቸው ወይም በቁመታቸው ልክ ለፌደራል መንግስት ሰው ያዋጡ ከተባለ ብዙ ኣባል ያለው ብዙ ያዋጣ ትንሽ ያለው ትንሸ ያዋጣል ብንል በቃ ፍትህ ተበየነ ማለት ነው? ያ ብዙ ያለው በዚህ ስርዓት መሰረት ዋና ዋና ስልጣኖችን ይይዛል በጣም ትንሽ ቁጥር ያለው ደሞ ኣንድም ሚንስቴር ላያይ ይችላል። በዚህ ታዲያ ፍትህ ተሰራ ማለት ነው ወይ?   እኩል ተሳትፎ ማለትስ ምን ማለት ነው?  ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች በቁጥራቸው ኣስር ኣስር ሚሊዮን ቢሆኑ እኩል እኩል ሰው ኣዋጥተው በተራ በተራ ጠቅላይ ሚንስተር ወይም ፕሬዚዳንት እየሆኑ ይኖሩ ነበር። ይህ በተግባር ኣይገጥምም ቢሆንም በዚህ ፍትህ ወረደ ማለትም ኣይደለም። በመሆኑም የዚህ የፖለቲካ ውክልና ጉዳይ ከቡድነኝነት ወይም ዘመናዊ በሆነ ኣገላለጽ ከማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) ኣስተሳሰብ ሲመነጭ ብዙ ያልጠሩ ችግሮች ይገጥማሉ።
ያ ትውልድ ጥሩ ጥያቄዎችን ኣንስቶልናል። ያንን መሰረት ኣድርጎ የዛሬው ትውልድ በጥልቀት ተወያይቶ ኣዲስ ስርዓት መፍጠር ኣለበት ያልነው እንዲህ ያልጠሩ ጉዳዮች ስላሉ ነው። ፍትህ እኩልነት በብሄሮች ቁመት ወይም የተፈጥሮ ሃብት የተለያዩ ህዝቦች ባሉበት እንዴት ሊበየን እንደሚችል መላ ማለት ወቅታዊ ጉዳይ ሆኑዋል። ወያኔ የዋለልኝን ጥያቄዎች ለማየት በቂ ኣመታት ያሳለፈ ቢሆንም መጀመሪያ ከሰረጸው የግራ ዘመም ኣስተሳሰብ መረብ (trap) ለመውጣት ባለመቻሉ የብሄር ፌደራሊዝምን ተግባራዊ ኣደረገ።
ዋለልኝ የባህል የበላይነት መኖር ሁል ጊዜ የኢኮኖሚ የበላይነትን ያመጣል ብሎ የሚያምን ሲሆን ይህን ኣሳቡን ዛሬ ደርሶ ቢሆን ይቀይረው ነበር። ዛሬ ወያኔ ለባህል የበላይነት ፈጽሞ ደንታ የለውም። የትግራይ ቋንቋ ወይም ባህል በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ በባህልና ቋንቋ የበላይ ለመሆን ኣይሰራም። ነገር ግን ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በጥቂት ከኣንድ ቡድን በመጡ ሰዎች ተቆጣጥሮታል።ድሮ ኣማራ ወይም ትግራይ ያልሆኑ ከፍተኛ መኮንኖች ጥቂት ናቸው ይላል ዋለልኝ ዛሬ የብሄር ፌደራሊዝም ተመስርቶ የጦር ኣመራሩ ከፍተኛ መኮንኖች ሰባቱም ከትግራይ የተወለዱ ናቸው።
የብሄር ፌደራሊዝም ለቡድኖች ፍትህም ቢሆን ዋስትና ኣይሆንም። የባህል የበላይነት ሳይኖርም የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይ ሆኖ ገዢ መሆን ይቻላል።ፍትህ ኣልተበየነም። ኣንዳንዶች የብሄር ፌደራሊዝም በራሱ መጥፎ ኣይደለም ወያኔ ነው ያጠፋው ይላሉ። ይሁን እንጂ ለስቴት እኩል ተሳትፎ ቀመር መስራት ኣይችሉም። ከፍ ሲል እንዳልነው በቁመት ካረጉት ፍትህ በዚያ ኣይበየንም። ኣንስተኛ የሆነ ኣባል ያላቸውን ተስፋ ያስቆርጣል።
ኣንድ በጣም ኢንተረስቲንግ የሆነ ነገር ላጫውታችሁ። ምያንማር ወይም በርማ የምትባል ደቡብ ምስራቅ እስያ ውስጥ የምትገኝ ኣንድ ኣገር ኣለች። በዚህች ኣገር ኣንዳንዶች እንደሚሉት 135 ብሄሮች ኣሉ። ከነዚህ ውስጥ ኣንዱ ባርማ የሚባለው በጣም ብዙ ኣባላት ያሉት ሲሆን 68 በመቶ የሚሆነውን ሽፋን ይይዛል። ሌሎች ከመቶ በላይ የሆኑት የቀረችውን እጅ ተከፋፍለው ያሉ ሲሆን ኣንዳንዶቹ በጣም ትንሽ ኣባላት ነው ያላቸው። እነዚህ በጣም ኣነስተኛ ኣባል ያላቸው ኣንድ ጊዜ በተደረገ ጥናት መሰረት በብሄራቸው ራሳቸውን ሲገልጹ ምቾት ኣይሰማቸውም። በዚህ በብሄር ዙሪያም ብዙ ሲወራ ይሰጋሉ።  ለነሱ የሚመቻቸውና ደስ የሚላቸው በብሄራዊ ማንነታቸው ሲጠሩ ወይም በርሚስ ሲባሉ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ምን ኣልባት የሃገራቸው የፖለቲካ ጨዋታ በብሄር ቁመት ከሆነ እኛ ምን ይውጠናል ተወዳድረን መቆም ኣንችልም ከሚል ስጋት ይመስላል። በጣም ያሳዝናሉ። ከዚህ ስጋት የሚያሳርፋቸውን ጥበብ ይሻሉ።
ዋናው የኛ ምሳሌ ምንድን ነው በሃገራችን ኢትዮጵያም በብሄር ቁመት ፍትህ ስለማይበየን ጨዋታው ሁሉን ነጻ ሊያወጣ በሚችል መንገድ ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን በተለያየ ኣቅጣጫ ሊንከባከብ የሚችል ስርዓት በግድ መውለድ ኣለብን።
ቀጥሎ ያነሳነው ኣሳብ ከዚህ በፊት በእንግሊዝኛ ለየት ባለ መንገድ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ኣንዳንድ ወገኖች በኣማርኛ እንዲቀርብ በሰጡን ኣስተያየት መሰረት በኣማርኛ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን የማህበራዊ ፖለቲካ (Socio Politics) ጉዞ ስናይ  ሚዛን ከጎደለው ውህደት (assimilation) ወደ ልዩነት(Ethnic federalism) የመጣ ሲሆን በነዚህ በሁለቱም ስርዓቶች ኢትዮጵያ ስላጉረመረመችኣዲስ ኪዳን ልንገባ ይገባናልና ኑ እንግባ የሚል ግብዣ ነው።ከሁሉም በላይ ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ወይም ብሄራዊ ማንነትን(National Identity) ለያይተን እንድንንከባከብ የሚመክር ኣሳብም ያዘለ ነው።
ክፍልአንድ
የአዲሱ መዋቅር ስያሜ
ይህ አዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ መዋቅር በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ኣንድነት (conventional cultural unity- CCU) የተሰኘ ንደፈ ሃሳብ ነዉ፡፡ ይህ ንደፈ ሃሳብ የኢትዮጵያን ብሄሮች ወይም ባህላዊ ቡድኖች ወደ አንድ አዲስ ኪዳን የሚጋብዝ ሃሳብ ነዉ፡፡
ክፍል ሁለት
የአዲሱ መዋቅር ወይም የቡድኖች ኪዳን ዓላማዎች (purposes) የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
1ኛ. ኢትዮጵያ ያሏትን የበለጸጉ ባህሎች በከፍተኛ ሁኔታ ለመጠቀም እና ሚዛናዊ
የሆነ የባህል ዝዉዉር ለማድረግ፣ማንበራዊ እድገቷን ለማፈጠን::
2ኛ. ባለፉት ሁለት ስርዓቶች ልባቸዉ የቆሰለባቸዉን ወገኖች ለመፈወስና አጠቃላይ
በዜጎች ዘንድ የህሊና ጽዳት ለማምጣት፣
3ኛ.  በልዩነት (በብሄር ፖለቲካ) ምክንያት የመጣዉን የማህበራዊ ኢኮኖሚና
የፍትሃዊ  እድገት ችግሮችና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት፣
4ኛ.  አንድነትን ለማጠናከር ናቸዉ፡፡
ክፍል ሶስት
የንድፈ ሃሳቡ ዳራ
በሰዉ ልጆች የማህበራዊ እድገት ታሪክ ዉስጥ የታየዉ ነገር አገር ሲመሰረት በአብዘኛዉ በጦርነት መሆኑ ነዉ፡፡ በጥንት ጊዜ ቡድኖች በኮሚኒኬሽን ችግር እና በነበራቸዉ ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና ምክንያት በተፈጠሩበት መልከኣ ምድር ተወስነዉ ይኖሩ ነበር፡፡ ቀስ እያለ የሰዉ ልጆች ንቃተ ህሊና ሲጨምር አካባቢያቸዉን ማሰስ (explore ማድረግ) ሲጀምሩ ቡድኖች ከሌሎች ቡድኖች ጋር መተያየትና መገናኘት ጀመሩ፡፡ ቀስ እያለም ግዛት የማስፋፋት ስሜት እያየለ በመምጣቱ ሃይለኛዉ ቡድን ደከም ያለዉን እየወረረ ግዛት የማስፋፋት ስራ ተጀመረ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ አለማቀፋዊ ይዘት ያለዉ ሲሆን እጅግ ብዙ ሃገሮች ዛሬ የምናያቸዉ ብዙህ (plural) አገሮች ሁሉ በዚህ ሁኔታ ተመስርተዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ጊዜ ሀይለኛዉ ቡድን ሌሎቹን ቡድኖች እየተጫናቸዉ ስለሚሄድ ባህላቸዉንና ቋንቋቸዉን ያለ ዉዴታ በግዴታ እንዲጥሉ የተደረጉበት ሁኔታ በሰፊዉ ታይቷል፡፡ በዓለም ላይ የታየዉ ይህ ክስተት የጭካኔ ደረጃ እንደየ ሀገሩ የተለያየ ነዉ፡፡ ሃገሮች በሚመሰረቱበት ጊዜ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ቋንቋ በሚናገሩ ህዝቦች መካከል በተለያዩ የግዛት አስተዳዳሪዎች መካከልም ዉጊያ ተካሂዷል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረዉ የሰዉ ልጆች የመረዳት ደረጃ መሰረት ሰፊ መሬት መያዝና ብዙ የሰዉ ሃይል መኖር የመንግስት ጥንካሬና ሃያልነት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር ነዉ፡፡ በዚህ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ጊዜ በኣንዳንድ ኣገሮች በከፍተኛ ሁኔታ በሃይል የሚደረግ የባህል ዉህደት (forceful cultural assimilation) ተካሂዷል፡፡ ሃሳባችንን በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ በጉልበት የሚደረግን የባህል ዉህደት በሁለት አቅጣጫ በምሳሌ አስደግፈን እንመልከት፡፡
1ኛ. በአንድ ሃገር ዉስጥ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የተደረገ ዉህደት (Intra forceful assimilation)
ይህ አይነት የባህል ዉህደት የታየዉ የተለያዩ ብሄሮች ባሉባቸዉ የአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል ሲሆን፣ ለምሳሌ በ1930 ዓ.ም. የቱርክ መንግስት በገሃድ የዉህደት ፖሊሲ አዉጥቶ ኩርዶች በግድ እንዲዋሃዱ ተገደዉ ነበር፡፡ በዚህ ገሃድ በሆነ አስገዳጅ ፖሊሲ ምክንያት የኩርድ ሰዎች በግድ አንዋሃድም ባህላችንን አንጥልም በማለት ትግል አድርገዋል፡፡ የቡልጋሪያ መንግስት ደግሞ ከ1984-1989 ድረስ በቱርክ ቡልጋሪያዊያን ላይ እንዲሁ በግድ እንዲዋሃዱ ተጽዕኖ የተደረገባቸዉ ሲሆን የቡልጋሪያ መንግስት በቱርክ ቡልጋሪያዊያን ላይ የዉህደት (assimilation) ዘመቻ (campaign) አድርጓል፡፡ የቱርክ ቡልጋሪያዊንን ዜጎች የቤተሰብ ስማቸዉን (family name) እየቀየሩ በቡልጋሪያዊያን የቤተሰብ ስም እንዲጠሩ ተገደዋል፡፡ መንግስት ራሱ ስማቸዉን እየቀየረ መታወቂያ ያዘጋጅ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡
የቀድሞዉ የዮጎዝላቪያ ሞቆዶንያ ሪፐብሊክ ባህል ከአልባናዊያን ወደ እነሱ እንዳይፈስ ለመከላከል ፖሊሲ አዉጥተዉ ነበር፡፡ ፖሊሲዉ የአልባናዊያንን ባህል ለማቋረጥ የታቀዳም ይመስላል፡፡
2ኛ. አገር አቋረጭ የሆነ የዉህደት ዓይነት (Inter forceful assimilation)
ይህ ዓይነቱ ጉልበት የተሞላበት የባህል ዉህደት ደግሞ በቅኝ ግዛቱ ዘመን ታይቶ የነበረ ነዉ፡፡ ገዥዎች ቅኝ የገዟቸዉን ህዝቦች ለማስተዳደርና ለረጅም ጊዜ ለመግዛት ይጠቅመናል ብለዉ የተጠቀሙበት ኣንዱ ስልት በግድ የሆነ የባህልና የቋንቋ ዉህደት በመፈጽም ነበር፡፡ ይህ ድርጊት እንደየ ሀገሩ የተለያየ ግዝፈት (degree) የነበረዉ ሲሆን ከዓለም ታሪክ ጥቂት ምሳሌዎችን እናንሳ፡፡
የኮሪያዊያንን ታሪክ ስናይ ከ1910 – 1945 ድረስ በጃፓኖች ቅኝ ተገዝተዉ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ቅኝ ገዥ ጃፓኖች ኮሪያዊያንን በቢሮ ቋንቋ ጊዜ ቋንቋቸዉን እንዳይጠቀሙ ጃፓንኛ እንዲጠቀሙ ተገደዉ ነበር፡፡ የኮሪያዊያንን ፊደልና ታሪክ ለማጥፋት ብዙ ጥረዋል፡፡ ኮርያዊያን ስማቸዉን እንዲቀይሩ ይገደዱም ነበር፡፡
አየርላንድና ካሪቢያኖችም እንዲሁ በቅኝ ገዥዎቻቸዉ ተጽዕኖ የደረሰባቸዉ ሲሆን አየርላንዶች ዛሬ ዋና ቋንቋቸዉ የቅኝ ገዥዎቻቸዉ የእንግሊዞች ቋንቋ እንግሊዘኛ ሆኗል፡፡
በ19ኛዉና 20ኛዉ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ ቅኝ የተገዙ ሀገራትም እንደዚሁ ፈረንሳይ ባወጣቻቸዉ የዉህደት ፖሊሲዎች ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል፡፡ የምዕራቡ ሃገራት በተለይም ሴኔጋል ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች፡፡ በብዙ ሃገራት በቅኝ ግዛት ጊዜ ይህ የዉህደት ተግባር በሰፊዉ ተፈጽሞ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አንድ ሀገር በመሰረቱ ብዙ ቡድኖች መካከልም ይሁን ባህር እየተሻገሩ ቅኝ ግዛት በተፈጸመባቸዉ አገሮች ዘንድ ይህ በግድ የሆነ ዉህደት ይፈጸም የነበረበት ምክንያት አንደኛ በዚያን ጊዜ የነበረዉ መረዳት የቋንቋና የባህል ልዩነት እንደ እምቅ ችግር (potential conflict) ተደርጎ በመታየቱ ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የበላይ ሆኖ መኖር የሚፈልገዉ ቡድን የበላይነቱን ከሚያረጋግጥበት መንገድ ኣንዱ ባህልን በሃይል በማዋሃድ መስሎ ከመታየቱም ሌላ በአንድ ሀገር ዉስጥ የበላይ የሆነዉ ቡድን ደግሞ በባህልና በቋንቋ የበላይ መሆኑን ዘላለማዊ በማድረግ የረጋ መንግስት ለመመስረት ያስችላል በሚል እምነት ነው።
