Wednesday, August 7, 2013

እነሱ እና እኛ! (ቴዲ - አትላንታ)

እነሱ እና እኛ!
(ቴዲ - አትላንታ)

መቼም የተሻለ እስክናይ ድረስ ያለንን ማድነቃችን የሚጠበቅ ነው። የተሻለ ስናይ ደግሞ የኛም እንደዚያ እንዲሻል ስለምንፈልግ፣ የተሻለውን ካልተሻለው እያነጻጸርን መፍትሄ መጠቆማችን እንዲሁ የሚጠበቅ ነው። ሁሉ ለበጎ ነውና በዚህ ሂሳብ መሰረት እስቲ ትንሽ እንጨዋወት።

ቢዮንሴ ኖውልስ የታወቀች አርቲስት ነች። በዓለም ላይ በዝናም ይሁን በሃብት፣ በውበትም ቢሆን ከሚጠሩ እንስት አርቲስቶች መካከል ከቁንጮዎቹ ተርታ የማትጠፋ ነች። በፌስ ቡክ ገጿ 48 ሚሊዮን የሚሆኑ ተከታዮች አሏት። ይህች አርቲስት በቅርቡ እዚህ አትላንታ አንድ የሙዚቃ ዝግጅት አቅርባ ነበር።

ዝግጅቱን ካየሁ በኋላ የመንጠራራት መብቴን በመጠቀም፣ የኛን ኮንሰርቶች በጥቂቱ ማነጻጸር ፈለግኩ። ጥሩ ፍርደኛ እንድሆን ያተኮርኩት ማስተካከል በምንችላቸው ነገሮች ላይ ብቻ እንጂ፣ የማንችላቸው ነገሮች ላይ አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ነገር አይወድልንም ያለው ማነው?! ከሰአት ማክበር ልጀምር።

ሰአት ማክበር
የቢዮንሴ ዝግጅት ልክ ከምሽቱ 2 ሰአት በኢትዮጵያ አቆጣጠር ( 8ፒ ኤም ውጭ አገር) ይጀመራል ተባለ። ልክ በሰአቱ የአዳራሹ የመግቢያ ሙዚቃ ጀምሮ ነበር። ከ 15 ሺ የማያንሰው ተመልካች ወደ አዳራሹ ሲገባ ፣ ኮሽታና ግርግር ፣ ሰልፍና ግፊያ አልነበረም። በቂ አስተናጋጆች፣ በቂ የመግቢያ በሮች ነበሩ። ሁሉም እንደደረጃው - እንደከፈለው መጠን - በተለያዩ በሮች ገባ - አለቀ። በተባለው ሰአት የመድረኩ ሙዚቃ ተለቀቀ። የቢዮንሴን የሙዚቃ ትርዒት የሚያሳዩ ፊልሞች በትልቅ እስክሪን በሙዚቃው ታጅበው ቀረቡ። እሷ ሳትታይ ፣ ያለች ያህል ስሜት ፈጠረ። ልክ 8፡ 30 ሲል ቢዮንሴ ወጣች። አወጣጧ ራሱ ትልቅ ዝግጅት የተደረገበትና ልብን ቀጥ እንዲያደርግ የተለፋበት እንደነበር ያስታወቃል። አጨራረሱ ራሱ ታሪክ ስላለው መጨረሻ ላይ አነሳዋለሁ።

የኛ ኮንሰርትና ሰአት
እዚህ አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ኮንሰርት ሲደረግ ከምሽቱ 4 ሰአት (10 ፒ ኤም) ይጀምራል ቢባል፣ ቢያንስ 3 ሰአታት ያህል መጠበቅ ግድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁለትና ሶስት ዘፋኞች እንኳን እያሉ ከሌሊቱ 7 ሰአት ( 1 ኤ ኤም) ካልሆነ በቀር ወደ መድረክ ብቅ አይሉም። በር ላይ ለመግባት ስልፍ ግዴታ ነው፣ አንዳንዴም አውቀው (ቢዚ ለመምሰል) ያስልፋሉ ይባላል። የገባውም ሰው ቆሞ ቆሞ ከደከመውና ኸረ ጀምሩ ብሎ ከጮኸ በኋላ ነው አርቲስቱ ብቅ የሚለው። በተባለው ሰአት መጀመርን መጠየቅ ቅንጦት አይደለም። አዳራሽ ገብተን ያለ ሥራ ሶስት ሰአት በመቆየት የምናባክነውን ጊዜ ማነው የሚከፍለን? .. .. ልቀጥል .. ከዚያ ዘፋኙ ይወጣል .. ሲወጣ በጣም ከጥቂቶች በቀር ዝም ብሎ መውጣት እንጂ ምንም አወጣጥን ማሳመር የለም። አወጣጤ እንዴት ቢሆን የበለጠ ይስባል? ብሎ የሚጨነቅ አርቲስት እስካሁን አልታየም።

