Thursday, October 24, 2013

የነጠፈው የኢትዮጵያ ማህጸን!



ነጠፈው የኢትዮጵያ ማህጸን!?
ሀ ብሎ ሲጀምር ጥበብን የጠራ፣
አክሱም ላሊበላን በእጆቹ የሠራ፣
ያንን ምጡቅ ትውልድ ሲያፈራ የኖረ፣
ወላድን በድባብ ከድኖ ያከበረ፣
ምን ሆኖ ደረቀ/ነጠፈ ያ ለምለም ማህፀን፣
ምክነያቱ ጠፋኝ ግራ ገባኝ እኔን፡፡
በእግዚአብሔር አምላክ ፊት ሲቦርቅ አይተሽው፣
ምን አልባት ዳዊትን በልብሽ ንቀሽው፣
የሳዖል ልጅ ሜልኮል የደረሳት ዕጣ፣
ያ የእግዚአብሔር በትር ያ የእግዚአብሔር ቁጣ፣
ዘላለም እንዳትወልጅ ዳግም በአንቺ መጣ?
ነገሩን ሳስበው የአንቺ ከእሷ ባሰ፣
መዘጋት መድረቁ ደግሞ ባላነሰ፣
አራሙቻ አብቅሎ አገር አረከሰ፡፡
ምንኛ ቢከፋ ታዲያ የአንቺ ኃጥያት፣
እንዳልተባለልሽ የጠቢባን እናት፣
ያ ለም ማህጸንሽ የተዘመረለት፣
መንጠፉ ሳያንሰው አረም በቀለበት!?
ኃጥያትሽ በዝቶ እንደሁ ተስፋ ሳትቆርጪ፣
አጥቦ ያፀዳሽ ዘንድ እምባሽን አመንጪ፣
በአፍኝሽ ሙይና እርጪው ወደ ሰማይ፣
መስዋዕት ይሁንሽ በአምላክሽ ፊት ይታይ፡፡
በፀፀትሽ ብዛት አስቦ ታሪክሽን፣
ዳግም እንድከፍተው ለምለም ማህፀንሽን፡፡
ስቃይዋ ቢበዛ ብታጣ ልጆቿን፣
መጽናናጽ ቢሳናት ልቧ ገብቶ ሐዘን፣
ስቅስቅ ብላ አልቅሳ አውጥታ የአንጀቷን፣
ብሶቷን አሳፍራ ብትልክ አምባዋን፣
እግዚአብሔር ስለእሷ ሕዝቡን መመልከቱን፣
ያቺን የሐዘን እናት አስቢ ራሄልን!!!

የታላቋ ቀን ልጅ በጥቅምት 2006 ዓ.ም-የተስተካከለ-ዋናው በ1994ዓ.ም
(Son of the great day modified in October 2013- Original in 2002)

No comments:

Post a Comment