Wednesday, August 21, 2013

ደብዳቤ ከመለስ ዜናዊ (ይድረስ ለጓድ ጠቅላይ ሚንስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ)

ደብዳቤ ከመለስ ዜናዊ (ይድረስ ለጓድ ጠቅላይ ሚንስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ)

f44997cb312b542bbd55c895274ee230_XL220px-Meles_Zenawi_-_World_Economic_Forum_Annual_Meeting_2012
ካለሁበት ቦታ ጓዳዊ ሰላምታየ ይድረስህ። ከመጣሁ ጀምሮ ደብዳቤ ልጽፍልህ አስቤ ሳይሳካልኝ ስለቀረ እስከአሁን ቆየሁ። እዚህ ከመጣሁ ብዙ ነገር አጋጥሞኛል። በየጊዜው ብዙ ሰወች ስለሚመጡ፣ ስለናንተ ብዙ ነገር ይደርሰኛል።
እኔ ያለሁበት ቦታ በጣም የተለየ ቢሆንም፣ እዚህ ከመጣሁ በጣም ብዙ ሰው አግኝቻለሁ። ብዙወች ያውቁኛል። እኔም የማውቃቸው ብዙ ናቸው። ተሰባስበው ያነጋገሩኝ ብዙወቹ እኔ በተለያየ መንገድ ከምድር ወደዚህ የላኳቸው ናችው።
እንድሁም ታዋቂ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞችም በቦታው ነበሩ። የኢትዮጵያዊያኖችን በይበልጥም የዘመዶቻቸውን ቁስል ላለመቀስቀስ ስል ስም አልጠራም። ዝርዝሩን ከፈለግክና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲናገር ከፈቀድክለት ይነግርሃል። የደህንነት መስሪያ ቤታችን ያረጋግጥልሃል።
በጣም ቁጥር ስፍር የሌላቸው፣ ትግራይን ለማስገንጠልና ኤርትራን ነፃ ለማውጣት ብለህ፣ ከኢትዮጵያ ጦር በኩል፣ ከህወሃት በኩል፣ ከሻብያ በኩል፣ ያስጨረስከን ነን ይሉኛል። በጣም የገረመኝ ሁሉም በአንድ ሆነውና ተስማምተው ነው
ያነጋገሩኝ። በተደጋጋሚ ያቀረቡልኝም ጥያቄ እኛን አስጨረሰህ ትግራይና ኤርትራ ምን የተሻለ ነገር አገኙ፤ ህዝቡ ከመለመን፣ ከመሰደድ፣ ከርሃብ፣ ከድንቁርና፣ ከአምባገነን አገዛዝ ነፃ ወጣ ወይ የሚል ነበር። እንድሁም በትግራይ ተራራወች የጨፈጨፍናቸው የደርግን ግድያ ሸሽተው የነበረ የኢህአፓ ወጣቶች፣ በአዲስ አበባ ጎንደርና ሌሎች ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው በአጋዚ አነጣጣሪ ተኳሾች በኔ ትዛዝ ያስገደልኳቸው፤ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በደቡብ ህዝቦች በዘር ለያይተን ያጋደልናቸውና፣ በበደኖ፣ አርባጉጉ ከነህይወታቸው ገደል ያስጨመርናቸው፣ የብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል በማለት ቀስቅሰን በየጫካውና በየከተማው ኦነጎች ናችሁ እያልን የገደልናቸው የወለጋ፣ ባሌ፣ ጅማና ሃረር ወጣቶች፤ እንዲሁም ነፍጠኛ በማለት ፈርጀን እንዲፈናቀሉና እንዲገደሉ ያደረግናቸው ገበሬወች ነበሩ። በተጨማሪም በኤርትራ በየዋሻው ታስረው በርሃብና በግዳጅ ስራ ጠያቂ ሳይኖራቸው ያለቁ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ በተለያዩ ቦታወች እየተያዙ እንዲገደሉና እንዲሰወሩ ያደረግናቸው ኢትዮጵያዊያን በጣም ብዙ ነበሩ። እነዚህም ያናገሩኝ በአንድ ላይ ሆነው ነው። ሌሎቹ ቁጥራቸው የሚበዛው ከኢሳያስ ጋር በነበረን የግል አለመግባባት በባድሜ ስም ጦርነት ከፍተን ያስጨፈጨፍናቸው ነበሩ። ሁሉም እንዲወክላቸው የመረጡዋቸው፣ እቤታቸው በር ላይ በህወሃት ተኳሾቸ ያስገድልኩዋቸው መምህር አሰፋ ማሩ ነበሩ። ሁሉም ባንድ ቃልና በከፍተኛ ትዕግስት አናገሩኝ። አንተም ወደዚህ ትመጣለህን ብለው የተወሰኑት ቀለዱብኝ። ያሉበትን አለም የሚገዛው፣ እውነት፣ ሰባአዊነትና ትግስት ነው። ብዙወቹ ለአገር ሰማዕታት የሚሰጥ ልዩ የክብር ቦታ ተሰጥቷቸዋል።