በአንድ ሀገር ዉስጥ ባሉ በተለያዩ ብሄሮች መካከል የነበረዉ የሃይል ዉህደት በአንዳንድ ሀገሮች እጅግ የከፋ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ባይሆንም ከፍተኛ ግፍ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ለማንኛዉም ግን እነሆ ዛሬ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የዓለም ህዝቦች ያለፉበትን ይህን ታሪክ በአብዘኛዉ እንደ የሰዉ ልጆች የእድገት ታሪክ እያዩት ያለፈዉን ታሪክ ችላ ብለዉ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ባህል ቀልባቸዉን ስቦት ይታያል፡፡ ቅኝ የገዙና የተገዙ አገሮች የጠበቀ ወዳጅነት መስርተዉ የዛሬዉን ትዉልድ የበለጠ ቀልቡን የሳበዉን የሳይንስ፣የቴክኖሎጆና የዴሞክራሲ ስራዎች ተባብረዉ ይሰራሉ፡፡ በአንድ አገር ዉስጥም አገር ሲመሰርቱና ከመሰረቱም በኃላ የአንዱን ባህል አንዱ የተጫነበትን ታሪክ እንደ የሰዉ ልጆች ታሪክ እያዩ ያለፋዉን ስህተት ዛሬ የሰዉ ልጅ በደረሰበት ንቃተ ህሊና ላይ ሳይመዝኑ ያገኙትን ባህል የጋራ አድርገዉ የሚኖሩ አገሮች ብዙ ናቸዉ፡፡ በርግጥ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ያለፈን ታሪክ መዝገብ እያገላበጡ በደልን እየቆጠሩ ከይቅርታ ይልቅ በቀልን የመረጡም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የኋላ ታሪክን በዛሬዉ መረዳት ልክ የሚመዝኑ ወገኖች ባለፋዉ የነበረዉን በግድ የሆነ ወይም ሚዛኑን ያልጠበቀ የባህል ዉህደት የተፈጠረዉን አገር እንደገና እግዜር ሲፈጥረን በነበርንበት ቡድን ተመልሰን የብሄር ፌደራሊዝም መስርተን ታሪክን መበቀል አለብን የሚል ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ የሌሎች ህዝቦችን ቀልብ ከሳበዉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የ21ኛ ክፍለ ዘመን ባህል ይልቅ የጥንቱ ጉዳይ ልባቸዉን የያዘዉ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ለማንኛዉም ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደድን ጠላንም ያለፈዉን ታሪክ ለመበቀል እንደገና እንድንበታተን እና በቋንቋችን የወሰን ድንጋይ እንድናኖር ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሚዛን ባልጠበቀ ሁኔታ የተዋሃደችዉን ኢትዮጵያ በብሄር ፌደራሊዝም ለመፍታት የተሞከረዉ ሙከራ የበለጠ ኪሳራን በማምጣቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን የግድ አንድ አዲስ ኪዳን የምንገባበት አዲስ ስርዓት የምንፈጥርበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ዉህደት ታሪካዊ አመጣጥም ያለፉትን ሁለት የማህበራዊ ፖለቲካ ስርዓቶች በማጤን እና ከሁለቱም ማህበራዊ ፖለቲካዎች በመማር የተፈጠረ ንድፈ ሃሳብ ሲሆን ይህ አዲስ መዋቅር የኢትዮጵያን ማህበራዊ ፖለቲካ ቅርጽና ይዘት በማስተካከል ካለዉና ከነበረዉ የተበላሸ ማህበራዊ ፖለቲካ ካመጣዉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያወጣን ይችላል፡፡
ከፍል አራት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (conventional cultural unity) ልዩ ባህርያት
ከፍ ሲል ታሪካዊ አመጣጡን ያየን ሲሆን በዚህ ክፍል ስር ደግሞ የዚህን ንደፈ ሃሳብ ባህርያት በአጭሩ እናያለን፡፡ በመጀመሪያ ግን በስምምነት ላይ ያልተመሰረተዉና የግድ የሆነዉ የባህል ዉህደት ሁለት ባህሪያት ያሉት ሲሆን አንደኛዉ ጉልበት ነዉ፡፡ ሌላዉ ሁለተኛ ባህርይዉ ደግሞ የባህል ፍስስት (diffusion of culture) ባለ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነዉ፡፡ ባህል የሚሰጠዉ ወይም የሚግተዉ አካል በግድ ባህል ይሰጣል እንጂ የሚቀበል ልብ የለዉም፡፡
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) ደግሞ ከፍ ሲል ካነሳነዉ የባህል ዉህደት የተለየ ባህርያት አሉት፡፡ እነዚህ ባህርያት፡-
1ኛ. በስምምነትላይየተመሰረተ (conventional) ነዉ፡፡
ይህ ማለት በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት ብሄሮች አንዳሉ በሚገባ መታወቅና መመዝገብ አለበት፡፡ አንዳንድ የሚያሳፍር ነገር ትሰማላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት ብሄር አለ? ሲባል ከ82 በላይ በተለምዶ ይባላል፡፡ ይህ አይሰራም፡፡ በትክክል ተቆጥሮ ስማቸዉ በክብር በህገ መንግስታቸዉ ላይ መስፈር አለበት፡፡ ከዚህ በኃላ እነዚህ ብሄሮች ሁሉ አንድ አዲስ ኪዳን ይገባሉ፡፡ ይህ ኪዳን በብሄሮች ወይም ባህላዊ ቡድኖች ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ለማድረግ የሚስማሙበት መሃላ ነዉ፡፡ ይህ ሂደት የዚህ አዲስ ስርዓት ዋና ቁለፍ ጉዳይ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ በቡድኖች ፍቃድ (will) ላይ የተመሰረተች ኣገር ልትሆን ስለሚገባት ቡድኖች ሁሉ ወደዚህ ስምምነት መግባታቸዉ የመጀመሪያዉ ተግባር ነዉ፡፡ በህገ መንግስታቸዉ ተስማምተዉ የባህል ዉህደት አንቀጽ ሊያስገቡ ይችላሉ ማለት ነዉ፡፡ ኪዳናቸዉ በህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን በባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማትም ሊገለጽ ይችላል፡፡
2ኛ. ባለብዙ አቅጣጫ ነዉ፡፡
በግድ የሆነ የባህል ዉህደት ሰጪና ተቀባይ እኩል ሚዛናዊ የሆነ የባህል ዝዉዉር አያደርጉም ብለናል፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ ጊዜ ግን የባህል ፍስስቱ (diffusion of culture) የኢትዮጵያን ብዙህ (plural) ተፈጥሮ ያገናዘበ በመሆኑ ባህል የሚፈስባቸዉ ብዙ ቦዮች በፖሊሲ ይቀረጻሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እዉነተኛ መልኳ እስኪጎላ ድረስ ባህል ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሁሉም አቅጣጫ እንዲዘዋወር ይበረታታል፡፡ይህ ለኣንዳንዶች በጣም ኣሳባዊ (too ideal) ሊመስል ይችላል። ግን ይቻላል። ብሄሮች ባለፈው በጭቆና ኣጣነው ያሉትን ባህልና ቋንቋ ሁሉ በማስመለስ (restoration) ፖሊሲዎች ልንበቀል እንችላለን። ማህበራዊ እድገትን እንዲህ ባሉ የፖሊሲ ከባቢዎች እየገሩ ሚዛን መጠበቅ ይቻላል።
ክፍልአምስት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) ለኢትዮጵያ ያለዉ ጠቀሜታ፡፡
1ኛ. እዉነተኛዉን መልካችንን ለማጉላት
ኢትዮጵያ ብዙህ (plural) ሀገር መሆኗን የሚያሳይ መልክ የሚኖራት ሚዛናዊ የባህል ዝዉዉር ሲኖር ይህንንም ተከትሎ የሚፈጠሩ የጋራ እሴቶች ሲኖሩ ነው፡፡ ይህንን እዉነተኛ መልኳን የሚያሳይ ስርዓት ደግሞ ሚዛኑን ያልጠበቀ የባህል ዝዉዉር ማለትም ኢትዮጵያ ከ22 ዓመት በፊት የነበረችበት ሳይሆን አሁን ያለዉ በየቤትህ እደር የሚለዉ የጎሳ ፌደራሊዝምም ሳይሆን በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ማለትም የሃገሪቱን እዉነተኛ ማንነት ወይም ብሄራዊ ማንነት አንጥሮ በማዉጣት ረገድ ይህ ጽንሰ ሃሳብ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
2ኛ. ለአንድነት
እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለን ልዩነት በዘር ደረጃ የሚታይ አይደለም፡፡ በዘር ክፍፍል ዉስጥ ሁላችን ምስራቅ አፍሪካዊያን ጥቁሮች ነን፡፡ ልዩነታችን ባህልና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የባህላዊ ቡድን ልዩነት ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ታዲህ እኛ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያለን ቡድኖች አንድ ነን ስንል ምን ማለታችን ነዉ? አንድነት በኢትዮጵያ አዉድ (context) ምን ማለት ነዉ? በሚለዉ ላይ መወያየት አለብን፡፡
አንድ ጊዜ በዚህ በአንድነት ኢለማንቶች ዙሪያ አንዲት አጭር ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ አንደገለጽኩት ኢትዮጵያ አራት የአንድነት ኢለማንቶች ያሏት ሃገር ናት፡፡ እነዚህ ኢለማንቶች
1ኛ. ታሪክ
2ኛ. መሬት
3ኛ. የጋራ እሴት (ማህበራዊ ካፒታል )
4ኛ. ፍትህና አስዳደር ናቸዉ፡፡
እንግዲህ አንድ ነን ስንል አንዱ የኣንድነታችን መገለጫ የጋራ ታሪካችን ነዉ፡፡ አጼ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ድል ካደረጉ በኃላ የዘመተዉን ወታደር በብሄር ስታትስቲክስ ሰርተዉ ይህን ያህል ኦሮሞ፣ ይህን ያህል አማራ፣ ይህን ያህል ትግሬ ወዘተ ብለዉ መዝገብ አላስቀመጡልንም፡፡ ድሉ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን ነዉ፡፡ ለዚህ ድል ወታደሩ ብቻ ሳይሆን ቀረጥ ሲከፍል የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ (Jurisdiction) የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድሉ ነዉ፡፡ ሌሎች ቁሳዊና መንፈሳዊ ታሪኮቻችን ሁሉ የጋራ ታሪካችን መሆናቸዉን ስንቀበል ስንስማማ ነዉ አንዱ የአንድነት መገለጫ፡፡ ሌላዉ ሁለተኛዉ ደግሞ መሬት ሲሆን ሁላችን ቡድኖች የተፈጠርንበትን መሬት ሁሉ አገጣጥመን የሰራናት ይህቺ አንዲት ዉብ ኢትዮጵያ አንድ ስትሆን በዚህም ነዉ አንድነታችን የሚገለጸዉ፡፡ ሌላዉ ሶስተኛዉ ፍትህና እኩልነት ሲሆን ሁላችን እኩል ስንሆን፣ በብሄሮች መካከል ትልቅና ትንሽ ሲጠፋ አንድነታችን በዚህም ይገለጻል፡፡ በእዉነተኛ ዴሞክራሲ ፊት ትልቅና ትንሽ ብሄር አይኖርም፡፡ ሌላዉ አራተኛዉና ከዚህ ርዕስ ጋር በቀጥታ የሚያያዘዉ የጋራ እሴት ግንባታዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንግዲህ እነዚህ ብዙ ብሄሮች ያሏቸዉን ጥበቦች እያዋጡ በጋራ የሚሰሩበት ባህል ሄዶ ሄዶ የጋራ ባህላቸዉን እያበዛ ተግባቦታቸዉን እየጨመረ ሲሄድ አንድነታቸዉም እንደዚያዉ እየጠነከረ ይመጣል፡፡ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ለማድረግ ብሄሮች ሲስማሙና ኪዳን ሲገቡ አንዱ የሚሆነዉ ነገር ብሄሮች ሁሉ ቋንቋቸዉንና ባህላቸዉን ለጋራዋ አገራቸዉ ለኢትዮጵያ መስዋዕት ያደርጋሉ፡፡ ስማቸዉ በህገ መንግስታቸዉ ላይ ሲሰፍር የሚገቡት ኪዳን አንዱ ይህ ነዉ፡፡ የፈጠሩት ጥበብ (art) ሁሉ ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት ይሆንና ንብረትነቱ የነሱ ብቻ ሳይሆን የወል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ በዚህ መሰረት የኮንሶዎችን ባህልና ቋንቋ የሚንከባከበዉ የኮንሶ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዋነኝነት ተንከባካቢ ትሆናለች ማለት ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ኪዳን ስትገባ የሚጠፉ ብሄሮች አይኖሩም፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት እኛ ኢትዮጵያዊያን ባህላዊ ቡድኖችን ዘላለም የማኖር አለማቀፋዊ ሃላፊነትም ይኖርብናል፡፡ የአንድ ባህላዊ ቡድን መጥፋት የአንድ ቋንቋ ከምድር ላይ መጥፋት የአለም ህዝብ ኪሳራም ተደርጎ ይታያል፡፡ በመሆኑም ብሄሮች ባህልና ቋንቋቸዉን ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት ካደረጉ በኃላ ለመንከባከብ መልሰዉ ሃላፊነት ቢወስዱም ንብረትነቱ ግን የኢትዮጵያዊያን ነዉ፡፡
ሌላዉ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታየዉ ነገር አንዱ አንድነት ከሚገለጽባቸዉ ጉዳዮች መካከል አስተዳደርና ፍትህ ነዉ ብለን ነበር፡፡ እዉነት ነዉ ይህ ንድፈ ሃሳብ ፖለቲካዉ ራሱ በአንድ ማንነት (identity) ላይ ብቻ አንዲመሰረት የሚታገል ነዉ፡፡ ይህ ማንነት (identity) ብሄራዊ ማንነት (national identity) የሚባል ሲሆን የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የተለያየ ፖሊሲ ይዘዉ ግን የሚቋቋሙት በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ነዉ፡፡ ይህ አጀንዳቸዉ ዶግማ ሲሆን ፖሊሲዎቻቸዉ ቀኖናዎች ናቸዉ፡፡ ይህ የማይለወጥ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸዉ ብሄራዊ ማንነት ሲሆን አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ነዉ፡፡ ይህ አንድነት በርግጥ የሚመጣዉ በመጀመሪያ ስንስማማ ነዉ፡፡ በዚህ ንደፈ ሃሳብ መሰረት ዜግነት የባለቤትነት ጥያቄ ሲሆን በዜግነታችን ለኢትጵያዊነት የተሰዉትን ባህሎችና ቋንቋዎች ሁሉ፣ ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ሃብቶችን ሁሉ ባለቤት የሚያደርገን በአዲስ ኪዳን የጸና ሀብት ማለት ነዉ፡፡ በብሄራዊ ማንነታችን አንድ ብቻ መሆኑ ነዉ አንዱ አንድ ነን ሊያሰኘን የሚችለዉ ነገር ለማለት ነዉ፡፡
3ኛ. በከፍተኛ የባህል ተዋጽኦ ዜጎችን ለማርካት
ኢትዮጵያ የባህል ሃብታም ናት፡፡ የተለያዩ የምግብ አሰራሮች፣ የተለያዩ የአልባሳት ጥበቦች፣ የተለያዩ የሰርግ ስርዓቶች፣ የተለያዩ ዘፈኖችና ሙዚቃዎች ወዘተ በገበያ ላይ ሲወጡ ዜጎች ብዙ ምርጫዎች (varieties) ያገኛሉ፡፡ ይህ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖረዉ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
4ኛ. ለማህበራዊ ክህሎት (social skill development)
ይህ ንድፈ ሃሳብ ሌላዉ ጠቀሜታዉ ኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ክህሎቶቻቸዉን እንዲያዳብሩ ባይልንጉዋል (bilingual) እንዲሆኑ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን የሚፈጥር በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ክህሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ተቻችሎ የመኖር ችሎታንም ለማዳበር እንድንችል የሚጠቅመን ነዉ፡፡
