Tuesday, October 29, 2013

“ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ይውደም!!!” የሃገራችን ጉዳይ ሁላችንንም ያሳስበናል::




አገር ትልቅ ለውጥ ላይ ናት፤ ከፍተኛ የትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ነን እየተባለ፤ በጐን የዝርፊያ የኮንትሮባንድ እና “በአንድ ጀንበር ፎቅ ሠርቼ ልደር” ዓይነት ዘመናዊ ምዝበራ ይታያል፡፡የጥፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ወገኖች ለሀገር እንደቆሙ፤ የህዝብ ልጆች እንደሆኑ አድርገው መጮሃቸውና ሀቀኛ መምሰላቸው፤ ሌላው እንዳይናገር በር ይዘጋል፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንከኖቻችን ጥቅል ውጤት ማስጨነቁና ማሳሰቡ የሀገርና የህዝብ ስሜት ላለው ሁሉ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ዱሮ የእጅ - እላፊ ይባል የነበረው የምዝበራና አገርን የማራቆት ተግባር፣ (ዛሬ ሙስና የተባለውን)፤ “ባንዱ ያለማ ባንዱ ያደለማ” ሆኗል፡፡ “በአንዴ ዘጋ/ዘጋች” ዛሬ የተለመደ ቋንቋ ነው፡፡ እንደነናይጄሪያና እንደነናይሮቢ (“ናይሮበሪ” እንደተባለው) ዐይን - ያወጣ የቀን ተቀን ዘረፋ የሚመጣው ከላይ እስከታች እየተወሳሰበ ያለው ሙስና ፍፁም ወደፈጠጠ ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡

አንድም ሙስናው በየአቅጣጫው መሆኑ፤ አንድም ደግሞ ቢሮክራሲያዊ መጠቅለያ መኖሩ እጅግ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ (ዱሮ “ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ይውደም” የሚል መፈክር ነበር፤ ነብሱን ይማረው!) በዚህ ላይ የግለሰቦች አሻጥር ሲጨመርበት፣ ከቁጥጥር ውጪ ወደሆነ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ የመሬት አሰቃቂ አወሳሰድ፣ ከፍተኛ የኮሚሽንና የድለላ ሥራ፣ አደገኛ ወገናዊ አሠራር…በአስደንጋጭ የድህነት መቀመቅ ውስጥ ለገባች አገር ከምትሸከመው በላይ ትከሻ አጉብጥ ሸክም ይሆንባታል፡፡ የባሰ ዘግናኝ የሚሆነው ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት በምዝበራ ምክንያት መታሰር ራሱ እየተለመደና ቀላል እየመሰለ መምጣቱ ነው፡፡ “እገሌ ታሠረኮ” ሲባል፤ “ተወው በልቷል - የሚበቃውን ቀለብ አከማችቷል” ማለት እንደሰላምታ የሚነገር መሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡

ዱሮ “በሥራው አጋጣሚ በእጁ የገባውን የመንግሥት ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ” የሚለው ሐረግ ነበር ሬዲዮንና ቴሌቪዥን ያጣበበው፡፡ ዛሬ ዳር እስከዳር በየሰው አፍ የሚወራ ነገር ሆኗል፡፡ ዝርፊያው ዓይነት በዓይነት ሆኗል፡፡ ተወርቶም በቀላሉ ይረሳል፡፡ በተለይ ለህብረተሰብ ቀጥተኛ መጥፊያ የሚሆኑ እንደመድሃኒት ያሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ባመቸው መንገድ ሁሉ ተበርዘው ከተባዙ፣ ምን ያህል አሰቃቂ የሆነ ዕልቂት እንደሚያስከትሉ መገመት አያዳግትም፡፡ የሚያስገኙት ገንዘብ የትየለሌ፣ የሚፈጁት ህዝብ የትየለሌ!!

ማናቸውንም የጥፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ወገኖች ለሀገር እንደቆሙ፤ የህዝብ ልጆች እንደሆኑ አድርገው መጮሃቸውና ሀቀኛ መምሰላቸው፤ ሌላው እንዳይናገር በር ይዘጋል፡፡ They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ - ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ እንደማለት ነው፡፡ ጩኸቱ በቅጡ ለገባው አገር - ወዳድ ሰው ግን፤ “ቤቱን አቃጥሎ እንዴት ብሩህ ቀን እንደሆነ ተመልከቱ” አለ እንደተባለው ነው፡፡ ልዩነቱ ያኛው ለግሉ እየተጠቀመ፤ ይሄኛው የገዛ ንብረቱን ጭምር እያወደመ የሚጃጃል መሆኑ ነው፡፡ ሁለቱንም መዋጋት ተገቢ ነው!(አዲስ አድማስ)
 

No comments:

Post a Comment