October 25, 2013 07:34 am By Leave a Comment
ይህንን
ጽሑፍ ከጻፍኩት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በወቅቱ ጽሑፎቸን ያስተናግድ የነበረ አንድ ዝነኛ የሬዲዬ (የነጋሪት-ወግ)
ዝግጅት የጽሑፉን ይዘት ነግሬው እንዲያቀርበው ስጠይቀው አይ ስላለ የሚስተናገድበትን የነጋሪተ-ወግ መድረክ በማጣት
በኋላም ተዘንግቶ ቆይቶ አንድ ሰነድ ፈልጌ ካርቶን ሳገላብጥ አገኘሁትና አሀ……. ለምን ታዲያ አሁን ቢያንስ
በጋዜጣና በመካነ-ድሮች በኩል ለአንባቢያን አላደርሰውም በሚል አምጥቸዋለሁ የተጻፈው እንዳልኳቹህ ከ4 እና 5
ዓመታት በፊት ነው እንካቹህ፡-
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ-ኩነት) ራሱ ጣቢያው
ያዘጋጀውን አንድ ውይይት ተመለከትኩ የመወያያ ርእሳቸው የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የሀብታም ልጆች
በሚማሩባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች በከፊሎቹ ልክ ተማክረው ያደረጉት በሚመስል መልኩ ማሰብ ከሚችሉ ዜጎች ፈጽሞ
የማይጠበቁና የድፍረት ድርጊቶች በመፈጸሙ ማለትም ‹‹አማርኛ የሚያወራ አሕያ ነው ፣አማርኛ መናገርና ድንጋይ
መወርወር ክልክል ነው›› የመሳሰሉትን ጽሑፎችን እየለጠፉ እንደ ውይይቱ አዘጋጆች አገላለጽ ‹‹ልጆቹ የገዛ
ቋንቋቸውን እንዲጠሉና እንዲንቁ እየተደረጉ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ልንል እንችላለን?›› በሚል የሚመለከታቸው
የባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ኃላፈዎች ወይም ተወካዮች የሌሉበት ያልተገኙበት በራሳቸው ምክንያት በራሳቸው መንገድ
ከየቦታው የጋበዟቸውን ግለሰቦች ይዘው ውይይቱን አድርገው ሲያበቁ ያንን ውይይትም እንደወረደ ለተመልካች አቀረቡ፡፡
መቅረቡ ባልከፋ እንዲህ ዓይነት አጥቂና አጸያፊ ድርጊት ተፈጽሞ ሲገኝ ማጋለጥ ሕዝቡም እንዲያውቀውና መፍትሔ እንዲሻ
ማድረግ የብዙኃን መገናኛዎች ድርሻና ኃላፊነት ነውና፡፡ ስለእውነት ከሆነ ከባድ ጥፋትና ወንጀል ተፈጽሟል ፡፡
ምንም በማያውቁ ሕፃናት ላይ እንዲህ ዓይነት የማሸማቀቅና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ከመፈጸም የከፋ ጭካኔና ጠላትነት አለ
ብየ አላስብም ፡፡ እንዴት የሰው ልጅ አሕያ ይባላል? ሕፃናቶቹን ምን ማስተማር ነው የተፈለገው? ለምን? ይሄ
ሚያሳየው ሰዎቹ ምን ያህል ደናቁርት መሆናቸውን ነው፡፡
በእርግጥ ይሄ የተሳሳተና የማይገባ የቃላት አጠቃቀም
(ዳኅፀ-ልሳን) እንደዚህ በትምህርት ተቋማት ውስጥ በሕፃናት ላይ ሆን ተብሎ ባይሆንም ሁሉንም ሰው የሚያስት ጥፋት
ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንኳንና እነኘህን ቁንጽላን ይቅርና መጀመሪያ የዐፄ ቴዎድሮስ 2ኛ ቀጥሎ የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ
በመጨረሻም የዐፄ ምኒልክ 2ኛ የፍትሕ ጉዳዮች ዋና ሹም (ሚንስትር) የነበሩትን የፍትሐ ነገሥቱ ፣የብሉያቱና
