Thursday, October 31, 2013

ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ


(ገለታዉ ዘለቀ)
reinventing
መግቢያ
የዛሬው የመወያያ ሃሳብ ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ መዋቅር በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ መዋቅር ኢትዮጵያን ወደ ኣዲስ ኪዳን የሚጋብዝ ነው። ኢትዮጵያ የገጠማት የከፋ ችግር በኣብዛኛው ከታችኛው የማህበራዊ ፖለቲካ (socio politics) መዋቅር ጋር የተገናኘ በመሆኑ በዚህ ላይ ኣማራጭ ሃሳብ ማምጣት በተለይ ይህ የኣሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ይመስላል። ያለፉትን ችግሮች ኣስር ጊዜ እያወጣን ብናወርዳቸው ድካም ብቻ ይሆንብናልና።
በተለምዶ ያ ትውልድ እያልን የምንጠራው ቀዳሚው ትውልድ ኣንድ የሆነ ሼል ሰብሮ የወጣ ነበር። ያ ትውልድ ለዘመናት የነበረውን ዘውዳዊ ኣገዛዝ ደፍሮ የጠየቀ፣ የፍትህና የእኩልነትን ጥያቄዎች ኣንግቦ ግንባሩን ለጥይት የሰጠ በመሆኑ ታሪክ ሁልጊዜም ያ ትውልድ….እያለ ሲያስታውሰው እንዲሁ ይኖራል።
ያ ትውልድ የሆነ ሼል ሰብሮ ሲወጣ ፍትህና እኩልነት እንደ እንጀራና ውሃ ለሰው ልጅ ያስፈልጋሉ ብሎ ያመነ እንደነበር መረዳት እንችላለን። ያ ትውልድ ለበሩለት ለነዚህ ቁልፍ ጉዳዩች ታላቅ ንቅናቄን ኣድርጓል። ይሁን እንጂ ፍትህና እኩልነት የሚበየኑበት ወይም መሬት ላይ ወርደው የሚከፋፈሉበት ሜካኒዝም በሚገባ ማጤን ተገቢ ነበረና ያ ትውልድ  ይህን ሃላፊነትም ተሸክሞ ነበር። የዘውዳዊው ኣገዛዝ ማክተሙ ብቻ ሳይሆን ፍትህ እንዴት በኢትዮጵያ ሁኔታ ይበየናል? የሚለው ጉዳይ ታላቅ የቤት ስራ ነበር።
የታሪክ ኣጋጣሚ ሆነና በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ ኢትዮጵያን ተጭኖ ስለነበር ፍትህና እኩልነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩበትን ወይም የሚተረጎሙበትን መነጽር በወጣቶች ላይ ኣደረገ። ንጹህ ኣይምሮ ይዘው ፍትህና  እኩልነትን ያነሱ ወጣቶች የፍትህና የእኩልነትን ትርጓሜ ሶሻሊዝም ባጠለቀላቸው መነጽር ማየት ጀመሩ። ሳይንሳዊ መሆኑ ብዙ ልባቸውን የማረካቸው ወጣቶች ፍትህን እና አኩልነትን በወል የማየትና የመተርጎም ኣስተሳሰብ ሰረጻቸው። ከፍ ሲል እንዳልነው ኣማራጭ የኣስተሳሰብ ዘየ ባለማየሉ እነዚህን ጥያቄዎቻቸውን በነሲብ እንዲያዩ ስላደረጋቸው ይህ ዝንባሌ በተፈጥሮ በቋንቋና ባህል ተቦድኖ ባለው ቡድን ላይ የፖለቲካ ኣይናቸው እንዲያርፍ ኣቀብሎ ሰጣቸው። ችግሩን የስርዓት ኣድርጎ ከማየት በላይ የብሄር ጥያቄ በማንሳት ፍትህ በኢትዮጵያ የሚበየንልን ብሄሮች እኩል ሲሆኑ ነው የሚል ኣስተሳሰብ በሃይል ሰረጸ።
ዋላልኝ መኮንን በኖቬምበር  17, 1969  የሁሉን ስሜት የነካ “On the Question of Nationalities in Ethiopia” የተሰኘ ኣርቲክል ጽፎ በ ስትራግል መጽሄት ላይ  ኣሳተመ። ዋለልኝ ለውይይት ብሎ ያነሳው የመወያያ ሃሳብ በሁለት ዋና ዋና ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን ኣንደኛው ኢትዮጵያ ከማህበራዊ (Sociological) ቅርጿ ኣንጻር እውነተኛ መልኳን ኣናይም የሚል የባህልና የቋንቋ ተዋጽኦን የሚመለከት ሲሆን ይህንን መልኳን ዋለልኝ “ፌክ” ነው ብሏል። በዚህ ረገድ ያነሳው የውይይት ሃሳብ እውነት ያለው ሲሆን እንዴት ግን  ሚዛናዊ የሆነ የባህል ዝውውር ሊፈጠር ይችላል? ለሚለው ተግባራዊ ጥያቄ በዚያን ጊዜም ውይይት የተደረገበት ኣይመስልም እስካሁንም የጠራ ዘዴ ኣልተፈጠርም።
ዛሬ በምንሰጠው ኣሳብ ዋለልኝ የናፈቀውን የኢትዮጵያን እውነተኛ መልክ ሊያሳይ የሚችል ቅርጽ ለውይይት ለማቅረብ እንሞክራለን። ከዚያ በፊት ግን ሁለተኛውን የዋለልኝን የመወያያ ሃሳብ እንመልከት። ሁሉተኛውና በጣም ከባድ ሆኖ የመጣው ጥያቄ የብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ተሳትፎ ይኑራቸው የሚለው የፖለቲካ ጥያቄ ነበር። ከፍ ሲል እንዳልነው የጸዳውን ኣይምሮ ገና ብቅ ሲል የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ ቀልሞ ይዞት ነበርና የኢትዮጵያ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ በቡድን እኩልነት ጥያቄ ላይ ነው ቤቱን የሰራው።ፍትህና እኩልነት የሚሰፈሩትም በዚሁ በቡድን ቁና እንደነበር መረዳት ይቻላል። በመሰረቱ ግን ቡድኖች ኣልነበሩም የተጎዳዱት። የሆነ ስርዓት ነው የሃገሪቱን ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ኢፍትሃዊ እንዲሆን ያደረገው።
ዋለልኝ በጻፈው ኣርቲክል ላይ ኢትዮጵያዊ ለመባል ኣማርኛ መናገር፣ በኣማራ ስም መጠራት፣  ያስፈልጋል… ብሎ ኣጥብቆ ይኮንናል። የሚገርመው ግን ራሱ ዋለልኝ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበረው የወሎ ዘየ መሳቂያ ሆኖ በግቢው ውስጥ ኣማርኛ መናገር ኣቁሞ በእንግሊዝኛ መናገር ጀምሮ ነበር። በቀየው ኣማርኛ ይሸማቀቅ ያፍርና መግቢያ ያጣ ነበር ማለት ነው። ዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ኦሮሞዎች ወይም ወላይታዎች የራሳቸውን ቋንቋ ሲነጋገሩ ከሚሰማቸው በላይ እሱ በወሎው ዘየ ተጠቅቶ ስለነበር ኣማርኛ መናገር ኣቁሞ እንደነበር ኣብረውት የነበሩ ሲመሰክሩ ስምተናል። ራሱ ከኣማርኛ ተናጋሪም ሆኖ ነጻነት ያስፈልገው ነበር ማለት ነው። ከጎጃም ከመንዝ የመጡ በስሞቻቸው ኣዲስ ኣበባ ላይ ይሸማቀቁ ነበር። ኣሁንም ይህ ነገር ኣለ። በርግጥ ይህ ችግር የመጣው የፖለቲካው ችግር ብቻ ሳይሆን በገጠሩና በከተማው መካከል እያደር እየሰፋ የመጣው ምጣኔ ሃብታዊ ልዩነት የፈጠረው ልዩነትና በኋላቀርነትና በሞደርናይዜሽን መካከል ያለ ሽሙጥም ሊሆን ይችላል።