5ኛ. የብሄር ፖለቲካን ተከትሎ ለመጣ ቀዉስ መዉጫ በር ነዉ፡፡
የብሄር ፖለቲካን ተከትሎ ሌላዉ የመጣዉ ችግር የሀገሪቱን ማህበራዊ ኢኮኖሚ (social economy)፣ የኢኮኖሚ ፍትህ (economic justice) እንዲሁም ፍትሃዊ እድገት ችግር የሚፈታዉ በሌላ ስርዓት ነዉ፡፡ ዛሬ በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ያለዉ አድልዎ የዚህ የልዩነት ወይም የብሄር ፖለቲካ ዉጤት ነዉ፡፡ የማንነት ፖለቲካ አንዱ መገለጫዉ አድልዎ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ አድልዎ በሀገራችን አለ፡፡ የክልሎች እድገት የተመጣጠነ አይደለም፡፡ ስልጣን ያያዘዉ ቡድን ሌሎች ቡድኖችን በዉስጡ እየሰራ ከፍተኛ የሆነ ያልተመጣጠነ እድገት ይታያል፡፡ የብሄር ፌደራሊዝም በሰፈነበት አገር ፍትሃዊ እድገት የኢኮኖሚ ፍትህ (economic justice) ሁልጊዜ በከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በአጠቃላይ ፍትህ  በብሄር ፌደራሊዝም ጊዜ በጣም ስለሚጎዳ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት እነዚህን ኢፍትሃዊ ችግሮች ለማቃለል ይረዳል፡፡
ክፍል ስድስት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል አንድነት (CCU) የእድገት አቅጣጫዎች
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ባህል አዳጊ ነው፡፡ ባህል በተፈጥሮው ዳይናሚክ በመሆኑ በኣንድ ቡድን ህይወት ውስጥ ትውልዶች በራሳቸው ዘመን የየራሳቸውን ፈጠራ እየጨመሩበት ወደላይ ያድጋል:: በሌላ በኩል ደሞ  ባህል ወደ ጎን ካለው ሌላ ቡድን ጋር ሲነካካ(interact ሲያደርግ) እሴት እየተጋባ ወደ ጎንም ያድጋል።ወደ ጎን ሲያድግ ብዙ ያጋራ እሴቶችን ስለሚገነባ የነዚያ እሴቶች ያዢ(holders) ሁሉም ቡድኖች ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ያደረገውም እነዚህን ሁለት የባህል የእድገት ኣቅጣጫዎች ነው።
ሌላው የዚህ ንድፈ ሃሳብ መነሻ ደግሞ ሊመልሰው የሚገባ አንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህም በስምምነት ላይ የሚደረግ የባህል ውህደት ኣንዱ ግቡ አንድነት ሲሆን የዚህ ንድፈ ሃሳብ የመጨረሻ ግብ (ultimate goal) ሄዶ… ሄዶ…. አንድ ነጠለ ህዝብ (homogeneous society) ለመፍጠር ይመስላል የሚል ጥያቄ ይሆናል፡፡ በመሰረቱ ግን የዚህ ንድፍ ሃሳብ አላማ ይሄ አይደለም፡፡ ዓላማው ወደ ላይም ወደ ጎንም ባህል ሊያድግ ስለሚችል ቋንቋዎች ዘላለም የሚኖሩበትን፣ ቡድኖች ዘላለም የሚኖሩበትን በአንጻሩ ጥበባቸውን እየተካፈሉ ወደ ጎንም እያደጉ መሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው፡፡ እንዴት ወደ ላይ ወደ ጎንም ይታደጋል? ካልን እንዴት አንድ ሰው ሁለት ቋንቋ ሊናገር አይችልም በሚል አጸፋ እንመልሳለን፡፡ ይቻላል፡፡ ሁልጊዜም ወደ ሁለት አቅጣጫ ማደግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቡድኖች ወደ ላይ /vertical/ እድገት ባንድ በኩል እያሳዩ ወደ ጎን /horizontal/ እድገት በማሳየት የጋራ እሴት እየገነቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ቡድኖች በስምምነታቸው ጊዜ ህገ-መንግስታቸውን፣ የሃይማኖት ተቋሞቻቸውን፣ ባህላዊ ቡድናቸውን ይዘው ኪዳን ሲገቡ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለኢትዮጵያዊነት ይሰዋሉ፡፡ ይህን መስዋዕት ካደረጉ በኃላ ኢትዮጵያ መልሳ ቋንቋና ባህል እንዲንከባከቡ ለቡድኖች ትሰጣለች፡፡ ንብረትነቱ ግን የቡድኖቹ ብቻ ሰይሆን የኢትዮጵያዊነት ይሆናል ብለናል፡፡ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተወለደበት ማህበረሰብ ውስጥ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪና የባህሉ ተካፋይ እስከሆነ ድረስ ከባህላዊ ቡድነኝነት አንጻር የዚያ ቡድን አባል ይሆናል ማለት ነው፡፡  እናትና አባት ኦሮሞ ሆነው ልጅ አማራ የመሆን መብት አለው፡፡ ቋንቋና ባህል ውጪያዊ ልምምድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህሎችና ቋንቋዎች የኢትዮጵያዊነት በመሆናቸው ዜጎች በዜግነታቸው ያገኙዋቸው መብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በኦሮሞ ህዝብ ቸርነትና ፍቅር ልቧ የተነካው የእኔ እናት ኦሮሞ የመሆን መብቷም ይጠበቅላታል፡፡ በዚህ ስምምነት ጊዜ ቡድኖች ክፍት ሆነው ግን ቋንቋና ባህላቸውን ለማሳደግ ጠንቃቃዎች ይሆናሉ፡፡
ከፍል ሰባት
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት የብሄራዊ ቋንቋና የስራ ቋንቋ ጉዳይ እንዴት ይታያል?
በመጀመሪያ ደረጃ  ዜጎች ይህንን ጥያቄ ሊያዩት የሚገባው ከገቡት ኪዳን አንጻር ነው፡፡ በዚያ ከፍታ ላይ ሆነው ሲያዩ ቋንቋዎች ሁሉ ብሄራዊ ናቸው።የኢትዮጵያ ሃብት የሆኑ ቋንቋዎች ለምሳሌ ኣፋርኛ፣ ኣገውኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ ወዘተ. ብሄራዊ ቋንቋ ተብለው ይጠራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ቋንቋዎች ብሄራዊ ናቸው ሲባል ከፍ ሲል በሰጠነው የስምምነት መነሻ ኣሳብ ላይ ከተስማሙ የነዚህ ቋንቋዎች ሁሉ ባለቤት ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ ቡድኖችም ቋንቋዎቻቸውን ይዘው ሆ! ብለው መስዋእት ስላደረጉ በመብት ደረጃ ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ብሄራዊ ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ኣንድ ወይም ከኣንድ በላይ ቋንቋ መርጠው ዋና መግባቢያ ይኖራቸዋል።  ዋና የስራ  ቋንቋ  ሲመርጡ ምናልባትም የሚያዩት አብዘኛው ህዝብ የሚናገረውን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በመለስ በቁጥሩ ከፍ ያለ ህዝብ የሚናገራቸው ሌሎች ቋንቋዎችም ካሉ እነሱንም አካቶ ዋና ቋንቋን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሁኔታ አማርኛና ኦሮምኛን ዋና ቋንቋ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ እንግሊዘኛንም በስራ ቋንቋ ውስጥ በማካተት በአለም ተፎካካሪ ለመሆን ሶሊዳሪቲ ለማሳየት ይጠቅማል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በቋንቋ ጉዳይ እንዳይጋጩ ይህ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት እንደ መልህቅ ይይዛቸዋል፡፡ ይህ ስምምነት ሲወርድ በዋና ቋንቋ ምርጫ ጊዜ የኦሮምኛ ቋንቋ  ዋና ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጋር ሊሰራ ይገበዋል የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ከኦሮሞዎች ብቻ አይሆንም፡፡ እኔም ይህንን እንዳነሳ ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም የኦሮምኛ ቋንቋ ባልናገረውም የእኔም ቋንቋ ሃብቴ ነውና፡፡ ሃገሬ ሁለትና በላይ ዋና ዋና ቋንቋዎች ቢኖራት የበለጠ ታተርፋለች እንጂ አትከስርምና፡፡
ሌላው መገንዘብ ያለብን አንድ ቋንቋ ዋና ሆነ ማለት የዚያ ቋንቋ ፈጣሪ የሆነ ቡድን ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደልም፡፡ ቋንቋው  ዋና  በመሆኑ የተለየ ተጽዕኖ ሊያሳድርም አይችልም፡፡ ሌላው መረዳት ያለብን ደግሞ ቋንቋዎች ወደ ዋና መግባቢያነት መምጣታቸው ለእንክብካቤ የተመቹ እንዲሆኑና ሌሎቹ የመጥፋት አደጋ እንደተቃጣባቸው ተደርጎ ሊታሰብም አይችልም፡፡  በተግባር እንደምናየው እንደውም የመበወዝ /standardized የመሆን/  እድሉ ሰፊ የሚሆነው ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ መስጠት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የአለም ቋንቋ የሆነውን እንግሊዘኛን ብንወስድ አሁን ያለውን የቋንቋውን ይዘት ስናይ 60% የሚሆነው ቃል ከተውሶ የመጣ ነው፡፡ ከላቲን፣ ከጣሊያን፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ ወዘተ. የመጡ ቃላቶች የእንግሊዘኛ ቃልን በውዘውት አርባ በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው የኦርጂናሉ የእንግሊዞች እንግሊዘኛ ያለው፡፡ኣሁንም ገና እየተበወዘ ነው። ቴክኖሎጂ ሲያድግ፣ የኣለም ህዝቦች ንቃት ሲጨምር እንግሊዘኛ እየተበወዘ ይሄዳል። በዚህ እንግሊዝ አልተከፋችም፡፡ ያላትን ቋንቋ ለአለም ህዝቦች መስዋዕት አድርጋ ቋንቋው ሲያድግ የምትደሰት ነው የሚመስለን፡፡ ይህን ያመጣነው አንደኛ ቋንቋ አዳጊ መሆኑን እና በሌላ በኩል የመበወዝ እድሉ ሰፋ የሚለው የብሄራዊ ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ዋናው ቡድኖች የሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ስምምነቱን ከልብ በመቀበሉ ላይ ሲሆን ከዚያ በሁዋላ በዋና መግባቢያ ቋንቋ ላይ የሚደረገው ምርጫ ከፍ ባለ መረዳት ላይ ተመርኩዞ ስለሚሆን እንቅፋቶች አይገጥሙትም፡፡
አሁን ቡድኖች የኔም ቋንቋ ዋና መግባቢያ ይሁን የሚያስብላቸው ነገር አንደኛ ፖለቲካው የብሄር በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ፈጣሪዎች የዚያን ቡድን ቋንቋና ባህል ለብቻቸው ስለተሸከሙ እና ፖለቲካው ራሱ አእምሮአችንን ስለሚያሞስሰው /corrupted ስለሚያደርገው/ እንዲሁም አንድ ቋንቋ ዋና መግባቢያ በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ይህን ተንተርሶ ሌሎች የስነ-ልቦናና የማቴሪያል ጥቅም ያገኛል የሚል ስሜት ስላለ ነው፡፡ እነዚህ ስሜቶች መጀመሪያውን ወደ ስምምነቱ ስንመጣ የሚቀሉ ይሆናሉ።
ክፍል ስምንት
ማጠቃለያ፣ የፖሊሲ የስትራተጂ ኣቅጣጫዎች
ይህ ንድፈ ሃሳብ ዋናው ኣላማው በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ሲሆን ይህ ትራንስፎርሜሽን የማህበራዊ ፖለቲካችንን መሰረት ያስተካክላል ወይም ይፈውሳል በሚል ልብ ነው። ዛሬ በሃገራችን ፍትህ ሲጎድል ስናይ ይህን ለመዋጋት ሮጠን የፖለቲካ ቤት የምንሰራበት መሰረት ያስፈልገናል። ይህ መሰረት ኣንድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ማንነት ሲሆን ይህን ማህበራዊ ለውጥ ማስቀደሙ ጠቀሜታው ፖለቲካችንን  ስለሚያስተካክለው ነው።
ጥቂት የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችን ለመጠቆም ያህል ደሞ፣
  • ሚዛናዊ የሆነ የባህል ውህደትን ማራመድ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አለ የተባለው በሃይል የተደረገ የባህል ውህደት በሌሎች ዘንድ ሚዛኑን ያልጠበቀ ግን የከፋ አልነበረም የሚባለው ውህደት የታየው 20% ግድም በሚሆነው የከተማ ነዋሪው አካባቢ ነው፡፡ በየገጠሩ የሚኖረው ህብረተሰብ በባህል ደረጃ እምብዛም ለውህደት የተጋለጠ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ሚዛኑን የጠበቀ የባህል ውህደት ለማካሄድ ሰፊ እድል አላት፡፡ በመሆኑም መንግስት ሚዛኑን የጠበቀ አቅጣጫ በማሳየትና በማበረታታት የባህል ፍስስቱን ባላንስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ቀላል ምሳሌዎችን እናንሳ፡፡ ለምሳሌ መዲናችን የሆነችውን አዲስ አበባን መልኳን ብናይ የብዙ ብሄሮች ርዕሰ ከተማ አያስመስላትም፡፡ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ አንድም ቀን የኮንሶዎች ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ በደቡብ አካባቢ የሚታወቀው የኩርኩፉ ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ የሃመሮች ምግብ ቤት፣ የቦረናዎች ምግብ ቤት ወዘተ አላየሁም፡፡ እነዚህ ቡድኖች የየራሳቸው ጣፋጭ የምግብ አሰራርና ዓይነት ቢኖራቸውም መዲናዋ ላይ ገበያ ላይ አልወጣምና አዲስ አበባን እውነተኛ መልኳን እንዳታሳይ አድርጓታል፡፡ በሌላ በኩል ሰርግ የሚያደርጉ ድርጅቶች (wedding halls)  በውስጣቸው ብዙ የሰርግ ስርዓቶችን የሚያሳይ ሜኒዩ (menu) ቢኖራቸው መልካም ነው፡፡ ተጋቢዎች ወደዚያ ሄደው ከሜኒዩው መርጠው በዚያ ስርዓት ቢጋቡ ደስ ይላል፡፡ ፍቅራችን፣ አክብሮታችንና፣ አንድነታችን፣ መቀባበላችን በዚህም ይገለጽ ነበር፡፡ በኣልባሳት በኩል፣ በሙዚቃ በኩል እንዲሁ የኢትዮጵያን ቡድኖች የሚያሳዩ ቤቶች ሊታዩ ይገባል፡፡ ሚዛናዊ የባህል ውህደትን የሚያመጣው አንዱ የቡድኖችን ጥበብ በሚታይ ስፍራ በማውጣት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ይቻላል፡፡ይህን ስንል ምን ኣልባት ኣንዳንዶች ይህ ኣይነቱ ሂደት በፖሊሲ የሚሰራ ኣይሆንም መንግስት ኮንሶዎች እዚህ ጋር ምግብ ቤት ክፈቱ፣ ሃመሮች እዚህ ቦታ ላይ መጠጥ ቤት ክፈቱ ኣይልም እንዲህ ኣይነት ስፔሲፊክ ጉዳይ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት የሚያመጣው ነው ልንል እንችላለን። ግን ኣይደለም። መንግስት ከባቢየሆኑ ፖሊሲዎችን ማውጣት ይችላል። ከባቢዎች ሲኖሩ፣ ቡድኖች እውቅና ሲያገኙና ስምምነቱ ሲገባቸው እነዚህ ጉዳዩች የመንግስትን ምቹ ፖሊሲዎች እየተከተሉ የሚከሰቱ ናቸው። የታቀደ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት ማምጣት ይቻላል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ብሄር ያላቸው ኣገሮች በእቅድ በተደገፈ ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ ሲያልፉ ነው ሰላምና ልማታቸው የሚጠነክረው። በሌላ በኩል ቋንቋዎችን ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ መንደፍ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአማራው አካባቢ የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማሪያ አካዳሚዎች ቢኖሩ፣ በትግራይ የኮንሶዎችን ቋንቋ የሚያስተምሩ አካዳሚዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን እየተማሩ በዚያ ስራ የመያዝ እድል ቢኖራቸው በዚያው የቋንቋ ሃብትን የመጠበቅ ሃላፊነት ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የቱሪስት መስህብ ለማግትኘም ጭምር የባህል መንደር /cultural villages/ መመስረት፣ የባህል ተቋማትን በየቀበሌው ማቋቋም ቡድኖች ሁሉ ነቃ ነቃ እንዲሉ በሃገራቸው ምስረታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የባህል ልውውጥ ፕሮግራሞች ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል በትምህርት ካሪኩለሞቻችን ውስጥም የተለያዩ ባህሎቻችንን እየሰገሰጉ ማስተማር ጠቃሚ የሆኑትን እየነቀሱ እያወጡ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