ክፍያ
የቢዮንሴ ኮንስርት ክፍያ ከትንሽ እስከ ትልቅ - እንደደረጃው - የተለያየ ነው፣ ሰዉ በከፈለው ልክ መቀመጫም ሆነ መቆሚያ ያገኛል፣ በቂ የክፈለ አጠገቧ ይሆናል፣ .. በቂ ያልከፈለ ራቅ ብሎም ያያታል። ቁምነገሩ ክፍያው የታወቀና የማይለወጥ ነው - ትኬቱም መሸጥ የሚጀመረው ገና ዝግጅቱ 3 እና 4 ወር ሲቀረው ነው።

የኛ ክፍያ
እኛጋ ክፍያ እንደ አዲስ አበባ አየር በየደቂቃው ይለዋወጣል። ቀድሞ 40 ዶላር ይባልና፣ በሩ ላይ ሰልፍ በዛ ሲል .. 60 ሆኗል ይባላል ..፣ ቀድሞ የሚገዛ 30 ዶላር ነው ይባልና፣ በብዛት ሰው ቀድሞ መግዛት ሲጀምር፣ ትኬት ይነሳና አልቋል ይባላል.. [በር ላይ በበለጠ ዋጋ ለመሸጥ መሆኑ ነው) .. ... አንዱ አዘጋጅ በሩ ላይ 40 ዶላር እየተቀበለ ሲያስገባ፣ በሌላው በር 50 ካልሆነ አትገቡም የሚል አለ ...፣ በር ላይ ያለው ክርክር ሌላ ነው። ዋጋው 30ም ይሁን 100 .. ቀድሞ ማሳወቅ ይገባል። ዘፋኝ በመጣ ቁጥር የሚመጣው ተመሳሳይ ሰው ሆኖ ሳለ፣ ልክ በአንድ ቀን እንጨርሰው አይነት ስሜት ትክክል አይደለም። ካስፈለገ እኮ ሰው ለከፈለው ነገር ደረሰኝ መጠየቅም ይችላል። መስጠት ደግሞ - በህጉ ግዴታ ነው። ያ ማለት የሚታተመው የመግቢያ ትኬት ላይ ዋጋው በትክክል መጻፍ አለበት ማለት ነው። ካስፈለገ ደግሞ የተለያየ አይነት ደረጃ ያለው ዋጋ መተመን ሌላው አማራጭ ነው።

የጊዜ አጠቃቀም
ቢዮንሴ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ( 8ፒ ኤም) ሙዚቃዋን መጀመሯ ዕድሜያቸው ከ 18 በታች ግን ከ 13 በላይ የሆኑ አድናቂዎቿ ወጣቶች እንዲገቡ ከማስቻሉም በላይ በጊዜ መጀመሩ በጊዜ ኮንስርቱ እንዲያልቅ አድርጓል። 8 ጀመረች፣ 11፡45 (ለ እክለ ሌሊት ሩብ ጉዳይ) ጨረሰች። በማግስቱ ሥራ ያለው፣ ከመሸ በኋላም ሌላ ቦታ መሄድ ያለበት፣ ሌላው ቀርቶ የሌሊት ሥራ ያለበት እንኳን ቢሄድ ይደርሳል - ምንም የባከነ ጊዜ የለም።

የኛ ጊዜ አጠቃቀም
በኛ ኮንስርት ከ እኩለ ሌሊት በኋላ ይጀመራል። መጀመሪያ ነገር የኛ ኮንሰርት ያው "አዳር" እንደሆነ ስለሚታወቅ፣ ሰዉ ቀን ይተኛል ...፣ ከዚያ ሌሊቱን ሙሉ እዚያው አድሮ ሊነጋ ሲል ቤቱ ይሄዳል፣ ከዚያ እንደገና ቀኑን ይተኛል - ስለዚህ ለአንድ ኮንሰርት ሁለት ቀንና አንድ ሌሊት ባከነ ማለት ነው። አሁንም .. በጊዜ ጀምሮ ፣ በጊዜ መጨረስን መጠየቅ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም - ማድረግ የሚቻል እንጂ። ቀን ብናደርገው ማን ይመጣል? የሚሉ አሉ .. መች ተሞክረ? ነው መልሱ።

