Tuesday, August 27, 2013

ሳያጡ እየተራቡ ያሉ ዜጎች ጩኸትና የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን

በወገን በለጠ
ይህችን የተራቡና የዕለት ጉርስ ሳያጡ እንዲራቡ የተፈረደባቸውን የዋና ከተማችን ዋና ከተመኞች የተማፅኖ ደብዳቤ በጋዜጣችሁ ላይ አስፍራችሁ የጌቶቻችንን ቢሮ፣ በርና ልቦና እንድታንኳኩልን ብሎም ርህራሔያቸውን እንዲያሳዩንና እንዲታደጉን ታደርጉልን ዘንድ የእናንተንም አዘኔታና እገዛ እንማፀናለን፡፡
የተማፅኖ ደብዳቤያችን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የዘቀጠና የማን አለብኝነት ሕገወጥ ተግባር ዙሪያ የምታጠነጥን ብትሆንም፣ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ መብራት ጠፍቶብን የአርሴና የማንቼ ጨዋታ አመለጠን ወይም የሞስኮ የአትሌቲክስ ውድድር ሳናየው አለፈ፣ የእሑድ መዝናኛ ፕሮግራምን ማየት አልቻልንም ወዘተ ሳይሆን፣ መልካም አስተዳደር ሰፍኗል፣ የተዘረጋው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ከሚጠበቀው በላይ ውጤት አምጥቷል፣ ሙስናን አከርካሪውን ለመምታት እየሠራን ነው፣ በዚህም የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እያገኘ ነው እየተባለ በሚደሰኩርበት አገርና ከተማ በመልካም አስተዳደር ዕጦት በገዘፈና ይፋ በሆነ የሙስና አሠራር በማን አለብኝነትና በጥቅም በታወረ አመራር ምክንያት፣ በመቶዎችና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጦማቸውን እንዲያድሩ እየተፈረደባቸው ስለሆነ ይህንን መልዕክታችንን አስፍሩልን፡፡
ምንም ቢቸግረው ጅብ አይበላም አፈር፣
ደሞዝ ተቀብሎ ደጃች ውቤ ሠፈር፤
እና ሌሎችም በርካታ ግጥሞች የተገጠሙላት ደጃች ውቤ ሠፈር በፊት ገጽታዋ ዛሬም እንደ ጥንቱ ቢራዋን ገችራ ውስኪዋን ደርድራ ዘመነኞችን እያስተናገደች ቢሆንም፣ በጀርባዋ ግን በዘመን ጉዞ ዕርጅና ተጭኗት በመሠረተ ልማት ግንባታ ዕጦት ተደቁሳ፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት እያነባች ድሆቿን በውስጧ ታቅፋ ዛሬም አለች ፡፡
ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ/ባለሥልጣን ፊት ለፊት ተነስቶ እስከ አዲሱ የአፍንጮ በር ድልድይ ባለው አውራ መንገድ ግራና ቀኝ የተደረደሩትን ግሮሰሪዎችና ቡና ቤቶች፣ እንዲሁም ጥቂት ሥጋ ቤቶችን ጨምሮ ከጀርባ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚኖሩባቸው መንደሮች መጠሪያ ጥንትም ሆነ ዛሬ ደጃች ውቤ ሠፈር ነው፡፡
በእነዚህ መንደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ለመንግሥት ተቀጥረው በደመወዝ የሚተዳደሩና በየወሩ ከሚያገኙት ደመወዝ ላይ ከአንድ አራተኛ የማያንስ ገቢያቸውን ሕጋዊና ዜግነታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ግብር በትክክል የሚከፍሉ፣ ለአገራዊ የልማት አጀንዳዎች ማስፈጸሚያዎች ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ድርሻቸውን የሚወጡና የተወጡ ወገኖች፣ እንዲሁም ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ሲባዝኑ የሚውሉ ምስኪን ዜጎች ይኖራሉ፡፡
በዋናው መንገድ ፊት ለፊት በተደረደሩት መሸታ ቤቶች ቀንም ማታም ይጠጣል፣ ይበላል፣ ይዘፈናል፣ ይጨፈራል፡፡ የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች በቆርቆሮ፣ በብረትና በሸራ ታጥረው መሸታ ይመሸትባቸዋል፣ ዳንኪራ ይረገጥባቸዋል፡፡
የቀዘቀዘ ቢራ እንዳይታጣ፣ የውስኪ መጠጫ በረዶ እንዳይጠፋ፣ የሙዚቃው ቃና እንዳይደበዝዝ ኤሌክትሪክ እንዳይቋረጥ አንዳንድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ነቅተውና ተግተው ይሠራሉ፡፡ ድንገት በአጋጣሚ ቢጠፋም ከአንዱ ባለግሮሰሪ ባለቤት በግል ስልካቸው ላይ ተደውሎ ይነገራቸዋል፡፡ በአስቸኳይና በሽሚያ መጥተው ይሠራሉ፡፡ በሚቀርብላቸው እጅ መንሻ ቢራና ውስኪ ተንበሽብሸው በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር ቢያጋጥም ‹‹እጃችሁ ላይ ነን፤›› ብለው ይሸኛሉ፡፡ ምን ችግር አለ?
