- ዐሥር አህጉረ ስብከት የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል፤ በፓትርያርኩ፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የተያዙና በቁጥር ከ10 – 12 የሚኾኑ የታሳቢ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ዝርዝር ለምልአተ ጉባኤው እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
- በተጭበረበረ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃና የዶክትሬት መመረቂያ ጥናትን አስመስሎ መቅዳት/plagiarism/ ክሥና ወቀሳ እየቀረበባቸው የሚገኙት፣ ሓላፊነትን በተገቢው ኹኔታ ባለመወጣትና በትጋት ባለመሥራት የተገመገሙት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በከባድ እምነት ማጉደል በተቀሰቀሰባቸው የካህናትና ምእመናን ተቃውሞ ከቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪነት የሚነሡት አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንንና የመሰሏቸው ቆሞሳት ከታሳቢ ዕጩዎች መካከል መገኘታቸው በምርጫው አግባብነት ላይ ጥያቄ አስነሥቷል፡፡
- ‹‹የምንሾማቸው ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይኾኑ የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራ ለመቀበል የተዘጋጁ ሊኾኑ ይገባል›› ከሚለው የፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ጋራ በቀጥታ የሚጣረስ አይደለምን? የቤተ ክርስቲያንንስ አመራር ከወቀሳ ያድናል?
- የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናትና የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ተግዳሮቶች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደራዊ ችግርና የሊቀ ጳጳሱ ዕጣ ፈንታ እንዲሁም በሊቃነ ጳጳሳቱ ዝርዝር እይታ ላይ የሚገኘው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ምልአተ ጉባኤውን በስፋት እንደሚያነጋግር ተጠቁሟል፡፡
- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንፃን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ያስተዳድራል፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ልዩ ልዩ ገቢዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ተካተው በሚመደብላቸው በጀት ብቻ ይሠራሉ፡፡
- በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከኦዲት ምርመራ ጋራ በተያያዘ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቀረበውን ግለሰባዊ ትችት ምልአተ ጉባኤው በከፍተኛ ድምፅ ውድቅ በማድረግ የዘገየው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ተጠናቆ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
- ሊቃነ ጳጳሳቱ በ‹‹መቻቻል›› ላይ የሰነዘሩት ትችት መንግሥትን አሳስቧል፤ የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋራ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፤ በደኅንነት ስም በየሊቃነ ጳጳሳቱ ቤት የሚዘዋወሩ ግለሰቦች ዝርዝር ለመንግሥት ይቀርባል፡፡
- የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ሓላፊነታቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ በአውስትራልያ በአሜሪካው ሲኖዶስ አስተዳደር ሥር የምትገኝ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እልቅናን በውዝግብ መሾማቸው ተነግሯል፡፡
አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ 28
የመነጋገርያ አጀንዳዎችን በማጽደቅ መወያየቱን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ተጀምሮ በጥብቅ
ምስጢራዊነት በመወያየት ላይ የሚገኘው ምልአተ ጉባኤው መግባባትና ግልጽነት በሰፈነበት ኹኔታ ዓመታዊ ስብሰባውን
እያካሄደ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
ከዐርባ ያላነሱ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት የተገኙበት ምልአተ ጉባኤው በቆይታው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ
አቡነ ሉቃስ ያቀረቡትን ሪፖርት አዳምጧል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የ፳፻፮ ዓ.ም. በጀትና
በዕቅድና ልማት መምሪያ ተዘጋጅቶ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ የቀረበውን የበጀት ዓመቱን መሪ ዕቅድ