ከቡድን እይታ ወጥተን ፍትህና እኩልነት በግለሰቦች ደረጃ የሚበየንበትን ስርዓት በመፍጠር ላይ ነበር ውይይት የሚያስፈልገው።ያ ማለት የቡድን ጥያቄ ዳዋ ይብላው ማለት ኣይደለም። እሱም ቅርጹን ጠብቆ ሊፈታ ይገባዋል።እንደ ኣጠቃላይ እንደ ሃገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውና ያለው ችግር የቡድኖች መጎዳዳት ሳይሆን የስርዓት ነው። ኢትዮጵያ የኣንድ ብሄር ኣገር ማለትም የኣማራው ብቻ ብትሆን ኖሮም ያን የዘውድ ኣገዛዝ ተቃውሞ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ኣይቀርም ነበር እኮ።መሬት ላይ ያለውን ነገር ብናይ ኣንድን ሃጎስ ኪሮስ የሚባል የትግራይ ገበሬ፣ ኣንድን በርሶማ ገለታ የተባለ የኦሮሞ ገበሬ፣ ኣንድን ኣበበ ስንሻው የተባለ የኣማራ ገበሬና ሌሎችም ገሬዎች ብናይ የሚኖሩበት ቤት፣ ለስልጣኔ ያላቸው መጋለጥ፣ የኢኮኖሚ ህይወታቸው ሁሉ እጅግ ተቀራራቢ ነው። ስለ ገበሬው  የምናወራው ኢትዮጵያ ስንል ሰማኒያ ፐርሰንት በላይ ገበሬ በመሆኑ ኣጠቃላይ ቁመናዋን ስለሚያሳይ ነው። ይህን ያመጣነው ኢፍትሃዊነቱ ያለው በተወሰኑ የስርዓቱ ኣራማጆች ኣካባቢ በመሆኑ የፍትሁ ጥያቄ በግለሰቦች ዘንድ እንዲበየን ሆኖ በሌላ በኩል የባህል ፍስሰት ሚዛናዊ የሚያደርግ ስርዓት መቀርጽ ያሻል ያ ነው መፍትሄው ለማለት ነው።።  በርግጥ ያ ትውልድ የቻለውን ሰርቷል። ከዚህ በሁዋላ ተተኪው ትውልድ ደግሞ ኣይምሮው ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን ፈጥሮ ሊመራ ይገባዋል። ምን ኣይነት ኢትዮጵያን ነው የምፈልገው?  ብሎ በኣይምሮው መሳል ኣለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ድቡልቡል የሆኑ የዴሞክራሲና የእኩልነት ኣንቀጾችን ብቻ ሳይሆን ካለፉት የውህደትና የልዩነት ማህበራዊ ቅርጾች የተለየ ኣዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ ስርዓት ነድፈው ሊታገሉ ይገባል።
ከፍ ሲል እንዳልነው ዋለልኝ ብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ተሳትፎ ያሻቸዋል ብሎ ነበር። ግን እንዴት ነው ብሄሮች እኩል ተሳትፎ የሚያደርጉት?  በተግባር መሬት ላይ ኣሳዩን ቢባል ኣስቸጋሪ ሁኔት ይመጣል። በመጀመሪያ ደረጃ እኩል ማለት እኩል ቁመት በሌላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች ሁኔታ (context) ምን ማለት እንደሆነ መተርጎም ኣለበት።እኩል የሚለው ነገር በቡድን ታጅሎ ስለመጣ ነው ለማስተናገድ የሚያስቸግረው። ብሄሮች ሁሉ እኩል ይሳተፉ የሚለው ኣረፍተ ነገር ጠቅላላ እውነት ያለው ስለሚመስል ልብ ያማልላል። ነገር ግን በኢትዮጵያ የብሄሮች ተፈጥሮ ኣንጻር እኩል በስቴት ዙሪያ እንዴት ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል የሚለውን በጥልቀት መወያያት ያስፈልጋል። የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ መጀመሪያ የተጫነው ወገን እኩልነትን ለመበየን ቀመር (formula) ሲያወጣ በብሄሮች ቁጥር ሊያደርገው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄሮች በስቴት ጉዳይ እኩል ይሳተፉ የሚለው ጠቅላላ እውነት እንደተድቦለቦለ ጥሩ ቢመስለንም ይህንን ለመበየን ከሚያስቸግርበት ኣንዱ ነገር ብሄሮች በቁጥር ቁመታቸው እጅግ ስለሚለያዩ ነው። ከሺህ እስከ ሚሊዩን ይለያያሉ። ሶሻሊስታዊ በሆነ እይታ ምን ኣልባት በቁጥራቸው ወይም በቁመታቸው ልክ ለፌደራል መንግስት ሰው ያዋጡ ከተባለ ብዙ ኣባል ያለው ብዙ ያዋጣ ትንሽ ያለው ትንሸ ያዋጣል ብንል በቃ ፍትህ ተበየነ ማለት ነው? ያ ብዙ ያለው በዚህ ስርዓት መሰረት ዋና ዋና ስልጣኖችን ይይዛል በጣም ትንሽ ቁጥር ያለው ደሞ ኣንድም ሚንስቴር ላያይ ይችላል። በዚህ ታዲያ ፍትህ ተሰራ ማለት ነው ወይ?   እኩል ተሳትፎ ማለትስ ምን ማለት ነው?  ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች በቁጥራቸው ኣስር ኣስር ሚሊዮን ቢሆኑ እኩል እኩል ሰው ኣዋጥተው በተራ በተራ ጠቅላይ ሚንስተር ወይም ፕሬዚዳንት እየሆኑ ይኖሩ ነበር። ይህ በተግባር ኣይገጥምም ቢሆንም በዚህ ፍትህ ወረደ ማለትም ኣይደለም። በመሆኑም የዚህ የፖለቲካ ውክልና ጉዳይ ከቡድነኝነት ወይም ዘመናዊ በሆነ ኣገላለጽ ከማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) ኣስተሳሰብ ሲመነጭ ብዙ ያልጠሩ ችግሮች ይገጥማሉ።
ያ ትውልድ ጥሩ ጥያቄዎችን ኣንስቶልናል። ያንን መሰረት ኣድርጎ የዛሬው ትውልድ በጥልቀት ተወያይቶ ኣዲስ ስርዓት መፍጠር ኣለበት ያልነው እንዲህ ያልጠሩ ጉዳዮች ስላሉ ነው። ፍትህ እኩልነት በብሄሮች ቁመት ወይም የተፈጥሮ ሃብት የተለያዩ ህዝቦች ባሉበት እንዴት ሊበየን እንደሚችል መላ ማለት ወቅታዊ ጉዳይ ሆኑዋል። ወያኔ የዋለልኝን ጥያቄዎች ለማየት በቂ ኣመታት ያሳለፈ ቢሆንም መጀመሪያ ከሰረጸው የግራ ዘመም ኣስተሳሰብ መረብ (trap) ለመውጣት ባለመቻሉ የብሄር ፌደራሊዝምን ተግባራዊ ኣደረገ።
ዋለልኝ የባህል የበላይነት መኖር ሁል ጊዜ የኢኮኖሚ የበላይነትን ያመጣል ብሎ የሚያምን ሲሆን ይህን ኣሳቡን ዛሬ ደርሶ ቢሆን ይቀይረው ነበር። ዛሬ ወያኔ ለባህል የበላይነት ፈጽሞ ደንታ የለውም። የትግራይ ቋንቋ ወይም ባህል በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ በባህልና ቋንቋ የበላይ ለመሆን ኣይሰራም። ነገር ግን ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በጥቂት ከኣንድ ቡድን በመጡ ሰዎች ተቆጣጥሮታል።ድሮ ኣማራ ወይም ትግራይ ያልሆኑ ከፍተኛ መኮንኖች ጥቂት ናቸው ይላል ዋለልኝ ዛሬ የብሄር ፌደራሊዝም ተመስርቶ የጦር ኣመራሩ ከፍተኛ መኮንኖች ሰባቱም ከትግራይ የተወለዱ ናቸው።
የብሄር ፌደራሊዝም ለቡድኖች ፍትህም ቢሆን ዋስትና ኣይሆንም። የባህል የበላይነት ሳይኖርም የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይ ሆኖ ገዢ መሆን ይቻላል።ፍትህ ኣልተበየነም። ኣንዳንዶች የብሄር ፌደራሊዝም በራሱ መጥፎ ኣይደለም ወያኔ ነው ያጠፋው ይላሉ። ይሁን እንጂ ለስቴት እኩል ተሳትፎ ቀመር መስራት ኣይችሉም። ከፍ ሲል እንዳልነው በቁመት ካረጉት ፍትህ በዚያ ኣይበየንም። ኣንስተኛ የሆነ ኣባል ያላቸውን ተስፋ ያስቆርጣል።
ኣንድ በጣም ኢንተረስቲንግ የሆነ ነገር ላጫውታችሁ። ምያንማር ወይም በርማ የምትባል ደቡብ ምስራቅ እስያ ውስጥ የምትገኝ ኣንድ ኣገር ኣለች። በዚህች ኣገር ኣንዳንዶች እንደሚሉት 135 ብሄሮች ኣሉ። ከነዚህ ውስጥ ኣንዱ ባርማ የሚባለው በጣም ብዙ ኣባላት ያሉት ሲሆን 68 በመቶ የሚሆነውን ሽፋን ይይዛል። ሌሎች ከመቶ በላይ የሆኑት የቀረችውን እጅ ተከፋፍለው ያሉ ሲሆን ኣንዳንዶቹ በጣም ትንሽ ኣባላት ነው ያላቸው። እነዚህ በጣም ኣነስተኛ ኣባል ያላቸው ኣንድ ጊዜ በተደረገ ጥናት መሰረት በብሄራቸው ራሳቸውን ሲገልጹ ምቾት ኣይሰማቸውም። በዚህ በብሄር ዙሪያም ብዙ ሲወራ ይሰጋሉ።  ለነሱ የሚመቻቸውና ደስ የሚላቸው በብሄራዊ ማንነታቸው ሲጠሩ ወይም በርሚስ ሲባሉ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ምን ኣልባት የሃገራቸው የፖለቲካ ጨዋታ በብሄር ቁመት ከሆነ እኛ ምን ይውጠናል ተወዳድረን መቆም ኣንችልም ከሚል ስጋት ይመስላል። በጣም ያሳዝናሉ። ከዚህ ስጋት የሚያሳርፋቸውን ጥበብ ይሻሉ።