የደጃች ውቤ ሠፈር የፊት ለፊት ገጽታና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ ይህን ሲመስል፣ ከጀርባ ያሉት ነዋሪዎች ግን ለቀናት ብሎም ለሳምንታት በየተራ በኤሌክትሪክ ዕጦት ይሰቃያሉ፡፡
ይህ ችግር ከጊዜ ጊዜ ይሻሻላል በሚል ተስፋና ከኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ክፍል በማያልቅና በየጊዜው እየተቀያየረ የሚሰጥ መግለጫን በማመን፣ በእርግጥም በኃይል አቅርቦት ዕጥረት ወይም በመስመሮች አሮጌ መሆንና ኃይልን የመሸከም አቅም ብቃት ማነስ ይሆናል በማለት ስንሸነገል ብንኖርም፣ ይህ አለመሆኑን በግልጽ ስለተረዳንና ከሠራተኞቻቸውም ስለተነገረን ችግሩም ከዕለት ዕለት ከወር ወር እየባሰና እየጨመረ በመምጣቱ፣ ጌቶቻችን ብሶታችንን ቢሰሙ ብለን ይህንን አቤቱታ አቅርበናል፡፡
እነሆ ጎን ለጎን ባሉና ፊትና ኋላ በሚገኙ ቤቶች መካካል ልዩነት በማድረግና የኤሌክትሪክ ኃይል በማጥፋት እንዲሠራላችሁ ከፈለጋችሁ ገንዘብ አዋጥታችሁ ስጡንና እንሠራላችኋለን ማለት ከተደረሰ፣ የሕዝብ ንቀትና ማናለብኝነት በድሆች ላይ በደል እየተፈጸመ ነው፡፡
በዚህ በያዝነው ወር ብቻ በተደጋጋሚ ለቀናትና ለሳምንት ለዘለቀ ጊዜ መብራት በማጥፋታቸው እንዲሠሩልን በተደጋጋሚ የተለያዩ የሰሜን አዲስ አበባ የኮርፖሬሽኑ መሥሪያ ቤቶች በመገኘት (ራስ ደስታ አካባቢ፣ ሰሜን ማዘጋጃ ቤት በታች፣ ቸርችል ጎዳና፣ አንበሳ ፋርማሲ ፊት ለፊት) በሚገኙ ቢሮዎች ብናመለክትም ሆነ ብንጮህ ሰሚ አጥተን በጨለማ ተውጠን እንገኛለን፡፡
ጌቶቻችን ሆይ !
ረሃብ ቀን ይሰጣል? የዘንድሮስ ኢኮኖሚ ደሃን ዳቦውን ያስጥላል? እናንተ ግን እየተራብን የእናንተን ርህራሔና መልካም ፈቃድ የሚገኝበት ቀንን እንድንጠብቅ፣ ሰላሳ ቀናት ለፍተንና ባዝነን ባገኘናት ጥቂት ገንዘብ የሸመትናትን እህል እንበላለን ብለን አቡክተን መጋገሪያ አጥተን ተበላሽቶ እንዲደፋ፣ ሊትሩን በአሥራዎችና በሃያዎች በሚቆጠር ብር ገዝተን ሕፃናት ልጆቻችን እንመግባለን ብለን ያስቀመጥነውን ወተት ማፍላትና መስጠት አቅቶን እንዲደፋ፣ ወይም ጥሬውን ጠጥተው ለበሽታ እንዲዳረጉ እያደረጋችሁ ነው፡፡ ዕድሜ ለእናንተ ሳይተርፈን እየደፋን ነው፡፡
አዛውንቶች በዚያ ጎርበጥባጣና በፈራረሰ መንገድ እየመረጡ እንዳይራመዱ እንኳን በጨለማ እንድንዋጥ አድርጋችሁ ቁጥራቸው ከሦስት ያላነሱ አዛውንቶች ወድቀው እንዲሰበሩ ምክንያት ሆናችኋልና በመልካም ተግባራችሁ ተደሰቱ፡፡ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ረሃብ ቀን አይሰጥምና በእንጨት በከሰል ወይም በጋዝ ለመጠቀም አቅማችን አልፈቀደምና እባካችሁ ተለመኑን፡፡
በእርግጥ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አጋጥሞናል የምትሉም ከሆነ ውስኪው ሠፈር ብቅ ስትሉ የኛንም ችግር እንድትፈቱልን ስንጠይቃችሁ ብልሽቱ የት ቦታ ነው? አሳዩን እያላችሁ አትመፀደቁብን፡፡ እናንተ እንጂ እኛ የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች አይደለንምና፡፡ ቢያንስ የቢራና የውስኪ ግብዣ ለመታደም በመንግሥት መኪና ስትመላለሱና በግብር ስም ከእኛ የተሰበሰበውን ገንዘብ በትርፍ ሰዓት ስም ሳትሠሩ ሲከፈላችሁ ኃፍረት ይሰማችሁ፡፡