እረፍት የለም
ቢዮንሴ መድረክ ላይ ለ 3 ሰአት ተኩል ያህል ስትጫወት እረፍት የሚባል ነገር አልወሰደችም። ገንዘቡን ለከፈለው ሰው ክብርና ዋጋ ስለሰጠች ያለማቋረጥ ነበር የተጫወተችው .. መድረክ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች የማትታየው ልብሷን ለመቀየር ስትገባ ብቻ ነው .. እሱም ከ 3 ደቂቃ አይበልጥም - እሱም ቢሆን ዳንሰኞቿ ዳንሳቸውን፣ ሙዚቀኞቹም ሙዚቃቸውን ሳያቆሙ ነው። በየት ገብታ በየት እንደወጣች ሳይታወቅ ልብሷን ቀይራ መድረክ ላይ ነች። "የዲጄ እረፍት" የሚባል ነገር የለም። የከፈልነው እሷን ለማየት ነው - ለገንዘባችን ዋጋ ሰጥታለች - እሷንም ያለረፍት አይተናታል።

የኛ እረፍት
አንድ ዘፋኝን ተዉትና ሁለትና ሶስት ዘፋኝ እንኳን ኖሮ፣ ለዚያውም ከ እኩለ ሌሊት በኋላ ዘፈኑ ተጀምሮ ፣ በየ 4 ዘፈኑ "ትንሽ ልረፍ" የሚለን አርቲስት ብዙ ነው። እንዲያውም ዘፋኙ ከሚጫወተው በላይ የዲጄው ሙዚቃ ቢቆጠር ይበልጣል። የከፈልነው ለዘፋኙ ነው ለዲጄው? የሚያሰኝ ነው። ሰዉ የከፈለው እኔን ለማየት ነው፣ ስለዚህ ላስደስተው ብሎ የሚያስብ አርቲስት እንፈልጋለን። እንዲያውም [ዲጄዎች ቅር እንዳይላችሁ እንጂ] ዲጄ መኖርም የለበትም። አንዳንዱ ኮንስርት የአርቲስቱ ነው ወይስ የዲጄ ኮንስርት? ያሰኛል እኮ! ረጅም ሰአት በመዝፈን ቢያንስ መሃሙድ አህመድን አደንቃለሁ - ሌሎቹማ በየ 20 ደቂቃው የ 20 ደቂቃ እረፍት ሲወስዱ ምንም ቅር አይላቸውም። በሰአት 7 ዶላር የሚከፈለው ሰው የሙሉ ቀን ክፍያውን ከፍሎ እንደገባ የሚያውቁ አይመስለኝም። ቢዮንሴ ሶስት ሰአት ያለማቋረጥ ከዘፈነች የኛ አርቲስቶች ምን ያቅታቸዋል? እንደሷ ስፖርት መስራት፣ ራስን መጠበቅ .. "ምናምኑን" መቀነስ ነው ... ለታዳሚው ክብር ሊሰጡ ግድ ነው። ይህም ጥያቄ ሊሆን የሚችል እንጂ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም።

ማይክራፎንና ሳውንድ
ቢዮንሴ መድረኩ ተከፍቶ ብቅ ብላ "ሃሎ አትላንታ" ካለችበት ሰአት አንስቶ ፣ "ቀስ እያላችሁ ንዱ፣ መልካም መንገድ እወዳችኋለሁ" ብላ እስከተሰናበትችበት ደቂቃ ድረስ ጥርት ያለ ሙዚቃ፣ ቅልብጭ ያለ ድምጽ ነበር። ሁሉ ነገር ቀድሞ ሰው ሳይመጣ በፊት ምናልባትም ከአንድ ቀን በፊት ተስተካከሎና ተመጥኖ የተዘጋጀ ነበር። መጋረጃው ተከፈተ፣ ቀጥታ እሷና ባንዷ ሙዚቃ ጀመሩ .. ጨረሱ - በቃ!

የኛ ማይክራፎንና ሳውንድ
እኛ ጋ ስንመጣ ገና ሲጀመር "ሙከራ አንድ ሁለት ሶስት" የማይቀር ነው። አንዳንዴማ በሚያሳፍር መልክ እዚያው መድረክ ላይ ዘፋኙና ሳውንድ ማኑ ይከራከራሉ፣ ጊታሪስቱ ጊታሩን የሚሞክረው እዚያው ነው፣ ሰው 40 እና 50 ዶላር ከፍሎ ፣ ሁለትና ሶስት ሰአት ቆሞ ጠብቆ ገና ማይክራፎን ላዩ ላይ ነው የሚሞከረው። ይህ በቀላል ቋንቋ ንቀት ነው። አንድ አርቲስት እንዴት በራሱ ዝግጅት ላይ ቀድሞ መጥቶ ሁሉ ነገር መስተካከሉን አያረጋግጥም? አንዳንዶቹ ለስሙ ሳውንድ ለመሞከር ብለው ከዝግጅቱ በፊት ይመጣሉ፣ ምኑን እንደሚሞክሩት ግን አይታወቅም በኋላ ላይ ሰው ፊት በመብራቱና በድምጹ "ሲበሳጩና ችግርም ሲኖር በሳውንድ ማኑ" ሲያላክኩ ይታያሉ። የሚገርመው አንዳንዶቹ አርቲስቶች ሳውንድ ለመሞከር ሌላ ሁለተኛ ዘፋኝ ወይም ከባንዱ ተጫዋቾች እንዱን ነው የሚልኩት ይባላል። "የኔ ሾው ነው" ብሎ መጨነቅ አይታይባቸውም። ታዳሚ ቆሞ እየጠበቀ፣ እንዴት ሰው ላይ ማይክራፎን ይሞከራል? .. ቀድማችሁ በጊዜ ሁሉን ሞክሩ፣ እኛን አክብሩን.. ከመሬት የተገኘ ገንዘብ አይደለም የምንክፈለው ብንል ይህም የቅንጦት ጥያቄ አይደለም - ሊሆን የሚችል እንጂ!

ሙዚቃ ፣ መብራትና አለባበስ
የቢዮንሴ ሾው ራሱ ፊልም ነበር ማለት ይችላል። ለአድናቂዎቿ ክብር ከመስጠቷ የተነሳ ለዚያ የሶስት ሰአት ዝግጅት ራሱን የቻለ ሳውንድ ትራክ - ለዚያውም በፊልም የታጀበ - ቀድሞ ተዘጋጅቶለት ነበር።፡ በያንዳንዱ ዘፈን ላይ በደቂቃ ውስጥ ቀይራ የምትወጣው ልብስ ከያንዳንዱ ዘፈን ጋር አብሮ የሚሄድ ነበር። ምናልባት ለአንድ ኮንሰርት አራት ሻንጣ ልብስ ሳትይዝም አልቀረችም። ስለዚህ ሙዚቃው የተለየ ውበት ነበረው። ያን ያደረገችው ለዝግጅቷ ከመጨነቋ የተነሳ ነው። ይህች በመላው ዓለም የተደነቀች አርቲስት "ታዋቂ ነኝ" ብላ አትኮፈስም፣ እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ሰዉን ለማስደስት የታለመ ነው። ስትደንስና ስትዘል በፍጹም ጉልበቷን አትቆጥብም። ስለዚህ ሶስት ሰአት ተኩሉ ጊዜ ምንም ሳይታወቅ ሰው በጥፍሩ እንደቆመ አለቀ።

የኛ አለባበስና አቀራረብ
የኛ አርቲስቶች የትም ከተማ፣ የትም መድረክ ላይ ቢሄዱ ያው አንድ ናቸው፣ ለዚያ ሾው፣ ለዚያች ቀን ብለው የሚዘጋጁበት የተለየ ነገር የለም። ከጥቂቶች በቀር ለአለባበሱ የሚጨነቅም የለም። አንድ ስታይል ካለ በቃ በዚያችው ይነጋል። አንዳንዴ በፒጃማ ይሁን በተቀደደ ጂንስ፣ በቲሸርትና በቱታ ... ወጥተው የሚዘፍኑም አሉ - [ስም እንጥራ እንዴ?] .. ይቅር .................. ግን ሰው ሰርግ ቤት እንኳን ሲሄድ ለሙሽሮች ክብር ይዘንጣል - ለቦታው የሚሆን ልብስ ይልብሳል። የኛ አርቲስቶች - ከጥቂቶች በቀር - ግድም የላቸው። ከ 10 እስከ 20ሺ ዶላር ይዘው ለሚሄዱበት ኮንሰርት ፣ ያንንም ለሚከፍላቸው ታዳሚ ቢጨንቁ ምን አለበት? በሙዚቃው ተመስጠው እኛንም ቢመስጡን፣ ለኛ እንደተጨነቁልን እንዲሰማን እንዲያደርጉ መጠየቅ .. ይህም የቅንጦት ጥያቄ አይደለም- ሊሆን የሚችል እንጂ።