ዋናው የኛ ምሳሌ ምንድን ነው በሃገራችን ኢትዮጵያም በብሄር ቁመት ፍትህ ስለማይበየን ጨዋታው ሁሉን ነጻ ሊያወጣ በሚችል መንገድ ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን በተለያየ ኣቅጣጫ ሊንከባከብ የሚችል ስርዓት በግድ መውለድ ኣለብን።
ቀጥሎ ያነሳነው ኣሳብ ከዚህ በፊት በእንግሊዝኛ ለየት ባለ መንገድ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ኣንዳንድ ወገኖች በኣማርኛ እንዲቀርብ በሰጡን ኣስተያየት መሰረት በኣማርኛ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን የማህበራዊ ፖለቲካ (Socio Politics) ጉዞ ስናይ  ሚዛን ከጎደለው ውህደት (assimilation) ወደ ልዩነት(Ethnic federalism) የመጣ ሲሆን በነዚህ በሁለቱም ስርዓቶች ኢትዮጵያ ስላጉረመረመችኣዲስ ኪዳን ልንገባ ይገባናልና ኑ እንግባ የሚል ግብዣ ነው።ከሁሉም በላይ ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ወይም ብሄራዊ ማንነትን(National Identity) ለያይተን እንድንንከባከብ የሚመክር ኣሳብም ያዘለ ነው።
ክፍልአንድ
የአዲሱ መዋቅር ስያሜ
ይህ አዲስ የማህበራዊ ፖለቲካ መዋቅር በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ኣንድነት (conventional cultural unity- CCU) የተሰኘ ንደፈ ሃሳብ ነዉ፡፡ ይህ ንደፈ ሃሳብ የኢትዮጵያን ብሄሮች ወይም ባህላዊ ቡድኖች ወደ አንድ አዲስ ኪዳን የሚጋብዝ ሃሳብ ነዉ፡፡
ክፍል ሁለት
የአዲሱ መዋቅር ወይም የቡድኖች ኪዳን ዓላማዎች (purposes) የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
1ኛ. ኢትዮጵያ ያሏትን የበለጸጉ ባህሎች በከፍተኛ ሁኔታ ለመጠቀም እና ሚዛናዊ
የሆነ የባህል ዝዉዉር ለማድረግ፣ማንበራዊ እድገቷን ለማፈጠን::
2ኛ. ባለፉት ሁለት ስርዓቶች ልባቸዉ የቆሰለባቸዉን ወገኖች ለመፈወስና አጠቃላይ
በዜጎች ዘንድ የህሊና ጽዳት ለማምጣት፣
3ኛ.  በልዩነት (በብሄር ፖለቲካ) ምክንያት የመጣዉን የማህበራዊ ኢኮኖሚና
የፍትሃዊ  እድገት ችግሮችና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት፣
4ኛ.  አንድነትን ለማጠናከር ናቸዉ፡፡
ክፍል ሶስት
የንድፈ ሃሳቡ ዳራ
በሰዉ ልጆች የማህበራዊ እድገት ታሪክ ዉስጥ የታየዉ ነገር አገር ሲመሰረት በአብዘኛዉ በጦርነት መሆኑ ነዉ፡፡ በጥንት ጊዜ ቡድኖች በኮሚኒኬሽን ችግር እና በነበራቸዉ ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና ምክንያት በተፈጠሩበት መልከኣ ምድር ተወስነዉ ይኖሩ ነበር፡፡ ቀስ እያለ የሰዉ ልጆች ንቃተ ህሊና ሲጨምር አካባቢያቸዉን ማሰስ (explore ማድረግ) ሲጀምሩ ቡድኖች ከሌሎች ቡድኖች ጋር መተያየትና መገናኘት ጀመሩ፡፡ ቀስ እያለም ግዛት የማስፋፋት ስሜት እያየለ በመምጣቱ ሃይለኛዉ ቡድን ደከም ያለዉን እየወረረ ግዛት የማስፋፋት ስራ ተጀመረ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ አለማቀፋዊ ይዘት ያለዉ ሲሆን እጅግ ብዙ ሃገሮች ዛሬ የምናያቸዉ ብዙህ (plural) አገሮች ሁሉ በዚህ ሁኔታ ተመስርተዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ጊዜ ሀይለኛዉ ቡድን ሌሎቹን ቡድኖች እየተጫናቸዉ ስለሚሄድ ባህላቸዉንና ቋንቋቸዉን ያለ ዉዴታ በግዴታ እንዲጥሉ የተደረጉበት ሁኔታ በሰፊዉ ታይቷል፡፡ በዓለም ላይ የታየዉ ይህ ክስተት የጭካኔ ደረጃ እንደየ ሀገሩ የተለያየ ነዉ፡፡ ሃገሮች በሚመሰረቱበት ጊዜ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ቋንቋ በሚናገሩ ህዝቦች መካከል በተለያዩ የግዛት አስተዳዳሪዎች መካከልም ዉጊያ ተካሂዷል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረዉ የሰዉ ልጆች የመረዳት ደረጃ መሰረት ሰፊ መሬት መያዝና ብዙ የሰዉ ሃይል መኖር የመንግስት ጥንካሬና ሃያልነት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር ነዉ፡፡ በዚህ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ጊዜ በኣንዳንድ ኣገሮች በከፍተኛ ሁኔታ በሃይል የሚደረግ የባህል ዉህደት (forceful cultural assimilation) ተካሂዷል፡፡ ሃሳባችንን በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ በጉልበት የሚደረግን የባህል ዉህደት በሁለት አቅጣጫ በምሳሌ አስደግፈን እንመልከት፡፡
1ኛ. በአንድ ሃገር ዉስጥ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የተደረገ ዉህደት (Intra forceful assimilation)
ይህ አይነት የባህል ዉህደት የታየዉ የተለያዩ ብሄሮች ባሉባቸዉ የአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል ሲሆን፣ ለምሳሌ በ1930 ዓ.ም. የቱርክ መንግስት በገሃድ የዉህደት ፖሊሲ አዉጥቶ ኩርዶች በግድ እንዲዋሃዱ ተገደዉ ነበር፡፡ በዚህ ገሃድ በሆነ አስገዳጅ ፖሊሲ ምክንያት የኩርድ ሰዎች በግድ አንዋሃድም ባህላችንን አንጥልም በማለት ትግል አድርገዋል፡፡ የቡልጋሪያ መንግስት ደግሞ ከ1984-1989 ድረስ በቱርክ ቡልጋሪያዊያን ላይ እንዲሁ በግድ እንዲዋሃዱ ተጽዕኖ የተደረገባቸዉ ሲሆን የቡልጋሪያ መንግስት በቱርክ ቡልጋሪያዊያን ላይ የዉህደት (assimilation) ዘመቻ (campaign) አድርጓል፡፡ የቱርክ ቡልጋሪያዊንን ዜጎች የቤተሰብ ስማቸዉን (family name) እየቀየሩ በቡልጋሪያዊያን የቤተሰብ ስም እንዲጠሩ ተገደዋል፡፡ መንግስት ራሱ ስማቸዉን እየቀየረ መታወቂያ ያዘጋጅ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡
የቀድሞዉ የዮጎዝላቪያ ሞቆዶንያ ሪፐብሊክ ባህል ከአልባናዊያን ወደ እነሱ እንዳይፈስ ለመከላከል ፖሊሲ አዉጥተዉ ነበር፡፡ ፖሊሲዉ የአልባናዊያንን ባህል ለማቋረጥ የታቀዳም ይመስላል፡፡
2ኛ. አገር አቋረጭ የሆነ የዉህደት ዓይነት (Inter forceful assimilation)
ይህ ዓይነቱ ጉልበት የተሞላበት የባህል ዉህደት ደግሞ በቅኝ ግዛቱ ዘመን ታይቶ የነበረ ነዉ፡፡ ገዥዎች ቅኝ የገዟቸዉን ህዝቦች ለማስተዳደርና ለረጅም ጊዜ ለመግዛት ይጠቅመናል ብለዉ የተጠቀሙበት ኣንዱ ስልት በግድ የሆነ የባህልና የቋንቋ ዉህደት በመፈጽም ነበር፡፡ ይህ ድርጊት እንደየ ሀገሩ የተለያየ ግዝፈት (degree) የነበረዉ ሲሆን ከዓለም ታሪክ ጥቂት ምሳሌዎችን እናንሳ፡፡
የኮሪያዊያንን ታሪክ ስናይ ከ1910 – 1945 ድረስ በጃፓኖች ቅኝ ተገዝተዉ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ቅኝ ገዥ ጃፓኖች ኮሪያዊያንን በቢሮ ቋንቋ ጊዜ ቋንቋቸዉን እንዳይጠቀሙ ጃፓንኛ እንዲጠቀሙ ተገደዉ ነበር፡፡ የኮሪያዊያንን ፊደልና ታሪክ ለማጥፋት ብዙ ጥረዋል፡፡ ኮርያዊያን ስማቸዉን እንዲቀይሩ ይገደዱም ነበር፡፡
