Monday, October 28, 2013

የአብርሃ ደስታ በፌስቡክ ላይ የተለቀቁ ምርጥ የሳምንቱ ጽህፎች


ከዉቅሮ የደረሰኝ መረጃ

Abrham Destaባለፈው ቅዳሜ ዓረና ፓርቲ በዉቅሮ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ህወሓቶች ትናንት እሁድ በዉቅሮ ሰለማዊ ሰልፍ መጥራታቸው ይታወቃል። ዛሬ ሰኞ ደግሞ ለዉቅሮ ህዝብ (በህወሓት ዘመን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ) ፊኖ፣ ስንዴ፣ ሱኳርና ዘይት እንደጉድ እያደሉ ይገኛሉ።
በዉቅሮ ከተማ ለህዝብ ፊኖ ዱቄትና ዘይት ለህዝብ ሲታደል የማስታውሰው በደርግ ግዜ ነበር። ደርጎች የትግራይን ህዝብ ወንበዴዎችን እያገዘ ሲያስቸግራቸው በሆዱ ለመደለል ፊኖና የምግብ ዘይት ያድሉት ነበር። ግን አልተሳካላቸውም፤ ምክንያቱም ሰው (ምግብ ማግኘቱ ጥሩ ቢሆንም) ለዓላማ እንጂ ለሆዱ አይኖርም። የትግራይ ህዝብም በሆዱ አልተገዛም። የትግራይ ህዝብ ብዙ መስዋእት የከፈለበትን ትግል በግለሰቦች ተጠልፎ የነፃነት ዒላማው ስቶ ለስልጣን ቢውልም በምግብ ተሸውዶ ትግሉ አላቋረጠም።
ህወሓቶችም ከደርግ ጋር ተመሳሰሉብኝ። የዉቅሮ ህዝብ ከመቼ ጀምሮ ነው ፊኖና ዘይት የሚታደለው? ይህ የፈራ መንግስት ምልክት ነው። ግን ጥሩ ነው። ዓረና ትናንት በዉቅሮ ከተማ ስለተንቀሳቀስን ዛሬ ምግብ እየታደለ ነው።
እንቅስቃሲያችን እንዲህ ዉጤታማ ከሆነ ወደ ሁሉም የትግራይ ወረዳዎች በተመሳሳይ መልኩ መንቀሳቀስ አለብን ማለት ነው። ህዝቡ የፊኖ ዱቄትና የምግብ ዘይት (የደርግ ዓይነቱ) እንዲሰጠው።