የሐዲሳቱ መጻሕፍት፣ የቅኔውና የአቋቋሙን ታላቅ ሊቅ አባ ገብረ ሐናን እንኳን አሳስቷል ለከፉ ፈተናም ዳርጓል
ዳኅፀ-ልሳን፡፡
አባ ገብረሐና ተረበኛና ቧልተኝነታቸው ሰዎችን ለሚያስቀይም
ለሚያስከፋ ክፉ የቃላት አጠቃቀም (ዳኅፀ-ልሳን) ዳረጓቸው ነበር፡፡ አባ ገብረሐና ያን ያህል ታላቅ ሊቅ እና
የሃይማኖት አባት የነበሩ ስለነበሩ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ያውም በተደጋጋሚ ይሠራሉ ተብሎ ጨርሶ አይታሰብም
እይጠበቅምም ነበር፡፡ ነገር ግን እነኛን ተደጋጋሚ ስሕተቶች ሆን ብለው ይሠሩ በነበሩበት ወቅት ጤነኛ መሆናቸው
እንኳን አጠራጣሪ የነበረና እንኳንና በእነ ሐድጎ የሃይማኖት መሠረት በሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ሳይቀር ሲያፌዙና
ሲሳለቁ በወቅቱ ቅንጣት ታክል እንኳን የማይሰቀጥጣቸው ሰው ነበሩ፡፡ ታሪኩ እረጅም ነው አባ ገብረሐና እራሳቸው
በፈጠሩት መዘናጋት ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ምንኩስናቸው በመፍረሱ በእግዚአብሔር አኩርፈው የተበቀሉት
መስሏቸውም ይሁን ተስፋ ቆርጠው አይታወቅም ቅዱስ ቃሉን መዘባበቻ አድርገውት ነበር ፡፡ የኋላ ኋላ ግን መድኃኔዓለም
ሲታደጋቸው ልባቸውን መለሰላቸውና እጅግ በመጸጸታቸው በንስሐ ሕይወት ውስጥ እንዳሉ አርምሞ (በምነና ሕይዎት ያለ
ሰው ከሚያደርጋቸው የተጋድሎ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ትርጉሙም ከማንኛውም ሰው ጋር ምንም አለመነጋገር ዝምታ ማለት
ነው) እናም ዘመዶቻቸው አባ ገብረሐናን ጋኔን ልሳናቸውን ዘግቶት ነው ብለው ጸበል የተባለበት ቦታ ሁሉ እያዞሩ ብዙ
ያንገላቷቸው ነበር፣ ከስንት ቀን አንድ ጊዜ ለቁመተ ሥጋ ታክል ጥቂት በመቅመስ ብቻም ሰውነታቸውን በመቅጣትና
በማድከም መጻሕፍትን ከፊታቸው ደርድረው ድንጋይ እየተሸከሙ አብዝተው በመስገድ መዘባበቻ አድርጌያችኋለሁ ይቅር በሉኝ
ይሉ ነበር፡፡ ሌሎች የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲፈጽሙ ቆይተው በመጨረሻ ከአምላካቸው ለሠሩት ሁሉ ኃጢአት
ሥርዬት ከማግኘታቸውም በላይ በቅተው (ከቅድስና ደረጃ ደርሰው) እንዳረፉ ታሪካቸውን በቅርብ የሚያውቁ አረጋዊያን
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡
ለመሆኑ ግን አባ ገብረሐና ከሐድጎ ጋር የነበራቸው ግጭት ምን
ነበር ብትሉ ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ብላታ ሐድጎ ማለት የዐፄ ቴዎድሮስ ታማኝና ትጉ አገልጋያቸው የነበረ
ሰው ነው፡፡ አባ ገብረሐና ታዲያ የሐድጎን መጠሪያ ስምና የዘሩን ሥያሜ ወደ እማርኛ በመተርጎም ሐድጎ(አሕዮ)፣
ትግሬ(መረገጫ፣ ተረጋጭ) እያሉ እያበገኑ ቢያስቸግሩት በነገራችን ላይ ይሄንን የአባ ገብረሐናንና የሐድጎን ታሪክ
የሚጽፉ ሰዎች አባ ገብረሐና ሐድጎንና ስሙን በተመለከተ የተናገሩትን ብቻ እንጅ የዘሩን ሥያሜ በተመለከተ ትግሬ
መረገጫ ተረጋጭ እያሉም ያበግኑት እንደነበር እስከማውቀው ድረስ አንድም ሰው እንኳ እንደጻፈ ሰምቸና ዓይቸ
አላውቅም፡፡ በእርግጥ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኔም እንደነሱው ሁሉ ይህችን “ትግሬ መረገጫ ተረጋጭ”
የምትለዋን ነገር ለመዝለል የሚያበቃ ወይም የሚያስገድድ ምክንያት ሳይኖረኝ ቀርቶ እልነበረም፡፡ ነገር ግን “ ታሪክ
ታሪክ ነው በምንም ምክንያት ቢሆን መስተካከል ወይም መቆነጻጸል(edit) ሊደረግ አይገባም አይቻልምም ይህ
ከተደረገ ታሪክነቱ ይቀርና የሰዎች ተረት ይሆናል” የሚለውን የታሪክ ጥናት ሞያ መርሕ ወይም መመሪያ
(principle) ለመጠበቅ ብዬ እንጅ ስለ እውነት ይሄንን ጉዳይ መጻፍ ፈልጌ አልነበረም፡፡ ለማንኛውም አባ
ገብረሐና እንዲያ እያሉ ሐድጎን ያቆስሉት ነበር፡፡
ዛሬ ይሄ የሚያንገበግባቸው የእግር እሳት የሆነባቸው የሐድጎ
ወገኖች ትግሮች(በእርግጥም እንደ ሰው ሊሰማቸውም ይገባል) ቢቸግራቸው በተለይ ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ ትግሬ
የሚለውን ቃል ትርጉም አባ ገብረሐና ከሚሉት ከዚያ ትርጉሙ ለማራቅ ቃሉን ትግራወይ ወደሚል ቃል ቀይረው ይሄንንም
ቃል ለማስለመድ እየተጣጣሩ ነው አሁንም ግን ሥርዎ ቃሉን አለቀቀምና አልሸሹም ዞር አሉ ነው የሆነው፡፡ ለማንኛውም
አባ ገብረሐና ሐድጎን እንዲህ እያሉ እየተረጎሙና እየመሰሉ ቢያስቸግሩት ለዐፄ ቴዎድሮስ ከሶ አቀረባቸው፡፡
አባገብረሐና ግን እኔ ምን አደረኩ? ወላጆቹ ባወጡለት ስምና በግብሩ ነው የጠራሁት መተርጎሜ ከሆነ መተርጎም እኮ
ሞያዬ ነው ጃንሆይ! እያሉ ሊታረሙ ስላልቻሉ ሐድጎ ጨለማን ተገን አድርጎ አሸምቆና አድብቶ ማንነቱን ሰውሮ ሠዋራ
ቦታ ጠብቆ ክፉኛ ደበደባቸው አባ ገብረሐናም ክፉኛ ተጎድተው ነበርና ለአልጋ ተዳረጉ፡፡ ታዲያ ሰው ሁሉ እየመጣ
ሲጠይቃቸው ሐድጎም ነገሩን እንደማያውቅ ሰው ጨዋ ጠያቂ መስሎ ሊጠይቃቸው ወደ ቤታቸው ሄደና “አባገብረሐና
እግዚአብሔር ይማርዎት ምን አገኘዎት ከቶ?” ሲል በማስተዛዘን ጠየቀ ፡፡ እሳቸውም ለካ እንደዛ እድርጎ የደበደባቸው
እሱ እንደሆነ አውቀው ኖሮ “ምን እባክህ ሐድጎ አንድ ክፉ አሕያ አለኝ እሱ ክፉኛ እረግጦኝ ነው እንዲህ ለአልጋ
የበቃሁት” ሲሉት ቦግ ብሎ ተነሥቶ እየነደደ እያረረ ወጥቶ ሄደ፡፡
እሳቸው ግን ከአልጋ ከተነሡም በኋላ ጭራሽ ብሶባቸው መውጫ
መግቢያ አሳጡት፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም እንደበረቱበት ሰምተው ተጠርተው እንዲቀርቡ አደረጉና ያ የበገነ አገልጋያቸው
አንጀቱን ያርስ ብለው አባገብረሐና ሸምገል 㝕ከማለታቸውና ሐድጎ ደግሞ ጎረምሳ ከመሆኑ የተነሣ እንደሚያሸንፋቸው
በመተማመን ዐፄ ቴዎድሮስ አባገብረሐና ብለው ተጣሩና በሉ እንግዲህ ምላሱ ይቅርና ታግላቹህ ይዋጣላቹህ ወንዱ ይለይ
ብለው ዐዘዙ፡፡ አባ ገብረሐናም አይ አይሆንልኝም አልችልም እንዳይሉ 1ኛ. ወደዱም ጠሉ የንጉሥ ትዕዛዝ በመሆኑ
የማይቀርላቸው ነገር መሆኑን በመረዳት 2ኛ. በተለያየ አጋጣሚ በእርሳቸው ተረብ የቆሰሉ በዙሪያቸው ያሉ በአባ
ገብረሐና ላይ አንዳች ነገር አግኝተውባቸው ለመሳቅና ለማፌዝ ቁጭታቸውንም ለመወጣት አጋጣሚ ይፈልጉ በነበሩት
መኳንንት ዘንድ ምላስ ብቻ ፈሪ ተብዬ ስም ከሚወጣልኝና መሳቂያ መሳለቂያ ከመሆን የቻልኩትን ያህል ልታገል ብለው
