Friday, October 25, 2013

ዳግም በሀገር ፍቅር ስሜት ያስተሳሰሩን ዋልያዎቹ

በፍቅር ለይኩን
The Ethiopia national football team
‹‹ሀገሬ ናይጄሪያ ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ምትችልበት ብቸኛው መንገድ አንድም ጸሎት አሊያም ዕድል ነው፡፡›› የቀድሞው ዝነኛውና ኮከብ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የሆነው ካኑ ለአንድ ታዋቂ የስፖርት ድረ ገጽ በሰጠው አስተያየት ነበር እንዲህ ያለው፡፡ በጨዋታው ላይ የሆነው ሁሉ እንዳለ ሆኖ በእውነትም ካኑ እንደገመተው የናይጄሪያዎቹ ፈጣን ንስሮች ‹‹በጸሎትም ወይም በዕድል›› ሊባል በሚችል ሁኔታ የኢትዮጵያ አቻዎቻቸውን 2-1 በማሸነፍ ለ2014 የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ብሩህ ተስፋን የሰነቁና መንገዱን ያስተካከሉ መስለዋል፡፡
ንስሮቹ በጸሎትም ይባል በዕድል አሸንፈውናል፡፡ ግና ይህ የታሪክ አጋጣሚ አንድ ታላቅ እውነትን አስረግጦልን አልፏል፡፡ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት … ልዩነት ሊናድ፣ ሊደበዝዝ የማይችለውን በፍቅር ውል ኪዳን የጸናውን የኢትዮጵያዊነትን፣ የሀገርን ፍቅር፣ ልዩ ስሜት፣ ወኔና ክብር!!!
ዋልያዎቹ ከአፍሪካ ንስሮች ጋር ያደረጉትን ጨዋታ መላው የእግር ኳስ አፍቃሪ በታላቅ ጉጉትና በጭንቀት የጠበቀው ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የመላው እግር ኳስ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያን ትንፋሽ የተቆጣጠረው በመሰለው ጨዋታ ሀገራችን ለሽንፈት ብትዳረግም ዋልያዎቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ድንቅ የሆነ ብቃታቸውን ያሳዩበት ጨዋታ ነበር ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ለዚህም ነው ታላላቅ የሚባሉ መገናኛ ብዙኃንና የስፖርት ተንታኞች ሳይቀሩ የዋልያዎቹን የእግር ኳስ ጥበብ ከአውሮጳውያኑ ታላላቅ ክለቦች የአጨዋወት ስልት ጋር ለማነጻጸር የተገደዱት፡፡ በእርግጥም ዋልያዎቹ በእግር ኳስ ጥበብ ያላቸውን ብቃትና ችሎታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉና ዓለምን እያስደመሙ ናቸው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ከዚሁ ከእግር ኳሱ ጋር ተያይዞ ከማሸነፍና ከመሸነፍ ባሻገር የሚታየውና በብዙዎች ልብ ውስጥ ነግሦ የሚያቅበጠብጠው የሀገር ፍቅር ሰሜቱ፣ በቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ክቡር ደም፣ ውድ ሕይወት፣ ለወገንና ለሀገር ክብር ሲባል የተከሰከሰው አጥንት፣ የተከፈለው ዋጋ፣ የሰንደቀ ዓላማችን ከፍ ብሎ የመውለብለብ ታላቅ ክብር፣ ከማሸነፍና ካለመረታት ስሜት የሚቀዳው ጉጉት፣ ጭንቀት፣ እልክ፣ እንባና ሲቃ በቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነው፡፡ ገና ከእሑዱ ዕለት ጨዋታው ዋዜማ ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ የተስተዋለውም ይኸው ልዩ ስሜት፣ ይኸው የሀገር ፍቅር፣ ይኸው የወገን ክብር ነበር፡፡ ከሀገር፣ ከወገን፣ ከሕዝብ፣ ከሰንደቀ ዓላማ ፍቅርና ክብር የመነጨ የኢትዮጵያዊነት ታላቅ፣ ክቡር ስሜት ከዳር እስከ ዳር የናኘበት፣ ያየለበት፣ የበራበት፣ የደመቀበትና የነገሠበት፡፡
ይህን በብዙዎች ልብ ውስጥ የነገሠ የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ስሜት ዳግም በፍቅር ውል ኪዳን በአንድነት አስተሳስሮን በልዩ ሕብረ ዜማ እንገልጸው ዘንድ ዋልያዎቹ የዚህ ትውልድ፣ የኢትዮጵያዊነት ክብርና ፍቅር የታሪክ ባለ አደራና ምክንያት ሊሆኑ በመቻላቸው ዕድለኛ ናቸው፡፡ ባለፉት ሳምንታት በመላው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የነበረውን ኃያል ስሜት፣ ታላቅ ጉጉት፣ ልዩ የሆነውን የሀገርና የወገን ፍቅርና ክብር ላስተዋለ ሰው በእርግጥም ስፖርት ያለውን ምትሐታዊ ኃይል እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡ የእሑዱ ዕለት የዋልያዎቹና የንስሮቹ ጨዋታ ከተለያየ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ የተገኘን ሕዝቦች ግን ደግሞ ልዩነታችን በአንድነታቸውን ውብ ሆኖ ለዓለም ሁሉ የታየበት፣ የሰው ዘርን ሁሉ ያስደመመ ልዩ ትዕይንት፣ ልዩ ክስተት ነበር ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ይህ ከሰብአዊነት ልብና ሕሊና የመነጨ ውብ ስሜት የሀገርን ድንበር እንኳን ሳይቀር ተሻግሮ በሀገራትና በሕዝቦች መካከል አንድነትንና ወንድማማችነትን በጽናት የሰበከ እውነታ መሆኑን ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ ንስሮቹን ለመደገፍ ከናይጄሪያ የመጡት እግር ኳስ አፍቃሪዎች ባረፉበት ሆቴል አካባቢ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ከናይጄሪያዎቹ ደጋፊዎች ጋር በኅብረት ያዜሙበት፣ የጨፈሩበትና መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ ያስተዋልኩበት አጋጣሚ በእግር ኳስ ሰበብ ደምቆና ገዝፎ የወጣው የኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ፍቅርና ክብር ነው፡፡ በተጨማሪም የስፖርቱ መድረክ በእርግጥም የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት መድረክ መሆኑን ዳግመኛ በተግባር እንድገነዘብ ያደረገኝ ክስተት ነበር፡፡
በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ አሸብርቀውና ተውበው ለዋልያዎቹ ያላቸውን አለኝታነትና ክብር የገለጹበት ልዩ ስሜት ናይጄሪያዎቹንና መላው ዓለምን ጭምር ሳይቀር በእጅጉ ያስደነቀና ያስደመመ ነበር፡፡ ይህ በአረንጓዴው፣ በቢጫውና በቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን የአንድነታችን ልዩ የፍቅር ኪዳን ተውቦ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስ፣ ክብርና ወኔ የታየበት የእግር ኳሱ ውድድር ለብዙዎች፣ ለወዳጆቻችንም ሆነ ለጠላቶቻችን ታላቅ የሆነ መልእክትን ያስተላለፈ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚጠፋ ሳይሆን የሚዳፈን እሳት፣ የሀገራት ድንበር፣ የተራሮች ክፍታ፣ ውቅያኖስና ባሕር የማያግደው ከአድማስ አድማስ በርቶና ደምቆ የሚታይ ነበልባል መሆኑን ያሳየ፡፡
በእግር ኳስ መድረክ ውራ ሊባል በሚችል ተርታ የተሰለፈችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት አንስቶ መሥራችና ዋና ተሳታፊ ከሆነችበት የአፍሪካ ዋንጫ ከበርካታ ዓመታት በኋላ መመለሷ የፈጠረው ስሜት እጅግ ድንቅ ነው፡፡ ይኸው መልካም ጅማሬ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካለፉት ምርጥ የአፍሪካ አሥር ቡድን ውስጥ መቀላቀል መቻሏ በራሱ ትልቅ ስኬትና ድል ነው የሚሉ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ይህን ዋልያዎቹን ስኬት ተከትሎ እጅግ በርቶና ደምቆ በመላው ሀገሪቱ የታየው የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ያለውን ልዩ ክብርና ስፍራ በግልፅ ያሳየ ነው ለማለት ያስደፈራል፡፡
ይህን ለብሔራዊ ቡድናችን ያለውን ድጋፍ ለመግለፅ በየአደባባዩ በሰንደቀ ዓላማ ተውቦና ደምቆ የታየውን ሕዝብ ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ በጨዋታው ዋዜማ የአዲስ አበባን ድምቀትና ስሜት የታዘበው ቢቢሲው የስፖርት ዘጋቢ መዲናችንን ‹‹በኳስ ያበደች ከተማ!›› ሲል ነበር በአጭር ቃል በአድናቆትና በመገረም የገለጻት፡፡ ምናልባት ይህ ዘጋቢ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁር እስከ አፈ ነቢብ፣ ወንድ ሴት፣ ወጣት አዛውንት፣ ጎልማሳ ሕፃን ሳይል በእያንዳንዱ ኢትዮጵዊ ልብ ውስጥ የተዳፈነውንና የሚንቀለቀለውን የሀገር ፍቅር ስሜት ነዲድ እሳት ቀረብ ብሎ ለመረዳት ቢሞክር ኖሮ የዚህ ደስ የሚል እብደት ምንጩ ከኳሱ ባሻገር የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ክብር ምን መሆኑን በወጉ ለመረዳት በቻለ ነበር፡፡
በእርግጥም ገና ከጨዋታው በፊት በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ የክልል ከተማዎች የታየው የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ጉጉት በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ነው፡፡ ይህ ሺሕ ዘመናትን በጽናት የተሻገረ፣ ዓመታትን ያስረጀ፣ በመሥዋዕትነት የጸና፣ በፈጣሪ ልዩ ጥበብ የተሸመነ፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉንም ልብ በፍቅር በአንድነት ያስተሳሰረ ኪዳን ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያዊነት፣ የሀገር ፍቅርና ስሜትና ወኔ ትናንትና የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚኖር እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ጠፍቷል ሲሉት የሚበራ፣ ወድቋል ሲሉት በኃይል የሚነሳ፣ ጠውልጓል ሲሉት የሚፈካ፣ ጨልሟል ሲሉት ደምቆ የሚበራ፣ ሞቷል ሲሉት ሕያው የሚሆን … እንጂ፡፡ ዋልያዎቹ የዚህ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ስሜት፣ ውበት፣ ጥበብ፣ ክብርና  ኩራት፣ ማድመቂያ፣ ማንቂያ ደወልና ምክንያት ሆነውናልና ፍቅርና አድናቆት ይገባቸዋል፡፡
ሰላም! ሻሎም!

 https://ecadforum.com/Amharic/archives/10033/

No comments:

Post a Comment