Thursday, August 15, 2013

“አስማተኛ ወይም ጠንቋይ አይደለሁም” – የታገዱት መምህር ግርማ ወንድሙ

“አስማተኛ ወይም ጠንቋይ አይደለሁም” – የታገዱት መምህር ግርማ ወንድሙ

ዘ-ሐበሻ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መምህር ግርማ ወንድሙ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ እንዳያጠምቁና ትምህርት እንዳይሰጡ መታገዳቸውን እስከ እግድ ደብዳቤው በማቅረብ መዘገቧ ይታወሳል። የርሳቸው ጉዳይ አሁንም አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ይመስላል። ለዚህም ነው በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ላይፍ መጽሄት መምህር ግርማን ቃለ ምልልስ አድርጎ አቅርቧል። ለግንዛቤ ከጠቀመ በሚል በድረገጻችን አካፍለናችኋል።
ላይፍ፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የጥምቀትና የትምህርት አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱበት ምክንያት ምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ምክንያቱም ሰው በመዳኑ እና የዲያቢሎስ ሚስጥር በመጋለጡ እንዲሁም ህብረተሰቡ ለከፋ መንፈስ ግንዛቤው እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ እኔ እየሩሳሌም አገልግሎት ሄጄ እያለ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልክአ ኃይል አባ ሚካኤል የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነን በሚሉ ግለሰቦች አማካኝነት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ብዙ ወጪ ወጥቶበት ተገንብቶ የነበረውን መድረክ እና የምዕመና መቀመጫዎች በመንቀልና በመሰባበር ከጥቅም ውጪ አደረጉት፡፡ እነኚህ ሰዎች ያልተረዱት ቢረዱትም ግድ የማይሰጣቸው ያወደሙት ንብረት የእኔ ሳይሆን የእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መሆኑ ነበር ፤ በቤተክርስቲያን ዙሪያ በሰንበት ትምህር ቤት ብዙ ችግሮች ይሰማሉ፡፡ እነኚህ የሰንበት ትምህር ቤትን ምግባርና ስርዓት ሳይኖራው በስም ብቻ የተጠለሉ አንዳንዶቹ እንደ ክርስቲያን ሳይሆን የእርኩሳን አሰራር የሚፈጽሙ እንደነበር ብዙዎች አገልጋዮች ያውቃሉ፡፡በተጨማሪም ማታ ማታ በድራፍትና በመጠጥ ዙሪያ ሲንካኩና ሲጨፍሩ አምሽተው ጠዋት መጥተው ከበሮ የሚደበድቡ ናቸው፡፡ ጸጉራቸው እንኳን ምስክር ነው፡፡ የተንጨባረሩ ፍጹም ቦዘኔና ዘላን መልክና ገጽታ ያላቸው ናቸው፡፡ ለአባቶቻቸው ክብር የሌላቸው፡፡ ማዋረድ ስራቸው የሆነ ፤ የስነ ምግባር መንፈሳዊ ትምህርትን ከምንም ቦታ ያልያዙ እንደዚሁ የመደዴነት ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ ነው የቤተክርስቲያኗ መድረክና ንብረት ያወደሙት፡፡
ላይፍ፡- ከዚህ በፊት በማን ጥሪ መሰረት ነው እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲሰጡ የነበረው ?
መምህር ግርማ፡- በደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ሰላም አማካኝነት ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ቦሌ አቦ ፤ ኪዳነምህረት ፤ ፉሪ ሥላሴ ፤ ጭቁኑ ሚካኤል ፤መገናኛ እግዚአብሔር አብ በጠቅላላው በከተማይቱና ወጣ ባሉ ያሉ ደብሮች አገልግያለሁ፡፡
ላይፍ፡- ለስንት ዓመት አገልግሎት ሰጥተዋል?
መምህር ግርማ፡-ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እዚህ አዲስ አበባ ያልተቋረጠ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
ላይፍ፡- በእነዚህ አገልግሎት ዘመናት ለቤተክርስቲያን ምን አስተዋጽ አበርክተዋል ?
መምህር ግርማ፡- በእስጢፋኖስ ደብር ጣሪያው ውሃ ያስገባበት ወቅት 3 ሚሊየን ብር ገቢ አሰባስቤ አድሳት አድጌአለሁ፡፡
ላይፍ፡- ለምን ያህል ህሙማን ከህመማቸው የመፈወስ እና ትምህርት አገልግሎት ሰጥተዋል..?
መምህር ግርማ፡- ለ4 ሚሊየን ሰው የፈውስ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
ላይፍ፡- በተለይ በምን አይነት ህመም ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎችን አድነዋል ?
መምህር ግርማ፡- አይናቸው የጠፋ ፤ ሰውታቸው አልታዘዝ ብሎ አልጋ ላይ ውለው የነበሩ ፤ እጅና እግራቸው ሽባ የነበሩ ሰዎችን ፈውሻለሁ፡፡
ላይፍ፡- ሁላችሁም የእግዚአብሔር ቃል የእመቤታንን በረከት የምታስተምሩበት ቤተክርስቲያን ለምን እንዲህ አይነት መከፋፈል መጣ ብለው ያስባሉ ?
