Saturday, August 17, 2013

ስለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ምን ይላሉ? (ዳዊት ከበደ ወየሳ – ከአትላንታ)

ስለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ምን ይላሉ? (ዳዊት ከበደ ወየሳ – ከአትላንታ)

EMF – ሰሞኑን በግብጽ አገር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ በቲቪ መስኮት እናያለን፤ ወሬውንም እንሰማለን። በግብጽ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል ማለት ትልቅ ሙዚየምን ማቃጠል እንደማለት ነው። አንዳንዶች ግን ይህን እውነት ዘንግተው በሌላ እምነት ተከታዮች ላይ ባላቸው ጥላቻ ብቻ በመነሳት ታሪካቸውን በአሳፋሪ መንገድ በ እሳት በመጻፍ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ታሪክ ከግብጽ ታሪክ ጋር የሚያመሳስለው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውውም ጭምር ሊሆን ይችላል። የቃጠሎው ዜና ከማሳዘን አልፎ፤ ወደፊት በኢትዮጵያ የማይከሰት ስለመሆኑ መቶ በመቶ ህዝቡ የሚተማመንበት ዋስትና የለውም። ይህን ዋስትና በመጠኑም ቢሆን አለማግኘት ደግሞ መጪውን ግዜ በፍርሃት፤ ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ በጥርጣሬ ቀለበት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል።
በግብጽ የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ
በግብጽ የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዮዲት ይሁዲት ተነስታ ቤተ ክርስቲያን አቃጥላለች። ግራኝ አህመድ ብዙ ጥፋት ሰርቷል። አጼ ቶሃንስም ነግሰው ብዙ ሙስሊም በግድ አጥምቀዋል። በሃይማኖት ምክንያት እዚህም እዚያም የደም መፋሰስ ተከስቷል። ወዳለንበት ዘመን ስንመጣ ደግሞ፤ በምኒልክ ዘመን እስላም እና ክርስቲያን በአንድ ገበታ መብላት ብቻ ሳይሆን፤ ተጋብቶና ወልዶ አብሮ መኖር ጀምሯል። ቤተ ክርስቲያን ሲሰራ ሙስሊሙ ገንዘብ ከማዋጣት ጀምሮ የመሰረት ድንጋዩን ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር አብሮ ጥሏል። በክፉም ሆነ በደግ ዘመን “አገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት የግል ነው” የሚለውን የንጉሠ ነገሥቱን ቃል ይዞ ዘመን ተሻግሯል። ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው።
በአገራችንም ቢሆን ከጥቂት አመታት በፊት “አላህ ኩበር” እየተባለ ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል፤ የሃይማኖት አባቶች ተገድለዋል። ይህ ደግሞ በቪዲዮ ተቀርጾ አሁንም online የሚታይ እውነት ነው። ሆኖም የትኛውም ሃይማኖት ከህንጻውና ከሰዎች በላይ በመሆኑ፤ ህንሳው ቢቃጠልን ወይም ጥቂት ሰዎች ቢሞቱ፤ ሃይማኖቱ እንደሃይማኖት ተጠናክሮ ይቀጥላል። በመሆኑም መስጊድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ቢቃጠል የእምነቱ ተከታዮች አምላካቸውን ማምለካቸው አይቀሬ ነው። በዚህ የማይናወጥ መሰረተ ሃሳብ ላይ መስማማት ከቻልን፤ ማንም የማንንም ህንጻ ለማቃጠል እሳት አይለኩስም። በማቃጠል እና በመገዳደል ቢሆን ኖሮ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለቱም ሃይማኖት አለመስፋፋት ብቻ ሳይሆን፤ የደም መፋሰሱም በሰፊው በተከሰተ ነበር – ይህ ግን አልሆነም። የሃይማኖት ደም መፋሰስ አለመኖሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ጨዋነት፤ ብሎም የሃይማኖት መሪዎቹን አስተዋይነት ያሳያል።