ትንሽ ስለ ዳዊት ከበደ

ይድረስ የዳዊትና የአብርሃ ጉዳይ ለምታመሳስሉ
የአውራምባታይምስ ጋዜጣ ኢዲተር ዳዊት ከበደ ከስደት ኑሮ ወደ ሀገሩ ተመልሷል አሉ (ከፌስቡክ ሰማሁ)። ዳዊት ለስደት የተዳረገው በምን ምክንያት ነበር? በኢትዮዽያ ዉስጥ መስራት አስቸጋሪ ስለሆነበት ነው ? ወይስ የዉጭ ሀገር ህይወት ስላማረው ነው? ተገቢ መልስ ያስፈልገዋል። ላሁን ግን የተባለውና የሰማነው እንውሰድ። ዳዊት ከሀገሩ የተሰደደው የኢህአዴግ መንግስት አላሰራ ስላለው ነው።
መንግስት አላሰራ ሲለው ከሀገር መውጣቱ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ያኔ የመንግስትን ዓፈና ፈርቶ ወጣ፤ አሁን ደግሞ በሆነ ምክንያት (ወደ ሀገሩ የተመለሰበት ትክክለኛ ምክንያት በትክክል ስለማላውቅ ነው) ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ስለዚህ መሄዱም ትክክል ነው፣ መመለሱም ትክክል ነው። ምክንያቱም ይህ ጉዳይ የሚወሰነው በራሱ በዳዊት ነው። ከሀገር የወጣበትና ተመልሶ የገባበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ዳዊቶም እንኳን በደህና መጣህ።
ስለ ዳዊት ጉዳይ ለመፃፍ የተገደድኩበት ምክንያት “አብርሃ ደስታስ ከዳዊት ከበደ ምን ይማራል?” የሚል ሐሳብ ስለተነሳ ነው። ስለዚህ የዚህ ፅሑፍ ዋና ቁምነገር ስለ ዳዊት ከበደ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ስለ አብርሃ ደስታ ነው።
ዳዊት ኢትዮዽያ ዉስጥ እያለ ገዢውን ፓርቲ የሚተቹ ፅሑፎች በማሳተም ይታወቃል። በንዲህ ዓይነት ፅሑፍ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለእስር ተዳርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው። እንደሰማነው መንግስት ስጋት ስለፈጠረበት ከሀገር ወጣ። እስካሁን የሰራው ጥፋት የለም። ከሀገር ከወጣ በኋላ ዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉለት። አሁንም ችግር የለውም። ምክንያቱም ኢህአዴግን ለሚተች ሰው አቀባበል ማድረግ ምን ይደንቃል?! ምክንያቱም እነሱም ተቃዋሚዎች ናቸው።
ከተወሰነ ግዜ በኋላ ዳዊት ከዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ተጣላ። ዳያስፖራው ዳዊትን ለማጥላላት ሞከረ። ዳዊትም ስለነሱ መጥፎነት ነገረን። ከዛ ዳዊት “ዓቋሜን እንደገና ለመፈተሽ ተገድጃለሁ” ብሎ ወደ ሌላኛው ጎራ አዘነበለ። ወደ ሀገሩ ገባ። “ዳዊት ከኢህአዴግ ጋር ታርቋል” የሚል ጥርጣሬ መጣ (ከተቃዋሚዎች)። “ከኢህአዴግ ጋር ታርቋል” የተባለበት ምክንያት የተቃዋሚ መሪዎች መተቸት ስለጀመረ ነው (ምክንያቱም ዳዊት ከኢህ አዴግ ሲታረቅ ወይ ሲፋታ አላየንም)። ቀጥሎም ዳዊት አቋሙ የቀየረበትና ወደ ሀገሩ ለመግባት የወሰነበት ምክንያት ዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ብሄር ተኮር (የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ) የሆነ የማጥላላት ዘመቻ ስለከፈቱበት ነው ተባለ (በትግራይ ተወላጆች)።
ብዙ የትግራይ ተወላጆች እንደሚገምቱት ዳዊት ከበደ ከሀገር ሲወጣ “የጀግና አቀባበል” ያደረጉለት ለራሳቸው ስለሚጠቅማቸው ነው። በኋላ እነሱን በአሉታ የሚነካ ሐሳብ ሲያነሳ ግን ብሄሩን ጠቅሰው ማጥላላት ጀመሩ። ስለዚህ እነሱ የሚያመኳሹት ሰው ለራሳቸው ዓላማ ለማሳካት የሚረዳቸው ሰው ብቻ ነው። ከተጠቁሙት በኋላ ያጥላሉታል ወዘተ ብለው ያስባሉ።
ከዚህ ተነስተው የአብርሃ ደስታ ነገር ከዳዊት ከበደ ጉዳይ ያገናኙና “አብርሃም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይደርሰዋል” ብለው ያስባሉ። አብርሃ ደስታ ከዳዊት ከበደ መማር እንዳለበትም ይመክራሉ። በዚህ ጉዳይ አስተያየት ልስጥ።
በመጀምርያ ዳዊት ከበደ ጋዜጠኛ ነው። የኢህአዴግ መንግስት ለነፃ ጋዜጠኞች እንደማይመችና ብዙ ችግር እንደሚያደርስ እናውቃለን። ስለዚህ ዳዊት ከሀገሩ ሲሰደድ ምክንያት አለው። ዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም ይህን የጋዜጠኞች የሀገር ዉስጥ ችግር ተረድተው ለዳዊት ጥሩ አቀባበል ማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ምክንያቱም ስደት ከባድ ነው፤ ወገኖቻችንን መተባበር አለብን።
ዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የዘነጉት ነገር ግን አለ። ዳዊት ከበደ ጋዜጠኛ እንጂ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ አይደለም። አንድ ጋዜጠኛ ያገኘውን መረጃ ቢጋለጥ ለህዝብ ይጠቅማል ብሎ ያመነበትን ማንኛውም ነገር ለህዝብ የማድረስ መብትም ግዴታም አለበት። ጋዜጠኛ ገዢውን ፓርቲ የሚተች ወይም የሚያወድስ ነገር ሊፅፍ ይችላል። አንድ ጋዜጠኛ ገዢውን ፓርቲ ስለነቀፈ የተቃዋሚዎች ደጋፊ ነው መባል የለበትም። ተቃዋሚዎች ስለነቀፈም የገዢው ፓርቲ ሰላይ ነው ማለት የለብንም። አንድ ገለልተኛ ጋዜጠኛ መወቀስ ያለበትን ይወቅሳል (ገዢውም ተቃዋሚውም)።
እኛን ሲያወድስ እውነተኛ ጋዜጠኛ፣ እኛን ሲተች ደግሞ ቅጥረኛ ሰላይ … የምንለው ከሆነ ስለ ጋዜጠኝነት ያለን ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። ዳዊት ኢትዮዽያ ዉስጥ እያለ ብልሹ ያለውን የኢህአዴግን አሰራር ያጋልጥ ነበር። ዉጭ ሲሄድ ደግሞ ብልሹ ያለውን የዳያስፖራ ተቃዋሚዎችን አሰራር ቢያጋልጥ ምንድነው ችግሩ? ስለዚህ ጋዜጠኛ እስከሆነ ድረስ የፈለገውን የመፃፍ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። በዳዊት ላይ የተፈፀመ የማጥላላት ዘመቻም ትክክል አይደለም።
ወደ ዳዊት ልመለስ። ዳዊት ጋዜጠኛ ነው ብለናል። ጋዜጠኛ ከሆነ ታድያ ለምን በዳያስፖራዎች የማጥላላት ዘመቻ ተሸበረ? ዳያስፖራዎች ሲነቅፉት ለምን ሌላኛው ጥግ ያዘ? ጋዜጠኛ ከሆነ ለምን “አቋሜን ለመፈተሽ ተገድጃለሁ” አለ? የትኛው አቋሙ ነው የሚፈትሸው? የፖለቲካ አቋም አለው ወይ ነበረው ማለት ነው? የአንድ ጋዜጠኛ አቋም የጋዜጠኝነት ሙያ ማክበር ነው መሆን ያለበት። ሌላ ሊፈተሽ ወይ ሊቀየር የሚችል አቋም ካለው እሱ ጋዜጠኛ ሳይሆን ፖለቲከኛ መሆን አለበት። ጋዜጠኛ ሁኖ ሳለ “አቋሜን ለመፈተሽ ተገድጃለሁ” ካለ “ጋዜጠኛነቱን አቆማለሁ” እያለን መሆን አለበት።
ፖለቲከኛ መሆንም ችግር የለውም። ግን የጋዜጠኛ ፖለቲከኛ ሁኖ ሲሰራም ዳያስፖራዎች ከተጠራጠሩት በኋላ እንደገና ለመፈተሽ የፈለገው አቋሙ ምንድነው? ዳያስፖራዎች ባያጣጥሉትና ባይጠራጠሩት ኑሮ እንደገና የማይፈት ሸው አቋሙ ምንድነው? ዳዊት በዳያስፖራዎች መጠራጠርና ማጥላላት ከተከፋ አቋሙ ወይ ዓላማው እነዚህ ዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ለማስደሰት ነበር ማለት ነው። ተቃዋሚዎች ወይ ደጋፎዎች ወይ ሌሎች ለማስደሰት ተብሎ የሚሰራ ማንኛውም ተግባር ዉጤቱ መከፋት ነው የሚሆነው።
ዳዊት ዳያስፖራ ተቃዋሚዎችን የማስደሰት አቋም ወይ ዓላማ ይዞ ባይንቀሳቀስ ኑሮ በእርግጠኝነት ዳያስፖራዎች በሰሩበት ነገር ይህን ያህል ባልተከፋ ነበር። ምክንያቱም ዓላማው ሌሎችን ማስደሰት ወይ ማስከፋት ባይሆን ኑሮ በሰዎች አስተያየት ወይ አመለካከት እንዲህ ዓይነት ሌላኛው ጥግ የሚያስይዝና አቋም የሚያስቀይር ተግባር ባልሰራ ነበር። አንድ ጋዜጠኛ ለእውነት በመቆም ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ለህዝብ ማድረስ አለበት። ከዛ ማንኛውም ዓይነት አስተያየት ሳይሸበር መቀበል አለበት። ስለዚህ ዳዊት በዳያስፖራዎች አስተያየት እንዲህ መሆኑ ስህተት ነው።
በዳያስፖራ ይሁን በገዢው ፓርቲ ወይም በሌላ ስህተት ሲኖር መተቸት አለብን። እኛ ሌሎችን ስንተች የሌሎችን ትችት በፀጋ መቀበል ይኖርብናል። የዓላማ አቋማችን በሰዎች አስተያየት የሚቀየር ወይ የሚፈተሽ መሆን የለበትም፣ አስተያየቱ ወይ ትችቱ አሳማኝና ተቀባይነት ያለው ካልሆነ በቀር። የሰዎች አስተያየት ትክክል መሆኑ ካመንበት በዛ መሰረት አቋማችንን እንደገና መፈተሽ እንችላለን። ሰዎች እኛን የሚተች አስተያየት ስለሰጡን ብቻ አቋማችን የምንቀይር ከሆነ ግን በትክክል እውነተኛ ዓቋም አልነበረንም ማለት ነው።
ዳያስፖራዎች ዳዊትን የተቹበት ምክንያት የትግራይ ተወላጅ ስለሆነ ነው የሚለው ክስ ግን አልተቀበልኩትም። ምክንያቱም ዳያስፖራዎች ሁሌ የሚጠቀሙት ስትራተጂ ማጥላላት ነው። ይሄ የማጥላላት ስትራተጂያቸው አልደግፈውም። ምክንያቱም ስህተት ነው። የዳያስፖራ የማጥላላት ሰለባ የሆነው ዳዊት ከበደ (የትግራይ ተወላጅ) ብቻ አይደለም። ጃዋር መሐመድ፣ ልደቱ አያሌውና ሌሎች ፖለቲከኞች የማጥላላት ዘመቻው ሰለባ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ስለሆኑ አይደለም።
የዳያስፖራዎች የማጥላላት ስትራተጂ ለሁሉም ነው። እኔው ራሴ ከጃዋር ጋር የማጥላላቱ ዘመቻ ሰለባ ነበርኩ። በጃዋር ላይ የተከፈተው የጥላቻ ዘመቻም በግልፅ ተቃውምያለሁ። ምክንያቱም የማጥላላት ዘመቻው ለሀገር አንድነት የሚጠቅም ሳይሆን የሚጎዳ ነው። ሰውን በመሳደብ አንድነትን ማፍረስ እንጂ መጠበቅ አይቻልም። ዳያስፖራዎች እኛ የማንደግፈው የማጥላላት ዘመቻ ስለሚከተሉ እኛ ኢህአዴግን መቃወም መተው አለብን በሚል ግን አልስማማም። ምክንያቱም እኛ ኢህአዴግን የምንቃወመው ለዳያስፖራዎች ለማገዝ (ወይ ላለማገዝ) ብለን ሳይሆን ለራሳችን ነፃነት ብለን ነው። ስለዚህ የኛ ትግል በዳያስፖራዎች የትግል ስትራተጂ የሚወሰን አይደለም።
በኔና በዳዊት ልዩነት አለ ብዬ አስባለሁ። እኔ ማንም ዳያስፖራ ወይ ሌላ ተቃዋሚ ወይ ገዢው ፓርቲ ለማስደሰት ወይ ለማስከፋት አልተነሳሁም። “ዳዊትስ መቼ ለዚህ ዓላማ ተነሳ?” ልትሉኝ ትችላላቹ። መልሴ ዳዊት እነሱን ለማስደሰት ባይነሳ ኑሮ በነሱ ነቀፌታ ባልተቆጣ ነበር ባይ ነኝ። እኔ እነሱን ለማስደሰት ወይ ለማናደድ ብዬ እስካልፃፍኩ ድረስ እነሱ በሚሰጡኝ አስተያየት አልሸበርም፣ አቋሜን እንደገና አልፈት ሽም። ምክንያቱም እኔ ኢህአዴግን ስቃወም ሰዎችን ከማስደሰትና ከማናደድ የዘለለ የራሴ ዓላማ አለኝ።
የኔ ዓላማ ሰላምዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ማገዝ ነው። የሕግ የበላይነት የሚከበርባት ሀገር፣ ፍትህና እኩልነት የነገሰባት፣ ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት አንድነቷ የጠበቀች ሀገር ማየት እፈልጋለሁ። ስለዚህ መቃወሜን የማቆመው እነዚህ እሴቶች በተግባር ሲረጋገጡ እንጂ ዳያስፖራዎች እኔን ማጥላላት ሲጀምሩ አይደለም። ዳያስፖራዎች እኔን ማጥላላት ከጀመሩ የራሳቸው ጉዳይ ነው። እኔ ደግሞ የራሴ ጉዳይ አለኝ። ነፃነት ያስፈልገኛል። ከሁሉም (ከተቃዋሚዎችም ከኢህአዴግን) ነፃ መሆን አለብኝ።
ኢህአዴግን የምንቃወም ሌሎችን ለማስደሰት ከሆነ ዓላማችን ነፃነትን ማግኘት ሳይሆን ገዢውን (የሰው ጌታ) መቀየር ነው (To be free is not to change a slave master; In order for a slave be free, s/he has NO slave master)። አሁን ኢህአዴግን እቃወማለሁ። ሌሎች ኢህአዴግን የመሰሉ ሃይሎች ስልጣን ከያዙ ደግሞ ትግሌን እቀጥላለሁ። ስልጣን የሚይዘው አካል ማንም ይሁን ማን የዜጎች ነፃነት ካላረጋገጠ እቃወመዋለሁ። ስለዚህ ዓላማዬ ድርጅቶች ማገዝ ሳይሆን ነፃነትን ማግኘት ነው።
ስለዚህ አብርሃ ደስታ ከዳዊት ከበደ የሚማረው ነገር ቢኖር ሰው ሲቃወምም ሲደግፍም ትርጉም ላለው ዓላማ እንጂ ግለሰቦች ለማስደሰት ወይ ለማስከፋት መሆን እንደሌለበት ነው። ከዳዊት የምማረው ነገር በሌሎች አስተያየት መቆጣት እንደሌለብኝ ነው። ዓላማየ ሌሎች ድርጅቶችን ማስደሰት እስካልሆነ ድረስ ሌሎች ሰዎች በሚሰጡኝ አስተያየት አልሸበርም። ሁላችን የምንታገለው የግል ነፃነታችን በማግኘት ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት።

ከህወሓቶች የወጣ ሚስጢራዊ ደብዳቤ

ከህወሓቶች የወጣ ሚስጢራዊ ደብዳቤ ተቀበልኩ፤ ፊርማና ማህተም የሚመስል ነገር አለው (ማህተሙ በግልፅ አይታይም)። በፓርቲው መወሰድ ስላለባቸው ተግባራት ይጠቁማል። ግን ሆን ተብሎ ለስለላ የተሰራ ሊሆን ይችላል (ደብዳቤው ከሁለት ወር በፊት የተፃፈ ነው)። በደብዳቤው ከተጠቀሱት ነገሮች አንድ ልጥቀስ (ስለደብዳቤው እውነትነት ወይ ሰላይነት ለማረጋገጥ ይረዳልና)።
ኢያሱ ተስፋይ ስለ ተባለ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የተፃፈው … ድሮውም ታማኝ እንዳልሆነና ከህወሓት ከፍተኛ ሐላፊነት ወርዶ ወደ ዞን አስተዳደር መቀየር (ከመቐሌ መራቅ) እንዳለበት ያስቀምጣል።
ኢያሱ ተስፋይ የተምቤን ተወላጅ ሲሆን በአንድ ወቅት በማእከላዊ ስብሰባቸው ‘ለምንድነው የሐውዜን ጉዳይ መፍታት ያቃተን?’ ብሎ ጠይቆ ነበር። አሁን በነበረበት ሐላፊነት ነው ያለው ወይስ በደብዳቤው መሰረት ወደ ዞን አስተዳደር ቀይረው ከመቐለ ከተማ እንዲርቅ ሁነዋል???
እስቲ ይጣራ!

የዓረና የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ቶርቸር ተደረገ

ጓዶች የዉቅሮ ስብሰባ ሪፖርት ሳላቀርብ ጠፋሁ። የውቅሮ ከተማ የዓረና ቅስቀሳና የህወሓቶች ምላሽ የሚገርም ነበር። እኛ በደንብ ቀሰቀስን። የዉቅሮ ህዝብ የህወሓትን አገዛዝ እንዳንገሸገሸው ተረዳን።
የኛ ቅስቀሳ ሲጠናቀቅ ህወሓቶች የራስቸው ቅስቀሳ ጀመሩ። ‘የመለስ ራእይ…’ እያሉ እንደተለመደው መዘመር ጀመሩ። (በሚቀጥለው ምርጫ የሚጠቀሙት ቅስቀሳ ‘የመለስ ራእይ’ የሚል መሆኑ ከወዲሁ ማወቅ ችለናል)። ወደ ማታ አከባቢም ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ፣ እያንዳንዱን ወላጅ ልጆቹ ወደ ስብሰባው እንዳይሄዱ መምከር እንዳለበት ካልሆነ ግን መንግስት እንደካደ ይቆጠርና በመንግስት እርምጃ እንደሚወሰድበት ያስፈራሩት ገቡ።
ቅዳሜ ጠዋት (የስብሰባው ቀን) ሁሉም የዉቅሮ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የስብሰባው አደራሽ በር ላይ ተገኝተው ወደ ስብሰባው የሚገባ ሰው መከልከል ጀመሩ። የነሱ መከልከል ያልበገረው ሰው ደግሞ ፎቶ ማንሳት ጀመሩ። የቀበሌ ሰራተኞች ህዝብ የቀበሌያቸው ሰው መቆጣጠር ያዙ።
ሲገርመን እኛ ደግሞ እነዚህ ህዝብ የሚቆጣጠሩ ሰዎች ፎቶ ማንሳት ጀመርን። (ካድሬዎቹ ፎቶ እንዳናነሳቸው ይፈሩ ነበር)። አንዱ ሲከለክል አይቼው ፎቶ አነሳሁት። ተናዶ ወደኔ እየሮጠ መጣ። ‘ለምን ያለፍቃዴ ፎቶ ታነሳኛለህ?’ አለኝ። ‘አንተስ ለምን ህዝብ ያለፍቃዱ በስበሰባ እንዳይሳተፍ ታደርጋለህ?’ አልኩት። ‘እኔኮ ፀጥታ የማስከብር ፖሊስ ነኝ’ ብሎ መታወቅያውን አሳየኝ። ይገርማል ። ስሙ ተክላይ ይባላል። የዉቅሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ነው። ‘ታድያ ፖሊስ ከሆንክ ለምን ፎቶ መነሳቱ አስፈራህ? ሕጋዊ ስራ እየሰራህ ከሆነ ለምን ትፈራለህ?’ አልኩት። ለመግባት የመጣ ሰው የኛ ንትርክ ለመስማት ከበበን። ፖሊስ አዛዡ (ሲቪል የለበሰ ነው) ‘ዞር በሉ’ ብሉ በተናቸው።
እንዲህ እንዲህ እያለ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ሆነ (ስብሰባው መጀመር የነበረብት 2:30 ነበር)። እኛ በገቡ ሰዎች ስብሰባውን ለመጀመር ወደ አደራሹ ገባን። ከጭቅጭቁ በኋላ ዞምቢዎቹ ሰው በቀጥታ ከመከልከል ወደ በዝምታ መከታተልና በቪድዮ ካሜራ መቅረፅ ተሸጋገሩ።
ስበሰባው ተጀመረ። ህወሓቶች ገብተን ተሰብሳቢውን እንቀርፃለን አሉ። በስሰባው የነበሩ ‘ወጣቶች ህወሓቶች እኛን ለመጉዳት ነው የሚቀርፁት፤ ስለዚህ አስወጡልን’ አሉን። ፖሊስ እንዲወጡ አደረገ። ካድሬዎቹ ከፖሊስ ተጋጩ። ካድሬዎቹና የኛ ሦስት ሰዎች እየተከራከሩ ፖሊስ ጣብያ ዋሉ።
እንዲህ ሁኖ ሰብሰባው በሦስት ሰዓት ተጀምሮ በስምንት ሰዓት በጥሩ መንፈስ ተጠናቀቀ። የህዝብ ብዛት ግን አነስተኛ ነበር። በነበረው መንፈስ መሰረት በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ጠብቀን ነበር (ካድሬዎቹ ባይከለክሉት ማለት ነው)። የመጣ ግን በመቶዎች የሚቆጠር ነበር። እንዲህ ሁኖም ጥሩ ነው። መልእክታችን በሁሉ ቦታ ደርሷል። ያልሰማ የለም ማለት ይቻላል።
ህወሓቶች ፈሪዎች ናቸው። አቶ ገብሩ አስራት ‘ኢህአዴጎች በግለሰብ አስተያየት የሚደነግጡ ናቸው’ ብሎ ነበር። እዉነት ነው። ህወሓቶች ደንግጠው የዉቅሮ ከተማ በየካቲት 11 እንኳ የማይደረግ ቅስቀሳ ጀምረዋል። ዛሬ እሁድ ህዝብ ለሰለማዊ ሰልፍ እንዲወጣ አስገድደው ሰልፍ ጠርተው ነበር። ሰለማዊ ሰልፍ አይፈቀድም እያሉ ራሳቸው ሰለማዊ ሰልፍ ይጠራሉ። በጣም መደንገጣቸው መበስበሳቸው ያሳያል።
ሰብሰባው አጠናቀን ወደ መቐለ ጉዞ ጀመርን። ስብሰባው ይመሩ ከነበሩ የዓረና አመራር አባላት አንዱ የዉቅሮ ከተማ (አጉላዕ) ተወላጅ የሆነና በ2002ዓም ዓረና ወክሎ የፓርላማ ተወዳዳሪ የነበረ መምህር ይልማ ኩኖም ነበር። እኛ ወደ መቐለ ጉዞ ስንጀምር እሱ ቤተሰቡ ለመጠየቅ ዉቅሮ ቀረ።
የህወሓት ፖሊሶች ተከታትለው ያዙት። ስልኩን ነጠቁት። በፖሊስ መኪና ወደ መቐለ ይዘዉት መጥተው ቶርቸው ሲፈፅሙበት አደሩ። አለን የሚሉት የመግረፍት እርምጃ ካደረሱበት በኋላ አሁን ለቀቁት። መምህር ይልማ ኩኖም የዓረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የዉቅሮ ከተማ ተወዳዳሪያችን ነው። ለ24 ሰዓት ቶርቸር የሚፈፅሙ አምባገነኖች ያልታገልን ለማን ልንታገል ነው? የሚፈፅሙት ቶርቸር ደርጋዉያን ይፈፅሙት ከነበረ የከፋ ነው።

ዉቅሮ ነኝ ያለሁት!

ዉቅሮ ነኝ ያለሁት። ነገ ለሚካሄድ ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳችን ጨርሰን አልጋ የያዝንበት ሆቴል ዉስጥ አረፍ ብለናል። የዉቅሮ ህዝብ ለውጥ ፈላጊ ይመስላል፤ አይፈራም። በህዝቡ አቀባበል ተደስተናል።
ከምሽቱ 12:00 ሰዓት በኋላ ቅስቀሳ ማድረግ ስለማይፈቀድ አቁመናል። በቅስቀሳችን የተደናገጡ የከተማው አስተዳዳሪዎች ለብዙ ግዜ ስራ አጥ የነበሩ ወጣቶችና የኮብልስቶን ስራ ተከልክለው የነበሩ ሰራተኞች በማዘጋጃቤት ሰብሰብው የሚቀጥለው ሰኞ (ከቅዳሜ ስብሰባችን በኋላ) ለሁሉም ወጣቶች ስራ እንደሚፈጥሩላቸውና የኮብስቶን ስራ እንደሚጀምሩ ዛሬ ነግሯቸዋል። ዛሬ እንዲፈርስ ቀነ ገደብ ተይዞበት የነበሩ ቤቶችም አይፈርሱም ተብሏል (የዓረና ስብሰባ እስኪያልፍ ማለት ነው)።
ቤት የሚፈርሳቸውና ስራ ተከልክለው የነበሩ ሰዎች በዓረና ስብሰባ ካልተሳተፉ ከሰኞ ጀምሮ ሁሉም ነገር እንደሚደረግላቸው ተነግሯቸዋል።
አሁንም ከ12:00 ሰዓት ጀምሮ እስካሁን (3:00 ሰዓት ) በትልቅ ስፒከር በመለስ ራእይ ቅስቀሳ እየተደረገ ነው። የመለስ ራእይ ለማሳካት ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ለህዝብ የሚጠቅም ስራ እንደሚሰራ ቃል እየገቡ ነው። በመለስ መሬት ዃዂቶ (ቋቚማ) እንደማይበቁል እየዛቱ ነው። ዃዂቶ፣ ጉርዲ ወዘተ የሚሉ ስድቦችም እየተነገሩ ነው።
አልጋ የያዝንበት ሆቴል አጠገብ በስፒከር እየነገሩን ነው። ለህዝቡ ሳይሆን ለኛ ለመንገር የፈለጉ ይመስላሉ። ሆቴሉ በብዙ የደህንነትና የፀጥታ ሰዎች ተጥለቅልቋል። አብዛኝው የሆቴሉ አልጋ በነሱ ተይዟል።
መንግስት ይህን ያህል ይፈራል እንዴ? በጣም ነው የገረመኝ።
በእውነት ኢህአዴግ እንዲህ ፈሪ ከሆነ በሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ የምናሸንፈው ይመስለኛል።

ከዓድዋ የተላከልኝ አስተያየት!

አንድ የፌስቡክ ወዳጄ በዉስጥ መስመር የላከልኝ እንዳለ ልለጥፈው ወድድኩ።
“የተከበርክ መምህር ኣብርሃም፣ ስለ ዓድዋ የፃፍከው ፅሁፍ አነበብኩኝ፡፡ በርግጥ አንድም ቀን ራሴን እንደተቀዋሚ ቆጥሬ አላውቅም፡፡ ይህ ማለት ግን ራሴን የማላውቅ ደጋፊ ነኝ ማለት አይደለም፡፡ በአድዋ ከተማ በአስተማሪነት ለአስራ አምስት አመታት ያክል አገልግያለሁ፡፡ ስለሆነም ነው አንተ በአድዋ ከተማ ተዘዋውሬ የሰማሁት የመልካም አስተዳደር እጦትና የነዋሪው ብሶት ብለህ የፃፍከውን ፅሁፍ ለማጣጣል የተነሳሁት፡፡ ውድ አብርሃም በርግጥ አንተ ያየሀው የመልካም አስተዳደር እጦት ይህ ብቻ ከሆነ፤ በጭራሽ አድዋ ከተማ አልመጣህም፡፡ ብትመጣ ኖሮ በከተማ ያየኸውን የጥቂት ግለሰቦች ችግር ብቻ ባላነሳህ ነበር፡፡ በአድዋ ከተማ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር እጦትና ብሶት ለማየት በከተማው የሚገኙ መምህራንን ማነጋገር በቂህ ነበር፡፡ ሕወሓት በአባልነት የሚመለምላቸው የስራ ፍቅር የሌላቸው፣ ወሬ የሚያቀባብሉ፣ የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት በቅጡ ማሸነፍ የማይችሉ፣ ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በአጠቃላይ የህዝቡንና የሃገሪቱን ሃብት በማባከን ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው፡፡ አንተ ያላየኸው እኔ የማውቀውና እነሱም አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩበት አንድ ነገር ልንገርህ፤ ትምህርት ቤት ማለት ከፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ሌሎች የፀዳ ክልል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን በትምህርት ቤት ውስጥ የፖለቲካ እምነታቸውን በውድ ሳይሆን በግድ እያስፋፉ ነው፡፡ ለምሳሌ በኛ ትምህርት ቤት ውስጥ /ንግስተ ሳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት/ ዲፓርትመንት ሄድ፣ የክለብ አስተባባሪ፣ ዩኒት መሪ፣ ወዘተ ለሕወሓት አባላት የሚሰጡ እንጂ በመማር ማስተማር ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ላለው አስተማሪ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ተማሪዎች እድሜያቸው ከ18 በታች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሳይፈልጉና ሳይነገራቸው የሕወሓት የአባልነት ክፍያ የሚከፍሉና እንደአባላት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ 2006 ዓ.ም የተማሪዎች የአባልነት ክፍያ ተማሪዎቹ ሳያውቁና ሳይነገራቸው ከትምህርት ቤት መመዝገቢያ ክፍያ ጋር እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ በርካታ በመማር ማስተማር ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው መምህራንም አባላት ባለመሆናቸው ምክንያት ይገለላሉ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው አመት አራት አስተማሪዎች ለሕወሓት አባላት መልካም አስተያየት የላችሁም፣ አባላትን ትገመግማላችሁ ተብለው ከብሄራዊ ፈተና እንዲገለሉ ተደርጓል፡፡ እኔም ብሆን የሕወሓትን አባላት ታንቋሽሻለህ ተብየ በተዘዋዋሪ 2500 ብር ተቀጥቼ እየከፈልኩኝ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በአድዋ ከተማ በተለይ አስተዳደሩ አከባቢ የሚገኙ ሰዎች ህዝቡ አያስፈልጉንም እያለ ብሶቱን እያሰማ ግን መልካም ሰዎች ከአስተዳደሩ እንዲባረሩ እየተደረገ እነዚህ ህዝቡን ወደከፋ ብሶት የሚመሩ ሰዎች እንዲመሩ እየተደረገ ነው፡፡ የተሰራ ስራ ሳይኖር በሪፖርት ብቻ ከተማዋ ደህና እንደሆነች እየተደረገ ይነገራል፡፡ ኧረ ሁሉን ብታወራው ማለቂያ የለውም ባክህ፡፡ ምን ዋጋ አለው እናንተም እየጠነከራችሁ አይደለም፡፡ በርቱ!”
የተከበርክ ወዳጄ…
በነዚህ ነጥቦች ያላተኮርኩበት ምክንያት በሌላው የትግራይ አከባቢዎችም የተለመዱ በመሆናቸው ነው። ለሰጠኸኝ አስተያየት አመሰግናለሁ።

ለዉቅሮና አከባቢዋ ኗሪዎች!

ዓረና ትግራይ ፓርቲ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት16, 2006 ዓም በሚሊንየም አዳራሽ (ዉቅሮ) ከጠዋቱ 2:30 በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከከተማው ህዝብ ጋር ይወያያል። የቻላቹ በህዝባዊ ስብሰባው እንድትገኙ ተጋብዛችኋል። ኑና እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንጠያየቅ፣ እንገናኝ።
ጥረታችን ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም እንቅስቃሴያችን ሁሉ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም። ምክንያቱም ዓላማችን የኢህአዴግን መንግስት በሌላ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መተካት መቻል ነው።
ከኢህአዴግ የተሻለ ዴሞክራሲ የሚያሰፍን፣ ልማትና ፍትሕ የሚያረጋግጥ፣ የዜጎች ነፃነት የሚያከብር መንግስት እንመሰርታለን ብለን ቆርጠን ተነስተናል። የምንመሰርተው መንግስት ከኢህአዴግ የተሻለ ባይሆንስ? አዎ!ስልጣን የምንይዝበት መንገድ ሰለማዊ እስከሆነ ድረስ ስልጣን ይዘን ከኢህአዴግ መንግስት ባንሻል እንኳ ለመጀመርያ ግዜ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር እዉን ስለሚሆን ይህ (ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር) በራሱ በኢትዮዽያ የፖለቲካ ታሪክ ትልቅ አስተዋፅዖ ሁኖ ይመዘገባል። ስለዚህ ትግላችን ዋጋ አለው።
ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር እዉን ማድረጉ ባይሳካልንስ? ያው መንገዳችን ህዝብ በማስተማር የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት እስከሆነ ድረስ ስልጣን መያዙ ላይ ባይሳካልንም ህዝብ ስለ ዴሞክራሲ ማስተማርና አማራጭ ሁኖ መቅረብ በራሱ ትልቅ የዴሞክራሲያዊነት አስተዋፅዖ ነው።
ስለዚህ ጥረታችን በማንኛው መልኩ ለሀገራችንና ህዝባችን ጠቃሚ ነው። ነገ በዉቅሮ ከተማ እንገናኝና እንነጋገር።
ነገ ጠዋት ዉቅሮ ነኝ።
It is so!!!
It is so!!!

zehabesha

No comments:

Post a Comment