ወሰኑና ትግሉን ግብግቡን ገጠሙ ትንሽ እንደታገሉ ሐድጎ አወረደና አፈረጣቸው ወዲያው ዐፄ ቴዎድሮስ እህ ለዚህ
ኖሯል?፡፡ ከዚህች በኋላ ‹‹አሕዮ ምንትስ›› የምትባል ቃል ብሰማ ውርድ ከራሴ ብለው በኃይልና በቁጣ የመጨረሻ
ማስጠንቀቂያ እየሰጡ እንዳሉ አባ ገብረሐና መለሱና ድሮስ ቢሆን ታዲያ ርግጫ የአሕያ አይደለም እንዴ! ከአሕያ ጋር
ታግዬ ላሸንፍ ኖሯል? በማለት አሁንም ማቁሰላቸውን ማብገናቸውን በመቀጠላቸው ዐፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተቆጥተው
የመንግሥታቸውን ፍትሕ ጉዳይ ከፍተኛውን ባለሥልጣን ከጎንደር አባርረው እንዲሰደዱ ፈረዱባቸው፡፡ አባ ገብረሐናም
ተሰደዱ የድፍረታቸው ድፍረት ደሞ ሲሰደዱ የት ይሰደዳሉ? ያ ሲያበግኑት ወደ ነበረው ሰው ሀገር ትግራይ ተሰደዱ ፡፡
ያንጊዜ ትግሬ የሚባለው ሀገር ዛሬ እንደምናየው ያህል ሰፊ ሳይሆን ትንሽ የነበረች ሰሜን ኢትዮጵያ መሀል ያለች
ትንሽ ሀገር ነበረች፡፡ ከዚያም ለካ ወሬው ቀድሞ ተሰምቶባቸው ኖሮ የሚያያቸው ሁሉ እየተጠቋቆመ ‹‹ እህ አንተማ
አንድ ጊዜ አሕያ አንድ ጊዜ መረገጫ ተረጋጭ የምትለን አይደለህ? እያሉ የሚያዝንላቸው አተው ›› ዐፄ ቴዎድሮስ
ሞተው የመጀመሪያው የትግሬ ንጉሥ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ነግሠው የእሳቸውም የፍትሕ ጉዳዮች ከፍተኛ
ባለሥልጣን (ሚንስትር) እስኪሆኑ ድረስ በሕይዎታቸው ጨርሶ ማይረሱትን የረሀብና የችግር የመቆራመድና የጠኔ የፈተና
ጊዜ አሳለፉ ፡፡ አባ ገብረሐና በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ሞገሥ አግኝተው ለዚያ ሥልጣን ይብቁ እንጂ
ሕዝቡ ግን የያዘባቸውን ቂም ጨርሶ ሊረሳላቸው አልቻለም ነበር ከሳቸው በኋላ የሳቸውን ማለትም የአባገብረሐናን ይዘው
ሌሎች ሰዎችም ትግሮችን ልክ አባገብረሓና ሐድጎን ይሉት በነበረው መጣራትና መዝለፍ በመቀጠላቸው እንዲህ ዓይነት
እንደ መርግ የሚከብድ አዋራጅና ሰብእናን የሚነካ የስድብ ሸክም የጫኑበትን ሰው አባ ገብረሐናን በተለያዬ መንገድ
ከመበቀልም አልፎ የሳቸውን ዘር (አማራን) ባጠቃላይ እሳቸው በሰደቡት ስድብ መልሶ በመስደብ ቁስሉን ለማከምና ይህ
ስድብ ምን ያህል እንደሚያም ለማሳየት ጥረት ያደርጋል፡፡ ሥራዬ ብለውም ለልጆቻቸው ያስጠናሉ፡፡
ወደቀደመው ነገራችን እንመለስና አሁን ደግሞ እነኝህ ቁንጽላን
ከአባ ገብረሐና መልካሙን ሳይሆን ክፉውን መላውን ዕውቀቱን ሳይሆን ስድብና ነውሩን ዋዛ ፈዛዛውን ተምረው ለዛውም
ሕፃናትን ‹‹አሕያ›› ብለው በመስደብ በሰብእናቸው ላይ ተረማመዱባቸው፡፡ የእነርሱ ሳያንስ ደግሞ የኢትዮጵያ
ምርዓየ-ኩነት (ቴሌቪዥን) የዚያ ውይይት አዘጋጆች የት/ቤቶቹን ስሞች ሳይጠቅሱ አንዳንድ ት/ቤቶች በማለት
‹‹በአማርኛ የሚያወራ አሕያ ነው ፣ አማርኛ ማውራትና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው ወ.ዘ.ተ›› ብለው በመለጠፍ
በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመነጋገር መብታቸውን እየጣሱባቸው ነው በሚልና የባዕድ ቋንቋ ተጽዕኖ እስከምን ድረስ ሄዷል?
