Wednesday, August 14, 2013

መድረክ አንድነት በተናጠል የሚያደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አላስደሰተውም

‘‘የአንድነት መጠናከር የመድረክ መጠናከር ነው’’
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በቅርቡ
‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ በሚል የፀረ-ሽብር ሕጉን ለማሰረዝ የጀመረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ መድረክን
አላስደሰተውም።አንድነትን ጨምሮ አራት ፓርቲዎችን በግንባርነት ያቀፈው መድረክ ባለፈው ቅዳሜ በየስድስት ወሩ የሚያካሂደውን
ጉባኤ ባደረገበት ወቅት በአንድነትና በመድረክ መካከል ያለው ግንኙነት በአጀንዳነት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም
ላይ አንድነት ፓርቲ የመድረክን እንቅስቃሴ የሚጎዳ ተግባር ላይ በመሰማራቱ ቀደም ሲል የመድረክ የስራ አስፈፃሚ በአንድነት
ፓርቲ ላይ ሰጥቶ የነበረውን ማስጠንቀቂያ ጠቅላላ ጉባኤው እንዲፀና አድርጓል።
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የጉባኤው ተሳታፊ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ጉባኤው አንድነት ፓርቲ
በፈጠረው ችግር ላይ ከተወያየ በኋላ ጉዳዩ በማስጠንቀቂያ አልፎታል። በጉባኤው ላይ የአንድነት ፓርቲ ወክለው የተገኙ
አባላት የአንድነትን አቋም ለጉባኤው አባላት ቢያስረዱም ፓርቲው ከግንባሩ ህግና ደንብ ውጪ ለመንቀሳቀስ በመሞከሩ
ለፓርቲው ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ተደርጓል።
ሌላው በጉባኤው ላይ የተነሳው ነጥብ አንድነት ከሰሞኑ በተናጠል በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያደረገ ያለው
የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ አንፃር ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል። በመድረክ የመተዳደሪያ ደንብ
መሠረት አገራዊ ጉዳዮችን በጋራ መስራት ግዴታ መሆኑ፣ በተለይም መድረክ ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ በመድረክ አመራር
ለሕዝብ የማስተዋወቅ ሥራ መካሄድ ቢኖርበትም አንድነት ግን ‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ በሚል መሪ ቃል የራሱን
የፖለቲካ እንቅሰቃሴ ብቻ ይዞ መቀጠሉ ተገቢ አለመሆኑና በዚህም ላይ ጉባኤው ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ምንጫችን
ገልጿል።
በመድረክ ማኒፌስቶ የተካተቱ ጉዳዮች ፓርቲዎቹ በጋራ የሚፈፅሟቸው እንደሆነ ቀደም ሲል ስምምነት
የተደረሰባቸው ቢሆንም በአንድነት በኩል ግን አንድን ጉዳይ (የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉን ብቻ) በመነጠል የፖለቲካ ዘመቻ
መጀመሩ ተገቢ አለመሆኑ ተነስቶ ውይይት ተካሂዶበታል። በመድረክ የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት አንድ አባል ፓርቲ
መድረክ በማይደርስባቸው አካባቢዎች በስተቀር መድረክ በሚሸፍንባቸው አካባቢዎች ለብቻው መንቀሳቀሱን የሚደገፍ
አይደለም፤ ነገር ግን አንድነት መድረክ እንቅስቃሴ ለማድረግ ባቀደባቸው አካባቢዎች የራሱን ፕሮግራም አስቀድሞ እየሄደበት
ያለው አካሄድ የሌሎች አባል ፓርቲዎችን አላስደሰተም።
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች አቶ ዳንኤል ተፈራ እና አቶ ሀብታሙ አያሌው
ስለጉዳዩ በጋራ በሰጡት ማብራሪያ በመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአንድነት ፓርቲ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተወሰኑ
አባላት ዘንድ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቢነሳም የማስጠንቀቂያ ውሳኔ ተላልፏል መባሉን አስተባብለዋል።
የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ለአንድነት ፓርቲ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አንድነት ፓርቲ ባወጣው የግምገማ ሰነድ ላይ