የኔ መምጣት እንደተሰማ ካናገሩኝ ውስጥ ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ አጼ ምኒሊክ፣ አጼ ዩሃንስ፣ ደጃችህ ገረሱ ዱኪ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ በላይ ዘለቀ፣ ሞገስ አስገዶም፣ አብርሃም ደቦጭ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ አርበኞች ነበሩ። ከሁሉም ግን ራስ
አሉላ በጣም ተበሳጭተዉና ደማቸው ፈልቶ፣ ይህን ከሃዲ አምጡልኝ በማለት፣ ምን ለማድረግ ነው ስንት ህዝብ መስዋዕት ሆኖ ያቆያትን አገር ለማፍረስ ይህን ሁሉ ያደረግከው በማለት ጠየቁኝ። እኔም በፀፀትና በፍርሃት መንቀጥቀጥ ጀመርኩ። ከዚያም ከፊቴ ጥፋ ብለው አባረሩኝ። እኔም በሁለት እሳት መካከል ሆንኩ፣ አንዱ በስራዬ የተፈረደብኝ ሌላው ደግሞ የደረሰብኝ ፀፀት ነበር። ከዚያም ሃጢያቴን ለመናዘዝ አባታችን መምጣታቸውን ስለሰማሁ መፈለግ ጀመርኩ። እንደምንም አገኘኋቸው። እንደፊቱ የሚፈሩኝ መስሎኝ አባት ያሳልሙኝ ብዬ ጠጋ ስል፣ ክላ በማለት መቋሚያቸውን አንስተውና እኔንም አሳስተህ አስቀስፈኸኛል ብለው አባረሩኝ። ተስፋ ባለመቁረጥ ስፈልግ ሌላ አባት አገኘሁ። ቀረብ ብዬ አባት ሃጢያቴን መናዘዝ፣ ንስሃ መግባትና ካለሁበት እሳት መውጣት እፈልጋለሁ ስላቸው፣ ስለአንተ ቀድሜ ብዙ ሰምቻለሁ፣ መብርቅ መትቶህ በድንገት ነው እንዴ ወደዚህ የመጣህው አሉኝ። አይ አይደለም፣ ለረጂም ጊዜ ታምሜ ነበር አልኳቸው። እሳቸውም መልሰው ታዲያ የንስሃ እድሜ ተሰጥቶህ ይህን ሁሉ ጉድ ሃጥያት ተሸክመህ እንዴት ሳትናዘዝ ትመጣለህ ብለው በመገሰጽ ይቅርታ መጠየቅና ንስሃ መግባት ያለብኝ ግፍ በፈፀምኩበት በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት መሆኑን ነገሩኝ። በዚህም የተነሳ ይህን ደብዳቤ ፃፍኩልህ።
ጓድ ሃይለማርያም፣ በቅርብ የመጡ ብዙ ሰወች አገኘሁ። ከሁሉም የሰማሁት ተመሳሳይ ነው። አንተና የህወሃት ኢህአድግ ሰወች የመለስን “ሌጋሲ” (ውርስ) ሳይበረዝ ሳይከለስ እንቀጥላለን እያላችሁ ትፎክራላችሁ አሉ። ይህ የምትሰሩት
ስራ ሃጢያቴን እያባዘው ነው። አዜብ የመለስ ህይወት ታሪክ ሲነገር ገድሉ በአግባቡ አልተገለፀም አለች አሉ። ይህ ሁሉ ለኔ ምን ይጠቅመኛል? ያለሁበት ቦታ ውሸት፣ ከንቱ ውዳሴና ማሞካሸት የሚያስፈልገው አይደለም። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት የማይቀረው እየመጣ መሆኑን አውቄ እንኳ የሰረፀብኝን ትዕቢት ማሸነፍ፣ እውነቱን መቀበል፣ ያጠፋሁትን መናገርና ይቅርታ መጠየቅ አልፈለግኩም። እንዳውም እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ ከከፋፋይና ዘረኛ ስራየ አልተገታሁም።