መምህር ግርማ፡- በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንክርዳድ በስንዴው መሀል እንደሚዘራው ሁሉ ያም በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ፡፡ ገበሬው መልካም ስንዴን ዘራ የሚለው ከውጭ አይደለም፡፡ ዘሩ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ህይወትና በልቦና ውስጥ መጀመርና በስጋ ህይወት መጀመር ልዩነት አለው፡፡ አምኖ መጀመርና ሳያምኑ መጀመር የእዚያን ያህል ነው፡፡ ሰሞኑን ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው የሚኖሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከተለያዩ የአስማት ስራ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሲጠጉ ብዙ መልካም ነገር አይጠበቅባቸውምና ይህንን የሚመለከት ‹‹በማለዳ መያዝ›› የሚለው መጽሀፌ ላይ ሰፋ ባለ መልኩ አስቀምጬዋለሁ፡፡ ንጹህ የአምልኮት ፍላጎትና እንዲሁ ደግሞ በደብዛዛው በሚመላለሱ ሰዎች መካከል ዲያቦሎስ በደንብ ይሰራል፡፡ በተለይ ኦርቶዶክስ እምነት ላይ ሰይጣን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከታሪክ እውነታም አንጻር እነዚህ ሰዎች ህይወት ውስጥ የተለየ እድል አለ፡፡ ገብቶ ይቀመጥና በጎው መጥላት መልካሙን እንደክፉ ማየት ማሳደድ ያለው መናፍቆች ላይ ሳይሆን እኛ ጋር ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የሃይማኖቱ አንዱ በረከት ነው፡፡ ለምን ፈሪሳውያንን ክርስቶስ በመጣ ጊዜ እምነቱን ተራ ወግና ተራ የሆነ የይስሙላ አድርገውት ነበር፡፡ ያ ሂደት ደግሞ እንደዚሁ በቆየን ቁጥር የአዲስ ኪዳንንም ህይወት እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ፈሪሳውያን ጠላት ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ እውነቱ እየጠፋ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣልቃ ይገባሉና ያንን ለመለየት የመንፈስ ቅዱስ ስራም የአጋንንት የቅንነትም ስራ ስለሚያስፈልግ ዛሬ ያ ቅንነቱ እና በጎነቱ በክፋት በተንኮል በምቀኝነት የተሞላ ስለሆነ ያ ሂደት ሊያደርገን አልቻለም፡፡
ላይፍ፡- ብዙ ሰባኪያን ወደ እርስዎ ፕሮግራም የማይመጡት ለምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ይህንን የፈውስ ሂደት ስላለመዱት ልክ እንደ መተት እንደ ጠንቋይ አሰራር አድርገው እስከዛሬ ድረስ ሲያወሩ እንደቆዩ ያው የተለመደ ነገር ነው፡፡ስላልተለመደ እንግዳ ነገር ነው የሆነው፡፡ በተለይ በግለሰብ ጸጋ አልተለመደም፡፡ ይህንን ያልተለመደ ነገር እንዲህ ሲወጣ ሁሉም እየተረባረበ ማጨለም ነው የሚፈልገው፡፡ የእግዚአብሔር ስራ ደግሞ ስለማይጨልም ሂደቱን ጠብቆ ይበራል፡፡ ከዚህም በፊትም የተደረጉብኝ ዘመቻዎች ብዙ ናቸው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ እንዲያውም የመጨረሻው ደካማ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ሰዎች መንፈሳዊ አንድነታቸው በክፉ ሰዎች መንፈስ ተመቷል፡፡ በራስ እይታም ተመቷል፡፡ የምቀኝነት መንፈስ አጠናክረው በመያዛቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ጸጋ በረከት መለያ መንፈስ አጥተዋል፡፡ አንድነትና ተስማምቶ መዝለቅን በዚህ ዘመን ውስጥ የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም፡፡ ግን እውነት ዞሮ ዞሮ ደረጃዋን ጠብቃ ስለምትወጣ ያን ያህል አስጊ አይደለም ማለቴ ነው፡፡
ላይፍ፡- ከአስተዳዳሪው ጋር የነበራችሁ አለመግባባት ከየት የመጣ ነው?
መምህር ግርማ፡- አስተዳዳሪው መልአከ ኃይል አባ ሚካኤል በአንድ ላይ ቁጭ ብለን በተካፈልንበት ጉባኤ ላይ ሁለት ክፍል ያለው ኮንዶሚኒየም ገዝቼ እንድሰጣቸው ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡
ላይፍ፡-ለቤተክርስቲያን የሚገባውን ሙዳይ ምጽዋት ይካፈላሉ ?
መምህር ግርማ፡- ኧረ በጭራሽ ምጽዋቱ ለቤተክርስቲያን ነው የሚሆነው፡፡
ላይፍ ፡- ታዲያ ከየትኛው ገቢዎ ላይ ነው አስተዳዳሪው ኮንዶሚኒየም ገዝተው እንዲሰጧቸው የጠየቁዎት ?
መምህር ግርማ፡-እንዲያው ለትራንስፖርት ፤ ለምንም ወይም ሲዲ ወይም መቁጠሪያ የምሸጠው አለ፡፡ ከእሱ እንደምንም አቻችልና ግዛልኝ ፡፡ አለበለዚያ ደግሞ ሕዝቡን አስተባብረህ የበረከቱ ነገር ወደ እኔ አዙረው ነው ያሉት ሰውየው፡፡
ላይፍ፡- እኛ ከዚህ በፊት ስለዚህ ኮንዶሚኒየም ግዙልኝ ብለው ጠይቀው እንደሆነ ጠይቀናቸው በጭራሽ አልጠየኩም በማለት መልስ ሰጥተው ነበር ?
መምህር ግርማ፡- እውነት በቃል ማስተባበር ይቻል ይሆን ? ከህሊና እና ከእግዚአብሔር መሰወር ግን እንዴት ይቻላል ?
