Tuesday, October 22, 2013

አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ክፍል 3


ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን! አቤቱ አባት ሆይ ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ ከእኛ ወገን በሆነች ቅድስት፣ በንጽህትና ዘላለማዊት ድንግል እናትህ ሥም እለምንሀለሁ! አሜን!
በቅዱስ መጻህፍ ስለ እምነት (ሐይማኖት) የተነገረው በዚህ ዘመን ሲሆን አናየውም፡፡ ሊያውም በማያሻማ ቃል ለሚያምን ሁሉ ይሆንለታል ነው የሚለው፡፡  ብዙ ሰባኪያን ነን የሚሉ መጽሐፉን እያነበቡ ይላል እያሉ ይነግሩናል እንጂ በእነሱም ሕይወት ያ የተጸፈው የሀይማኖት ኃይል አይታይም፡፡ የጥንቶቹ ሀይማኖት ተራራ ያፈልሳል ቢሉ እውንም በአስፈለጋቸው ጊዜ ተራራውን አፍልሰውት ይሆናል፡፡ ለመጥቀስ ያህል ሙሴ ቀይ ባህርን፣ ኤልሳዕ ዩረዲያኖስን እንደከፈለ፣ ኢያሱ ጸሀይን እነዳቆመ፣ ኤልያስ ሰማይን እደለጎመ፣ ሌሎችንም በሰው ልጆች የተከናወኑ የእግዚአብሔር ሥራ አንብበናል፡፡  የእኛው ዘመን ነገር ግን ግራ አጋቢ ነው፡፡ ዝም ብለን በጅምላ እንጓዛለን! የጥንቶቹ እንዲህ የሀይማኖትና የራዕይ ኃይል ሲጠፋ እግዚአብሔር በአንድ ነገር አዝኖብናል ብለው በለሆሳስ ጩኸታቸውን (እግዚአብሔር ብቻ በሚሰማው) ለልዑል አማላክ ያሰማሉ፡፡ የዛሬዎቹ ሰባኪያን ጆሮ በሚበጥስ ሜጋፎን ጩኸታቸውን ከተማና መንደር እስከሚበጠብጥ የሀይማኖት ምንነት ለተምታታበት ሕዝብ ያሰማሉ፡፡ የዱሮዎቹ የልዑል አምላክ ኃይል እያስጨነቃቸው ይናገራሉ የዛሬዎቹ ንግግራቸው እንዲደነቅላቸው ይጨነቃሉ፡፡ ብቻ በዚህ ዘመን የእግዚአብሔርን ኃይል የካዱ ሕዝብን ሀያማኖት በሚል ማስፈራሪያ አጥምደው ራሳቸውን አግዝፈው የሚኖሩ ሰባኪ ወይም ደግሞ አገልጋይ ተብዬዎች እንደበዙብን እናስተውላለን፡፡ ራሳቸው የማያደርጉትን ሕዝብ ላይ ይጭናሉ፡፡ እርግጥ ነው ጌታ የሚሏችሁን እንጂ የሚያደርጉትን አታድርጉ ብሎ ነበር የአይሁድ ካህናትን አስተምህሮት እንዲሁ እንደዛሬዎቹ ሆኖበት፡፡ በአሁን ጊዜ ግን የሚሉንም ጥፋት ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ የሚያሻው ሆኗል፡፡
እንግዲህ በራስ የሚገለጥ እምነት ሳይኖር ሌላውን ለማስተማር መሞከር ምን ያህል አደጋ እንዳለው እናስተውል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ ምክነያቱ ብዙ አገልጋይ ተብዬዎች ለሥጋዊ ጥቅም ሲሉ ያገለግላሉ እንጂ ለእውነትና የሀይማኖት ነገር አስጨንቋቸው አይደለም፡፡ ጌታ በአንደ ወቀት ብዙ ሕዝብ ሲከተሉት አይቶ ስለበላችሁ ተከተላችሁኝ ግን ስለማመናችሁ አይደለም ብሎ ነበር፡፡ ለእውነተኛ አገልጋዮቹ (ሐዋርያት) ግን የነበረው ትዕዛዝ "በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ" ነበር፡፡ እንግዲህ ዛሬ በደሞዝና አበል ካልሆነ ንቅንቅ አንልም የሚሉት አገልጋይ ተብዬዎች ናቸው የእኛው ዘመን የሐዋሪያትን ቦታ የያዙት፡፡ እና እነዚህ ማንን እያገለገሉ ነው? ስለበሉ (ስለተከፈላቸው) እንጂ ስለማመናቸው እያገለገሉ ነው?  ይበልጥ ክፋቱ ደግሞ እነዚህ የሥጋ ጥቅም አገልጋዮች ከላይ እስከ ታች ቁልፍ የሀይማኖት መዋቅራዊ ሰንሰለቶችን ስለተቆጣጠሯቸው የንጹሀን አገልጋዮች ሥራ ሊታይ አልቻለም፡፡  ብዙ ተራ ምዐመን በየ አቢያተክርስቲያናቱ በነጻ አልፎም የራሱን ሀብትና ንብረት በመስጠት ያገለግላል፡፡ በዚህ ዘመን ክፍያ የለም ቢባል አገልጋይ ነኝ የሚል ምን አልባት በጣም ጥቂቶች ሲቀሩ ግማሹም ቀሚሱን ሌላውም ከራቫቱን እያወለቀ መንገድ ላይ ወጥቶ አገለግላለሁ የሚልበትን ሀይማኖት ሊረግም ቀዳሚ ይሆናል፡፡ እና እነዚህ የሚያስተምሩት ነው ሀይማኖት?! እነዚህ የሚመክሩን ነው ተግሳጽ?! በውልም ሲታዩ ሁሌም ወደበሉበት እንጂ ወደ አመኑበት አይደሉም፡፡ በአገራችን በየሀይማኖቱ ውስጥ ያለውን የአገልጋይ ተብዬዎች የጥቅም ማደርን ስናይ አስደንጋጭነቱ የከፋ ነው፡፡ ለዛም ይመስላል ዛሬ ብዙዎች በጥቅም ሲያኮርፉ ከአንዱ ወደሌላ የማይመስላቸው ሀይማኖት ያለምንም ጭንቀት የሚቀያየሩት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በገንዘብ ግዝፈት ሲታይ አነስተኛ መንግስት ሊያሰኛት ይችላል ግን ምን ዋጋ አለው በአብዛኛው የማያምኑ አገልይ ተብዬ ጠላቶቿ እጅ እንደገባ እናስተውል፡፡ አትስረቅ የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ በይፋ የተሰረዘባት ሆናለች!  ሰይጣን ብዙዎችን በጥቅም አውሮ ሥራውን እያጣደፈ ይገኛል፡፡ እምነቱም ሕዝብ ጋር እንጂ አገልጋዮች ጋር በጥቂቶች ብቻ እንደቀረ እንገምታለን፡፡ የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ሂደት ቀስ እያለ ወዴት እንሚያመራ አናስተውል፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ  ውሻ ይደፋብሻል፡፡
የብዙ የቀደሙ አባቶች በገሀድ የሚታይ ለየት ያለ ጸጋ ምክነያቱ እራሳቸውን ከሥጋ ጥቅም ገድበው ለሰማያዊ ክብር ካላቸው ናፍቆት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለሚበላው ምግብ ሳይቀር ለሚያገለግላቸው ሰዎች እንዳይከብድ ይበልጠውንም ለእግዚአብሔር መንግስት ስብከት አገልግሎት የሚረዳውን ድንኳን ይሰፋ እንደነበር እናስተውል፡፡ ይህ ሰው እንግዲህ የሚሰፋው ድንኳን ቁርጥራጭ ጨርቅ ሳይቀር ድውይን የሚፈውስ ነበር፡፡ በዘመናት ያሉ አባቶችም ተመሳሳይ ሕወት ያላቸው እንደነበሩ የተመዘገቡ ታሪኮች ይጠቁማሉ፡፡ ከራሳቸው ለሌላ እንጂ ለእግዚአብሔር ለሚውል አገልግሎት ዋጋ የማይቀበሉ ነበሩና፡፡ በመሆኑም ያ በመፅሐፍ የተገለጸው የእምነት ኃይል የሚታይባቸው ነበሩ፡፡ በዘመናችን ጥቂት ቀሩ የተባሉ ለየት ያለ ፀጋ ያላቸው የሕወት ሚስጢር ሲታይ ለእምነት አገልግሎት ዋጋ የማይቀበሉ ቢቀበሉም ለሌላ የሚሰጡት እንደሆኑ እናያለን፡፡ እንደነዚህ ያሉት አገልጋዮች ከመሠረቱም ስለሚያገለግሉት ሰማያዊ አምላክ የተረዱ፣ ጸሎታቸውም ከእምነት የሆነ፣ አኗኗራቸውም በአምላካቸው ሥርዓት እንደሆነ እናያለን፡፡ ለምሳሌ በዘመናችን የልዑል አምላክን ኃይልና የክፉ መናፍስትን ሴራ ገሀድ እያወጡ ያሉት የፈላስፋው የመ/ር ግርማ ሚስጢር ይሄው ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አገልጋዮች ለሚያምኑት አምላክ ያገለግላሉና ጸጋው ቢኖራቸው አይናሩም፡፡ በተመሳሳይ ሌላ በቅርበት የማውቃቸው ካህን ጸጋ አውቃለሁ፡፡ እኚህ ሰው በቅርብ የማቃቸውም ቢሆን ከእኔ ይልቅ ለዘመናት ሌሎች ሰዎች ጸጋቻን ያውቁ ነበር፡፡ እኔ አላውቅም ነበር ስለማይነግሩኝም፡፡ ካሕን ናቸው ግን አምስት ሳንቲም ከቤተክርስቲያን አይቀበሉም፡፡ ለእኔም አንድ ወቅት ጠይቄያቸው እኔ ጉልበት (ወጣት ናቸው) አለኝ ሰርቼ መኖር እችላለሁ፡፡ እግዚአብሔርን እየተከፈለኝ ካገለገልኩት ለእኔ ዋጋዬ ምኑ ላይ ነው ነበር ያሉች፡፡ እኚህ ሰው እንዳልኳችሁ የቅርቤ ሰው ቢሆኑም ጸረ-አጋንንት እንደሆኑ የሰማሁት ከሌላ ሰው ነው፡፡ እኔም አልጠይቃቸውም፡፡ አንዳንዶች እንዲህ ያሉ አሉ ግን እነሱን ማንም አያውቃቸውም፡፡ ሰው የሚያውቀው ሰፋፊ እጄታ ያለውን ቀሚስ ለብሰው በየአደባባዩ የሚታዩትን በየጉባኤው ከፍተኛ ድምጽ የሚያሰሙትን ነው፡፡
ብዙዎች መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጭዎች ከነሱ ሌላ ለሕዝብ ያላቸው ግምትም የተዛባ ነው፡፡ ሰባኪው ከእሱ ሌላ አዋቂ የለም፣ ዘማሪውም ከእሱ ሌላ መንፈሳዊ ዘማሪ የለም፣ በአጠቃላይ እነዚህ ሰዎች ከነሱ ሌላ መንፈሳዊ የለም፡፡ ግን እንደዚህ ያሉ አገልጋዮች የአምልኮት መልክ አላቸው እንጂ ከመሠረታዊ ነገራቸው ሁሉ ከአምልኮት የራቀ ሥጋዊ ብቻ የሆነ አገልግሎት እንደሆነ እናስተውል፡፡ ብዙዎቹ ለቅዳሴና ሌሎች የልዑል አምላክን ኃይል የሚያሰጡ ጸሎት ሥርዓት ላይ እንኳን አይገኙም፡፡ ሰባኪው  ሜጋፎን፣ መድረኩና ሌሎች የመድረክ አሸንክታቦች ከተዘጋጅቶለት በኋላ ነው የሚታየው፡፡ ብዙም ጊዜ በሚሰበኩበት ጉባዔ የመክፈቻ ፀሎት ላይ አንኳን ሰባኪ ተብዬዎች አይገኙም፡፡ ዘማሪ ነን ባዮችም እንደዚያው ነው፡፡ እንደዛሬ ከሜዳ እንደመጡ ዘው ተብሎ እንደሚጋበበት ሳይሆን ድሮ ድሮ በኪዳን ላይ ያልተገኘ ካህንና ዲያቆን በቅዳሴ አይሳተፍም፡፡ ምክነያቱ ደግሞ ከዋናው አገልግሎት በፊት በጸሎት አምላክን ስለአገልግሎታቸው መጠየቅ ነበረባቸውና ነው፡፡ እንግዲህ እናስተውል ብዙ ሰባኪ ነን፣ ዘማሪ ነን፣ ሌላ አገልግሎት ሰጭ ነን የሚሉ ሁሉ የሚያደርጓቸው ምን ያህል ከመሠረታዊ የአምልኮት ሥርዓት እንደ ወጡ፡፡ ከእነዚህ አይነት አገልጋዮች በየቧህነት የሚሰማቸው ምዕመን በብዙ እጥፍ እንደሚበልጣቸው ሳያውቁ ሕዝቡን ይንቁታል፡፡ እነሱን ግን ሁሉን የሚያይ አምላክ ንቋቸዋል፡፡
ዛሬ ዛሬ በከተሞች በተለይ በአድስ አበባ ይባስ ደህና ክፍያ የሚከፈላቸው ብዙ ዲያቆናትና ካህናት ቅዳሴ ገብቶ ላለመቀደስ ሌላ አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው በገንዘብ ገዝተው በእነሱ  እንዲያገለግል የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እንግዲህ ቅዳሴን የሚያህለ ጸሎጽ ይህንን ያህል ከመጥላት የመጣ የክፉ መንፈስ ልዩ ሴራ እንደሆን እንገንዘብ፡፡ ገንዘብ ተከፍሎት በእነሱ ቦታ የገባውም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የሚቀድስ ሳይሆን ስለተከፈለው "ይቀድሳል"፡፡   እንግዲህ ይሄ ነው አገልግሎት ብለው የሚየወሩት፡፡ በቤተክርስቲያኗ ብዙ ክፍያ የሚከፈለቸው ሥማቸውን ያገዘፉ "ሊቀ ምናምን፣ መጋቤ ምናምን፣ መምህር እከሌ ምናምን" የሚሉ ትልልቅ ሥሞችን ተሰጣጥተው በየክበረ በዓላቱና በየመድረኩ ከእግዚአብሔር ሥም ይልቅ አንዱ የሌላው  እያነሳ እየተሞጋገሱ ሕዝብን የሚያሰለቹ ናቸው፡፡ እንደነሱ በየጉባዔው የሚገኘው ሁሉ ከእነሱ በታች የሆነ ነው፡፡ እርግጥ ነው በቤተክርስቲያኗ ቅኔ እየተባለ በሚቀርበው መወድስም ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ይህ ራስን ማወደስ ልምድ ቀስ እያለ የልዑል አምላክን ክብር እየረሳ ለሰው በሚደረግ ውዳሴ የመጣ ልክፍት ነው፡፡ ማህሌታዊውን ያሬድ እንመስለዋለን የሚሉት እንግዲህ እነዚህ ናቸው፡፡
ድምጻቸው በጉባዔ ነጎድጓድ እንዲመስል ይፈልጋሉ፡፡ አንዳነዶቹም በተፈጥሮ የሌላቸውን ድምጽ ለማውጣት ይሞክራሉ፡፡ ከአንደበታቸው ግን ምንም የሚረባ ቃል አይወጣም፡፡ ሕዝቡን አስሬ "እልል በሉ፣ አመስግኑ" እያሉ ስለምን እነኳን እልል እንደሚል ሳይገባው እልል አያስባሉ ሕዝቡን አደንዝዘውታል፡፡ በቅርብ በአንድ ክብረ-በዓል ላይ ተገኝቼ አንድ  ስለዚህ የሕዝብ መደንዘዝ፣ መድረኮች በጩኸት እንጂ ለሰው በሚገቡ ቃላት እንዳልታነጹ የተረዳ አገልጋይ ሕዝቡን መጀመሪያ ከልባቸው እንዲያደምጡ ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሆን ብሎ "ኢትዮጵያ በኤች አይቪ ከአፍሪካ አንደኛ ሆነች ደስ ይበላችሁ" ይላል ከዚያ ቅልጥ ያለ እልልታ ይሆናል፡፡ በጣም እያዘነ አሁንም ሕዝቡ ከልቡ እንዲሆን ከመከረ በኋላ ስብከቱን ቀጠለና የሆነ ቦታ ሲደርስ "ኢትዮጵያ በአለም ዲክሸነሪ ሳይቀር በረሀብ ትታወቃለች ደስ ይበላችሁ" አለ አሁንም እልልታው ቀለጠ፡፡ በዚህ ጉባዔ የአዲስ አበባ ቤተክህነት ሥራ-አስኪያጅና ሌሎች ትላልቅ አባቶች ነበሩ፡፡ በቃ ሕዝቡ ሰባኪ ነን በሚሉ ጩኸት ደንዝዟል! አሳዛኝ ነው! ሌላው ሥብከት በየካሴቱ ቪሲዲው ምናምን ሲያደምጥ ይውላል፡፡ ግን ስብከቶች ሁሉ ድንፋታ እየሆኑ ስለመጡ ይህን የዘመኑት የድነፋታ ስብከት ተለማምዷል፡፡ እንደ አሸን ከሞላው የሰባኪያንና ስብከት በጣም ጥቂት ከሚባሉት በቀር በደንብ አስተውላችሁ ከሆነ አንድም ቁም ነገር የለበትም፡፡ ግን በከባድ በከባድ ቃላት በማጀብ በደንብ በሚያስተጋባ ድምጽ ሲቀርብ ደህንነት የሚሰብክ ይመስላል፡፡ የብዙ ሰባኪያን ርዕስንም ስንመለከት ከእግዚአብሔር መንግስት ጋር ሳይሆን ለካሴትና ቪሲዲ ምቹ መሆን አለመሆኑ ነው ዋናው አላማ፡፡ አንድ ለየት ያለ አጋጣሚ ከተፈጠረ ያንን አጋጣሚ በቪሲዲ አውጥቶ ለመቸብቸብ ነው እንጂ እውንም ስለሕዝብ ከመጭነቅ አይመስልም፡፡ ስለሕዝብ ከመጨንቅ አንጻር ቢሆን ዛሬ ሚዲያ በሞላበት ዘመን ከአንዱ ጋር በመተባበር በነጻ  ባስተላለፉት ነበር፡፡ በዚያውም ብዙ ሕዝብን በአንደ ጊዜ ማዳረስ በሚቻልበት ሁኔታ፡፡ ጉዳዩ ግን ሐይማኖትን ተገን ያደረገ ንግድ ነው፡፡ መዝሙሩም እንደዚያው፡፡       
ጥንታዊያን የሀይማኖት ፈላስፎቹ/ጠቢባኖቹ የቱንም ያህል ጻድቅ ቢሆኑ ጽድቃቸው ለእግዚአብሔር ምንም እንዳልሆነ ያውቁታል፡፡ አዚህ ላይ ጠቢብ እውንም ጻድቅ የነበረው ኢዮብ ጻድቅ እንደሆነ በማሰቡ ከእሱ(ኢዮብ)ና ሶስቱ የኢዮብ ወዳጆች በእድሜ የሚያንሰው ግን በጥበብ የሚበልጣቸው ኤልዩስ ኢዮብን ሲገስጸው "ጻድቅ ብትሆንስ ለእግዚአብሔር ምን ታደርግለታለህ፤ ሐጢያተኛስ ብትሆን እግዚአብሔርን ምን ታደርገዋለህ" ብሎት ነበር፡፡ እውነት ነው! ጻድቅስ ብንሆን ለእግዚአብሔር አውን ምን እናደርግለታለን ለራሳችን ተጠቀምን እንጂ! ኀጥያተኛስ ብንሆን እግዚአብሔርን ምን እናደርገዋለን ለራሳችን ተጎዳን እንጂ፡፡ እውነተኛ አገልጋይ እንኳን ብንኆን ለእግዚአብሔር ምንም እንዳላደረግንለት ማሰብ መቻል ነው የጥበብ ሚስጢሯ፡፡ የዛሬዎቹን አገልጋይ ተብይዎች እንዲህ የሚስታብያቸውና   የሚነዳቸውም አብሯቸው የተወለደ ዛር፣ ልክፍትና ለእውቀት ይሆናል እየተባለ በድግምትና በአብሾ የገባ ክፉ መንፈስ መሆኑን አንዳነዶቹ አይረዱትም የሚረዱትም ለሥጋዊ ጥቅማቸው እየረዳቸው ስለሚመስላቸው ተደብቀውበታል፡፡ ሕዝብ ግን ስለጮሑ ብቻ እውነተኞች አድረጓቸዋል፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል!
