Friday, October 18, 2013

እግርኳሳችን ጀርባ…


ከብስራት ገብሬ
ethiopia fan 2
መቼም የእግር ኳሱ ነገር ዛሬም አልበረደም። አሁንም ይወራል። ለምን ተሸነፍን የሚለውን ሠፋ አድርጎ ከማብራራት ጀምሮ አሰልጥኙንም በመውቀስ ቀጥሎ ጌታነህ ከበደ አውቆ ነው ያልተጫወተው እስከሚለው እስከሚለው ያልተረጋገጠ ሀሳብ ድረስ ይዘልቃል ። በተቃራኒውም ብሔራዊ ቡድኑ አኩርቶናል፣ እንደዚህ ያኮረንና ያስደሰተንም ቡድን የለም የሚሉም ሞልተዋል። እዚህ ላይ ለምን የተለያዩ ሀሳቦች ተፈጠሩ ተብሎ ባይጠየቅም የተሻለና ሀሳብ የተባለውንና አሳማኝ ሊባል የሚችለውን ነጥብ ግን ልንቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ያስፈልጋል። ጥቅሙ ለጋራ ስለሆነ፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን እዚህ እስኪደርስ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ እንደመጣ መገመት ይቻላል ። እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውልን፤ ዕድልም ተጨምሮ የተደሰትናባቸው ጊዜያት ነበሩ ።
አቶ ሠውነት እንዳሉት ዕድል የሚሰጠው አንድ እና ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜም ሊኖር ይችላል፣ ሁሌም በየጨዋታውም ሊኖር ይችላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዚህ ቀደም ባልነበረ ሁኔታ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጥቂት የሚባሉ ጨዋታዎችን መጫወት በቂ ሆኖ መገኘቱ ነው ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር መጫወታችን ሌላኛው ጥሩ ሊባል የሚችል ዕድላችን ነበር፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ከሱዳን ጋር የተፋጠጥንበት ጨዋታ ነው፡፡
በተጨማሪም እንደከዚህ ቀደሙ ከሰሜን ወይም ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ቢደርሰን ኖሮ በቀላሉ ለአፍረካ ዋንጫ እናልፋለን ብሎ መናገር ይከብዳል።
ወጣም ወረደ ቁምነገሩ ግን ያገኘነውን ዕድል መጠቀማችን ላይ ነው። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዕድል በራሱ ንጉስ ያደርጋል፡፡ በአንድ ወቅት የግሪክ ብሔራዊ ቡድን የአውሮፓ ዋንጫን በማንሳት ዓለምን ጉድ አሰኝቶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ የግሪክ ብሔራዊ ቡድንና የኛ ልዩነት ዕድልን ወደ ውጤታማነት መቀየሩ ላይ ነበር፡፡ ግሪኮች በርትተው እስከመጨረሻ በመሄድ አሸናፊ ከሆኑ በኋላ የማይሻር ታሪክን አስቀምጠው አለፉ፡፡ ቀጣዮቹን ዓመታት የት እንደገቡ እንኳን ለማወቅ እስኪያቅት ጠፉ፡፡ እኛ ግን ዕድላችንን ወደ ውጤታማነት ለመቀየር ተስኖን ነበር፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን በራሱ ድል እንደሆነ አስበን መፅናናታችን በጀን እንጂ በውጤት ደረጃ ውራ/ መጨረሻ ሆነን ነበር የጨነስነው፡፡ ለመሽንፈታችን ምክንያት አንድ ያልገባን ነገር ቢኖር እንጂ የልምድ ማጣት ብቻ አልነበረም ፡፡ ምክንያቱም ልምድ የሌላቸው ግሪኮች ልምድ ያላቸውንና አስፈሪ ሊባሉ የሚችሉ ቡድኖችን በማሸነፍ ዋንጫ እስከማንሳት ደርሰዋልና፤ አዋርደውም ክብር አግኝተዋልና፡፡ በተቃራኒው እኛ ደግሞ ወደ ፈተናው ስንገባ መጨረሻ ሆነን ነው የጨረስነው። አልቻልንም ። በወቅቱ ለምን እንደዚህ ሆንን ተብሎ ሲጠየቅ በምትኩ ጥሩ ተጫውተናል የሚል ነበር መልሳቸው። ሁለት የማይታረቁ ሀሳቦች ማለት ይህ ነው፡፡ ጥሩ መጫወት ጥሩ ቡድን መሰራቱን አያሳይም፡፡ 90 ደቂቃ የሚሰጠው ከተቻለ ጥሩ ተጫውቶ ለማሸነፍ ካልሆነ ደግሞ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው ›› እንደሚባለው በማንኛውም መንገድ ጎል አግብቶ ለማሸነፍ ነው፡፡ ይኸው ነው እግር ኳስ ማለት ፡፡
ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ እውነተኛ ገጠመኝ አጠር አድርጌ ልንገራቹ። በአንድ ወቅት አንድ ተማሪ የትምህርት ማስረጃ ውጤቱ በተለምዶ ሰርተፊኬት ተብሎ የሚጠራውን ይዞ መጣና ለእናቱ ያሳያል።አባትም የኔ አንበሳ ስንተኞ ወጣህ ብሎ ይጠይቀዋል። ልጅም ፈጠን በማለት መጨረሻ ነው የወጣሁት፤ ለምን መጨረሻ እንዳስወጡኝ አላውቅም ይላል ። አባትም ልጄ ተበድሎ ይሆን እንዴ ብሎ ለምንድነው መጨረሻ ያስወጡኽ፤ ለምንድን ነው እንደዛ ያደረጉት ይለዋል። ልጅም የልብ ልብ እየተሰማው ” እህ…ህ. . . አንደኛ የወጣችው ልጅ እንኳን እንደኔ ደብተሯን በንፅሕና አትይዝም . . . እኔ በደንብ ነው ጠረዤ(ሸፍኜ) ዓመቱን ደብተሬ ሳይበላሽ የተማርኩት። እህ… ህ ሁለተኛ የወጣውም ሁልጊዜ አርፍዶ ነው ክፍል የሚገባው እኔ ሁልጊዜ እንደቀደምኩት ነው። በዛ ላይ እኔ ክፍል ውስጥ አላወራም” . . . . ልጅ ምክንያት ያለውን ሁሉ እየዘረዘረ ነው። አባት ከአሁን አሁን ለምን ውጤቱ እንደተበላሸ ይነግረኛል ብሎ ሲጠብቀው ሲጠብቀው ልጅ ሌላ ሌላውን ያወራል። በዚህ መሀል የአባቱ ጥያቄና ሁኔታ ምንም ያላማረው ልጅ ድንገት ለቅሶውን አቀለጠው። የእናት ልብ እንደሚባለው እናትም ውይ ልጄን ብላ ታባብለው ጀመር። አባቱም ሌላ ቀን እናወራልን ብሎ ተነስቶ ወጣ . . . ልጁም እናቱን ጥብቅ አድርጎ ይዞ በሹክሹክታ “እንዴ… ምን አድርግ ነው የሚለኝ ከዚህ በላይ በምን ልብለጣቸው”
getaneh
ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሳችን በብዙ መልኩ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። ደካማ የሆነውን የተሳትፎ ታሪካችንን መለወጥ ተችሏል። ይህ ለኛ ቀጣይ ለምንፈልገው ግብ መልካምና ጠንክረን እንድንሰራ መንገድ ከፋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እንደሚታወቀው እግርኳሳችን አድጓል የሚባል አይደለም፤ ገና ነው አላደገም ትልልቅ የሚባሉ ቡድኖችን ማሸነፍ ላይ ገና ብዙ መስራት እንዳለብን ታይቷል። ጨዋታችን ቆንጆ ነበር ብሎ ሀሳብ ማቅረብ እግርኳስ የሚፈልገውን