አየርላንድና ካሪቢያኖችም እንዲሁ በቅኝ ገዥዎቻቸዉ ተጽዕኖ የደረሰባቸዉ ሲሆን አየርላንዶች ዛሬ ዋና ቋንቋቸዉ የቅኝ ገዥዎቻቸዉ የእንግሊዞች ቋንቋ እንግሊዘኛ ሆኗል፡፡
በ19ኛዉና 20ኛዉ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ ቅኝ የተገዙ ሀገራትም እንደዚሁ ፈረንሳይ ባወጣቻቸዉ የዉህደት ፖሊሲዎች ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል፡፡ የምዕራቡ ሃገራት በተለይም ሴኔጋል ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች፡፡ በብዙ ሃገራት በቅኝ ግዛት ጊዜ ይህ የዉህደት ተግባር በሰፊዉ ተፈጽሞ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አንድ ሀገር በመሰረቱ ብዙ ቡድኖች መካከልም ይሁን ባህር እየተሻገሩ ቅኝ ግዛት በተፈጸመባቸዉ አገሮች ዘንድ ይህ በግድ የሆነ ዉህደት ይፈጸም የነበረበት ምክንያት አንደኛ በዚያን ጊዜ የነበረዉ መረዳት የቋንቋና የባህል ልዩነት እንደ እምቅ ችግር (potential conflict) ተደርጎ በመታየቱ ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የበላይ ሆኖ መኖር የሚፈልገዉ ቡድን የበላይነቱን ከሚያረጋግጥበት መንገድ ኣንዱ ባህልን በሃይል በማዋሃድ መስሎ ከመታየቱም ሌላ በአንድ ሀገር ዉስጥ የበላይ የሆነዉ ቡድን ደግሞ በባህልና በቋንቋ የበላይ መሆኑን ዘላለማዊ በማድረግ የረጋ መንግስት ለመመስረት ያስችላል በሚል እምነት ነው።
በአንድ ሀገር ዉስጥ ባሉ በተለያዩ ብሄሮች መካከል የነበረዉ የሃይል ዉህደት በአንዳንድ ሀገሮች እጅግ የከፋ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ባይሆንም ከፍተኛ ግፍ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ለማንኛዉም ግን እነሆ ዛሬ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የዓለም ህዝቦች ያለፉበትን ይህን ታሪክ በአብዘኛዉ እንደ የሰዉ ልጆች የእድገት ታሪክ እያዩት ያለፈዉን ታሪክ ችላ ብለዉ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ባህል ቀልባቸዉን ስቦት ይታያል፡፡ ቅኝ የገዙና የተገዙ አገሮች የጠበቀ ወዳጅነት መስርተዉ የዛሬዉን ትዉልድ የበለጠ ቀልቡን የሳበዉን የሳይንስ፣የቴክኖሎጆና የዴሞክራሲ ስራዎች ተባብረዉ ይሰራሉ፡፡ በአንድ አገር ዉስጥም አገር ሲመሰርቱና ከመሰረቱም በኃላ የአንዱን ባህል አንዱ የተጫነበትን ታሪክ እንደ የሰዉ ልጆች ታሪክ እያዩ ያለፋዉን ስህተት ዛሬ የሰዉ ልጅ በደረሰበት ንቃተ ህሊና ላይ ሳይመዝኑ ያገኙትን ባህል የጋራ አድርገዉ የሚኖሩ አገሮች ብዙ ናቸዉ፡፡ በርግጥ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ያለፈን ታሪክ መዝገብ እያገላበጡ በደልን እየቆጠሩ ከይቅርታ ይልቅ በቀልን የመረጡም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የኋላ ታሪክን በዛሬዉ መረዳት ልክ የሚመዝኑ ወገኖች ባለፋዉ የነበረዉን በግድ የሆነ ወይም ሚዛኑን ያልጠበቀ የባህል ዉህደት የተፈጠረዉን አገር እንደገና እግዜር ሲፈጥረን በነበርንበት ቡድን ተመልሰን የብሄር ፌደራሊዝም መስርተን ታሪክን መበቀል አለብን የሚል ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ የሌሎች ህዝቦችን ቀልብ ከሳበዉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የ21ኛ ክፍለ ዘመን ባህል ይልቅ የጥንቱ ጉዳይ ልባቸዉን የያዘዉ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ለማንኛዉም ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደድን ጠላንም ያለፈዉን ታሪክ ለመበቀል እንደገና እንድንበታተን እና በቋንቋችን የወሰን ድንጋይ እንድናኖር ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሚዛን ባልጠበቀ ሁኔታ የተዋሃደችዉን ኢትዮጵያ በብሄር ፌደራሊዝም ለመፍታት የተሞከረዉ ሙከራ የበለጠ ኪሳራን በማምጣቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን የግድ አንድ አዲስ ኪዳን የምንገባበት አዲስ ስርዓት የምንፈጥርበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ዉህደት ታሪካዊ አመጣጥም ያለፉትን ሁለት የማህበራዊ ፖለቲካ ስርዓቶች በማጤን እና ከሁለቱም ማህበራዊ ፖለቲካዎች በመማር የተፈጠረ ንድፈ ሃሳብ ሲሆን ይህ አዲስ መዋቅር የኢትዮጵያን ማህበራዊ ፖለቲካ ቅርጽና ይዘት በማስተካከል ካለዉና ከነበረዉ የተበላሸ ማህበራዊ ፖለቲካ ካመጣዉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያወጣን ይችላል፡፡
ከፍል አራት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (conventional cultural unity) ልዩ ባህርያት
ከፍ ሲል ታሪካዊ አመጣጡን ያየን ሲሆን በዚህ ክፍል ስር ደግሞ የዚህን ንደፈ ሃሳብ ባህርያት በአጭሩ እናያለን፡፡ በመጀመሪያ ግን በስምምነት ላይ ያልተመሰረተዉና የግድ የሆነዉ የባህል ዉህደት ሁለት ባህሪያት ያሉት ሲሆን አንደኛዉ ጉልበት ነዉ፡፡ ሌላዉ ሁለተኛ ባህርይዉ ደግሞ የባህል ፍስስት (diffusion of culture) ባለ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነዉ፡፡ ባህል የሚሰጠዉ ወይም የሚግተዉ አካል በግድ ባህል ይሰጣል እንጂ የሚቀበል ልብ የለዉም፡፡
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) ደግሞ ከፍ ሲል ካነሳነዉ የባህል ዉህደት የተለየ ባህርያት አሉት፡፡ እነዚህ ባህርያት፡-
1ኛ. በስምምነትላይየተመሰረተ (conventional) ነዉ፡፡
ይህ ማለት በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት ብሄሮች አንዳሉ በሚገባ መታወቅና መመዝገብ አለበት፡፡ አንዳንድ የሚያሳፍር ነገር ትሰማላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት ብሄር አለ? ሲባል ከ82 በላይ በተለምዶ ይባላል፡፡ ይህ አይሰራም፡፡ በትክክል ተቆጥሮ ስማቸዉ በክብር በህገ መንግስታቸዉ ላይ መስፈር አለበት፡፡ ከዚህ በኃላ እነዚህ ብሄሮች ሁሉ አንድ አዲስ ኪዳን ይገባሉ፡፡ ይህ ኪዳን በብሄሮች ወይም ባህላዊ ቡድኖች ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ለማድረግ የሚስማሙበት መሃላ ነዉ፡፡ ይህ ሂደት የዚህ አዲስ ስርዓት ዋና ቁለፍ ጉዳይ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ በቡድኖች ፍቃድ (will) ላይ የተመሰረተች ኣገር ልትሆን ስለሚገባት ቡድኖች ሁሉ ወደዚህ ስምምነት መግባታቸዉ የመጀመሪያዉ ተግባር ነዉ፡፡ በህገ መንግስታቸዉ ተስማምተዉ የባህል ዉህደት አንቀጽ ሊያስገቡ ይችላሉ ማለት ነዉ፡፡ ኪዳናቸዉ በህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን በባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማትም ሊገለጽ ይችላል፡፡
2ኛ. ባለብዙ አቅጣጫ ነዉ፡፡
በግድ የሆነ የባህል ዉህደት ሰጪና ተቀባይ እኩል ሚዛናዊ የሆነ የባህል ዝዉዉር አያደርጉም ብለናል፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ ጊዜ ግን የባህል ፍስስቱ (diffusion of culture) የኢትዮጵያን ብዙህ (plural) ተፈጥሮ ያገናዘበ በመሆኑ ባህል የሚፈስባቸዉ ብዙ ቦዮች በፖሊሲ ይቀረጻሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እዉነተኛ መልኳ እስኪጎላ ድረስ ባህል ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሁሉም አቅጣጫ እንዲዘዋወር ይበረታታል፡፡ይህ ለኣንዳንዶች በጣም ኣሳባዊ (too ideal) ሊመስል ይችላል። ግን ይቻላል። ብሄሮች ባለፈው በጭቆና ኣጣነው ያሉትን ባህልና ቋንቋ ሁሉ በማስመለስ (restoration) ፖሊሲዎች ልንበቀል እንችላለን። ማህበራዊ እድገትን እንዲህ ባሉ የፖሊሲ ከባቢዎች እየገሩ ሚዛን መጠበቅ ይቻላል።
ክፍልአምስት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) ለኢትዮጵያ ያለዉ ጠቀሜታ፡፡
1ኛ. እዉነተኛዉን መልካችንን ለማጉላት
ኢትዮጵያ ብዙህ (plural) ሀገር መሆኗን የሚያሳይ መልክ የሚኖራት ሚዛናዊ የባህል ዝዉዉር ሲኖር ይህንንም ተከትሎ የሚፈጠሩ የጋራ እሴቶች ሲኖሩ ነው፡፡ ይህንን እዉነተኛ መልኳን የሚያሳይ ስርዓት ደግሞ ሚዛኑን ያልጠበቀ የባህል ዝዉዉር ማለትም ኢትዮጵያ ከ22 ዓመት በፊት የነበረችበት ሳይሆን አሁን ያለዉ በየቤትህ እደር የሚለዉ የጎሳ ፌደራሊዝምም ሳይሆን በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ማለትም የሃገሪቱን እዉነተኛ ማንነት ወይም ብሄራዊ ማንነት አንጥሮ በማዉጣት ረገድ ይህ ጽንሰ ሃሳብ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
2ኛ. ለአንድነት
እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለን ልዩነት በዘር ደረጃ የሚታይ አይደለም፡፡ በዘር ክፍፍል ዉስጥ ሁላችን ምስራቅ አፍሪካዊያን ጥቁሮች ነን፡፡ ልዩነታችን ባህልና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የባህላዊ ቡድን ልዩነት ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ታዲህ እኛ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያለን ቡድኖች አንድ ነን ስንል ምን ማለታችን ነዉ? አንድነት በኢትዮጵያ አዉድ (context) ምን ማለት ነዉ? በሚለዉ ላይ መወያየት አለብን፡፡
አንድ ጊዜ በዚህ በአንድነት ኢለማንቶች ዙሪያ አንዲት አጭር ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ አንደገለጽኩት ኢትዮጵያ አራት የአንድነት ኢለማንቶች ያሏት ሃገር ናት፡፡ እነዚህ ኢለማንቶች
1ኛ. ታሪክ
2ኛ. መሬት
3ኛ. የጋራ እሴት (ማህበራዊ ካፒታል )
4ኛ. ፍትህና አስዳደር ናቸዉ፡፡
እንግዲህ አንድ ነን ስንል አንዱ የኣንድነታችን መገለጫ የጋራ ታሪካችን ነዉ፡፡ አጼ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ድል ካደረጉ በኃላ የዘመተዉን ወታደር በብሄር ስታትስቲክስ ሰርተዉ ይህን ያህል ኦሮሞ፣ ይህን ያህል አማራ፣ ይህን ያህል ትግሬ ወዘተ ብለዉ መዝገብ አላስቀመጡልንም፡፡ ድሉ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን ነዉ፡፡ ለዚህ ድል ወታደሩ ብቻ ሳይሆን ቀረጥ ሲከፍል የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ (Jurisdiction) የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድሉ ነዉ፡፡ ሌሎች ቁሳዊና መንፈሳዊ ታሪኮቻችን ሁሉ የጋራ ታሪካችን መሆናቸዉን ስንቀበል ስንስማማ ነዉ አንዱ የአንድነት መገለጫ፡፡ ሌላዉ ሁለተኛዉ ደግሞ መሬት ሲሆን ሁላችን ቡድኖች የተፈጠርንበትን መሬት ሁሉ አገጣጥመን የሰራናት ይህቺ አንዲት ዉብ ኢትዮጵያ አንድ ስትሆን በዚህም ነዉ አንድነታችን የሚገለጸዉ፡፡ ሌላዉ ሶስተኛዉ ፍትህና እኩልነት ሲሆን ሁላችን እኩል ስንሆን፣ በብሄሮች መካከል ትልቅና ትንሽ ሲጠፋ አንድነታችን በዚህም ይገለጻል፡፡ በእዉነተኛ ዴሞክራሲ ፊት ትልቅና ትንሽ ብሄር አይኖርም፡፡ ሌላዉ አራተኛዉና ከዚህ ርዕስ ጋር በቀጥታ የሚያያዘዉ የጋራ እሴት ግንባታዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንግዲህ እነዚህ ብዙ ብሄሮች ያሏቸዉን ጥበቦች እያዋጡ በጋራ የሚሰሩበት ባህል ሄዶ ሄዶ የጋራ ባህላቸዉን እያበዛ ተግባቦታቸዉን እየጨመረ ሲሄድ አንድነታቸዉም እንደዚያዉ እየጠነከረ ይመጣል፡፡ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ለማድረግ ብሄሮች ሲስማሙና ኪዳን ሲገቡ አንዱ የሚሆነዉ ነገር ብሄሮች ሁሉ ቋንቋቸዉንና ባህላቸዉን ለጋራዋ አገራቸዉ ለኢትዮጵያ መስዋዕት ያደርጋሉ፡፡ ስማቸዉ በህገ መንግስታቸዉ ላይ ሲሰፍር የሚገቡት ኪዳን አንዱ ይህ ነዉ፡፡ የፈጠሩት ጥበብ (art) ሁሉ ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት ይሆንና ንብረትነቱ የነሱ ብቻ ሳይሆን የወል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ በዚህ መሰረት የኮንሶዎችን ባህልና ቋንቋ የሚንከባከበዉ የኮንሶ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዋነኝነት ተንከባካቢ ትሆናለች ማለት ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ኪዳን ስትገባ የሚጠፉ ብሄሮች አይኖሩም፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት እኛ ኢትዮጵያዊያን ባህላዊ ቡድኖችን ዘላለም የማኖር አለማቀፋዊ ሃላፊነትም ይኖርብናል፡፡ የአንድ ባህላዊ ቡድን መጥፋት የአንድ ቋንቋ ከምድር ላይ መጥፋት የአለም ህዝብ ኪሳራም ተደርጎ ይታያል፡፡ በመሆኑም ብሄሮች ባህልና ቋንቋቸዉን ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት ካደረጉ በኃላ ለመንከባከብ መልሰዉ ሃላፊነት ቢወስዱም ንብረትነቱ ግን የኢትዮጵያዊያን ነዉ፡፡
ሌላዉ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታየዉ ነገር አንዱ አንድነት ከሚገለጽባቸዉ ጉዳዮች መካከል አስተዳደርና ፍትህ ነዉ ብለን ነበር፡፡ እዉነት ነዉ ይህ ንድፈ ሃሳብ ፖለቲካዉ ራሱ በአንድ ማንነት (identity) ላይ ብቻ አንዲመሰረት የሚታገል ነዉ፡፡ ይህ ማንነት (identity) ብሄራዊ ማንነት (national identity) የሚባል ሲሆን የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የተለያየ ፖሊሲ ይዘዉ ግን የሚቋቋሙት በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ነዉ፡፡ ይህ አጀንዳቸዉ ዶግማ ሲሆን ፖሊሲዎቻቸዉ ቀኖናዎች ናቸዉ፡፡ ይህ የማይለወጥ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸዉ ብሄራዊ ማንነት ሲሆን አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ነዉ፡፡ ይህ አንድነት በርግጥ የሚመጣዉ በመጀመሪያ ስንስማማ ነዉ፡፡ በዚህ ንደፈ ሃሳብ መሰረት ዜግነት የባለቤትነት ጥያቄ ሲሆን በዜግነታችን ለኢትጵያዊነት የተሰዉትን ባህሎችና ቋንቋዎች ሁሉ፣ ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ሃብቶችን ሁሉ ባለቤት የሚያደርገን በአዲስ ኪዳን የጸና ሀብት ማለት ነዉ፡፡ በብሄራዊ ማንነታችን አንድ ብቻ መሆኑ ነዉ አንዱ አንድ ነን ሊያሰኘን የሚችለዉ ነገር ለማለት ነዉ፡፡
3ኛ. በከፍተኛ የባህል ተዋጽኦ ዜጎችን ለማርካት
ኢትዮጵያ የባህል ሃብታም ናት፡፡ የተለያዩ የምግብ አሰራሮች፣ የተለያዩ የአልባሳት ጥበቦች፣ የተለያዩ የሰርግ ስርዓቶች፣ የተለያዩ ዘፈኖችና ሙዚቃዎች ወዘተ በገበያ ላይ ሲወጡ ዜጎች ብዙ ምርጫዎች (varieties) ያገኛሉ፡፡ ይህ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖረዉ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት (CCU) በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
4ኛ. ለማህበራዊ ክህሎት (social skill development)
ይህ ንድፈ ሃሳብ ሌላዉ ጠቀሜታዉ ኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ክህሎቶቻቸዉን እንዲያዳብሩ ባይልንጉዋል (bilingual) እንዲሆኑ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን የሚፈጥር በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ክህሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ተቻችሎ የመኖር ችሎታንም ለማዳበር እንድንችል የሚጠቅመን ነዉ፡፡
5ኛ. የብሄር ፖለቲካን ተከትሎ ለመጣ ቀዉስ መዉጫ በር ነዉ፡፡
የብሄር ፖለቲካን ተከትሎ ሌላዉ የመጣዉ ችግር የሀገሪቱን ማህበራዊ ኢኮኖሚ (social economy)፣ የኢኮኖሚ ፍትህ (economic justice) እንዲሁም ፍትሃዊ እድገት ችግር የሚፈታዉ በሌላ ስርዓት ነዉ፡፡ ዛሬ በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ያለዉ አድልዎ የዚህ የልዩነት ወይም የብሄር ፖለቲካ ዉጤት ነዉ፡፡ የማንነት ፖለቲካ አንዱ መገለጫዉ አድልዎ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ አድልዎ በሀገራችን አለ፡፡ የክልሎች እድገት የተመጣጠነ አይደለም፡፡ ስልጣን ያያዘዉ ቡድን ሌሎች ቡድኖችን በዉስጡ እየሰራ ከፍተኛ የሆነ ያልተመጣጠነ እድገት ይታያል፡፡ የብሄር ፌደራሊዝም በሰፈነበት አገር ፍትሃዊ እድገት የኢኮኖሚ ፍትህ (economic justice) ሁልጊዜ በከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በአጠቃላይ ፍትህ  በብሄር ፌደራሊዝም ጊዜ በጣም ስለሚጎዳ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት እነዚህን ኢፍትሃዊ ችግሮች ለማቃለል ይረዳል፡፡
ክፍል ስድስት
በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል አንድነት (CCU) የእድገት አቅጣጫዎች
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ባህል አዳጊ ነው፡፡ ባህል በተፈጥሮው ዳይናሚክ በመሆኑ በኣንድ ቡድን ህይወት ውስጥ ትውልዶች በራሳቸው ዘመን የየራሳቸውን ፈጠራ እየጨመሩበት ወደላይ ያድጋል:: በሌላ በኩል ደሞ  ባህል ወደ ጎን ካለው ሌላ ቡድን ጋር ሲነካካ(interact ሲያደርግ) እሴት እየተጋባ ወደ ጎንም ያድጋል።ወደ ጎን ሲያድግ ብዙ ያጋራ እሴቶችን ስለሚገነባ የነዚያ እሴቶች ያዢ(holders) ሁሉም ቡድኖች ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ያደረገውም እነዚህን ሁለት የባህል የእድገት ኣቅጣጫዎች ነው።
ሌላው የዚህ ንድፈ ሃሳብ መነሻ ደግሞ ሊመልሰው የሚገባ አንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህም በስምምነት ላይ የሚደረግ የባህል ውህደት ኣንዱ ግቡ አንድነት ሲሆን የዚህ ንድፈ ሃሳብ የመጨረሻ ግብ (ultimate goal) ሄዶ… ሄዶ…. አንድ ነጠለ ህዝብ (homogeneous society) ለመፍጠር ይመስላል የሚል ጥያቄ ይሆናል፡፡ በመሰረቱ ግን የዚህ ንድፍ ሃሳብ አላማ ይሄ አይደለም፡፡ ዓላማው ወደ ላይም ወደ ጎንም ባህል ሊያድግ ስለሚችል ቋንቋዎች ዘላለም የሚኖሩበትን፣ ቡድኖች ዘላለም የሚኖሩበትን በአንጻሩ ጥበባቸውን እየተካፈሉ ወደ ጎንም እያደጉ መሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው፡፡ እንዴት ወደ ላይ ወደ ጎንም ይታደጋል? ካልን እንዴት አንድ ሰው ሁለት ቋንቋ ሊናገር አይችልም በሚል አጸፋ እንመልሳለን፡፡ ይቻላል፡፡ ሁልጊዜም ወደ ሁለት አቅጣጫ ማደግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቡድኖች ወደ ላይ /vertical/ እድገት ባንድ በኩል እያሳዩ ወደ ጎን /horizontal/ እድገት በማሳየት የጋራ እሴት እየገነቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ቡድኖች በስምምነታቸው ጊዜ ህገ-መንግስታቸውን፣ የሃይማኖት ተቋሞቻቸውን፣ ባህላዊ ቡድናቸውን ይዘው ኪዳን ሲገቡ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለኢትዮጵያዊነት ይሰዋሉ፡፡ ይህን መስዋዕት ካደረጉ በኃላ ኢትዮጵያ መልሳ ቋንቋና ባህል እንዲንከባከቡ ለቡድኖች ትሰጣለች፡፡ ንብረትነቱ ግን የቡድኖቹ ብቻ ሰይሆን የኢትዮጵያዊነት ይሆናል ብለናል፡፡ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተወለደበት ማህበረሰብ ውስጥ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪና የባህሉ ተካፋይ እስከሆነ ድረስ ከባህላዊ ቡድነኝነት አንጻር የዚያ ቡድን አባል ይሆናል ማለት ነው፡፡  እናትና አባት ኦሮሞ ሆነው ልጅ አማራ የመሆን መብት አለው፡፡ ቋንቋና ባህል ውጪያዊ ልምምድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህሎችና ቋንቋዎች የኢትዮጵያዊነት በመሆናቸው ዜጎች በዜግነታቸው ያገኙዋቸው መብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በኦሮሞ ህዝብ ቸርነትና ፍቅር ልቧ የተነካው የእኔ እናት ኦሮሞ የመሆን መብቷም ይጠበቅላታል፡፡ በዚህ ስምምነት ጊዜ ቡድኖች ክፍት ሆነው ግን ቋንቋና ባህላቸውን ለማሳደግ ጠንቃቃዎች ይሆናሉ፡፡
