Thursday, October 24, 2013

አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ክፍል 4




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን! አቤቱ አባት ሆይ ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ ጥበብህን በማስተዋል በኖሩት ወዳጆችህ ሥም እለምንሀለሁ! አሜን!
ባለፈው ጽሑፌ እርኩስ መንፈስ እንዴት በዘመናዊነታችን ውስጥ እየሸረሸረን እንዳለ ጥቂት ማሳያዎችን ጠቁሜ ነበር፡፡  በመሠረቱ ዘመናዊነት ብልጽግናን ከሚያሳየው ትርጉሙ አንጻር ችግር የለበትም፡፡ እንዲህ ያለው ዘመናዊነት የቀደመውንም ጠንቅቀው በሚያውቁ መጻዒውንም በሚተነብዩ ለየት ያለ ማስተዋል በሚኖራቸው ሰዎች የሚታይ አኗኗር ነው፡፡ ይሄኛው አይነት ዘመናዊነት በትክክልም የሰው ልጆችን ጥበብ ከጊዜ ወደጊዜ እያደባረ የሚሄድ ዘመናዊነት ነው፡፡ ለብዙዎቻችን ትርጉም የሚሰጠን ዘመናዊነት ግን ከዚህ የሚቃረን ገጽታ ያለው ነው፡፡ በአጠቃላይ በእኛ ዘንድ ትልቅ ትርጉም ቦታ ያለው ዘመናዊነት መነሻው ጥበብ ንቃ የከዳችው ተቦርቡሮ ባለቀ አእምሮ የሚታሰብ እንደሆነ ለብዙዎቻችን ግልጽ አይደለም፡፡ የጥበብ ምንጭ የሆነችውን ትተን በእንዲህ ጥበብ በናቀቻት ዘመናዊነት ደግሞ እንድንጠለፍ ምክነያቱም  የእርኩሳን መናፍስት ሴራዎች እንደሆኑ አይገባንም፡፡ የእኛንው አገር እንደ አንድ ጥበብ እንደከዳቻት አገር ስናይ ሂደቶችን ሁሉ ለሚያስተውል አስገራሚና ምን እየሆንን ነው የሚሰኝ ግራ መጋባትን ይፈጥርበታል፡፡ በክፍል አንድ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ጽሑፌ በአንድ ታዋቂ ሰው ግብዣ ከአንድ መጸሐፍ ውስጥ ስለአነበብኩት አስገራሚ አንቀፅ ጠቁሜ ነበር፡፡ መልዕክቱም "የኢትዮጵያውያንን አእምሮ ማይክሮ ችፕስ በመጠቀም እናፈዘዋለን ከዚያም የአሪቱን ሀብትም አገርቱንም እንቆጣጠራለን" የሚል ነበር፡፡ እንደነገርኳችሁ በወቅቱ ቀልድ ነገር አድርጌ ወስጄው ነበር፡፡ ነገሩ ግን እየቆየ እውነት የሚሆን ነገር እንደሚሆን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ሂደቱንም በሚታዩ ክስተቶች ጭምር ማገናዘብ ጀመርኩ፡፡
በብዙ የበለጸጉ አገራት ድርጊቶች በአብዛኛው ትርጉም ያላቸውና ምክነያታዊ ናቸው፡፡ የእኛው አገር ግን ለምን ቢባል መልስ የማይገኝላቸው ብዙ ክስተቶች በተለይም አሁን አሁን የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ጉዳዮቹ ከአገር መምራት እስከ የግል ኑሮ ሥር የሰደዱ ስለሆኑ ለማሳያነት ብቻ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
