Wednesday, August 28, 2013

ጌሾና ጫት – በአውስትራልያ(daniel kibret)



ጌሾና ጫት – በአውስትራልያ(daniel kibret)



አሁን አብዛኛው አውስትራልያ የገባ ኢትዮጵያዊ በሚገኝባት የሜልበርን ከተማ ውስጥ አበሻው ሰብሰብ ብሎ በሚኖርባትና በሚሠራባት ፉትስክሬይ በተባለችው መንደር እንገኛለን፡፡ ይህች የሜልበርን ምዕራባዊ ቀበሌ የሆነች መንደር ጥንት የኤስያውያን መናኸርያ ነበረች ይባላል፡፡ ዛሬ ግን ዋናዋ የአፍሪካውያን ስደተኞች መሰባሰቢያ ናት፡፡ በዚህች ከ74000 ትንሽ ከፍ የሚል ሕዝብ በሚኖርባት መንደር ውስጥ ከ135 ሀገሮች የመጡ ስደተኞች ይኖሩባታል፤ ከ85 ቋንቋ በላይ ይነገርባታል፡፡ እንዴው መርካቶ በሏት፡፡
በአውስትራልያ ታሪክ የመጀመሪያው የእንጀራ መሸጫ ሱቅ የተከፈተው እዚህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር እንጀራ በዋናነት ከስንዴ ወይም ከሩዝ ዱቄት ተቦክቶ የማሽላ ዱቄት ይቀላቀልበታል፡፡ የታደሉት ደግሞ ከሀገር ቤት የመጣ የጤፍ ዱቄት ለአመል ይጨምሩበታል፡፡ ስፋቱ የአገር ቤት እንጎቻ የሚያህል ሲሆን ውፍረቱ የሰንበት ቂጣ ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ኮከብ የመሰለ ዓይን ባያገኝም፣ ሞጭሟጫ ከመባል ለጥቂት ይተርፋል፡፡ በብዛት የሚጋገረው ከብረት በተሠራ ምጣድ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከሀገር ቤት የሸክላ ምጣድ የሚያመጡ አሉ፡፡ ሳይሰበር ከደረሰላቸው፡፡
በፉት ስክሬይ ከደርዘን በላይ የኢትዮጵያውያን ሱቆች፣ ከአምስት በላይ ምግብ ቤቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በአካባቢው ስትዘዋወሩ ቢያነጥሳችሁ ‹ይማርህ› የሚል አታጡም ይባላል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ስለሚዘዋወሩበት፡፡ በርግጥ ወጣቶቹና ጎልማሶቹ እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም፡፡ የሚገርማችሁ እንዲያውም እዚህ አካባቢ አበሻና አበሻ ሲገናኝ ቁጣ እንጂ ሰላምታ አይሰጣጥም፡፡ ሁለቱም ፊታቸውን ኮስተር አድርገው ነው የሚተላለፉት፡፡ እኔ እንዲያውም ‹እዚህ ሀገር የመጣው ያኮረፈው ተመርጦ ነው እንዴ› ብዬ ነበር፡፡
በፉት ስክሬይ የሚጠፋ ቅመማ ቅመም የለም፡፡ በተለይም ሕንድ ሱቅ ውስጥ በሀገራችን የጠፋው ቅመም ሁሉ ይገኛል፡፡ ሞያ በሜልበርን በሽ በሽ ነው፡፡ በርበሬ ከሀገር ቤት ለማስመጣት የአውስትራልያ የምግብ ሕግ ሲያስቸግር እዚሁ ሌላ በርበሬ ተፈጥሯል፡፡ ከሕንዶች ሱቅ የሚገዛ የሚያቃጥል ቀይ ቃሪያ አለ፡፡ እርሱን በኮረሪማ መፍጫ መፍጨት ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ቅመማ ቅመሙን ለብቻ ፈጭቶ መጨመር፡፡ በመጨረሻም አውስትራልያ ሠራሽ ምርጥ ድልህ ይሆንላችኋል፡፡
 አንድ ወዳጃችን ‹ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ› ቢልም ከሀገር ሲወጡ አንዱ የሚናፍቀው ግን ሽሮ ነው፡፡ በአውስትራልያ ልዩ የሆነ የሽሮ አዘገጃጀት ተፈጥሯል፡፡ የባቄላው ዱቄት ከሕንድ ሱቅ ይገዛል፡፡ ከዚያም አመስ አመስ ይደረጋል፡፡ ለቅመማው አስፈላጊ የሆነውን ቅመምም ሕንዶቹ ያመጡታል፡፡ እርሱንም በቡና መፍጫ ፈጭቶ በመጠኑ ማመስ ነው፡፡ ከዚያም ሁለቱን በባለሞያ እጅ ደባልቆ ምርጥ የውጭ ሀገር ሽሮ ማግኘት፡፡ ችግር ብልሃትን ይፈጥር የለ፡፡
