Friday, October 18, 2013

አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በማርክሲዝምና ፕሮቴስታንት እምነት የተዳቀለን እምነት ምን ይሉታል? ነው ሁሉም የስልጣን መሰላል ናቸው?



አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የአቶ መለስን ቡራኬ እንዲያገኙ ያስቻላቸው አምባገነኖች የግለሰብ ነጻነትን ለማፈን የሚጠቀሙበትን የካድሬ ስርዓት 1 ለ5 በሚል አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲሆን ቀዳሚውን ሚና መጫወት በመቻላቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመሆኑም የሌሎች ቄሶችን ትዕዛዝ ተቀብለው ከማስፈጸም አልፈው የ1ለ5 ጥርነፋ መሰራች እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሀይለማሪያ ደሳለኝ የግራ ዘመሙን እምነት ለመቀላቀል ዳዴ እያሉም ፕሬቴስታንት መሆናቸውን ለመናገር አልታከቱም፡፡ በማርክሲዝምና ፕሮቴስታንት እምነት የተዳቀለን እምነት ምን ይሉታል? ነው ሁሉም የስልጣን መሰላል ናቸው?
እውን አቶ ሀይለማሪያም እምነት አላቸውን?
ኢህአዴግን ላለፉት አመታት በጠቅላይ ሚኒስተርነት የመሩት አቶ መለስ ቢያንስ ስልጣን እስኪይዙ ድረስ ጸረ እምነት የሆነው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አቀንቃኝ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን እምነታቸው ከዚሁ ማርክሲዝም ያልወጣ እንደነበር ይከተሏቸው በነበሩትና ከአሁን በኋላም
‹‹በሌጋሲ›› መልክ ከቀጠሉት ፖሊሲዎች መመልከት ይቻላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስትና ሌሎችም ፖሊሲዎች ከግራ ፖለቲካው የተቀዱ ናቸው፡፡ እነዚህ የግራ ዘመም ርዕዮቶች የተቀዱት ፖሊሲዎችም በእምነት ላይ ያላቸው አመለካከት ደግሞ አሉታዊ ነው፡፡ ለይስሙላህም ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስተርነቱን ስልጣን የተረከቡት አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በእምነት ከአብዛኛዎቹ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች የተለዩ መሆናቸው ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አቶ ሀይለማሪያም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይና ልጆቻቸውም በዚሁ ቤተ እምነት ያገለግሉ እንደነበር ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል አቶ ሀይለማሪያም እናታቸው ፕሮቴስታንት ባለመሆናቸው ከፍተኛ ቁጭት እንደሚሰማቸው መግለጻቸው በአንድ ወቅት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ፕሮቴስታንት ከኦርቶዶክስና ሮማን ካቶሊክ ጋር ሶስተኛው የክርስትና እምነት ነው፡፡ ፕሮቴስታንት አጥባቂ ከሚባሉት ሁለት የክርስትና ዘርፎች በተቃራኒ የለውጥ እምነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የተለያዩ የፕሮቴስታንት እምነት ክፍሎች ቢኖሩም ሁሉም የእምነቱ ክፍሎች በሌሎቹ የክርስትና ክፍሎች የእምነቱ ቁንጮና ትልቅ ስልጣን ያለው አድርገው የሚቆጥሩትን የጳጳስን ስልጣን አይቀበሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ የመጽሃፍ ቅዱስ የበላይነትና የግለሰቦች እምነት ነጻነትን ይፈቅዳል፡፡ ግለሰቦች ፈጣሪያቸውን በቀጥታ ማግኘት እንዲሚችሉ የሚያምንና ነጻነትን የሚፈቅድ የእምነት አይነት ሲሆን ይህን ነጻነት ለማምጣት ሉተርና መሰሎቹ ሲያገለግሉበት ከነበሩት ቤተክርስትያኑ ጀምሮ በየደረጃው ጠንካራ ተቃውሞ ቢገጥማቸውን ከፍተኛ መስዋትነት እንደከፈሉ ይነገራል፡፡