ማይክሮ ችፕስ 1፡ ትውልድን የሚያመክን የትምህርት ሂደት፡  ለአንድ አገር ብልጽግና መሠረት የዜጎች በዕውቀትና በጥበብ መበልጸግ እንጂ ሕንጻና ግድብ መገንባት እንዳልሆነ የትኛውም ጤነኛና አስተዋይ አእምሮ የሚስበው ነው፡፡ ዜጎችን በዕውቀትና በጥበብ ለማነጽ  ደግሞ ትምህርት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እውነተኛውንም ዘመናዊነት ለማምጣት ቁልፍ ነው፡፡ አንድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስት መቶ ክፍለ ዘመን ተነገረ የተባለ የቻይናውያን ድንቅ አባባል አለ "ለአመት ብቻ የምታቅድ ከሆነ አዝዕርት ዝራ ወይም ጎመን ትከል፣ ለአመታት የምታቅድ ከሆነ ዛፍ ትከል፣ ለብዙ ዘመናት የምታቅድ ከሆነ ትውልድህን በጥበብ አሳድግ" ይላል፡፡ ምን አልባት ይህ መርሆ በጥንታዊያኑ ኢትዮጵያውያን ተተግብሮ ይሆናል፡፡ ቢያንስ ከነላሊበላውያን/ዛግዌዎቹ በኋላ ግን የእኛው አገር ዜጎችን በጥበብ የማነጽ ሂደት የክፉ መንፈስ ሰለባ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ እንኳን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ጥበብ ሊቀርልን በጥበብ ስም ጠብባን የሚጠፉበት ልዩ የመናፍስት ሴራ በዚች አገር ራሱን ጥበብ አድርጎ ብቅ አለ፡፡ የዕፅዋትን ምርምር አድርገው ለሰው ልጆች የተለያዩ ደዊያት ፈውስ የሚሆኑ መድሀኒቶች ጥልቅ ዕውቀታቸውን ለትውልድ እንዲደርስ በዚያ አለም ኋላ ቀር በነበረበት ዘመን በመጽሐፍ መዝግበው ያቆዩት የጥንታዊያኑ አባቶች ጥበብ አጋንትንና ሰይጣናትን አጋዥ በሚያደርጉ ክፉ ደብተራዎች እጅ ገባ፡፡ ከዚያ በኋላ ይሄው እስከዛሬም ድረስ እነዚህ ድንቅ መድሀኒቶች ጥበብን በማያውቋት መሐይም ደብተራዎች እጅ ድብቅ ሆነው ለሌላ ላለማስተላለፍ ካለቸው ስግብግብነት ሲሞቱ አብዋቸው እየሞቱ ጥበቡ እየመነመነ ይገኛል፡፡ በጥንታዊያኑ ጠበብቶች የተጻፉትም መጽሐፍቶች ጥበብን ለሚናፍቁ የሌሎች አገራት እጅ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ በምሳሌነት በእንግሊዝ አሉ ተብለው የሚገመቱ የመጽሐፈ ፈውስንና መጽሐፈ-መድሀኒትን ማንስት ይቻላል፡፡
በስነሕንጻው ብዙ ማለት አያስፈልግም፡፡ ከቅድመ ታሪክ እስከ ዘመነ መሳፍንት ድረስ ብንወስድ ቢያንስ ሶስት ዛሬም የቆሙ አበይት ግዑዛን ምስክሮችን እናያለን፡፡ የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያን፣ የጎንደር/ሐረር ግንብ፡፡ በእኔ መስፈርት ሳወዳድራቸውና እኔ እንዳነበብኳቸው በረቂቅነታቸውና በአስደናቂነታቸው የጥንቱ በኋላ ከመጣው ይበልጣል፡፡ የአክሱምን ሀውልት ያየ ሰሞኑን በዘመናዊ ጠቢባን የተገነባ እንጂ ከአንደ ወጥ ድንጋይ ሌላ ቦታ ተሰርቶ እዛ መጥቶ የተተከለ የቅድመ ታሪክ አሻራ አይመስልም፡፡ ከአንድ ድነጋይ እንደተሰራ እኔ ማስተዋል የቻልኩት ወድቆ  ከተጋደመውና ከተሰበረው ሀውልት ነው፡፡  አፈጻጸሙም በዘመናዊ ማሽኖች  ይመስላል፡፡ ላሊበላም ከብዛቱና ብዛቱና ግዝፈቱ ጋር ድንቅ መባል ያንሰዋል፡፡  ጎንደር ስመጣ ግን ምንም ይሄ ግባ የሚባል አስደናቂ ነገር ለማየት አልቻልኩም ከታሪክ ምስክርነቱ ውጭ፡፡ የጎንደር ግንቦች ሲሰሩ በአውሮፓ አስደናቂ የተባሉ እነ ፓሪስ ሳይቀር በከተማነት ደረጃ ተሰርተዋል፡፡ ጎንደርም የተሰራችው በኢትዮጵያውያን ሳይሆን ከዚያ (ከአውሮፓ) በመጡ ሰዎች ነው፡፡ ምህክነያቱም እኛ ጋር ምንም የቀረ ጥብብ ስላልነበረ ምንአልባት የእኛ ተሳትፎ ለጎንደር ግንብ ሊያውም አላዋቂ የሰራው ዝም ብሎ የድንጋይ ካብ ለሆነው ዛሬ ለቻይናዊያን እያደረግን እንዳለንው ያኔም ድንጋ አቀብለን ይሆናል፡፡  ከላሊበላ እስከ ፋሲል ግንብ ግን ምንም ምልክት የሚሆን የለም፡፡ ነጉስ ተብዬ ዱርዬ ነገስታትም እንደ ተራው ሰው ይኖሩ ነበር፡፡ የነጠፈ አእምሮ ትውልድ ነበርና፡፡
በእነዚህ ዘመናት በሚበልጠው (ጥቂት ወደላሊበላ በተጠጉት ዘመናት በቀር) ሀይማኖታዊ የሆኑ ስነአእምሮዎች የነጠፉበት በተቃራኒው የክፉ መናፍስት አገዛዞች የገዘፉበት ነበር፡፡ በእነዚህ ዘመናት ቤተመቅደሳት በክፉ መናፍስት አገልጋ ደብተራዎች እጅ የወደቁበት፤ ባህል የክፉ መናፍስት ሥርዐት አስተናጋጅ የሆነበት ነበር፡፡ ደብተራዎች በቤተመቅደስ ቃልቻና ዛር እንጋሾች በየሰፈሩ አገሪቷን አጥለቀለቋት፡፡ ጥበብ አገር ጥላ ተሰደደች፡፡ ክፍ መናፍስትን በአብሾና በተለያየ መልክ ወደ ራሱ እያስገባ ሕዝብን ለሞትና ለስቃይ፣ አገርን ለውድቀት የሚዳርግ ደብተራና ጠንቋይ ቦታውን ተኩ፡፡ ትውልድም አሜን ብሎ ተቀበላቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ሁለት ነገስታትን ገድሎ (ቴዎድሮስንና ዩሐንስን) በብዙ ትግል በሶስተኛው(በሚኒሊክ) የተሸነፈው የአገሪቱ የክፉ አገልጋዩች (ደብተራና ጠንቋይ) ሴራ ሌላ ዕድል ለማግኘት አደፈጠ፡፡ ሚኒሊክም የዘመናውያን ጥበብ በአገሪቱ እንዲጀምር ብዙ ታገሉ ለብዙዎችም ዛሬ አሉን ለምንላቸው ቴክኖሎጅዎች ወደ አገራችን መምጣት ምክነያት ሆኑ፡፡ የብልጽግናው ሂደት ዋስትና እንዲኖረው በዘመናዊ ጥበብም ትውልድ የመታነፅበትን መሠረት ጣሉ፡፡ እንዲህ ለአገር እድገትና ብልጽግና ለሕዝብም ሟች የነበሩት ሕዝብም እምዬ ይላቸው የነበረው ሚኒሊክንም ቢሆን በመጨረሻ በደብተራ መተት በአጭር እንደተቀጩ ይነገራል፡፡ የጀመሩት የትውልድን በትምህርት ማነጽና ብልጽግና ሂደት ተስፋፍቶ በቀጣይ ነገስታት ወደ ዩኒቨርሲቲነት አደገ ውጤቱ ግን ዛሬም ድረስ ያ ትውልድ እያለ እራሱን የሚያኮፍሰውን የ60ዎቹ የሞት ትውልድ ሆነ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ክፉው መንፈስ ወሳኝ ገድል የሚፈፅምበትን ልዩ አጋጣሚ እየጠበቀ ነበር፡፡ ተሳክቶለትም ሶሻሊዝም በሚል የተነሳ ከውጭ በመጣ አጋዥ የክፉ መንፈስ ኃይል የተለፋበት ሁሉ መና ሆነ፡፡ ማንም ይሄንን ሂደት ሊያስተውለው አልፈቀደም፡፡ ሁሉም ግን የክፉ መንፈስ ሴራ እንደነበር ለማስተዋል እንሞክር፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል! ከወደመው የቀረው ያ እግዚአብሕርን የማያውቅ የጥፋት ትውልድ (በእርኩስ መንፈስ የተለከፈው) እስከዛሬም ድረስ ቀጥሎ በመከኑ አስተሳሰቦች ሌላ የመከነ ተተኪ እያፈራ ይገኛል፡፡ አንዱ ከሌላው ጎራ ለይቶ እርስ በእርሱ ከአንተ የእኔ ሀሳብ ይሻላል በሚል ይነታረካሉ፡፡ አንዳቸውም ግን የተሸለ ለማሰብ የሚችል አእምሮ የላቸውም እግዚአብሔርን ለማወቅ ያልወደደ የማይረባ አእምሮ ነውና፡፡ በመሀከል እነሱን የሚያደምጠው ተተኪው ትውልድ ከነአካቴው ጠፋ፡፡ ለጎንደር ግንብ መገንቢያ ለፖረቺጊዝ አላዋቂ ግንበኞች ድንጋይ ያቀብል እንደነበረው ገበሬ ዛሬም አለም በስልጣኔ የት በደረሰበት ዘመን እኛ ከዩኒቨርሲት  በምህንድስና ተመርቀን ለቻይና ግንበኞች ድንጋይ አቀባይ ሆንን፡፡ እስካሁን ያለው የተሸለ የተባለው ነው እንግዲህ ከድንጋይ አቀባይነት ያለፈ ጥበብ ያጣው ትውልድ፡፡ አሁን በዩኒቨርሲቲ ያለውን ጨምሮ ከታች ያለው ግን ይሄንንም ሊኖረው የሚያስችል አይመስልም፡፡  
ብዙ የግል የሚባሉ ትምህርት ቤቶች በሕግ እንኳን የሚዳኙ አይመስሉም፡፡ ብዙዎቹም የመካን አእምሮ መፍለቂያዎች ናቸው፡፡ ድሮ በግል ትምህርት ቤት መማር እንደ ልዩ እድል ነበር የሚታየው በአሁኑ ዘመን ግን ብዙዎቹ ለአገር አደራ የሚሆንን ዜጎችን እያሰለጠኑ ነው የሚመስለው፡፡ ባህልንም፣ ቋንቋንም ስነምግባርንም የካደ ትውልድ መፍለቂያዎች ሆነዋል፡፡ ኢንግሊዘኛ የሚናገር ግን ኢንገሊዘኛም ሆነ አማርኛ የማያነብ የ8ኛ፣ 9ኛ፣ 10ኛ ክፍል ተማሪ ቢገጥመን ብዙም ሊያስገርመን አይገባም በእነዚህ ትምህርት ቤቶች፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ራሳቸው ከሥያሜያቸው ጀምሮ አማርኛ ወይም ሌላ የአገር በቀል ቋንቋ ለማስተናገድ አይፈቅዱም፡፡ የትምህርት ቤቶቹን ሥያሜ ለተመለከተ በጣም አስገራሚና ትርጉሙ ራሱ ምን እንደሆነ ባልገባቸው መሀይሞች እንደተሰየመ እንረዳለን፡፡ ሲጀምር በየትኛውም መስፈርት ቋንቋ ሳይንስ አይደለም፡፡ አንድም በአለም ላይ በለጸገ የተባለ አገር በተውሶ ቋንቋ ያደገ አላውቅም፡፡ ብዙ የአለማችን በተለይም በቴክኖሎጂ ጣሪያ የደረሱ አገራት በራሳቸው ቋንቋ እንጂ በተውሶ አይደለም፡፡ አለምን ዛሬ በሳይንስ እያስደመሙት የሚገኙት አገራት ለምሳሌ ራሺያ፣ ጃፓን፣ ኮሪያ፣ ቻይና እና ሌሎች አሁን በጣም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉ አገራት ሳይንቲስቶቻቸው ሳይቀር እንግሊዘኛ የማይናገሩ ናቸው፡፡ እንግሊዘኛ የሚነገርባቸው (ዋናዎቹን እንግሊዝን፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኒውዚላንድ፣ አውስተራሊያን ሳይጨምር) አገሮች በሙሉ ማለት ይቻላል በራሷ ከሕንድ በስተቀር አንድም አገር የተሻለ እድገት የሚታይበት አገር አላውቅም፡፡ ሆንግኮንግ፣ ሲንጋፖርና የእኛዋ ደቡብ አፍሪካ በልዩ የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹ አገራት ተጽዕኖ ያደጉ ይመስላሉ፡፡ ሁሉም ግን የቀድሞ ቀኝ ገዥዎቻቸው ሆን ብለው (ልዩነትን ለመፍጠር) በሚያደርጉላቸው እገዛ ነው፡፡ አፍሪካዊቷ ደበብ አፍሪካ ለነባር ዜጎቿ አሁንም ቅኝ ግዛት ሥር ነች፡፡ ሕንድን ስናይ ኢንግሊዘኛውን ለዘመናት የአገሪቱን ቋንቋዎች እንዳይበክል የታገለች አገር ናት፡፡ ዛሬም ድረስ የሕንድ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ ከመሠረታዊ የአእምሮ ባርነት ጋር ይያያዛል፡፡
ብዙዎች የቀድሞ ቅኝ ግዛት አገራት ዛሬም ድረስ በአእምሮአቸው ባሪያዎች ስለሆኑ የድሮ ገዥዎቻቸው ነገር እንጂ የራሳቸው ዋጋ ያለው አይመስላቸውም፡፡ ሕንድን ስናይ ከአእምሮ ባርነት ነጻ የወጣ ሕዝብ ያላት ናት፡፡ ቀድሞም ቅኝ ግዛቱን ለዘመናት ታግላው ባሕሏ ሳይበረዝ አሸንፋዋለችና፡፡ ወደ አፍሪካ ስንመጣ ጉዳዩ ከተማሪው እስከ መሪው ባርነትን የሚወድ የራሱን ክብር ያዋረደ ነው፡፡ የእኛው አገር ደግሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አለመገዛታችን ከአእምሮ ባርነት ነጻ ሊያደርገን አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለንው ከተገዙትም በባሰ ባሪያ ሆነናል፡፡ እንዲህ ይህን ባርነት በግልጽ ስናገረው አይደለም ብሎ የሚያስብ ሊኖር ይችላል፡፡ እውነታው ግን ይሄ ነው! ይህንን ጉዳይ በማይከሮ ችፕስ 2 ላይ በሰፊው ላገልጸው እወዳለሁ አሁን የተነሳሁበት ማይክሮ ችፕስ 1 (ትውልድን የሚያመክን የትምህርት ሂደት) ስለ ሆነ ከትምህርት ሂደቱ ጋር ለማያያዝ አስቤ ነው ያነሳሁት፡፡ እንግዲህ የአብዛኞቹ በተለይም ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈልባቸው ከመዋለ-ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች የዚህ ባርነት ሁነኛ ተጠቂዎች እንደሆኑ እናስተውል፡፡   ወላጅ ደግሞ ምናአልባትም አዚም እየተደረገብት ሊሆን ይችላል (ዛሬ ብዙ ንግዶች የሚንቀሳቀሱት በሟርትና፣ ከሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ በሚደረግ የእርኩሳን መናፍስት አጋዥነት ነው) አንዲህ ባሉትን ትምህርት ቤቶች ውድ ዋጋ እየከፈሉ ልጆቻቸውን "ያስተምራሉ"፡፡ ማንነቱን የረሳ ተመራቂ ሆኖ ይወጣላቸዋል ማለት ነው፡፡
