Wednesday, August 21, 2013

በቀጣዩ ወር ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ሌላ ዙር የቤት ምዝገባ ሊካሄድ ነው

Addis Ababa Condominium house
በፀጋው መላኩ ሰንደቅ ጋዜጣ
የአዲስ አበባ ከተማን የመኖሪያ ቤት እጥረት በዋነኝነት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማቃለል ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ምዝገባ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በመስከረም ወርም 2006 ዓ.ም ሌላ ዙር የቤት ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
የ2005 በጀት ዓመት የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት የእቅድ አፈፃፀምን አስመልክተው ባለፈው ቅዳሜ መግለጫ የሰጡት የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በመስከረም ወር ተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። ምዝገባው በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያድርግ ነው። የቤቱ አይነት 40/60 ሲሆን በሰራተኞቹ ስም ሙሉ ክፍያውን እንዲፈፅም የሚደረገው ሰራተኞቹ የሚሰሩበት የልማት ድርጅት ነው። የልማት ድርጅቶች በእያንዳንዱ ተመዝጋቢ ስም መቶ ፐርሰንት የቤቱን ዋጋ መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሰራተኛው በአንፃሩ ከሚሰራበት የልማት ድርጅት ጋር በሚፈጽመው ውል መሰረት በወር የሚከፍለውን የገንዘብ መጠን በተመለከተና በሌሎች ዝርዝር ግዴታዎችና መብቶችን ለይቶ እንዲያውቅ ይደረጋል።
እንደ አቶ መኩሪያ ገለፃ የልማት ድርጅቶቹ ከሰራተኞቻቸው ጋር ይገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ውሎች መካከል በልማት ድርጅቶቹ አማካኝነት የቤት ልማት ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ሰራተኞች የአገልግሎት ጊዜ ነው። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ አንድ የልማት ድርጅት በሰራተኞቹ ስም የቤት ልማት ገንዘብን መቶ ፐርሰንት ክፍያን ሲፈፅም አሰሪና ሰራተኛው በሚገቡት ውል መሰረት ሰራተኛው መሥሪያቤቱን ለተወሰኑ ዓመታት ለቆ ሳይሄድ የማገልገል ግዴታ ይጠቅበታል።
ይሁንና አንደ ሰራተኛ ቤቱን ተረክቦ ከገባው ውል ውጪ የቤት ባለቤት ያደረገውን የልማት ድርጅት ለቆ ቢሄድ ግለሰቡ በየወሩ የከፈለው ገንዘብ እንደኪራይ ተቆጥሮ ቤቱን እንዲለቅ የሚደረግ መሆኑን አቶ መኩሪያ አመልክተዋል። መመሪያው እየተዘጋጀ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ከመስከረም 15 እስከ መስከረም 30 ቀን 2006 ባሉት ቀናት ምዝገባውን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው አመልክተዋል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስት ይዞታ ስር ሆነው በትርፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ንግድ ባንክና የመሳሰሉት ድርጅቶች ናቸው።

 http://news.yehabesha.com

No comments:

Post a Comment