በሚል ጉዳይ ላይ ከተጋበዙት አንዳንድ ‹‹ምሁራን›› ያሏቸውንና ከሌሎችም ጋር የተደረገውን ውይይት ለሕዝብ ዓሳዩ
አስደመጡ፡፡ ችግሩ ለሕዝብ መታየቱ ላይ አልነበረም ነገር ግን ይህ ችግር ለውይይት ከቀረበና ያን ስሕተት የፈጸሙት
ሰዎችም መወቀሳቸው ካልቀረ የልጆቹን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመነጋገር መብታቸውን በመንፈጋቸው ብቻ ሳይሆን ይልቁንስ
መነጋገሪያ መሆን የነበረበት የፈጸሙት ስሕተት ከባድና ለዚያውም በምንም መመዘኛ ለማይገባቸው ልጆች በመስጠታቸው
፣የሥነ-ልቡና ጥቃቱን በማድረሳቸው ፣ በሌለባቸው ነገር ላይ እስከ የማንነትና ክብር ጥቃት የሚደርስ ወንጀል
በመሥራታቸው ምክንያት ግለሰቦቹም ሆኑ ት/ቤቶቹ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ በሚያስገነዝብና ለሌላውም ትምህርት ሊሰጥ
በሚችል መልኩ ውይይቱ መኪያሄድ ሲገባው ከነገሩ ክብደት የተነሣ ጉዳዩን በውይይቱ ላይ ባቀረቡት መልኩ አቅለው
ያዩታል ተብሎ ሊገመት በማይችል ሁኔታ እንደነገሩ አድርገው ግመሉ ሳይታያቸው ከግመሉ ላይ ስላለችው ትንኝ አውርተው
ውይይቱን ቋጩት፡፡
አድማጭ ተመልካችም በእነዚህ ት/ቤቶች ውስጥ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው
ተማሪዎች ባልተናነሰ %ረ እንዲያውም በባሰ መልኩ የታሰበው ስውር ጥቃት ሰለባ ወይም ተጠቂ ሆነ እኔ በግሌ በወቅቱ
የተሰማኝ ነገር ቢኖር እንዴ! ኢቴቪ. ማድረግ ፈለገው ይሄንን ነው ማለት ነው? ብየ እራሴን እንድጠይቅ
አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ካነሡት ርእሰ ጉዳይ ክብደት አንፃር ሊባሉ የሚገባቸው
ነገሮች ሳይባሉ ተድበስብሰው በመታለፋቸውና ተባለ የተባለውን ነገር ለአድማጭ ተመልካቹ አድርሶ ከማቁሰል ውጭ ምን
ጉዳይ ከውነው እንደሄዱና ውይይቱ ራሱ ለምን ቁምነገር እንደተዘጋጀ በግልጽ ሊያስገነዝብ በማይችል መልኩ አዘጋጅተው
ወዲያውም ደምድመውታልና፡፡
እንደኔ እንደኔ ኢ.ቴ.ቪ ሳይነግረን በቀረና ባልሰማነው በተሸለ
ነበር ባይ ነኝ፡፡ ከነ ተረቱስ ‹‹ከሰደበኝ የነገረኝ›› አይደለም እንዴ የሚባለው ለማንኛውም ግን ይሄንን ጉዳይ
በተመለከተ እውነቱ መነገር ስላለበትና ማረሚያ ወይም ማስተካከያ መሰጠቱ አስፈላጊ መስሎ ስለታየኝ ያንን ስሕተት
ለፈጸሙት መምህራን ተብዬዎችና ለመሰሎቻቸው እርማቱን ወይንም ማስተካከያውን እነሆ፡-
በቅድሚያ እስኪ የአሕያን ማንነትና መገለጫዎቿን ባጭሩ
እንመልከት፡- ሁላችንም እንደምናውቀው አሕያ ከጋማ ከብቶች አንዷ እንደመሆኗ ለሸክም እንደተፈጠረችና ለምን እንደሆነ
ባይታወቅም የተናቀች ክብርም የሌላት እንስሳ ናት ፡፡ አሕያ የሰውን ልጅ በሸክም እጅግ በጣም ታግዛለች የቱንም
ያህል ክብደት ይኑረው የመጨረሻ አቅሟ በፈቀደላት መጠን የጫኗትን ሁሉ በመጫን ለጌቶቿ ታገለግላለች፡፡ አሕያ ራቅ
ያለውን ማየት የማትችል የጥቂት እርምጃዎችን ርቀት ያህል ብቻ የመመልከት ውስን ዐቅም ያላት ጀሮዋ ግን እጅግ
በሚገርም ሁኔታ የሩቅና ከየአቅጣጫው ያለውን ኮሽታም እንኳ ሳይቀር ከዛም አልፋ ከደመና በላይ ያለውን ቅድመ ዝናብ
ያለውን እንቅስቃሴ ጨርሶ ለመስማት የማይቻለውን ዝናብ የመምጫ ምልክቶችን የመስማትና እራሷን የማዘጋጀት አስደናቂ
የመስማት ችሎታ ያላት እንስሳ ነች፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በተለይ ሆዷ እስከሞላላት ድረስ ምንም ይጫኗት ምን ለምን ነው
የምጫነው? እንዴት? እምቢ! የሚባል የሞራልና መብት ጥያቄ የማታነሣ ፣ነገር የማይገባት ምስኪን እንስሳ ናት፡፡
እንግዲህ ከእነዚህ የአሕያ መገለጫዎች አንፃር የሰው ልጅ አሕያ
አይባልም እንጂ ነገር ግን ሰብእናቸውና ግብራቸው ይመስላልና እንበል ከተባለ በነዚህ ት/ቤቶች ውስጥ የተፈጸመውን
ነገር ዓይተን፣ የአሕያዋን መገለጫዎች ወደ ሰውኛ ለውጠን አሕያው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ መምህርነትና
ማስተማር ማለት እራሱ ምን ማለት እንደሆነና ማንን ምን እናስተምራለን? እንዴት እናስተምራለን? ለምን
እናስተምራለን? የሚሉ ሞራላዊና(ግብረ-ገባዊና) ሞያዊ ጥያቄዎችን ለራሳቸው አንሥተው ሳይመልሱና ሳይመረምሩ ጌቶቻቸው
አድርሱ ብለው የጫኗቸውን ወይም ያሸከሟቸውን ብቻ በዜጋ ዐይን ሳይመረምሩ ለጌቶቻቸው ጥቅሞች ፍጹም ታማኝ በመሆን
በቀጥታ በሕፃናቱ ላይ ለማራገፍ የፈለጉትና የሞከሩት መምህራን ተብዬዎች የዘመናዊው ቅኝ አገዛዝ (the modern
colonization) ባንዶችና ቅጥረኛ አገልጋዮች ናቸው እንጂ አሕዮቹ በሚገርምና በሚደንቅ መልኩ ገና በለጋና
በሕፃንነት እድሜያቸው የኛስ ከማን ያንሳል በሚል እሳቤ በራሳቸው ነገር የኮሩት፣ በዚህ እድሜያቸው የማንነትና
የክብር ነገር የገባቸው፣ይሄም ስለሆነባቸው ተሰምቷቸው ቋንቋቸውን ሙጥኝ ያሉቱ ሕፃናት እንዳልሆኑ ባለ አዕምሮ ወይም
ሙሉ የሆነ ዜጋ ሁሉ የሚረዳውና የሚመሰክረው እውነት ነው፡፡ እንዲያውም ስለ እውነት ከሆነ ሕፃናቱ ሽልማት
የሚገባቸው አርበኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ማንነታቸውንና ክብራቸውን የሚደፍርን ባንዳ ተጋትረዋልና ፡፡
እንደሚታወቀው ምዕራባዊያን በምንም ነገር ይሁን ከማንም የበለጥን
ነን ብለው ያስባሉና ይሄንን የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን በተለይ ቅኝ ይገዟቸው የነበሯቸው ሀገሮችንና ሌሎችንም
የራሳቸው የሆነ የማንነት መገለጫዎች እንበል የተሟሉ ቋንቋ ማለትም ባለ ፊደል እና አኃዝ ፣ ባሕልና ሃይማኖት
ወ.ዘ.ተ የሌሏቸውን ሀገሮች ከእነኝህ እሴቶች ከፊሎቹ ያሏቸውንም ሀገሮች ቢሆን ቅኝ ገዥዎቹ በቀላሉ ከቋንቋቸውም
ሌላ ባሕላቸውንና ለቅኝ ግዛታቸው እንደዋነኛ መሣሪያ ይጠቀሙበት የነበረውን ሥጋዊ ፈቃዳቸውን የሞሉበትን
ሃይማኖታቸውን በቀላሉ በመጫን የቅኝ ግዛታቸው ደዌ ሰለባ አድርገዋቸው ቀርተዋል፡፡ እንደነዚሁ ሀገሮችም ሁሉ
ሀገራችንንም ከነዚሁ ሰለባዎች አንዷ ለማድረግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ባንዳዎቻቸውን ወይም
አገልገዮቻቸውን(አሕዮችን) በመጠቀም ከሥራችን ነቅለው ለመጣል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማያደርጉትና ያላደረጉት ጥረት
የለም አልነበረም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን አንፃራዊ በሆነ መልኩ በእግዚአብሔር ቸርነት እስከ አሁን ከዚህ
አጋንንታዊና አሕያዊ ሸር ልንተርፍ ችለናል፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር ፊደል ከቆጠረው የማኅበረሰባችን ክፍል
ውስጥ እንግሊዝኛ ቋንቋን ማወቅ ብቻ በራሱ ሥልጣኔን መጨበጥ ማለት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ በዚሁ እረከረተው
ሌሎችን የትምህርት ወይም የሙያ ዓይነቶችን ቸል የሚሉና የሚተው ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ
እንግሊዝኛ ቋንቋን ብቻ አይደለም ሌሎችንም ቋንቋዎች ጠንቅቆ ማወቅና ልሣነ ብዙ (multilingual) ወይም
(polyglot) መሆን ቋንቋውን ከሚናገሩት ሰዎች ጋር ለመግባባት የእነሱ የሆነውን ነገር ለመረዳትና ለመጠቀምም
በጣም ይበጃል፡፡በአንፃሩ ግን እንግሊዝኛ ዐወቅን ማለት የሮኬት ሳይንስን (የውንጫፍ መጣቅን) ወይም የኑኩሊየር
ሳይንስን (የርእሰ-ኃይል መጣቅን) ዐወቅን ማለት አይደለም፡፡
አኀዛዊ መረጃውን ብዘነጋውም በታላቋ ብሪታንያ ውስጥ እንግሊዝኛ