አሁን ሌላ ሰው ነኝ፤ አልዋሽህም። ሃላፊነትን ከመውሰድ ይልቅ ስክድና ሚልዮኖችን እንዳሸበርኩ ሁሉ፣ ጥላየን ስፈራ፣ ራሴን በከንቱ ስከላከል ኖሪያለሁ። እናንተም በፍርሃትና በጭንቀት ተሸፍናችሁ ማየት ያልቻላችሁትን እኔነቴን ልግለጽላችሁ። መሪ መሆን ማለት ከምንም ነገር ቅድሚያ ሃላፊነት መውሰድ ነው። ምንም እንኳ በስሬ የተሰለፉት እበላ ባዮች የተንኮል ተልዕኮየን ለማሳካት ቢረዱኝም፣ በአገሩ ጉዳይ ገለልተኛ ሁኖ፣ የተጫነውን ሁሉ ተሸክሞ የሚኖረው ብዙ ኢትዮጵያዊ ላደረግኩት በደል በዝምታው አስተዋፅዖ አድረጓል። እኔም ለማደርገው ሁሉ ሃላፊነት ሳይሰማኝ የኢትዮጵያን ህዝብ ሳሰቃይና ስጨርስ ኖሪያለሁ። አንተ ደግሞ የኔን ስራ ያለምንም ለውጥ እደግማለሁ ብለህ መነሳትህ፣ ከምንም ነገር በላይ አሳሰበኝ።
እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የተጠናወተኝን አገር የመከፋፈልና ኤርትራን የማስገንጠል አባዜ ሳነበንብ በወንጀል ላይ ወንጀል ስሰራ ወደዚህ መጣሁ። ኢትዮጵያን ነፃ ለማወጣት ሳይሆን ትግራይን ለመገንጠል፣ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር
(ህወሃት) ብለን ተነስተን በብዙ ሺወች የሚቆጠሩ የትግራይን ወጣቶች በከንቱ አስጨረስን። ያአገር ድንበር ለማስከበር የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ ጨፈጨፍን። በመሰሪና መርዝ በሆነ ቅስቀሳችን በደርግ የግፍ አገዛዝ የተማረረውን ህዝብ አታለልን። ስውር ተልእኳችንን አሳካን።
ብዙ ኢትዮጵያዊያንና በለንደኑ ጉባኤ ያደራደሩን ፈረንጆች ሳይቀሩ የመከሩኝን ባለመስማት፣ ለኢሳያስ የገባሁትን ቃል ለመጠበቅና፣ ለአንድ አገር እድገት የባህር በር አያስፈልግም በማለትና የሃሰት ታሪክ በመፍጠር፣ ኤርትራን ከናት አገሯ
አስገንጥየ፣ ቀሪውን የኢትዮጵያን ህዝብ በጠመንጃ ሃይል አፍኘ፣ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል በማለት የተለየ ሃሳብ ያቀረቡትንና የተቃወሙትን ሁሉ ተራ በተራ አጠፋሁ። ኢትዮጵያን ያለባህር በር አስቀረሁ። ኤርትራን ከማስገንጠል አልፌ በአለም አቀፍ መድረክ የመጀመሪያውን እውቅና ለኤርትራ ሰጠሁ። በኢትዮጵያ ስም ተበድሬ ከፍተኛ ገንዘብ ለኤርትራ አስተላለፍኩ። ስራየ ሁሉ የኤርትራን ጥቅም ማስጠበቅ ሆነ።
የውጭ ጥቃት ይመጣል ተብሎ ሲሰጋ፣ አገሪቱን ከጥቃት ሊከላከል የሚችለውን የባህርና አየር ሃይል በተን። መውጫና መግቢያችን በትንሿ አገር ጂቡቲ መልካም ፈቃድ የሚወሰን ሆነ። ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላምና በአንድነቱ
እንዳይኖር፣ ጠባብ የዘር ፖለቲካ በመስበክና በህገመንግስቱ ዉስጥ የብሄረሰቦች መብት ያለገደብ እስከመገንጠል የሚለውን በማጽደቅ፣ አገሪቱን ጣሊያኖቹ ባሳዩን መንገድ በዘር ከፋፈልን፣ የአገሪቱን አንድነትና ደህንነት ለአደጋ ተጋልጦ እንዲኖር ህጋዊ መሰረት አስቀመጥን። ኢትዮጵያዊነትና የጋራ እሴት የሆነውን ሁሉ መግደል ዋናው ስራየ ሆነ። በአጭሩ በአዲስ አበባ የሚኖር የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርን ዓላማ አስፈፃሚና የኢሳያስ አምባሳደር ሆንኩ። በጣም የሚያስገርመው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የሚለውን ስማችንን እንኳ ሳንቀይር ኢትዮጵያን ይህን ያህል ዘመን መግዛታችን ነው።ይህን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ ብየ ሳይሆን ነገርን ከስሩ በየ ነው። ለነገሩ እኛ መግዛት ከጀመርን የተወለዱትና የኛን ዘረኛ ቅስቀሳ እንደወተት እየጠጡ ላደጉት ወጣቶች ይህን ስራየን ባሳውቃቸው ምን ይከፋል።