አድርገናል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ተማሪው እንደዚህ አድርገን እንደዚህ ሆነን ማለት ብቻ ሳይሆን እግርኳሱ የሚፈልገውን መሆን መቻል ነው ያለብን። ደብተር መያዝ ብቻ ጎበዝ ተማሪ እንደማያስብል ሁሉ ጥሩ መጫወትም በተመሳሳይ ጉንጭ ከማልፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ጨዋታ አድርገናል ትልልቅ ሊባሉ የሚችሉ ጨዋታዎችን ተጫውተናል። ከቱኒዝያ እስከ ዛምቢያ ከሊቢያ እስከ ደቡብ አፍረካ ከቡርኪናፋሶ እስከ ናይጄሪያ ተፋልመናል። መቼም ከዚህ በላይ ከማን ጋር መጫወት እንዳለብን ለመናገር ይከብዳል።እዚህ ላይ እግርኳሳችን ሙሉ ለሙሉ የተሟላ እና በሁሉም ረገድ ምሉዕ ነው ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ በብዙ ነገሮች ኋላ-ቀር እንደሆንን እና የበዙ ችግሮች በእግርኳሳችን ዙሪያ እንዳሉ እሙን ነው፡፡ ይህም ከግምት ሲገባ ውጤታችን መልካም የሚባል ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ነገርግን እግርኳስ እንደመሆኑ መጠን ከላይ ያልኩትን የተሰጠንን ዕድል ወደ ውጤታማነት ለመቀየር መስራት አለብን፡፡በወቅቱ አንድም ጨዋታ ሳናሸንፍ አቀርቅረን ነበር የወጣነው ከቢጫ ማልያችንና ከደጋፊዎቻችን ውጪ ሰዎች አህምሮ ውስጥ ያስቀመጥነው ነገር አልነበረም፡፡ በተለይ በውጪው ዓለም፡፡
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የተመደብንበትም ምድብ ያን ያህል ከባድ የሚባል እንዳልሆነ እግርኳስ የሚያውቁ ሰዎች ይናገሩታል። ምድቡንም በአንደኝነት አጠናቀን እንደጨረስን ይህ ቡድን እየተለወጠ ነው ወይ ወይስ ገና አልተፈተነም ተብሎ የክርክር መነሻ እስከመሆንም ተደርሶ ነበር፡፡ ቀጣይ ጨዋታ ነው ብሔራዊ ቡድናችን አቅም እንዳለው በሙሉ አፍ መናገር የሚያስችለው ያሉም ነበሩ። በወቅቱ ይህን ከሚያስቡ ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም ከቀሪዎቹ ዘጠኝ ምድቦች አንደኝ ሆነው ከፈፀሙት የአፍሪካ ሀገራት በዕጣ ከሚደርስን ከአንዱ ጋር መጫወት ጥንካሬያችን ምን ድረስ እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል፡፡ ጠንካራ እና አሸናፊ ለመሆን ሁልጊዜም እራሳችንን መመዘን ያለብን አድገዋል ከምንላቸው ሀገራት ጋር በመጫወት መሆን አለበት። ለወዳጅነት ጨዋታ አነ ሱዳንን አንገጥምም. . . እነ ሩዋንዳን አንገጥምም ተብሎ የነበረው ከእነሱ ምንም ስለማናገኝ እንዲሁም ያለንበትም ደረጃ ለማወቅ ስለማያስችለን ነው፡፡ ከዛ ይልቅ ትልቅ ናቸው የምንላቸውን ጋናን ግብፅን ካሜሮንን ነበር ስንፈልግ የነበረው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከፍተኛ የሆነ አቅምና ልምድ እንዳላቸው ከእነሱ ጋር መጫወት እርግጥም ጥቅሙ የትየለሌ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ተጫዋቾቻንም ሆኑ አሰልጣኞቹ ከእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ነው ሊማሩ የሚችሉት።