  • መልክአ ምድራዊ ተዋጽኦ /spatial diversity/
የሰፈራ ፕሮግራሞች እንዲሁም የፌደራል ስርዓቱ ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረጉ ሳይሆን የህብረተሰቡን ተግባቦትም ያገናዘበ መሆን አለበት ብሎ ይህ ንድፈ ሃሳብ ያምናል፡፡ አንዱ የአንድነት መገለጫ የመሬት አንድነት በመሆኑም ይህንን አንድነት የሚያሳይ መልክአ ምድራዊ አሰፋፈር ያስፈልጋል፡፡
  • በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቅርጽ መፍጠር
ሌላው የታችኛውን ማህበራዊ ጉዳያችንን እያሻሻልን ሳለ ኣብረን ትኩረት ሰጥተን ልንፈታው የሚገባው ጉዳይ የፖለቲካ ኣወቃቀራችንን ነው። የእኛ የኢትዮጵያዊያን ችግር የሚፈታው በዚህ በባህልና በቋንቋ አካባቢ ያለንን መዋቅር ስናሻሽል እና ፖለቲካችንን ከባህል ማንነት አውጥተን ወደ ብሄራዊ ማንነት ስናሸጋግር ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅርጿን በ ኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ በመስራት ማህበራዊ ፖለቲካዋን ትራንስፎርም ልታደርግ ያስፈልጋታል። በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት ብሄራዊ እርቅን የሚያበረታታ፣ ለጋራ በጋራ የምትሆን ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ /reinventing Ethiopia/ የሚረዳ ነው ብለን ኣምነን ነው፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

 https://www.goolgule.com/reinventing-ethiopia-2/

ኢትዮጵያ- የፖሊስ መንግስት ያንሰራፋባት ሀገር (ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማርያም)

ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ህገመንግስት በህግ ከለላ ጥላ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ዜጎችን አስመልክቶ የሚከተሉትን መብቶች ያጎናጽፋል፡፡“በህግ ከለላ ጥላ በቁጥጥር ስር የዋለ ማንኛውም ሰው በህግ አግባብ መብቱ ተጠብቆ ይያዛል፡፡ ማንኛውም ሰው በሀሰት ለመረጃ ጠቀሜታ ተብሎ በማስገደድ እንዲያምን  ወይም የተባለውን እንዲቀበል አይገደድም፡፡ ማንኛውም በማስገደድ የተገኘ መረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡“ ይላል አንቀጽ 19(2)(5)፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ይህ የይስሙላ ሙበት የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ ያህል የለዉም፡፡
ባለፈው ሳምንት ሂዩማን ራይትስ ዎች “HRW“ የተባለው ዓለም ዓቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ መንግስት “የፌዴራል ፖሊስ ማዕከላዊ ምርመራ” እየተባለ በሚጠራው የፖሊስ ጣቢያ የሚፈጸሙትን አስደንጋጭና አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ዘገባ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ይህ የፖሊስ ምርመራ ማዕከል በጥርጣሬ የተያዙ ዜጎችን በማሰቃየት ይታወቃል፡፡
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ “በቁጥጥር ስር ባሉ እስረኞች ላይ በተለይም ያለው መንግስት ይቃወሙኛል በሚላቸው የፖለቲካ እስረኞች ላይ ማዕከላዊ ምርመራ እየተባለ የሚጠራው የምርመራ ተቋም እልህ አስጨራሽ የምርመራ ሂደት በማድረግ እስረኞችን በግድ ወንጀል ሰራን ብለው አንዲአምኑ በማስገድድ፣ እንደሚያሰቃይና ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ“ እየፈጸመ እንደሆነ በማረጋገጥ በዘገባው ይፋ አድርጓል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በማያያዝም “ማዕከላዊ ምርመራ እየተባለ የሚጠራው ተቋም ብዙ የተቃዋሚ የፖለቲካ እስረኞች፣ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች፣ መንግስት የብሄር ግጭት ተንኳሾች ናቸው በሚላቸውና ሌሎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በጅምላ ተይዘው የሚሰቃዩበት የምርመራ ማዕከል” ነው ብሎታል፡፡
ገጣሚው ዊሊያም ኤርነስትን አባባል በመዋስ “ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል”  የሰቆቃ መደብር በለቅሶና በሰቃይ የታጠረ የጭለማ ቤት ነው :: የገዥው መንግስት ተቃዋሚዎች፣ አመጸኞች፣ የሚላቸዉን የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ሌሎች እስረኞች በሙሉ በምርመራ ጊዜ ሰቆቃ ተጠቅሞ አራሳቸዉን አንዲወነጅሉ ያስገደዳቸዋል:: እንዲሁም ብዙዎቹ ማሰቃየትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ይፈጸሙባቸዋል፡፡
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች አባባል ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የምርመራ ተቋም “አስቀያሚው የአካልና የስነ ልቦና ማሰቃያ እንዲሁም አስገድዶ የማሰመኛ ምሽግ” መሆኑን በመጠቆም በማዕከሉ ከሚፈጸሙ የማሰቃየት ወንጀሎች እነዚህ ከብዙ ጥቂቶቹ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጿል፡፡ አኔም በግሌ  ከአስፈሪው ማአከላዊ ምርመራ መዳፍ የተረፉ የቀድሞ እስረኞችን አነጋገሬ አውቃለሁ::
እ.ኤ.አ. በ2011 የአሜሪካ መንግስት መምሪያ በዓመታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዘገባው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማሳየት የሚከተለውን ማጠቃለያ አስፍሯል፡፡
ብዙ ተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት እ.ኤ.አ. በ2009 በአዲስ አበባ የሚገኘው ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የፖሊስ ምርመራ ማዕከል ፖሊስ ኃይልን በመጠቀም አስረኞችን አስገድዶ ለማሳመን የአካል ማሰቃየት ሰቆቃ ድርጊት ሲፈጽም ነበር፡፡ ይህ ዓይነት የማሰቃየት ዘዴ በአሁኑ ጊዜም በተግባር ላይ እየዋለ ያለ መሆኑን ዜጎች ያላቸውን ሰፊ እምነት አጽንኦት በመስጠት እየገለጹ ነው፡፡ ባለስልጣናቱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ማዕከላዊ ምርመራን ለመጎብኘት የሚያቀርቡት ጥያቄ አሁንም በመንግስት በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኘ ይታወቃል፡፡“ በማለት ድርጅቱ ያለውን ሀሳብ ቋጭቷል፡፡
የ15ኛው ክፍለ ዘመን የሰቆቃ ስልት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ!
በአዲስ አበባ እምብርት ላይ የሚገኘው ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የማሰቃያ ምርመራ ተቋም በመካከለኛው (15ኛው) ዘመን በአውሮፓ የሰብአዊ መብት ረጋጮች በንጹሀን ዜጎች ላይ ይደረግ የነበረውን አስፈሪ፣ አስደንጋጭና ተስፋቢስ የማሰቃየት ስልት ገጽታ መለስ ብለን እንድናስታውስ ያስገድደናል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ “የማዕከላዊ ምርመራ ፖሊሶች በህግ ጥላ ስር የተያዙ የህግ አስረኞችን እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ በግድ ለማሳመን፣ መግለጫ እንዲሰጡና ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ በእስረኞች ላይ ማሰቃየትን ጨምሮ የተለያዩ የማስገደጃ  ዘዴዎችን እና ልዩ ልዩ ኢሰብአዊ ድርጊቶቸን ይፈጽማሉ፡፡ እንደ መካከለኛው የአውሮፓ ዘመን መብት ረጋጭ ተቋሞች ሁሉ የኢትዮጵያው የምርመራ ማዕከልም እንደመርማሪዎቹ ፍላጎትና አመችነት ሁኔታ እስረኞችን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች መድቧቸዋል፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ ማዕከል በተለያዩ የእስረኞች አያያዝና እያንዳንዳቸው ባላቸው ቅጽል ስም የሚታወቁ አራት አይነት የማጎሪያ እስር ቤቶች አሏቸው፡፡ እነርሱም፣ 1ኛ) ጨለማ ቤት፣ ይህ እስር ቤት በጣም አስቸጋሪና ብርሀን የማይገኝበት የማጎሪያ ክፍል ነው፡፡ በዚህ እስር ቤት እስረኞቹ የፀሐይ ብርሀን እና የመጸዳጃ ቤት የማግኘት ዕድላቸው በጣም ጠባብ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ለብቻ የመታሰር ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል፣ 2ኛ) ጣውላ ቤት፣ ይህ እስር ቤት በክፍል ውስጥ እንደልብ መዘዋወር የማያስችል ሲሆን ክፍሎቹም በቁንጫ ተባይ የተወረሩ ናቸው፡፡ 3ኛ) ሸራተን፣ በቅርብ ጊዜ ከእስር ቤት የማይለቀቁ ብዙዎቹ እስረኞች ወደዚህ የማጎሪያ ቤት እንዲዛወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው ሆቴል ስም የተሰየመው እስር ቤት እስረኞቹ የተሻለ የአካል እንቅስቃሴ የማድረግና በህግ አማካሪዎቻቸውና በዘመዶቻቸውም መጎብኘት እንዲችሉ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ፈቃድ የላላበት ነው፡፡ 4ኛ)የተፋፈገው የሴት እስረኞች ማጎሪያ፣ ይህ እስር ቤት በገፍ ሴት እስረኞችን አጭቆ የያዘ ነው፡፡”
ገዥው የኢትዮጵያ አስተዳደር ከተቃዋሚ የፖለቲካ እስረኞች መረጃዎችን፣ መግለጫዎችን እና ተገደው የእምነት ቃል እንዲሰጡ ለማድረግ የተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች አንደጠቀሰው: “እስረኞች በተደጋጋሚ በጥፊ ይጠናገራሉ፣ በእርግጫ ይመታሉ፣ በቦክስ ይደለቃሉ፣ በዱላና በጠብመንጃ ሰደፍ ይደበደባሉ፡፡ አንዳንዶች እንደተናገሩት በሚያስጨንቅ ሁኔታ [በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ‘እጅን በገመድ አስሮ ገልብጦ ከጣራ ወደ ታች በማንጠልጠል እንዲወድቁ በማድረግ የማሰቃየት’] ወይም ሁለት እጆችን ወደ ላይ ከእራስ በላይ ከፍ አድርጎ በገመድ አስሮ በማቆም ለበርካታ ሰዓታት በማቆየት በተደጋጋሚ ያሰቃዩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁንም [በመካከለኛው ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ] በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ምርመራ ማዕከልም የእስረኞችን እጆች በካቴና በማስገባት ለበርካታ ጊዜ ታስረው እንደሚቆዩ እንዲያውም አንድ እስረኛ ከአምስት ተከታታይ ወራት በላይ እጁ በካቴና ታስሮ እንደቆየ እና ማቋረጫ በሌለው የቃል ጥያቄ ምርመራ በታሳሪዎቹ ዘንድ ፖሊስ ተደጋጋሚ ዛቻ እንደሚያደርግ ተረጋግጧል፡፡” በጥንት ጊዜ ‘በእስፓኞች ይደረግ እንደነበረው አሰቃቂ የምርመራ ሂደት‘ አንዳንዶቹ እስረኞች ለበርካታ ጊዜ ተገልለው ለብቻቸው እስራታቸውን እንዲገፉ ተበይኖባቸዋል፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የእስር ቤት ማጎሪያዎች ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እስረኞቹ የፀሐይ ብርሃን የማግኘት መብታቸውን ይከለከላሉ፣ በደካማ የንጽህና አያያዝና በውሱን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ይሰቃያሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በተለይም በመጀመሪያ ለምርመራ  የቀርቡትን ተጠርጣሪዎች ላይ የበለጠ አሰቃቂ ይሆናሉ፡፡”