ተመልክቷል፤ የማስተካከያ ሐሳቦችን በማከል ለዳግም እይታ እንዲቀርብም አዝዟል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከሚገኝበት የፋይናንስ አቅም ጋራ ተያይዞ ስለ በጀት ምንጮች መነጋገሩ የተዘገበው ምልአተ
ጉባኤው÷ መንፈሳዊ ኮሌጆች የሚቆጣጠሯቸው ሕንጻዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት
ድርጅት ሥር ኾነው ድርጅቱ እንዲያስተዳድራቸው፣ ሌሎች የገቢ ምንጮቻቸውም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ተካተው
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በሚመድብላቸው በጀት እንዲተዳደሩ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
በዚህ የስምምነት ውሳኔ መሠረት በዕሥራ ምእቱ መባቻ በ57 ሚልዮን ብር ተገንብቶ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጠውና የውስጥ ገቢ የሚያስገኘው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንጻ ከኮሌጁ አስተዳደር ቁጥጥር የሚወጣ ይኾናል፡፡ ኮሌጁ ከሌሎች የውስጥ ገቢዎቹ ማለትም ከቀን ተመላላሽ፣ ከማታ ተከታታይ፣ ከርቀት ትምህርትና ከድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሮች፣ ከአዳራሽ፣ ከመማሪያ ክፍሎችና ከካፊቴሪያ ኪራይ በወር
በድምር የሚያገኘው ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ከሕንጻው ኪራይ በወር ይሰበስበዋል ከሚባለው ሌላ አንድ ሚልዮን
ብር ያህል ገቢ ጋራ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ይዞራል፤ ኮሌጁም በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ ፵፪/፭/መ
መሠረት ሁሉም አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው በሚመድቡለት የአምስት ፐርሰንት አስተዋፅኦ ተልእኮውን ይፈጸማል
ማለት ነው፡፡
ፓትርያርኩን ጨምሮ በምልአተ ጉባኤው የተደገፈውን ይህን ስምምነት ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ የተወሰነባቸው የበላይ
ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኮሌጁ ሕንጻውን እንዲያስተዳድርና የውስጥ
ገቢውን እንዲደጉም ጽፈውት የነበረውን ደብዳቤ በአስረጅነት በማቅረብ ተቃውመውታል፡፡ የሕንጻው አስተዳደር ከኮሌጁ
ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በመዞሩ ያልተደሰቱ ወገኖች ‹‹ተወሰደበት›› በሚል ውሳኔውን ነቅፈዋል፡፡
በአንጻሩ ግዙፉ ሕንጻ የኮሌጁን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ቢገነባም ከገቢው ሳይጠቀምና ከበጀት ችግሩ ሳይላቀቅ
መቆየቱን፣ የደቀ መዛሙርት አልጋ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ ሳይቀየር፣ ለመምህራኑ በፍትሐዊነት ደመወዝ ሳይስተካከል
ጥቂቶች ብቻ የደመወዝ ጭማሪ ያገኙበትን ኹኔታ በመጥቀስ ውሳኔውን ደግፈዋል፤ ለአስተዳደሩ ብልሽት ግንባር ቀደም
ተጠያቂ የሚያደርጓቸው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ከቦታው የማግለል ጅምር መኾኑም ታምኖበታል፡፡
የፓትርያርኩ በዓለ ሢመት ቀን በጾም የሚውልባቸው ጊዜያት በመኖራቸው ቀኑን በለውጥ ስለ መበየን
በጽ/ቤታቸው በቀረበው አጀንዳ ላይ ምልአተ ጉባኤው የተለያዩ አማራጮችን አይቷል፡፡ ከአማራጮቹ መካከል፡- ሢመተ
ፕትርክናው የተፈጸመበት የካቲት ፳፬ ቀን ዐቢይ ጾምን ሊነካ ስለሚችል በሱባኤው ለአክብሮ በዓል ከምንወጣ በርክበ
ካህናት/በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን/ አድርገን በዚያው የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ይኹን የሚለው አንዱ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ በዓለ ሢመትን የምናክበረው ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራስዋን የመቻሏን ነጻነት
ለመዘከርም በመኾኑ ቀኑ በወርኃ ጾም መዋሉ አይከለክለንም የሚሉ በበኩላቸው የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን
በፊልጵስዩስ የታነፀችበት(ሕንፀታ ቤተ ክርስቲያን)፣ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ
የተሾሙበትን ሰኔ ፳፩ ቀን በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ክንውን በየራሱ ታሪክ ስላለው ታሪኩ መጠበቅ
ይኖርበታል በሚለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፕትርክና የተሠየሙበት የካቲት ፳፬ ቀን ዕለቱን እንዳይለቅ
በዚያው ጸንቷል፡፡
http://haratewahido.wordpress.com
No comments:
Post a Comment