ሳይሆን የግምገማ ሰነዱ ለመድረክ ፓርቲዎች ሳይደርስ አስቀድሞ ሚዲያ ላይ መውጣቱ ተገቢ አለመሆኑ ላይ ነው ሲሉ
በሰነዱ ላይ ሳይሆን በአካሄዱ ላይ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎቹ ገልፀዋል።
አንድነት የጀመረው ‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ የሚለው የሦስት ወር የፖለቲካ ንቅናቄ መድረክን ያጠናክራል
እንጂ የሚጎዳ ባለመሆኑ ተቃውሞ መነሳት እንደሌለበትም አቶ ዳንኤልና አቶ ሐብታሙ ተናግረዋል። በመድረክ ጠቅላላ
ጉባኤም ጉዳዩ መነሳቱ እውነት መሆኑ ጠቅሰው የተነሳበት ነጥብ የአንድነት የሦስት ወራት የሕዝብ ንቅናቄ በመድረክ ውስጥ
ማለፍ እንዳለበት የሚያስገነዝብ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአንድነት በኩልም ጤናማ በሆነ መንገድ በጉዳዩ ላይ ክርክር
መደረጉንም ገልፀዋል።
በአንድነት በኩል መድረክ የሚያመጣቸውን ማናቸውንም እቅዶች ለማስፈፀም አንድነት ግዴታ እንዳለበት የጠቀሱት
ኃላፊዎቹ፤ የመድረክ መተዳደሪያ ደንብም ፓርቲዎች በተናጠል የራሳቸውን ሥራ መስራት የለባቸውም ስለማይል አንድነት
‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ነፃነት’’ ብሎ መንቀሳቀሱ ተገቢና ገንቢ ነው ብለዋል።‘‘አንድነት ጠንካራ መሆኑ ለመድረክ መጠናከር ትልቅ
አስተዋፅኦ አለው’’ ያሉት ኃላፊዎቹ አንድነት የጀመረውን
እንቅስቃሴ እንደማያቆም ይልቁኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል አንድነት በአምስት አመት የስትራቴጂክ እቅዱ ላይ ግልፅ
እንዳደረገው በፓርቲዎች መሰባሰብ ላይ የሚያምን እንደመሆኑ መጠን ፓርቲው ብቻውን ለመቀጠል ፍላጎት የለውም
የሚሉት ኃላፊዎቹ፤ አንድነት መድረክን የሚያዳክም ተግባር አይፈፅምም ብለዋል። የተቀሩት የመድረክ አባል ፓርቲዎች
የራሳቸውን ፕሮግራም በመቅረፅና አንድነትም የዘረጋውን የሦስት ወር እቅድ በማስተባበር ጭምር አጋርነታቸውን
እንዲያሳዩም የጠየቁ ሲሆን አንድነት አሁንም ቢሆን በመድረክ የታቀዱ ፕሮግራሞችን በጋራ ለመተግበር ዝግጁ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሳምንታት አንድነት በኦሮምያ ከተሞች ለሚያካሂደው እንቅስቃሴ መድረክ ከወዲሁ እገዛ ማድረግ
እንዳለበትና በሂደቱም ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቀዋል። በቅርቡ መድረክ በባህርዳር በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ እንዲሳካ
አንድነት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን በማስታወስ የተጠናከረ መድረክ መፍጠር ፍላጎታችን ነው ብለዋል።
አዲሱ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የሚሊዮኖች ሆነ የቢሊዮኖች
ድምፅ በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ጉዳዩ ከጉባኤው አጀንዳዎች አንዱ እንደነበር ጠቅሰው በመድረክና በአንድነት
መካከል የአሰራር ክፍተቶች ተለይተው እንደገና ለማየትና ለማስተካከል አስበናል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና መድረክ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው መደበኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዶ/ር መረራ ጉዲናን የግንባሩ ሊቀመንበር
አድርጎ የመረጠ ሲሆን በሌሎች የስራ አስፈፃሚ እርከኖች ላይ በአብዛኛው ወጣት አባላት የተካተቱበትን ምርጫ አድርጓል።
በአሁኑ ጉባኤ የግንባሩ ነባር አመራ ውስጥ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ጥላሁን እንዳሻውና አቶ ገብሩ አስራት
ምትክ ሌሎች ወጣት አመራሮችን መርጧል። ፕሮፌሰር በየነም ለግል ጉዳየ ለአንድ አመት ወደ አሜሪካ በማቅናታቸው
ከግንባሩ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ውጪ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
(ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment