Thursday, October 24, 2013

በምእራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አጅላ ዳሌ እና አዋዲ ጉልፉ የሚኖሩ አማራዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን አሉ


  Amhara people(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አጅላ ዳሌ እና አዋዲ ጉልፉ የሚኖሩ አማራዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን ሲሉ መግለፃቸው ተዘገበ፡፡
ነዋሪዎቹ “ከ1200 በላይ አባወራ ስንሆን፤ ከአስር ሺህ በላይ ነዋሪዎች በሞትና በአደጋ ውስጥ እንገኛለን” ሲሉ ስጋታቸውን መግለፃቸውን ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ በዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም እትሙ ዘግቧል፡፡
የችግሩ ሰለባ ከሆኑት አርሶአደሮች መካከል አቶ አድማስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደማንኛውም የአካባቢ ነዋሪ የእርሻ መሬት ተሰጠን፣ግብሩን እየከፈልን ለልማት የሚፈለግብንን እያዋጣን በማንኛውም በማኀበራዊ ጉዳይ እንኖር ነበር፤ ይሁን እንጂ በ2001 ዓ.ም የመሬት ባለቤት ደብተራችችንን ሰበሰቡ፡፡ ይህንንም ለምንድነው? ብለን ስንጠይቅ፤ አማራ የሆነ ሰው የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር መያዝ አይችልም አሉን፡፡ ከመጋቢት 22 ቀን እስከ ሰኔ 20 ቀን 2005 ዓ.ም የአማራውን መሬት እየነጠቁ ለኦሮሞ ወጣቶች አደሉ በዚህም የአማራ ወጣት መሬት አይሰጠውም፡፡ እኛም ይህንን በመቃወም ምን ሰርተን እንብላ፤ እኛ ዜጋ አይደለንም ወይ? ብለን ብንጠይቅ የተለያየ ጥቃት ተፈርዶብናል ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
አርሶአደሩ አያይዘውም ፤ በተለይ መስከረም 4 ቀን 2006 ዓ.ም ወጣቶችን በማደራጀት ህዝቡን አስጨፈጨፉት ጉዳት ከደረሰባቸውም መካከል አቶ ክብረት ጌጡ የተባሉ የ6 ልጆች አባት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ ባለቤቱና ልጆቹም እስካሁን ያለአንድ እረዳት ባዶ ሜዳ ላይ ቀርተዋል ማለታቸውን ጋዜጣው ለንባብ አብቅቷል፡፡
በተመሳሳይም 24 ሰዎች በዱላና በካራ ተጎድተው የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል በደሎችን የሚፈፅሙት የወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች እንደሆኑና፤ ይህንንም ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ቢያመለክቱም መፍትሄ እንዳላገኙ ጋዜጣው አስነብቧል፡፡

zehabesha

No comments:

Post a Comment