ቅደም ተከትልና አጨራረስ
ቢዮንሴ ኖውልስ የሙዚቃዎቿ ቅደም ተከተል ቀድሞ በጥናት የተዘጋጀና የታወቀ ነው። እነዚያን ሰአታት እንደ እምቦሳ እየዘለለች ስትደንስና ስትዘፍን . አንዴም ወደ ሙዚቀኞቿ ዞር ብላ እንኳን አላየችም። እነሱም ሥራቸውን ያውቃሉ፣ እሷም ታውቃለች - ተግባብተዋል። ትኩረቷ ታዳሚው ላይ ስለሆነ ሰዉም ትኩረቱ እሷና ሙዚቃው ላይ ነው። ስሜት የሚሰርቅ ባዕድ ነገር የለም። አጨራረሷም ለየት ያለ በልዩ የሙዚቃ ቅንብርና መብራት የታጀበ፣ ምስጋናና ሙገሳ ያለበት፣ ልብ የሚያንጠለጥል አጨራረስ ነበር። ሁሉን አመስግና ፣ ሰዉ ቀስ ብሎ እንዲነዳ ነገራ፣ በሰላም እንድንገባ ምኞቷን ገልጻ (ንግግሯ ሁሉ በልዩ ሙዚቃ የታጀበ ነበር) ተሰናበተች።

የኛስ ሙዚቃ አካሄድ?
እኛ ጋ ስንመጣ፣ አርቲስቱ አንድ ዘፈን ዘፍኖ ፣ ሁለተኛው ገና ዞሮ ከባንዱ ጋር አውርቶ ነው የሚወስነው፣ እንዲያውም ጀምሩ ሁሉ ብሎ አስጀምሮ ነው ወደ ሰዉ የሚዞረው፣ ይህ በጣም አሳፋሪ ነው፣ ለሰው ጀርባ አይሰጥም። ሙዚቃ የሚመረጠውም መድረክ ላይ አይደለም። ይህ ቀድሞ አለመዘጋጀትን ነው የሚያሳየው። አንዳንዶቹማ (ታዋቂ የሚባሉት ጭምር) ሙዚቃው ተጀምሮ ሁሉ ያስቆማሉ. . እና "ልክ አይደለም - እንደገና" ሲሉ እዚያው ለባንዱ ትዛዝ ይሰጣሉ። አሳፋሪ ነው። እንኳን የተከፈለበት፣ የነጻ ዝግጅት እንኳን "ዝግጅት" ያስፈልገዋል። በአንድ ኮንሰርት ላይ ስንት ዘፈን፣ የትኛው ዘፈን እንደሚዘፈን ቀድሞ መዘጋጀት ምን ያቅታል? ለታዳሚው ክብር ከተሰጠ ይህ ቀላል ነው። .. እንደዚያም ሆኖ ዝግጅቱ የሆነ ሰአት ላይ አለቀ ይባላል ..፣ አንዳንዱ አርቲስት ደህና እደሩ ይላል .. አንዳንዱ ደግሞ እየዘፈነ በዚያው ወደውስጥ ይገባል እዚያው ይቀራል.. ሌላው ደግሞ "ትንሽ እረፍት" ብሎ ሄዶ በዚያው ይቀራል. .. የፈረደበት ዲጄ ይጨርሰዋል። ቀድማችሁ የምትዘፍኑትን አውቃችሁ ፣ ባንዱም አውቆና ተራ አስይዞ እንዲመጣ አድርጉ፣ አስሬ ጀርባችሁ እየሰጣችሁን ፣ ምን እንዝፈን እያላችሁ አትመካከሩብን ብንል ይህም የቅንጦት ጥያቄ አይደለም . በቀላሉ የሚሆን እንጂ።