የፈለግኩትን ሁሉ አፍርሸ እንደገና እገነባዋለሁ የሚል ከንቱ አመለካከት ነበረኝ። በዚህም መሰረት ያአገሪቱን ምሁራን አባርሬ ሌላ ምሁራንን በራሴ አምሳል እፈጥራለሁ በማለት፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸውንና ይተቹኛል ብየ የፈራኋቸውን
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ችሎታ የላቸውም በማለት፣ ለአገር በሚጠቅሙበትና ብዙ ሊያስተምሩ በሚችሉበት እድሚያቸው፣ አባረርኩ። ያገሪቱን ምሁራን በማሳደድ ያለፍላጎታቸው የባዕድ አገር አገልጋይ እንዲሆኑና ብዙወችም
ተበሳጭተውና ተሰቃይተው እንዲሞቱ አደረግኩ። ለዚህ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ትልቅ ሚና ተጫውታልኛለች። በየመስርያ ቤቱ የኛን የዘር ፖለቲካ የማይቀበሉትን ሁሉ አባረርን። ምንም ችሎታው በሌላቸው ታጋዮች ተካን። ታማኞቻችንን በከፍተኛ ቦታ ለመመደብ ብዙው ሰው ድንጋይ መፈልፈያ እያለ በሚጠራው ሲቭል ሰርቪስ ኮሌጅ በማስገባት ዲግሪ አደልን። እንዲሁም ከአውሮጳ የተልዕኮ ዩኒቨርስቲወች “ድፕሎማ ሚልስ” በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ዲግሪ በመግዛት አደልን። ዛሬ እኔ ሳነጥስ አብረው ያነጥሱ የነበሩት በስሬ ያሰማራኋቸው አድርባዮች ሁሉ ባለ ማስተርስ ዲግሪ ተብለዋል። ለምን ያን ያህል የውጭ ምንዛሬ እንደአወጣሁና ትምህርት መርጃውን ራሴ እያተምኩ እንዳልሰጠኋቸው እስካሁን ለራሴም አልገባኝም። ታዲያ ነገሩ ሁሉ የኔን ቃላት እንደ ፀሎት መድገምና ድንቁርናን በአገሪቱ ማባዛት ሆነ።
ፈረንጆቹን ለማታለል፣ ከፍተኛ ብድር ለመበደርና ዕርዳታ ለማግኘት፣ የተጋነነና የውሸት መረጃ በመሰብሰብ፣ ለማስመሰል ያህል ህንጻ በመገተር ትምህርትን አስፋፋሁ አልኩ። ለህሊናቸው የሚገዙትንና የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ምሁራን
በስለላ ድርጅታችን ተብትበን በመያዝ አሽመደመድናቸዉ። ባጭሩ ተቋማቱ የካድሬ መፈልፈያና፣ እንደኮብል ድንጋይ ቀርጸው ካስቀመጡባቸው የማይንቀሳቀሱ፣ ሰምተውና አስበው የማይጠይቁ፣ አምባገነንን የሚያመልኩ በቀቀኖች ማምረቻ ሆኑ። በአገሪቱ እኔው ምሁር፣ እኔው ተመራማሪ፣ እኔው ህግ፣ እኔው ህግ አውጭ፣ እኔው ዳኛ፣ እኔው ፖሊስ፣ እኔው የጦር መሪ ሆኜ ኖርኩ።
በዘረኝነት መርሃችን የትግራይን ህዝብ እንዲጠላ ለማድረግና ምንጊዜም የኛ ደጋፊ ለማድረግ በሸርብነው ሴራ፣ ለሙን የጎንደርና፣ የወሎን መሬት ወደ ትግራይ ከለልን። ብዙ የዋህ ኢትዮጵያዊያን የትም ክልል ይሁን የኢትዮጵያ አካል
እስከሆነ ድረስ ብለው ተቀበሉት። የግል ደጋፊወቻችንን ሰፊና ዘመናዊ እርሻ እንዲኖራቸው በሁመራ ሰሊጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ በማድረግ የዛሬ ሃብታሞች የነገ አገር መሪዎችን ፈጠርንበት። ቀሪው ኢትዮጵያን የመግዛት ዘመናችን ካለቀ ግን፣ በጠባቡ አመለካከታችን ትግራይን ገንጥሎ ወደ ኤርትራ ለመቀላቀል የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጀን። ለዚህም እርዳታ እንድናገኝና