እንግዲህ አቶ ሀይለማሪያም በግለሰብ ነጻነት በሚያምን፣ የቄስና ጳጳስ የበላይነትን በማይቀበል፣ ግለሰቦች ራሳቸው ፈጣሪያቸውን ማግኘት ይችላሉ ከሚለውና እውነት ብለው ባመኑበት ከፍተኛ መስዋትነት ተከፍሎበታል ከሚባለው እምነት አባል መሆናቸው ነው፡፡ በፕሮቴስታንት እምነት መሰረት ከመጽኃፍ ቅዱስ ውጭ ሌሎች መጽሃት እምብዛም ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ከእየሱስ ክርስቶስ ውጭም የሚያመልኩት አምላክና አማላጅ የለም፡፡ በዚህ የጳጳስና ቄስ ይልቅ ግለሰቦች ነጻነትን እንደሚፈቅድ የሚነገርለት እምነት ተከታይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ግን የሚተገብሩት ተቃራኒው ነው፡፡

ለአቶ ሀይለማሪያም በአቶ መለስ ዜናዊ ጵጵስና የሚያምኑ ሰው ናቸው፡፡ እያንዳንዱ አቶ መለስ የተናገሩት፣ ጻፉት የተባለው ነገር ሁሉ ለአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ቅዱስ ነው፡፡ በአቶ መለስ ዘመን የተደረሱት አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት የመሳሰሉ ግራ ዘመመም ፖሊሲዎች አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከእምነታቸው በተቃራኒ ሊያስቀጥሉ የቆረጡባቸው ጉዳዮች ሆነዋል፡፡ ለአቶ ሀይለማሪያም ኢትዮጵያዊያን ከግለሰባዊ ነጻነት ይልቅ አቶ መለስ ተብትበውት ባለፉት የብሄር ማንነት፣ የካድሬ ስርዓትና የመሳሰሉት ግራ ዘመም ፖለቲካ ስዓቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሆነዋል፡፡