የእነዚህ ሁሉ የማሰቃየት ተግባራት ዋና ዓላማው በእስረኞች ላይ ታላቅ ጫና በመፍጠር ትክክል ይሁንም አይሁን ለቀረበባቸው የወንጀል ክስ ፈጻሚ መሆናቸውን እንዲያምኑ በማስገደድ መግለጫ፣ የእምነት ቃልና መረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ ነው፡፡ እነዚህን በማስገደድ የተሰጡ መግለጫዎችና በግዳጅ የተገኙ የእምነት ቃሎችን አንዳንድ ጊዜ ተወንጃዮቹ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ያለውን መንግስት ተገደው እንዲደግፉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤቶች በሚታይበት ጊዜም መንግስት እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ስለሚፈልጋቸው ነው፡፡
በማዕከላዊ እስር ቤት እስረኞች ለደረሱባቸው የአለአግባብ መታሰርና መንገላታት የሚጠየቅም ሆነ የሚገኝ ካሳ የለም፡፡ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማየት ነጻነት የላቸውም፡፡ ፍርድ ቤቶች የማዕካላዊ ምርመራ ፖሊስ በምርመራ ጊዜ በእስረኞች ላይ የማሰቃየትና ህገወጥ ድርጊቶችን ፈጽሟል የሚል ውንጀላ ለፍርድ ቤቶች ቢቀርብ ተገቢውን የማጣራት ሂደት በማከናውን እርምጃ ለመውሰድ አይችሉም፡፡ በሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ መሰረት የቀድሞ እስረኞች የማዕከላዊ ምርመራን የበቀል እርምጃ በመፍራት በምርመራ ወቅት የደረሱባቸውን በደሎች ለፍርድ ቤቶች ለማቅርብ ስለሚፈሩ ዝምታን እንደሚመርጡ ጠቁሟል፡፡ አንዳንዶቹም ከፍርድ ቤቶች ችሎት በፍጹም ደርሰው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በጁላይ 2008 በዓለም በደህንነት ሙያ ታዋቂ የሆኑት እንግሊዛዊው ጡረተኛ ኮሎኔል ሚካኤል ዴዋርስ የኢትዮጵያን የእስር ቤቶች አያያዝ ሁኔታ አጥንተው የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተዋውለው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ እስር ቤቶችን ከጎበኙ በኋላ በተጨባጭ የተመለከቱትን የእስር ቤቶችን ሁኔታ እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡ እንደዚህም ይተርኩታል፡፡
“እስረኞቹ ወዳሉበት ግቢ ውስጥ እንድገባ ጥያቄ አቀረብኩ፣ ይህ ግቢ ረዥም የሆነ በአንድ ጎኑ በኩል መጠለያ ሊሆን የሚችል ዳስ ይዟል፣ ግቢው በግንብ አጥር የታጠረ ሲሆን ለአካባቢው ጥበቃ እንዲያመች ሆኖ የተሰራ የጥበቃ ማማና ጥበቃዎች አሉት፡፡ በግቢው ውስጥ ከ70 እስከ 80 የሚሆኑ እስረኞች በተጎሳቆለ ሁኔታ ይታያሉ፡፡ ለሁሉም እስረኞች በምንጣፍ ለመጋደም የሚያስችል በቂ ክፍል የለም፣ መብራት የሚባል ነገር የለም፣ ቦታው በአይነምድርና በሽንት በሚሰነፍጥ ሽታ ታውዷል፣ በግቢው ውስጥ ምንም ዓይነት ውኃም ሆነ የመጸዳጃ ፋሲሊቲ የለም፣ በግቢው ውስጥ ለሴት እስረኞች ተብሎ ትንሽ የሳር ጎጆ ተቀልሳ በቅርብ እርቀት ትታያለች፣ ሆኖም ግን ግቢውን ለማሻሻል ተብሎ በግቢው ውስጥ የተሰራ ምንም ነገር የለም፣ አብዛኞቹ እስረኞች በትናንሽ ወንጀሎች በተለይም በሌብነት ወንጀል እየተያዙ ወደ እስር ቤቱ በተደጋጋሚ የሚመጡ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ለወራት በዚሁ እስር ቤት የቆዩ ናቸው…፡፡”
ኮሎኔል ዴዋርስ በእስር ቤቱ የተመለከቱትን በሚከተለው መልክ አጠቃለዋል፣ “የእስረኞቹ አያያዝ  በሚያሳፍር ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም ሁኔታ ፌዴራል ፖሊስን ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ትችት እንዲጋለጥ አድርጎታል፣ ማንም ቢሆን እስር ቤቶች እንደ ሂልተን ሆቴል መሆን አለባቸው ብሎ ሀሳብ የሚያቀርብ የለም ነገር ግን ማንም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ላይ ተገኝቶ ቅኝት ቢያደርግ እኛ ያደረግነውን ጥረት የሚደግፉ መረጃዎችን ማውጣት ይችላል… የዚህ ሁሉ የመጨረሻ ውጤቱ ሁከት፣ የእስረኞች ፍትህ አልባነትና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች መወገዝ ነው፡፡”
እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 2013 ሂዩማን ራይትስ ዎች ባቀረበው ዘገባ መሰረት “ባለፉት አስር ዓመታት ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ማለትም በዘፈቀደ ማሰርና ማጋዝ፣ ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ ድርጊት እና ማሰቃየት በተለያዩ ህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ እስር ቤቶች ውስጥ መፈጸማቸውን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጠው ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡”
ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል ቤት: ኢትዮጵያ እስር ቤት መሆኗን ይመሰላል  
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የእስር ቤቶችን አያያዝ ሁኔታዎች በተመለከተ ገንቢ ትችት ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 2012 ባቀረብኩት ትችት የኢትዮጵያ መንግስት በየፖለቲካ እስረኞች ማጎሪያዎች ላይ በዘፈቀደ የሚፈጽማቸውን የሰብአዊ መብት ረገጣዎችና ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ ለማጋለጥ ሞክሪያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 2013 ኢትዮጵያን “በአፍሪካ የፖሊስ ረጋጭ መንግሥት ተምሳሌትነት በመፈረጅ ጠንካራ ትችት አቅርቢያለሁ፡፡ የክርክር ጭብጤንም እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ፡፡
“የሌባ ፖሊስ መንግስት ብቸኛ መለያው — ልዩ መታወቂያው — በማያቋርጥና በየቦታው የሚፈጽማቸው የዘፈቀደ እስሮች፣ ዜጎችን ማደንና ወደ እስር ቤት ማጋዝ ናቸው፡፡ ማንም ሰው በከፍተኛም ሆነ በዝቅተኛ የመንግስት ባለስልጣን ስሜታዊ ትዕዛዝ በቀጥጥር ስር ውሎ የሚታሰር ከሆነ ይኸ የፖሊስ መንግስት መገለጫ ነው፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ የዜጎች መብት የሚጣስ ወይም የሚረገጥ ከሆነ ያ በጣም አስቀያሚ የፖሊስ መንግስት መገለጫ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ከህግ በላይ በሆነ ፖሊስ አዛዥ የሚተካ ከሆነ ያ የሌባ ፖሊስ መንግስት ተምሳሌት ነው፡፡”
በዚያ ባቀረብኩት ትችት በአዲስ አበባ ከተማ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የፍተሻ ወረቀት ሳይዙ በሌሊት በግልሰቦች ቤት በመሄድ በሚያካሂዱት ህገወጥ ፍተሻ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በአንዱ ህገወጥ የቤት ፍተሻ ላይ የተደረገው የሚቆጠቁጥ ድርጊት ግን የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎች በሙስሊም ዜጎች ቤቶች በመግባት የፈጸሙት የገንዘብ፣ የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ የሃይማኖት መጻህፍትና ሌሎች የግል ቁሳቁሶች ላይ የተደረገው ዝርፊያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ክፍለ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ለሆነ ሰው የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም ጋዜጠኛ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማንሳት ቃለመጠይቅ ሲያቀርብለት እንዲህ የሚል አሳፋሪ ማስፈራሪያ ሰጥቷል፣ “ዋሽንግተንም ሆነ በሰማይ ቤት ብትኖር ደንታዬ አይደለም፣ ከቁብ አልቆጥረውም፣ነገር ግን አዚያው ድረስ መጥቼ አንጠልጥልዬ አመጣሀለሁ፣ ይህን ልታውቅ ይገባል” ብሎ ዛተበት፡፡
እ.ኤ.አ. ጁላይ 2012 ኤርን በርኔት የተባለቸው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ኢትዮጵያን ከጎበኘች በኋላ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
“ባለፈው ወር ኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ የፖሊስ መንግስት ምን እንደሚመስል ለመመልከት ችያለሁ… አውሮፕላን ማረፊያው በቆየሁበት ጊዜ የጉምሩክ የስራ ሂደቱን ለማጠናቀቅ አንድ ሰዓት ወስዶብኛል፣ ይህም በሰልፉ መብዛት ምክንያት አይደለም ነገር ግን በፍተሻና በሚቀርቡት ጥያቄዎች መንዛዛት ምክንያት ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣኖች ብዙ ጊዜ በመንግስት መኪናዎች እንድንንቀሳቀስ ይፈልጋሉ፣ ይህም ወዴት እንደምንሄድ ለማወቅ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ በመቶሺዎች የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ያላቸው የቴሌቪዥን መሣሪያዎች  በአውሮፕላን ማሪፊያው  ከተውን በኋላ ብቻ ነው ቁጥጥራቸው በመጠኑም ቢሆን መላላት የቻለው፡፡”
የፖሊስ መንግስት ቃለመጠይቅ አንዴት አይነት አንደሆነ በቪደኦ ማየት ይቻላል!?
ሂዩማን ራይትስ ዎች በተቃዋሚ ፖለቲካ እስረኞች ወይም መብታቸውን ለማስከበር በሚጠይቁ ዜጎች ላይ በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ዘገባ በማረጋገጥ በየጊዜው ዘገባዎችን እያዘጋጀ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ የሙስሊሙን አመጽ መርቷል በሚል ውንጀላ ተከሶ የተያዘ ወጣት ግለሰብ ቃለ መጠይቅና የእምነት ቃሉን በቪዲዮ በመቅረጽ ህዝብ እንዲያየው ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ከሁለት ዓመት በላይ ጀምሮ መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን ያቁም በማለት ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡
ከታወቁ የዜና ምንጮች መረዳት እንደተቻለው በቪዲዮ የተቀረጸው ቃለ መጠይቅ በማዕከላዊ ምርመራ በአንደ ፖሊስ ወይም ደህንነት ባለስልጣን ቢሮ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቃለመጠይቅ መስጫው ክፍል ውስጥ ሌሎች ሰዎች የነበሩ ሲሆን የሚሰማው የዋናው ቃል  ጠያቂ ድምጽ ነበር፣ (የሌላ ሰው ድምጽ መስማማቱን ለመግለጽ ዋናውን ቃለ መጠይቅ አድራጊ ሲያቋርጠው ለተወሰነ ጊዜ ይሰማ ነበር፡፡)

የቃለ መጠይቅ ማድረጊያው ክፍል ባለመስታወትና ባለፋሽን በር ያለው ነው፡፡ በመሰረቱ ላይ ባለ ነጭ ቀለም መጋረጃ ይታያል፡፡ በጣም ውድ የሆኑ ከውጭ ኢምፖርት ተደርገው የገቡ ባለ ረዥም መደገፊያ በቆዳ የተለበዱ የባለስልጣን ወንበሮች እና ግማሹ የቃለ መጠይቅ ማድረጊያ ክፍል በሶፋዎች ተሞልቶ በካሜራ ሌንሱ ይታያል፡፡ ከተጠርጣሪው ጎን የኢትዮጵያ ካርታ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ ቃለ መጠይቁ በጨለማው የማዕከላዊ ምርመራ ክፍል ውስጥ አለመደረጉን ያሳያል፡፡ እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ከሆነ ቃለ መጠይቁ የተካሄደው በማዕከላዊ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ቢሮ ውሰጥ እንደሆነ ይገመታል፡፡
በቪዲዮ ቴፑ እንደሚታየው ተጠርጣሪው ሰው ሁለት እጆቹን በካቴና ታስሮ ለጸሎት እንደሚተጋ ሰው መዳፎቹን ከወዲያ ወዲህ ሲያወራጭ ይታያል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ለወጣቱ ተጠርጣሪ ዝርዝር ቃለመጠይቅ ሰጠ፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው የሚያስጠላ አዛዣዊ ድምጽ የሚያስተላልፍ መሆኑን ያሳብቅበታል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የማስገደድ ዝርዝር ቃለ መጠይቅ ሁኔታ ይታይበት ነበር፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በፍርሀትና በለሆሳስ ድምጽ የሚናገረውን ተጠርጣሪ ስለእምነቱና ሌሎችም ጉዳዮች በጥያቄ ያዋክበው ነበር፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በሚያስፈራ መልክ ስለሰለፊያ እምነት ምንነትና ስለእስላም አክራሪነት እንዲሁም በሌሎች ላይ ሰለሚኖረው መልካም አስተሳሰብ አደገኛነት ሲጠይቀው ተስተውሏል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን በአሽሙር በመሸንቆጥ ሲያስጨንቀው ታይቷል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን የሙስሊም ትምህርት ቤቶችን ሽፋን በማድረግ እሱ እና መሰሎቹ በኢትዮጵያ የእስላም መንግስት ለማቋቋም ጥረት እንደሚያደርጉ ወንጅሎታል፡፡ የተጠርጣሪው ድርጀት የገንዘብ ምንጩ ከየት እንደሆነ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ደጋግሞ በመጠየቅ ሲያባሳጨው ታይቷል፡፡ በቃለ መጠይቅ ሂደቱ ሁሉ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በተጠርጣሪው ላይ ሲያፌዝ፣ ንቀት ሲያሳይ፣ ሲቀልድና በንቀት ሲሳለቅ ታይቷል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪው እንዲናገር ዕድሉን ከሰጠ በኋላ ተጠርጣሪው በማስተባበል መናገር ሲጀምር ቃለ መጠይቅ አድራጊው ወዲያውኑ በማቋረጥ ያስቆመዋል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ወጣቱ ተጠርጣሪ በተስፋቢስነት በረዥም የባለስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ ሁለት እጆቹን በካቴና ታስሮ ቃለ መጠይቅ አድራጊውን በአክብሮት ዓይን እያየ በለሆሳስ ቅላጼና በጉልህ በማይሰማ ድምጽ በሚናገርበት ጊዜ የበላይነት ስሜት ያንጸባርቅበታል፣ ይረብሸዋል፣ እንዲሁም በተለየ መልኩ ያንቋሽሸዋል፡፡
እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ከሆነ በቪዲዮው ላይ የተደበቀ ብዙ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል የተቀረጸው  የቪዲዮ ቃለ መጠይቅ ከመደረጉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለመደብደብ ወደ ኋላ በማይሉ ዝቅተኛ የፖሊስ ባለስልጣኖች በማለሳለስና ተገድዶ ላመነው የቪዲዮ ቀረጻ ተባባሪ እንዲሆን በማድረግ ሙሉ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት ነበር፡፡ የቪዲዮ ቀረጻ ቃለ መጠይቁ በሚደመጥበት ጊዜ ሌሎች የፖሊስ አባላትና የሲቪል ሰራተኞች እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ እንዲገኙ የተደረገበት ዋና ዓላማም ጉዳዩ ለፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ተጠርጣሪው ግለሰብ ያለምንም ተጽዕኖ በእራሱ ፈቃድ አምኖ የተናገረው መሆኑን መመስከር እንዲችሉ ለማመቻቸት ነው፡፡ (በቪዲዮ የተቀረጸውን ቃለ መጠይቅ ቅጅ ለተከላካይ ጠበቆችም ሆነ ለፍርድ ቤቱ የተሰጠ ነገር የለም፡፡) ቃለ መጠይቁ የተቀረጸው የፖሊስ ማስፈራሪያነት በሌለበትና ከጣልገብነት ነጻ በሆነ መልኩ በተረጋጋና በጥሩ የንግግር ቅላጼ መሰረት ተደርጎ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ በመስክ ላይ እንደሚፈነዳ ደማሚት ተደርገው በዘዴ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ጥያቄ አቅራቢው ተጠርጣሪው የየትኛው ድርጅት አባል እንደሆነ፣ ምን ፍልስፍና እንደሚከተል፣ እነማን ደጋፊዎቹ እንደሆኑ፣ የገንዝብ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ፣ የተከሰሰበት ወንጀል ምን እንደሆነና የመሳሰሉት አጠቃላይ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ተጠርጣሪው ድርጊቱን ለመፈጸሙ ሊያሳምን በሚችል መልኩ ተያያዥነት ያላቸው በሚመስል መልኩ ሌሎች ሁለተኛ ዙር ጥያቄዎች ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌም ተጠርጣሪውን ለምንድን ነው የዚህ ድርጅት አባል የሆንከው? አባል ሆኖ ምን ሚና እንደተጫወተ እንዲሁም እነዚህን የተወነጀለባቸውን ድርጊቶች ለምን ሪፖርት እንዳላደረገና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ይጠየቃል፡፡ የቪዲዮ ቃለ መጠይቁ ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙን ለማመኑ ትክክለኛ መረጃና ለእራሱ መስቀያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ዋና የፖሊስ መርማሪዎች ጭካኔና አስገዳጅነት የተሞላበትን በቪዲዮ የተቀረጸ ቃለ መጠይቅ ያለበት የምርመራ ውጤት ማስቀረት አይፈልጉም፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጭች ተጠርጣሪው ወጣት እጆቹን በካቴና ታስሮ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ መደነቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ እጁን በካቴና ታስሮ ለአንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን ቃለመጠይቅ የሚሰጥ ተጠርጣሪ የጥያቄና መልስ ሂደት በቪዲዮ ቴፕ ተቀርጾ ማየት በጣም አስደንጋጭ ከመሆኑም በላይ እንደ አንዳንድ የውስጥ ምንጮች ተጠርጣሪውን ወጣት በካቴና አስሮ ቃለ መጠየቅ ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም የቪዲዮ ቀረጻ ቃለ መጠይቁ መንግስት በተቃዋሚ የፖለቲካ ደርጅቶች ላይ የስነ ልቦና ጦርነት በማካሄድና በማስፈራራት ረገድ ጠቀሜታ ያስገኝለታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ሁኔታ ተጠርጣሪዎችን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ ለተቃዋሚ ኃይሎችና ለአመጸኞች ማዳከሚያ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ በጥንካሬና በጽናት የተሞሉ ወጣት የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች በማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል መዳፍ ስር ወይም መንጋጋ ከገቡ ፍርሀትና መደናገጥ አንደሚታይባቸው ለሕዝብ ለማሳየት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የተቃዋሚ ድርጀት መሪዎች ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል ከደረሱ እንደሚሰባበሩ፣ እንደሚደቆሱ፣ እንደሚታኘኩና እንደሚበጣጠሱ የማያዳግም መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴ ነው፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ከሆነ ተገዶ ማመን አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ሳይወዱ በግድ መንግስትን እንዲደግፉ የሚደረጉበት ዘዴ ነው፡፡
ይህም ሆኖ በቪዲዮ የተቀረጸውን የቃለ መጠይቅ አድራጊውን ሙሉና የተጠርጣሪውን መብት በመጣስ ለእይታ የበቃውን ድራማ መመልከት “በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች በፍርድ ቤት ወንጀለኛነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ናቸው፣ እንዲሁም ተገደው በእራሳቸው ላይ ምስክርነት አይሰጡም“ የሚለውን ህገመንግስታዊ መብት የጣሰ የማይታመንና አስደንጋጭ ሁኔታ ነው (አንቀጽ 20(3) ፡፡ ቃለ መጠይቅ  አድራጊው የወጣቱን ተጠርጣሪ ህገመንግስታዊ መብት በኮርማ እንደተናደ የሴራሚክ ቁልል ደፍጥጦታል፡፡ ወጣቱ ተጠርጣሪ “ያለመናገር መብት“ እንዳለው በግልጽ የተቀመጠውን ህገመንግስታዊ መብት ቃለ መጠይቅ አድራጊው ከቁብ የቆጠረው  አይመስልም (አንቀጽ 19(2)(5) ፡፡ “በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ያለመናገር መብት አላቸው፡፡ በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ተገደው የእምነት ቃል እንዲሰጡ አይደረግም ተገደው የሰጡትም ቃል ለማስረጃነት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማንኛውም ማስረጃ በህግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡” ቃለ መጠይቁ በሚደረግበት ጊዜ የተጠርጣሪው የህግ ጠበቃ እንዲገኝ አለመደረጉ ቃለ መጠይቅ አድራጊውን የሚያሳስበው አይመስልም (አንቀጽ 20(5)፣ አንቀጽ 21(2) ፡፡ “የተከሰሱ ሰዎች የህግ ጠበቃቸው የመጎብኘትና… ከህግ ጠበቃቸው ጋር የመመካከር መብት አላቸው፡፡“  “ተጠርጥሮ በህግ ከለላ ጥላ ስር የዋለው ተጠርጣሪ ስለቀረበበት ክስ አስቀድሞ በቃለ መጠይቅ አድራጊው አልተገለጸለትም፡፡“ አንቀጽ 20(2) “የተከሰሱ ሰዎች ስለቀረበባቸው ክስ ዝርዝር መረጃ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀና ይህም በጽሁፍ ሊደርሳቸው ይገባል፡፡“
ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን ከየትኛው የእስልምና እምነት ክፍል እንደሆነ በማስፈራራት መረጃ ለማግኘት ሞክሯል፣ ለማስረዳትም ጥረት አድርጓል፣ አክራሪነት የየትኛው የእስልምና አስተምህሮ እንደሆነና ተጠርጣሪው ይህንን አውግዞ መንግስት የሚፈልገውን እንዲመርጥ በመጠየቅ የተጠርጣሪውን መብት ደፍጥጦታል፡፡ አንቀጽ 27(1)(3) “እያንዳንዱ ሰው የራሱ የእምነት ነጻነት አለው… ይህ መብት ግለሰቡ የመረጠውን ኃይማኖት በግሉ ወይም ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ የመከተልና የማራመድ መብትን ጭምር ያጠቃልላል… (3) ማንም የመረጠውን የራሱን እምነት ለማራመድ የሚያግደው ወይም የሚከለክለው የለም፡፡“ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ለተጠርጣሪው ስለኃይማኖት እንቅስቃሴውና ስለእምነት ምርጫው ሲጠይቅ “ተጠርጣሪው በግል ወይም ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን የመሰብሰብ፣ የጦር መሳሪያ ሳይዙ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት” (አንቀጽ 30(1) እንዳለው የተረዳ አይመስልም፡፡ በአጭሩ ቃለ መጠይቅ አድራጊው የተጠርጣሪውን መብት የደፈጠጠው ህገመንግስቱ ያጎናጸፈውን የኢትዮጵያን ህገመንገስት በመጣስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ደንቦችን በመናድ ጭምር ነው፡፡
ጥፋተኝነትን ለመከላከል የአሜሪካ ህገመንግስት 5ኛ ማሻሻያ
ጥፋተኝነትን መከላከል ወይም ያለመናገር መብት የአሜሪካ ህገ መንግስት ለዜጎቹ ያጎናጸፋቸው ዋነኛ የመብት ስብስቦች ናቸው፡፡ ማንም ሰው “በማንኛውም የወንጀል ጉዳይ ተገዶ ምስክርነት እንዲሰጥ አይደረግም“ በማለት አምስተኛው የአሜሪካ ህገ መንግስት ማሻሻያ ይደነግጋል፡፡ ከእንግሊዝ ተሰደው አሜሪካንን በቅኝ ግዛትነት የያዟት የስነምግባር ሰዎች ናቸው ይህንን የተገበሩት፡፡ ምክንያቱም በእምነታቸው ሰዎች ሲጠየቁ ዝም የማለት ወይም በጌቶቻቸው ስቃይ ተገድደው መልስ ያለመስጠት መብት እንዳላቸው የጸና እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡  የበላይ ጠያቂ ጌቶች ብዙውን ጊዜ ደጋጎቹን የእምነት ሰዎች የያዙት እምነት ምን እንደሆነ እንዲያምኑ ያስገድዷቸውና ያሰቃዩአቸው ነበር፡፡ ዝም ካሉና ካልተናገሩ ጥፋተኛ ብለው ይፈርጇቸው ነበር፡፡ የእንግሊዝ ህግ በ1600ዎቹ አጋማሽ ጥፋተኝነትን የመከላከል መብት ለዜጎቹ አጎናጽፏል፡፡
ይህ እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል የተቀደሰ መብት የአሜሪካ የወንጀል መከላከል ህግ መሰረት ነው – ማንም የተከሰሰ ሰው ጥፋተኝነቱ ባስተማማኝ ሁኔታ ከጥርጣሬ ባለፈ መልኩ በመንግስት እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ነው፡፡ ጥፋተኛ መሆን አለመሆኑን የማረጋገጡ ተግባር ደግሞ የመንግስት፣ የአቃቢያን ህግና የፖሊስ ነው፡፡ የተከሰሰን ሰው ጥፋተኝነት ለማረጋጥ የተከሰሰው ግለሰብ ምንም ነገር ማድረግ የለበትም፣ በተለይም ከፖሊስ ወይም ከአቃቤ ህግ ጋር መነጋገር ወይም መተባበር ግዴታ የለበትም፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም ሆነ የአካባቢ ፖሊስ የአሜሪካንን ዜጋ በማስገደድ ለጥፋተኝነታቸው ማስረጃ የሚሆኑ መግለጫዎችን እንዲሰጥ/እንዳይሰጥ  ወይም እንዲያምን/እንዳያምን ማድረግ አይችሉም፡፡
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርደ ቤት የፖሊስን አስገዳጂ የምርመራ ቃለ መጠይቅ ተግባር ያቆመው እ.ኤ.አ. በ1966 ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የህግ መብት ማስጠንቀቂያ“ ለተባለ ቀላል የአሰራር ሂደት ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ በተግባር ሲታይ ይህ የፖሊስ ምርመራ የህግ መብት ፖሊስ ምርመራ ሊያደርግ በሚፈልግበት ጊዜ ተጠርጣሪውን/ዋን በቢሮው ወይም የተጠርጣሪውን/ዋን ነጻነት ሊያውክ በማይችል ሁኔታ መሆን እንዳለበት፣ ተከሳሹ/ሿ ዝም የማለት መብት እንዳላቸው፣ በተጠርጣሪው/ዋ የተሰጠው ምስክርነት ለተጠርጣሪው/ዋ ማስረጃነት ሊውል እንደሚችል፣ተጠርጣሪው/ዋ ከመጠየቁ/ቋ በፊት ከህግ አማካሪው/ዋ ጋር የመምከር መብት እንዳለው/ላት እና ተጠርጣሪው/ዋ የህግ ጠበቃ ለማቆም አቅም ከሌለው/ላት መንግስት ምርመራ ከመጀመሩ በፊት ጠበቃ እንደሚያቆም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ግን ድርጊቱ ሆን ተብሎ በማወቅ የተፈጸመ ከሆነ፣ ወይም ከስለላ ስራ ጋር የተያያዘ ከሆነ፣ ወይም አንድን ዓላማ ለማሳካት መሰረት አድርጎ የተፈጸመ ከሆነ ወይም በፖሊስ ህገወጥ የምርመራ ዘዴ የተገኘ መረጃ ከሆነ እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል መብት ወይም የህግ የምክር አግልግሎት የማግኘት መብትን ያስነሳል፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን “ሚራንዳህ ወይም በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የህግ መብት በቀን ተቀን የፖሊስ ምርመራ ተግባራት ሁሉ እንዲካተት አውጇል፣ ማስጠንቀቂያዎቹም አገር አቀፋዊ ባህል ሆነው እስኪሰርጹ ድረስ ይሰራል”፡፡