ብዙዎችም ቤተክርስቲያኗ ከምትከፍላቸው በተጨማሪ በመተትና ሟርት ሥራ ገንዘብ እየተቀበሉ የሕዝብና የሀገር ሞት የሆኑትን፡፡ እኛን አባቶች የሚመስሉን እነግዲህ እነዚህ ሁሉ ናቸው፡፡ አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል፡፡ አንዳንዴም እንዲ አደርግሃለሁ እያሉ በግልጽ ያስፈራራሉ፡፡ ብዙዎች ከመሠረታዊ የትምህርት ሂደታቸው ላይ የተበከለ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡ ትምህርት ይገልጣል እየተባለ በአብሾ የተለከፉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በአብዛኞቹም የክፉ መንፈስ ተለካፊዎች ሆነው ራሳቸውም አያውቁትም፡፡ እነሱም ሌላውን በክፉ መንፈስ ሲመረዙ ራሳቸው ነጻ እንደሆኑም የሚያስቡ አሉ፡፡ አብዛኞቹንም ያ ሲያገለግሉት የኖሩት ድብቅ መንፈስ አይሆኑ አድርጎ ሲገድላቸው ይታያል፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ  ውሻ ይደፋብሻል!
በአጠቃላይ እኛ አገልጋይ እያልን በተከተልናቸው ብዙ አገልጋይ ተብዬዎች መንገድ እንደሳትን እናስተውል፡፡ ይህን አጋጣሚ አገልጋይ ነን የሚሉ ሁሉ ከሁሉ በፊት ለልዑል አምላክ እንዲንበረከኩ የግድ ይላቸዋል አላለሁ፡፡ ሕዝብን ከመሠረታዊ አምልኮት እያደነዘዙት መሆኑን ይረዱ፡፡ አገልጋይ ነኝ የሚል መጀመሪያ ከልዑል አምላክ ኃይልን ይቀበል፡፡ ከዚያ ያዩታል፡፡ ድምጻቸው ዝም ብሎ ጩኸት ሳይሆን የሄ ሕዝቡን የሚያደነዝዘውን አጋንንትን የሚያስበረግገው ይሆናል፡፡ አስተውሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲያስተምሩ ብዙ ርኩሳን መናፍስት በአደሩባቸው ሰዎች ይጨነቃሉ፡፡ ሕዝቡ እጅግ በመመሰጥ ያደምጣል፡፡ ንግግራቸው ልብ የሚሰብር ነው፡፡ በአንዲት የጉባዔያቸው ቀን ብዙዎችን ወደ ንስሀ የመልሳሉ፡፡
አቤቱ አባት ሆይ ሕዝብህን በአንተ አምልኮት የሚያነጹ፣ ምህረትህን የሚያሰጡን እውነተኛ አገልጋዮች ስጠን! አሜን! 
የታላቋ ቀን ልጅ ጥቅምት 12 2006 ዓ.ም (Son of the great day, October 22, 2013)    
     

No comments:

Post a Comment