Friday, August 23, 2013

ወደ ውጭ ሃገር ለስራ የሚሄዱ ዜጎች የብቃት ምዝና ሊወስዱ ነው

ወደ ውጭ ሃገራት ለስራ የሚጓዙ ዜጎች የብቃት ምዘና እንዲወስዱ ሊደረግ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ወደ ውጭ ሃገር በሚሄዱ ዜጎች የስራ ስምሪትና ደህንነት ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
ከ2006 ጀምሮ ወደ ውጭ ሃገራት ለስራ በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ለቤት ሰራተኝነትና ለሌሎች የጉልበት ስራዎች ለሚሄዱ ሰራተኞች በመሰረታዊ የቤት ወስጥ አገልግሎትና በሌሎች ክህሎቶች ላይ  ከ45 እስከ 60 ቀናት ስልጠና በመስጠት እንዲመዘኑ ይደረጋልም ብሏል፡፡
የብቃት ምዝናውን የሚያሟሉ ወደ ሚፈልጉት ሃገር በህጋዊ መንገድ ሲሄዱ ምዘናውን የማያሟሉ ደግሞ ለተጨማሪ ስልጠና ወደ ማሰልጠኛ ይገባሉ ፡፡
የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህብራዊ  ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተለያዩ አማራጭ ስልቶች እየተነደፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ቢሮው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና አስተማማኝ የስራ አካባቢ ለመፍጠር ተገቢውን አደረጃጀትና ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር የግንዛቤ ማሳደጊያና የተሟላ የህግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን መዳረሻ በዋናነት መካከለኛው ምስራቅ፣ምስራቅ አፍሪካና አውሮፓ ሃገራት እንደሆነ በውይይቱ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ማህበራዊና ሰራተኛ ጉዳይ ቢሮአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጥቃቅና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቢሮቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲና የውጭ ሃገራት ሰራተኛና አሰሪ ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
በዕለቱ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሃገራት በህጋዊ መንገድ ለሚሄዱ 18 ሺ ዜጎች ስልጠና ለመስጠት አቅዷል፡፡
ሪፖርተር፣ ሰለሞን ፀጋዬ
erta

No comments:

Post a Comment