Tuesday, October 22, 2013

ዶ/ር መረራ የፍንዳታውን ዜና “እንጠራጠረዋለን” አሉ


"በአዲስ አበባው ፍንዳታ የሞቱት ኢትዮጵያዊያን ናቸው"

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ሰፈር የደረሰውን ፍንዳታ አስመልክቶ ኢህአዴግ ያሰራጨውን ዜና የሚቃረኑ መረጃዎችና አስተያየቶች ቀረቡ። ለኢህአዴግ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ አስተያየት ሲሰጡ ዶ/ር መረራ “አትፍቶ ጠፊ አጥፍቶ ይጠፋል እንጂ በሜዳ ዝም ብሎ አያጠፋም” ሲሉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ በፍንዳታው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ናቸው ሲል ስም ገልጾ የኢህአዴግን ዜና አጠጥሎታል።
በፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቁት ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚታሙ ፓርቲዎች “የጸረ ሽብርተኞች አዋጅ ሊጠናከርና ሊጠብቅ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የኢራፓ፣ የኢሴዳፓ፣ ቅንጅትና አዲአን ተወካዮች በየተራ የኢህአዴግን ዜና የሚቃወሙና በጥርጣሬ የሚመለከቱትን አውግዘዋል። በወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያውም አንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ ጠርተውት በነበረው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ “የጸረ ሽብርተኛነት አዋጅ ለሌላ ተግባር መዋሉን እንቃወማለን” በማለት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ በማሳየት ዜናውን ለማጀቢያነት ተጠቅሞበት ነበር።
በግል አስተያየታቸውን የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው “ብዙዎች፣ እኔም ጓደኞቼም በጥርጣሬ ነው ያየነው” ሲሉ ከተቆረጠው ንግግራቸው ተደምጧል። ዶ/ር መረራ “አጥፍቶ ጠፊ አጥፍቶ ይጠፋል እንጂ በሜዳ ዝም ብሎ ራሱን አያጠፋም” ካሉ በኋላ “ስለዚህ እውነት ተደርጓል?” የሚለው ትልቁ ችግርና የጥርጣሬው መነሻ እንደሆነ አመልክተዋል።
ስለዚህ በሚል ድምዳሜ “ሰው አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ለራሱ ፖለቲካ ብሎ የሚያደርገው ያው የለመደው ስራ ነው” እንደሚል ዶ/ር መረራ በተቀነጨበው አስተያየታቸው ሲናገሩ ተሰምቷል። በተቃራኒ ከላይ በስም የተዘረዘሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ኢላማና የአልሸባብ ስጋት ላይ ያለች አገር በመሆኗ ኢህአዴግ ህዝብን የመጠበቅና ደህንነትን የማስጠበቅ አደራ ስላለበት እነሱን ጨምሮ እንዲጠብቃቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሙ የሚነሳውና በታጣቂ ሃይሉ ፈርጣማነት የሚታወቀው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  /ትህዴን/ በቦሌ ክፍለ ከተማ በቤት ውስጥ ፈነዳ በተባለው ፈንጂ ህይወታቸው እንዳለፈ የተገለጸው ሁለት የሶማሌ ዜጎች አይደሉም ሲል ከሁሉም ወገን የተሰራጨውን ዜና በዜሮ አጣፍቶታ። በፈንጂው የሞቱት ሁለት ሰዎች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ስማቸውም “ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ መላኩ የተባሉ የፖሊስ አባልና አቶ ሞገስ አስቻለው የተባሉ ሲቪል ናቸው” ሲል የገለጸው ትህዴን የሟቾቹ ስም በመታወቂያ መረጋገጡን አመልክቷል።የመታወቂያውን ቅጂ ግን በገጹ አላተመም። ከአደጋው ጋር በተያያዘ በስፍራው ታይታችኋል በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰራቸውን በመግለጽ የሶስት እስረኞችን ስም ይፋ ያደረገው ኦክቶበር 19 ቀን 2013 በራሱ ኦፊሳላዊ ድረገጽ ላይ ነው። ኢህአዴግም ቢሆን ሞቱ የተባሉትን ሰዎች ይህ ዜና እስከተጻፈበት ቀን ድረስ በሰነድ አስደግፎ አላቀረባቸውም።
በሌላ በኩል ኦክቶበር16 ለንባብ የበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 3ቀን 2006ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ማዞሪያና ቦሌ ሚካኤል መግቢያ አካባቢ በቦምብ ፍንዳታ ሕይወታቸው ያለፈው ሁለት ሶማሊያውያን ሽብርተኞች መሆናቸውን ማረጋገጡን፣ የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስታወቁን ዘግቧል።
የአንድ ግለሰብ ሰርቪስ ቤት ተከራይተው ከነበሩት ሶማሊያውያኑ መካከል፣ አንደኛው ከ20ቀናት በላይ የቆየ ሲሆን፣ ሌላኛው ፍንዳታው ከመድረሱ ከሁለት ሰዓታት በፊት የደረሰ መሆኑን ግብረ ኃይሉ ማረጋገጡን ያመለከተው ሪፖርተር ሽብርተኛ የተባሉት ሶማሊያውያኑ ካፈነዱት ቦምብ በተጨማሪ መጠናቸው ያልተገለጸ ቦምቦችና አንድ ሽጉጥ ከሁለት ካርታ ጥይት ጋር መገኘቱን፣ የፈንጂ ማቀጣጠያና የአደጋ መከላከያ ጃኬቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያና ቀበቶዎች መገኘታቸውም ጠቁሟል፡፡ ከሶማሊያውያኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎችና የቤቱ አከራይ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄባቸው መሆኑንም ግብረ ኃይሉ አክሏል በማለት ሪፖርተር ዘግቧል። አዲስ አድማስ በበኩሉ አልሸባብ ለጥቃቱ ሃላፊነት መውሰዱን አድራሻው አልተመዘገበ የትዊተር ማረጋገጫ በማመላከት ከዚህ በታች ያለውን ዜና አስነብቧል።
