የሰንደቅ ዜናዎች (ጥቅምት 20/2006)
-
የሹመቱ አግባብነት ጥያቄ አስነስቷል
-
አፈጉባዔ አባዱላ ጠ/ሚኒስትሩ በሹመቱ ላይ
ማብራሪያ ለመስጠት አይገደዱም አሉ
በፍሬው አበበ
የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን
ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊነት ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን ሹመት ተቀብሎ አጸደቀ። በዚሁ መሠረት
ድርጅቱን ለረዥም ጊዜ በቦርድ ኃላፊነት ባገለገሉት አቶ በረከት ስምኦን ምትክ አቶ ሬድዋን ሁሴን የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው
ተሹመዋል።
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ትናንት ለም/ቤቱ በላኩትና የአማካሪ
ም/ቤት አስቀድሞ ሳይመክርበት በድንገት በቀረበው ደብዳቤ መሰረት ለኢትዮጵያ ራዲዮና
ቴሌቪዥን ድርጅት ስምንት አባላት ያሉት የስራ አመራር ቦርድ አባላትን መሾማቸውን አሳውቀዋል። በዚሁ መሠረት በቅርቡ የመንግሰት
ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ሬድዋን ሁሴን የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ በቅርቡ ለረዥም ጊዜ ካገለገሉበት
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸው ተነስተው በጠ/ሚኒስትር
ጽ/ቤት የሕዝብ ተሳትፎ አደረጃጀት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት አቶ ደስታ ተስፋው አባል፣ በቅርቡ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ
የምክትል ጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን የተሾሙት አቶ አማኑኤል አብርሃም አባል፣ አቶ ዓቢይ መሐመድ ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል፣
አቶ ገበየሁ በቀለ ከአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ አባል፣ ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ ከአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ አባል፣ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ከእምነት
ተቋማት አባል፣ አቶ ዘርዓይ አስገዶም ከኢቲቪ አባል በመሆን ተሹመዋል።
የተሰናባቹ የኢትዮጵያ
ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ አባል መሆናቸውን የተናገሩ አንድ የም/ቤት አባል ሹመቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት
ሹመቱ ግልጽነት የጎደለው መሆኑን በመጥቀስ ማብራሪያ ጠይቀዋል። እንደእሳቸው አባባል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጠሪ የሆኑ የመንግስት
የሚዲያ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆናቸውን በማስታወስ ለሁለቱ ተቋማት
4ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሹመት መስጠቱን አስታውሰዋል። አሁን የቴሌቪዥን ቦርድ በድክመት ባልተገመገመበት ሁኔታ ለብቻው ተለይቶ
በተናጠል እንዴት ሹመት ሊሰጥ እንደቻለ ጠይቀዋል። “ምናልባት ሰብሳቢው ቦታውን ለውጦ ከሆነ ያ ቦታ የተካው ሰው መያዝ ሲገባው
የስራ አመራር ቦርድ አባላት ድክመት ባልገመገምንበት ሁኔታ ቦርዱ እንደ አዲስ ሊሰየም የተፈለገበት ምክንያት አልገባኝም” ሲሉ አባሉ
አስቀምጠዋል። በተጨማሪም የቀድሞ ቦርድ ቁጥሩ ዘጠኝ የነበረ ሲሆን አሁን ቁጥሩ ለምን ወደ ስምንት ዝቅ አለ ሲሉ የጠየቁ ሲሆን
ሌሎች የም/ቤቱ አባላትም ከእምነት ተቋም ተወካይ ቦርዱ ውስጥ የገባበት ምክንያት እንዳልገባቸው፣ ከዚህ ይልቅ ከሲቪል ማህበር ቢሆን
ይሻል እንደነበር እንዲሁም የሴቶች ተሳትፎ በሹመቱ ውስጥ መዘንጋቱ በጥያቄ መልክ ተነስቷል።
አቶ አባዱላ ገመዳ የም/ቤቱ አፈጉባዔ በሰጡት ምላሽ ጠ/ሚኒስትሩ በማንኛውም ጊዜ
ሚኒስትሮችን ሲያነሱ ማብራሪያ እንደማይጠየቁ ሁሉ የቦርድ አባላትንም ሲሰየሙ ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይገደዱ ተናግረዋል። የአሁኑ
ቦርድ አሰያየም ፖለቲካን ብቻ ሳይሆን የሙያ አቅምንም መሰረት ያደረገ ነው ካሉ በኋላ የሴቶች ተሳትፎ መጓደልን በተመለከተ መልዕክቱን
እንደሚያደርሱ ገልፀዋል።¾
No comments:
Post a Comment