Friday, August 23, 2013

ግብፅን ሁለት ቦታ የከፈለው ብጥብጥ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊቀየር ይችላል

ለ30 ዓመታት ግብፅን የመሩት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በሕዝባዊ አብዮት ሥልጣናቸውን ከለቀቁበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ ግብፅ ከፍተኛ የሆነ ደም አፋሳሽ ግጭት ያስመዘገበችው ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ወዲህ ነው፡፡
የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሙባረክ በሕዝብ ንቅናቄ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመጀመርያ ጊዜ የተመረጡት ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ፣ በምርጫ ያገኙትን የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን ለመምራት በለስ አልቀናቸውም፡፡ አገሪቷን መምራት በጀመሩ በዓመታቸው የተለያዩ ሚዲያዎች ‹‹አብዛኛው ሕዝብ›› እያሉ በሚዘግቡት ግብፃውያን ተቃውሞ ሳቢያ የአገሪቱ ጦር ኃይል ከሥልጣን አውርዷቸዋል፡፡
የአገሪቱ ጦር ኃይል ፕሬዚዳንት ሙርሲን ከሥልጣን ካወረደበት እ.ኤ.አ ከሰኔ 26 ቀን ጀምሮ ግን ግብፅ ሰላም አላገኘችም፡፡ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ከሥልጣን ይውረዱ በማለት ለተቃውሞ ወጥተዋል የተባሉት 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ግብፃውያን ከጐዳና ወደቤታቸው ሲገቡ፣ የሙርሲ ደጋፊ የሆኑት 14 ሚሊዮን ይጠጋሉ የተባሉ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት ለተቃውሞ ጐዳና ወጥተዋል፡፡
‹‹የሽግግር መንግሥቱን አንደግፍም፣ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ይፈቱ፣ መሪያችን ፕሬዚዳንት ሙርሲ ናቸው፣ የወታደሩን ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን፣ በግብፅ ታይቶ የነበረው ዴሞክራሲ ተረግጧል፣ ወዘተ›› በማለት በየጐዳናው መጠለያ በመሥራት ከሳምንታት በላይ ውሎና አዳራቸውን ውጭ ያደረጉት የፕሬዚዳንት ሙርሲ ደጋፊዎች፣ ከጐዳና ወደቤታቸው እንዲገቡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የፕሬዚዳንት ሙርሲ ደጋፊዎችን የጐዳና ላይ ተቃውሞ መታገስ ያልቻለው ጦር ኃይሉ ባለፈው ሳምንት በወሰደው የመበተንና መጠለያዎችን የማፍረስ ዕርምጃ የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል፡፡
በግብፅ ለደረሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በከረረ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች፣ በሙርሲ ደጋፊዎችና በተቃዋሚዎች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ ግብፃውያንን ለሁለት ከፍሏል፡፡ ግብፃውያን ፕሬዚዳንት ሙርሲን የሚደግፍና የማይደግፍ በመባባል መገዳደል ጀምረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናትም እየተቃጠሉ ነው፡፡ መስቀል አንገታቸው ላይ ያንጠለጠሉ እየተገደሉ ነው፡፡ ግብፃውያን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባቸው በሚችል ሁኔታ ተበጣብጠዋል፡፡ የተፈጠረው ግጭት በቀላሉና በአጭር ጊዜ ሊበርድ እንደማይችልም የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት መሐመድ ሙርሲ የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎችና የሽግግር መንግሥቱን እየጠበቀ ያለው ጦር ኃይሉ በአንድነት ተወቃሽ በሆኑበትና ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በተጀመረው ግጭት ብቻ 638 ግብፃውያን ተገድለዋል፡፡ በዚህ ቀን ለሞቱት ሰዎች ምክንያቱ የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች ቀድመው በፖሊሶች ላይ በመተኮሳቸው ነው ቢባልም፣ ሁለቱም ወገኖች እየተወቀሱ ነው፡፡
የ638 ሰዎችን መሞት ተከትሎ ሐሙስ ነሐሴ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. የመንግሥት ተቋማትን ከሙርሲ ደጋፊዎች ጥቃት ለመጠበቅ ፖሊስ መሣሪያ እንዲጠቀም መፈቀዱ በግብፅ ግድያው እንዲጨምር፣ ግጭቱ እንዲባባስና አቅጣጫ እንዲቀይር አድርጐታል፡፡ በረቡዕ ዕለት የተከሰተውን ግድያ በመቃወም ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. በካይሮ ራማሲስ አደባባይ በወጡ የሙርሲ ደጋፊዎችና ፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት 117 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በፖሊስና በሙርሲ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አቅጣጫውን በመሳቁ፣ የሙርሲ ደጋፊዎች ብሶታቸውን ሕንፃዎችን በማቃጠል ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ክርስቲያኖችን መግደል መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡
እስልምናን ለማስፋፋትና በግብፅ እስላማዊ መንግሥት ለማስፈን ዓላማ አድርጐ መነሳቱ የሚነገርለት በምርጫ በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን በማግኘትና በኋላም አገሪቱን ለመምራት መብቃቱ የሚነገርለት የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች፣ ማክሰኞ ምሽት ለሕትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ 37 አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠላቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡
ፖሊስ 36 የሙርሲ ደጋፊዎችን ከካይሮ ወደ ሌላ እስር ቤት ሲያዘዋውር ለማምለጥ ባደረጉት ጥረት አስለቃሽ ጭስ በመተኮሱ በጭስ ታፍነው ሞተዋል፡፡ 25 የፖሊስ አባላት በሙስሊም ታጣቂዎች መገደላቸው የተሰማውም ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
በግብፅ ግድያና እስር አይሏል፡፡ ትክክለኛው ቁጥር ግልጽ ባይወጣም አንድ ሺሕ የሚደርሱ የሙርሲ ደጋፊዎችና የፖሊስ አባላት መገደላቸው በመንግሥት ተረጋግጧል፡፡ የሙርሲ ደጋፊዎች የሟቾችን ቁጥር 2,600 አድርሰውታል፡፡
የሙስሊም ብራዘርሁድ አቅጣጫ ያላማረው የሽግግሩ መንግሥት ድርጅቱ በሕጋዊ መንገድ እንዲፈርስ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የሙስሊም ብራዘርሁድ መፍረስ ወይም አለመፍረስ ለግብፅ ሰላምን ያመጣል ወይ? የሚለው ለብዙ ግብፃውያን ጥያቄ ሆኗል፡፡ ግብፃውያን ዛሬ ላይ ሆነው ግራ ተጋብተዋል፡፡ ያጠፋው ማነው? ትክክለኛውና የተሳሳተው ማን ነው? በሚለው ውዥንብር ውስጥ ሆነው ሞትን ያስተናግዳሉ፡፡
የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኞች ግብፃውያን አሁን ባሉበት ሁኔታ ማንን መደገፍ እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የመንግሥትና የግሉ ሚዲያ ዘገባ ደግሞ የበለጠ ግራ እያጋባቸው ነው፡፡
የአገሪቱ ሚዲያዎች ወታደራዊ ክፍሉ ዕርምጃ እየወሰደ የሚገኘው የፖለቲካ ልዩነት ባላቸው የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች ላይ ሳይሆን በአሸባሪዎች ላይ ነው ቢሉም፣ ግብፃውያን ማንን መደገፍ፣ ማንን ማመንና መውቀስ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡
ኤንቢሲ ኒውስ እንደዘገበው፣ ግብፅ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ማን ተወቃሽ ማን ወቃሽ እንደሆነ የማይለይበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ የሳቢያን ሴንተር ፎር ሚድል ኢስት ፖሊሲ አባል ካሊድ ኢልጊንዲ፣ ‹‹ሁሉም ወገኖች ከሚገባው በላይ በመሄዳቸው ሕዝቡ በከፍተኛ ፍርኃት ተውጧል፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሔ የማያዋጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ግብፅ በከባድ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታለች፤›› ብለዋል፡፡
ግብፅ በብጥብጥ ማዕበል ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ሪፐብሊካንና ዲሞክራት የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች አሜሪካ ለግብፅ በየዓመቱ የምትሰጠውን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ቢያንስ ብጥብጡ እስኪቆም እንድታቆም የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደርን ጠይቀዋል፡፡
በአሜሪካ ሕግ መፈንቅለ መንግሥት ለተካሄደበት አገር ዕርዳታ እንዳይሰጥ የሚያግድ ቢሆንም፣ አሜሪካ እስካሁን በፕሬዚዳንት ሙርሲ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል ከማለት መቆጠብን መርጣለች፡፡ ሆኖም አሜሪካ ለግብፅ ለመሸጥ ተስማምታ የነበሩትን አፓቼ ሔሊኮፕተሮች ለጊዜው አዘግይታለች፡፡ ከግብፅ ጋር ያላትን ጥምር ወታደራዊ ልምምድም ማቆሟን አስታውቃለች፡፡
ይህ ግን የእስራኤል ባሥልጣናትን ዓይን አስፈጥጧል፡፡ እስራኤል በሲናይ በረሃ የእስላም አክራሪነት እንዲለዝብ ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም አሜሪካ ለግብፅ ጦር ኃይል የምታደርገው ድጋፍ መቋረጥ የለበትም የሚል አቋም አላት፡፡ በመሆኑም እስራኤል የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር ለግብፅ ጦር ኃይል የሚያደርገውን ዕርዳታ እንዳያቆም እንደምትወተውት ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡
በግብፅ ማህሙድ ባድኤን ጨምሮ ከፍተኛ የሙስሊም ብራዘርሁድ ባለሥልጣናት ታስረዋል፡፡ አልቃይዳ ደግሞ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት መታሰርና መገደልን ከበፊት ጀምሮ ለያሁው የእስልምና አክራሪነት ዓላማ ማራመጃ እየተጠቀመበት ነው፡፡
አሶሼትድ ፕሬስና ሮይተርስ እንደዘገቡት፣ የአልቃይዳ የምሥራቅ አፍሪካ ብንፍ የሆነው አልሸባብ በግብፅ ያለውን ነውጥ አስመልክቶ ‹‹አልቃይዳን ለመደገፍ ጊዜ አሁን ነው፡፡ በግብፅ የአልቃይዳን ባንዲራ ማውለብለብ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፤›› ብሏል፡፡
ሚስተር ኢሊጊንዲ የግብፅ ጦር ኃይል፣ ሙስሊም ብራዘርሁድና አልቃይዳ አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ የግብፅ ወታደሮች በሙስሊም ብራዘርሁድ ላይ ከፍተኛ ዕርምጃ መውሰድ ከጀመሩ፣ የሙስሊም ብራዘርሁድ ካድሬዎች ወደ ጂሃዲስትነት ሊቀየሩ ይችላሉ ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በግብፅ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ከመሆኑም በላይ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ያነግሳል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
source... https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/08/23/2342-2/

No comments:

Post a Comment