Ethiopia national teamከ . . . ናይጄሪያ

የኛ ብሔራዊ ቡድን በብዙ መልኩ መሻሻል ያለበት ነገር አለ፡፡ ሕዝቡ ስለሚጮኸ እንደምንችልም መታሰን የለበትም። ብዙ ግዜ ሳስበው የምንሸነፈውም ስለማንችል ሳይሆን ይነስም ይብዛ ያገኘነው ልምድና ተነሳሽነት በአግባቡ ባለመጠቀማችን ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ደግሞ የቡድንን እና የእያንዳንዱን ተጫዋች ብስለት ይጠይቃል፡፡መብሰል ሲባል ጫናን መቆጣጠር ሊሆን ይችላል፤ መብሰል ማለት እራስን ዝቅ አለማድረግ ሊሆን ይችላል፤ መብሰል ማለት ኃላፊነትን መቀበል እና በአግባቡ መጠቀምም ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የተቀናቃኝን ድክመትና ክፍተት መጠቀም መቻልም ነው። ልምድ ያስፈልጋል የሚባለው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ እኛ ያለን ልምድ ለዚህ ጊዜ ሊጠቅመን ይገባል።
እግርኳስ አስተማርናቸው . . . ጉድ አስባልን. . . ተደነቅን እየተባለ ነው። በወቅቱ ወይም አሁንም ሊሆን ይችላል ከስሜታዊነት ወጥተን ብንመለከት እነሱ ናቸው ኳስን ያስተማሩን፤ ጉድም የሰሩን። ከናይጄሪያ መማር ያለብን ይህን ነው። የሕዝቡን ጫና መቋቋም ችለዋል። መንቀዥቀዥ አይታይባቸውም ነበር። ፍፁም እርጋታ ነበራቸው በተጨማሪም ሁሉም ተጫዋቾች ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ውጤት ለመቀየር ሲታትሩ ነበር። ኳሱን ለኛ ትተው ስራቸውን ይሰሩና ኃላፊነታቸውን ይወጡ ነበር። እንዲሁም የኛ ተጫዋቾች ይሰሩት የነበረውን ስህተት ለመጠቀም የነበራቸው ጉጉትና ዝግጁነት ይገርም ነበር። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው አሰልጣኝ ሠውነት አዳነን ደክሟል ብለው ሲቀይሩት( አዳነ ግን ለአንድ ሬዲዮ ጣቢያ በወቅቱ ምንም አልደከመኝም ቢልም) ወዲያውኑኑ ነው ጫናዎች የበዙብን በተጨማሪም ጎሎችም የተቆጠሩብን። እግርኳስ እንደመሆኑ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ከስህተት ሽንፈት እንደሚመጣ ሁሉ መማርንም መዘንጋት የለብንም። ናይጄሪያ አሁን ያለንበት ደረጃ የት እንደሆነ በደንብ የሚያሳየን ቡድን ነው፡፡ ማደጋችንንም አለማደጋችንንም በእነሱ መመዘን እንችላለን፡፡ ድክመቶቻችንንም ጠንክረን መስራት በመስራት እነሱ ወደደረሱበት ደረጃ መሻገር እንችላለን፡፡ በዚህ መሐል እኔ የሚባል ነገር ሳይሆን በጋራ ለመስራት መነሳት ያስፈልጋል፡፡ አቶ ሠውነት እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት እንዳሉት ሳይሆን ስህተትንም መቀበል፣ ድክመትንም አሜን ብሎ ለማሻሻል መነሳት ያስከብር ከሆነ እንጂ ጉዳት የለውም። ጥሩ ሲሰሩ አንደተወደሱ ሁሉ ትችትም ሲመጣ በተመሳሳይ መንገድ ለመቀበል መዘጋጀት ያስፈልጋል። ኃላፊነትም ለማሸሽ መሞከር ከመተዛዘብ እና እግርኳሳችንን ከመግደል ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ መቼም ስህተት ሆን ተብሎ አይሰራም አውቆ የሚሳሳትም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ስህተትን አብዝቶ ላለማብዛት ነው መጣር ያለበት። ናይጄሪያዎች ክንፍ ባይኖራቸውም በሜዳችን አሸንፈውናል። የበላይነታቸውን አሳይተውናል። ወደፊትም ታሪክ የሚነግረን መሸነፋችንን ነው። የትኛውም የእግርኳስ ታሪክ ቅድሚያ የሚናገረው ውጤትን ነው። ምን ተባለልን… ዓለም ተገረመብን… እገሌ አደነቀን… ሶስት እና አራት የወጪ ጋዜጦች ላይ ተዘገበልን በማለት መኮፈስ እና የደስታ ማዕበል መግባት ብቻ ሳይሆን ሁሉም በሚመለከተው መስክ ሀገራችንን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ስራ መስራት አለበት፡፡ ለዚህም አቅሙ አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ለማድረግም ጠንክረን መስራት ነው የመጀመሪያ ምርጫችን መሆን ያለበት፡፡ እግርኳስ የቡድን ስራ ነው፡፡ ሀገር የምታድገው በቡድን ስራ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የግለሰቦች ተፅዕኖ ኖሮ ምናልባት ውጤት ሊመጣ ቢችልም ይህ ግን ወቅታዊ ውጤትን ጊዜያዊ ደስታን ያመጣ ይሆናል እንጂ ለዘለቄታዊት ማስተማመኛ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ይህንን ቡድን የሚመለከታችሁ እንዲሁም የሚመለከተን በሙሉ በመተባበር ላቅ ወዳለ ደረጃ እናድርሰው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ
ድል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

/bisrat-views.blogspot.com/

zehabesha

No comments:

Post a Comment