ባለፈው እሁድ በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ከደረሰው ፍንዳታ ጋር ተያይዞ ሁለት ተጨማሪ የፍንዳታ ጥቃት ለማድረስ አልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ቡድን እንደዛተ የገለፀው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ የዛቻው ተአማኒነት ባይረጋገጥም በኢትዮጵያ የሚገኙ አሜሪካዊያን ጥንቃቄ እንዳይለያቸው ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ በመግለጽ ዜናውን የከፈተው አዲስ አድማስ፣ “የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ቡድኖች ግጥሚያ በሚካሄድበት ሰዓት ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ሁለት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በማወጅና ሽብር ለመፈፀም በመዛት የሚታወቀው አልሸባብ “ድርጊቱ በኔ አባላት የተፈፀመ ነው” ብሏል በማለት አልሸባብ በቦሌ ሚካኤል ለተከሰተው ፍንዳታ ሃላፊነት እንደሚወስድ በትዊተር እንዳስታወቀ ማሰራጨቱን፤ በፒያሳና በቸርችል ጐዳና አካባቢ የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እንደዛተም ገልጿል፡፡
በቦሌ ሚካኤል በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተከሰተው ፍንዳታ ሁለት የሶማሊያ ተወላጆች መሞታቸውን የገለፀው ፖሊስ፤ ከሟቾቹ አንዱ የኢትዮጵያ ማሊያ በመልበስ ከኳስ ተመልካቾች መሃል የፍንዳታ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀ እንደነበር መጠቆሙን አዲስ አድማስ በዜናው አውጇል። አዲስ አድማስም ሆኑ ሪፖርተር ፖሊስ የነገራቸውን ከመዘገብ ውጪ ከሌሎች ሚዲያዎች፣ በተለያዩ ማህበረ ገጾችና በቅርበት ከህብረተሰቡ የሚሰጡትን አስተያየቶች አስመለክቶ ዜናውን ላቀበላቸው ክፍል አላቀረቡም።
የኢህአዴግ አንደበትና የንግድ ድርጅት የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የደረሰው የፈንጂ ፍንዳታ በሁለት ሶማሊያውያን አሸባሪዎች የተፈፀመ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩን ጠቅሶ አስታውቋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳለው ፍንዳታው የደረሰው በክፍለ ከተማው ወረዳ 01 ቀበሌ 01 በተለምዶ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በአንድ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ነው። ፖሊስ ፍንዳታው ፈንጂ መሆኑንና በጥቅም ላይ የዋለው ቲ ኤም ቲ የተባለ የፈንጂ ዓይነት መሆኑን እንደደረሰበት አረጋግጧል። ፍንዳታውንም ሁለት ሶማሊያውያን ማቀነባበራቸውን ፖሊስ እንዳረጋገጠና ግለሰቦቹ የአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ አባል መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መገኘታቸውን ጄኔራል አሰፋ አብዩ መናገራቸውን የጠቆመው ፋና ከሁለቱ አሸባሪዎች መካከል አንደኛው ወገቡ ላይ የታጠቀና ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር የተዘጋጀ መሆኑን ያመላክታል ብሏል።
ሌላኛው አሸባሪ በሻንጣ ፈንጂ የያዘ ሲሆን፥ የፈነዳውም ፈንጂ በሻንጣው ውስጥ የነበረ መሆኑን ነው ጀነራል አሰፋ ያስረዱት። ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር ሲዘጋጅ የነበረው ግለሰብ የታጠቀው ፈንጂ ግን እንዳልፈነዳ አመልክተዋል። አሸባሪዎቹ በአጠቃላይ ሶስት ፈንጂዎችንም ይዘው ነበር። አሸባሪዎቹ ህዝብ ባለበት ስፍራ አደጋ ለማድረስ ተከራይተው በነበሩበት ቤት ውስጥ ሲዘጋጁ ፍንዳታው ደርሷል ብሎ ፖሊስ እንደሚጠረጥር ነው የጠቆሙት። ከአሸባሪዎቹ ጋር ፖሊስ የእጅ ቦምቦችንና ሽጉጥ ከነጥይቱ አግኝቷል።
የፋናን ዜና ተንተርሶ የተሰነዘሩ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት ሪፖርተር በፈነዳው ፈንጂ ህይወቱ ያለፈው አንደኛው ሰው ሰውነቱ መበታተኑና የአይን እማኞችን ገልጾ መዘገቡን ያስታውሳሉሉ። ፈነዳ የተባለው ፈንጂ ከፈነዳ በሁዋላ አጥፍቶ ለመጥፋት የተዘጋጀው ሰው የታጠቀው ፈንጂ አለመፈንዳቱ መገለጹ ከሙያ አንጻር ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ፣ ከዚህም በላይ ድርጊቱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጋር ለማገናኘት የብሔራዊ ቡድን መለያ ሹራብ ተገኘ መባሉ ድርጊቱን ድራማ ያስመስለዋል ባይ ናቸው። (ፎቶ: ሪፖርተር)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment