Friday, October 18, 2013

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደገና በአዋጅ ሊቋቋም ነው


  
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ፣መከላከያና ደህንነት ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን እንደገና ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

ረቂቀ አዋጁ ያስፈለገው በሀገሪቱ በኮምፒውተር የሚሰሩ ማንኛውም የመሰረተ ልማት ተቋማትና የመረጃ አገልግሎት  የኔትወርክ አውታሮች ላይ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የኮምፒውተር ቫይረስን ጨምሮ በተለያየ መንገዶች የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መሆኑን ነው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ተክለብርሀን ወ/ዓረጋይ የገልፁት፡፡

ረቂቅ አዋጁ ህግ ሆኖ ሲፀድቅም የሀገሪቱን የመረጃ ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የመንግስትና የግል የልማት ድርጅቶች ከሳይበር ወይም ከኮምፒውተር  ጥቃት በመከላከል የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ያስችላልም ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አዋጁ ኤጀንሲው የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ቀድሞ በማወቅ እና በመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ የመረጃ ማምረትና ተደራሽ የማድረግ ተግባራትን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ደግሞ አዋጁ ምስጢራዊ የሀገር ደህንነት መረጃዎችን እና የኢንዱስትሪዎችን ፣የባንኮችን ፣የቴሌኮሚኒኬሽን ፣የኤሌክትሪክ ሀይል ፣የመገናኛ ብዙሀንን ተቋማት እንዲሁም የግዙፍ ፕሮጀክቶች የኮምፒውተር ኔትወርክ አውታሮች ከሳይበር ጥቃት እንዲጠበቁ እንደሚያስችልም በውይይቱ ተብራርቷል፡፡

ድንበር የለሹ ይህ የኮምፒውተር ወንጀል አዲስ የሀገር ልዋላዊነት የጥቃት ምንጭ እንደሆነ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች የሽብር ፣የፖለቲካ ፣የወንጀል ምክንያቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዓላማዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው በረቂቅ አዋጁ ላይ ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ከብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ፣ከህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥቶቷል፡፡  

የውጪ ጉዳዩችና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴና ባለድርሻ አካላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ያቀረቡትን የማሻሻያ ሀሳብ በማካተት ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በማቅረብ አዋጁ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፦ሰለሞን አብርሃ

No comments:

Post a Comment