Wednesday, August 28, 2013

በአማራ ክልል የጫት ማሳ መስፋፋት ስጋት ፈጥሯል

በአማራ ክልል የጫት ማሳ መስፋፋት ስጋት ፈጥሯል

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 21 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል አርሶ አደሮች በሌሎች የግብርና ምርት ውጤቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ማሳቸውን በጫት ተክል እየሸፈኑት መጥተዋል።
በክልሉ ርዕሰ መዲና ባህር ዳር የአባይን ወንዝ እንደተሻገሩ ልዩ ቦታው አባይ ማዶ በሚባል አካባቢን ያገኛሉ።
በዚህ  ስፍራ ቁጥሩ በርከት ያለ የጫት ችግኝ ይቸበቸባል ፤ ብዙ ገበያተኛም ይታያል ።
ለወትሮ ለምግብነት በሚውሉ የሰብል ምርቶች የማውቃቸው የባህር ዳር ዙሪያ አካባቢዎች አሁን በጫት ማሳ እየተወረሩ መምጣታቸው ነው የሚነገረው።
ከእነዚህ አካባቢዎች ተፈልቶ የሚመጣው የጫት ችግኝ ደግሞ ዋነኛ የመገበያያ ቦታው እዚህ አባይ ማዶ የሚባለው አካባቢ ነው።
አርሶ አደር ህሩይ ዳኛው የሜጫ ወረዳ አብሮ መኖር ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ፥ ለረጅም ዓመታት የጫት ችግኝ እያፈሉ ሸጠዋል።
እኝህ አርሶ አደር  ጫትን ሸጠው የፍላጎታቸውን ማሟያ ገቢ ያስገኝላቸው እንጂ የሰብል ማሳቸውን በጫት ተክል መተካታቸው  ሊኖረው የሚችለውን  አሉታዊ ተፅእኖ የተረዱ አይመስሉም።
አሁን የጫት ችግኛቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች አድማሱን እንዳሰፋ አርሶ አደሩ ነግረውናል።
ከባህር ዳር ከተማ የተነሳው የጫት ችግኝ ወልዲያና የቅባት እህል አምራች ወደ ሆነው መተማም እየተስፋፋ ስለመሆኑ በገበያ ላይ ያገኘናቸውና  ስማቸውን መግለፅ ካልፈለጉ ነጋዴዎች ለማወቅ ችለናል።
ከየአርሶ አደሩ ማሳ የተለቀመው ጫት በገፍ ለገበያ የሚቀርብባት የባህር ዳር ዙሪያ ዘንዘልማ ከተማ ገበያው ከእለት ወደ እለት እየደራባት ነው ።
ከተማዋ የባህር ዳር ጫት እየተባለ ወደ ተለያዩ የሃገራችን ከተሞች የሚሰራጭባት ዋነኛ መነሻ ናት።
አብዛኞቹ  አርሶ አደሮች  ጤፍን ሸጠው  ከሚያገኙት ገቢ የጫት ብልጫውን ስለሚወስድ ማሳቸውን በጫት መተካትን እንደመረጡ ይናገራሉ።
የጫት ማሳ እየተስፋፋ ስለመሆኑ የታዘቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች  በመንግስት ችላ ሊባል እንደማይገባ ይናገራሉ።
የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አምላኩ አስረስ የጫት እርሻ እየተስፋፋ ስለመሆኑ በመቀበል የጫት ማሳ እንዲስፋፋ አንድም የመንግስት ድጋፍ የለበትም ይላሉ።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በእርግጥ አርሶ አደሩ ምን ቢያመርት እንደሚያዋጣው መለየቱ በጎ እንደሆነ ያነሳሉ።
አርሶ አደሩ የጫት እርሻውን ትቶ ወደ ሌላ አዋጭ የግብርና ምርቶች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ አስተሳቡን መቀየር እንጂ አዋጅ በማውጣት ማስቆም እንደማይቻል ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ  አርሶ አደሩ ከጫት ይልቅ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አማራጭና አዋጭ የግብርና ስራዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይጠይቃል።
የአርሶ አደሩ በጫት ማሳ  ላይ የአትክትልትና ፍራፍሬ ውጤቶችን በስፋት ማምረት ቢችል ከጫት በላይ ከፍተኛ ገቢ ያስገኝለታል የሚሉት አቶ ተፈራ  የከብት እርባታና ንብ  ማነብ  ቢሆንም  የአርሶ አደሩን ገቢ የተሻለ ያደርግለታል ብለዋል።
እነዚህን የግብርና ስራዎች በአማራጭነት ለአርሶ አደሩ በፍጥነት መሳየት ተገቢ መሆኑን ነው አቶ ተፈራ የተናገሩት።

በታደሰ ብዙዓለም

http://www.fanabc.com





No comments:

Post a Comment