ላይፍ፡- ታዲያ ምን ምላሽ ሰጠዋቸው ?
መምህር ግርማ፡-በወቅቱ ያንን ማድረግ አቅሙ ስለሌለኝ ጥያቄያቸውን እንደማልቀበል ገልጬላቸዋለሁ፡፡
ላይፍ፡- ምላሽዎ በግሳጼ ወይስ ሌላ ገጽታ ነበረው…?
መምህር ግርማ፡- በግሳጼ መልኩ አልመለስኩም፡፡ ለምን ያው የሕዝቡ ችግር ስለማውቅ ሁኔታዎችን ስጠብቅ በራሱ ጊዜ ገነፈለና የሰውየው ኃይል ወጣ፡፡ እኔ መገሰጽ አልፈለኩም፡፡ ምክንያቱም ችግሩን አውቃለሁ፡፡ እንዲህ የተወሳሰበ የሙስና አሰራሮች ከመጀመሪያው ጀምሮ በየደረጃው ስር ሰደዱ ናቸው፡፡ በአንድ ዘመን ሳይሆን እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ሰውየው ወደ ማዕረጉ እና ወደ አስተዳደሩ ሲመጡ 60 ሺህ ብር ከፍለው ነው ለዚህ የበቃሁት ይላሉ ፤ ያንን በተለያዩ መንገዶች ማቻቻል አለብኝ ማለት ነው፡፡
ላይፍ፡- የኮንዶሚኒየም ግዢ ይህን ያል ያወጣል ብለው ግምቱን ነግርዎት ነበር ?
መምህር ግርማ፡- በቃ ሁለት ክፍል ያለው ኮንዶሚኒም ነው ይገዛልኝ ያሉት ፡፡ ግምቱንም ያውቁታል፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ አለኝ የሚሉት የፈውስ ጸጋ ከየት የመጣ ነው ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡- ይህ እኮ አንድና ሁለት ነው እንደሚባለው አይነት ፎርሙላ ወጥ አድርገህ የምታሳየው ነገር አይደለም፡፡ ይህ በጸሎት በስግደት በቅዱስ ቁርባን በመመጽወት ከሰማይ የሚለቀቁት እንጂ ከማንኛውም ሰው የምትገዛው ወይም የምትለውጠው ትርፍ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ይህ ከሰማይ የሚሰጥ እንጂ በስጋዊ ጥበብባ ዘዴ ወይም ምርምር ወደ ላብራቶሪ የሚመጣና የሚገኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሰራር ደግሞ አለምም ሆነ ስጋውያን አያውቁትም፡፡ መንፈሳውያንም ተቸግረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ የገዛ አባቶቼ እንኳን ሳይቀሩ ይህንን መንፈሳዊ ጸጋ ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም ከእኛ በኩል ካፈሰሰ ነው እኮ አሁን ችግሩ፡፡ ከእኔ በኩል ካልፈሰሰ እንዴት በዚህ ዘመን ከእግዚአብሔር ይመጣል ፤ የሚል ዋጋ ቢስ እና ተስፋ አስቆራጭ የመንፈሳዊ ህይወት ጉዞን የለመዱት ባህሪ ለማንጸባረቅ ሲሞክሩ ነው አሁን ነገሮች ወደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡት፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ ተሰጥቶኛል የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ስያሜ ሰጥተውታል ?
መምህር ግርማ፡- እንደዚህ ያለ ነገር የለም እንጂ ምን ስሜ ይሰጠዋል ? ክፉ መናፍስን የሚቃወም የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስና ክፉ መንፈስ ደግሞ አይገናኙም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ ክፉውን መለየት ፤ ክፉው ማስወገድ ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አጋንንትን አወጡ ይል የለም እንዴ? በአሁኑ ዘመን አጋንት አስገባ ቢባል ሁሉም ይወደኛል፡፡ አጋንንት ማስወጣት እኮ ነው የተለየ ጠንቋይ ያደረገኝ፡፡
ላይፍ፡-አለኝ የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ ? ወይስ እርስዎ ጋር ነው ሊቀር የሚችለው ?
መምህር ግርማ፡- የኤልያስ መንፈስ በኤልሳ እንዳደረ ሁሉ የፈለገው ሁሉ ያገኛል፡፡ እኔም የማስተምረው እኮ ክርስቲያኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ነው፡፡ ጠላቱን እንዲጋፈጥ ፤ ክፉ መንፈስ እንዲያሸንፍ ፤ የዲያቢሎስ ትውልድ መሆኑ እንዲቆም ፤ ከዚያም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስራ የእግዚአብሔር ክብርና ኃይል እየጨመረ እንዲመጣ ፤ የአለም ጥበብ ከእግዚአብሐየር መላዕክ አሰራር ጋር ክርስቲያኖች በረከት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡፡ አሁን ለምሳሌ በአሜሪካ በስልክ የሚሸኝላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በእጄ ማስረጃ አለኝ፡፡ በስልክ የሚሸኝላቸው ራዲዮ አቢሲኒያ ላይ ከቁትር 1 ጀምሮ እስከ 34 ድረስ ያለውን ትምህርት በመከታተል እየጸለዩ እየሰገዱ በመቁጠሪያ እየቀጠቀጡ መንፈሱን ያዳክሙታል፡፡ ከዚያ በኋላ መንፈሱ ራሱ እኔ አይ ጥላ ነኝ ፤ ቡዳ ነኝ ፤ አብሬ ነው የተወለድኩት እያለይነግራቸዋል፡፡ በመጨረሻ ከተዳከመ በኋላ አንዳዴ ራሱ ‹‹ሸኙኝ›› ብሎ ይደውላል፡፡ በእጄ የቀረጽኳቸው ከ200 በላይ በስልክ የሸኝሁላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አሁን አባቶች ይህ ነገር ሲሰሙ ይደነግጣሉ፡፡ ምክንያም እንዴት በስልክ ሰይጣን ይወጣል ብለው አንድ ወቅት ላይ አቅርበው ጠይቀውኛል፡፡ ስለዚህ ጸጋው የቤተክርስቲያን እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ መቁጠሪያው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ ውዳሴው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ መላከ ትግሉ የቤተክርስቲያን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የእኔ የያዝኳቸው የምትሀት አሰራር የለም፡፡ ስለዚህም ሁሉም ህዝብ በውጭ አለም ያለው በተለይ ከክፉ መንፈስ ጋር ያለውን ፍልሚያ በሚገባ ስለተገነዘበ እያንዳንዱ ራሱ በመቁጠሪያ እየተጠቀመ የሸኝውም አለ፡፡
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ ጉባኤ ተገኝተው በረከት ይሰጡ ነበር ወይ ?
መምህር ግርማ፡- እኔ በማገለግለው ላለመገኝት ብዙዎች ይሸሻሉ ተሰልፈው ዝቅ ብለው የህዝብን ችግር ለማየት እስከ አሁን በጎ ህሊና አላገኝሁም፡፡ ሃገር እንደ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማው ኃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አይነቱ በተደጋጋሚ የህዝቡን ችግር ተረድተው በተደጋጋሚ ወደዚያ እየሄድኩ ሳገለግል መንፈሳዊ ድጋፋቸውን ለህዝቡ ካለው ችግር ለልማቱም ከማሰብ ቢርሌ የሰጡት ቦታና ስራ አለ፡፡
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት አስተያየታቸው ምንድነው ?
መምህር ግርማ፡- ብዙዎች ይህንን መንፈሳዊ ድርሻ ለመወጣት በማደርጋቸው ጥረቶች ላይ በጎ ድጋፍ የላቸውም፡፡ ከተለያዩ አይነት መንገድ ለመዳንም ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን አንዳዶች እንዲያውም የሸናሻም መተት ይህን ያደርጋል፡፡ የሸናሻም አስማት ይህንን ይሰራል እያሉ ለአስት አሰራር ትልቅ ድጋፍና የሰይጣን አሰራር ትልቅ ሞራል ሲሰጡ ነው የሚሰማው፡፡
ላይፍ፡- ይህንን እርስዎ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ አገልግሎት ሌሎች አባቶች ያምኑበታል ?
መምህር ግርማ፡- እኔም በጣም ግራ የሚገባኝ ዲያቢሎስ የሚያደርገው ጥቃት በመጽሀፍ ቅዱስ በረጅሙ እና በስፋት ጥልቀት ባለው ሁኔታ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት አጋንንትን እያወጡ የሰዎችን ደህንነት ሲያበለጽጉ ይታያል፡፡ በቤተክርስያንም እደዚሁ በመንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ስራ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ሰዎች በክፉ መንፈስ አሰራር ወይም አያምኑም አልያም በእዚአብሔር አሰራር አያምኑም፡፡ በዚህ መንታ መንገድ ላይ መታየት አሁን አይቻልም፡፡ ምክንያም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዲያቢሎስ ተጠቅቷል፡፡ ወይ ዲያቢሎስ እንዲበላ ማድረግ ነው አልያም በቤተክርስቲያን መንፈስና ጸጋ ህዝቡ ችግር ውስጥ ገብቶ ችግሩን ማየት ነው፡፡ ገለልተኛ ሆኖ መኖር አሁን አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ስለዚህ ያምናሉ አያምኑም የሚለው ነገር እርሳው እኔን ቢረዱኝ ደስ ባለኝ፡፡ በተሰጣቸው ጸጋ ክፉ መንፈስ ነው ካሉ የእኔን መንፈስ ማወጣት መቻል፡፡ ሁሉም ቢተባበሩኝ መልእክት አስላልፋለሁ ፡፡ እንዲያውም በቤተክርስቲያን ይኖር የነበረ አስማተኛ መንፈሱን አስወጣንለት ብለው ለአለም ዜና ቢያቀርቡ ደስ ባለኝ ነበር፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኗ ወታደርና ነጋዴ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አይሆንም የሚል ሕገ ደንብ አላት፡፡ እርስዎ ግን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ወታደር እንደነበሩና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ 1.5 ሚሊየን የሚገመት ቤት ገዝተው እየኖሩ ነው ይባላል በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡-ዛሬ ሰማዕቱ ሀገር ጠባቂ የምንለው ቅዱስ ጊዮርጊስም የመቶ አለቃ ወታደር ነበር፡፡ ግብጽ ውስጥ ያሉ ብዙ ታላላቅ አባቶችም እንደዚያው ናቸው፡፡ በአሁንም ዘመን ያሉ ብዙ መነኮሳቱ እስከ ጳጳሳቱ ወታደር የነበሩ ናቸው፡፡ ወታደር ማለት የእግዚአብሔርን ስራ አይሰራም ማለት አይደለም ፡፡ እኔ ደግሞ ልቀድስ ላቁርብ አላላኩም ፤ በተሰጠኝ ጸጋ ላገልግል ነው ያልኩት፡፡ ቤት ምናምን የሚሉት ቤቱን የገዛልኝ የተፈወሰ ሰው ነው፡፡ ቤቱን የገዛልኝ እግዚአብሔር በሰው በኩል ነው ፡፡ ቤቱን የገዙልኝ ሰው በተጨባጭ ከጎኔ አሉ፡፡ ይህንን እንደ አንድ እንደ ትልቅ ነገር ማንሳት በራሱ ምንን ያመለክታል ፤ ምቀኝነትን ነው ፤ ያው ከደማችን ውስጥ የተለመደ ምቀኝነት ስላለ እንጂ ከነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ እንዳሰራ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡
ላይፍ፡- እርስዎን አስማተኛ እና ጠንቋይ ናቸው የሚሉዎት ሰዎች ምላሽ ምንድነው ?