በአሜሪካ ህገ መንግስት አምስተኛ ማሻሻያ የተሰጠውን እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል መብት መከላከል እንድችል የህግ ባለሙያነቴ የሰጠኝ መብት በኩራት እንድሞላ አድል ደርሶኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1998 በህዝብና በፒቪ መካከል በነበረው ጉዳይ የሚራንዳህ የህግ ስርዓት ታስቦበትና ሆን ተብሎ የምስክርነት ማስረጃው (ጥፋተኝነትን አስገደድዶ መቀበል፣ በግዳጅ ማሳመን) በመጣሱ በካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቤ ሽንጤን ገትሬ በመከራከር ማስቀየር በመቻሌ ልዩ ክብርና ሞገስ ይሰማኛል፡፡ በዚያን ወቅት በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኙ የፖሊስ መምሪያዎች ተጠርጣሪዎች በምርመራ ጊዜ ያለመናገርና የህግ ባለሙያ የማናገር መብት እንዳላቸው እየታወቀ ፖሊስ አፋጥጦ በመጠየቅ መረጃን የማግኘት ጥረቱ በጊዜው በነበረው አሰራር ተቀባይነት ነበረው፡፡ ይህ በተወሰኑ የፖሊስና አቃብያነ ህጎች ክልል ወስጥ ይደረግ የነበረው ህገወጥ የአጠያየቅ ስርዓት “ከሚራንዳህ ህግ ውጭ” በመባል ይታወቅ ነበር፡፡
በካሊፎርኒያ ግዛት በፒቪ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት “ከሚራንዳህ ምርመራ ውጭ“ የሚደረግ የምርመራ አሰራር በፍፁም አንዲቆም ተደረገ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 ዘጠነኛው የተዘዋዋሪ ችሎት በሲኤሲጀ እና በሳንታ ሞኒካ ከተማ ተካሂዶ ተጠርጣሪዎች በምርመራ ጊዜ ያለመናገር መብት እንዳላቸው እየታወቀ ይህንን ጥሰው ከሚራንዳህ የምርመራ ህግ ውጭ አስገድዶ ለማሳመን እና ጥፋተኝነትን እንዲቀበሉ ብለው የሚፈጽሙ ፖሊሶች በህገ መንግስቱና በሲቪል ህዝቡ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት በግል ተጠያቂና ተከሳሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
በማስገደድና በማሰቃየት የተገኘ የእምነት ቃል ፍትሀዊም ተዓማኒነትም የለውም
በወንጀል መከላከል ህግ ተጠርጣሪውን/ዋን አስገድዶ በማሳመን ጥፋተኛ በማድረግ የተገኘ መረጃን ያህል ትኩረትን የሚስብ ነገር የለም፡፡ ፖሊስ ምርመራ የሚያደርግበት ዋና ዓላማ እውነታው ላይ ለመድረስ ወይም ተጠርጣሪው ነጻ መሆኑን ለማረጋገጥ አይደለም፡፡ ብቸኛውና ዋናው ዓላማ የጥፋተኝነት መግለጫዎችን እና የእምነት ቃል ከተጠርጣሪው አንደበት ለመስማትና ይህንን መሰረት በማድረግ በተከሳሹ/ሿ ላይ ክስ ለመመስረት እንዲቻል ነው፡፡ በማስገደድ የፖሊስ ምርመራ ሂደት ጊዜ ተጠርጣሪው ከጥፋተኝነት ነጻ መሆኑን በራሱ አንደበት መግለጽ ይጠበቅበታል፣ ወይም ደግሞ ጥፋተኛ ተብሎ እንዲወሰንበት መንግስትን በማገዝ መተባበር ይጠበቅበታል፡፡ “የፖሊስ የበላይነት” በተንሰራፋበት አካባቢ እራስን ጥፋተኛ አድርጎ ማቅረብ ሜዳውን ለእብሪተኛና ለመሰሪ ፖሊሶች ምርመራ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዜጎችን ለፍትህ እጦት ሰለባ ያደርጋል፡፡
የተጠርጣሪው ወይም የተከሳሹ በፖሊስ ምርመራ ሂደት ዝም የማለት መብት የጥፋተኝነትና የቅጣት ሰለባ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት አንጻር ብዙ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ ዋናው ጠቃሚ ነገር ፍትሀዊነት ነው፡፡ በሙያው የሰለጠነ የምርመራ ፖሊስ የህግ ጥሰት ፈጽሟል ባለው ተጠርጣሪ ዜጋ ላይ ጥያቄዎችን እንዲያቀርብ በመፍቀድ የግዳጅ የእምነት ቃል ማግኘት በምንም መልኩ ፍተሀዊነትን አያሳይም፡፡ የማስገደድ የምርመራ ዘዴ ፍትሀዊነት በጎደለው መልኩ ሕገመንግስታዊ የማስረጃ ማቅረብን ግዴታ ከመንግስት ከሳሽ አጅ ወደ ተጠርጣሪው እንዲዞር ያደርጋል፡፡ ተጠርጣሪው ፍትህን በአግባቡ ማግኘት እንዲችል ከተፈለገ በፖሊስ የምርመራ ሂደት ጊዜ ተጠርጣሪው የምክር አግልግሎት እንዲያገኝ የህግ ባለሙያ እንዲያገኝ የማድረጉ ሂደት ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ የተጠርጣሪውን የህግ ጉዳይ ፍሬ ነገሩን የተጠርጣሪው የህግ አማካሪ ሳያየው ተጠርጣሪውን ወይም ተከሳሹን በፖሊስ እንዲመረመር ማስገደድ ተገቢነት የለውም፡፡ ለማንኛውም የምርመራ ጥያቄ ተጠርጣሪው ምን መልስ መስጠት እንዳለበትና መልስ መስጠት የሌለባቸውን ጉዳዮች  የህግ ባለሙያው ካጠናው በኋላ  የተጠርጣሪው የህግ አማካሪ መንግስት ምን መረጃ እንደሚፈልግና ምን መከላከያ ማስረጃዎች እንዳሉ ማወቅ አለበት፡፡
በማሰቃየት ወይም ማንኛውንም የሰብአዊ መብት ረገጣ ዘዴዎች በመጠቀም የተገኘ የእምነት ቃል በምንም ዓይነት ሁኔታ አስተማማኝ መረጃ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ተጠርጣሪዎች በመርማሪ ፖሊሶች የሚደርስባቸውን የአካልና የአዕምሮ ስነ ልቦና ስቃይ ለማቆም ሲሉ ያልሰሩትን ነገር እንደሰሩ አድርገው የእምነት ቃል ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ምግብ፣ ውኃና የመኝታ አገልግሎት የተነፈጉ ተጠርጣሪዎች ግራ በመጋባትና ስቃዩን በማስቀረት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ የእምነት ቃል ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ነጻ የሆኑ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ሲጠየቁ ከክሱ ነጻ የሚያወጣቸው እየመሰላቸው ስለእውነት ብቻ ይናገራሉ፡፡ በመሰሪ ፖሊሶች የሚዘረጉላቸውን አሽክላዎች አይገነዘቡም፡፡ እውነቱን መናገር ነጻ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል፣ ሆኖም ግን ብዙውን ጊዜ እውነታው በተቃራኒው በሰለጠኑ የፖሊስ መርማሪዎች ተጠምዝዞና ተፐውዞ ተጠርጣሪውን ለማዳካም ሲባል ፖሊስ አደናጋሪ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ በማስፈራራት፣ በመዛትና በማታለል ዓላማውን ለማሳካት ጥረት ያደርጋል፡፡ ነጻ የሆኑ ሰዎች የማያቋርጥ ለሰዓታት የዘለቀ የፖሊስ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ያልሰሩትን ወንጀል እንደሰሩ (የሀሰት የእምነት ቃል) የሚያያረጋግጡ ብዙ ማህበራዊና ሳይንሳዊ ጥናቶች አሉ፡፡ በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የተጠርጣሪው ዝምታ በዓለም ላይ ከወርቅ፣ ፕላቲኒየም፣ የተከበረ ድንጋይ ወይም አልማዝ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡
ማስመሰል ለምን? ጨካኔንና ተያቂ አልባነትን መፍጠር
በ15ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ አገር በተራ ፍርድ ቤቶች ሊከሰሱ የማይችሉና በጣም ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ የሚያይ ተጠያቂነት የሌለው ፍርድ ቤት (በፍርድ ቤቱ ጣሪያ ላይ የኮከብ ምልክት ያለበት) ተመሰረተ፡፡ ይህ ፍርድ ቤት በሚስጥርና የህግ ሂደትን ሳይከተል ምስክሮቸን ሳይሰማ ብይን ይሰጥ ነበር፡፡ በመጨረሻም ንጉሱ ይህን ተጠያቂነት የሌለው ፍርድ ቤት ተፎካካሪያቸውን፣ ተቃዋሚዎቻቸውን እና ትችት የሚያቀርቡባቸውን አካላት ጸጥ ለማድረግና ለማስወገድ ሲሉ ወደ ማጥቂያ ህጋዊ መሳሪያነት አሸጋገሩት፡፡ ገዥው የኢትዮጵያ መንግስትም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ የራሱን ተጠያቂ አልባ የፔንታጎን ቅርጽ ያለው ፍርድ ቤት በማቋቋምና በጣራው ላይ የኮከብ ምልክት ያለበትን ባንዲራ በመስቀል ስራውን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ህግ የማያከብር መንግስት የማስገደድ እምነት፣ ለህግ ንቀትን የሚፈለፍል ገዥ
የራሱን ህገመንግስት መረን በለቀቀ አኳኋን የሚደፈጥጠውን አገዛዝ ሁኔታ ሁልጊዜ ባሰብኩ ቁጥር እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ሁልጊዜ ህገመንግስታችን እየተባለ በመንግስት መሪዎች የሚለፈፈው እርባናየለሽ ዲስኩር ከማሳቁም በላይ ምንም እውቀቱ ሳይኖረው ከቅዳሳን መጽሐፍት እየጠቀሰ የሚያነበንበውን የኃይማኖት ደቀመዝሙር እና  ምን እንደሚልና ምን እንደሚያደርግ ትርጉም ያለው እውቀት ሳይኖረው በዘልማድ ባህላዊ ባላትን ለማክበር ሽርጉድ የሚለውን ባተሌ እንዳስታውስ ያደርገኛል፡፡ “ሰይጣን ለዓላማው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል“ የሚለውን የሸክስፒርን ስንኝ እንዳስታውስም ያደርገኛል፡፡ የስርዓቱ ገዥዎች ህገመንግስቱን ከአደጋና ከተቃዋሚዎች ጥቃት ለመጠበቅ ከነፋስ የፈጠኑ ናቸው፣ የራሳቸውን ህገመንግስት እራሳቸው በመጣስ ዋጋውን እንዲሚያሳንሱት በውል የተረዱት አይመስልም፡፡ ለዓመታት ደጋግሜ እንደተናገርኩት ለኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች ስለህገ መንግስት ወይም የህግ የበላይነትን መስበክ ለተሰበሰቡ አረማውያን (አህዛብ) መጽሐፍ ቅዱስን እንደመስበክ ወይም በጥቁረር ባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ይቆጠራል፡፡ በቅርቡ የወጣው የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ገዥው ስርዓት ስለ የህግ የበላይነት ያለውን ጥልቅ ንቀት በጉልህ ያሳያል፡፡
በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚገኙ ታላላቅ የህግ ዳኞች አንዱ የሆኑት ሌውስ ብራንዴስ እንዳመለከቱት “ህግ ባለበት መንግስት አገር መንግስት ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ የህግ ጥበቃ ካላደረግ የመንግስት ህልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ መንግስታችን ጠንካራና በየትም ቦታ የሚገኝ መምህር ነው፡፡ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር እራሱን ምሳሌ አድርጎ ለህዝቡ ያስተምራል፡፡  ወንጅል ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ መንግስት እራሱ ህግ የሚጥስ ከሆነ ለህግ ያለውን ንቀት ይፈለፍላል፣ እያንዳንዱ ዜጋ እስከ እራሱ ድረስ ህግ እንዲጥስ ይጋብዘዋል፣ ስርዓተ አልበኝነት እንዲነግስ ይገፋፋል፡፡ የወንጀል ህግን ከማስተዳደር አንጻር ዓላማው ፍጻሜውን ሊያሳምር ይገባል፡፡ የግል ወንጀለኛን ለመዳኘት ሲል መንግስት እራሱ ወንጀልን የሚፈጽም ከሆነ አደገኛ በቀልተኝነት ይሆናል፡፡“ ብራንዴስ “በመንግስት በኩል የግል የስልክ መስመሮችን በመጥለፍ የስለላ ስራ በማካሄድ የእራስን የጥፋተኝነት መረጃ ለማቅረብ የሚደረግ አሰራር ህገወጥ ነው“ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ገዥው አስተዳደር ህግን የሚጥስ ከሆነ ምን መደረግ አለበት? ህገመንግስት ደፍጣጭ ሲሆን? ገዥው አስተዳደር ለህግ የማይገዛ ወንበዴ ከሆነ ምን መደረግ አለበት? ህግን የማያከብርና የሚደፈጥጥ ገዥ አስተዳደር ህግን በሚያከብር መንግስት መተካት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ መንግስት ይቃወሙኛል የሚላቸውን ከህግ ውጭ እያስገደደና እያሰቃየ በማሳመን የሚያገኘው የእምነት ቃል ሳያውቀውና ሳይገነዘበው ቀስ በቀስ እራሱ ህግ አልባ ለመሆኑ የእምነት ቃል መስጠቱን ይመሰክርበታል፡፡
ecadforem

እረፍት የሚነሳው ህምም


የኮንትራት ሰራተኞች ስቃይ፣ የእኛ ፍርሃትና የፖለቲከኞች ጭካኔ
saudi 1
እረፍት አደርግ ብየ ከማህበራዊ መገናኛ መድረኩ ገለል ባልኩባቸው እንደ ብርሃን ፍጥነት በሚወረወሩት ባለፉት ጥቂት ቀናት ከበርካታ ወዳጆቸ በርካታ መልዕክቶች ይደርሱኛል። ብዙው መልዕክት ደግሞ የሚያጠነጥነው በጅዳ እና በአካባቢው በተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች አሰቃቂ ስቃይ ላይ ያተኮራል … ለነገሩ የአብዛኞቹ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆኑ ከመልዕክቶች ጋር የሚላኩልኝ መረጃዎች እረፍት የሚነሱ ናቸው! …
አዎ ተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር በመረጃነት የታጨቀባቸውን የመልዕክት መረጃ ጭብጦች እውነታ ለማረጋገጥ ወደ ጅዳ ቆንስል አመራሁ … መኪናየን አቁሜ ትንሽ እንደ ተራመድኩ እያለ ከፊት ለፊቴ  አንዲት ልጅ እግር ኢትዮጵያዊ ብቻዋን እያወራች ስታልፍ ስመለከት በመደናገጥ ሰላምታ አቅረብኩላት፣ መልስ ሳትሰጠኝ አለፈች!  ደነገጥኩና ባለሁበት ቆሜ በአይኔ ተከተልኳት … በፈጣን እርምጃ የሚያቃጥል የሚለበልበውን መሬት የምትደቃበትን የጠቆረ ባዶ እግሯን፣ እንደነገሩ ከላይዋ ላይ ደረብ ያደረገችውን ጥቁር “አበያዋን” እና ከፍ ሲል የተንጨፈረረ ጸጉሯን እያየሁ ፈዝዠ ቀረሁ … ከድንጋጤና ከፍርሃት ለአፍታ ነፍሴ መለስ ሲልልኝ ጠደፍ ጠደፍ ብየ ወደ ሔደችበት አቅጣጫ ተከተልኳት … ርቃኛለች … ሮጨ ልደርስባት ባለመቻሌ መኪናየን ወዳቆምኩት በመሔድ አስነስቸ ተከተልኳት … በደቂቃዎች ልዩነት ተሰወረችኝ! ምናልባት በዙሪያው በቆሙት መኪኖች መካከል፣ በመንገዱ ዳርም ሆነ በቤቶች አጥር ጥላ ፈልጋ ደክሟት አረፍ ብላ እንደሆነ በማለት መኪናየን አቆሜ ፍለጋየን ቀጠልኩ … ብዙ ሞክሬ አልተሳካልኝም … ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰላም እያልኳት ገላምጣኝ የሄደቸው እህት የለችም!