አለበለዚያም መልካም ፈቃዳችሁ ሆኖልን ኤሌክትሪክ የምታጠፉበትንና የምታበሩበትን ቀን በቅድሚያ ንገሩንና ቁርጣችንን አውቀን በፕሮግራም እንራብ፡፡ ያቦካነው ሊጥና የጣድነውን ሽሮ እየራበን ሳይተርፈን እንድንደፋ አታስገድዱን፡፡
ትልልቆቹ ጌቶቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አቶ ዓለማየሁ ተገኑና አቶ ምህረት ደበበ መብራት ጠፍቶባችሁ እንደማያውቅ አንድ ሺሕ ጊዜ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ጉዳቱንም አታውቁትም፡፡ ረሃብንም የምታውቁ አይመስለኝም (እንደሌሎቹ ከበረሃ አልመጣችሁምና)፡፡ እግዚአብሔርን እንደምታውቁ ግን አውቃለሁና ስለአግዚአብሔር ብላችሁ ምን እየተሠራ ነው ብላችሁ ጠይቁ፡፡ ሕዝባችሁንም በእኩል ዓይን አስተዳድሩ፡፡ የደሃ ጩኸት ይሰማችሁ፡፡
የመለስ መልካም አስተዳደር፣ ደሃ ተኮር ልማትና ዕድገት የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከሙስና የፀዳና ሙስናን የማይሸከም ኅብረተሰብ የመፍጠር ራዕይ የሚሳካው በመዝሙርና በመፈክር ሳይሆን፣ የዜጎችን ቁልፍ ችግሮች በመፍታት ጭምር መሆኑን ተገንዝባችሁ እባካችሁ ጓዳችሁን ፈትሹና መፍትሔ ስጡ፡፡ በተለይ አቶ ምህረት የቅርብ ኃላፊ ነዎትና ዝቅ ብለው አሠራሮችን ይፈትሹ ያስፈትሹ፡፡ ለመሆኑ የኤሌክትሪክ አደጋ ደርሶ እንኳን ጥሪ ለማድረግ ለኮፖሬሽኑ ብንደውል ለአደጋ ማሳወቂያ የተመደቡት ስልኮች የማይነሱና ምላሽ የማይሰጥ መሆኑን ያውቃሉ? እስኪ የሰሜን ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስልክ ይሞክሩ፡፡ ወይም ጊዜ ከሌለዎት ሌሎች ባልደረቦችዎ ሞክረው ውጤቱን ይንገርዎት፡፡ የቴሌ ችግር እንዳይባል ስልኩ ይሠራል፡፡
የሰሜን አዲስ አበባ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች እስቲ በግንባር ቀርበን ያስመዘገብነውን ተመልከቱ፡፡ መቼ ነው? ችግሩ ምንድን ነው? ለምን አልተሠራም? ብላችሁ ጠይቁ፡፡ የሕዝብን አደራ ተወጡ፣ የወገን ችግር ይግባችሁ፡፡
በተረፈ ይህንን ጻፉ ብላችሁ በእኔም ሆነ በጎረቤቶቼ ላይ ተጨማሪ የረሃብ ቅጣት እንደማትጥሉብን ተስፋ እያደረግኩና ቢደረግም ትልልቆቹ ጌቶቻችን እንደሚታደጉን ተስፋ እያደረግሁ በዚሁ ላብቃ፡፡
የራበው ሰው እንኳን ብዙ አያወራም ችግሩ ቢፀናብን ነውና ይቀርታችሁ አይለየን፡፡ ይልቁንስ ሳምንት አካባቢ የጠፋውን መብራት አብሩልንና እንጀራችንን ጋግረን ሽሯችንን አሙቀን እንብላ፡፡ ወዳጆቻችሁና ጓደኞቻችሁም የኛን ማላዘን ሳይሰሙ ያላበው ቢራ ይጠጡ፤ ውስኪ በበረዶ ያንቆርቁሩ፡፡ አንዳንዶቹ ሠራተኛዎቻችሁም የእኛን ሳንቲም መቀላወጥ ትተው የቢራና ውስኪ ቅልውጡ ላይ ይበርቱ፡፡ ‹‹ዘለለ ዕለትነ›› ብለን የዕለት ጉርሳችንን እንዳይነሳን ፈጣሪን እየለመንን የምንኖር እንጂ፣ ለእናንተ እጅ መንሻ ለመስጠት አቅም ያለን አይደለንምና፡፡
እኛ እንራብ፤
ለእናንተ ሰላም ይሁን፡፡
Source Reporter

No comments:

Post a Comment