Saturday, October 19, 2013

ነገረ ደብረ ማርቆስ-አሁን ደግሞ በቆሎ ይሆን የሚዘራዉ?


ከጥቂት አመታት በፊት ደብረ ማርቆስ ከተማ ዉስጥ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተካሂዶ ነበር:: በዚሁ ባዛር ላይም የከተማዋንና የአካባቢዋን ነዋሪዎች የሚያስፈነድቅ ዜና ተሰማ:: ደብረ ማርቆስ ዉስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነዉ የሚል ዜና! ዜናዉንም እስክንጠግብ ድረስ ታማኙ ኢቴቪ(ትምህርተ ስላቅ) ደጋገመልን:: ለካስ ኢቴቪ የሚያወራዉ እኛ ስለማናዉቃት ደብረ ማርቆስ ኖሮዋል ዜናዉ ተነግሮ ፋብሪካዉ የዉሀ ሽታ ሆኖ ቀረ:: ለነገሩ ለኢቴቪ አመቱን ሙሉ አፕሪል ዘፉል ነዉ አይደል የተባለ! ዜናዉም አፕሪል ዘፉል ሆኖ ቀረ:: የፋብሪካዉ መገንባት ወሬ ሆኖ ሲቀር የከተማዋና የአካባቢዉ ነዋሪዎች መቆጣታቸዉ አልቀረም ::መቀሌ ነዉ እንጂ ደብረ ማርቆስ አይገነባም ተብሎ ነዉ የቀረዉ የሚል ወሬ ተናፈሰ:: ነገሩን ለማሳመር ይሁን የእዉነት ባላዉቅም እህል የማያበቅል መሬት መቀሌ እያለ ለምለሙን መሬት ፋብሪካ ለመገንባት አናዉለዉም ብሎ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳስቀረዉ መወራት ጀመረ:: ይህን የህዝብ ቅሬታ የተመለከቱት በእየርከኑ ያሉ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ህዝቡን ለማሳመን በየስብሰባዉ መወትወት ጀመሩ ::ፋብሪካዉ ሳይገነባ የቀረዉ ሊገነባ ቃል የገባዉ ሰዉ ገንዘብ የለኝም ስላለን ነዉ እያሉ ህዝብ ሊያሳምኑ ሞከሩ:: በዚህም አላበቁ ነበር በጣም የሚገርምና አስቂኝ ብቻ ሳይሆን የካድሬዎችን የማሰብ ችሎታ የወረደ እንደሆነ የታዘብንበት መልስ ተሰጠን ይህም "ስንዴ ልዝራበት እንጅ ፋብሪካ ለመገንባት አልችልም" አለን የሚል መልስ:: አይ ካድሬ አሁን እንዲህ ይላቸዋል ብሎ የሚያምን ሰዉ አለ ብለዉ ማሰባቸዉ ይገርማል ነዉስ ህዝብን ንቀት? ምንም ይሁን ምን የፋብሪካዉ ችሎት በዚህ መልኩ ተዘግቶ እንዳለ ከአንድ አመት በፊት ስለ ኢህአዴግ ቅዱስነትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸባሪነት ቀባጥራ የማትሰለቸዉ ሚሚ ስብሀቱ ሀብት የሆነዉ ዛሚ ሬዲዮ በእናስተዋዉቃችሁ ፕሮግራሙ ደብረ ማርቆስ በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንዳለ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳዉን ነዛ:: ይህም አልፉዋል:: መኪና ፋብሪካና ደብረ ማርቆስ ስማቸዉ መያያዙ አሁንም አልቀረም:: ሰሞኑን ደግሞ ድሬ ቲዩብ እና ፋና ብሮድካስቲንግ በድህረ ገፃቸዉ ይህን መሰል ዘገባ ይዘዉ ወጥተዋል::ድሬ ቲዩብ "የድብረ ማርቆስ መንገዶች በቅርቡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎች ባለቤት ይሆናሉ" ብሎ እንዳስነበበን ከሆነ እነዚህ መኪናዎች የሚመጡት ከአሜሪካ እንደሆነና ቻርጅ የሚደረጉት ማርቆስ እንደሆነ ገልፆ ቻርጅ የሚያደርገዉ ፋብሪካ ግንባታ 2005 አጋማሽ ላይ ተጀምሮ 2006 አጋማሽ እንደሚጠናቀቅና ስራ እንደሚጀምር አክሎዋል::ፋናም እንዲሁ:: እንዲህ ከሆነ መልካም ነዉ::እንደ ቀድሞዉ ፋብሪካ በወሬ ከቀረ ግን ባለስልጣናትና ካድሬዎች ምን ይሉን ይሆን? ቀድሞ ስንዴ ልዝራዉ አለን ስላሉ አሁን ደግሞ ተራዉ የበቆሎ ይሆን? አደራ በቆሎ ሊዘራ ነዉ እንዳትሉን::

መብራት የሌላት በመብራት የሚሰራ መኪና ሊገነባላት የታሰበች ከተማ

መልካም መመኘት አይከፋምና ፋብሪካዉ እዉን ይሆናል ብለን ብናስብ እንኩዋ ጥያቄዉ መኪናዉ የሚሰራዉ በምንድነዉ የሚለዉ ነዉ::በኤሌክትሪክ እንዳንል መብራትና ማርቆስ የተጣሉ ይመስላል::ዉሀና መብራት ማርቆስ ላይ ቅንጦት ሆነዋል::መብራት ለአንድ ቀን እንኩዋ ሳይጠፋ አይዉልም::ፀጉር ቤት ገብተህ መብራት ሳይጠፋ ተስተካክለህ ከጨረስክ አንተ እድለኛ ነህ ወይም ፀሎትህ መሬት ላይ ጠብ አይልም ማለት ነዉ:: አልያም ደግሞ ማርቆስ ዉስጥ ስለመሆንህ ተጠራጠር::መብራት እንደ ዲም ላይት ብልጭ ድርግም ማለት የማርቆስ ልዩ መለየዋ ነዉና::ሆቴል ዉስጥ ተመግበህ ዉሀ ብትፈነዳ አታገኝም::ታዲያ መኪናዉ በነፋስ ይስራ ? ለማናኛዉም ቆሞም ቢቀር ዜናዉ እዉን ይሆን ዘንድ መልካሙን እንመኛለን ::
 
 
Solomon Tibebu

No comments:

Post a Comment