ተጨማሪና ማጠቃለያ
በቢዮንሴ ኮንስርት አዳራሹ ውስጥ 15ሺ ያህል ሰው ሲኖር መጠጥ የሚሸጠው ከአዳራሹ ውጭ ነበር፣ እናም ሁሉም ያቅሙን (ሳያበዛ) ቀምሶ ይገባል፣ ሺሻ ወይም ሲጋራ የሚባል ጭስ አይፈቀድም። የፈለገ ውጭ ማጨስ ይችላል። ስለዚህ ያለ ጭስ ሽታ የተረጋጋ ግን ደስ የሚል ኮንስርት ነበር። በጊዜ የሚያልቅ መሆኑ በራሱ ሰው ለተጨማሪ መዝናናት (መጠጣትም ቢፈልግ) ስለሚችል ስክሮ የሚጋፋ .. ካልሰከርኩ መደነስ አፍራለሁ የሚል ሰው አልነበረም። እኛ ጋ ስንመጣ መድረኩና የመጠጥ መሸጫው ምንም ያህል አይራራቅም፣ አንዳንዱም (አሁን ወደኛ ስመጣ) ካልሰከረ (ች) መደነስ የሚችሉ የማይመስላቸው ብዙ አሉ። ስለዚህ በሙዚቃ መካከል ስክሮ የሚጋፋ፣ ሴቱን የሚጎትት .. በሞቅታ መድረክ ላይ ካልወጣሁ የምትል ...አሉ። አሁን አሁን ሺሻ የሌለበት ማምሻም ሆነ ኮንስርት እንዳይኖር የተባለ ይመስል፣ የሚያጨስም የማያጨስም በጭስ መታፈኑ ግድ ነው። ለመጨፈር ለኮንስርት የመጣ ሰው ቁጭ ብሎ ሺሻ የሚያጨስበት ምክንያት በግሌ አይገባኝም። አርቲስት ያለበት ኮንስርትና የዲጄ ኮንስርት የተደባለቀብን ይመስለኛል። ስለዚህ ጭስ የማይፈልጉ ሰዎች ከአበሻው ኮንስርት እያዘኑ ተሰናብተዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው አዘጋጆቹ በር ላይ ከሚገኘው በተጨማሪ በሺሻውም በመጠጡም ገንዘብ ማግኘት ስለሚፈልጉ ነው።

አንድ ምክር - ለዚህ ለዚህ እኮ .. የሙዚቃ ዝግጅቱ በጊዜ (እንደ ቢዮንሴ ሾው) ቢጀመር - በነገራችን ላይ አብዛኛው የአሜሪካውያን ትላልቅ ኮንስርት በጊዜ ተጀምሮ እኩለ ሌሊት ላይ የሚያበቃ ነው - ሰዉ በሙዚቃው ተደስቶ እኩለ ሌሊት ላይ ሲያልቅ፣ እዚያው በዲጄ መጠጡንም ጭሱንም ማስኬድ ይቻላል ... ያኔ የማይፈልገው ይሄዳል .. ሌላውም በነጻነት ይቆያል። ሁለት ዓይነት ገቢ ተገኘም ማለት ነው። የሚጨስ ነገር ከሌለና በጊዜ ከተጀመረ ሰው ከነወጣት ልጆቹ ፣ እቤት ያሉ ካገር ቤት የመጡ አባትና እናትን ጭምር ይዞ ሊመጣ ይችላል። ታዳሚው ይበዛል ማለት ነው። በማግስቱ ግዴታ ሥራ መግባት ያለበትም ሰው እንዲሁ በጊዜ ስለሆነ ይመጣል .. ጥቅሙ ብዙ ነውና ይታሰብበት።

ስለዚህ .. የባሰ አታምጣ እያልን ወደታች ሳይሆን የተሻለ አምጣ እያልን ወደላይ ልናይ ያስፈልጋል። ለኛ ኮንስርት የሚከፈለው ለቢዮንሴም ሾው የሚከፈለው ነው። እኛ ክብርና ጥሩ ነገር ፣ ጥራትና ንጹህ የሆነ ነገር፣ የተጠና እና የተቀናጀ ነገር አይወድልንም ያለው ማነው? በርግጥ ይወድልናል - ማግኘትም መብታችን ነው። ሁላችሁም ይህን ነገር ለምታውቋቸው ብታስተላለፉ ጥሩ ነው። የተሻለ ማግኘት እየቻልን በትንሽ ነገር የምንቀረው ስለማንናገር ነው። ቢዮንሴ ኖውልስ ያን ሁሉ አድናቂ ያፈራችው በ ዕድል አይደለም - እንዲህ ተጨንቃ ለፍታና አክብራ ነው።

"Don't settle for less, when you can get more" ይላሉ ፈረንጆች።
source...www.facebook.com/dinqmagazine

No comments:

Post a Comment