የትምህርት ጥራትን በተመለከተ በተለያዩ አካለት ሲደሰኮር ይሰማል፡፡ ግን በትክክልም ለተባለው ግብ የሚበቃ ትውልድን ለማፍራት የሚያስችል የትምህርት ጥራት ለመተግበር አንድም ቦታ ቁርጠኝነት ያለው አሰራር አይታይም፡፡ ሰይጣንም አብሮ ልክ ነው ጥራት መሻሻል አለበት እያለ ትውልድን የሚያመክነውን ልዩ ሴራ በስፋት ተያይዞታል፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻ! ዛሬ ከታች ከአጸደ ሕጻናት እስከ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ተማሪ ተብዬው የክፉው መንፈስ ቀለበት ውስጥ እንደገባ ላስተዋለው በገሀድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ትውልድን በዕውቀትና ጥበብ ያበለጽጋሉ የተባሉት ትምህርት ቤቶች  (ከመዋዕለ-ሕጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ) ዛሬ ክፉው መንፈስ በግልጽ ከልቅ የሆነ ወሲባዊ ልምምድ ወደ ግብረሶዶማዊነት አሳድጓቸዋል፡፡ ይህ ነገር አሁንም የግል በተባሉት ት/ቤቶች የከፋ ሂደተ ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውቻችን በጫትና በሌሎች ሱሶች የመከነ፣ በራምፓና ኦሾ የክህደት መንፈስ ያበደ ትውልድ መፍለቂያ ሆነዋል፡፡ የዛሬዎቹ ተማሪዎች ያ እራሱን እንደ ልዩ አዋቂ አድርጎ የሚቆጥረው እግዚአብሔርን የካደው የ60ዎቹ ዘመን ልጆች እንደሆኑ ልብ እንበል፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለግንወ መጠን የማይገባውን እናደርግ ዘንድ ተላልፈን እንደተሰጠንም ልብ እንበል! እውነት ነው! ግን ማንም ይህን አስተውሎ እግዚዖ ሊል የወደደ የለም፡፡ ሁላችንም አልተሳሳትንም በሚለው ድፍንነታችን ቀጥለናል፡፡ ልክ እንደ ኖህ ዘመን ሰዎች ይመስላል የእኛ ነገር፡፡ አነሱም ውሃው አስጥሞ እስኪያልቁ ድረስ እሰጠሙ እንኳን ሐጥያትን መሠራት ቀጥለው ነበርና፡፡ እግዚአብሔርን የካደ ትውልድ በራሱ እየሆነ ያለውንም ለማስተዋል በፍጹም አይቻለውም፡፡  ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ ተሰጥቷልና፡፡ የእዚህ አእምሮ አዛዥ ሰይጣን ስህተቱን ልክ ነው እያለ አንድንገፋበት ያደረገናል መጨረሻም ከእሱ ጋር ወደ ገሀነም የሚወድቁትን አባላቱን እያበዛ፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል!
በሚቀጥለው እንደ እግዚአበሔር ፍቃድ ማይክሮ ችፕስ 2 (ባህልንና፣ ሀይማኖትንና ራስ መሆንን ማሳጣት)፣ ማይክሮ ችፕስ 3 (የሕዝብ አስተዳደርና ፖለቲካን ማዘባረቅ/መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ) በሚሉ  የማይክሮ ችፕስ ሂደቶችን  አቀርብላችኋለሁ፡፡
እሰከዚያው ሁሉም እግዚአበሔርን ለማወቅ ሙከራ ያደርግ ዘንድ የታላቋ ቀን ልጅ ይማጸናል፡፡
አቤቱ አባት ሆይ እርግማናችን ይብቃ! በደላችንንም ይቅር በል! እናስተውል ዘንድ አእምሮአችንን ክፈት! አሜን! 
የታላቋ ቀን ልጅ ጥቅምት 14ኛው ቀን 2006 (Son of the great day 23 October 2013)         

No comments:

Post a Comment