Friday, October 11, 2013

ፍጥጫ በሞላበት የብአዴን አባላት ግምገማ ከ 1 መቶ 70 በላይ ሰዎች በአንድ ጊዜ መልቀቂያ አስገቡ

ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በ2005 ዓም የስራ ክንውንና በ2006 ዓም የስራ እቅድ በሚል ርእስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የኢህአዴግ አባላት ግምገማዎች እየተካሄዱ ነው።
በኦሮሚያ ክልል በርካታ የኢህአዴግ አባላት የሆኑ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች አክራሪነትንና ሽብረተኝነትን በተመለከተ ኢህአዴግ የሚከተለውን ፖሊሲ መተቸታቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ግምገማ ደግሞ በርካታ የብአዴን አባላት በፓርቲውና በስርአቱ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
ኪራይ ሰብሳቢነት በሚለው አጀንዳ አባላቱ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ከተፈለገ እኛን ሳይሆን ሚሊዮኖችን የሚዘርፈውን አካል በቅድሚያ መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
እኛን እስክርቢቶ ወስዳችሁዋል በማለት ከምትገመግሙን ከአገር የሚወጣውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በጊዜ ብትቆጣጠሩ ይሻላል ሲሉ በምሬት የገለጹዩ ነበሩ።
ለአባልነት በሚል በየወሩ 105 ብር በግዴታ እየወሰዳችሁብን የምንበላው ፣ የቤት ኪራይ የምንከፍለው አጥተናል ያሉት አባላቱ፣ በዚህም የተነሳ የድርጅቱ አባላት በየጊዜው የአባልነት መልቀቂያ እያስገቡ ነው ብለዋል።
በ2005 ዓም ብቻ 173 የብአዴን አባላት መልቀቂያ አስገብተዋል።
ለብአዴን አባላት መገምገሚያ ተብለው ከቀረቡት አዳዲስ መስፈረቶች መካከል አንዱ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን መዋጋት የሚለው ይገኝበታል። የድርጅቱ አባላት አክራሪነትን ከደገፉ፣ አክራሪዎችን እያዩ ዝም ብለው ካለፉ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ካበሩ፣ አክራሪነትን በሚደግፉ ሰልፎች ላይ ከተገኙ በአክራሪነት ይፈረጃሉ። አክራሪዎችን መደገፍ የሚለው የሁሉም የሲቪል ሰራተኞች መገምገሚያ መሰፈርት ሆኖ መቅረቡን መዘገባችን ይታወቃል።
በባህርዳር በተደረገው ግምገማ ኢሳት የሚያቀርበውን መረጃ በተመለከተም ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።
የክልል ሀላፊዎች ከኢሳት የሚወጡትን መረጃዎች ተከታትለው ምላሽ በመስጠት፣ ቢቻል በመቅደም ካልተቻለ ደግሞ ዘግይቶም ቢሆን በቀረበው ዜና እና ፕሮግራም ላይ ከልማት አንጻር እየታየ መለስ እንዲሰጡ ታዘዋል።
ኢህአዴግ ኢሳት ለሚያሰራጨው ዜና ፣ የቻይናን የሚዲያ ፖሊሲ በመከተል ማምከን የሚል ስትራቴጂ ለመከተል እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው።
“ኢሳት ለምን እንደ ችግር ሆኖ ይቀርባል ፣ ችግር የሰለቸው ህዝቡ ነው በማለት ” አስተያየት የሰጡም ነበሩ።
ግምገማው ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ እርከኖች እየተካሄደ ይገኛል።
የግምገማውን ተጨማሪ ዘገባ በነገው እለት ይዘን እንቀርባለን።

 https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/10/11/79-2/

No comments:

Post a Comment