ቋንቋ ቋንቋቸው ሆኖም ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ዜጎቻቸው ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑ ለኞቹ እንግሊዝኛ መናገር
የሥልጣኔ መጨረሻ ነው ብለው ለሚገምቱትና ሥፍራ ለሚጠባቸው ሰዎች እንግሊዝኛ ቋንቋ ማለት እንደሌላው ቋንቋ ሁሉ
ከቋንቋነት የማያልፍ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ይመስለኛል፡፡
አንድ ሌላ ማስገንዘቢያ ላንሣ ጃፓን እንሂድ በጃፓን
ዩንቨርስቲዎች(መካነ-ትምህርቶች) ውስጥ ካሉት ጃፓናዊያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች(ሊቆችና ሊቀ-ሊቃውንቶች) ወይም
ምሁራን አደራ ልሂቃን እንዳትሉ ልሂቃን ማለት ሽማግሎች ማለት ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ቃሉ መነገር የጀመረው
ማን እንደጀመረው አላውቅም ግሱ ለሀቀ ነው አደገ ጎለመሰ ማለት ነው ልሂቃን ማለት ደግሞ ሽማግሎች ማለት እንጅ
ሊቃውንት ማለት አይደለምና እንታረም፡፡ እናም በእነዚያ የጃፓን መካነ ትምህርት ከስንት አንድ ነው እንግሊዝኛ
ተናጋሪ የሚገኙት እነሱም በውጭ ቋንቋዎች ክፍለ ጥናት (foreign languages department) ውስጥ ያሉ
ሆነው ይገኛሉ፡፡ እነኝህ እንግሊዝኛ የማያውቁ ምሁራን ግን የራሳቸውን ቋንቋ በመጠቀም በሳይንስና ቴክኖሎጂ
(በመጣቅና ኪነ-ብጀታ) ሀገራቸውን የት እንዳደረሷት ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ አለማወቃቸው
ቅንጣት ታክል ከምንም ነገር አላገዳቸውም ጃፓንን በሀብቷና በቴክኖሎጂ (በኪነ-ብጀታ) እድገቷ ከአውሮፓ ሀገራት ልቃ
ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኝነት ደረጃ የምትገኝ ታላቅ ሀገር እንድትሆን አስችለዋታል፡፡
ይሄ ታዲያ የገዛ ቋንቋቸውን ንቀውና ትተው እንግሊዝኛ ብቻ
የሥልጣኔ መግቢያ በር ነው ብለው ለሚያስቡ ማስተዋል ለጎደላቸው ዜጎቻችን የሚያስቡት ነገር ልክ እንዳልሆነ
ሚያስተምረው ቁም ነገር አይኖርም ይሆን?፡፡ ለዚያውም እኮ ይሄ‹‹ሙጥኝ ያለ እሱ›› የሚሉለት ቋንቋ እኮ በራሱ
የተሟላ ቋንቋ አይደለም፡፡ ምን ለማለት ነው እንግሊዝኛ ቋንቋ የራሱ ሆሄያትና አኀዛት የሉትም ሆሄያቱን ከላቲን
አኀዛቱን ደግሞ ከዓረብ ወስዶ ነው እራሱን ሙሉ ለማድረግ የሞከረው፡፡ በቋንቋው ውስጥ ካሉት ቃላቶቹም ከ30 በመቶ
በላይ አንዳንዶች ከ60 በመቶ በላይ ነው ይላሉ ከሌሎች ቋንቋዎች ለቃቅሞ የሰበሰባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር
ባንዶች (አሕዮች) ሊያጠፉብን የሚታትሩበት ቋንቋችን ከማንም ምንም ሳይሰርቅ የራሱ የተሟላ ሆሄያትና አኅዛት ያለው
በመሆኑ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በለጠ ማለት አይደለምን? ይሄስ በመሆኑ አያኮራንምን? በዚህ የቀኑብን ምዕራባዊያን እኛን
ማለትም ሐበሾችንና የእኛ የግእዙም(የአማርኛው) ፊደላት የገቡት ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሰው ባሕር ተሻግረው ነው
ይላሉ፡፡ የግእዙ(የአማርኛው) መሠረታዊያን ፊደላቱ እነሱ የሳባዊያን የሚሏቸውን ፊደላት የያዙ በድንጋይ ላይ
የተቀረጹ ጽሑፎች በዓረብ ሀገሮች ተገኝተዋልና የግእዝ(የአማርኛ) ፊደሎች ምንጩ ደቡብ ዓረብ ነው ብለው ይናገራሉ፡፡
እርግጥ ነው የተባሉት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች በተባሉት ቦታዎች
ይገኛሉ፡፡ እነኝህ ጽሑፎች በእነዚህ ቦታዎች የመገኘታቸው ብቸኛ ምክንያት ወይም ምሥጢር ግን እነሱም ሆኑ ዓረቦች