በትካዜ ተውጨ በአሳቻ መንገድ አገኛት እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባው እያማተርኩ ሳቀና ከጅዳ ቆንስል ግቢ በግምት 600 መቶ ሜትር ርቀት በአንድ አረብ ቱጃር ቤት አጥር ስር በሚገኝ አንድ ዛፍ ስር፣ ከመንገዱ ዳር አንዲት እህት ወድቃ ተመለከትኩ! ክው ክው ብየ ደነገጥኩ … ተጠጋኋት! የሚያምረው አይኗ ወይቧል፣ ሰውነቷ ደግሞ ዝላለች፣ ላብ ፊቷን አውዝቶታል፣ አፏ ግን አመድ መስሎ ደርቋል!  ጠይም ባለ ሰልካካዋ አፍንጫ ለግላጋ መልከ መልካሟን እህት ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ማውራት ቻልኩ … ለነገሩ ማውራት አይባልም! ለረጅም ደቂቃዎች ለማውራት ያደረግኩት ሙከራ በሰጠችኝ ጥቂት መልስ አፏ ተፈታ ማለቱ ይቀላል! ዝርዝር ማውራት ግን አትፈልግም … ምንም አይነት እርዳታ እንደማትፈልግ በአጭሩ ገለጸችልኝ! … በቃ ከዚህ ባለፈ ብዙ ማውራትና መቀጠል አልቻልኩም!  የማደርገው ባጣ ቢያንስ በቆንስሉ መጠለያ ግቢ ከታጨቁትና በከፋ አደጋ ላይ እንዳሉ ከሰማሁትና አይቸ ካረጋገጥኩት 150 ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ጋር ቢደባልቋት በሚል ለጅዳው ቆንስል ሃላፊ ለአቶ ዘነበ ከበደና ለዲያስፖራው እና በመጠለያ ላሉት ተፈናቃዮች እህቶች ተጠሪ ዲፕሎማት ለወ/ሮ ሙንትሃ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩላቸው አያነሱም …
የማደርገውን እያሰላሰልኩ ሳልራመድ በአጋጣሚ አይኔን ወደ ቀኝ አሻግሬ ስመለከት አንድ ሌላ እህት ከቅርብ ርቀት ወድቃ ተመለከትኩ … ይህችው እህት በቁራጭ ካርቶን ቢጤ ተቀምጣና ጀርባዋን ለመንገዱ ሰጥታ እጇን እያፍተለተለች ትዘፍናለች ትስቃለች! ይህችንም ደጋግሜ ጠየቅኳት እየገላመጠች እያየችኝ መልሳ ትስቅና ትዘፍናለች! ዘፈኑ ኦሮምኛ መሆኑን እንጅ ዘፋኝና ትርጉሙን አላውቀውም! …  ፈዝዠ ቀረሁ!
saudi 2ደጋግሜ ወደ ቆንስሉ ሃላፊዎች፣ ወደ ኮሚኒቲ ሹሞች ብደውልም ስልኬን አይመልሱትም! … እንዲህ ስባዝን አንድ ለቆንስል እና ከኮሚኒቲ ሃላፊዎች ቅርበት ያለው ወንድም ከበስተኋላየ መጥቶ ጀርባየን ቸብ አድርጎ አስደነገጠኝ!  ድንጋጤየ ገርሞት “አቶ ነብዩ ምነው? ደነገጥክኮ!” አለኝ በአግራሞት እንደ መሳቅ እያለ  … የደነገጥኩት ከበስተኋላ የተኛቸው እህት ተነስታ የነረተችኝን መሰሎኝ መሆኑን እውነቱን ገልጨለት እንደ ቀልድ አድርገን ተሳሳቅን፣ ብዙም ሳንቆይ ስለ ወደቁት ለእህቶች አንስተን ተጨዋዎትን … ወዳጀ በቅርብ ርቀት የወደቁ እህቶች እያሳየኝ እንዲህ አለኝ “አየህ ይህችኛዋ ለሶስት ቀናት አንዴ እዚህ ትወድቃለች አንዴ እዚያ ታገኛታለህ ፣ ያችኛዋንም እንደዚያው …” ብሎ ሊቀጥል ሲል በጥያቄ አስቆምኩት ታዲያ ምን አደረግክ?  “እኔ ምን አደርጋለሁ!  የእኛ ዜጋ ረክሷል እኮ … እስኪ ወደ መጠለያውና ግባ፣ ያበዱ የታመሙ ደህና መጥተው በመጠለያው የሚያብዱትን ሲያዩ እነሱም የሚያብዱት ቁጥር እኮ ቀላል አይደለም!” ሲል የመርከሳችን ነገር ሊያስረግጥልኝ ሞከረ!   ግን ይህንን ስታይ ለምን ወደ ምትቀርባቸው ሃላፊዎች ደውለህ አታስረዳቸውምና ሌላው ቢቀር ከግቢው ውስጥ ከተደባለቁ ይበዱም ይሙቱ ማንነታቸው ቢያንስ ይታወቃል?  አልኩት፣ ከግቢ ውጭ እንዲህ ሲወድቁ የሚከተልባቸው አደጋ እንደሚከፋ፣ ከወራት በፊት ከቆንስሉ እና ከመጠለያው ግቢ በር  ካለው ዛፍ ራሷን ሰቅላ ስለሞተቸው፣ ከቅርብ ርቀር ከሚገኘው ሌላ ዛፍ ወድቃ ስለሞተችው እህት የሚያውቀው የምናውቀውን አሳዛኝ ክስተት ለማስረዳትም ላማስረዳትም  እየሞከርኩ ብየ አከልኩለት … አይገባህም እንደ ማለት የለበጣ ሳቁን ከፊቱ ላይ እየነሰነሰ ምላሽ ንግግሩን  ቀጠለ …  “ያንተ ነገር እኔ መቸም እንዳንተ አላበድኩም፣ ፓስፖርት ማደስ፣ ቤተሰቦቸን ሃገር ቤት ሔጀ መጠየቅ እፈልጋለሁ፣ አንተ እንኳ ዱላውንና መገፋቱን ለምደህዋል፣ በል አሱን ተወው!” ሲል እያሳሳቀ ደገመና “እንዳንተ መች አበድኩ!” ብሎኝ አረፈው …
ፍርሃትን ፈርቶ ሰብዕናውን የደፈጠጠበት ይህ አጋጣሚ ቢያስቆጣኝም የተሰማኝን አፈንድቸ ወዳጀን ላስበረግገው አልፈለግኩም … እንዲያውም ላግባባው ሞከርኩ … ለሁሉም እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥም አንድም ለሃላፊዎች አለያም ያገባኛል ለምንል ሰወች መረጃውን ብታቀብሉን መልካም ነበር በማለት ሃላፊዎች ለማግኘት እና ለማሳወቅ ፈልጌ አይመልሱም ብየ ወሬየን ሳልጨርስ ንግግሬን ከአፌ አቋረጠው እና መለሰልኝ “አትድከም ማናቸውም ላንተ አይመልሱልህም፣ እያጋለጥካቸውና ድክምታቸውን ለአለም እያሳየህ ባይመልሱልህ አይደንቀኝም፣ በነገራችን ላይ ሳልፈልገው ልንገርህ አስገደድከኝ፣ ባለቤቴ የፌስቡክ ጓደኛህ ነች፣ በጣም ትከታተልሃለች፣ ታከብርሃለች፣ ባንተ ነገር ሁሌ እንጣላለን። እኔ በሃላፊዎች አካባቢ የምትባለውን ስለምሰማ ለእለት ጉርሱ ሳያነሰው ለምን ይጽፋል፣ ለምን ከመንግስት ጋር ይፋጠጣል፣ ልጆቹን ለምን አርፎ አያሳድግም ባይ ነኝ። እርሷ ግን በእኔ ሃሳብ ፍጹም አትስማማም። መረጃውን የሚቀበል አጣ እንጅ ጠቃሚ ነው ትላለች። እኔም የምለው ያንን ነው ሰሚ ሳይገኝ መጮህ አንተን ይጎዳሃል ባይ ነኝ … እና ብዙ ጊዜ በዚህ ተጣልተን ሁሉ እናውቃለን። አንድ በቅርቡ የሰራችውን ልንገርህ … ከሁለት ቀን በፊት ስለ መጠለያው ቪዲዮ በፌስቡክ መልዕክት መቀበያ አልደረሰህም?” ሲል ጠየቀኝ፣ ማን እንደላከው ንገረኝና ልነገርህ አልኩት፣ ነገረኝ፣ መረጃው እንደደረሰኝ አረጋገጥኩለት፣ ተግባባን … ንግግሩን ቀጠለ …saudi 3
“አየህ ሚስቴ እኔ እንድታየው ብሰጣት ላንተ ላከችልህ። ያበዱትን እና በጸሃይ ላይ የሚንቀለቀሉ እህቶች ቢያሳዝኑኝ፣ በቅርቡ በድብቅ በመጠለያው ያነሳሁት ነው። እንግዶች ሃገር ቤት ይመጣሉ ስለተባለ እና ለሃላፊዎች ሁኔታውን ለማሳየት ያነሳሁትን ቪዲዮ ነው!” ብሎ በጠራራው ጸሃይ አቁሞ ካወራኝ በኋላ ከእኔ ጋር እዚህ አካባቢ መቆሙን ከአሸባሪ ጋር እንደ መተባበር ይቆጠራል የሚል በነገር ቀልድ ሸንቁጦኝ መልሴን ሳይጠብቅ እየሳቀ ተሰናብቶኝ እየተጣደፈ ወደ ቆንስሉ ግቢ አመራ  …
ፊቴን ወደ ወደቁት ሁለት እህቶች መለስ ቀለስ እያደረግኩ ብቻየን ቀረሁ! የማደርገው ጠፋኝ … አሁንም መልሸ መላልሸ ወደ ቆንስል ሃላፊዎች ደወልኩ … ወዳጀ እውነቱን ነው፣ አያነሱም!… ሁሌ ሲከፋኝ እና መፍትሔ ሳጣ የምጠይቀውን ጥያቄ ራሴን ጠየቅኩት … ግን ለምን?  አልኩ … መልስ ባላገኝም …!
ብዙም ሳልቆይ ወደ ቆንስሉ ግቢ አመራሁ፣ ወደ ግቢው ዘልቄ ገባሁ፣  ግቢው በሰው ተሞልቷል። ኢትዮጵያዊው ወገን የሳውዲ ምህረት አዋጅ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከመጠናቀቁ በፊት የተለያዩ ሰነዶችና አገልግሎት ፈልጎ የመጣ መሆኑን አውቃለሁ፣ እኒህኞቹ ችግር ቢገባኝም፣  ዛሬ አንገብጋቢ ሆኖ አልታየኝም። ተጋፍቸ ወደ ቆንስል ሃላፊው የሚወስደው በር ብደርስም ወደ ፎቅ የሚወስደው በር በካሜራና በአውቶማቲክ በር ተጠርቅሟል። የበሩን መክፈቻ በመጫን አያንጫረርኩት ለማስከፈት ሞከርኩ፣ አልተቻለም … ተሰላችቸ ልመለስ ስል መልስ ተሰጠኝ “ሁሉም ዲፕሎማቶች ስብሰባ ላይ ናቸው”  የሚል መልስ! ከቶ ለማን ይሆን የሚሰበሰቡት?  አልኩ … ለእኛ መሆኑ አልዋጥልህ አለኝ እና እያጉረመረምኩ ግቢውን ለቅቄ ወደ መጠለያው አመራሁ …
ወደ መጠለያው ከመግባቴ በፊት ወድቀው ያየኋቸውን እህቶች ለማንሳት ከመጠለያው በር ያገኘኋትን እህት ትተባበረኝ ዘንድ ለምንኳት፣ “እሽ!” አለችኝ! ተያይዘን ወደ ወደቁት እህቶች  አመራን … አገኘናቸው አግባብተን ማስገባት ቀርቶ ማነጋገር አልቻልነም …  ይህች እህቴ ያየችውን ማመን አቅቷት በእንባ ተሞላች፣ ሳታስበው ሃዘን ውስጠ ከተትኳት፣ አዘንኩ! እሷኑ አይዞሽ ብየ ሸኝቸ፣ ለራሴው ሰላም አጥቸ ወደ መጠለያው አመራሁ …
ከዚህ ቀደም በደረሰኝ መረጃ የተመለከትኳቸው ያበዱ የታመሙትን ጨምሮ ጤነኞች ተፈናቃይ እህቶች ከግቢው ፈሰው ተመለከትኩ … ልብስ ታጥቦና ሳይታጠብ እንደ ሃገር ቤት በየአጥሩ፣  በደረጃው፣ በመሰላሉና በበሮቹ ላይ ተሰቅሏል … ሻንጣው በአንድ ጥግ ተከምሯል … ይህን ጨምሮ አሳዛኙን የተፈናቃዮች ውሎ በፎቶ ሆነ ቪዲዮ ማንሳት ክልክል ነው ስለተባለ ማንሳት አልፈልግኩም! ግቢው ጉስቁልናቸው ከፊታቸው በሚነበብ እህቶች፣  ባዘኑ በተጨነቁ፣ በውስጥ ደዌ የተደቆሱ፣ በአዕምሮ ጭንቀት በተለከፉ፣ በተዳከሙ፣ ተስፋ በቆረጡ እህቶች ጢም ብሎ ሞልቷል፣ ወደ 150 ደርሰዋል፣ የሚያድሩት በጠባቧ ክፍልና ሜዳ ላይ እንደሆነ ሰምቻለሁ … ያየሁት አንገቴን አስደፍቶ አሳፈረኝ!  ወደ ካፍቴሪያው ዘለቅኩ …
በካፍቴሪያው እንደገባሁ መቀመጫ ስፈልግ ቅድም በር አግኝቸው የነበረው ወንድምና ካፍቴርያውን ሳይሳለሙ ውለው ከማያድሩት ሌሎች ባልንጀሮቸ ተቀምጦ አየሁት … የደመቀ ወሬ ይዘዋል።እንዴት እንዳየኝ ባይገባኝም እጁን እያወናጨፈ ጠርቶ እንድቀመጥ ጋበዘኝ! ራመድ ራመድ ብየ ሄጀ ሰላምታ ከተለዋዎጥኩ በኋላ ተቀመጥኩ፣ ከቀናት በፊት በካፍቴርያው ያለውን የሟች ጠቅላይ ሚኒስትርን ፎቶ በቦርሳዋ ስትደበድብ ያየኋት እህት በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከጓኛዋ ጋር ተረጋግታ ተቀምጣለች። ዛሬ ተሽሏታል ብየ ሳላበቃ “ወግዱልኝ!” ብላ አምባርቃ ጮኸች …  ከወዳጆቸ ጋር ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩባት ቅጽበት እስክነሳ በጠረጴዛው ይወራ የነበረውን ወሬ ለመጻፍ ግን ይከብደኛል … ብቻ በግቢው ችግረኛ ግፉዕ ወገን እየተንገላታ እንደሆነ ተረስቷል … ሰብዕና ሳይሆን ተራ የፖለቲካ ቡትቶ ጉዳይ ሆኖ እና የባጥ የቆጡን  ወሬ እያመጡ የማውራቱ እና የመፈላሰፉ ወሬ ግን ያስጠላል …. በሽታ ሆነኝ …
ከቶ ይህ መከራ እየታየ እንዴት ይታረፋል! ብጣቂ መረጃ እንኳ እንካችሁ! ከእረፍት ስመለስ ከደረሰኝ እና ከማውቀው መረጃ አልፎ አልፎ ጨልፊም ቢሆን በቅርቡ ሳላስቃኛችሁ አልቀርም …
ለሁሉም አንድየ ቸር ያሰማን! የምስራች የምናዎራ ያድርገን!
ነቢዩ ሲራክ

googlgul