ከፍል ሰባት
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት የብሄራዊ ቋንቋና የስራ ቋንቋ ጉዳይ እንዴት ይታያል?
በመጀመሪያ ደረጃ  ዜጎች ይህንን ጥያቄ ሊያዩት የሚገባው ከገቡት ኪዳን አንጻር ነው፡፡ በዚያ ከፍታ ላይ ሆነው ሲያዩ ቋንቋዎች ሁሉ ብሄራዊ ናቸው።የኢትዮጵያ ሃብት የሆኑ ቋንቋዎች ለምሳሌ ኣፋርኛ፣ ኣገውኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ ወዘተ. ብሄራዊ ቋንቋ ተብለው ይጠራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ቋንቋዎች ብሄራዊ ናቸው ሲባል ከፍ ሲል በሰጠነው የስምምነት መነሻ ኣሳብ ላይ ከተስማሙ የነዚህ ቋንቋዎች ሁሉ ባለቤት ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ ቡድኖችም ቋንቋዎቻቸውን ይዘው ሆ! ብለው መስዋእት ስላደረጉ በመብት ደረጃ ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ብሄራዊ ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ኣንድ ወይም ከኣንድ በላይ ቋንቋ መርጠው ዋና መግባቢያ ይኖራቸዋል።  ዋና የስራ  ቋንቋ  ሲመርጡ ምናልባትም የሚያዩት አብዘኛው ህዝብ የሚናገረውን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በመለስ በቁጥሩ ከፍ ያለ ህዝብ የሚናገራቸው ሌሎች ቋንቋዎችም ካሉ እነሱንም አካቶ ዋና ቋንቋን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሁኔታ አማርኛና ኦሮምኛን ዋና ቋንቋ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ እንግሊዘኛንም በስራ ቋንቋ ውስጥ በማካተት በአለም ተፎካካሪ ለመሆን ሶሊዳሪቲ ለማሳየት ይጠቅማል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በቋንቋ ጉዳይ እንዳይጋጩ ይህ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት እንደ መልህቅ ይይዛቸዋል፡፡ ይህ ስምምነት ሲወርድ በዋና ቋንቋ ምርጫ ጊዜ የኦሮምኛ ቋንቋ  ዋና ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጋር ሊሰራ ይገበዋል የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ከኦሮሞዎች ብቻ አይሆንም፡፡ እኔም ይህንን እንዳነሳ ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም የኦሮምኛ ቋንቋ ባልናገረውም የእኔም ቋንቋ ሃብቴ ነውና፡፡ ሃገሬ ሁለትና በላይ ዋና ዋና ቋንቋዎች ቢኖራት የበለጠ ታተርፋለች እንጂ አትከስርምና፡፡
ሌላው መገንዘብ ያለብን አንድ ቋንቋ ዋና ሆነ ማለት የዚያ ቋንቋ ፈጣሪ የሆነ ቡድን ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደልም፡፡ ቋንቋው  ዋና  በመሆኑ የተለየ ተጽዕኖ ሊያሳድርም አይችልም፡፡ ሌላው መረዳት ያለብን ደግሞ ቋንቋዎች ወደ ዋና መግባቢያነት መምጣታቸው ለእንክብካቤ የተመቹ እንዲሆኑና ሌሎቹ የመጥፋት አደጋ እንደተቃጣባቸው ተደርጎ ሊታሰብም አይችልም፡፡  በተግባር እንደምናየው እንደውም የመበወዝ /standardized የመሆን/  እድሉ ሰፊ የሚሆነው ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ መስጠት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የአለም ቋንቋ የሆነውን እንግሊዘኛን ብንወስድ አሁን ያለውን የቋንቋውን ይዘት ስናይ 60% የሚሆነው ቃል ከተውሶ የመጣ ነው፡፡ ከላቲን፣ ከጣሊያን፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ ወዘተ. የመጡ ቃላቶች የእንግሊዘኛ ቃልን በውዘውት አርባ በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው የኦርጂናሉ የእንግሊዞች እንግሊዘኛ ያለው፡፡ኣሁንም ገና እየተበወዘ ነው። ቴክኖሎጂ ሲያድግ፣ የኣለም ህዝቦች ንቃት ሲጨምር እንግሊዘኛ እየተበወዘ ይሄዳል። በዚህ እንግሊዝ አልተከፋችም፡፡ ያላትን ቋንቋ ለአለም ህዝቦች መስዋዕት አድርጋ ቋንቋው ሲያድግ የምትደሰት ነው የሚመስለን፡፡ ይህን ያመጣነው አንደኛ ቋንቋ አዳጊ መሆኑን እና በሌላ በኩል የመበወዝ እድሉ ሰፋ የሚለው የብሄራዊ ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ዋናው ቡድኖች የሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ስምምነቱን ከልብ በመቀበሉ ላይ ሲሆን ከዚያ በሁዋላ በዋና መግባቢያ ቋንቋ ላይ የሚደረገው ምርጫ ከፍ ባለ መረዳት ላይ ተመርኩዞ ስለሚሆን እንቅፋቶች አይገጥሙትም፡፡
አሁን ቡድኖች የኔም ቋንቋ ዋና መግባቢያ ይሁን የሚያስብላቸው ነገር አንደኛ ፖለቲካው የብሄር በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ፈጣሪዎች የዚያን ቡድን ቋንቋና ባህል ለብቻቸው ስለተሸከሙ እና ፖለቲካው ራሱ አእምሮአችንን ስለሚያሞስሰው /corrupted ስለሚያደርገው/ እንዲሁም አንድ ቋንቋ ዋና መግባቢያ በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ይህን ተንተርሶ ሌሎች የስነ-ልቦናና የማቴሪያል ጥቅም ያገኛል የሚል ስሜት ስላለ ነው፡፡ እነዚህ ስሜቶች መጀመሪያውን ወደ ስምምነቱ ስንመጣ የሚቀሉ ይሆናሉ።
ክፍል ስምንት
ማጠቃለያ፣ የፖሊሲ የስትራተጂ ኣቅጣጫዎች
ይህ ንድፈ ሃሳብ ዋናው ኣላማው በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ሲሆን ይህ ትራንስፎርሜሽን የማህበራዊ ፖለቲካችንን መሰረት ያስተካክላል ወይም ይፈውሳል በሚል ልብ ነው። ዛሬ በሃገራችን ፍትህ ሲጎድል ስናይ ይህን ለመዋጋት ሮጠን የፖለቲካ ቤት የምንሰራበት መሰረት ያስፈልገናል። ይህ መሰረት ኣንድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ማንነት ሲሆን ይህን ማህበራዊ ለውጥ ማስቀደሙ ጠቀሜታው ፖለቲካችንን  ስለሚያስተካክለው ነው።
ጥቂት የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችን ለመጠቆም ያህል ደሞ፣
  • ሚዛናዊ የሆነ የባህል ውህደትን ማራመድ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አለ የተባለው በሃይል የተደረገ የባህል ውህደት በሌሎች ዘንድ ሚዛኑን ያልጠበቀ ግን የከፋ አልነበረም የሚባለው ውህደት የታየው 20% ግድም በሚሆነው የከተማ ነዋሪው አካባቢ ነው፡፡ በየገጠሩ የሚኖረው ህብረተሰብ በባህል ደረጃ እምብዛም ለውህደት የተጋለጠ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ሚዛኑን የጠበቀ የባህል ውህደት ለማካሄድ ሰፊ እድል አላት፡፡ በመሆኑም መንግስት ሚዛኑን የጠበቀ አቅጣጫ በማሳየትና በማበረታታት የባህል ፍስስቱን ባላንስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ቀላል ምሳሌዎችን እናንሳ፡፡ ለምሳሌ መዲናችን የሆነችውን አዲስ አበባን መልኳን ብናይ የብዙ ብሄሮች ርዕሰ ከተማ አያስመስላትም፡፡ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ አንድም ቀን የኮንሶዎች ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ በደቡብ አካባቢ የሚታወቀው የኩርኩፉ ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ የሃመሮች ምግብ ቤት፣ የቦረናዎች ምግብ ቤት ወዘተ አላየሁም፡፡ እነዚህ ቡድኖች የየራሳቸው ጣፋጭ የምግብ አሰራርና ዓይነት ቢኖራቸውም መዲናዋ ላይ ገበያ ላይ አልወጣምና አዲስ አበባን እውነተኛ መልኳን እንዳታሳይ አድርጓታል፡፡ በሌላ በኩል ሰርግ የሚያደርጉ ድርጅቶች (wedding halls)  በውስጣቸው ብዙ የሰርግ ስርዓቶችን የሚያሳይ ሜኒዩ (menu) ቢኖራቸው መልካም ነው፡፡ ተጋቢዎች ወደዚያ ሄደው ከሜኒዩው መርጠው በዚያ ስርዓት ቢጋቡ ደስ ይላል፡፡ ፍቅራችን፣ አክብሮታችንና፣ አንድነታችን፣ መቀባበላችን በዚህም ይገለጽ ነበር፡፡ በኣልባሳት በኩል፣ በሙዚቃ በኩል እንዲሁ የኢትዮጵያን ቡድኖች የሚያሳዩ ቤቶች ሊታዩ ይገባል፡፡ ሚዛናዊ የባህል ውህደትን የሚያመጣው አንዱ የቡድኖችን ጥበብ በሚታይ ስፍራ በማውጣት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ይቻላል፡፡ይህን ስንል ምን ኣልባት ኣንዳንዶች ይህ ኣይነቱ ሂደት በፖሊሲ የሚሰራ ኣይሆንም መንግስት ኮንሶዎች እዚህ ጋር ምግብ ቤት ክፈቱ፣ ሃመሮች እዚህ ቦታ ላይ መጠጥ ቤት ክፈቱ ኣይልም እንዲህ ኣይነት ስፔሲፊክ ጉዳይ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት የሚያመጣው ነው ልንል እንችላለን። ግን ኣይደለም። መንግስት ከባቢየሆኑ ፖሊሲዎችን ማውጣት ይችላል። ከባቢዎች ሲኖሩ፣ ቡድኖች እውቅና ሲያገኙና ስምምነቱ ሲገባቸው እነዚህ ጉዳዩች የመንግስትን ምቹ ፖሊሲዎች እየተከተሉ የሚከሰቱ ናቸው። የታቀደ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት ማምጣት ይቻላል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ብሄር ያላቸው ኣገሮች በእቅድ በተደገፈ ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ ሲያልፉ ነው ሰላምና ልማታቸው የሚጠነክረው። በሌላ በኩል ቋንቋዎችን ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ መንደፍ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአማራው አካባቢ የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማሪያ አካዳሚዎች ቢኖሩ፣ በትግራይ የኮንሶዎችን ቋንቋ የሚያስተምሩ አካዳሚዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን እየተማሩ በዚያ ስራ የመያዝ እድል ቢኖራቸው በዚያው የቋንቋ ሃብትን የመጠበቅ ሃላፊነት ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የቱሪስት መስህብ ለማግትኘም ጭምር የባህል መንደር /cultural villages/ መመስረት፣ የባህል ተቋማትን በየቀበሌው ማቋቋም ቡድኖች ሁሉ ነቃ ነቃ እንዲሉ በሃገራቸው ምስረታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የባህል ልውውጥ ፕሮግራሞች ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል በትምህርት ካሪኩለሞቻችን ውስጥም የተለያዩ ባህሎቻችንን እየሰገሰጉ ማስተማር ጠቃሚ የሆኑትን እየነቀሱ እያወጡ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
  • መልክአ ምድራዊ ተዋጽኦ /spatial diversity/
የሰፈራ ፕሮግራሞች እንዲሁም የፌደራል ስርዓቱ ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረጉ ሳይሆን የህብረተሰቡን ተግባቦትም ያገናዘበ መሆን አለበት ብሎ ይህ ንድፈ ሃሳብ ያምናል፡፡ አንዱ የአንድነት መገለጫ የመሬት አንድነት በመሆኑም ይህንን አንድነት የሚያሳይ መልክአ ምድራዊ አሰፋፈር ያስፈልጋል፡፡
  • በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቅርጽ መፍጠር
ሌላው የታችኛውን ማህበራዊ ጉዳያችንን እያሻሻልን ሳለ ኣብረን ትኩረት ሰጥተን ልንፈታው የሚገባው ጉዳይ የፖለቲካ ኣወቃቀራችንን ነው። የእኛ የኢትዮጵያዊያን ችግር የሚፈታው በዚህ በባህልና በቋንቋ አካባቢ ያለንን መዋቅር ስናሻሽል እና ፖለቲካችንን ከባህል ማንነት አውጥተን ወደ ብሄራዊ ማንነት ስናሸጋግር ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅርጿን በ ኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ በመስራት ማህበራዊ ፖለቲካዋን ትራንስፎርም ልታደርግ ያስፈልጋታል። በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት ብሄራዊ እርቅን የሚያበረታታ፣ ለጋራ በጋራ የምትሆን ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ /reinventing Ethiopia/ የሚረዳ ነው ብለን ኣምነን ነው፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

 https://www.goolgule.com/reinventing-ethiopia-2/

No comments:

Post a Comment