Thursday, October 24, 2013

ፍራንክፈርት፣ ሳዋ ፣ሳሃራ ፣ ሜዲትራንያን፣ ላምባዱሳ


በልጅግ ዓሊ
ይህ የሆነው ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ ነው። ወቅቱ በጋው ላይ ነው። እንደ አብዛኛው የአውሮፓ
ከተማዎች የፍራንክፈርት ውበት በበጋው ደመቅ ያለ ነው። በእንደዚህ ደስ በሚል ቀን ከትልቁ ባቡር ጣቢያ
ተነስቼ ሃብትቫኸ(Hauptwache) ወደሚባለው የከተማው ማዕከል ከዚያም አልፌ በእግር መጓዝን
እወዳለሁ። በጉዞዬ ወቅት በስተጎን እያለፍኩት የምሄደው ካይዘር መንገድ(Kaiserstraße) በመባል
የሚታወቀው የሴተኛ አዳሪዎች መንደር አለ። እዚህ መንገድ አካባቢ ተኮልኩለው የሚውሉትን ዕጽ
ተጠቃሚዎች በጎን እየገላመጥኩና የስልጣኔን በሽታ እያወገዝኩ አልፋለሁ።
Hauptwache3
እነሱን አልፌ ሴተኛ አዳሪዎቹ ከሚገኙበትን ፎቅ ስደርስ የተለመደውን ግር ግር ማየት ደስ ይለኛል።
ሴቶቹን ፍለጋ ፎቁን ለመውጣት የሚራወጠው ጎረምሳና አንዳንዴም የሽማግሌ ችኮላ የማያቋርጥ የሁል ጊዜ
ክስተት ነው። ገና ጀርመን እንደመጣን ለማየትም ይሁን ለሌለ ነገር በዚህች ፎቅ ዙሪያ ያልተመላለስን
አልነበረም። የተለያዩ ሃገር ሴቶች በሚማርክ ሁኔታ ደንበኛ ሲጠብቁ ማየት የሚገርም ነው። ገንዘብ ቀንሺ፣
የለም አንተ ጨምር፤ ክርክሩ አይጣል ነው። በምንም ቋንቋ የማይግባቡ የሁለት አህጉር ሰዎች በምልክት
ተግባብተው አንሶላ ተጋፈው በትንሽ ደቂቃ ይለያያሉ። ተግባራዊ ንቅናቄ እንጂ ንግግር የለም። በገንዘብ
የተስማማው ጭልጥ ብሎ ክፍሉ ውስጥ ሲገባና ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ላብ ጠምቆት የግንባሩን ላቦት
እየጠረገ ፈትለክ ብሎ ለማምለጥ የሚደርገው ሙከራ ሲገባ አንበሳ ሲወጣ ድመት ያስመስለዋል። ጥድፊያው
ከበዛበት የአውሮፓ ኑሮ ጋር እንኳን ሲወዳደር ካይዘር መንገድ ላይ ከሁሉም የበለጠ ጊዜ ወርቅ ነው።
ሰውየው ከወጣ በኋላ እመቤቲቱ ተሽሞንሙና እንደገና ከሌላው ጋር መደራደር ትጀምራለች። ይህ ሁሉ
በሃብታሙ የጀርመን ሃገር በሕግ ተፈቅዶ የሚደረግ አይመስልም።
ከፎቆቹ በታች ደግሞ እየተከፈለ የሚታይ ራቁታቸውን የሚደንሱ ቆነጃጅቶች አሉ። እነዚህን ማየት
የሚያዘወትሩት በብዛት ግዜ ያለፈባቸው ሽማግሌዎች ናቸው። ልብ ብሎ ለተመለከታቸው ሽማግሌዎቹ እኛ
ካረጀን ምን ዓይነት ሰውነት ተፈጥሮ ይሆን? ብለው ይህኑን አዲስ ሰውነት በማየት ልጅነታቸው ይመለስ
ይመስል ጠዋት ማታ ይመላለሳሉ።
ይህን ሁሉ ቲያትር ሳይመለከት ሻንጣ እየጎተተ ወደ ከባቡር ጣቢያ የሚነጉድ መንገደኛ ደግሞ ባቡር