መምህር ግርማ፡- እኔ አስማተኛ ከሆንኩ እኔ ጋር መጥተው አስማቱን ማውጣት ነው፡፡ እኔ ጋር መጥተው አስማቴ የት ጋር እንደተቀበረ ፈልገው ማውጣት ነው፡፡ ክንዴ ላይ ወይም እግሬ ላይ ወይም ጭንቅላቴ ላይ እንዳለ ደንበኛ ራጅ ይዘው መጥተው ፈልገው ማውጣት፡፡ ወይም መንፈስ ከሆነ ያስወጡልኝ፡፡ ቢረዱኝ እኮ ለእኔም ደስ ይለኛል፡፡ ግልግል ነበር፡፡ እስቲ አስማቴን ኑ እና አስወጡልኝ እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብዬ እለምናችኋለሁ፡፡

4 comments:

  1. ብዙዎች እግዚአብሔርን በአካል ቢያዩት ሊያምኑት እንደሚችሉ ይገምቱ ይሆናል፡፡ ብናየውም ጭራሽ ኋላ ለመጠየቅ እዳ ይሆንብናል እንጂ ብዙዎቻችን አናምነውም፡፡ እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ (በሙሉ ግርማውና ክብሩ) ለማየት ሲጀምር ለእኛ ሊቻለን የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ብዙ ነብያትና ጻድቃን አዩት ቢባልም ለእነሱ በሚቻላቸው ሁኔታ እንጂ እግዚአብሔርን ከቶም ለማየት አይቻልም፡፡ እሱ በወደደው መልክ ሲታየንም ለማየት አእምሮአችን ብቃት ላይኖረው ይችላል፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ለዘመናት እንዲጠብቁት አስቀድሞ ተነግሯቸው ሰው ሆኖ ቢመጣ ሥራውን ሁሉ በአይናቸው እያዩ ሊያዩት ያልቻሉት ካህናትና የካህናት አለቆችን ጨምሮ ብዙ ክርስቶስን የተቃወሙት ናቸው፡፡ ዳህራዊ እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ ወደዚህ የምትወስድ ፍልስፍና ደግሞ እጅግ የረቀቀ ማስተዋልንና መሻትን የምትጠይቅ ናት፡፡ በአይን ማየት ለእንደዚህ ያለችቱ ፍልስፍና ለመቀበል ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ የአእምሮ መከፈት ከሌለ፡፡ ችግሩ ደግሞ እናውቃለን በሚሉ ሰዎች ይበዛል፡፡ እራሳቸውን በእግዚአብሔር ደረጃ ይኮፍሳሉና፡፡ እግዚአብሔር አለም-አለማትን (The entire universe) እንደፈጠረ አነበብንው እንጂ አላስተዋልንውም፡፡ ሳይንስ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ቢሊየን (ቁጥሩ ሳይንስ የሚለው እንጂ ትክክለኛው አይደለም) ዓመታት እንደተቆጠሩ ያምናል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብርሃናቸው በሰኮንድ 300000 ኪሎ ሜትር በደቂቃ 18 ሚሊዮን ኪሎሜትር፣ በሰዓት 1.08 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር፣ በዓመት 394.2 ቢሊዮን ኪሎሜትር (ከፀሐይ እስከ መሬት 8 ደቂቃ ብቻ ነው) እየነጎደ እስከዛሬም መሬት ያልደረሰ ብርሃን ያላቸው ከዋክብት ወይም ሌሎች ብርሃናዊ አካላት እንዳሉም ያምናል፡፡ እንግዲህ እግዚአበሔር የእነዚህ ሁሉ ርቀትና አለማት ፈጣሪ ነው! ለዛም ሳይሆን አይቀርም በእሱ ጥበብ የተመሰጡት ፈላስፋዎች የእግዚአብሔርን አኗኗር ለማውቅ የሚችል ምን አእምሮ፣ ምን ፍልስፍና፣ ምን ሐሳብ ነው የሚሉት!!! እግዚአብሔርን ይቅርና በእነዚህ ሁሉ ርቀትና አለማት እንኳን ምን እንዳለ ሳይንስ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የምድሩን እንኳን የሚያውቀው በጣም ኢምንት በሚባል ደረጃ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በሥራውና እሱ በፈቀደው የአካል መጠን ቢገለጥም ብዙ ጊዜ ለመቀበል አንችልም፡፡ በዚህ ምክንያት እንኳን ለሰማንው እራሳችን በአይናችን ላየንው ነገር ለመመስከር አይቻለንም፡፡ የዘመኑ ሚዲያዎችም አይደፍሩትም፡፡ በተቃራኒው ያለው ፍልስፍና ግን ወሬ ከተሰማ በቂ ነው፡፡ የአለም ዜና ማሰራጫዎች ሳይቀሩ ላልታየው በወሬ ብቻ ለተሰማው እንዲህ ያለው ፍልስፍና ቀዳሚ ዘጋቢ ለመሆን ከፍተኛ እሽቅድምድም ያደርጋሉ፡፡

    ReplyDelete