ጠንቅቀው እንደሚያውቁት የዛሬን አያድርገውና ሀገራችን ኢትዮጵያ ኃያልና የግዛት ስፋቷ ከበስተምሥራቅ በኩል
የመካከለኛው ምሥራቅ የመንን ጨምሮ እስከ ሳውዲዓረቢያ አልፎም ወደታች እሰከ ህንድ ምን ህንድ ብቻ ከዚያም አልፎ
እስከ የቻይና የባሕር ጠረፍ ድረስ ከበስተምዕራብ በኩል ደግሞ ከጥንት የአውሮፓ ሀገራት የዓለም ካርታዎች መረዳት
እንደምንችለው አትላንቲክ ውቅያኖስን የኢትዮጵያ ውቅያኖስ የሚል ሥያሜ ማስያዝ የቻለችና ግዛቷም ያን ያህል የሰፋ
ስለነበረ ነገሥታቶቻችን አዋጅና ሌላ ንጉሣዊ ወይም መንግሥታዊ መልእክት ለማስተላለፍ ሲሉ እነዚያ ጽሑፎች በድንጋይ
ላይ ሊጻፉና ከዚህም የተነሣ ጽሑፎቹ ሀገራችን ስትገዛቸው በነበረቻቸው አካባቢዎች ሊገኙ ቻሉ፡፡ የሆነ ሆኖ
ምዕራባዊያኑ መሠረታዊያኑ 29(26) የግእዝ ፊደላት ኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጠሩም አሉ እንጅ እናንተ
አልፈጠራቹሀቸውም አላሉም፡፡ እኛን እራሳችንን ፊደሎቻቹህን ይዛቹህ ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሳቹህ ገባቹህ አሉ እንጅ፡፡
ምዕራባዊያኑ ሀቁ ተሰውሮባቸው ነው የሚል እምነት የለኝም ነገር
ግን ኢትዮጵያን በተመከተ ነገር ሁሉ ውስጣቸውን በሚያቃጥለው ሰይጣናዊ ቅናት የተነሣ እንኳንና ሊመስል የሚችል
ምክንያትና ሰበብ አግኝተው ቀርቶ ሆን ብለው የፈጠራ መረጃ በመፈልሰፍ የኛ የሆነን ነገር ሁሉ ከእኛ የማራቅ አባዜ
እጅጉን ስለ ተጣባቸው እንጅ፤ አሁን በዚህ ዘመን ደግሞ በዓለምአቀፋዊነት ወይም በሉላዊነት
(Globalization) እንቅስቃሴ አሳበው በሚያደርጉት የባሕል ወረራ ዘመቻ ይሄንን የቀኑበትን ቋንቋችንን
ከነፊደላቱ ሌሎች የማንነት መገለጫዎቻችንን ሁሉ ደብዛውን ለማጥፍት እየጣሩ እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ
ነው፡፡
በመሆኑም ያን የመሰለ ድንቁርና የፈጸማቹህ መምህራንና ተመሳሳይ
አመለካከት ያላቹህ ግለሰቦች ሆይ ‹‹አሕያ›› የሚባለው እምቢ ለክብሬ ፣እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ፣ለማንነቴ፣እምቢ
ለሀገሬ የሚለው ከራሱ ግላዊ ጥቅሞች ወይም ከሆዱ ይልቅ ለሀገሩ፣ ለማንነቱ፣ ለክብሩ፣ለነፃነቱ፣ ለታሪኩ ለድንበሩ
ቀናዒ የሆነና የእነዚህ ሀብቶቹ እሴቶቹ ነገር የሚከነክነው የሚያንገበግበውና ዕረፍት ሚነሳው ባለአደራነት የሚሰማው
ተዋርዶ ከመጥገብ ይልቅ ተርቦ መኩራትን የሚመርጠው የሰብአዊ ባሕርይ መገለጫ የያዘው ነፃና ኩሩ ዜጋ፣ ኩራት እራቴ
የሚለው የሀገር ልጅ ሳይሆን ከሀገሩ ከራሱ ከማንነቱ ጥቅሞች በተፃራሪ የቆመ፣ ለባዕድ ወይም ለጠላት ጥቅም ያደረ ፣
የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ብሎ ነገር የማይገባው ፣ማንነት ክብር ነፃነት ሳይል እንደ እንስሳ ሆዱን ብቻ በማሰብ
ሆዱን እስከሞሉለት ጊዜ ድረስ የጫኑትን ሁሉ የሚጫን ያሸከሙትን ሁሉ የሚሸከም፣ ፋሽስት እንደፈለገ እንዳሻው
ሲገጥበው የኖረው አሁንም የእነሱን የጌቶቹን ጥቅም ለማስጠበቅ ሀገርና ሕዝብን እጅግ የሚያሳዝነው፣የሚያኮራውንና
የሚያሳፍረውን መለየት የማይችል፣የማንነት የክብር፣ የነጻነት፣ የሀገር፣ የድንበር፣ የታሪክ ነገር የማይገደው
የማይሰማውና ማይገባው፣ በፍርፋሪውም በምኑም የሚደልሉት እንስሳዊ ባሕርይ ያለው የባዕድ ወይም ለጠላት ባሪያ
አገልጋይ (ባንዳ) ነው “አሕያ” የሚባለው እሽ? አወ እሱ ነው አሕያ ማለት፡፡ እሽ አላቹህ? አዋ እንደሱ ነው
ጎሽi እንዲህ አድርጌ ፈትፍቸ አስረድቸ ካልገባቹህማ ይሄ የማንነታቹህ ጉዳይ ነው ማለት ነውና አዝናለሁ ምንም
ላደርጋቹህ አልችልም እግዚአብሔር ይርዳቹህ ልቡናቹህን ያብራላቹህ አሜን አሜን አሜን፡፡
amsalugkidan@gmail.com
googlgule
No comments:
Post a Comment