ቀደም ብሎ በጫካ እያለን የተደረገልንን ውለታ ለመመለስ የጎንደርን ሰፊ ለም መሬት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቅ፣ ለሱዳን አሳልፈን ሰጠን። በተወሰነ የህውሃት መሪወች በተቆጣጠርነውና ከኢትዮጵያ ተዘርፎ፣ ከመንግስት ባንኮች ተውስዶ፣ በተቋቋመው፣ በግልጽ ባለቤትነቱ በማይታወቀው፣ የሂሳብ አያያዙ በማይመረመረው፣ ግብር በማይከፍለው፣ በትግራይ ልማት ድርጅት (ኤፈርት) ስም፣ ሌላ ባለሃብቶችን በማዳከም፣ ያአገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጠርን።
ሌላው ወንጀሌ የኢትዮጵያን የመሬት ስሪት በማስመልከት የፈፅምኩት ነው። መሬት የመንግስት ነው ብለን ስንነሳ የረቀቀ የረጅም ጊዜ ዓላማ ይዘን የኢትዮጵያን መሬት ለመሽጥ፣ ለፈለግነው ደጋፊወቻችን ለመስጠት መሆኑን የተረዱ ብዙ
አልነበሩም። የኢትዮጵያን ህዝብ ከመመገብ አልፎ ለሌላ አገር ይተርፋል የተባለውን ቆላማ መሬት ለውጭ ባለሃብቶች ለመሽጥ በነበረን የረጅም ጊዜ ዕቅድ መሰረት፣ መጀመሪያ ያደረግነው ህዝቡን በዘር መከፋፈልና ካአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሂዶ እንዳይሰራ ማድረግ ነበር። በዚህም ከበሽታና ከርሃብ ተርፈው የተቋቋሙትን ሰፋሪወች ከጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ባሌና ደቡብ ህዝቦች እንዲፈናቀሉና እንዲገደሉ አደረግኩ። የብዙ ህፃናትና ደካሞች ህይወት ሳይቀር አለፈ። ብዙ የመሃል አገር ሰወች በአርባጉጉ፣ በበደኖ እና ሌሎች ቦታወች ነፍጠኛ እየተባሉ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። ብዙ የመንግስት ሰራተኞች ክልላችሁ አይደለም እየተባለ ተባረሩ። የኢትዮጵያ ባንድራ ተወረወረ። ኢትዮጵያዊነት እዲጠፋ፣ ጎሰኝነት እንድነግስ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘመቻ አደረግን። በዚህ ረገድ እነ ጓድ ታምራት ላይኔና አሰን አሊ በዘረኛ ቅስቀሳቸው ያደረጉት አስተዋጾዖ ከፍተኛ ነበር። ዛሬ ግን ታምራት እኔና ባለቤቴን እግዚአብሄር በተደጋጋሚ በገሃድ መጥቶ አናገረን እያለ ፈረንጆቹን ያታልላል አሉ። ድሮም ብልጣ ብልጥ ነበር። በዕውነት እግዚአብሄር ከቀረበው ቅድሚያ የኢትዮጵያን ህዝብ ነበር ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት። በዚህም መሬት ስሪትና ዘረኛ መርህ በሚስጥር በሚደረግ ስምምነት ሰፋፊ በአገር የሚተካከል መሬት ለነ ካራቱሪ፣ ሸህ አላሙዲንና ሌሎችም ሸጥን። በጋምቤላና ሌሎች ቦታዎች ብዙ ህዝብ ተገደለ፣ ተፈናቀለ፣ ሰፊና ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብቱ ተጨፈጨፈ። መሬቱ ሃላፊነት በጎደለው መንገድ በኬሚካል እንዲበከልና የአካባቢው ህዝብ በበሽታ እንዲለከፍ ተደረገ። እንዲሁም የከተማውን ቦታ ዋጋ ጣራ በማድረስ ከመንግስት የተጠጉና መሬት በተለያየ መንገድ በእጃቸው የገባ ደጋፊወቻችንን ሚሊዮነሮች እንድሆኑ አድርገናል። እኛን ያልደገፉትን ግን ኪራይ ሰብሳቢ በማለት በማሰር አሰቃይተናል።
ጓድ ሃይለማሪያም፣ ካደረግኩት ነገር ሁሉ አንተን ወደ ስልጣን ማስጠጋቴ የተሻለ ስራ የሰራሁ መስሎኝ ነበር። ምክንያቱም ፈርሃ-እግዚአብሄር አለህ ሲባል ሰምቸ ስለነበር ነው። እንዲሁም ደግሞ አንተ እንደ እኔ የሰው ህይወት እያጠፋህ፣ በሰው አካል ላይ እየተረማመድክ የመጣህ ጨካኝ ስላልሆንክ ነው። በተጨማሪም የተማርክ በመሆንህ የምታገናዝብና በራስህ የምትተማመን ትሆናለህ በየ ስለገመትኩ ነው። ምንም እንኳ ከስሬ ያላችሁትን ሁሉ ረግጬ በመያዝ፣ በኔ አዕምሮ እንድታስቡ ባደርጋችሁና የህወሃት ሰወች አላሰራም ቢሉህም፣ በምድር ሳልኖር ግን ይህን ያክል እኔን የምትፈራበትና፣ እኔን ለመሆን የምትጥርበት ጉዳይ አልገባኝም። ይህን ስራህን ያዩ ኢትዮጵያዊያን “the cloned” መለስ
እያሉ እንደሚጠሩህ ሰማሁ። “ዘላለማዊ ክብር ለመለስ ዜናዊ” ማለትህንም ሰማሁ። እንዴት ብትፈራኝ ነው? በዕውነት ይህ ለኔ ይገባልን? ደግሞ መለስ “የሚማሩበት፣ የሚመራመሩበትና በርካታ ለመጪው ትውልድ አመራር አባላት በቂ የመነሻ ሃሳብ የሚያገኙበት በጥቅሉ ለጥልቅ ጥናትና ምርምር አንጡራ ሀብት ነው” ብለህ ማለትህ አሽሙር መናገርህ ነው። ጥሩ ብልሃል። የሰራሁት ወንጀል በዕውነትና በአግባቡ ተጠንቶና በመረጃ ተደግፎ ተጠናቅሮ ይቀመጥ ማለትህ ከሆነ ጥሩ ብለሃል። በትክክል እውነቱ ከወጣና ከተጠና የኔን ወንጀል ባለመድገም ከኔ የምትማሩት ብዙ ነገር አለ። አንተ ባትነግራቸውም ግን ብዙ ኢትዮጵያዊያን መረጃቸውን ሰብስበው ቀን እየጠበቁ መሆኑን አውቃለሁ። የትም ማምለጥ
አይቻልም፤ ወዮላችሁ።
ሰው እድሜው ሲጨምር ይበልጥ ራሱን ይሆናል ይባላል። አንተ ግን በየዕለቱ እኔን ለመሆን እየጣርክ ነው። ምነው አዕምሮህን ለኔ ባሪያ የምታደርገው? አንተ እኔ በየድንጋዩ ስር ስደበቅ፣ ስትማር፣ ስትመራመርና ስታስተምር ነበር።
እኔ በኮሚንስት አመለካከቴ እግዚአብሄርን ሳልፈራ እንዴት የሰውን ህይወት እደማጠፋ ሴራ ሳውጠነጥን ብዙውችን ስረሽን ሳስረሽን፣ አንተ የእግዚአብሄርን ቃል ስታነብ ነበር። ራስህን ሁን እንጂ ጓድ ጠቅላይ ሚንስተር። እኔን ሁነህ በጠባብ ህወሃቶች ከምትወደድ፣ ራስህን ሆነህ፣ ለህሊናህ ተገዝተህ ብትጠላ አይሻልምን?
ሌጋሲ ሌጋሲ የምትሉትና ባስለመድኳችሁ ጥራዝነጠቅ ቃላት የምታደናግሩት፣ ህዝቡ አይገባውም ብላችሁ ይሆን? እኔ ከዚህም ከዛም የባዕዳን ቃላትና ቁንጽል ሃሳብ በመቦጨቅ አንድ ጊዜ ትራንስፎርሜሽን፣ ሌላ ጊዜ ኪራይ ሰብሳቢ
ልማታዊ ባለሃብት እያልኩ የኢትዮጵያን ህዝብ ሳደናግርና ሳሳስት ኖሪያለሁ። አሁንማ ሰዉ ሲሰክር ሁሉ የሚሰዳደበው ኪራይ ሰብሳቢ እያለ ነው አሉ። እኔ ኪራይ ሰብሳቢ (ሬንት ሲከር) የሚለውን ሃረግ ስዋስ ያደረግኩት መርሁን ላጥላላ በተቃራኒው ግን ከህወሃት የተጠጉትን የስልጣን ባለቤት ብቻ ሳይሆን፣ በኪራይ ሰብሳቢነት መርህ፣ ማለትም መንግስት የሚያደርገውን ቁጥጥር፣ እገዳና አዋጅ በመጠቀምና፣ አዲስ ምርት ወይም አዲስ ሃብት በመፍጠር ሳይሆን፣ የነበረውን በመሰብሰብ፣የመንግስት የሆነውን መሬትና ንብረት በመሸጥ፣መንግስት የሚያወጣውን ጨረታ በአቋራጭ በመውሰድ፣ እንዲበለጽጉ በማድረግ፣ ሚሊዮነሮች እንድሆኑ ነው። በዚህም፣ በቅርቡ አቦይ ስብሃት እንደገለጠላችሁ፣ የኔ ዋናው ዓላማ የአሁኑን ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በሃብታቸው ተጽኖ ኢትዮጵያን ሲገዙ የሚኖሩ የአገሪቱን ሃብት የሚቆጣጠሩ፣ የህወሃት የገዢ መደብ መፍጠር ነው። ብዙ ሰው ሊረዳ ያልቻለውና የኔ ውስብስቡ አላማ ከጊዚያዊ ስልጣን መያዝ አልፎ ለመጭወቹ ምእተ ዓመታት የሚቆይ ገዥን መፍጠር ነው። ለዛም ነው የኔን ልጅ እንግሊዝ አገር ሳስተምር፣ አቦይ እንደነገራችሁ የሱን ልጆች ጣሊያንና ቻይና በመላክ፣ እንዲሁም የሌሎች ጓዶቻችንን ልጆች አሜሪካ አውሮፓ ልከን በማስተማርና ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተሻለ አዋቂ በማስመሰል ለቀጣይ ገዥነት እያዘጋጀን ያለነው። በአገር ውስጥ ግን ከመቀሌ በስተቀር ህንጻ ገተርን እንጅ ሌላውን ኢትዮጵያው ማደንቆር፣ ማዳከምና የትምህርት ጥራት እንዲወድቅ ነው ያደረግነው። በተጫማሪም ወጣቱን በዘርና በቋንቋ ከፋፍለን፣ የጋራ መግባቢያ እንዳይኖረው፣ ካንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዳይሰራ፣ ከጎሳው ውጭ ለአገር እንዳያስብ አድርገነዋል።
በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ ሰው የለም ማለትህን ሰማሁ። ታዲያ እስር ቤቱን ሁሉ ያጣበቡት የኦሮሞ ወጣቶች፣ ነፃ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪወችና የሙያ ማህበር መሪወች ከኔ ጋር በምን ተጣልተው መሰለህ። እኛ ያገባናል ብለን
በጠመንጃ ሃይል፣ የሺዎችን ህይዎት አጥፍተን፣ ስልጣን ስንይዝ፣የፈለግነውን ሁሉ ያለገደብ ስናደርግ፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ግን ሰው የዘር ሃረጉ እየተቆጠረ አይገደል፣ አይፈናቀል፣ የመናገር መብቱ አይታፈን፣ መሰረታዊ ሰበአዊ መብት ይከበር፣ ስላሉና በሰላም በበዕራቸው ስለታገሉ ስንቶቹን በእስር፣ በድብደባ፣ አሰቃየን። ስንቶቹን ገደልን። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት ስላሉ፣ የሰው ልጅ በቋንቋው ተለይቶ መገደል የለበትም ስላሉ አስቃይተን የገደልናቸውና የብዙ ኢትዮጵያዊን ህይወት ያተርፉ የነበሩትን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ሰምቻቸው ቢሆን ኖሮ፣ የብዙ ኑፁሃንን ህይወት ማዳንና የግፍ ግድያን ማስቆም፣ ብቻ ሳይሆን ወንጀለኞች እንኳ ፍትህ የሚያገኙባት ኢትዮጵያን በፈጠርን ነበር። ስህተታችንን ሊጠቁሙ የሚችሉትንና የህዝብ አይን፣ ጆሮና አንደበት የሆኑትን የግል ጋዜጠኞችን አሰርን፣ ብዙወች አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አደርግን። ዛሬ የመንግስትን ሃብት የሚዘርፉትን ባለስልጣናት የሚያጋልጥ ነፃ ጋዜጠኛ በመታፈኑ፣ ትንሹን ሌባ የሚያጋልጠው፣ ትልቁ ዘራፊ ሆኗል። ስንንቃቸው፣ ስናዋርዳቸውን ስናሳድዳቸው የነበሩ ጋዜጠኞች ናቸው አሉ፣ በአገር ውስጥ እውነቱን የሚናገር ጋዜጠኛ በጠፋበት ጊዜ፣ በተሰደዱበት አገር ሁነው የኔን ዜና ዕረፍት እንኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሰሙት። ዛሬ ለህይወታቸው ሳይፈሩ የህዝብ መብት ይከበር ብለው በሰላም ስለጠየቁ፣ የኔና አገዛዝ ብልሹ አሰራር ስለተቹ፣ አስረን የምናሰቃያቸው እነ እስክንድር ነጋ፣ ብርሃኑ አራጌ፣ የኦሮሞና የኦጋዴን ወጣቶች፣ንጹሃን የፖለቲካ እስረኞች ካልሆኑ ምን ሊሆኑ ነው።
በህዝቡ መካክል ልዩነትን መፍጠርን የነበረም ልዩነት ካለ ማባባስ ዋናው የመግዣ ስልቴ ነበር። በዘር መካካል የማይታረቅ ልዩነት እንዲኖር መርዛማ የሃሰት ታሪክ በመፍጠርና የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ነው ብሎ በመቀስቀስ
ብዙዎችን ማሳሳትና በጠባብ የዘር ፖለቲካ እንዲጠመዱ አድርገናል። በሃይማኖት መካከልና ልዩነት መኖሩ የስልጣን እድሜየን ለማራዘምና የኢትዮጵያ አንድነት ደጋፊዎችን ያዳክምልኛል ብየ በማሰብ፣ ልዩነቱ እየሰፋ ሲሄድ ዝም ብየ
ከመመልከትም አልፌ ልዩነቱን ለማስፋት የሚረዱኝን ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዲወጡና ነገሩን እንዲያባብሱ አድርጊያለሁ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቅርብ ጊዜ የምዕራባዊያንን ቀልብ ለመሳብ ረድቶኛል። በተጨማሪም የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘትና ተቃዋሚዎችን ለማፈን፣ እንደ ሶማሊያ ያለውንም አለመረጋጋት ተጠቅሜበታለሁ።
አኔና ህወሃት በደርግ ጊዜ የነበረዉን ጊዚያዊ ችግርን በዘላቂ በሽታ ተካን። ለመጭው ትውልድ ያተርፍንለት በቀላሉ የማይነቀል የዘረኝነት በሽታ ነው። የጎሰኝነት መጨረሻው ምን እንደሆነ ከሶማሊያ የበለጠ ሊያስተምረን የሚችል
ምን ነገር ይኖራል? በቅርብ ጊዚያት በግብፅ፣ ሶሪያ፣ቱኒሲያና ሊቢያ የተከሰተው ነገር ባግባቡ ላስተዋለው ትልቅ ትምህርት ነው። ከምንም ነገር በላይ የታፈነ ህዝብ በድንገት ተነስቶ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ አሳይቶናል። የአምባገነኖች
መጨረሻቸው ምን እደሆነ ታይቷል:: ዛሬ አድናቆታቸው ያልተለየህ ሃያላን ቀን ሲጥልህ ከጎንህ እንደማይቆሙ ከሆስኒ ሙባረክ ሁኔታ የተማርክ ይመስለኛል። ብዙወቻችሁ የኔ እድል ላያጋጥማችሁና ባቋራጭ ወደዚህ አትመጡ ይሆናል። ዘመኑ የመረጃ ጊዜ በመሆኑና ከህዝብ የተደበቀ ነገር ሊኖር ባለመቻሉ ለፍርድ በምትቆሙበት ጊዜ የሚከላከልላችሁ ነገር ካለ የራሳችሁ ስራ ብቻ ነው። አስተውሉ። ጥሩ መሪ ችግር ድንገተኛ አደጋ ሁኖ ከመምጣቱ በፊት ያስተውላል ሲባል
አልሰማህምን?
ጨካኝ መሪን ባያሳድገውም ብዙ ጊዜ የሚወልደው አምባገነን መሪ ነው። የኔ ትልቁ ፍራቻ፣ ከኔ የባሰ ጨካኝ መሪ ኢትዮጵያን እንዳይቆጣጠራት ነው። ደርግ አገሪቱን ለኛ እንዳስረከበው፣ እኔና እኔ የፈጠርኩት አምባገነን ስርዓት ደግሞ አገር ሊመሩና ለኢትዮጵያ ሊያስቡ የሚችሉትን ሁሉ ተራ በተራ በማጥፋት፣ የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ለሚችሉና በድንገት ስልጣን ላይ ለሚወጡ ክፉ አምባገነኖች ኢትዮጵያን አመቻቸናት። ላንተ ያወርስኩህ ኢትዮጵያ ይህች ናት። ስለዚህ የኔ ዋናው መለዕክት የመለስ ሌጋሲ፣ የመለስ ሌጋሲ የምትለውን ትተህ ራስህን ሁን። እኔም ልረፍበት። የአጠቃላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን መሪ ሁን። ከኔ መጥፎና ዘረኛ አገዛዝ ተማር። ዛሬ በመካድ የነገን ተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም። እኔ የፈጸምኩትን ስህተታት አትድገም። ይህን መልዕክት ደግሞ በስርህ ለተሰለፉት ባለስጣኖችህና ኢትይጵያዊያን አስተላልፍልኝ። ለኢትዮጵያ መልካም ነገር ታደርግ ዘንድ እግዚአብሄር ብርታቱን፣ ጥበቡንና ድፍረቱን
ይስጥህ።
ሰላም ለኢትዮጵያ ይሁን
መለስ ዜናዊ
ከላይኛው ቤት

No comments:

Post a Comment