  2. በተመሳሳይ እኚህ በዘመናችን የተነሱት የእምነት ፈላስፋ መምህር ግርማ የቱንም ያህል የሚናገሩት ሰዎች እናምነዋለን የሚሉትን የክርስትና እምነት ፍልስፍና ቢሆንምና እሳቸው የሚናገሩት ነገር አንዳችም ስህተት እንደሌለበት ቢያውቁም ብዙዎች በተለይም ደግሞ የኦረቶዶክስ እምነት አስተምሮ እናውቃለን በሚሉ ሰዎች ከፍተኛ ፈተና እየገጠማቸው ላለፉት 20 ዓመታት በላይ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ግን ፍልሰፍናቸውን ፊት ለፊት ለማስተባበል የቻለ አንድም የቤተክርስቲያኗም ይሁን ከሌላ እምነት የሆነ ሰው ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ይልቁንም የኖረ ወግንና ባህልን ከእምነት የቀላቀሉ ስርአቶችን እንደ መቃወሚያ ስልት በመፍጠር በአሉባልታና በሰፈር ሀሜቶች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኙ መምህሩን የሚፈታተኗቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜም ጭራሽ ባልተፈጠሩ ባልተሰሙ የፈጠራ የውሸት ወሬዎችና ክሶች፡፡ እንደነዚህ ወሬዎች መምህሩ ብዙ ጊዜ ታስረዋል፣ ታግደዋል፣ ብዙም ጊዜም ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በመምህሩ አንዴም አልተፈጸሙም፡፡ አሁን በቅርቡ በግል ጥቅም ፍላጎት ሳቢያ በተፈጠረ መሰሪ ሴራ ያገለግሉበት ከነበረ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከሚገኘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን በጉልበተኞች፣ በዘመኑ የቤተክርስቲያኒቱ ባለስልጣኖችና አባሮቻቸው መታገዳቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ በይፋ ከመጻፉ ውጭ በሁሉም ደብሮች አገልግሎት ሲጅምሩም ተጋብዘው ነው ሲተውትም በራሳቸው ፍቃድ በአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ደስተኛ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በእስጢፋኖስም ከቀድሞው አስተዳዳሪ ጋር ጥሩ መግባባት ስለነበራቸው ጥሩ የአገልግሎት ሥርዓት (ከሕዝብ የሚሰበሰብን ገንዘብ በአግባቡ ለደብሩ በማስገባት ጨምሮ) ስለተመሠረተና ለሕዝብም ማዕከል ከመሆኑ ጋር ምቹ ቦታ ስለነበር እንጂ በኋላ በመጣው አስተዳደር ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በሕዝብ ግፊት እዛ ቆዩ እንጂ ብዙ ጊዜ ከዛ ቦታ ወደሌላ ሰላማዊ ደብር መሄድ እንዳለባቸው በጉባዔ ሳይቀር አስቀድመው ሲናገሩት የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡ ሆኖም ሕዝብና ብዙዎቹ የደብሩ ካህናት (ለደብሩ የእሳቸው ጉባዔ ወሳኝ ነበር) ሁኔታዎችን እንደሚያስተካክሉ ቃል ስለተገባላቸው ነበር እዛ የቆዩት፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ በጥቅም ያኮረፉት የደብሩ አስተዳዳሪና አባሮቻቸው አግደናል ብለው ጻፉ ለመምህሩም ጥሩ አጋጣሚ ሆነ ምንም እንኳን የደብሩ ካሕናትና (ደሞዝ ሳይቀር የሚከፈለው ከመምህሩ ጉባዔ ከሚገኝ ገቢ ነው) ሕዝብ (ማዕከል ነው) ቢጎዱም፡፡ ይህንን አጋጣሚ ግን ሌሎች ደብራት ጊዜ አልሰጡትም የመምህሩ ምርጫ ቀድሞም በየወሩ ሲያገልግሉበት የነበረው ምንም ሕዝብ የሌለው ልዩ ታሪክ እንዳለው የሚነገርለት የየርር ጽረሐአርያም ስላሴ ቢሆንም፡፡
    የመምህሩን ድንቅ የእምነት ፍልሰፍናና በተግባር የእግዚአበሔርን ኃይል የማሳየትና የእርኩሳን መናፍስትን ሴራ የማክሸፍ ሥራ ለሕዝብ ለማድረስ ብቸኛና ደፋር ሆኖ የተገኘው የብዙሃን ማሰራጫ አሜሪካን አገር የሚገኘው ንብረትነቱ አቶ አያልቅበት ተሾመ የሚባል ሰው የሆነው የአቢሲኒያ ሬድዩ ብቻ ነበር አሁንም ነው፡፡ የመምህሩን በልዩ ሴራ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መታገድ ለመዘገብ እንደ ታላቅ ምስራች የዛመቱት ሚዲያዎች ግን አጅግ ብዙ ነበሩ፡፡ ይባስ አሳፋሪነቱ ደግሞ አብዛኞቹ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ሚዲያዎች መሆናቸውና ባልታረሙና ለሕዝብ በማይመጥኑ በወረዱ ቃላቶች መዘገባቸው ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ የብዙዎችን ማንናት ያጋለጠ በመሆኑ ለሕዝብም ጠቅሟል፡፡ ሚዲያዎቹ ግን ራሳቸውን እንዴት እንደታዘቡ ቢነግሩን ጥሩ ነበር፡፡ ከሕዝብ የደረሳቸው ትችት ቢጠቀሙበት ጥሩ አስተማሪያቸው ነው፡፡ አጋጣሚው የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ሳይቀር እንዲፈተነበት የሆነ ነበር፡፡ ብዙዎቹም የሲኖዶሱ አባላት የመምህሩን ድንቅ ጥበብ በስብሰባቸው ሊመሰክሩ የተገደዱበት፡፡ አሁን የሚያገለግሉበት ደብር አስተዳዳሪ በስብሰባው ተካፍለው እጅግ የተደመሙበትና የተደሰቱበት፡፡ ጳጳሳቶቹ መምህሩን የሚመለከቷቸው እንደ ቤተክርስቲያኒቱ ብርቅዬ ልጅ እንጂ ሌሎች እንደሚያነሾካሹኩት ሀሜት እንዳልሆነ በግልጽ በስብሰባው ስለተነገራቸው፡፡ ምክነያቱም ከአንዳንድ ሰዎች ለምን ፈቀድህ የሚል የስልክ ጥሪ ይደርሳቸው ነበርና፡፡