እንዳያመልጠው ይኳትናል። እኔም ይህንን ሁሉ እየታዘብኩ የተለመደ ጉዞዬን እቀጥላለሁ። ፍራንክፈርት
በየዓመቱ ትለወጣለች። ሕንጻዎቹም እኛ ስንመጣ እንደነበሩት አይደሉም። ቁመታቸው እያደገ፣ ጥራታቸው
እየጨመረ መሄዱ የሚገርም ነው። የስራ መስኮችም በዚያው ልክ ይከፈታሉ። የውጭ ዜጋው ቁጥርም
ከሥራው መስክ ጋር አብሮ ይጨምራል።
ከሌሎች ከተሞች የሚገኙ ዜጎቻችን ሥራ ፍለጋ ወደ ፍራንክፈርት በመምጣታቸው የዜጎቻችንን
ቁጥር በዚያው ቀጥር እያበዛው መጥቷል። ከቁጥራችን መብዛት የተነሳ እንኳን የሩቁን፣ ከቅርብ ጎረቤቶቻችን
ጋር መነጋገር ተስኖናል። ከመብዛታችን የተነሳ መንገድ ላይ ስንተያይ ሰላም መባባል ከቆመ ስንበትበት ብሏል።
እንዲውም የቆየና አዲስ መጤ የሚ’ለይበት በሰላምታ ሆናል። የቆየው የስደተኛ ጉዳዩ ስለተፈጸመለት
የማያውቀውን ሰው ሰላም ማለቱን ትቶታል። አዲሱ ግን የሃገሩን ልጅ ወገኑን ሲያይ ብቸኝነቱ የሚቀልለት፣
ችግሩም የሚፈታለት፣ እየመሰለው ሰላም ማለት ያበዛል።
እኔ ግን ገና እንደ አዲስ መጤ ነው የሚያደርገኝ። ሰላም ሳልል ማለፍ አሁንም አይሆንልኝም።
እንኳን የሃገራችንን፣ የአህጉራችንንም ዜጎችን አላልፍም። እንዲውም በሰላምታዬ ግራ ተጋብተው የት ነው
የምናውቀው ብለው ለሚጨነቁት የተደጋገመ ሰላምታ እሰጣለሁ። በመርሳታቸው ራሳቸውን እንደ ጥፋተኛ
ቆጥረው ዓይናቸውን እስከሚያጥፉ ድረስ ትክ ብለው የሚያዩኝ ጥቂት አይደሉም።
ከዕለታት በአንዱ የተለመደ ጉዞዬ ላይ ወጣት የሆነ ዜጋችንን ሰላም አልኩት። ፈገግ ብሎ ጠጋ አለኝ።
ሁኔታው ከዚህ ቀደም የሚያውቀኝ መሆኑን ያሳብቃል። ዘንግቸው ይሆን? አሁን ጉድ ፈላ። አሁን የት ይሆን
የሚያውቀኝ? እኔው ራሴ ግራ ተጋባሁ። ሰላምታ ተለዋውጠን መንገዳችንን አንድ አድርገን ጉዟችንን ቀጠልን።
“እዚሁ ፍራንክፈርት ነው የምትኖረው?’’¤የኔ ጥያቄ ነበር።
“አይደለም አብረን ነው የምንኖረው ያወቅከኝ መስሎኝ ነው’ኮ።’’¤ረጋ ብሎ መለስ።
“ኦ ይቅርታ ዘንግቼ ይሆናል።’’ እንደ ሃፍረት ተሰማኝ። ማፈሬን አውቆብኝ በፈገግታ አበረታታኝ።
“ሰፈር ሁልጊዜ መንገድ ላይ ሰላም ስለምትለን የለየኸን መስሎኝ ነበር።’’
አሁን ገባኝ። የምኖርበት አካባቢ ከሚገኘው ቡና ቤት ደጃፍ ላይ በበጋው ተሰብስበው ከማያቸው
ወጣቶች መሃል ነው። “ይቅርታ ብዙ ስለሆናችሁ አልለየኋችሁም። ሁል ጊዜ ቡና ቤቷ ጋ ተሰብስባችሁ
ሳያችሁ ከእናንተ ጋር ተቀምጬ መጫወትን እፈልጋለሁ ግን እንዳልደብራችሁ በሚል ስጋት. . .’’ብየ የት
እንደምንተዋወቅ ሲገባኝ በድፍረት ቀጠልኩ።

zehabesha

No comments:

Post a Comment