coptic 4
አሁን ላይ ሆነን ያለፈውን ታሪክ የምናነሳው፤ ያለፈ ጥፋታችንን እንዳንደግም ነው። ካለፈው ጥፋታችን የምንማረው አንድ ቁም ነገር ቢኖር… ኢትዮጵያ ውስጥ ህንጻን በማቃጠል፤ ማንም የማንንም ሃይማኖት አለማጥፋቱን ነው። ከዚህ መሰረታዊ እውነታ በመነሳት ወደፊት በፍቅር እንጂ፤ በጸብ የማንኖርባትን ኢትዮጵያ፤ በመከባበር መገንባት ይኖርብናል። ከአንድ አመት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚያነሱት ጥያቄም የመብት ጥያቄ መሆኑን አብላጫው ህዝብ ያምንበታል። በእስር ቤት ከሚገኙት የኮሚቴ አባላት መካከል አንደኛው ሲናገር፤ “እኛ እኮ በምርጫውም ጊዜ ኢህአዴግን እንጂ ቅንጅትን አልመረጥንም” ቢልም እንኳን የቅንጅት ደጋፊ የነበሩ ሰዎች አላዘኑበትም፤ “የኢህአዴግ ደጋፊ ነኝ” ስላለም ኢህአዴግ አላዘነለትም – ትላንት ቅንጅቶች እና ጋዜጠኞች የታሰሩበት ቃሊቲ በሩን ከፍቶ ሁሉንም አስተናግዷል። ነገ ማን እንደሚስተናገድበት የሚያውቀው ግን አንድ አምላክ ነው። እናም እንዲህ ጊዜ እና ሁኔታ በሚፈራረቁበት ዘመን ላይ ሆነን፤ ከነልዩነታችንም ቢሆን፤ ቢያንስ ለሰው ልጆች መብት በእኩል መንፈስ ልንቆም ይገባል።
የሃሳብ እና የሃይማኖት ልዩነት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን የሰው ልጅ መብት ሲረገጥ “እሰይ ደግ አደረገ!” የሚል ሰይጣናዊ መንፈስ በውስጣችን ሊኖር አይገባም። ለዚህም ነው… ሙስሊም ወገኖች ሲታሰሩ እና ሲደበደቡ ሌላው ክርስቲያን ወገናቸው ድምጹን ደግሞ ደጋግሞ ሲያሰማ የነበረው። አንዳንዴ የክርስቲያኑም ሆነ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ጩኸት የሚሰማ እስከማይመስል ደረጃ ላይ ቢደረስም እንኳን፤ ኢህአዴግ እያደረሰ ያለውን የግፍ ተግባር ሁሉም ወገን እያወገዘው ይገኛል። የሰብአዊ መብት ረገጣን ማውገዝ ደግሞ ከአንድ የሰለጠነ ህዝብ የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን ግፍ የምናወግዘው ውለታ ለመቆጣጠር ሳይሆን፤ የሰለጠነ ህሊናችን ስለሚያስገድደን ነው።
ስለግብጽ ክርስቲያኖች በደል እና ለቅሶ ሙስሊሙም ድምጹን ቢያሰማ፤ ነገ እንዲህ ያለው ነገር በአገራችን እንደማይደገም ዋስትና ይሰጣል
ስለግብጽ ክርስቲያኖች በደል እና ለቅሶ ሙስሊሙም ድምጹን ቢያሰማ፤ ነገ እንዲህ ያለው ነገር በአገራችን እንደማይደገም ዋስትና ይሰጣል
ሆኖም አንድ ነገር ያሳስበናል። ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌላው ወገን ከሙስሊም ወንድሞቹ ጎን መቆሙን ደግሞ ደጋግሞ አረጋግጧል። ድምጹንም አሰምቷል። ይህ ድምጽ ግን ከጥቂት ሙስሊም ወገኖች በቀር ሌላው ዘንድ ዘልቆ መግባቱ ያጠራጥራል። ይህንን ለማለት ያነሳሳን ደግሞ ከቢላል ሚዲያ ጀምሮ እስከ ድምጻችን ይሰማ ድረስ የሚገኙ አካላት፤ ሌላው ወገን እያደረገ ያለውን ድጋፍ በሚዲያቸው ሲያቀርቡት ወይም በመልካም ምሳሌነት ሲያወድሱት አይታይም። በዚህ ምክንያት የኛ ድምጽ መሰማቱን እንድንጠራጠር ያደርገናል። አንዳንድ ግዜ ፍቅር እና መተሳሰቡ ከአንድ ወገን ብቻ መምጣት የለበትም። ሌላውም ወገን የተሰጠውን ፍቅር እና ድጋፍ ተቀብሎ ዝም ማለት ሳይሆን፤ ቢያንስ “አመሰግናለሁ” ማለት አለበት። ይህ ሲሆን ነው፤ የምንሰጠው ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱን የምናውቀው። አሁን ግን አንደኛው ወገን ለፍቅር ሲጮህ፤ ሌላኛው ወገን በዝምታ እየተመለከተ ይመስላልና እኛም “ድምጻችን ይሰማ” የሚል ኮሚቴ አቋቁመን፤ ድምጻችን እንዲሰማ ለሙስሊም ወገኖቻችን በየጊዜው መጮህ ሊኖርብን ነው።