    ከላይ እንደጠቆምኩት እንደነዚህ ያሉ ፍልስፍናዎች በመገናኛ ብዙሀን አይደፈሬ ከመሆናቸው አንጻር የአቢሲኒያ ሬድዮ በተቀዳሚነት ያሳየው መነሳሳትና ድፍረት አጅግ የሚያስደንቀው ነው፡፡ ሊያውም ሙሉ ወጭውን ራሱ ሬዲዎው ሸፍኖ የአየር ሰዓት ውድ በሆነበት አገር፡፡ ይህ ሬድዮ የመምህሩን ፍልስፍና (የሀይማኖት ትምህርት) ለአለም በማሰራጨቱ በየአህጉራቱ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማርኛ ቋንቋ አደማጮች (በየትኛውም እምነት ያሉ) የመምህሩን ትምህርት በመከታተል ከፍተኛ ጥቅም እዲያገኙ አድርጓል፡፡ በሬዲዮ የሰሙትንም በአካል ለማየትና ከአገልግሎቱም ተጠቃሚ ለመሆን ከየአህጉራቱ ወደ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ እየመጣ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የኢቢኤስ ቴልቪዥን ሁለተኛው በመሆን የመምህሩን ትምህርት ጅምሯል፡፡ ምንአልባትም በፊልም የተደገፉ ሌሎች ሥራዎች ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እነዚህ ሁለት ሚዲያዎች በዚህ ረገድ የታደሉ የሚያሰኛቸው ተግባር ለማከናወን ፊትአወራሪ ሆኑ ማለት ነው፡፡ ምን አልባት ከዚህ በኋላ ብዙ ሚዲያዎች መምህሩን ለማግኘት በር የሚያንኳኩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ልክ ዛሬ ብዙ ደብሮች እንደሚፈልጓቸው፡፡ ደብራቶቹ መምህሩን በአብዛኛው የሚፈልጓቸው የሚያስገኙላቸውን የገንዘብ ገቢ ታሳቢ አድርገው እንጂ እውንም የመምህሩን ልዩ ሀይማኖታዊ ፍልስፍና(ትምህርት)ና በተሰጣቸው ጸጋ ለሕዝብ የሚሰጡትን የፈውስ አገልግሎት አስበው አይመስልም፡፡ በመሆኑም መምህሩ ጥቂት በቅንነት ለጋበዟቸውና እግረመንገዱንም ችግር ላለባቸው ደብራት የበረከት ገንዘብ ለማሰባሰብ ካልሆነ ለብዙ ግብዣዎች ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፡፡

    ReplyDelete
  3. አሁን ላይ ሆኜ ሳስብ (ድሮ እንዲህ ለማሰብ እቸገር ነበርና) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው የሚለው ምክር ዘልማዳዊ አድርገንው በየግድግዳው፣ መኪናው ወይም በሚታይ ቦታ መለጠፉ ሳይሆን እውነትም ጥበብ እግዚአበሔርን ከማወቅ የምትመጣዋ ወደ መጨረሻ እውነት እንደምትወስድ አምኛለሁ፡፡ ግን እንዲህ ያለችውን ፍልስፍና ለማግኘት እጅግ የረቀቀ ማስተዋልን የሚጠየቅና ተራውን የአለም ፍልስፍና መናቅ የሚያስችል አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ለብዙዎች የእውነት መዳረሻዋ ፍልስፍና ሞኝነት ነችና፡፡ አስቀድሞ ለኖሕ፣ ከዚያም አብርሃም፣ ሙሴ፣ በልዓም (የሰባሰገሎቹ አባት)፣ ለኤልያስ፣ ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ፣ ሌሎች ነብያት፣ እያለ ከእንስቶች ለእናቱ ለድንግል ማርያምና ሌሎች፣ ለመቶ አለቃው (ቃል ተናገር ያለው)፣ ለዮሐንስ መጥምቅና ዮሐንስ የጌታ ወዳጅ (ወንጌላዊው)፣ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋሪያት፣ እያለ እስከዚ ዘመን ለደረሰቸው እግዚአብሔርን ለፈለጉት እየተሰጠች የምትገኝ ፍልስፍና ዛሬም አለች፡፡