   ለኢትዮጵያውያን እዚህ አንዱ ፈተና ከሀገር ቤት ባህላዊ ምግቦችን ማስመጣት ነው፡፡ የሀገሩ ሕግ ጥብቅ ስለሆነ፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ግን እንደ ካልዲ(የቡናን ፍሬ ያገኘው እረኛ) አዳዲስ ቅጠላ ቅጠሎችን የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን እዚህ ሞልተዋል፡፡ አንድ ቀን ነው አሉ፡፡ መቼም እኛ ታሪክን በጊዜና በሰዓት የመመዝገብ ችግር አለብን፡፡ (ተረቱም ታሪኩም ከዕለታት በአንድ ቀን ብሎ ነው የሚጀምረው) አንዲት የሀገሬ ሰው በግቢዋ ውስጥ ስትዘዋወር አንድ የምታውቀውን ቅጠል የሚመስል ነገር ታያለች፡፡ ጠጋ ብላ ቆረጠችውና መዳፏ ላይ አሸችው፡፡ ልክ ነው፤ እርሱ ነው፡፡ ወስዳ ለጓደኛዋ አሳየቻት፡፡ ሁለቱም ርግጠኞች ሆኑ፡፡ ጉዳዩን ወደ ልጅቱ እናት ‹ሪፈር› አደረጉት፡፡ እርሳቸውም እየተገረሙ ‹እርሱ ነው› አሉ፡፡ ለካስ ጌሾ ኖሯል፡፡ ጠላ ለመጥመቅ ችግር የነበረው ጌሾ በአውስትራልያ ምድር በቅሎ ተገኘ፡፡ ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ግቢ ውስጥ ጌሾ በቅሎ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
በዚህች ምድር በቅሎ የተገኘው ግን ጌሾ ብቻ አይደለም፡፡ መቼም አገር ደግ ነገር ብቻ አታበቅል፡፡ አንድ ወዳጃችን ሁል ጊዜ አንድ ቦታ እየሄደ ቅጠል ሸምጥጦ ሲወጣ ይታያል አሉ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ማንም ከቁም ነገር አልወሰደውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ሸምጣጩ በዛ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ግራ ገባቸው፡፡ በከተማዋ ውስጥም ወሬው ተባዛ፡፡ የሚሸመጠጥበት ቦታም በአንዳንድ ሰዎች መዘውተር ጀመረ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከሥሩ እየነቀሉ ወስደው በጓሯቸው ተከሉት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአውስትራልያ ፖሊሶች ጉዳዩን ሰሙትና ክትትል አደረጉ፡፡ ለካስ ያ በወፍ ዘራሽ በቅሎ አገር እየተራኮተ የሚሸመጥጠው ጫት ኖሯል፡፡ ፖሊሶቹ እዚያ ቦታ የነበረውን መድምደው አጠፉት፡፡ ችግሩ ግን እነርሱ ሳይደርሱ በፊት በየግቢው ተዛምቷል፡፡ አንዳንድ ቤት ስትሄዱ ጫት በኩራት በቅሎ ታዩታላችሁ፡፡
ፉት ስክሬይ በአበሾች ዘንድ ከምትታወቅበት ሀብቷ አንዱ ምርጥ የሆነ ቁርጥ ሥጋ መሸጫ ስለሆነች ነው፡፡ መቼም ቁርጥ እየበላን ቁርጥ ነገር አለመቻላችን የሚገርም ቢሆንም የሀገሬ ሰው የትም ቦታ ቢሄድ፣ ምንም ዓይነት ትምህርት ቢማር ሊያጣው የማይፈልገው ነገር ቢኖር ቁርጥ ሥጋ ነው፡፡ ከነአባባሉም ‹የተማረ ሰውና የተሳለ ቢላዋ ሥጋ አያጣም› አይደል የሚባለው፡፡ እዚህ ከተማ በጥሬ ሥጋ ሻጭነታቸው የታወቁ ቤቶች አሉ፡፡ ነጭ፣ ቀይ፣ ጎድን፣ ዳቢት፣ ሻኛ፣ ለቁርጥ፣ ለወጥ እያሉ የሚያስተናግዱ፡፡ እነርሱ ጋ ገብቶ አለበለዚያም ደግሞ ሰፈር ይዞ መጥቶ ቁርጥ በኅብረት መብላት እዚህ የተለመደ ነው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ አውስትራልያ ዘመድ ለመጠየቅም ሆነ ለመዝናናት የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በአውስትራልያ ቁርጥ ፍቅር ተነድፈው ነው የሚመለሱት፡፡ አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ወዳጆቼ ጋር ስንጻጻፍ እንዲያውም ‹የአውስትራልያን ቁርጥ ሳትበላ እንዳትመጣ› ይሉኛል፡፡ እስቲ ቀምሼ እመሰክርለታለሁ፡፡
‹አይ እኔ ማን እንደነካው የማይታወቅ ሥጋ አልበላም› ለሚሉ አለያም ደግሞ ‹የተሸረፈ ጥርስ፣ ደልደል ያለም ላት አይቶ መርጦ ተከራክሮ መግዛት› ለሚያምራቸው ወደ ገጠሩ ክፍል ወጣ ማለት ነው፡፡ ከበግ አርቢ ገበሬዎች ጋር ምን የመሰለ የደብረ ብርሃን በግ ይገኛል፡፡ ማረዱን ባይፈቅዱላችሁም መባረኩን ይፈቅዱላችኋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ገፍፈውና ቆራርጠው ይሰጧችኋል፡፡ ከዚያ በኋላማ ‹አቤት ባለፈው ለፋሲካ የገዛሁት ምን የመሰለ በግ› እያላችሁ ሾላ ገበያ የሄዳችሁ ማስመሰል ነው፡፡ 
ሜልበርን አውስትራልያ፡፡
 
ምንጭ  https://www.clickhabesh.com/~clickha1/?cat=185

No comments:

Post a Comment