አንድ ነገር ልቸምር። ፍቅርም ሆነ መደጋገፍ ከሁለቱም ወገን ሲሆን መልካም ነው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁኔታ፤ የታሰሩት ኮሚቴዎች ከተፈቱ የትግላቸው መቸረሻ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ። ሆኖም ጥያቄው ከኮሚቴዎቹ መፈታት በላይ መሆን ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብታቸው ተገፎ የታሰሩት ኮሚቴዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ፤ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞቻችን ጭምር መሆናቸውን ልናስታውስ ይገባል። ትላንት እስክንድር ነጋ ሲታሰር ሙስሊሙም ክርስቲያኑም “ሰብአዊ መብት ይከበር! እስንድር ነጋ አሸባሪ አይደለም!” ብሎ ቢነሳ ኖሮ፤ ኢህ አዴግ የልብ ልብ አግኝቶ የሙስሊሙን ኮሚቴ አባላት አያስርም ነበር። ዛሬ ኮሚቴዎቹም እነእስክንድርም አንድ እስር ቤት ናቸው። አሳሪዎቻችንም ተባብረውብናል። እኛ ከዚያ ውጪ ያለን ሰዎች ስለ ሃይማኖታችን ብቻ ሳይሆን፤ አምላክ ስለሰጠን የሰብአዊ መብት ጭምር በጋራ ልንቆም ይገባናል።
ይህም አለ። በዚህ ፎቶ ላይ በግብጽ የሚገኙ ሙስሊሞች እጅ ለ እጅ ተያይዘው ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ሙስሊሞች እንዳይቃጠል ሲከላከሉ ይታያል
ይህም አለ። በዚህ ፎቶ ላይ በግብጽ የሚገኙ ሙስሊሞች እጅ ለ እጅ ተያይዘው ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ሙስሊሞች እንዳይቃጠል ሲከላከሉ ይታያል
ወደማጠቃለያችን እናምራ። የትላንት ክፉና ደግ ታሪካችን በአንድነት እንድንጸና እንጂ እንድንለያይ አያደርገንም። በአንድነት ሆነን የምንጮኸው ድምጽ ተመሳሳይ ቃና ሊኖረው ይገባል። ለአንድ ወገን ብቻ መጮኻችን በቂ አይደለም። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም ለነእስክንድር ነጋም መጮህ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን፤ ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ ግፍ እና በደል ሲደርስ ለነሱም መጮህ ያስፈልጋል። በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል እና ክርስቲያኖች ሲገደሉ ዝም ማለት ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቃጠሎውን በደስታ ይቀበሉት ወይም በሃዘን ማወቅ የሚቻለው፤ ሙስሊሙን የሚወክሉ ወገኖች ወጥተው መናገር ሲጀምሩ ነው። የቢላል ሚዲያም ሆነ ድምጻችን ይሰማ ወይም ሌሎች የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎች፤ እስካሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ቢያቀርቡ፤ ነገ የበለጠ ስራ መስራት ይቻላል። ይህ ብቻ አይደለም – ዛሬ ግብጽ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ሙስሊም ወገኖቻችን ሲያወግዙ ካልሰማናቸው፤ ነገን መፍራት እንጀምራለን። መተሳሰባችን የእውነት ስለመሆኑ፤ የቃላት ጩኸት ብቻ እንዳልሆነ ለማወቅ ብዙዎች ይጓጓሉ። ስለዚህ የሙስሊሙ መሪዎች ድምጻችን ይሰማችሁ – የናንተንም ድምጽ እንስማ – ወቅታዊ መልእክታችን ነው!!

No comments:

Post a Comment