    ይህች ፍልስፍና በአለማውያን ዘንድ ሞኝነት ተደርጋ በታሰበችበት ልክ የዓለምን ጥበብ ሁሉ ሞኝነትና መካን ለማድረግ የማይታጠፍ ክንድ አላት፡፡ ሁሉን ትመረምራለች ግን አሷ በማንም አትመረመርመ! ለዚያም ነው ያወቁ የመሰላቸው ግን ያላወቁ ሞኞች ሞኝነት የመሰለቻቸው፡፡ እሷ የዳህራዊ እውነትን (የእግዚአብሔርን ሥም) አርማዋ አድርጋለችና፡፡ የዳህራዊ እውነት ፍልስፍና በታሪክ ብዙም ስለማትገለጽ ለዘመናትና ለብዙ ትውልድ ሳትገለጥ በአለም የሞኝ ፍልስፍና እድል አግኝታ ለዘመናት ትውልድን ሞኝ አድርጋለች፡፡ ዛሬ እኛ እድለኞች ሆነን የዳህራዊ እውነት ፍልስፍና በእኚች ፈላስፋ ተገልጣ ብዙ ሞኝነቶቻችንን (ለእኛ ጥበብ የነበሩ) አጋልጣብናለች ወይም አጋልጣልናለች፡፡ አለም በደረሰበት ጥበብ እልባት ያላገኙ ደዌያት በቃል ብቻ በልዑል እግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ስም ልቀቅ እየተባሉ ሰዎች ሲፈወሱ፣ ውስብስብ የኑሮ ችግሮች አቁም እየተባሉ ወደ ተደላደለና የደስታ ሕይወት መመለስ፣ ብዙ ትክክል ነን ሲሉ የነበሩ ፍልስፍናዎችና እምነቶች እራሳቸው ሐሰተኞች ነን እንዲሉ የተገደዱበት፣ ችግሮቻችንና በአብዛኛው ጥበቦቻችንም በድብቅ የክፉ መናፍስት ሴራዎች ሰለባ እንደሆኑ በገሀድ አየን፡፡ አሁንም ማስተዋሉን ከሰጠን ብዙ ጥያቄዎች አእምሮአችን ይጠይቃል፡፡ ማወቃችን ሁሉ አለማወቅ፣ ጥበባችን ሁሉ ሞኝነት፣ አለን የምንለው ሁሉ መና ሊሆን አንደሚችል ታዘብን፡፡ ሳይንስም ይሁን ሌላ ጥበብ ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡ የዕውቀታችን ውሱንነት ተጋለጠ፡፡ በተለይ የስነ ሕይወቱ ሳይንስ አቅጣጫ ሁሉ እንደሳት ታዘብን፡፡ በአንዱ በመምህር ግርማ ወደ ብዙ የፈላስፎች የደረሰች እውቀት ጥያቄ ጫረች፡፡ ጥበባችንና እውቀታችንን ሁሉ ናደች፡፡ በአጠቃላይ አለማዊ ፍልስፍናዎችን ተገዳደረች፡፡
    አምላክ ሆይ አንተ ሁሉን ፈጠርህ፣ አለም-አለማትን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ! እኛን ደግሞ ማስተዋልንና ጥበብን ሊለብሱ ከሚችሉ ከከበሩ ፍጥራታቶችህ ወገን አደረግከን! እኛ ግን የአንተን የከበረ አባታችንን ስጦታ ትተን ውርደትን መረጥን (የአሳማ ምግብ ተመኘን)! ብዙ በድለናልና አቤቱ ይቅር በለን! ዳግምም ወደ ሰጠህን የክብር ጥበብ (ፍልስፍና) መልሰን! ሁሉን መምርመር የምታስችለንን ፍልስፍና እንከተላት ዘንድ አቤቱ አእምሮአችንን ክፈት!! አሜን!

    ReplyDelete
  4. Correction the part in above comment
    "ሳይንስ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ቢሊየን (ቁጥሩ ሳይንስ የሚለው እንጂ ትክክለኛው አይደለም) ዓመታት እንደተቆጠሩ ያምናል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብርሃናቸው በሰኮንድ 300000 ኪሎ ሜትር በደቂቃ 18 ሚሊዮን ኪሎሜትር፣ በሰዓት 1.08 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር፣ በዓመት 394.2 ቢሊዮን ኪሎሜትር (ከፀሐይ እስከ መሬት 8 ደቂቃ ብቻ ነው) እየነጎደ እስከዛሬም መሬት ያልደረሰ ብርሃን ያላቸው ከዋክብት ወይም ሌሎች ብርሃናዊ አካላት እንዳሉም ያምናል፡፡ሳይንስ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ቢሊየን (ቁጥሩ ሳይንስ የሚለው እንጂ ትክክለኛው አይደለም) ዓመታት እንደተቆጠሩ ያምናል፡፡" is corrected as below. It is not 394.4b Km per year instead it is computed to be 23,652 billion kilo meters per year (amazing!!!). Imagine the figure in billion years which science assumes to be the age of the earth!But forget what science says about the age of earth! The eight thousand years (as per religion) is already too much! Truly, less likely that earth can count over this 8K years!


    "ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብርሃናቸው በሰኮንድ 300000 ኪሎ ሜትር በደቂቃ 18 ሚሊዮን ኪሎሜትር፣ በሰዓት 1.08 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር፣ በቀን 64.8 ቢሊዮን ኪ.ሜ. እያለ በዓመት 23,652 ቢሊዮን ኪሎሜትር (ከፀሐይ እስከ መሬት 8 ደቂቃ ብቻ ነው) እየነጎደ እስከዛሬም መሬት ያልደረሰ ብርሃን ያላቸው ከዋክብት ወይም ሌሎች ብርሃናዊ አካላት እንዳሉም ያምናል"

    ReplyDelete