Wednesday, October 30, 2013

ቅዱስ ሲኖዶስ ለ‹‹ገለልተኛ›› አብያተ ክርስቲያን ጥሪ ያደርጋል


  • የአቡነ ጢሞቴዎስ ዐምባገነንትና የኮሌጁ ጉዳይ ምልአተ ጉባኤውን ሲያወያይ ዋለ
  • ሊቀ ጳጳሱ በበላይ ጠባቂነት ተወስነው የሽግግር ዋና ዲን እንዲሾም ሐሳብ ቀርቧል
  • የኮሌጁ ሥራ አመራር ቦርድ ዛሬ ለምልአተ ጉባኤው ማብራሪያ ይሰጣል
የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ወጥተው በገለልተኛ አስተዳደር ለሚመሩ አብያተ ክርስቲያን የአንድነት ጥሪ ሊያስተላልፍ ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው በትላንት፣ ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ውሎው የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና መዋቅር ከማጠናከር አንጻር በገለልተኛ አስተዳደር ለሚመሩ አብያተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ተግባራት መፈጸም እንደሚገባቸው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በቀጥታ ይከታተለዋል በተባለው በዚሁ የቤተ ክርስቲያንን ማእከላዊ መዋቅር የማጠናከር ተግባር፣ ለገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን የአንድነት ጥሪ የሚተላለፍ ሲኾን ጥሪውን የተቀበሉት አብያተ ክርስቲያን በሚያነሧቸው ጉዳዮች ላይ የሚወያይ ራሱን የቻለ አካል እንደሚቋቋም ተጠቁሟል፡፡ በውይይቱ በሚደረስበት መግባባት አብያተ ክርስቲያኑ በውጭ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች አስተዳደር ሥር ተካተው የሚያስፈልጓቸው አገልግሎቶች ሁሉ በማእከል እንዲሟላላቸው መመሪያ መሰጠቱ ተገልጧል፡፡
ተጠሪነት ሳይኖር በራሳቸው ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን በገለልተኝነት የማቋቋም ኹኔታ ራሱን የቻለ መዋቅር መስሎ በይበልጥ የሚታየው በሰሜን አሜሪካ ነው፡፡ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በ፳፻፬ ዓ.ም. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው በአሜሪካ ባሉት ሦስቱ አህጉረ ስብከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙት አብያተ ክርስቲያን ቁጥር 56 ያህል ብቻ ነው፡፡
በክፍለ አህጉሩ የተበተነውን ምእመን ለመሰብሰብ፣ መሠረታዊና እውነተኛ የኾነውን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ለማስከበር ከባድ ውጣ ውረድ መታለፉን የገለጸው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በቀጣይነት ለማጎልበት÷ በመዋቅርና በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች በራሳቸው አነሣሽነትና ተቆርቋሪነት በመሠረቱት የአንድነት ማኅበር አማካይነት የወጣቶችን እንቅስቃሴ መደገፍ፣ የካህናትን የእርስ በርስ ግንኙነትና የጋራ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን ማጠናከር፣ ከሀ/ስብከታቸው ውጭ እየመጡ አብያተ ክርስቲያን በመክፈትና ክህነት በመስጠት ሊቃነ ጳጳሳት አንድነትን ከሚያናጋና ገለልተኝነትን ከሚያበረታታ ኢ-ቀኖናዊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግን በመፍትሔነት አቅርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ሲካሄድ ቆይቶ የተስተጓጎለው የዕርቀ ሰላም ሂደት እንዲቀጥል በአጀንዳ የተነጋገረው ምልአተ ጉባኤው፣ በስደት ያሉት አባቶች ፈቃድ ተጠይቆና አስፈላጊው ነገር ተሟልቶ ውይይቱ የሚቀጥልበት ኹኔታ እንዲመቻች መመሪያ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡

 http://haratewahido.wordpress.com

No comments:

Post a Comment