ከአቶ መለስ ዝቅ ሲልም የህውሃት/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች (ቄሶች) በኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ የጨቋኝነት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በግለሰብ ነጻነት ያምናል በተባለለት እምነት አማኝ እንደሆኑ የተነገረላቸው አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ‹‹ቅድስናውን›› ያገኙት በአቶ መለስ ቡራኬ ከመሆኑም ባሻገር ለአሁኞቹ ፖለቲከኞች (ቄሶች) ፍጹም ታዛዥ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በፕሮቴስታንት እምነት መጽኃፍ ቅዱስ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው፡፡ በፖለቲካው ደግሞ ህገመንግስት እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ሁሉ የህጎች ሁሉ የበላይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አቶ ሀይለማሪያም ግን ኢትዮጵያውያንን እያስገዙ የሚገኙት ከህገመንግስቱ (የፖለቲካው መጽሃፍ ቅዱስ) ውጭ በእየጊዜው ስልጣንን ለማስጠበቅ በሚያመች መልኩ በሚወጡት ጨቋኝ አዋጆች ነው፡፡ ጀርመናዊው ማክስ ቬበር እኤአ በ1905 ‹‹The Protestant Ethic and the Spirit of Capitalism›› በሚል መጽሃፍ አሳትሟል፡፡ እንደ መጽሃፉ ካፒታሊዝም የፕሮቴስታንት እምነት ውጤት ነው፡፡ ካፒታሊዝም በነጻ ገበያ ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው፡፡ በግለሰቦች ነጻነት የሚምነው ፕሮቴስታንቲዝም አውሮፓ ያመጣው ለውጥም ለዚህ ለግለሰቦች የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህራዊ ነጻነት ቀዳሚውን ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይ በመንግስት የበላይነት የማይመራ፣ ያልታቀደና ግለሰቦቹ በራሳቸው ፍላጎትና ውድድር የሚያደርጉት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የፕሮቴስታንት ነጸብራቅ መሆኑን ቬበር ይገልጻል፡፡ ከዚህ እምነት የመነጨ ተብሎ የሚታሰበው ካፒታሊዝምም ግለሰቦች መንግስት ባቀደው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ በነጻ ገበያ መወዳደር አለባቸው ይላል፡፡ የመንግስትንና የሌሎች አካላትን ጣልቃ ገብነትም ይቃወማል፡፡ ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ ሲሆን ፖለቲካዊ መስኩም ሌብራሊዘም ነው፡፡ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከአቶ መለስ ተቀብለው ‹‹እያስቀጠልኩት ነው›› የሚሉን ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ይህ ማክስ ቬበር ከሚጠቅሰው የፕሮቴስታንት መርህ በእጅጉ ያፈነገጠ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚሉት መርህ መሰረት የአቶ ሀይለማሪያም መንግስት በበላይነት በሚመራው የገበያ ስርዓት ውስጥ እየታመሱ ነው፡፡ ዜጎች፣ ድርጅቶችና ነጋዴዎች የሚንቀሳቀሱት መንግስት በየጊዜው በሚቀይሳቸው የገበያ ስርዓቶች ነው፡፡ መንግስት አትክልትና ፍርፍሬ ላይ ሳይቀር በነጋዴው ላይ ተመን ሲያወጣ በፓርቲ ደረጃ ባቋቋማቸው የንግድ ድርጅቶች እንደፈለገ ገበያውን ያተራምሳል፡፡ በአገራችን አቶ ሀይለማሪያም የሚመሩት መንግስት አምራችም፣ አከፋፋይ፣ ቸርቻሪም ነው፡፡ ይህ ጣልቃ ገብነት ደግሞ ቬበር ከሚለው የፕሮቴስታንት መርህ ይልቅ ጸረ እምነት ለሆነው ማርክሲዝም የተቀዳ ነው፡፡ የአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ መንግስት ካፒታሊዝምንም ሆነ ኒዮ ሌብራሊዘምን እንደ ጭራቅ ከመፍራት አልፎ ተቃዋሚዎችን ‹‹ተላላኪ፣ አፍራሽ….› በማለት መፈረጃ አድርጎታል፡፡ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በአንድ በኩል ፕሮቴስታንትነታቸውን ሲገልጹ በተቃራኒው የሚተገብሩት ግን የፖለቲካው ጳጳሳት ያስቀመጡትን ግራዘመም መርህ ነው፡፡ ምንም እንኳ እምነቱ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› ቢልም አቶ ሀይለማሪያም ግን የግራ ዘመሞቹን ‹‹ቄሶች›› ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ወኔ ያገኙ አይመስልም፡፡ ከእየሱስ ውጭ መታመን ያለበት ምንም ነገር እንደሌለ የፕሮቴስታንት መርህ ቢሆንም አቶ ሀይለማሪያም ግን በአቶ መለስ አምነው መላውን የአትዮጵያ ህዝብ ለማሳመንም ቀና ደፋ እያሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የአቶ መለስን ቡራኬ እንዲያገኙ ያስቻላቸው አምባገነኖች የግለሰብ ነጻነትን ለማፈን የሚጠቀሙበትን የካድሬ ስርዓት 1 ለ5 በሚል አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲሆን ቀዳሚውን ሚና መጫወት በመቻላቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመሆኑም የሌሎች ቄሶችን ትዕዛዝ ተቀብለው ከማስፈጸም አልፈው የ1ለ5 ጥርነፋ መሰራች እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሀይለማሪያ ደሳለኝ የግራ ዘመሙን እምነት ለመቀላቀል ዳዴ እያሉም ፕሬቴስታንት መሆናቸውን ለመናገር አልታከቱም፡፡ በማርክሲዝምና ፕሮቴስታንት እምነት የተዳቀለን እምነት ምን ይሉታል? ነው ሁሉም የስልጣን መሰላል ናቸው?
 
minilik salsawi

No comments:

Post a Comment